የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 9/1 ገጽ 19-24
  • ሕይወታችሁን ስኬታማ አድርጉት!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሕይወታችሁን ስኬታማ አድርጉት!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክ ሕግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
  • ‘ዕድሜያችንን መቁጠር’
  • በክፉ አድራጊዎች አትቅኑ
  • ባልንጀሮቻችሁን ምረጡ!
  • መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብ ጥቅም
  • የአምላክን መንገድ መከተል ስኬታማ ያደርጋል
  • ብልጽግና እምነትህን ሊፈትነው ይችላል
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኙ ወጣቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • እንደ ሌሎች ወጣቶች እንድደሰት የማይፈቀድልኝ ለምንድን ነው?
    ንቁ!—1996
  • ስኬታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 9/1 ገጽ 19-24

ሕይወታችሁን ስኬታማ አድርጉት!

“ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ . . . የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።”—⁠መዝሙር 1:​1, 3

1. (ሀ) በዓለም ያሉ ብዙ ወጣቶች ስለ ስኬት ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስኬታማ እንደሆነ የሚገልጸው ምን ዓይነቱን ሰው ነው?

ስኬት​—⁠ይህ ቃል ለእናንተ ምን ትርጉም አለው? “ዋነኛው ግቤ የተሳካልኝ ነጋዴ መሆን ነው” ሲል አንድ ወጣት ተናግሯል። አንዲት ወጣት ሴት ደግሞ “ትልቁ ሕልሜ ደስተኛ ቤተሰብ መመሥረት ነው” ብላለች። ሌላዋ ሴት ግን “የእኔ ምኞት ብዙ ክፍሎች ያሉት ትልቅ መኖሪያ ቤትና ጥሩ መኪና ማግኘት ነው . . . ራሴን ማስደሰት እፈልጋለሁ” ብላለች። ችግሩ ግን የእውነተኛ ስኬት መለኪያው ገንዘብ፣ ቤተሰብ ወይም ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ አይደለም። መዝሙር 1:​1-3 እንዲህ ይላል:- “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣ . . . በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ . . . የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።”

2. እውነተኛ ስኬት የሚገኘው የት ነው? ይህንንስ ማግኘት የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ምንድን ነው?

2 እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የትኛውም ሰው ሊሰጠን የማይችለውን እውነተኛ ስኬት እንደምናገኝ ተስፋ ይሰጠናል! ይሁን እንጂ ስለ ገንዘብ ትርፍ መናገሩ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው” በማለት ያስጠነቅቃል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​10) እውነተኛ ስኬት የሚገኘው ይሖዋን መታዘዝን ጨምሮ አምላክን ደስ የሚያሰኙትን ነገሮች በማድረግ ነው። እውነተኛ እርካታና ልባዊ ደስታ ሊያስገኝ የሚችለው ይህ ብቻ ነው! ምናልባት በይሖዋ ሕግ ሥር መሆንና እንዲህ አድርግ እንዲህ አታድርግ መባል ብዙም የሚዋጥ መስሎ አይታያችሁ ይሆናል። ይሁንና ኢየሱስ “በመንፈሳዊ የጐደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:​3 NW) እናንተ ተገነዘባችሁትም አልተገነዘባችሁት በተፈጥሮ ያገኛችሁት መንፈሳዊ ፍላጎት አለ። ይህም በውስጣችሁ የተተከለውን አምላክን የማወቅና ዓላማውን የመረዳት ጥልቅ ፍላጎት ይጨምራል። በመሆኑም እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምትችሉት ይህን ፍላጎታችሁን ካሟላችሁና ‘የይሖዋን ሕግ’ ከተከተላችሁ ብቻ ነው።

የአምላክ ሕግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

3. ይሖዋ ‘መንገዳችንን እንዲመራልን’ በመፍቀዳችን ደስተኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

3 ነቢዩ ኤርምያስ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱን ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ብሏል። (ኤርምያስ 10:​23) ይህ፣ ወጣት ሽማግሌ ሳይል ለሁሉም የሰው ልጅ የሚሠራ ሐቅ ነው። የራሳችንን ጎዳና ለማቅናት ጥበብ፣ ተሞክሮና እውቀት የሚያንሰን መሆናችን ብቻ ሳይሆን እንደዚያ ለማድረግ መብቱም አልተሰጠንም። መጽሐፍ ቅዱስ በራእይ 4:​11 ላይ እንዲህ ይላል:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።” ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን “የሕይወት ምንጭ” እርሱ ነው። (መዝሙር 36:​9) በመሆኑም ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን ከማንም በላይ የሚያውቀው እርሱ ነው። ከዚህ የተነሣ ሕጎችን ያወጣው እኛን ደስታ ለመንፈግ ሳይሆን ራሳችንን እንድንጠቅም ለመርዳት ብሎ ነው። (ኢሳይያስ 48:​17) የአምላክን ሕግጋት ችላ ብትሉ መጨረሻችሁ ውድቀት ይሆናል።

4. ብዙ ወጣቶች ሕይወታቸውን የሚያበላሹት ለምንድን ነው?

