በጥልቅ ማስተዋልና በማሳመን ችሎታ ተጠቅማችሁ አስተምሩ
“የጠቢብ ልብ ከአፉ ጥልቅ ማስተዋል እንዲፈልቅ፣ ከንፈሩም ሌሎችን የሚያሳምን እንዲሆን ያደርጋል።”—ምሳሌ 16:23 NW
1. የአምላክን ቃል ማስተማር እውቀትን ብቻ ከማካፈል የበለጠ ነገር የሚጨምረው ለምንድን ነው?
የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ግባችን ተማሪዎቻችን አእምሯቸው ብቻ ሳይሆን ልባቸው ጭምር መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲያገኝ መርዳት ነው። (ኤፌሶን 1:18) በመሆኑም ማስተማር ማለት እንዲያው እውቀት ማስተላለፍ ብቻ አይደለም። ምሳሌ 16:23 [NW] “የጠቢብ ልብ ከአፉ ጥልቅ ማስተዋል እንዲፈልቅ፣ ከንፈሩም ሌሎችን የሚያሳምን እንዲሆን ያደርጋል” ይላል።
2. (ሀ) ማሳመን ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) ሁሉም ክርስቲያኖች የማሳመን ችሎታ ያላቸው አስተማሪዎች ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ በማስተማር ሥራው ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሚገባ ተግባራዊ አድርጎታል። በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ “በየሰንበቱም ሁሉ በምኵራብ ይነጋገር ነበር፣ አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ [“ያሳምን፣” NW] ነበር።” (ሥራ 18:4) በአንድ ምሁር አባባል መሠረት እዚህ ላይ “ማሳመን” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “ምክንያታዊና ተቀባይነት ያለው ማስረጃ በማቅረብ አመለካከትን እንዲለውጡ ማድረግ” የሚል ትርጉም አለው። ጳውሎስ አሳማኝ በሆኑ የመከራከሪያ ነጥቦች በመጠቀም ሰዎች አስተሳሰባቸውን እንዲለውጡ ማድረግ ችሎ ነበር። ሌሎችን የማሳመን ችሎታው ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ ጠላቶቹ እንኳ ሳይቀር ይፈሩት ነበር። (ሥራ 19:24-27) ያም ሆኖ ግን የጳውሎስ የማስተማር ሥራ ሰብዓዊ ችሎታን ለማሳየት ተብሎ የተደረገ አልነበረም። የቆሮንቶስን ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል:- “እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፣ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፣ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።” (1 ቆሮንቶስ 2:4, 5) ሁሉም ክርስቲያኖች የይሖዋ አምላክን መንፈስ እርዳታ ማግኘት ስለሚችሉ ሁሉም የማሳመን ችሎታ ያላቸው አስተማሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ግን እንዴት? ቀጥለን ውጤታማ የሆኑ አንዳንድ የማስተማሪያ ዘዴዎችን እስቲ እንመልከት።
ጥሩ አዳማጭ ሁን
3. ሌሎችን በምናስተምርበት ጊዜ ጥልቅ ማስተዋል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ልቡን መንካት የምንችለው እንዴት ነው?
3 የመጀመሪያው የማስተማሪያ ዘዴ መናገርን ሳይሆን ማዳመጥን የሚመለከት ነው። በምሳሌ 16:23 ላይ እንደተገለጸው የምናሳምን ለመሆን ጥልቅ ማስተዋል ሊኖረን ይገባል። ኢየሱስ ያስተምራቸው ስለነበሩ ሰዎች ጥልቅ ማስተዋል እንደነበረው የተረጋገጠ ነው። ዮሐንስ 2:25 “ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና” ይላል። ሆኖም በምናስተምራቸው ሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ጥሩ አዳማጭ በመሆን ነው። ያዕቆብ 1:19 “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ . . . ይሁን” ይላል። እርግጥ ነው በቀላሉ ሐሳባቸውን የመግለጽ ችሎታ ያላቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ከልብ እንደምናስብላቸው ሲገነዘቡ ውስጣዊ ስሜታቸውን ለመግለጽ ይገፋፋሉ። የማስተዋል ችሎታን የሚመዝኑ በደግነት የቀረቡ ጥያቄዎች አብዛኛውን ጊዜ ልብን ለመንካትና ውስጣዊ ስሜትን ‘ለመቅዳት’ ያስችላሉ።—ምሳሌ 20:5
4. ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጥሩ አዳማጮች መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?
