‘ለሁሉ ጊዜ አለው’
“ለሁሉ ዘመን አለው፣ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1
1. ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ምን ችግር አለባቸው? ይህስ በአንዳንድ ሁኔታዎች ወደ ምን መርቷል?
ሰዎች ብዙውን ጊዜ “ቶሎ ባደረግሁት ኖሮ” ይላሉ። ወይም አንዳንድ ጊዜ ስላደረጉት ነገር መለስ ብለው ያስቡና “መቆየት ነበረብኝ” ይላሉ። እነዚህን የመሳሰሉት ሁኔታዎች ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች አንዳንድ ነገሮች የሚከናወኑበትን ትክክለኛ ጊዜ ለመወሰን እንደሚቸገሩ የሚያሳዩ ናቸው። ይህ የአቅም ገደብ እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት አሻክሯል። ብዙዎችን ለብስጭትና ለተስፋ መቁረጥ ዳርጓል። ከሁሉ የከፋው ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያላቸው እምነት እንዲመናመን ማድረጉ ነው።
2, 3. (ሀ) ይሖዋ የወሰነውን ጊዜ መጠበቁ ጥበብ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ፍጻሜ በተመለከተ ምን ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
2 ይሖዋ ሰዎች የሌላቸው ማስተዋልና ጥበብ ስላለው ከፈለገ የእያንዳንዱ ድርጊት ውጤት ምን እንደሚሆን አስቀድሞ ማወቅ ይችላል። “በመጀመሪያ መጨረሻውን” ሊያውቅ ይችላል። (ኢሳይያስ 46:10) በመሆኑም ማድረግ የፈለገውን ነገር ለማድረግ የሚያስችለውን አመቺ የሆነ ጊዜ ያለ ምንም ስህተት ሊመርጥ ይችላል። ጊዜን በተመለከተ ፍጽምና በጎደለው በራሳችን ማስተዋል ከመመራት ይልቅ ይሖዋ የወሰነውን ጊዜ መጠበቁ ጥበብ ነው!
3 ለምሳሌ ያህል የጎለመሱ ክርስቲያኖች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሚፈጸሙበትን ይሖዋ የወሰነውን ጊዜ በታማኝነት ይጠባበቃሉ። በሰቆቃወ ኤርምያስ 3:26 ላይ የሚገኘውን “ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት በአእምሯቸው በመያዝ በአገልግሎቱ ተጠምደው ይጠብቃሉ። (ከዕንባቆም 3:16 ጋር አወዳድር።) እንዲሁም አስቀድሞ የተነገረለት ይሖዋ የሚወስደው የፍርድ እርምጃ ‘ቢዘገይም በእርግጥ እንደሚመጣና እንደማይዘገይ’ ጽኑ እምነት አላቸው።—ዕንባቆም 2:3
4. አሞጽ 3:7ና ማቴዎስ 24:45 ይሖዋን በትዕግሥት እንድንጠባበቅ ሊረዱን የሚገባው እንዴት ነው?
4 በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ወይም በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ላይ የተሰጡ ማብራሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ለማስተዋል አለመቻላችን ትዕግሥት እንድናጣ ምክንያት ይሆነናልን? ይሖዋ ነገሮችን ግልጽ የሚያደርግበትን ጊዜ መጠባበቁ የጥበብ እርምጃ ነው። “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም።” (አሞጽ 3:7) እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! ይሁንና ይሖዋ ምሥጢራዊ ጉዳዮቹን የሚገልጠው እሱ የተሻለ ነው በሚለው ጊዜ እንደሆነ መገንዘብ አለብን። ለዚህ ዓላማ ሲል አምላክ ለሕዝቦቹ “[መንፈሳዊ] ምግባቸውን በጊዜው [የሚሰጣቸው]” “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾሟል። (ማቴዎስ 24:45 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ስለዚህ ስለ አንዳንድ ጉዳዮች የተሟላ ማብራሪያ ባለማግኘታችን ምክንያት ከልክ በላይ መጨነቅ ወይም መረበሽ የለብንም። ከዚያ ይልቅ ይሖዋን በትዕግሥት ከተጠባበቅን በታማኝና ልባም ባሪያ በኩል አስፈላጊው ነገር “በጊዜው” እንደሚቀርብልን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
5. መክብብ 3:1-8ን መመርመሩ ለምን ይጠቅማል?