4 ለምሳሌ ያህል በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በአደገኛ ዕፆች፣ በሴሰኝነትና በሌሎች መጥፎ ድርጊቶች ሕይወታቸውን የሚያበላሹት ለምን ይሆን ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? መዝሙር 36:​1, 2 እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ኃጢአተኛ በራሱ የሚያስት ነገርን ይናገራል፣ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዓይኖቹ ፊት የለም። በአንደበቱ ሸንግሎአልና፤ ኃጢአቱ ባገኘችው ጊዜ ይጠላታል።” ብዙ ወጣቶች ‘ለአምላክ’ ጤናማ ‘ፍርሃት’ ስለ ሌላቸው አደገኛ አካሄድ መከተል ምንም የሚያስከትለው መዘዝ የለም ብለው በማሰብ ራሳቸውን ያታልላሉ። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ የሚከተለውን የማይሻር መሠረታዊ ሥርዓት ለመጋፈጥ ይገደዳሉ:- “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።”​—⁠ገላትያ 6:​7, 8

‘ዕድሜያችንን መቁጠር’

5, 6. (ሀ) ወጣቶች ‘ዕድሜያቸውን መቁጠር’ ያለባቸው ለምንድን ነው? ይህስ ምን ማለት ነው? (ለ) ‘ታላቁ ፈጣሪያችንን ማሰብ’ ምን ማለት ነው?

5 ሕይወታችሁን ስኬታማ በማድረግ ‘የዘላለም ሕይወት ማጨድ’ የምትችሉት እንዴት ነው? ሙሴ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ዕድሜአችን ሰባ ዓመት ነው፤ ቢበዛም ሰማኒያ ዓመት ነው፤ . . . ዕድሜአችን በቶሎ ያልቃል፤ እኛም እናልፋለን።” (መዝሙር 90:​10 የ1980 ትርጉም) ስለ ሞት የምታስቡት ከስንት አንዴ ይሆናል። እንዲያውም የአንዳንዶቹ ወጣቶች ሁኔታ ሲታይ ሊሞቱ እንደሚችሉ እንኳ የሚያስቡ አይመስልም። ይሁን እንጂ ሙሴ ሕይወት አጭር የመሆኑን መራራ እውነታ ፊታችን ላይ ድቅን አድርጎ ያሳየናል። ሌላው ቀርቶ 70 ወይም 80 ዓመት እንኳ ለመኖራችን ዋስትና የለንም። “ጊዜና አጋጣሚ” ወጣትና ጤናማ የሆኑትን እንኳ ሳይቀር ያለ ዕድሜያቸው እንዲቀጩ ሊያደርግ ይችላል። (መክብብ 9:​11 NW) ታዲያ አሁን ያላችሁን ውድ ሕይወት የምትጠቀሙበት እንዴት ነው? ሙሴ “ጥበብ ያለው ልብ እናገኝ ዘንድ ዕድሜያችንን እንዴት መቁጠር እንደምንችል አስተምረን” ሲል ጸልዮአል።​—⁠መዝሙር 90:​12 NW

