የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በፍርድ ዙፋኑ ፊት የምትቀርበው እንዴት ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1995 | ጥቅምት 15
    • 4. ከዚህ በፊት የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ የሚፈጸምበትን ጊዜ የተረዳነው እንዴት ነበር? ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በዚህ ምሳሌ ላይ ትኩረት የምናደርገው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 4:18)

      4 ይህ ምሳሌ ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ በዙፋኑ ላይ ስለ መቀመጡ እንደሚናገርና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በበጎች ለተመሰሉት ሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት፣ በፍየሎች ለተመሰሉት ሰዎች ደግሞ ዘላለማዊ ጥፋት የሚያሰጥ ፍርድ በመፍረድ ላይ እንዳለ ከረጅም ጊዜ በፊት ተረድተን ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ምሳሌ እንደገና መመርመሩ ምሳሌው ስለሚፈጸምበት ጊዜና ስለሚገልጸው ነገር አዲስ ግንዛቤ አስገኝቷል። ይህ አዲስ ግንዛቤ የስብከት ሥራችንን አስፈላጊነትና ሰዎች የሚሰጡትን ምላሽ ወሳኝነት ያጠናክራል። ምሳሌውን በጥልቅ ለመረዳት የሚያስችል መሠረት እንዲኖረን መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋና ኢየሱስ በንጉሥነታቸውና በፈራጅነታቸው የሚያከናውኑትን ነገር በተመለከተ ምን እንደሚገልጽ እንመልከት።

      ይሖዋ በታላቅ ፈራጅነቱ የሚያከናውነው ተግባር

      5, 6. ይሖዋ ንጉሥም ዳኛም እንደሆነ አድርገን መመልከታችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

      5 ይሖዋ ከፍጥረታቱ ሁሉ የበላይ ሆኖ አጽናፈ ዓለምን ይገዛል። መጀመሪያና መጨረሻ ስለሌለው “የዘላለም ንጉሥ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17 አዓት ፤ መዝሙር 90:2, 4፤ ራእይ 15:3) ሕጎችን ወይም ሥርዓቶችን የማውጣትና የማስፈጸም ሥልጣን አለው። ይሁን እንጂ ሥልጣኑ ዳኝነትንም ይጨምራል። ኢሳይያስ 33:22 “እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፣ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፣ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው” ይላል።

      6 የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ የተለያዩ የፍርድ ጉዳዮችን ተመልክቶ እንደሚፈርድ ከረጅም ጊዜ በፊት ተገንዝበው ነበር። ለምሳሌ ያህል “የምድር ሁሉ ፈራጅ” የሰዶምና የገሞራን ክፋት ካመዛዘነ በኋላ ነዋሪዎቹ ጥፋት እንደሚገባቸው ከመፍረዱም በላይ ያን የጽድቅ ፍርድ አስፈጽሟል። (ዘፍጥረት 18:20–33፤ ኢዮብ 34:10–12) ይሖዋ ምን ጊዜም ፍርዶቹን የሚያስፈጽም ጻድቅ ዳኛ እንደሆነ ማወቃችን ምንኛ ሊያጽናናን ይገባል!

      7. ይሖዋ ከእስራኤል ጋር በነበረው ግንኙነት የዳኝነት ተግባር ያከናወነው እንዴት ነው?

      7 በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ በቀጥታ ፍርድ ይሰጥ ነበር። በዚያ ወቅት ብትኖር ኖሮ አንድ ፍጹም የሆነ ዳኛ የፍርድ ጉዳዮችን እንደሚመለከት በማወቅህ አትጽናናም ነበርን? (ዘሌዋውያን 24:10–16፤ ዘኁልቁ 15:32–36፤ 27:1–11) በተጨማሪም አምላክ ለፍርድ የሚያገለግሉ ጥሩ የአቋም ደረጃዎችን የያዙ “የፍርድ ውሳኔዎችን” ሰጥቷቸዋል። (ዘሌዋውያን 25:18, 19 አዓት ፤ ነህምያ 9:13፤ መዝሙር 19:9, 10፤ 119:7, 75, 164፤ 147:19, 20) እሱ “የምድር ሁሉ ፈራጅ” ስለሆነ ጉዳዩ ሁላችንንም ይነካናል።—ዕብራውያን 12:23

      8. ዳንኤል ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚዛመድ ምን ራእይ ተመልክቷል?