5 ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የራሳቸው የሆነ ጊዜ ያላቸው 28 የተለያዩ ነገሮችን ጠቅሷል። (መክብብ 3:1-8) ሰሎሞን የተናገራቸውን ነገሮች ትርጉምና አንድምታ ማስተዋላችን የተወሰኑ ድርጊቶችን የምናከናውንበት ጊዜ በአምላክ አመለካከት ትክክለኛ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለመለየት ይረዳናል። (ዕብራውያን 5:14) ይህ ደግሞ በተራው የሕይወታችንን አቅጣጫ ለማስተካከል ይረዳናል።
“ለማልቀስ ጊዜ አለው፣ ለመሳቅም ጊዜ አለው”
6, 7. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ሁኔታዎች የሚያሳስቧቸው ሰዎች ‘እንዲያለቅሱ’ የሚያደርጓቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ዓለም ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታ ለመሸፋፈን የሚሞክረው እንዴት ነው?
6 ‘ለማልቀስም ሆነ ለመሳቅ ጊዜ’ ቢኖረውም ከማልቀስ ይልቅ መሳቅን የማይመርጥ ማን ነው? (መክብብ 3:4) የሚያሳዝነው ነገር በምንኖርበት ዓለም ለማልቀስ ምክንያት የሚሆኑት ነገሮች ይበዛሉ። መገናኛ ብዙሃንን ያጨናነቁት አሰቃቂ ዘገባዎች ናቸው። ወጣቶች አብረዋቸው የሚማሩትን ልጆች ትምህርት ቤት ውስጥ በጥይት ደብድበው ስለ መግደላቸው፣ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ግፍ ስለ መፈጸማቸው፣ ንጹሐን ሰዎች በአሸባሪዎች ስለ መገደላቸው ወይም ስለደረሰባቸው የአካል ጉዳት እንዲሁም ተፈጥሯዊ ተብለው የሚጠሩ አደጋዎች በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ስለማድረሳቸው ስንሰማ እንዘገነናለን። በረሃብ የጠወለጉና ዓይናቸው የሰረጎደ ልጆች እንዲሁም ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ስደተኞች በቴሌቪዥን ላይ ትኩረታችንን የሚስቡ ነገሮች ናቸው። ቀደም ሲል እምብዛም የማይታወቁ እንደ ዘር ማጥፋት፣ ኤድስ፣ ባዮሎጂያዊ የጦር መሣሪያና ኤል ኒኞ የመሳሰሉ መጠሪያዎች በተለያየ መንገድ በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ ጭንቀት የሚፈጥሩ ነገሮች ሆነዋል።
7 በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም አሳዛኝ በሆኑና ቅስምን በሚሰብሩ ነገሮች የተሞላ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ያም ሆኖ ግን የጉዳዩን አሳሳቢነት ይቀንሰው ይመስል የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ፍሬከርስኪ፣ ለዛ የለሽና ብዙውን ጊዜም ሥነ ምግባር የጎደላቸው እንዲሁም ዓመፅ የተሞሉ ነገሮችን ያቀርብልናል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው ስቃይ ግዴለሽ ወደመሆን ሊመሩን ይችላሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው መዝናኛ የሚፈጥረው የግዴለሽነት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ከንቱ ሣቅ ከእውነተኛው ደስታ ጋር ሊምታታ አይገባም። የሰይጣን ዓለም የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነውን ደስታ ሊሰጠን ፈጽሞ አይችልም።—ገላትያ 5:22, 23፤ ኤፌሶን 5:3, 4
8. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለማልቀስ ነው ወይስ ለመሳቅ? አብራራ።
8 ዓለም ያለበትን አሳዛኝ ሁኔታ መገንዘባችን ያለንበት ጊዜ ለሚያስቁ ነገሮች ከሁሉ የላቀ ግምት የምንሰጥበት ጊዜ አለመሆኑን ለማስተዋል ያስችለናል። ያለንበት ጊዜ ለመዝናናትና ለመጫወት ስንል ብቻ የምንኖርበት ወይም ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ይልቅ “ሳቅና ጨዋታ” ቅድሚያውን እንዲወስድ የምናደርግበት ጊዜ አይደለም። (ከመክብብ 7:2-4 ጋር አወዳድር።) ሐዋርያው ጳውሎስ “በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ” ብሏል። ለምን? ምክንያቱም “የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነው።” (1 ቆሮንቶስ 7:31) እውነተኛ ክርስቲያኖች በየዕለቱ የሚመላለሱት የጊዜያችንን አሳሳቢነት ሙሉ በሙሉ መገንዘባቸውን በሚያሳይ መንገድ ነው።—ፊልጵስዩስ 4:8
እያለቀሱም ከልብ ደስተኛ መሆን!
