ከምንጊዜውም ይበልጥ መንቃት የሚያስፈልግበት ጊዜ አሁን ነው!
“ስላለንበት ዘመን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይኖራችሁ ተጠንቀቁ፤ ከእንቅልፋችን መንቃት የሚያስፈልግበት ጊዜ አሁን ነው።” (ሮሜ 13:11፣ ኖክስ) ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች ይህን መልእክት የጻፈው የአይሁድ ሥርዓት በ70 እዘአ ከመጥፋቱ ወደ 14 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ነበር። አይሁድ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ንቁ ስለነበሩ በዚያ ቀውጢ ወቅት በኢየሩሳሌም አልነበሩም፤ በመሆኑም ከሞት ወይም ከባርነት አምልጠዋል። ሆኖም ከተማዋን ለቀው መውጣት እንዳለባቸውና ወደዚያ መመለስ እንደሌለባቸው ሊያውቁ የቻሉት እንዴት ነበር?
ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላት ኢየሩሳሌምን እንደሚከባትና ነዋሪዎቿንም እንደሚገድል አስጠንቅቆ ነበር። (ሉቃስ 19:43, 44) ከዚያም ኢየሱስ ለተከታዮቹ የተለያየ ገጽታ ያለውና ለመገንዘብ የማያዳግት ምልክት ነገራቸው። (ሉቃስ 21:7–24) በኢየሩሳሌም ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች ከተማዋን ለቅቆ መውጣት ማለት ቤት ንብረታቸውንና ሥራቸውን መተው ማለት ነበር። ያም ሆኖ ግን ንቁ መሆናቸውና መሸሻቸው ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል።
ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት ትንቢት በተናገረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?” ሲሉ ጠየቁት። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ በሰጠው ምላሽ የእሱን የወደፊት መገኘት በኖኅ ዘመን ምድር አቀፍ የውኃ መጥለቅለቅ ከመድረሱ በፊት ከነበረው ጊዜ ጋር አወዳድሮታል። ኢየሱስ የውኃ ጥፋቱ ክፉዎችን በሙሉ ጠራርጎ እንዳጠፋ አመልክቷል። (ማቴዎስ 24:21, 37–39) በዚህ መንገድ አምላክ በሰዎች ጉዳዮች ውስጥ በድጋሚ ጣልቃ እንደሚገባ ጠቁሟል። አንድን ክፉ ዓለም ወይም የነገሮች ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ በማስወገድ ከፍተኛ እርምጃ ይወስዳል! (ከ2 ጴጥሮስ 3:5, 6 ጋር አወዳድር።) ይህ በጊዜያችን ሊፈጸም ይችላልን?
ሁሉም ነገር እንዳለ ነውን?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ ከነበሩት አይሁዳውያን መካከል ያቺ የተቀደሰች ከተማቸው ማለትም ኢየሩሳሌም ትጠፋለች ብለው ያሰቡት ጥቂቶች ነበሩ። በእሳተ ገሞራ አካባቢ በሚኖሩ ሆኖም የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ደርሶባቸው በማያውቁ ሰዎች ላይም ተመሳሳይ የሆነ ያለማመን ሁኔታ ይታያል። ብዙዎች ማስጠንቀቂያው ሲነገራቸው “ይህ በእኔ ዕድሜ አይከሰትም” የሚል ምላሽ መስጠታቸው የተለመደ ነው። “እሳተ ገሞራዎች የሚፈነዱት በየሁለት ወይም በየሦስት መቶ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው” ሲሉ የእሳተ ገሞራ ተመራማሪ የሆኑት ሊዎኔል ዊልሰን ይናገራሉ። “ወላጆችህ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት አካባቢያቸውን ጥለው ለመሄድ ተገደው ከነበረ መጨነቅህ አይቀርም። ነገር ግን ፍንዳታው የደረሰው በአያቶችህ ዘመን ከሆነ እንዲያው እንደ ተረት ሆኖ ሊሰማህ ይችላል።”
