128ኛው የጊልያድ ምረቃ
ሚስዮናውያን ሰዎችን ‘ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ተላኩ
“ሁሉም ብሔራት ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውንና ቤታቸውን ትተው ወደ ሌሎች አገሮች በመሄድ ምሥራቹን ለመስበክ ፈቃደኞች ሆነዋል።” የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን ከላይ ያለውን ሐሳብ በመናገር አድማጮቹ አስደሳች የሆነውን መንፈሳዊ ፕሮግራም በጉጉት እንዲጠብቁ አደረጋቸው።
መጋቢት 13, 2010 በተካሄደው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ128ኛው ክፍል የምረቃ ፕሮግራም ላይ ወደ 8,000 የሚጠጉ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ከ27 አገራት የመጡ የተመራቂዎች ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች በፕሮግራሙ ላይ ተካፍለው ነበር።
‘ደቀ መዛሙርቱ ቤታቸው ቁጭ ብለው አልጠበቁም’
የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው ወንድም ስፕሌን ስብሰባውን የከፈተው ኢየሱስ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ በማብራራት ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ወንድም ስፕሌን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ሰዎች እንደላካቸው ጎላ አድርጎ ገልጿል። እርግጥ ነው፣ በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት አንዳንድ ሰዎች ከመስጴጦምያ፣ ከሰሜን አፍሪካና ከተለያዩ የሮም ግዛቶች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው የነበረ ሲሆን ምሥራቹንም ሰምተዋል። ሆኖም “ደቀ መዛሙርቱ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ወደ እኛ ይመጣሉ ብለው በማሰብ ቤታቸው ቁጭ ብለው አልጠበቁም”፤ ከዚህ ይልቅ “ሰዎችን ለማግኘት እስከ ምድር ዳር ድረስ መሄድ ነበረባቸው” ሲል ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 1:8
ወንድም ስፕሌን እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲያደርጉት የሚፈልገውን ነገር በመናገር ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ ሥራውን እንዴት መሥራት እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። እንዲጸልዩ ከመንገር ባለፈ እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። እንዲሁም ስበኩ ከማለት ይልቅ እንዴት መስበክ እንዳለባቸው አሳይቷቸዋል። ጥሩ አስተማሪዎች መሆን እንዳለባቸው ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን ጥሩና ውጤታማ የሆነውን የማስተማሪያ ዘዴ ምን እንደሆነ በተግባር አሳይቷቸዋል።”
ሊቀ መንበሩ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ ለተመራቂዎቹ ወላጆች ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:20) ወንድም ስፕሌን ተማሪዎቹ በተመደቡባቸው አገራት ሲያገለግሉ ኢየሱስ እነሱን መንከባከቡን እንደሚቀጥል ለአድማጮቹ አረጋግጦላቸዋል።
“መኩራራታችሁን ቀጥሉ”