9. ከጥፋት ውኃ በፊት በነበሩት ጊዜያት ምን አሳዛኝ ሁኔታ ተከስቶ ነበር? በዛሬው ጊዜ ለምንገኘውስ ይህ ምን ትርጉም አለው?
9 በዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ ጊዜ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ሕይወትን በቁም ነገር መመልከት ተስኗቸው ነበር። “የሰው ክፋት በምድር ላይ [በመብዛቱ]” ከማዘን ይልቅ ‘ምድር በግፍ መሞላቷን’ አቅልለው በመመልከት የዕለት ተለት ተግባራቸውን ማከናወናቸውን ቀጠሉ። (ዘፍጥረት 6:5, 11) ኢየሱስ ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ በመጥቀስ በጊዜያችን ያሉ ሰዎችም ተመሳሳይ የሆነ አመለካከት እንደሚኖራቸው ተንብዮአል። እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።”—ማቴዎስ 24:38, 39
10. በሐጌ ዘመን ይኖሩ የነበሩ እስራኤላውያን ይሖዋ ለቀጠረው ጊዜ አድናቆት እንደሌላቸው ያሳዩት እንዴት ነበር?
10 የጥፋት ውኃው ከደረሰ ከ1,850 ዓመታት በኋላ በሐጌ ዘመን ብዙ እስራኤላውያን ተመሳሳይ በሆነ መንገድ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በቁም ነገር መመልከት ተስኗቸው ነበር። የግል ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት በሚያደርጉት ሩጫ በመጠመዳቸው ለይሖዋ ዓላማ ቅድሚያ መስጠት በሚያስፈልግበት ጊዜ ውስጥ የሚኖሩ መሆኑን ማስተዋል ተስኗቸው ነበር። እንዲህ እናነባለን:- “ይህ ሕዝብ:- ዘመኑ አልደረሰም፣ የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ጊዜ አልደረሰም ይላል ብሎ ተናገረ። የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ:- በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ።”—ሐጌ 1:1-5
11. ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቃችን ተገቢ ነው?
11 በዛሬው ጊዜ የምንገኝ የይሖዋ ምሥክሮችም በሐጌ ዘመን ይኖሩ እንደነበሩት እስራኤላውያን በይሖዋ ፊት የተሰጡን ኃላፊነቶችና መብቶች ያሉን በመሆኑ ልባችንን በመንገዳችን ላይ ማድረጋችንና ይህንንም በቁም ነገር መመልከታችን ተገቢ ነው። በዓለም በሚከናወኑ ሁኔታዎችና እነዚህም በአምላክ ስም ላይ በሚያመጡት ነቀፋ ምክንያት ‘እናለቅሳለንን?’ ሰዎች የአምላክን መኖር ሲክዱና የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ያለ ምንም ኃፍረት ቸል ሲሉ እናዝናለንን? ሕዝቅኤል ከ2,500 ዓመታት በፊት በተመለከተው ራእይ ላይ ከሚገኙ ምልክት የተደረገባቸው ግለሰቦች ጋር የሚመሳሰል ነገር እናደርጋለንን? ስለ እነሱ እንዲህ እናነባለን:- “እግዚአብሔርም:- [የጸሐፊ ቀለም ቀንድ ለያዘው ሰው] በከተማይቱም በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፣ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኩሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው።”—ሕዝቅኤል 9:4
12. ሕዝቅኤል 9:5, 6 በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ሰዎች ምን ትርጉም አለው?