6 ዕድሜያችሁን መቁጠር ማለት ምን ማለት ነው? ነጋ ጠባ ምን ያህል ዓመት እኖር ይሆን እያላችሁ መጨነቅ ይኖርባችኋል ማለት አይደለም። ሙሴ ሕዝቡ የቀረውን የሕይወት ዘመናቸውን ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይሖዋ ያስተምራቸው ዘንድ መለመኑ ነበር። እናንተስ እያንዳንዷን ዕለት ለይሖዋ ውዳሴ ለማምጣት እንደምታገለግል ውድ ነገር በመመልከት የሕይወታችሁን ቀናት እየቆጠራችሁ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ ለወጣቶች እንዲህ የሚል ማበረታቻ ይሰጣል:- “ሕፃንነትና ጉብዝና ከንቱዎች ናቸውና ከልብህ ኀዘንን አርቅ፣ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ። . . . በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ።” (መክብብ 11:​10–12:​1) ፈጣሪያችንን ማሰብ ማለት አምላክ እንዳለ ከማስታወስ የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። ወንጀለኛው ኢየሱስን “በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ብሎ ሲማጸን ስሙን እንዲያስታውስለት ብቻ መጠየቁ አልነበረም። አንድ ነገር እንዲያደርግለት ይኸውም ከሞት እንዲያስነሳው መለመኑ ነበር! (ሉቃስ 23:​42፤ ከዘፍጥረት 40:​14, 23፤ ኢዮብ 14:​13 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም ይሖዋን ማሰብ ማለት እርሱን የሚያስደስተውን ነገር ማድረግን ይጠይቃል። እናንተም እንዲሁ ይሖዋን እያሰባችሁት ነው ሊባል ይቻላልን?

በክፉ አድራጊዎች አትቅኑ

7. አንዳንድ ወጣቶች ፈጣሪያቸውን ላለማሰብ የሚመርጡት ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

7 ብዙ ወጣቶች የይሖዋ ምሥክር መሆን መታሰር ማለት እንደሆነ ስለተሰማቸው ይሖዋን ላለማሰብ መርጠዋል። አንድ በስፔይን የሚገኝ ወንድም በአሥራዎቹ እድሜ ላይ እያለ ምን ይሰማው እንደነበር በማስታወስ እንዲህ ብሏል:- “እውነት አስቸጋሪና ድርቅ ያለ ነገር እንደሆነ ስለተሰማኝ ወደ ዓለም ተሳብኩ። እውነት ማለት ለእኔ መቀመጥ፣ ማጥናት፣ ስብሰባ መሄድ፣ ክራቫት ማሰር ብቻ ነበር። እነዚህ ደግሞ እኔ የምወዳቸው ነገሮች አልነበሩም።” እናንተስ አምላክን በማገልገላችሁ አንዳንድ ጊዜ የቀረባችሁ ነገር እንዳለ ሆኖ ይሰማችኋል? ምናልባት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ ተመሳሳይ ስሜት አድሮበት እንደነበር ማወቃችሁ ያስገርማችሁ ይሆናል። እባካችሁ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ገልጣችሁ መዝሙር 73​ን አንብቡ።

8. አሳፍ ‘ጉራቸውን በሚነዙ’ ሰዎች የቀናው ለምን ነበር?

8 እስቲ ይህንን መዝሙር በጥቂቱ እንመርምር። ቁጥር 2 እና 3 እንዲህ ይላል:- “እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፣ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ። የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች [“ጉራቸውን በሚነዙ ሰዎች፣” NW] ቀንቼ ነበርና።” መዝሙሩ ከመጀመሩ በፊት ካለው መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው ይህን መዝሙር የጻፈው አሳፍ ነው። አሳፍ ሌዋዊ ሙዚቀኛ ሲሆን በንጉሥ ዳዊት ዘመን የኖረ ሰው ነበር። (1 ዜና መዋዕል 25:​1, 2፤ 2 ዜና መዋዕል 29:​30) በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ የማገልገል ግሩም መብት የነበረው ቢሆንም ስለ ዓመፅ ሥራቸው በመኩራራት ይናገሩ በነበሩ ክፉ ሰዎች ‘ቀና።’ ችግር ያለባቸው አይመስሉም፤ አልፎ ተርፎም ሰላምና መረጋጋት ያላቸው ይመስላሉ። እንዲያውም ያገኙት ስኬት ‘ከልባቸው ምኞት እንኳ ያለፈ’ ይመስል ነበር። (ቁጥር 5, 7) ስለ ብዝበዛቸው ‘ከፍ ከፍ አድርገው’ ማለትም በማናለብኝነት ስሜት ይናገሩ ነበር። (ቁጥር 8) በሰማይም ሆነ በምድር ላለ ለማንኛውም አካል ግድ የማይሰጣቸው ሰዎች ከመሆናቸው የተነሣ ‘አፋቸውን በሰማይ አኑረዋል፤ አንደበታቸውም በምድር ውስጥ ተመላልሷል።’​—⁠ቁጥር 9

9. ዛሬ አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች እንደ አሳፍ ሊሰማቸው የሚችለው እንዴት ነው?