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ፣ ተመራቂዎቹን “መኩራራታችሁን ቀጥሉ” በማለት አበረታቷቸዋል። ወንድም ሞሪስ ተገቢ የሆነና ተገቢ ያልሆነ የኩራት ዓይነት እንዳለ ተናግሯል። ተገቢ ያልሆነው ኩራት ለራስ ክብር በመፈለግ ላይ ያተኮረ ነው። ተገቢ የሆነው ኩራት ደግሞ በ1 ቆሮንቶስ 1:31 ላይ ተገልጿል፤ ጥቅሱ “የሚመካ በይሖዋ ይመካ” ወይም ይኩራራ ይላል። ወንድም ሞሪስ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ይሖዋ አምላክ ጥልቅ ማስተዋልና እውቀት ማግኘት በእርግጥ የሚያኮራ ነው። እውነት ነው፣ የይሖዋን ቅዱስ ስም መሸከማችንና የይሖዋ ምሥክር መሆናችን ለእኔም ሆነ ለእናንተ ትልቅ መብት ነው።”—ኤርምያስ 9:24
ከዚያም ወንድም ሞሪስ በአፍሪካ የሚገኝ አንድ ሚስዮናዊ ያጋጠመውን ተሞክሮ በመናገር የይሖዋን ስም ማሳወቅ ስላለው ጥቅም ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይህ ሚስዮናዊ ወንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ለመስጠት ከባለቤቱ ጋር እየሄደ ነበር። የፍተሻ ጣቢያ ላይ ሲደርሱ አንድ ወጣት ወታደር ጠመንጃውን ወንድም ላይ ደግኖ ማንነቱን ጠየቀው። ሚስቱም በጊልያድ ያገኘችውን ሥልጠና በማስታወስ ወደ ባለቤቷ ጠጋ ብላ በሹክሹክታ “የይሖዋ ምሥክር እንደሆንክና የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ለመስጠት እየሄድክ እንደሆነ ንገረው” አለችው። እሱም ምክሯን ተቀብሎ እንዳለችው አደረገ፤ በመሆኑም የፍተሻ ጣቢያውን እንዲያልፉ ተፈቀደላቸው። በሚቀጥለው ቀን ባልና ሚስቱ፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሚስዮናዊ ነን የሚሉ ነፍሰ ገዳዮችን ንቁ ሆነው እንዲጠብቁ ለወታደሮቹ ትእዛዝ አስተላልፈው እንደነበር በሬዲዮ ሰሙ! እነዚህ ባልና ሚስት ‘ሚስዮናውያን ነን’ ከማለት ይልቅ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ በመናገራቸው ከብዙ ችግር ድነዋል። ወንድም ሞሪስ “ወደተመደባችሁበት አገር ስትደርሱ መኩራራታችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ እናንተን በመጠቀም ለዘላለማዊ ክብሩ ሲል ወደፊት ስለሚፈጽመው ነገር በኩራት ተናገሩ” በማለት ንግግሩን ደመደመ።
“ተልእኳችሁን በተሟላ ሁኔታ ትፈጽማላችሁ?”
የበላይ አካል አባል የሆነውና ሚስዮናዊ የነበረው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ተማሪዎቹ ከላይ በተጠቀሰው ጥያቄ ላይ በቁም ነገር እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ወንድም “አንድ ሰው ሚስዮናዊ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው?” የሚል ጥያቄ አነሳ። ከዚያም “ሚስዮናዊ” የሚለው ቃል የመጣው ልዩ ተልእኮ የተሰጠውን ግለሰብ ወይም ቡድን ከሚያመለክት የላቲን አባባል እንደሆነ ገለጸ። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ተልእኳችን ምሥራቹን መስበክና ሌሎችን በመንፈሳዊ መርዳት ነው። ይህን ሥራ የምናከናውነው ወደ ምድር የተላከበትን ዓላማ ምንጊዜም በአእምሮው ይዞ የነበረውን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ነው። ኢየሱስ ለሮማዊው ገዥ ለጳንጥዮስ ጲላጦስ “ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት እንድመሠክር ነው” ብሎት ነበር።—ዮሐንስ 18:37