      8 ይህን ጉዳይ በተመለከተ አንድ “የዓይን ምሥክር” የሰጠው ምሥክርነት አለን። ነቢዩ ዳንኤል መንግሥታትን ወይም ነገሥታትን የሚያመለክቱ አስፈሪ አራዊትን በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ዳንኤል 7:1–8, 17) ከዚህም በላይ “ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፣ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ . . . ነበረ” ብሏል። (ዳንኤል 7:9) ዳንኤል ዙፋኖችንና ‘በዘመናት የሸመገለው [ይሖዋ] ተቀምጦ ’ እንደተመለከተ ልብ በል። ‘ዳንኤል እዚህ ላይ እየመሠከረ ያለው አምላክ መንገሡን ነውን?’ በማለት ራስህን ጠይቅ።

      9. በዙፋን ላይ ‘የመቀመጥ’ አንዱ ትርጉም ምንድን ነው? ምሳሌዎችን ስጥ።

      9 መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ በእንዲህ ዓይነቱ አነጋገር ስለሚጠቀም አንድ ሰው በዙፋን ላይ እንደ “ተቀመጠ” ስናነብ ይህ ሰው ነገሠ ብለን እናስብ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ “[ዘምሪ] ንጉሥም በሆነ ጊዜ፣ በዙፋኑም በተቀመጠ ጊዜ . . .” በማለት ይናገራል። (1 ነገሥት 16:11፤ 2 ነገሥት 10:30፤ 15:12፤ ኤርምያስ 33:17) አንድ መሲሐዊ ትንቢት “በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሣል” ይላል። ስለዚህ ‘በዙፋን ላይ መቀመጥ’ መንገሥ ማለት ሊሆን ይችላል። (ዘካርያስ 6:12, 13፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ይሖዋ በዙፋን ላይ እንደ ተቀመጠ ንጉሥ ተደርጎ ተገልጿል። (1 ነገሥት 22:19፤ ኢሳይያስ 6:1፤ ራእይ 4:1–3) እሱ “የዘላለም ንጉሥ” ነው። ሆኖም አንድ የተለየ የሉዓላዊነቱን ገጽታ በሚያረጋግጥበት ወቅት በአዲስ መልክ በዙፋን ላይ የተቀመጠ ያህል ንጉሥ ሆነ ሊባል ይችላል።—1 ዜና መዋዕል 16:1, 31፤ ኢሳይያስ 52:7፤ ራእይ 11:15–17፤ 15:3፤ 19:1, 2, 6

      10. የእስራኤላውያን ነገሥታት ዋንኛ ተግባር ምን ነበር? በምሳሌ አስረዳ።

      10 ይሁን እንጂ በጣም አስፈላጊው ነጥብ የሚከተለው ነው፦ የጥንት ነገሥታት ዋና ተግባር ክሶችን መስማትና ፍርድ መስጠት ነበር። (ምሳሌ 29:14) ሁለት ሴቶች ‘ሕፃኑ የእኔ ነው’ ብለው በተከራከሩ ጊዜ ሰሎሞን የሰጠውን ጥበብ የተሞላበት ፍርድ አስታውስ። (1 ነገሥት 3:16–28፤ 2 ዜና መዋዕል 9:8) ከመንግሥታዊ ሕንፃዎቹ አንዱ “የሚፈርድበት ዙፋን ያለበት” ሲሆን ሕንፃው “ፍርድ ቤት” ተብሎም ይጠራ ነበር። (1 ነገሥት 7:7) ኢየሩሳሌም ‘ዙፋኖች ለፍርድ የተቀመጡባት’ ቦታ እንደሆነች ተደርጋ ተገልጻለች። (መዝመር 122:5) ‘በዙፋን ላይ መቀመጥ’ ማለት መፍረድ ማለትም ጭምር እንደሆነ የተረጋገጠ ነው።—ዘጸአት 18:13፤ ምሳሌ 20:8

      11, 12. (ሀ) በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ ይሖዋ በዙፋን ላይ ስለ መቀመጡ የሚናገረው ሐሳብ ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) ሌሎች ጥቅሶች ይሖዋ ለፍርድ እንደ ተቀመጠ የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?