4 በተለይ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጥሩ አዳማጭ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ‘ለእያንዳንዱ እንዴት እንዲመልሱ እንደሚገባቸው ሊያውቁ’ የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው። (ቆላስይስ 4:6) ምሳሌ 18:13 “ሳይሰማ ነገርን በሚመልስ ስንፍናና እፍረት ይሆንበታል” ሲል ያስጠነቅቃል። አንዲት እህት ከአንዳንድ ስብሰባዎች መቅረቷን በመመልከት ሁለት ወንድሞች በቅን ልቦና ተነሳስተው ዓለማዊነትን የሚመለከት ምክር ሰጧት። ሽማግሌዎቹ የቀረችበትን ምክንያት ሳይጠይቋት ይህን በማድረጋቸው ይህች እህት ስሜቷ በጥልቅ ተጎዳ። ይህች እህት በቅርቡ ከተደረገላት ቀዶ ሕክምና ገና በማገገም ላይ ነበረች። ምክር ከመስጠት በፊት ማዳመጥ ምንኛ ተገቢ ነው!
5. ሽማግሌዎች በወንድሞች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት ይችላሉ?
5 የሽማግሌዎች የማስተማር ሥራ አብዛኛውን ጊዜ ምክር መስጠትንም ይጨምራል። እዚህም ላይ ጥሩ አዳማጭ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። በተለይ በመሰል ክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ማዳመጥ አስፈላጊ ነው። ሽማግሌዎች “ሳያዳላ . . . የሚፈርደውን አባት” ሊመስሉ የሚችሉት በመጀመሪያ የሚያዳምጡ ከሆነ ብቻ ነው። (1 ጴጥሮስ 1:17) አለመግባባት በሚከሰትበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ የስሜት መጋጋል ሊኖር ስለሚችል አንድ ሽማግሌ በምሳሌ 18:17 ላይ የሚገኘውን ምክር ማስታወስ ይኖርበታል:- “ወደ ፍርድ አስቀድሞ የገባ ጻድቅ ይመስላል፤ ባልንጀራው ግን መጥቶ ይመረምረዋል።” ጎበዝ የሆነ አስተማሪ ሁለቱም ወገኖች የሚናገሩትን ያዳምጣል። ጸሎት በማቅረብ ሁኔታውን ለማረጋጋት ይጥራል። (ያዕቆብ 3:18) ስሜታቸው እየተጋጋለ ከመጣ እርስ በርሳቸው መጨቃጨቃቸውን አቁመው ሁለቱም ጉዳያቸውን በየተራ በቀጥታ ለእሱ እንዲነግሩት ሐሳብ ሊያቀርብላቸው ይችላል። ሽማግሌው ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ ይችል ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ የግጭቶች መነሾ ተንኮል ሳይሆን ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት አለመኖሩ ሆኖ ይገኛል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጥሰው ከሆነ አፍቃሪ የሆነ አስተማሪ ሁለቱንም ወገኖች ካዳመጠ በኋላ ጥልቅ ማስተዋል ያለበት ትምህርት ሊሰጥ ይችላል።
ቀለል ባለ መንገድ ማስተማር ያለው ጥቅም
6. ጳውሎስና ኢየሱስ ቀላል በሆነ መንገድ በማስተማር ረገድ ምሳሌ የሚሆኑን እንዴት ነው?
6 ነገሮችን ቀለል ባለ መንገድ መግለጽ ሌላው ጠቃሚ የሆነ የማስተማር ችሎታ ነው። እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ‘ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የእውነት ስፋት፣ ርዝመት፣ ከፍታና ጥልቀት ምን ያህል መሆኑን እንዲያስተውሉ’ እንፈልጋለን። (ኤፌሶን 3:18) በጣም ማራኪና አብዛኛውን ጊዜ ግን በቀላሉ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶች አሉ። (ሮሜ 11:33) ያም ሆኖ ጳውሎስ ለግሪክ ሰዎች በሰበከበት ጊዜ ስለ ‘ክርስቶስ መሰቀል’ በሚናገረው ቀላል መልእክት ላይ ትኩረት አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 2:1, 2) በተመሳሳይም ኢየሱስ ግልጽና ማራኪ በሆነ መንገድ ሰብኳል። በተራራ ስብከቱ ላይ ቀላል በሆኑ ቃላት ተጠቅሟል። ይሁንና እስከ ዛሬ ከተነገሩት ሁሉ የሚበልጡ ጥልቅ እውነቶችን የያዙ ነበሩ።—ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7
7. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በምንመራበት ጊዜ ቀለል ባለ መንገድ መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?