ተናጋሪው፣ ተመራቂዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተጠቀሰው የኢያሪኮ ጦርነት እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል። እስራኤላውያን ተዋጊዎች ለስድስት ቀናት ማልደው በመነሳት የጦር መሣሪያቸውን ከታጠቁ በኋላ የኢያሪኮን ከተማ ዞረው ብቻ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። ተናጋሪው “ከሰው አመለካከት አንጻር ሲታይ የተሰጣቸው ተልእኮ ምክንያታዊ ያልሆነና ግራ የሚያጋባ ይመስል ነበር” ብሏል። ምናልባትም አንዳንድ ወታደሮች ‘የምን ጊዜ ማቃጠል ነው?’ የሚል ስሜት ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። በሰባተኛው ቀን ግን እስራኤላውያን ከተማዋን ሰባት ጊዜ ከዞሩ በኋላ ታላቅ የጦርነት ጩኸት እንዲያሰሙ መመሪያ ተሰጣቸው። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የኢያሪኮ ቅጥሮች ፈራረሱ!—ኢያሱ 6:13-15, 20
ወንድም ጃክሰን ስለ ኢያሪኮ ከሚገልጸው ዘገባ አራት ትምህርቶችን ማግኘት እንደሚቻል ገልጿል። (1) ታዛዥነት አስፈላጊ ነው። ነገሮችን ማከናወን ያለብን በይሖዋ መንገድ ነው፤ የራሳችን መንገድ የተሻለ እንደሆነ ማሰብ የለብንም። (2) በይሖዋ ላይ እምነት ማሳደርና በእሱ መተማመን እጅግ አስፈላጊ ነው። ‘የኢያሪኮ ግንብ የወደቀው በእምነት’ እንጂ በጦር መሣሪያ አይደለም። (ዕብራውያን 11:30) (3) ትዕግሥተኛ መሆን ይኖርብናል። ታጋሾች ከሆንን ከጊዜ በኋላ የይሖዋ በረከት ‘ያገኘናል።’ (ዘዳግም 28:2 የ1954 ትርጉም) (4) ተስፋ አትቁረጡ። ተልእኳችሁን ፈጽሞ አትርሱ። ወንድም ጃክሰን “ምንጊዜም እነዚህን ነጥቦች በአእምሯችሁ የምትይዙ ከሆነ ለይሖዋ ውዳሴና ክብር የሚያመጣውን ተልእኳችሁን በተሟላ ሁኔታ ትፈጽማላችሁ” በማለት ንግግሩን ደምድሟል።
ሌሎች የፕሮግራሙ ጎላ ያሉ ገጽታዎች
“መጽሐፍ ቅዱስንና ባለቤቱን ውደዱ።” የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ማክስዌል ሎይድ ያቀረበው ንግግር ርዕስ ይህ ነበር። ተመራቂዎቹን “መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው መጽሐፍ ሊሆንላችሁ ይገባል” ብሏቸዋል። ከዚያም እንደሚከተለው በማለት አበረታታቸው፦ ለይሖዋ አምላክ ያላችሁ ፍቅር እንዲዳፈን አታድርጉ። የምታስተምሩትን ትምህርት ሁሉም ሰው ይረዳዋል ብላችሁ አታስቡ። የምታስተምሩት ትምህርት ወደ ተማሪዎቻችሁ ልብ ዘልቆ እንዲገባ ለማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በቀላሉ በሚገባ መንገድ ለማቅረብ ጥረት አድርጉ። ትሑቶች ሁኑ። የተሻለ እውቀት እንዳላችሁ ሆናችሁ ለመቅረብ አትሞክሩ። ምሳሌ በመሆን አስተምሩ። ተማሪዎቻችሁ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ፍቅር እንዳላችሁ ይመልከቱ።
“ቁራዎችን አስተውሉ።” የጊልያድ አስተማሪ የሆነውና ሚስዮናዊ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ወንድም ማይክል በርኔት ከላይ ባለው ርዕስ ላይ የተመሠረተ ንግግር አቅርቦ ነበር። አልፎ አልፎ የሚያስጨንቁ ነገሮች እንደሚያጋጥሙን ገልጿል። ይሁንና ኢየሱስ “ቁራዎችን አስተውሉ፤ አይዘሩም፣ አያጭዱም . . . ሆኖም አምላክ ይመግባቸዋል” በማለት የሰጠውን ምክር ማስታወስ ይኖርብናል። (ሉቃስ 12:24) በሕጉ ቃል ኪዳን መሠረት ቁራዎች እንደ ርኩስ ስለሚታዩ አይበሉም ነበር። በመሆኑም እንደ አስጸያፊ ነገር ይቆጠሩ ነበር። (ዘሌዋውያን 11:13, 15) ቁራዎች እንዲህ የሚታዩ ቢሆንም እንኳ አምላክ ይመግባቸዋል። ወንድም በርኔት እንዲህ ብሏል፦ “እናንተም ወደፊት ከባድ የሆነ አስጨናቂ ሁኔታ ሲገጥማችሁ ቁራዎችን አስቡ። አምላክ ርኩስና አስጸያፊ ተደርጎ የሚቆጠረውን ይህን ወፍ እንዲህ የሚንከባከበው ከሆነ በእሱ ፊት ንጹሕ ሆናችሁ የተቆጠራችሁትን እናንተንማ እንዴት የበለጠ አይንከባከባችሁም?”