ሆኖም ትክክለኛ መረጃ ማግኘት የአደጋ ምልክቶችን ለመገንዘብና በቁም ነገር ለመመልከት ያስችለናል። ከፐሌ ተራራ አካባቢ ከሸሹት ሰዎች አንዱ ስለ እሳተ ገሞራዎች ግንዛቤ የነበረውና የአደጋ ምልክቶቹን ያስተዋለ ነበር። የፒነቱቦ ተራራ ከመፈንዳቱ ከጥቂት ጊዜ በፊትም እንዲህ ያሉ ምልክቶችን በትክክል ለመተርጎም ተችሎ ነበር። በተራራው ውስጥ እየተጠናከረ የመጣውን የማይታይ ኃይል በቅርብ ይከታተሉ የነበሩት የእሳተ ገሞራ ጠበብቶች በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ቦታውን ለቅቆ እንዲወጣ ለማሳመን ችለው ነበር።
እርግጥ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ሁልጊዜ ችላ የሚሉና ምንም ነገር አይከሰትም የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። እንዲያውም ቆራጥ እርምጃ በሚወስዱት ላይ ያሾፉ ይሆናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ የመሰለው አመለካከት በጊዜያችን የተለመደ እንደሚሆን ተንብዮ ነበር። “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም:- የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ” ብሏል።—2 ጴጥሮስ 3:3, 4
“በመጨረሻው ዘመን” እንደምንኖር ታምናለህን? ዘ ኮለምቢያ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ በተባለው መጽሐፍ ላይ ጆን ኤ ጋርቲ እና ፒተር ጌይ “ሥልጣኔያችን ፍርክርኩ እየወጣ እንዳለ ልብ ብለናል?” ሲሉ ጠይቀዋል። ከዚያም እነዚህ ታሪክ ጸሐፊዎች አስተዳደራዊ ችግሮችን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወንጀልና የሕዝባዊ ዓመፅ መበራከትን፣ የቤተሰብ መፈራረስን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት አለመቻላቸውን፣ የሥልጣን አለመረጋጋትና በዓለም ዙሪያ የተከሰተውን ሞራላዊና ሃይማኖታዊ ውድቀት ገምግመዋል። “እነዚህ ነገሮች የአንድ ፍጻሜ ምልክቶች ባይሆኑ እንኳ አንድን ፍጻሜ ከሚጠቁሙ ምልክቶች ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው” ሲሉ ደምድመዋል።
“መጨረሻ” መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን የሚያሳምኑን በቂ ምክንያቶች አሉን። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት” ብሎ ስለሚናገር ፕላኔቷ ምድር ራሷ ያከትምላታል ብለን ልንፈራ አይገባም። (መዝሙር 104:5) ሆኖም በሰው ልጅ ላይ ይህን ሁሉ መከራ ያስከተለው የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ ያከትምለታል ብለን ልንጠብቅ ይገባል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው መሠረት የዚህን ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ለይተው የሚያሳውቁ በርካታ ገጽታዎች መመልከት ስለምንችል ነው። (“የመጨረሻዎቹ ቀናት አንዳንድ ገጽታዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የኢየሱስን ቃላት በዓለም ላይ ከሚፈጸሙት ሁኔታዎች ጋር ለምን አታነፃፅርም? እንዲህ ማድረግህ ራስህንም ሆነ ቤተሰብህን የሚጠቅሙ ጥበብ የተሞላባቸው ውሳኔዎች እንድታደርግ ይረዳሃል። ይሁን እንጂ አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
ሁልጊዜ ንቁ ሆኖ መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው
ሳይንቲስቶች አንድ እሳተ ገሞራ ሊፈነዳ እንደተቃረበ ቢያውቁም በትክክል መቼ እንደሚፈነዳ መናገር ግን አይችሉም። በተመሳሳይም ኢየሱስ ስለዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ሲናገር “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ብሏል። (ማቴዎስ 24:36) የዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ መቼ እንደሚሆን በትክክል ስለማናውቅ ኢየሱስ ይህን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል:- “ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ [ኢየሱስ] በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።”—ማቴዎስ 24:43, 44
የዚህ ሥርዓት ጥፋት ይህ ዓለም ባልጠበቀው ጊዜ ድንገት ከተፍ እንደሚል የኢየሱስ ቃላት ያሳያሉ። የእሱ ተከታዮች ብንሆንም እንኳ ‘ተዘጋጅተን ልንጠብቅ’ ይገባል። ያለንበት ሁኔታ ባልጠበቀው ሰዓት ሌባ ቤቱን ሊዘርፈው ከሚችል ሰው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል።
በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚገኙ ክርስቲያኖች “የጌታ ቀን፣ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። . . . ወንድሞች ሆይ፣ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም” በማለት ተናግሯል። ጳውሎስ አክሎም “እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (1 ተሰሎንቄ 5:2, 4, 6፣ NW የግርጌ ማስታወሻ) ‘መንቃትና በመጠን መኖር’ ምን ማለት ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ለመዳን የኢየሩሳሌምን ከተማ ለቀው መሸሽ ነበረባቸው፤ የእኛ ሽሽት ግን አንድን ከተማ ለቅቆ መውጣትን የሚጠይቅ አይደለም። ጳውሎስ በሮም የሚገኙ የእምነት ጓደኞቹን ከእንቅልፋቸው እንዲነቁ ከነገራቸው በኋላ ‘የጨለማን ሥራ አውጥተው’ ‘ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲለብሱት’ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ሮሜ 13:12, 14) የኢየሱስን ዱካ በቅርብ በመከተል ስለጊዜያችን ሁኔታ ንቁ መሆናችንን እናሳያለን፤ በዚህ መንገድ በመንፈሳዊ ንቁ መሆናችን ደግሞ ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ መለኮታዊ ጥበቃ እንድናገኝ ያደርገናል።—1 ጴጥሮስ 2:21
ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከተሉ ሁሉ ትርጉም ያለውና አርኪ ሕይወት ያገኛሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቲያናዊ ደቀ መዝሙርነት ቀንበር ልዝብና መንፈስን የሚያድስ መሆኑን ተገንዝበዋል። (ማቴዎስ 11:29, 30፣ NW የግርጌ ማስታወሻ) ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ‘አምላክንና እሱ ወደ ምድር የላከውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ’ ነው። (ዮሐንስ 17:3) የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች ‘የእውነትን ትክክለኛ እውቀት’ እንዲያገኙ ለመርዳት ሲሉ በየሳምንቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ቤቶችን ይጎበኛሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ቤትህ ድረስ በመምጣት መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ምንም ክፍያ ሊያስጠኑህ ፈቃደኞች ናቸው። ስለ አምላክ ቃል ያለህ እውቀት እያደገ ሲሄድ አንተም ያለንበት ዘመን የተለየ መሆኑን እንደምትገነዘብ አያጠራጥርም። በእርግጥም ከእንቅልፍ የምንነቃበት አጣዳፊ ጊዜ አሁን ነው!
