“ዝም ለማለት ጊዜ አለው፣ ለመናገርም ጊዜ አለው”
“እንደዚህ ባላልኩ ኖሮ!” በማለት ምን ያህል ጊዜ ተቆጭተህ ታውቃለህ? ሆኖም ሐሳብህን ሳትገልጽ የቀረህባቸው ሌሎች አጋጣሚዎች እንደነበሩ ታስታውስ ይሆናል። ወደ ኋላ መለስ ብለህ ስታስብ ‘አንድ ነገር በተናገርኩ ኖሮ’ ብለህ ሊሆን ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፣ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:7) ሆኖም መቼ መናገርና መቼ ዝም ማለት እንደሚገባ መወሰን ያስቸግራል። አብዛኛውን ጊዜ ፍጹም ያልሆነው ሰብዓዊ ተፈጥሯችን አንዳንድ ነገሮችን ተገቢ ባልሆነ ጊዜ እንድናደርግና እንድንናገር ያስገድደናል። (ሮሜ 7:19) አስቸጋሪ የሆነውን አንደበታችንን መቆጣጠር የምንችለው እንዴት ነው?—ያዕቆብ 3:2
አንደበትን መቆጣጠር የሚቻልባቸው መንገዶች
መቼ መናገርና መቼ ዝም ማለት እንዳለብን ለመወሰን እንዲረዳን ሊያጋጥመን የሚችለውን እያንዳንዱን ሁኔታ ያካተተ ዝርዝር ሕግ አያስፈልገንም። ከዚህ ይልቅ የክርስቲያናዊ ስብዕና መሠረታዊ ክፍል በሆኑት ባሕርያት መመራት ይኖርብናል። እነዚህ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን የሚያንቀሳቅሳቸው ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር መሆኑን ገልጿል። “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) እንዲህ ዓይነቱን ወንድማማቻዊ ፍቅር በይበልጥ ባሳየን መጠን አንደበታችንን በተሻለ መንገድ መቆጣጠር እንችላለን።
በዚህ ረገድ ሁለት ተዛማጅ ባሕርያት ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታሉ። ከእነዚህ አንዱ ትሕትና ነው። ትሕትና ‘ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን እንድንመለከት’ ያስችለናል። (ፊልጵስዩስ 2:3) ሌላው ባሕርይ ‘መጥፎ ሁኔታ ሲያጋጥመን ራሳችንን እንድንቆጣጠር’ የሚያደርገን የዋህነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25 አዓት) ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልን ፍጹም ምሳሌ እነዚህን ባሕርያት እንዴት ማሳየት እንደሚገባ ለማስተዋል ይረዳናል።
በውጥረት ሥር በምንሆንበት ወቅት ከሌላው ጊዜ ይልቅ አንደበታችንን መቆጣጠር ይበልጥ ስለሚያስቸግረን ኢየሱስ ‘በጣም ተጨንቆ’ በነበረበት ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት የተፈጸመውን ሁኔታ እንመልከት። (ማቴዎስ 26:37, 38) የመላው የሰው ዘር ዘላለማዊ ተስፋ እርሱ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ በመቀጠሉ ላይ የተመካ ስለነበረ ኢየሱስ መጨነቁ አያስደንቅም።—ሮሜ 5:19-21
በዚህ ወቅት ኢየሱስ ከሰማዩ አባቱ ጋር መነጋገር ያስፈልገው እንደነበር አያጠራጥርም። ስለዚህ ሦስቱ ደቀ መዛሙርቱ ነቅተው እንዲጠብቁ ከነገራቸው በኋላ ሊጸልይ ሄደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተመልሶ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስን “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን?” አለው። ይህን ፍቅራዊ ወቀሳ ከሰጣቸው በኋላ ድክመታቸውን እንደተረዳ የሚገልጽ ቃል ተናግሯል። “መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው” ብሏል። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ እንደገና ተመልሶ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው። በአሳቢነት መንፈስ ካነጋገራቸው በኋላ ‘ትቶአቸው ሄደና ለሦስተኛ ጊዜ ጸለየ።’—ማቴዎስ 26:36-44
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለሦስተኛ ጊዜ ተኝተው ሲያገኛቸው በኃይለ ቃል አልተናገራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ እንዲህ አላቸው፦ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? አሁንም ዕረፍት ታደርጋላችሁን? እነሆ ሰዓቱ ደርሶአል፤ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል።” (ማቴዎስ 26:45 የ1980 ትርጉም) እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ጊዜ አንደበቱን በዚህ መንገድ ሊጠቀም የሚችለው አፍቃሪ ልብ ያለው፣ የዋህና ትሑት የሆነ ሰው ብቻ ነው።—ማቴዎስ 11:29፤ ዮሐንስ 13:1
ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ተይዞ ለፍርድ ቀረበ። እዚህ ላይ አንዳንድ ጊዜ በክርስቲያናዊ አገልግሎት በምንካፈልበት ወቅትም እንኳ ዝም ማለታችን የተሻለ እንደሚሆን እንማራለን። ሊቀ ካህኑ በክርስቶስ ላይ ክስ ለመመሥረት የሚያስችለውን መረጃ ለማግኘት እንጂ እውነትን ለማወቅ ምንም ፍላጎት አልነበረውም። ስለዚህ ኢየሱስ በዚህ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ወቅት አንድም ቃል አልተነፈሰም።—ከማቴዎስ 7:6 ጋር አወዳድር።
ሆኖም ሊቀ ካህኑ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” በማለት ጥያቄ ሲያቀርብለት ዝም አላለም። (ማቴዎስ 26:63) ኢየሱስ በመሐላ ስለ ተያዘ በዚህ ጊዜ መናገር ያስፈልገው ነበር። ስለሆነም “አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” በማለት መለሰ።—ማቴዎስ 26:64
በዚህ እጅግ ወሳኝ በሆነ ቀን ኢየሱስ አንደበቱን ፍጹም በሆነ ሁኔታ ተቆጣጥሯል። ፍቅር፣ የዋህነትና ትሕትና የስብዕናው ተፈጥሯዊ ክፍሎች ነበሩ። በውጥረት ሥር በምንሆንበት ወቅት አንደበታችንን ለመቆጣጠር እነዚህን ባሕርያት መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
በምንናደድበት ጊዜ አንደበታችንን መቆጣጠር
ስንናደድ ብዙውን ጊዜ አንደበታችንን መቆጣጠር ይሳነናል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት በጳውሎስና በርናባስ መካከል የሐሳብ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር። “በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይወስድ ዘንድ አሰበ፤ ጳውሎስ ግን ይህን ከእነርሱ ጋር ሊወስድ አልፈቀደም፣ ከእነርሱ ዘንድ ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበርና፣ ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም ነበርና። ስለዚህም እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ።”—ሥራ 15:37-39
ለተወሰኑ ዓመታት በግንባታ ፕሮጄክቶች ላይ የሠራው ማይክልa እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በግንባታው ቦታ በደንብ የማውቀውና የማከብረው አንድ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ዘወትር ሥራዬን ይነቅፍ ነበር። ምንም እንኳ ሁኔታው ያሳዘነኝና ያበሳጨኝ ቢሆንም ስሜቴን አልገለጽኩም። አንድ ቀን ግን አንድ ሥራ ሠርቼ ከጨረስኩ በኋላ ወዲያውኑ የሠራሁትን ሥራ ሲተች ሁሉ ነገር ተበላሸ።
“አምቄ ይዤው የነበረው ስሜት በሙሉ ገነፈለ። በወቅቱ በጣም ተናድጄ ስለ ነበር በዙሪያችን ባሉት ሰዎች ላይ የሚያሳድረው መጥፎ ስሜት ምንም አልታየኝም ነበር። በዚያን ቀን እንኳን ላናግረው ላየው እንኳ አልፈለግሁም ነበር። አሁን ግን ችግሩን በተገቢው መንገድ እንዳልፈታሁት ተገንዝቤአለሁ። ዝም ብዬ ቁጣዬ እስኪበርድልኝ ድረስ ከጠበቅሁ በኋላ ብናገር ይሻል ነበር።”
ደስ የሚለው እነዚህ ሁለት ግለሰቦች በክርስቲያናዊ ፍቅር ተገፋፍተው በመካከላቸው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ችለዋል። ማይክል “በጉዳዩ ላይ በግልጽ ከተነጋገርንበት በኋላ ይበልጥ መግባባት ከመቻላችንም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ጠንካራ ወዳጅነት መሥርተናል” ብሏል።
ማይክል እንደተገነዘበው ሁሉ ስንናደድ አንዳንድ ጊዜ ዝም ማለታችን ጥበብ ነው። ምሳሌ 17:27 “መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው” ይላል። አስተዋይነትና ወንድማማቻዊ ፍቅር እንደመጣልን ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ከመናገር እንድንቆጠብ ይረዳናል። አንድ ሰው ቅር ካሰኘን ሰላም ለማምጣት ስንል ግለሰቡን በየዋህነትና በትሕትና መንፈስ ብቻችንን እናነጋግረው። ሆኖም በቁጣ መንፈስ ተናግረን ከሆነስ? በዚህ ጊዜ ፍቅር የኩራትን መንፈስ አስወግደን በትሕትና አንዳንድ ማስተካከያዎች እንድናደርግ ያነሳሳናል። ይህ በቅን ልቦና የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ መጸጸታችንን መግለጽና ቅር ያሰኘናቸውን ሰዎች ይቅርታ መጠየቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው።—ማቴዎስ 5:23, 24
ዝምታ መፍትሔ በማይሆንበት ጊዜ