“ምንም የበደልኩህ ነገር የለም።” የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ማርክ ኑሜር ተሰብሳቢዎቹ ኢየሱስ ስለ ወይን እርሻ ሠራተኞች የተናገረውን ምሳሌ በትኩረት እንዲመረምሩ ረድቷቸዋል። አንዳንዶቹ ሠራተኞች ቀኑን ሙሉ ሲደክሙ ውለው ነበር። ሌሎቹ ሠራተኞች ደግሞ የሠሩት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነበር። ያም ሆኖ ሁሉም ተመሳሳይ ደሞዝ ተከፈላቸው! በዚህ ጊዜ ለረጅም ሰዓት የሠሩት ሠራተኞች አጉረመረሙ። የወይን እርሻው ባለቤት ከሚያጉረመርሙት ሠራተኞች ለአንዱ “ምንም የበደልኩህ ነገር የለም። የተስማማነው አንድ ዲናር እንድከፍልህ ነው፣ አይደለም እንዴ? ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ” አለው። (ማቴዎስ 20:13, 14) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ራሳችሁን ከሌሎች ጋር አታወዳድሩ። “ተገቢ ባልሆነ መንገድ ራሳችሁን ከሌሎች ጋር የምታወዳድሩ ከሆነ ደስታችሁን ታጣላችሁ” በማለት ወንድም ኑሜር ተናግሯል። አክሎም “እንዲያውም የአገልግሎት ክልላችሁን ትታችሁ እስከ መሄድ ብሎም ውድ የሆነውን ይህን መብታችሁን እስከ መተው ሊያደርሳችሁ ይችላል” ብሏል። ኢየሱስ በጊዜያችን የሚካሄደውን መንፈሳዊ የመከር ሥራ እየመራ እንደሆነና እሱም ለተከታዮቹ ደስ ያለውን ነገር ማድረግ እንደሚችል ተናጋሪው ተማሪዎቹን አሳስቧቸዋል። ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ለሌሎች ተጨማሪ መብት በመስጠታቸው ምንም የበደሏችሁ ነገር የለም። ባላችሁ መብት ላይ አተኩሩ እንጂ ሌሎች የተቀበሉት “ደሞዝ” ይሖዋ እንድትሠሩት ከሰጣችሁ ሥራ እንዲያዘናጋችሁ አትፍቀዱ።
ተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች
ተማሪዎቹ ትምህርት ላይ በማይሆኑበትና የቤት ሥራ በሌላቸው ወቅት በአካባቢያቸው ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ጋር በመተባበር በስብከቱ ሥራ ይካፈሉ ነበር። ከጊልያድ አስተማሪዎች አንዱ የሆነው ወንድም ሳም ሮበርሰን ለተወሰኑ ተማሪዎች ያገኟቸውን ተሞክሮዎች እንዲናገሩ ቃለ ምልልስ አድርጎላቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አሌሳንድራ ኪርክለ የተባለች እህት ከአንዲት እናት ጋር ተገናኝታ የነበረ ሲሆን ይህች ሴት የልጇ የማጨስ ልማድ በጣም ያሳስባት ነበር። ትንሽ ቆየት ብላ አሌሳንድራ ስለዚህ ጉዳይ የሚያወሳ አንድ የንቁ! መጽሔት ለእናትየው ይዛላት ሄደች። ሆኖም ቤት ውስጥ ማንንም ሰው አላገኘችም፤ ስለሆነም መጽሔቱን ትታ ሄደች። በኋላ ግን አሌሳንድራ ሴትየዋን ያገኘቻት ሲሆን እሷም ወደ ቤት እንድትገባ ጋበዘቻት። ሴትየዋ ስለ መጽሔቱ የተሰማትን አድናቆት ከገለጸችላት በኋላ “አምላክ ይህን ሁሉ መከራ የሚያደርስብኝ ምን እንድማር ፈልጎ ነው እያልኩ አስብ ነበር” አለቻት። አሌሳንድራ ክፉ ነገሮች እንዲደርሱብን የሚያደርገው አምላክ እንዳልሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየቻት። (ያዕቆብ 1:13) በአሁኑ ጊዜ ሴትየዋም ሆነች ልጇ መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ ይገኛሉ።
የአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ የሚሠራው ወንድም ማልቪን ጆንስ የቀድሞ የጊልያድ ተመራቂዎች ለሆኑ ሦስት ወንድሞች ቃለ ምልልስ አድርጎላቸዋል፤ እነሱም በአልባኒያ የሚያገለግለው ወንድም ዮን ሶውመሩድ፣ በኬንያ የሚያገለግለው ወንድም ማርክ አንደርሰንና ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤቶችን በሚከታተለው ክፍል ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኘው ወንድም ጄምስ ሂንደረር ናቸው። የጊልያድ ትምህርት ቤት፣ ተማሪዎቹ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንዲያውቁ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ምንም ዓይነት አስተዳደግ ይኑራቸው ወይም የትም አገር ያገልግሉ እነዚህን እውነቶች በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንደሚያስተምራቸው ሦስቱም ወንድሞች ገልጸዋል።
ከዚያም ከተማሪዎቹ መካከል አንዱ የተመራቂዎቹን አድናቆት የሚገልጽ ስሜት የሚነካ ደብዳቤ አነበበ። ከበላይ አካል አባላት ውስጥ በዕድሜ አንጋፋ የሆነው የ96 ዓመቱ ወንድም ጆን ባር የ128ኛው የጊልያድ ክፍል ተመራቂዎች የሚያከናውኑትን ሥራ ይሖዋ እንዲባርክላቸው በመጠየቅ ፕሮግራሙን በጸሎት ደምድሟል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ/ካርታ]
ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ
8 የተውጣጡባቸው አገራት
54 ተማሪዎች
27 ባልና ሚስት
35.2 አማካይ ዕድሜ
19.1 ከተጠመቁ በኋላ ያሳለፉት ዓመታት በአማካይ
13.8 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ
[ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ተመራቂዎቹ የተመደቡት ከታች ወደሚገኙት 25 አገራት ነው
ሚስዮናውያን የተመደቡባቸው አገራት
አልባኒያ
አሩባ
ቦሊቪያ
ካምቦዲያ
ኮት ዲቩዋር
ዶሚኒካን ሪፑብሊክ
ኢኳዶር
ጋና
ጓቲማላ
ጊኒ
ጋያና
ሆንዱራስ
ኢንዶኔዥያ
ኮሶቮ
ላትቪያ
ላይቤሪያ
ማዳጋስካር
ሞንጎሊያ
ናሚቢያ
ኒካራጓ
ፓራጓይ
ሩማንያ
ሩዋንዳ
ሰርቢያ
ታይዋን
(በአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር)
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ ተማሪዎች ካገኟቸው ተሞክሮዎች መካከል አንዱን በሠርቶ ማሣያ ሲያቀርቡ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ128ኛው ክፍል ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ኤሊያ ኬለር፣ ኢሻ ኦስቶፖቪች፣ ስቴፋኒ ጄከብሰን፣ ማሪ አርያስ፣ ኢቪ ዲክመን፣ ጂኒ ታናካ፣ ኪዮኮ ሃራዳ
(2) ሊሴት ካማቾ፣ አሌሳንድራ ኪርክለ፣ ሶንያ ሮዝሪገስ፣ ቤኪ ዎርድ፣ ኬሊ ትሬነሎን፣ ቪልመ ቪክቶሪያ፣ ፌቤ ኦክስሊ፣ ካን ንጅወን
(3) ኦዚ ኦክስሊ፣ አንድሬአ ዴ ዲዮስ፣ ሻርሎት ሊንድስትረም፣ ጁሊ አለን፣ ትሪሸ ሚድስ፣ ጃን ዋዲንግተን፣ ኤፍራኢን ቪክቶሪያ
(4) ሂሮኦ ሃራዳ፣ አሌክስ ሊንድስትረም፣ ኤሊያን ኦርሲኒ፣ ዳንየል ሎግ፣ ተኔል ሚሱድ፣ ሶንየ ቤርዥሮን፣ ጋብሪየል ካማቾ፣ ቲም ዎርድ
(5) ቪልፍሪት ኪርክለ፣ ሁዊ ንጅወን፣ ኢቫ ክሬመር፣ ሴሊን ቡዌርጎ፣ ናድየ ቲትመስ፣ ክሪስ ዴ ዲዮስ፣ አልቤርቶ ሮዝሪገስ፣ ማት ዋዲንግተን
(6) ጂም ዲክመን፣ ክሪስ አለን፣ ራየን ቲትመስ፣ ዣን አርያስ፣ ኤሪክ ቤርዥሮን፣ ጆ ኬለር፣ ፍሊንት ኦስቶፖቪች፣ ፍሬዴሪክ ቡዌርጎ
(7) ኬን ታናካ፣ ጂም ክሬመር፣ ራያን ጄከብሰን፣ ጄሚ ትሬነሎን፣ ጆርደን ሎግ፣ ዳርሲ ሚድስ፣ ዴቪድ ሚሱድ፣ አዳን ኦርሲኒ