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
የመጨረሻዎቹ ቀናት አንዳንድ ገጽታዎች
‘መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል’፣ ‘ሰላም ከምድር ይወሰዳል።’ (ማቴዎስ 24:7፤ ራእይ 6:4)
በዚህ ክፍለ ዘመን የተካሄዱት ሁለቱ የዓለም ጦርነቶችና ሌሎች በርካታ ግጭቶች ሰላምን ከምድር ላይ ወስደዋል። ታሪክ ጸሐፊው ጆን ኪጋን “አንደኛው ብሎም ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ቀደም ሲል ከተካሄዱት ጦርነቶች ሁሉ በመጠን፣ በኃይል፣ በስፋት እንዲሁም ባደረሱት የንብረትና የሕይወት ጥፋት የተለዩ ናቸው። . . . እነዚህ የዓለም ጦርነቶች ቀደም ሲል ከተካሄደ ከማንኛውም ጦርነት በበለጠ ስፋት የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፣ ብዙ ንብረት አውድመዋል፣ ብዙ ስቃይም አስከትለዋል።” በአሁኑ ጊዜ ጦርነቶች ይበልጥ የሚያጠቁት ከወታደሮች ይልቅ ሴቶችንና ሕፃናትን ነው። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እንዳሰላው ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ሁለት ሚልዮን ሕፃናት በጦርነቶች ተገድለዋል።
‘የምግብ እጥረት’ (ማቴዎስ 24:7 NW፤ ራእይ 6:5, 6, 8)
በ1996 የስንዴና የበቆሎ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቦ ነበር። ምክንያቱ ምን ነበር? በዓለም ጎተራዎች ውስጥ የሚገኘው የእነዚህ እህሎች ክምችት ለ50 ቀን ብቻ የሚበቃ እስከሚሆን ድረስ ማሽቆልቆሉ ሲሆን ይህ ደግሞ እስከ አሁን ከተመዘገቡት አኃዞች ሁሉ እጅግ አናሳው ነበር። መሠረታዊ በሆኑ የምግብ ዓይነቶች ላይ የዋጋ መናር ተከሰተ ማለት በድህነት የሚማቅቀው በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠረው የዓለም ሕዝብ ጦሙን ያድራል ማለት ነው። ከዚህ የዓለም ሕዝብ መካከል ደግሞ አብዛኞቹ ሕፃናት ናቸው።
‘የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ’ (ማቴዎስ 24:7)
ባለፉት 2,500 ዓመታት ከደረሱት የመሬት መንቀጥቀጦች ውስጥ እያንዳንዳቸው ከ100,000 በላይ ሰዎች የገደሉት ዘጠኝ ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህም አራቱ የተከሰቱት ከ1914 ወዲህ ነው።
‘የዓመፅ መብዛት’ (ማቴዎስ 24:12)
ሃያኛው መቶ ዘመን እየተገባደደ ሲሄድ ዓመፅ ወይም ሕገ ወጥነት እየተስፋፋ ሄዷል። አሸባሪዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት፣ ሰዎችን በጭካኔ መግደልና በጅምላ መጨፍጨፍ ከእነዚህ የመጨረሻ ቀናት አሰቃቂ ገጽታዎች መካከል የሚፈረጁ ናቸው።
“በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር” (ሉቃስ 21:11)
በ1990ዎቹ ዓመታት በሳንባ ነቀርሳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 30 ሚልዮን ይሆናል። በሽታ ተሸካሚ ባክቴሪያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መድኃኒት የማይበግራቸው እየሆኑ መጥተዋል። ሌላው ገዳይ በሽታ ወባ ሲሆን በየዓመቱ ከ300 እስከ 500 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎችን እንደሚይዝና ወደ 2 ሚልዮን የሚጠጉትን እንደሚገድል ተገምቷል። ይህ ክፍለ ዘመን ሲገባደድ ኤድስ በየዓመቱ 1.8 ሚልዮን ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳርግ ይጠበቃል። ዘ ስቴት ኦቭ ዘ ዎርልድ 1996 “ዛሬ ሰብዓዊው ፍጡር በወረርሽኝ በሽታዎች ተጥለቅልቋል” ሲል ገልጿል።
“ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል።” (ማቴዎስ 24:14)
በ1997 የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጥ ሰዓት አሳልፈዋል። ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡ ምሥክሮች በ232 አገሮች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ይህን መልእክት ያለማሰለስ ያደርሳሉ።
[ምንጮች]
FAO photo/B. Imevbore
U.S. Coast Guard photo
[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ንቁ ስለነበሩ ከኢየሩሳሌም ሸሽተዋል