9 ምናልባት በትምህርት ቤታችሁ ስላሉት እኩዮቻችሁም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻል ይሆናል። ስለ ፈጸሙት የጾታ ብልግና፣ ስላሳለፉት መረን የለቀቀ ጭፈራ እንዲሁም በአልኮልና በዕፅ ሲናውዙ መሰንበታቸውን እንደ ጀብድ በመቁጠር ሲያወሩ ትሰሟቸው ይሆናል። እንደ ተድላ የሚቆጥሩትን የእነርሱን አኗኗር እናንተ ከምትመላለሱበት ጠባብ የክርስትና ጎዳና ጋር ስታወዳድሩ አንዳንድ ጊዜ ‘ጉራቸውን በሚነዙ ሰዎች’ ቅናት ሊያድርባችሁ ይችላል። (ማቴዎስ 7:​13, 14) አሳፍ ራሱ እንደሚከተለው ሲል ሐሳቡን ገልጿል:- “በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፣ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ። ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፣ መሰደቤም በማለዳ ነው።” (ቁጥር 13, 14) አዎን፣ አምላክን ማገልገሉና የጽድቅ አኗኗር መከተሉ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው በማለት መጠየቅ ጀመረ።

10, 11. (ሀ) አሳፍ አሳቡን እንዲለውጥ ያደረገው ምን ነበር? (ለ) ክፉ አድራጊዎች ‘በድጥ ስፍራ’ እንዳሉ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

10 የሚያስደስተው አሳፍ በዚህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለረጅም ጊዜ አልቆየም። ብዙም ሳይቆይ፣ ክፉዎች ያገኙት መስሎ የሚታየው ሰላም የታይታ ብቻ እንደሆነና እንደማይዘልቅ ተገነዘበ! እንዲህ ብሏል:- “በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፣ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ።” (ቁጥር 18, 19) ብዙዎቹ እኩዮቻችሁም እንዲሁ ‘በድጥ ስፍራ ላይ’ ናቸው። ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ አምላካዊ ያልሆነው አኗኗራቸው ላልተፈለገ እርግዝና፣ በጾታ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች አልፎ ተርፎም ለእሥር ወይም ለሞት ይዳርጋቸው ይሆናል! ከሁሉ የከፋው ደግሞ ከአምላክ መራቃቸው ነው።​—⁠ያዕቆብ 4:​4

11 አንዲት በስፔይን የምትኖር ወጣት ምሥክር ይህን ሐቅ በራሷ ላይ ከደረሰው ሁኔታ ተምራለች። ወጣት በነበረችበት ጊዜ አምላካዊ አክብሮት ከሌላቸው ወጣቶች ጋር ጓደኝነት ይዛ ሁለት ዓይነት ኑሮ መምራት ጀምራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ከእነዚህ ወጣቶች መካከል የዕፅ ሱሰኛ ከሆነው ከአንዱ ጋር ፍቅር ይይዛታል። ራሷ ዕፅ የማትወስድ ብትሆንም ለእርሱ ግን ትገዛለት ነበር። “መርፌውን በመውጋት ሳይቀር እረዳው ነበር” ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች። ደስ የሚለው ግን ይህች እህት ወደ አእምሮዋ ተመልሳ መንፈሳዊ ጤንነቷ ተስተካከለ። ይሁን እንጂ ዕፅ ይወስድ የነበረው የወንድ ጓደኛዋ ከጊዜ በኋላ በኤድስ እንደሞተ ስትሰማ እንዴት እንደደነገጠች አስቡት። አዎን፣ ልክ መዝሙራዊው እንዳለው አምላካዊውን ጎዳና የማይከተሉ ሰዎች ‘በድጥ ስፍራ ላይ እንዳሉ’ ናቸው። አንዳንዶች ልቅ በሆነው አኗኗራቸው ምክንያት ሕይወታቸው በድንገት ሊቀጭ ይችላል። የቀሩት ደግሞ አኗኗራቸውን እስካልለወጡ ድረስ በቅርቡ ‘ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል የሚገለጥበትና እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን የሚበቀልበት ጊዜ’ ይጠብቃቸዋል።​—⁠2 ተሰሎንቄ 1:​7, 8

12. በጃፓን የሚኖር አንድ ወጣት በክፉዎች መቅናት ከንቱ እንደሆነ የተገነዘበው እንዴት ነው?

