ለዚህ ምን ያህል ዋጋ ትከፍል ነበር?
እርሱን ለማግኘት ስትል ማንኛውንም ነገር በፈቃደኝነት የምትሠዋለት በጣም ውድ የሆነ ነገር ታውቃለህን? ኢየሱስ እንዲህ አድርጓል፤ ለተከታዮቹም ስለዚሁ ውድ ነገር ተናግሯል።
እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።“—ማቴዎስ 13:45, 46
ያ ነጋዴ “ዕንቁ“ የሆነችውን የአምላክን መንግሥት ለማግኘት ሲል ያለውን ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ ነበር። ለምን? ምክንያቱም በዚህ ዓለም ከአምላክ መንግሥት ጋር የሚወዳደር ምንም ነገር ስለሌለ ነው። የአምላክ መንግሥት ጦርነት፣ ረሃብ፣ ወንጀልና ጭቆና ለመሳሰሉት ሰው መፍትሔ ያላገኘላቸው ችግሮች መፍትሔ ታስገኛለች። (መዝሙር 72:4-8, 13, 14) በመንግሥቲቱ አገዛዝ ሥር ኃጢአት፣ በሽታና ሞትም እንኳን ሳይቀር ይወገዳሉ። (ራእይ 21:4, 5) የጌታ ጸሎት (“አባታችን ሆይ“ በማለት የሚጀምረው ጸሎት) ሁለተኛው ልመና “መንግሥትህ ትምጣ“ የሚል መሆኑ አያስደንቅም!—ማቴዎስ 6:9, 10
በመንግሥቲቱ በረከቶች ተካፋይ ለመሆን ምን ዋጋ ትሰጣለህ? እርግጥ በረከቶቹ ዋጋ የሚከፈልባቸው አይደሉም። ይሁን እንጂ እነዚህን በረከቶች ለማግኘት መንግሥቲቱ ምን እንደሆነች ማወቅ፣ እውን መሆኗን ማመንና በሕይወትህ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ መስጠት አለብህ። ይህን ልታደርግ ትችላለህን? ለዚህ የሚረዳህ ዕውቀት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። የይሖዋ ምስክሮች ስለ አምላክ መንግሥት እንድትማርና መንግሥቲቱ አሁንም እንኳን እንዴት ልትጠቅምህ እንደምትችል እንድትገነዘብ እንዲረዱህ ለምን አትፈቅድላቸውም?