      11 አሁን ዳንኤል ‘በዘመናት የሸመገለው ተቀምጦ ’ ወዳየበት ትዕይንት እንመለስ። ዳንኤል 7:10 በዚህ ላይ ሲያክል “ፍርድም ሆነ፣ መጻሕፍትም ተገለጡ” ይላል። አዎን፣ በዘመናት የሸመገለው ስለ ዓለም አገዛዝና የሰው ልጅ የተባለው ለመግዛት ብቃት ያለው ስለ መሆኑ ፍርድ ለመስጠት ተቀምጦ ነበር። (ዳንኤል 7:13, 14) ከዚያም ‘በዘመናት የሸመገለው መጣ፤ ለልዑል ቅዱሳንም ተፈረደላቸው ’ የሚል እናነባለን። እነዚህ ቅዱሳን ከሰው ልጅ ጋር ለመግዛት ብቁ እንደሆኑ ተፈረደላቸው። (ዳንኤል 7:22) በመጨረሻም ይህ ‘ችሎት’ የፍርድ ጉዳዮችን ‘ማየቱን በመቀጠል’ በመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት ላይ በየነበት።—ዳንኤል 7:26a

      12 በዚህም ምክንያት ዳንኤል አምላክ ‘በዙፋን ላይ ተቀምጦ’ መመልከቱ አምላክ ፍርድ ለመስጠት መምጣቱን ያመለክታል። ቀደም ሲል ዳዊት “[ይሖዋ ሆይ] ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ” በማለት ዘምሮ ነበር። (መዝሙር 9:4, 7) በተጨማሪም ኢዩኤል “አሕዛብ ይነሡ፣ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፤ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ [እኔ ይሖዋ] በዚያ እቀመጣለሁና” በማለት ጽፏል። (ኢዩኤል 3:12፤ ከኢሳይያስ 16:5 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስና ጳውሎስ ሰዎች ክሶችን ለመስማትና ፍርድ ለመስጠት በተቀመጡባቸው ቦታዎች ለፍርድ ቀርበው ነበር።b—ዮሐንስ 19:12–16፤ ሥራ 23:3፤ 25:6

      የኢየሱስ ሥልጣን

      13, 14. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ኢየሱስ እንደ ነገሠ ምን ማረጋገጫ አላቸው? (ለ) ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው መቼ ነው? ኢየሱስ ከ33 እዘአ ጀምሮ በመግዛት ላይ ያለው በምን መንገድ ነው?

      13 ይሖዋ ንጉሥም ዳኛም ነው። ኢየሱስስ? የኢየሱስን ልደት ያበሰረው መልአክ “ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤. . . ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” ብሏል። (ሉቃስ 1:32, 33) ኢየሱስ የዳዊት ሥርወ መንግሥት ዘላለማዊ ወራሽ ይሆናል። (2 ሳሙኤል 7:12–16) ዳዊት “እግዚአብሔር ጌታዬን፦ ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው። እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ” ስላለ ኢየሱስ የሚገዛው ከሰማይ ሆኖ ነው።—መዝሙር 110:1–4

      14 ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ኢየሱስ ሰው በነበረበት ወቅት ንጉሥ ሆኖ አልገዛም። (ዮሐንስ 18:33–37) በ33 እዘአ ሞቶ ከተነሣ በኋላ ወደ ሰማይ አረገ። ዕብራውያን 10:12 “እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ” ይላል። ኢየሱስ ምን ሥልጣን ነበረው? “[አምላክ] ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይ . . . በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው . . . ከሁሉም በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።” (ኤፌሶን 1:20–22) ኢየሱስ በዚያ ወቅት በክርስቲያኖች ላይ ንጉሣዊ ሥልጣን ስለ ነበረው ጳውሎስ “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ሥርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” በማለት ሊጽፍ ችሏል።—ቆላስይስ 1:13፤ 3:1

      15, 16. (ሀ) ኢየሱስ በ33 እዘአ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ አልሆነም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት ላይ መግዛት የጀመረው መቼ ነው?