7 እኛም በተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በምናስተምርበት ጊዜ ነገሮችን ቀለል ባለ መንገድ መግለጽ እንችላለን። እንዴት? ‘ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች’ ላይ ትኩረት በማድረግ ነው። (ፊልጵስዩስ 1:10) ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶችን በምናብራራበት ጊዜ ቀለል ባለ መንገድ ለማስረዳት መሞከር አለብን። በአንድ ጽሑፍ ላይ የተጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በሙሉ ለማንበብና በእነሱም ላይ ለመወያየት ከመሞከር ይልቅ ቁልፍ በሆኑ ጥቅሶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባናል። ይህ በእኛ በኩል ጥሩ ዝግጅት ማድረግን ይጠይቅብናል። አላስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ በመግባት ተማሪውን ግራ ማጋባት የለብንም። ተማሪው ከምናጠናው ትምህርት ጋር ምንም ተዛማጅነት የሌለው ጥያቄ ካለው ትምህርቱ ካለቀ በኋላ እንደምንወያይበት በዘዴ ሐሳብ ልናቀርብለት እንችላለን።
ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም
8. ኢየሱስ ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ የተጠቀመባቸው እንዴት ነበር?
8 ሌላው ጠቃሚ የሆነ የማስተማር ዘዴ ውጤታማ የሆኑ ጥያቄዎች መጠየቅን የሚመለከት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ብዙ ጊዜ በጥያቄዎች ይጠቀም ነበር። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ጴጥሮስን እንዲህ ብሎ ጠይቆት ነበር:- “ስምዖን ሆይ፣ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸውን ወይስ ከእንግዶች? . . . ጴጥሮስም:- ከእንግዶች ባለው ጊዜ ኢየሱስ:- እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው።” (ማቴዎስ 17:24-26) ኢየሱስ፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሚመለከው አምላክ አንድያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ለቤተ መቅደሱ ቀረጥ የመክፈል ግዴታ አልነበረበትም። ይሁንና ኢየሱስ ይህን እውነታ የገለጸው ውጤታማ የሆኑ ጥያቄዎችን በመጠቀም ነበር። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ቀደም ሲል የሚያውቀውን ነገር መሠረት በማድረግ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ረድቶታል።
9. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንመራበት ጊዜ ጥያቄዎችን እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?
9 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንመራበት ጊዜ ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀም እንችላለን። አንድ ተማሪ የተሳሳተ መልስ በሚሰጥበት ጊዜ ትክክለኛውን መልስ መናገር እንፈልግ ይሆናል፤ ይሁንና ትምህርቱ በአእምሮው ሊቀረጽ ይችላልን? አብዛኛውን ጊዜ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ተማሪው ወደ ትክክለኛው መደምደሚያ እንዲደርስ መምራቱ የተሻለ ነው። ለምሳሌ ያህል መለኮታዊውን ስም ለምን መጠቀም እንደሚኖርበት የማስተዋል ችግር ካለበት እንዲህ ብለን ልንጠይቀው እንችላለን:- ‘ስምህ ለአንተ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? . . . ለምን? . . . አንድ ሰው በስምህ ሊጠራህ ፈቃደኛ ባይሆን ምን ይሰማሃል? . . . አምላክ በግል ስሙ እንድንጠቀም መጠየቁ ተገቢ አይደለምን?’
10. ሽማግሌዎች የስሜት ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች በሚረዱበት ወቅት በጥያቄዎች ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው?
10 በተጨማሪም ሽማግሌዎች መንጋውን በእረኝነት በሚጠብቁበት ጊዜ ጥያቄዎችን በጥሩ መንገድ ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ብዙዎች በሰይጣን ዓለም ስሜታቸው የቆሰለና የተደቆሰ በመሆኑ ንጹሕ ያልሆኑና የማይወደዱ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። አንድ ሽማግሌ እንዲህ ያለውን ሰው እንደሚከተለው በማለት በምክንያታዊነት ሊያነጋግረው ይችላል:- ‘አንተ ንጹሕ እንዳልሆንክ ቢሰማህም ይሖዋ ስለ አንተ ምን የሚሰማው ይመስልሃል? አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ለአንተ ሲል ልጁ እንዲሞትና ቤዛ እንዲሆን መፍቀዱ አምላክ እንደሚወድህ አያሳይምን?’—ዮሐንስ 3:16
11. መልስ የማይጠበቅባቸው ጥያቄዎች ለምን ዓላማ ያገለግላሉ? ለሕዝብ በምንናገርበት ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉትስ እንዴት ነው?
