-
ምሥራቹን የሚሰብኩት እነማን ናቸው?መጠበቂያ ግንብ—2011 | መጋቢት 1
-
-
ምሥራቹን የሚሰብኩት እነማን ናቸው?
“. . . በመላው ምድር ይሰበካል።”—ማቴዎስ 24:14
የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ እየሰበኩ ነው። ይህንንም የሚያደርጉት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ነው። ምሥራቹን የሚሰብኩበት አንዱ መንገድ የሚከተለው ነው፦
ሰዎችን በማነጋገር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንዳደረጉት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ሰዎች ወዳሉባቸው ቦታዎች በመሄድ ምሥራቹን ይሰብካሉ። (ሉቃስ 8:1፤ 10:1) ሰዎች እነሱ ወዳሉበት እስኪመጡ ድረስ አይጠብቁም። ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ለሰዎች በመስበኩ ሥራ ይካፈላሉ። ከቤት ወደ ቤት በመሄድ፣ በመንገድ ላይ፣ በስልክና በሌሎች መንገዶች ምሥራቹን ይሰብካሉ። ባለፈው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሥራ ላይ ከአንድ ቢሊዮን ተኩል በላይ ሰዓት አሳልፈዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሰዎች ኢየሱስ “[ያዘዛቸውን] ሁሉ እንዲጠብቁ” ጭምር ያስተምራሉ። (ማቴዎስ 28:20) በዓለም ዙሪያ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን በቋሚነት በነፃ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን የሚሰብኩት በ236 አገሮች ውስጥ ነው። የተለያየ የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎች ይሰብካሉ። በገጠርም ሆነ በከተማ፣ በአማዞን ጫካም ሆነ በሳይቤሪያ ደን፣ በአፍሪካ በረሃም ሆነ በሂማሊያ ተራሮች ይሰብካሉ። ይህን የሚያደርጉት ተከፍሏቸው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምሥራቹን የሚሰብኩት ለአምላክና ለሰዎች ካላቸው ፍቅር የተነሳ የራሳቸውን ጊዜና ገንዘብ መሥዕዋት በማድረግ ነው። ምሥራቹን ለማዳረስ የሚጠቀሙበት ሌላው መንገድ ደግሞ የሚከተለው ነው፦
በጽሑፎች። በአሁኑ ጊዜ በ185 ቋንቋዎች የሚታተመው የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የሚባለው ይህ መጽሔት በእያንዳንዱ እትም ከ42 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ይሰራጫል። በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጀው ንቁ! የተባለው መጽሔትም መንግሥቱን የሚያስታውቅ ሲሆን እያንዳንዱ እትም በ83 ቋንቋዎች ወደ 40 ሚሊዮን በሚጠጉ ቅጂዎች ይታተማል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን የሚያብራሩ መጽሐፎች፣ ብሮሹሮች፣ ትራክቶች፣ ሲዲዎች/ኤምፒ3ዎችና ዲቪዲዎች ወደ 540 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች ይዘጋጃሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ20 ቢሊዮን የሚበልጡ እንዲህ ዓይነት መርጃ መሣሪያዎችን አዘጋጅተው አሰራጭተዋል፤ ይህም ሲባል በምድራችን ላይ ለሚኖር ለእያንዳንዱ ግለሰብ በአማካይ ሦስት ሦስት ይደርሰዋል ማለት ነው!
ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸው ያዘጋጁትንም ሆነ በሌሎች የተዘጋጁ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ኃላፊነት ወስደው ያትማሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ተርጉመው የሚያትሙትና የሚያሰራጩት የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአሁኑ ጊዜ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በ96 ቋንቋዎች ይገኛል። ይህ ትርጉም እስከ አሁን ከ166 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ተሰራጭቷል። የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምሥራች የሚያሠራጩበት ሌላው መንገድ የሚከተለው ነው፦
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች። የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው ባሉ የመንግሥት አዳራሾች የሚያካሂዷቸው ሳምንታዊ ስብሰባዎች እንዲያው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ብቻ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ እውቀት ለማስጨበጥ ታስበው የሚዘጋጁ ናቸው። በስብሰባዎቹ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ ንግግሮች ይሰጣሉ፤ እንዲሁም በመጠበቂያ ግንብ መጽሔትና በሌሎች ጽሑፎች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ይጠናል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የበለጠ ውጤታማ የምሥራቹ ሰባኪዎች መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይማራሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ በዓለም ዙሪያ ባሉ ከ107,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ ተመሳሳይ ጽሑፎችን ያጠናሉ፤ ይህም ለአንድነታቸው አስተዋጽኦ ያበረክታል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ማንኛውም ሰው መገኘት ይችላል። እንዲሁም ሙዳየ ምጽዋት በፍጹም አይዞርም። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች የተማሩትን በተግባር የማያውሉ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሁሉ ነገሮች መና ሆነው ይቀሩ ነበር። በመሆኑም ሰዎች ምሥራቹን እንዲቀበሉ የሚከተለውን ያደርጋሉ፦
በግለሰብ ደረጃ ምሳሌ ይሆናሉ። ክርስቲያናዊ ባሕርያትን በማሳየት ሌሎች እንዲይዟቸው በሚፈልጉበት መንገድ እነሱም ሌሎችን ለመያዝ የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 7:12) ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት ስህተት የሚሠሩባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ሰዎችን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመያዝ ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ለሌሎች ምሥራቹን በመስበክ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች ተግባራዊ እርዳታ በመስጠት ጭምር ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች እነሱ በሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ብቻ ዓለም ትለወጣለች ብለው አያስቡም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው፣ ይሖዋ ይህ ሥራ እንደተጠናቀቀ ሲሰማው የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ይመጣል። ታዲያ ይህ ለምድርና በውስጧ ለሚኖሩት ሰዎች ምን ትርጉም ይኖረዋል?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ እየሰበኩ ነው
-
-
“መጨረሻው” የተባለው ምንድን ነው?መጠበቂያ ግንብ—2011 | መጋቢት 1
-
-
“መጨረሻው” የተባለው ምንድን ነው?
“. . . ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14
በአሁኑ ወቅት የዓለም መጨረሻን አስመልክቶ የማይባል ነገር የለም። ከቀልድ መጻሕፍት አንስቶ ሳይንሳዊ ይዘት እስካላቸው ፊልሞችና መጽሔቶች ድረስ ሁሉም በመዓት ቀን ይከሰታል ብለው ስለሚያስቡት መቅሰፍት ብዙ ይናገራሉ። ከሚነገሩት ነገሮች መካከል የኒውክሊየር ጦርነት፣ ተወርዋሪ ኮከቦች፣ አደገኛ የሆኑ ቫይረሶች፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ወይም ከሌሎች ዓለማት የሚመጡ ወራሪዎች የሚያስከትሉት እልቂት ይገኙበታል።
ሃይማኖቶችም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው፤ ብዙዎቹ ‘በመጨረሻው’ ጊዜ በምድር ላይ ያሉት ሕያዋን ነገሮች በሙሉ ድምጥማጣቸው ይጠፋል ብለው ያስተምራሉ። አንድ የሃይማኖት ምሑር ማቴዎስ 24:14ን አስመልክተው እንዲህ የሚል አስፈሪ ሐሳብ ጽፈዋል፦ “ይህ ጥቅስ በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት እጅግ ጠቃሚ ከሆኑት ሐሳቦች መካከል አንዱ ነው። . . . አሁን ባለው ትውልድ ላይ ብዙዎቻችን አሰቃቂነቱን ያልተገነዘብነው አውዳሚ የሆነ ጥፋት ተደቅኖበታል።”