      15 ሆኖም በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በአሕዛብ ላይ ንጉሥና ዳኛ አልሆነም። በአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ የሚሾምበትን ጊዜ እየተጠባበቀ በአምላክ አጠገብ ተቀምጦ ነበር። ጳውሎስ ስለ እሱ “ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል?” ሲል ጽፏል።—ዕብራውያን 1:13

      16 የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ በማይታዩት ሰማያት የአምላክ መንግሥት ገዢ በሆነበት በ1914 በመጠባበቅ የሚያሳልፈው ጊዜ እንዳለቀ የሚጠቁሙ ብዙ መረጃዎችን አሳትመው አውጥተዋል። ራእይ 11:15, 18 “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፣ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል።” “አሕዛብ ተቆጡ፣ ቁጣህም መጣ” ይላል። አዎን፣ ብሔራት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እርስ በርሳቸው በመዋጋት ቁጣቸውን ገልጸዋል። (ሉቃስ 21:24) ከ1914 ጀምሮ ያየናቸው ጦርነቶች፣ የመሬት መንቀጥቀጦች፣ መቅሠፍቶች፣ የምግብ እጥረቶች እና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ነገሮች ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደሆነና የመጨረሻው የዓለም ፍጻሜ መቃረቡን ያረጋግጣሉ።—ማቴዎስ 24:3–14

      17. እስካሁን ድረስ የትኞቹን ቁልፍ ነጥቦች ተረድተናል?

      17 ትንሽ ለመከለስ ያህል፦ አምላክ በዙፋን ላይ ንጉሥ ሆኖ ተቀምጧል ሊባል ይችላል፣ ሆኖም በሌላ መንገድ ደግሞ በዙፋኑ ላይ ለፍርድ ሊቀመጥ ይችላል። በ33 እዘአ ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ የተቀመጠ ሲሆን አሁን ደግሞ የመንግሥቱ ንጉሥ ሆኗል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ የሚገኘው ኢየሱስ በዳኝነት ሥራ እያገለገለ ነውን? ከዚህም በላይ በተለይ በዚህ ጊዜ ይህ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

      18. ኢየሱስ ዳኛም ጭምር እንደሚሆን ምን ማረጋገጫ አለ?

      18 ፈራጆችን የመሾም መብት ያለው ይሖዋ የእርሱን የአቋም ደረጃዎች ያሟላውን ኢየሱስን ለዳኝነት መርጦታል። ኢየሱስ በመንፈሳዊ ሕያው የሆኑ ሰዎችን በተመለከተ ሲናገር “ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም” ባለ ጊዜ ይህን አሳይቷል። (ዮሐንስ 5:22) ሆኖም ኢየሱስ በሕያዋንና በሙታን ላይ ስለሚፈርድ ፍርዱ ከዚህ የበለጠ ነገርንም ይጨምራል። (ሥራ 10:42፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:1) ጳውሎስ በአንድ ወቅት “[አምላክ] ቀን ቀጥሮአልና፣ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል” ብሏል።—ሥራ 17:31፤ መዝሙር 72:2–7

      19. ኢየሱስ በዳኝነት ተቀምጧል ብሎ መናገር ትክክል የሚሆነው ለምንድን ነው?