11 መልስ የማይጠበቅባቸው ጥያቄዎችን መጠየቅ ሌላው ጠቃሚ የሆነ የማስተማር ዘዴ ነው። አድማጮች ለእነዚህ ጥያቄዎች ጮክ ብለው መልስ እንዲሰጡ አይጠበቅባቸውም፤ ሆኖም በጉዳዩ ላይ እንዲያስቡበት ይረዷቸዋል። የጥንቶቹ ነቢያት አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን የመሳሰሉ አድማጮቻቸው በጥልቅ እንዲያስቡ የሚያደርጉ ጥያቄዎችን ይጠይቁ ነበር። (ኤርምያስ 18:14, 15) ኢየሱስ መልስ በማይጠበቅባቸው ጥያቄዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 11:7-11) እነዚህ ጥያቄዎች በተለይ ለሕዝብ በምንናገርበት ጊዜ ውጤታማ ናቸው። አድማጮች ይሖዋን ለማስደሰት በሙሉ ነፍስ እሱን ማገልገል እንዳለባቸው ዝም ብሎ ከመንገር ይልቅ ‘አገልግሎታችንን የምናከናውነው በሙሉ ነፍሳችን ካልሆነ ይሖዋ ይደሰታልን?’ ብሎ መጠየቁ ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።
12. የአመለካከት ጥያቄዎችን መጠየቅ ምን ጥቅም አለው?
12 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሚማረውን ነገር የሚያምንበት መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የአመለካከት ጥያቄዎችን መጠቀም ጥሩ ነው። (ማቴዎስ 16:13-16) አንድ ተማሪ ዝሙት ስህተት መሆኑን በትክክል ሊመልስ ይችላል። ይሁንና ቀጥላችሁ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ለምን አትጠይቁትም:- አንተ በግልህ አምላክ ስላለው የሥነ ምግባር አቋም ምን ይሰማሃል? የማያፈናፍንና ጥብቅ እንደሆነ ይሰማሃል? የአምላክን የአቋም መሥፈርቶች መከተሉ ወይም አለመከተሉ ልዩነት ያመጣል ብለህ ታስባለህ?
ልብ የሚነኩ ምሳሌዎች
13, 14. (ሀ) አንድን ነገር በምሳሌ ማስረዳት ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) ጥሩ ምሳሌዎች ውጤታማ የሆኑት ለምንድን ነው?
13 የአድማጮችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ልብ ለመንካት የሚያስችለው ሌላው መንገድ ውጤታማ የሆኑ ምሳሌዎችን መጠቀም ነው። “ምሳሌ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ጎን ለጎን ወይም አንድ ላይ ማስቀመጥ” ማለት ነው። ምሳሌ በምትጠቀምበት ጊዜ አንድን ነገር ተመሳሳይ ከሆነ ሌላ ነገር ‘ጎን በማስቀመጥ’ ታብራራለህ ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠይቆ ነበር:- “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን?” ኢየሱስ መልስ ሲሰጥ በሰፊው የሚታወቀውን የሰናፍጭ ቅንጣት ጠቅሷል።—ማርቆስ 4:30-32
14 የአምላክ ነቢያት ውጤታማ የሆኑ በርካታ ምሳሌዎችን ተጠቅመዋል። አምላክ እስራኤላውያንን ለመቅጣት መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመባቸው አሦራውያን የሚፈጽሙት የጭካኔ ተግባር እየተባባሰ ሲሄድ ኢሳይያስ በሚከተለው ምሳሌ ከገደብ ማለፋቸውን አጋልጧል:- “በውኑ መጥረቢያ በሚቆርጥበት ሰው ላይ ይመካልን? ወይስ መጋዝ በሚስበው ላይ ይጓደዳልን?” (ኢሳይያስ 10:15) ኢየሱስም በተመሳሳይ ሌሎችን በሚያስተምርበት ጊዜ ብዙ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። እንዲያውም “ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም” ተብሎ ተዘግቧል። (ማርቆስ 4:34) ጥሩ ምሳሌዎች አእምሮን ብቻ ሳይሆን ልብንም የሚያመራምሩ በመሆናቸው ውጤታማ ናቸው። አድማጮች አንድን አዲስ ትምህርት ቀደም ሲል ከሚያውቁት ነገር ጋር በማወዳደር እንዲቀበሉት ይረዳቸዋል።
15, 16. ምሳሌዎችን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ምሳሌዎች ስጥ።