እንዲህ ያለው አመለካከት ይሖዋ አምላክ ‘ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን’ እንዳልሆነ የሚናገረውን ወሳኝ ሐቅ ያላገናዘበ ነው። (ኢሳይያስ 45:18) በመሆኑም ኢየሱስ “መጨረሻው” ሲል ምድር ትጠፋለች አሊያም ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ከምድረ ገጽ ይጠፋል ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን ፍቅራዊ መመሪያዎች ለመከተል አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎች ማለትም ክፉዎች ይጠፋሉ ማለቱ ነበር።
አንድ ምሳሌ እንመልከት። እጅግ ያማረ ቤት አለህ እንበል፤ በዚህ ቤት ውስጥ ሰዎች በነፃ እንዲኖሩበት ፈቅደህላቸዋል። አንዳንዶቹ ነዋሪዎች ከሌሎች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ከመሆኑም በላይ ቤትህንም በጥሩ ሁኔታ ይዘውታል። ሌሎቹ ነዋሪዎች ግን ችግር ይፈጥራሉ፣ እርስ በርስ ይጋጫሉ እንዲሁም ሰላማዊ በሆኑት ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። እነዚህ ዓመፀኞች ንብረትህን ከማበላሸታቸውም በተጨማሪ መጥፎ ድርጊታቸውን ለማስቆም የምታደርገውን ጥረት ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም።
ታዲያ ሁኔታውን ለማስተካከል ምን እርምጃ ትወስዳለህ? ቤትህን ታፈራርሰዋለህ? እንደዚህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ዓመፀኞቹን ነዋሪዎች ከቤትህ አባረህ እነሱ በቤቱ ላይ ያደረሱትን ጉዳት ታስተካክላለህ።
ይሖዋም ቢሆን የሚያደርገው ተመሳሳይ ነገር ነው። መዝሙራዊው በመንፈስ ተገፋፍቶ የሚከተለውን እንዲጽፍ አድርጓል፦ “ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ። ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:9-11
ሐዋርያው ጴጥሮስም ስለዚሁ ጉዳይ ተናግሯል። ጴጥሮስ በመንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከጥንት ጀምሮ ሰማያት እንደነበሩ እንዲሁም ደረቁ ምድር በአምላክ ቃል ከውኃ በላይ ጸንቶ እንደቆመና በውኃ መካከል እንደነበረ [አያስተውሉም]፤ . . . በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በውኃ ተጥለቅልቆ ጠፍቷል።” (2 ጴጥሮስ 3:5, 6) እዚህ ላይ ሐዋርያው የጠቀሰው በኖኅ ጊዜ ስለተከሰተው የጥፋት ውኃ ነው። በዚያን ወቅት ፈሪሃ አምላክ ያልነበራቸው ሰዎች ጥፋት የመጣባቸው ሲሆን ምድር ግን አልጠፋችም። ዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ “ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ [ይሆናል]።”—2 ጴጥሮስ 2:6
ጴጥሮስ አክሎም “አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳት . . . ተጠብቀው ይቆያሉ” በማለት ጽፏል። ይህንን ሐሳብ ብቻ ካየን የተሳሳተ አመለካከት ልንይዝ እንችላለን። ይሁንና ጥቅሱ “ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት” እንደሚልም ልብ በል። ይጠፋሉ የተባለው ምድር ሳትሆን ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ናቸው። ቀጥሎስ? ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና [የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት] አዲስ ምድር [ጻድቅ የሆነ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ] እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።”—2 ጴጥሮስ 3:7, 13
ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች “መጨረሻው” የሚመጣበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ማቴዎስ 24:3-14ን እና 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን በማንበብ መጨረሻው ቅርብ እንደሆነ አንተው ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ።a
አንድ ትንሽ ልጅ እንኳ በቀላሉ ሊረዳው የሚችለውን ማቴዎስ 24:14ን አስመልክቶ ይህን ያህል ግራ መጋባት መፈጠሩ የሚያስገርም አይደለም? ይህ የሆነበት በቂ ምክንያት አለ። ሰይጣን፣ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ውድ እውነቶች እንዳይረዱ አሳውሯቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) በተጨማሪም አምላክ ዓላማውን የሚገልጠው ለትዕቢተኞች ሳይሆን ለትሑታን ነው። ይህንን በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥክላቸው በሕዝብ ፊት አወድስሃለሁ።” (ማቴዎስ 11:25) በእርግጥም የአምላክን መንግሥት ምንነትና ይህ መንግሥት እሱን ለሚደግፉ ሰዎች የሚያመጣቸውን በረከቶች በትክክል ከተገነዘቡ ሰዎች መካከል መሆን እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው!
-