      19 ታዲያ የተወሰነ የዳኝነት ሥልጣን ይዞ በክብራማ ዙፋን ላይ ተቀምጧል ብለን መደምደማችን ትክክል ይሆናልን? አዎን። ኢየሱስ ለሐዋርያት “እናንተስ የተከተላችሁኝ፣ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ ፣ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 19:28፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የመንግሥቱ ንጉሥ ቢሆንም እንኳ በማቴዎስ 19:28 ላይ የተጠቀሰው ተጨማሪ ሥራው በሺው ዓመት ለዳኝነት በዙፋን ላይ መቀመጥን ይጨምራል። በዚያን ጊዜ በመላው የሰው ዘር ማለትም በጻድቁም ሆነ በኃጢአተኛው ላይ ይፈርዳል። (ሥራ 24:15) ከዘመናችን ጋር በሚዛመዱትና ሕይወታችንን በሚነኩት የኢየሱስ ምሳሌዎች ላይ ስናተኩር ይህን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው።

      ምሳሌው ምን ይላል?

      20, 21. የኢየሱስ ሐዋርያት የጠየቁት ዘመናችንን የሚመለከት ጥያቄ የትኛው ነው? ይህስ ወደ የትኛው ጥያቄ ይመራል?

      20 ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሐዋርያቱ “‘እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?’ ብለው ጠየቁት።” (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ኢየሱስ ‘መጨረሻው ከመምጣቱ’ በፊት በምድር ላይ የሚፈጸሙትን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎች አስቀድሞ ተናገረ። ይህ መጨረሻ ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ብሔራት “የሰው ልጅን በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።”—ማቴዎስ 24:14, 29, 30

      21 የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ በእነዚህ ብሔራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ምን ዋጋ ይቀበላሉ? “የሰው ልጅ በከብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል” በማለት ከሚጀምረው ስለ በጎችና ፍየሎች ከሚናገረው ምሳሌ መልሱን ለማግኘት እንሞክር።—ማቴዎስ 25:31, 32

      22, 23. የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ በ1914 መፈጸም አለመጀመሩን የሚያመለክቱት የትኞቹ ነጥቦች ናቸው?

      22 ኢየሱስ በ1914 በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ እንደ ተቀመጠ ከብዙ ጊዜ በፊት ተረድተን ነበር፤ ታዲያ ይህ ምሳሌ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመፈጸም ላይ ነውን? ማቴዎስ 25:34 ኢየሱስን እንደ ንጉሥ አድርጎ ስለሚገልጸው ይህ ምሳሌ ከ1914 ጀምሮ መፈጸም ጀምሯል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። ይሁን እንጂ ከዚያ ጊዜ በኋላ ወዲያውኑ የተሰጠው ፍርድ ምን ነበር? “በአሕዛብ ሁሉ” ላይ ፍርድ አልተሰጠም። ከዚህ ይልቅ ‘የእግዚአብሔር ቤት’ ነን በሚሉት ላይ ትኩረቱን አድርጓል። (1 ጴጥሮስ 4:17) ከሚልክያስ 3:1–3 ጋር በሚስማማ መንገድ ኢየሱስ እንደ የይሖዋ መልእክተኛ በመሆን በምድር ላይ በቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ ፍርድ በመስጠት ምርመራ አካሂዷል። በተጨማሪም በሐሰት “የእግዚአብሔር ቤት” ነኝ በምትለዋ በሕዝበ ክርስትና ላይ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ ነበር።c (ራእይ 17:1, 2፤ 18:4–8) ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ ወይም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ አሕዛብን ሁሉ በጎችና ፍየሎች ናችሁ በማለት የመጨረሻ ፍርድ ለመስጠት እንደተቀመጠ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።

      23 ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ የሚያከናውነውን ተግባር ከመረመርን በመጨረሻ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ሲፈርድ እንመለከተዋለን። ምሳሌው ባለፉት አሥርተ ዓመታት የሞቱት ሰዎች ሁሉ ዘላለማዊ ሞት ወይም ሕይወት እየተፈረደባቸው ወይም እየተፈረደላቸው ይህ ፍርድ ለብዙ ዓመታት እንደሚቀጥል አያመለክትም። በቅርብ ዓመታት የሞቱ አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ሰው ልጆች ተራ መቃብር የሄዱ ይመስላል። (ራእይ 6:8፤ 20:13) ሆኖም ምሳሌው ኢየሱስ በሕይወት የሚኖሩትንና የፍርድ ውሳኔውን የሚቀበሉትን “አሕዛብን ሁሉ” የሚዳኝበትን ጊዜ ይገልጻል።

      24. የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው?