15 ልብ የሚነኩ ምሳሌዎችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ምሳሌ በመብራራት ላይ ካለው ሐሳብ ጋር በሚገባ የሚዛመድ መሆን አለበት። ንጽጽሩ ተስማሚ ካልሆነ ምሳሌው አድማጮች ሐሳቡ ግልጽ እንዲሆንላቸው ከመርዳት ይልቅ ከመስመር ሊያስወጣቸው ይችላል። በቅን ልቦና የተነሳሳ አንድ ተናጋሪ ቅቡዓን ቀሪዎች ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን ተገዢነት ለመግለጽ ሲል ከአንዲት የቤት ውሻ ጋር አነጻጽሯቸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የሚያቃልል ንጽጽር ተገቢ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ ሐሳብ ይበልጥ ማራኪ በሆነና ክብር ባለው ምሳሌ ገልጾታል። የኢየሱስን 144,000 ቅቡዓን ተከታዮች ‘ለባልዋ ከተሸለመች ሙሽራ’ ጋር አነጻጽሯቸዋል።—ራእይ 21:2
16 ምሳሌዎች ይበልጥ ውጤታማ የሚሆኑት ከሰዎች ሕይወት ጋር የተያያዙ ሲሆኑ ነው። በልጅነቱ እረኛ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ለበጎች ፍቅር የነበረው ንጉሥ ዳዊት፣ ናታን ስለ ታረደችው በግ በተናገረው ምሳሌ ልቡ ተነክቷል። (1 ሳሙኤል 16:11-13፤ 2 ሳሙኤል 12:1-7) በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው እንስሳ በሬ ቢሆን ኖሮ ይህን የመሰለ ውጤት መገኘቱ ያጠራጥራል። በተመሳሳይም ሳይንሳዊ ክስተትን ወይም እምብዛም የማይታወቁ ታሪካዊ ክንውኖችን መሠረት ያደረጉ ምሳሌዎች ለአድማጮቻችን እጅግም የሚፈይዱት ነገር አይኖርም። የኢየሱስ ምሳሌዎች በዕለት ተለት ሕይወት ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። መብራትን፣ የሰማይ ወፎችንና የሜዳ አበቦችን የመሳሰሉ በአካባቢው የሚታወቁ ነገሮችን ይጠቀም ነበር። (ማቴዎስ 5:15, 16፤ 6:26, 28) የኢየሱስ አድማጮች እነዚህን ነገሮች በቀላሉ ሊረዷቸው ይችሉ ነበር።
17. (ሀ) ምሳሌዎቻችን በምን ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይችላሉ? (ለ) በጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙትን ምሳሌዎች ከተማሪዎቻችን ሁኔታ ጋር ልናስማማ የምንችለው እንዴት ነው?
17 በአገልግሎታችን ላይ ቀላል ነገር ግን ውጤታማ የሆኑ ምሳሌዎችን መጠቀም የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉን። ጥሩ ተመልካቾች ሁኑ። (ሥራ 17:22, 23) ምናልባት ምሳሌያችን በሚያዳምጠን ሰው ልጆች፣ ቤት፣ ሥራ ወይም የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። ወይም በምናጠናው ጽሑፍ ላይ የቀረበልንን ምሳሌ ለማዳበር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው በግል የምናውቀውን ነገር ልንጠቀም እንችላለን። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 8 አንቀጽ 14 ላይ የሚገኘውን ውጤታማ ምሳሌ ለአብነት ያህል እንመልከት። ምሳሌው ጎረቤቱ በሐሰት ስሙን ስላጠፋበት አንድ አፍቃሪ ወላጅ ይናገራል። ይህን ምሳሌ ራሱ ወላጅ ከሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ጋር እንዴት ልናዛምደው እንደምንችል ጥቂት ልናስብ እንችላለን።
ጥቅሶችን እንደሚገባ ማንበብ
18. አቀላጥፈን ለማንበብ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
18 ጳውሎስ “ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ” በማለት ጢሞቴዎስን መክሮት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 4:13) መጽሐፍ ቅዱስ የትምህርታችን መሠረት እንደመሆኑ መጠን መጽሐፍ ቅዱስን አቀላጥፎ ማንበብ መቻል ጠቃሚ ነው። ሌዋውያን የሙሴን ሕግ ለአምላክ ሕዝቦች የማንበብ መብት ነበራቸው። ሲያነቡ ይደነቃቀፉ ነበርን? ወይም ስሜት አልባ በሆነ አንድ ዓይነት የድምፅ ቅላጼ ያነብቡ ነበርን? በፍጹም፣ መጽሐፍ ቅዱስ በነህምያ 8:8 ላይ “የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፣ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር” ይላል።
19. ጥቅሶች የማንበብ ችሎታችንን ልናሻሽል የምንችለው እንዴት ነው?