12 አጥፊውን መሣሪያ ለያዙት ስድስት ሰዎች የተሰጠውን ትእዛዝ በምናነብበት ጊዜ ዘገባው ለጊዜያችን ያዘለው ትርጉም ግልጽ ይሆንልናል:- “በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፤ ዓይናችሁ አይራራ አትዘኑም፤ ሽማግሌውንና ጎበዙን ቆንጆይቱንም ሕፃናቶቹንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፤ በመቅደሴም ጀምሩ።” (ሕዝቅኤል 9:5, 6) በፍጥነት በመቅረብ ላይ ያለውን ታላቅ መከራ በሕይወት ማለፋችን የተመካው ያለንበት ዘመን የምናዝንበት ጊዜ መሆኑን በመገንዘባችን ላይ ነው።
13, 14. (ሀ) ኢየሱስ ደስተኛ ብሎ የገለጻቸው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? (ለ) ይህ መግለጫ ለይሖዋ ምሥክሮች ተስማሚ ነው ብለህ ለምን እንደምታስብ አብራራ።
13 እርግጥ የይሖዋ አገልጋዮች አሳዛኝ በሆኑት የዓለም ሁኔታዎች ምክንያት ‘ማልቀሳቸው’ ደስታቸውን አይነጥቃቸውም። እንዲያውም ሁኔታው ተቃራኒ ነው! በምድር ላይ ከሚገኙ ሰዎች ይበልጥ እጅግ ደስተኞች የሆኑት ሕዝቦች እነሱ ናቸው። ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ ሲናገር ለደስታ ቁልፍ የሆነውን ነገር ገልጿል:- “በመንፈስ ድሆች የሆኑ . . .፣ የሚያዝኑ . . .፣ የዋሆች . . .፣ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ . . .፣ የሚምሩ . . .፣ ልበ ንጹሖች . . .፣ የሚያስተራርቁ . . .፣ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው።” (ማቴዎስ 5:3-10) ይህ መግለጫ ከማንኛውም ሃይማኖታዊ ድርጅት ይልቅ በጥቅሉ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚሠራ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።
14 በተለይ እውነተኛው አምልኮ በ1919 መልሶ ከተቋቋመ ወዲህ ደስተኛ የሆኑት የይሖዋ ሕዝቦች ‘የሚስቁበት’ ምክንያት አላቸው። በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከባቢሎን ከተመለሱት እስራኤላውያን ጋር የሚመሳሰል አስደሳች ተሞክሮ አጋጥሟቸዋል:- “እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፣ እጅግ ደስተኞች ሆንን። በዚያን ጊዜ አፋችን ደስታን፣ አንደበታችንም ሐሤትን ሞላ፤ . . . እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገልን፣ ደስም አለን።” (መዝሙር 126:1-3) ይሁንና ለመሳቅ ምክንያት የሚሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች ቢኖሯቸውም የይሖዋ ምሥክሮች ጥበበኞች በመሆን የጊዜውን አሳሳቢነት በፍጹም አይዘነጉም። አዲሱ ዓለም እውን በሚሆንበትና የምድር ወራሾች ‘እውነተኛውን ሕይወት በሚጨብጡበት’ ጊዜ ለቅሶ ለዘላለም በሣቅ የሚተካበት ጊዜ ይመጣል።—1 ጢሞቴዎስ 6:19፤ ራእይ 21:3, 4
“ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፣ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው”
15. ክርስቲያኖች ለጓደኝነት ስለሚመርጡት ሰው ጥንቃቄ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
15 ክርስቲያኖች ለጓደኝነት ስለሚመርጡት ሰው ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ያስታውሳሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) እንዲሁም ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” ብሏል።—ምሳሌ 13:20
16, 17. የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ጓደኝነት፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ ስለ መጫወትና ስለ ጋብቻ ምን አመለካከት አላቸው? ለምንስ?