      24 በሌላ አባባል ይህ ምሳሌ የሰው ልጅ በክብሩ የሚመጣበትን የወደፊት ጊዜ ያመለክታል። በዚያን ጊዜ በሕይወት በሚኖሩ ሰዎች ላይ ለመፍረድ ይቀመጣል። የሚሰጠው ፍርድ ባሳዩት ባሕርይ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ‘በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል ያለው ልዩነት’ በግልጽ ይታያል። (ሚልክያስ 3:18) ፍርዱ የሚሰጠውም ሆነ የሚፈጸመው በአንድ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በግለሰቦች ላይ በሚታየው ነገር መሠረት ትክክለኛ የፍርድ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል።—በተጨማሪም 2 ቆሮንቶስ 5:10ን ተመልከት።

      25. የሰው ልጅ በክብራማ ዙፋን መቀመጡን በተመለከተ ማቴዎስ 25:31 የሚገልጸው ምንድን ነው?

      25 ይህም ማለት በማቴዎስ 25:31 ላይ እንደ ተገለጸው ኢየሱስ ‘በክብሩ ዙፋን ላይ ተቀምጦ’ የሚሰጠው ፍርድ ይህ ኃያል ንጉሥ ወደፊት በአሕዛብ ላይ ፍርድ ለመስጠትና ያን ፍርድ ለማስፈጸም የሚቀመጥበትን ጊዜ ያመለክታል። አዎን፣ በማቴዎስ 25:31–33, 46 ላይ ኢየሱስን በተመለከተ የተገለጸው የፍርድ ትዕይንት በመግዛት ላይ ያለው በዘመናት የሸመገለው ንጉሥ የዳኝነት ተግባሩን ለማከናወን መቀመጡን ከሚናገረው በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ ካለው ትዕይንት ጋር የሚመሳሰል ነው።

      26. ይህን ምሳሌ በተመለከተ ምን አዲስ ግንዛቤ ተገኝቷል?

      26 የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ በዚህ መንገድ መረዳት በበጎቹና በፍየሎቹ ላይ ፍርድ የሚሰጠው ወደፊት እንደሆነ ያሳያል። በማቴዎስ 24:29, 30 ላይ የተጠቀሰው “መከራ” ከፈነዳና የሰው ልጅ ‘በክብሩ ከመጣ’ በኋላ የሚፈጸም ነገር ነው። (ከማርቆስ 13:24–26 ጋር አወዳድር።) ከዚያ በኋላ በጠቅላላው የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ ወቅት ኢየሱስ ችሎት ላይ ተቀምጦ ለአንዳንዶቹ ሲፈርድላቸው በሌሎች ላይ ደግሞ የጥፋት ፍርድ ይበይንባቸዋል።—ዮሐንስ 5:30፤ 2 ተሰሎንቄ 1:7–10

      27. የኢየሱስን የመጨረሻ ምሳሌ በማወቅ ረገድ ስለምን ነገር ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል?

      27 ይህም የኢየሱስ ምሳሌ የሚፈጸምበትን ማለትም በበጎቹና በፍየሎቹ ላይ ፍርድ የሚሰጥበትን ጊዜ በተመለከተ ያለንን ግንዛቤ ከፍ ያደርግልናል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት የምንሰብከውን እኛን የሚነካን እንዴት ነው? (ማቴዎስ 24:14) ሥራችንን አቅልለን እንድንመለከት ያደርገናል ወይስ ከባድ ኃላፊነት ይጥልብናል? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እኛ በጉዳዩ እንዴት እንደምንነካ እንመለከታለን።

  • የበጎቹና የፍየሎቹ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1995 | ጥቅምት 15
    • 2 ኢየሱስ በሰጠው የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ላይ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ” በማለት አንድ የተለየ ሥልጣን ይዞ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ ጠቁሟል። (ማቴዎስ 25:31) ኢየሱስ “እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠውን መልስ የደመደመው በዚህ ምሳሌ ስለሆነ ይህ ነገር የማወቅ ፍላጎት ሊያሳድርብን ይገባል። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ይሁን እንጂ ይህ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

      3. ኢየሱስ ቀደም ሲል ባቀረበው ንግግሩ ላይ ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ ወዲያውኑ ምን ይሆናል ብሎ ነበር?