19 አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ የሆኑ አንዳንድ ክርስቲያን ወንዶች በንባብ ረገድ ድክመት እንዳለባቸው ይታያል። መሻሻል የሚችሉት እንዴት ነው? ልምምድ በማድረግ ነው። አዎን፣ አቀላጥፈው ማንበብ እስከሚችሉ ድረስ ጮክ ብለው እያነበቡ ደጋግመው ቢለማመዱ ጥሩ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ የቴፕ ቅጂዎች በቋንቋችሁ የሚገኙ ከሆነ እነሱን በማዳመጥ አንባቢው እንዴት እንደሚያጠብቅና ድምፁን እንደሚለዋውጥ እንዲሁም እንግዳ የሆኑ ቃላትን እንዴት እንደሚያነብ መከታተሉ ጥበብ ነው። በተጨማሪም የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምን በቋንቋቸው የሚያገኙ ሰዎች ደግሞ ትክክለኛ የአነባበብ ድምፀትን ለመጠቆም በሚረዱት ምልክቶች ሊጠቀሙ ይችላሉ።a በቂ ልምምድ ካደረግን እንደ ማሄርሻልአልሃሽባዝ የመሳሰሉትን ስሞች እንኳ ሳይቀር ብዙም ሳንቸገር ለማንበብ እንችላለን።—ኢሳይያስ 8:1 NW
20. ‘ለማስተማር ሥራችን ልንጠነቀቅ’ የምንችለው እንዴት ነው?
20 የይሖዋ ሕዝቦች በመሆናችን አስተማሪ የመሆን ልዩ መብት አግኝተናል! ስለዚህ እያንዳንዳችን ይህን ኃላፊነት በቁም ነገር እንመልከተው። ‘ለራሳችንና ለማስተማር ሥራችን ዘወትር ጥንቃቄ’ እናድርግ። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ጥሩ አዳማጮች በመሆን፣ ነገሮችን ቀላል በማድረግ፣ ጥልቅ ማስተዋል የሚንጸባረቅባቸው ጥያቄዎች በመጠየቅ፣ ውጤታማ የሆኑ ምሳሌዎች በመጠቀምና ቅዱሳን ጽሑፎችን እንደሚገባ በማንበብ የተዋጣልን አስተማሪዎች መሆን እንችላለን። ሁላችንም ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቃሚዎች እንሁን። እንዲህ ማድረጋችን ‘የተማሩት ምላስ’ እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል። (ኢሳይያስ 50:4) ብሮሹሮችን፣ የቴፕ ክሮችንና የቪድዮ ካሴቶችን ጨምሮ ለአገልግሎታችን በቀረቡልን መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም በማስተዋልና በማሳመን ችሎታ ማስተማር የምንችልበትን መንገድ ልንማር እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የተጸውኦ ስሞች በሚነበቡበት ጊዜ የት ላይ መጥበቅና መላላት እንዳለባቸው የሚጠቁሙ ምልክቶችን ይጠቀማል።
ታስታውሳለህ?
◻ ጥሩ አዳማጭ መሆን በማስተማር ሥራችን ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ቀላል በሆነ መንገድ በማስተማር ረገድ ጳውሎስንና ኢየሱስን ልንመስላቸው የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ሌሎችን በምናስተምርበት ጊዜ በምን ዓይነት ጥያቄዎች ልንጠቀም እንችላለን?
◻ ይበልጥ ውጤታማ የሆኑት ምሳሌዎች ምን ዓይነት ናቸው?
◻ ለሕዝብ በማንበብ ረገድ ችሎታችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ አስተማሪ ጥልቅ ማስተዋል ለማግኘት እንዲችል ያዳምጣል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የኢየሱስ ምሳሌዎች በዕለት ተለት ሕይወት ከሚከናወኑ ነገሮች የተወሰዱ ነበሩ