16 የይሖዋ አገልጋዮች ለጓደኝነት የሚመርጡት ለይሖዋና ለጽድቅ ሥርዓቶቹ የእነሱን የመሰለ ፍቅር ያላቸውን ግለሰቦች ነው። ከወዳጆቻቸው ጋር አብሮ መሆንን የሚያደንቁትና የሚያስደስታቸው ቢሆንም ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወትን በተመለከተ በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ አገሮች ሰፍኖ ከሚታየው ልል የሆነ አመለካከት በጥበብ ይርቃሉ። ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወትን ምንም ጉዳት የማያስከትል ጨዋታ አድርገው ከመመልከት ይልቅ በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ነፃ የሆነ ሰው በአካል፣ በአእምሮና በመንፈሳዊ ዝግጁ በሚሆንበት ጊዜ ዘላቂ ወደ ሆነ የጋብቻ ዝምድና ለመግባት የሚወስደው ከባድ እርምጃ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።—1 ቆሮንቶስ 7:36
17 አንዳንዶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ ስለ መጫወትና ስለ ጋብቻ እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዝ ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች በጓደኛ ምርጫቸውም ሆነ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ ለመጫወትና ጋብቻ ለመመሥረት በሚያደርጉት ውሳኔ ላይ የእኩዮች ተጽእኖ እንዲያሸንፋቸው አይፈቅዱም። ‘ጥበብ በሥራዋ እንደምትጸድቅ’ ያውቃሉ። (ማቴዎስ 11:19) ሁልጊዜም የተሻለውን የሚያውቀው ይሖዋ ነው። ስለዚህ “በጌታ” ብቻ ስለ ማግባት የሰጠውን ምክር በቁም ነገር ይመለከቱታል። (1 ቆሮንቶስ 7:39፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14) ጋብቻው ካልሰመረ መፋታት ወይም መለያየት ተቀባይነት ያላቸው አማራጮች ናቸው የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በመያዝ ቸኩለው ትዳር አይመሠርቱም። የጋብቻ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ “አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” የሚለው የአምላክ ሕግ ተግባራዊ እንደሚሆን ስለሚገነዘቡ ተረጋግተው ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ይፈልጋሉ።—ማቴዎስ 19:6፤ ማርቆስ 10:9
18. ደስተኛ ለሆነ ጋብቻ መሠረት ሊሆን የሚችለው ምንድን ነው?
18 ትዳር በጥንቃቄ እቅድ ማውጣትን የሚጠይቅ የዕድሜ ልክ ቃል ኪዳን ነው። አንድ ወንድ ‘በእርግጥ ለእኔ የምትስማማ ናትን?’ ብሎ ራሱን መጠየቁ አይቀርም። ይሁንና እንደሚከተለው ብሎ መጠየቁም የዚያኑ ያክል አስፈላጊ ነው:- ‘በእርግጥ ለእሷ የምስማማ ሰው ነኝን? መንፈሳዊ ፍላጎቶቿን ላሟላ የምችል የጎለመስኩ ክርስቲያን ነኝን?’ መለኮታዊ ተቀባይነት የሚያስገኝ ጠንካራ የጋብቻ ጥምረት ለመፍጠር እንዲችሉ ሁለቱም ተጋቢዎች በይሖዋ ፊት በመንፈሳዊ የጎለመሱ የመሆን ግዴታ አለባቸው። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከመቀበል ይልቅ በመስጠት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ደስታ የሰፈነበት ትዳር ለመመሥረት ግሩም ጅምር እንደሚሆን በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያን ባለ ትዳሮች ሊያረጋግጡ ይችላሉ።
19. አንዳንድ ክርስቲያኖች ነጠላ እንደሆኑ የሚቀጥሉት ለምንድን ነው?