      3 ኢየሱስ ታላቁ መከራ ከፈነዳ “በኋላ ወዲያው” እንደሚከሰቱ የምንጠብቃቸውን አስደንጋጭ ሁኔታዎች አስቀድሞ ተናግሯል። በዚያን ጊዜ “የሰው ልጅ ምልክት” ይታያል ብሏል። ይህ ሁኔታ “የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ” የሚያዩትን “የምድር ወገኖች” በከፍተኛ ደረጃ ይነካል። የሰው ልጅ “ከመላእክቱ” ጋር ይመጣል። (ማቴዎስ 24:21, 29–31)a የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ የሚፈጸመው እንዴት ነው? ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶች በምዕራፍ 25 ውስጥ ያስቀምጡት እንጂ ይህ ምሳሌ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ ክፍል ሲሆን በክብሩ ስለሚመጣበት ጊዜ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚገኝበትና “በአሕዛብ ላይ” በመፍረድ ሥራው ላይ የሚያተኩር ነው።—ማቴዎስ 25:32

      በምሳሌው ውስጥ የተገለጹት

      4. በበጎቹና በፍየሎቹ ምሳሌ መጀመሪያ ላይ ስለ ኢየሱስ የተጠቀሰው ምንድን ነው? ሌሎችስ እነማን ተጠቅሰዋል?

      4 ኢየሱስ ምሳሌውን የጀመረው ‘የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ’ በማለት ነው። “የሰው ልጅ” ማን እንደሆነ ሳታውቅ አትቀርም። የወንጌል ጸሐፊዎች ብዙውን ጊዜ የሰው ልጅ የሚለውን አጠራር ኢየሱስን ለመግለጽ ይጠቀሙበታል። ኢየሱስ ራሱ እንኳ ራሱን የሰው ልጅ ብሎ የጠራው “የሰው ልጅ የሚመስል” “ግዛትና ክብር መንግሥትም” ለመቀበል በዘመናት ወደ ሸመገለው እንደ ቀረበ የሚገልጸውን የዳንኤል ራእይ በአእምሮው ይዞ እንደ ነበረ አያጠራጥርም። (ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 26:63, 64፤ ማርቆስ 14:61, 62) በዚህ ምሳሌ ውስጥ በዋነኛነት የተጠቀሰው ኢየሱስ ቢሆንም ሌሎችም አሉ። በማቴዎስ 24:30, 31 ላይ እንደ ተገለጸው ቀደም ሲል በዚህ ንግግሩ ውስጥ የሰው ልጅ ‘በኃይልና በብዙ ክብር ሲመጣ’ መላእክት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግሮ ነበር። በተመሳሳይም የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ ኢየሱስ ‘በክብሩ ዙፋን ላይ’ ለፍርድ ‘ሲቀመጥ’ መላእክት ከእሱ ጋር እንደሚኖሩ ያሳያል። (ከማቴዎስ 16:27 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ዳኛውና መላእክቱ በሰማይ ስለሆኑ በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች በሰማይ ናቸውን?

  • የበጎቹና የፍየሎቹ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1995 | ጥቅምት 15
    • ተመሳሳይነታቸውን አስተውሉ

      ማቴዎስ 24:29–31 ማቴዎስ 25:31–33

      ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ የሰው ልጅ ይመጣል የሰው ልጅ ይመጣል

      በታላቅ ክብር ይመጣል በክብር ከመጣ በኋላ

      በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል

      መላእክቱንም ይልካቸዋል ከመላእክት ጋር ይመጣል

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