12 እንግዲያውስ ‘አምላክን በማያውቁ’ ሰዎች መቅናት ምንኛ ሞኝነት ነው! እንዲያውም ሊቀናባቸው የሚገባው ይሖዋን የሚያውቁና ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎች ናቸው። በጃፓን የሚኖር አንድ ወንድም ይህን ጉዳይ ተገንዝቧል። ወጣት በነበረበት ጊዜ እርሱም “ተጨማሪ ነፃነት ማግኘት” ፈልጎ ነበር። ስለ ጉዳዩ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ነገር እንደቀረብኝ ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር። ግን ደግሞ ሕይወቴን ያለ እውነት መምራት ምን ሊመስል እንደሚችል አሰብኩ። ሰባ ወይም ሰማንያ ዓመት ብቻ ኖሬ ስሞት ታየኝ። ይሖዋ ግን ያዘጋጀልኝ የዘላለም ሕይወት ነው! ይህን ነገር መገንዘቤ ያለኝን ነገር እንዳደንቅ ረድቶኛል።” ያም ሆኖ ግን የአምላክን ሕግ በማይከተሉ ሰዎች ተከብበው እየኖሩ ታማኝ መሆን ቀላል አይደለም። እነዚያን ተጽእኖዎች ለመቋቋም ልታደርጓቸው የምትችሏቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ባልንጀሮቻችሁን ምረጡ!

13, 14. ባልንጀርነትን በሚመለከት መራጭ መሆን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 እስቲ ስኬታማ ስለሆነ ሰው በመዝሙር 1:​1-3 ላይ የተሰጠውን መግለጫ በድጋሚ እንመልከት:- “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፣ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋንም በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።”

14 በመጀመሪያ ደረጃ ባልንጀርነታችሁ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ልብ በሉ። ምሳሌ 13:​20 “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” ይላል። ይህ ማለት ግን የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑትን ወጣቶች ፊት እንነሳቸዋለን ወይም እናንጓጥጣቸዋለን ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን እንድንወድና ‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንድንኖር’ አጥብቆ ያሳስበናል። (ሮሜ 12:​18፤ ማቴዎስ 22:​39 NW) ይሁን እንጂ ከእነርሱ ጋር በጣም የምትቀራረቡ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በማይከተሉ ሰዎች ‘ምክር እየሄዳችሁ’ ሊሆን ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብ ጥቅም

15. ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

15 መዝሙራዊው እንዳስተዋለው ስኬታማ የሆነ ሰው የአምላክን ቃል ‘ቀንና ሌሊት ድምፁን እያሰማ በማንበቡ ደስ’ ይለዋል። (መዝሙር 1:​1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ እንደዋዛ የሚነበብ መጽሐፍ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። አንዳንድ ‘ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑ ነገሮች’ አሉት። (2 ጴጥሮስ 3:​16) ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አሰልቺ ሥራ ሊሆንብን አይገባም። ‘ተንኮል ለሌለበት የአምላክ ቃል ወተት ምኞት’ እንዲያድርብን ማድረግ ይቻላል። (1 ጴጥሮስ 2:​2) በየዕለቱ ትንሽ ትንሽ ለማንበብ ሞክሩ። ያልገቧችሁ ነጥቦች ካሉ ምርምር አድርጉ። ከዚያ በኋላ ስላነበባችሁት ነገር አስቡ። (መዝሙር 77:​11, 12) ሐሳባችሁን የማሰባሰብ ችግር ካለባችሁ ‘ድምፃችሁን አውጥታችሁ’ አንብቡ። ቀስ በቀስ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ያላችሁ ፍቅር ያድጋል። በብራዚል የምትገኝ አንዲት እህት እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ሁልጊዜ ይሖዋ ሩቅ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ይሁን እንጂ ከተወሰኑ ወራት ወዲህ የግል ጥናቴንና የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን አጠናክሬአለሁ። አሁን ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና እንደተጠናከረ ይሰማኛል። አሁን እርሱ ይበልጥ እውን ሆኖልኛል።”