19 አንዳንድ ክርስቲያኖች ለምሥራቹ ሲሉ ነጠላነትን በመምረጥ ‘ከመተቃቀፍ ይርቃሉ።’ (መክብብ 3:5) ሌሎች ደግሞ ተስማሚ የሆነ የትዳር ጓደኛ ለመሳብ የሚያስችል መንፈሳዊ ብቃት እንዳገኙ እስኪሰማቸው ድረስ የማግባት እቅዳቸውን ያራዝማሉ። ሆኖም የልብ ጓደኛና ከጋብቻ የሚገኘውን ጥቅም ለማግኘት አጥብቀው ቢፈልጉም የትዳር ጓደኛ እስከ አሁን ያላገኙ ነጠላ ክርስቲያኖች መኖራቸውን አንዘንጋ። ይሖዋ መለኮታዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሳይጥሱ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት እንደሚደሰት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በተጨማሪም ታማኝነታቸውን ልናደንቅና የሚያስፈልጋቸውን ማበረታቻ ልንሰጣቸው ይገባል።
20. ባለ ትዳሮች ጭምር አንዳንድ ጊዜ ‘ከመተቃቀፍ የሚርቁት’ ለምንድን ነው?
20 አንዳንድ ጊዜ ባለ ትዳሮችም ‘ከመተቃቀፍ መራቅ’ ይኖርባቸው ይሆን? ይህ ተገቢ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ መኖሩን ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ከተናገረው ለመመልከት ይቻላል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ።” (1 ቆሮንቶስ 7:29) በተመሳሳይም ትዳር የሚያስገኛቸው ደስታዎችና በረከቶች አንዳንድ ጊዜ ለቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች ቅድሚያውን መስጠት ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ጉዳይ ሚዛናዊ አመለካከት መያዙ ትዳርን የሚያዳክም ሳይሆን የሚያጠነክር ይሆናል፤ ምክንያቱም ሁለቱም ተጓዳኞች ለትዳራቸው ጥንካሬ ወሳኝ ሚና ያለው ይሖዋ መሆኑን ያስታውሳቸዋል።—መክብብ 4:12
21. ወላጅ የመሆንን ጉዳይ በተመለከተ ትዳር በያዙ ሰዎች ላይ መፍረድ የማይገባን ለምንድን ነው?
21 በተጨማሪም አንዳንድ ባለ ትዳሮች ለአምላክ የሚያቀርቡትን አገልግሎት በበለጠ ነፃነት ለማከናወን ሲሉ ልጆች ከመውለድ ተቆጥበዋል። ይህ መሥዋዕትነት ጠይቆባቸዋል፤ ሆኖም ይሖዋ በዚያው ልክ ይባርካቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ለምሥራቹ ሲባል ነጠላ መሆንን ቢያበረታታም በዚሁ ምክንያት ልጆችን ከመውለድ ስለ መቆጠብ የሰጠው ቀጥተኛ ሐሳብ ግን የለም። (ማቴዎስ 19:10-12፤ 1 ቆሮንቶስ 7:38፤ ከማቴዎስ 24:19ና ሉቃስ 23:28-30 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ባለ ትዳሮች ከግል ሁኔታቸውና ከሕሊናቸው በመነሳት የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ ይገባቸዋል። ማንኛውም ዓይነት ውሳኔ ቢያደርጉ ባለ ትዳሮቹ ሊነቀፉ አይገባም።
22. ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔያችን መሆን አለበት?
22 አዎን፣ “ለሁሉ ዘመን አለው፣ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።” ሌላው ቀርቶ “ለጦርነት ጊዜ አለው፣ ለሰላምም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:1, 8) የሚቀጥለው ርዕስ ያለንበት ጊዜ የጦርነት ይሁን ወይም የሰላም ለይተን ማወቃችን ለምን እንደሚጠቅመን ያብራራል።
ልታብራራ ትችላለህ?
◻ ‘ለሁሉ ጊዜ እንዳለው’ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ዛሬ ጊዜው በአመዛኙ ‘የማልቀስ ጊዜ’ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ክርስቲያኖች ‘የሚያለቅሱ’ ቢሆንም በእርግጥ ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው?
◻ አንዳንድ ክርስቲያኖች የአሁኑን ጊዜ ‘ከመተቃቀፍ የሚርቁበት’ ጊዜ አድርገው እንደሚመለከቱት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ክርስቲያኖች በዓለም ሁኔታዎች ምክንያት ‘የሚያለቅሱ’ ቢሆንም . . .
. . . በዓለም ላይ ከሚገኙ ሰዎች ይበልጥ እጅግ ደስተኛ የሆኑት ሕዝቦች እነሱ ናቸው
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ደስተኛ ለሆነ ትዳር ግሩም መሠረት ነው