ንዴት ወይም ብስጭት ያናደደንን ግለሰብ እንድናኮርፈው ሊያደርግ ይችላል። ይህም በጣም ሊጎዳን ይችላል። “በመጀመሪያው የትዳራችን ዓመት ባሌን ለበርካታ ቀናት የማኮርፍባቸው ጊዜያት ነበሩ” በማለት ማሪያb የሠራችውን ስሕተት ገልጻለች። “ብዙውን ጊዜ ይህ የሚሆነው በከባድ ችግሮች ምክንያት ሳይሆን ጥቃቅን የሆኑ የሚያስቆጡ ነገሮች በመጠራቀማቸው ነው። ተራራ የሚያክል እንቅፋት ሆነው እስኪታዩኝ ድረስ በእነዚህ የሚያስቆጡ ነገሮች ላይ ማብሰልሰሌን ቀጠልኩ። ከዚያም ችግሩን መቋቋም የማልችልበት ደረጃ ላይ ስለ ደረስኩ ብስጭቴ እስኪበርድልኝ ድረስ ከባሌ ጋር መነጋገሬን አቆምኩ።”
ማሪያ አክላ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “‘በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አስተሳሰቤን እንዳርም ረድቶኛል። እኔና ባለቤቴ ችግሮች እየተባባሱ እንዳይሄዱ የሐሳብ ግንኙነታችንን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት አደረግን። ይህ ቀላል የነበረ ባይሆንም ከአሥር ዓመታት የትዳር ሕይወት በኋላ በዝምታ የምናሳልፋቸው ጊዜያት በጣም በመቀነሳቸው ደስ ብሎኛል። ሆኖም አሁንም ቢሆን ይህን ዝንባሌ ለመቆጣጠር እየጣርኩ ነው።”—ኤፌሶን 4:26
ማሪያ እንደተገነዘበችው ሁሉ በሁለት ሰዎች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ የሐሳብ ግንኙነትን ማቋረጥ መፍትሔ አይሆንም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ቅሬታ እያደገ ሊሄድ ስለሚችል ዝምድናው ሊበላሽ ይችላል። ኢየሱስ ‘ስምምነት ለመፍጠር ፈጣኖች’ መሆን እንዳለብን ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:25) ‘በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል’ ‘ሰላምን ለመከተል’ ሊረዳን ይችላል።—ምሳሌ 25:11፤ 1 ጴጥሮስ 3:11
በተጨማሪም እርዳታ ሲያስፈልገን ሐሳባችንን ገልጸን መናገር ይኖርብናል። በአንድ መንፈሳዊ ችግር ምክንያት እየተሠቃየን ከሆነ ሌሎችን ላለማስቸገር ስንል ችግራችንን ከመግለጽ ወደ ኋላ እንል ይሆናል። ይሁን እንጂ ዝም ካልን ችግሩ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል። የተሾሙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለእኛ ስለሚያስቡ ችግራችንን ከገለጽንላቸው እኛን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። በዚህ ጊዜ መናገራችን አስፈላጊ ነው።—ያዕቆብ 5:13-16
ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ እንዳደረገው ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ከይሖዋ ጋር ዘወትር መነጋገር ያስፈልገናል። ለሰማዩ አባታችን ‘ልባችንን ማፍሰስ’ ይኖርብናል።—መዝሙር 62:8፤ ከዕብራውያን 5:7 ጋር አወዳድር።
ስለ አምላክ መንግሥት ‘መናገር የሚያስፈልግበት ጊዜ’
ክርስቲያናዊው አገልግሎት መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት መፈጸም የሚኖርበት መለኮታዊ ተልእኮ ነው። ስለሆነም በአሁኑ ወቅት የይሖዋ አገልጋዮች የመንግሥቱን ምሥራች ማወጃቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ አስፈላጊ ነው። (ማርቆስ 13:10) እንደ ሐዋርያት ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ‘ያዩትንና የሰሙትን ከመናገር ዝም ለማለት አይችሉም።’—ሥራ 4:20
እርግጥ ሁሉም ሰው ምሥራቹን መስማት ይፈልጋል ማለት አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት ሲልካቸው ‘የሚገባቸውን ፈልጉ’ በማለት መክሯቸዋል። ይሖዋ ማንንም ሰው እንዲያመልከው ስለማያስገድድ የመንግሥቱን መልእክት አልቀበልም ያለውን ግለሰብ ድርቅ ብለን ማነጋገራችን መቀጠል የለብንም። (ማቴዎስ 10:11-14) ይሁን እንጂ ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ’ ላላቸው ሰዎች ስለ ይሖዋ ንግሥና መናገራችን ያስደስተናል።—ሥራ 13:48፤ መዝሙር 145:10-13
ፍቅር፣ የዋህነትና ትሕትና እንዳመጣልን እንድንናገር ወይም እንድናኮርፍ የሚገፋፋ ፍጹም ያልሆነ ዝንባሌያችንን ለመቆጣጠር ሊረዱን የሚችሉ ባሕርያት ናቸው። እነዚህን ባሕርያት ባዳበርናቸው መጠን በየትኛው ጊዜ መናገር እንደሚገባንና በየትኛው ጊዜ መናገር እንደሌለብን ይበልጥ ጠንቅቀን ማወቅ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እውነተኛ ስሟ አይደለም።
b እውነተኛ ስሙ አይደለም።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ ችግሮችን መፍታት ይቻላል