16. ከጉባኤ ስብሰባዎች ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

16 በጉባኤ ስብሰባዎችም ላይ መገኘት ለመንፈሳዊ እድገታችሁ ወሳኝ የሆነ ነገር ነው። ‘እንዴት እንደምትሰሙ ከተጠነቀቃችሁ’ ብዙ ማበረታቻ ማግኘት ትችላላችሁ። (ሉቃስ 8:​18) አንዳንድ ጊዜ ስብሰባዎቹ ማራኪ እንዳልሆኑ ይሰማችኋል? እንደዚያ ከሆነ ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ:- ‘ስብሰባዎች አስደሳች እንዲሆኑልኝ እኔ በበኩሌ ምን ያደረግሁት ነገር አለ? በትኩረት እከታተላለሁ? እዘጋጃለሁ? ሐሳብ እሰጣለሁ?’ መጽሐፍ ቅዱስም ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንነቃቃ ዘንድ እርስ በርሳችን እንድንተያይና እርስ በርስ እንድንበረታታ’ ይነግረናል። (ዕብራውያን 10:​24, 25) ይህን ለማድረግ ደግሞ ተሳትፎ ማድረግ አለባችሁ! እርግጥ ለመሳተፍም አስቀድማችሁ ማጥናት ይኖርባችኋል። አንዲት ወጣት እህት “ተዘጋጅታችሁ የምትሄዱ ከሆነ በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ቀላል ይሆንላችኋል” ስትል ተናግራለች።

የአምላክን መንገድ መከተል ስኬታማ ያደርጋል

17. በትጋት መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብብ ሰው ‘በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለ ዛፍ’ የሚሆነው እንዴት ነው?

17 መዝሙራዊው በመቀጠል ስኬታማ የሆነን ሰው ‘በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለ ዛፍ’ አድርጎ ገልጾታል። የውኃ ፈሳሽ የተባለው ዛፎችን ወይም እርሻዎችን ለማጠጣት የሚቆፈረውን የመስኖ ጉድጓድ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። (ኢሳይያስ 44:​4 NW) በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያለማቋረጥ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከሚሰጥ ምንጭ ጋር የመገናኘት ያህል ነው። (ኤርምያስ 17:​8) ፈተናዎችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሟችሁ ለመቋቋም የሚያስፈልጋችሁን ብርታት በየዕለቱ ታገኛላችሁ። የይሖዋን አመለካከት መማራችሁ የጥበብ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ ይሰጣችኋል።

18. አንድ ወጣት ይሖዋን በማገልገል ስኬት እንዲያገኝ የሚረዱት ነገሮች ምንድን ናቸው?

18 አንዳንድ ጊዜ ይሖዋን ማገልገል አስቸጋሪ መስሎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ አድርጋችሁ በፍጹም ማሰብ የለባችሁም። (ዘዳግም 30:​11) ዋነኛ ግባችሁ የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት ከሆነ የምታደርጉት ነገር ሁሉ የኋላ ኋላ ‘እንደሚሳካላችሁ’ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣችኋል! (ምሳሌ 27:​11) ብቻችሁን እንዳልሆናችሁ ደግሞ አስታውሱ። የይሖዋና የኢየሱስ ክርስቶስ ድጋፍ አለላችሁ። (ማቴዎስ 28:​20፤ ዕብራውያን 13:​5) የሚገጥሟችሁን ተጽእኖዎች ስለሚያውቁ ፈጽሞ አይተዉአችሁም። (መዝሙር 55:​22) በተጨማሪም ‘መላው የወንድማማች ማኅበር’ አለላችሁ። ወላጆቻችሁም አምላክን የሚፈሩ ከሆኑ እነርሱም ይደግፏችኋል። (1 ጴጥሮስ 2:​17 NW) የእናንተ ቁርጠኝነትና ጥረት ታክሎበት የምታገኙት እንዲህ ያለው ድጋፍ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ለዘላለምም ስኬታማ ሕይወት እንድትኖሩ ያስችላችኋል!

ለክለሳ የቀረቡ ጥያቄዎች

◻ እውነተኛ ስኬት ምንድን ነው?

◻ ይሖዋ መንገዳችንን እንዲመራልን መፍቀድ ያለብን ለምንድን ነው?

◻ ወጣቶች ‘ዕድሜያቸውን መቁጠር’ የሚችሉት እንዴት ነው?

◻ በክፉዎች መቅናት ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ወጣቶች ስኬታማ ሕይወት እንዲመሩ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ወጣቶች ‘ለአምላክ’ ጤናማ ‘ፍርሃት’ ስለሌላቸው ራሳቸውን በሚጎዳ ልማድ ይጠመዳሉ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙውን ጊዜ ወጣቶች የሚያደርጉት ነገር የሚያስከትለው መዘዝ እንዳለ ይዘነጋሉ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ፍቅር ኮትኩቱ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተሳትፎ የምታደርጉ ከሆነ በስብሰባዎች መገኘት ይበልጥ አስደሳች ይሆንላችኋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