የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 3/15 ገጽ 10-15
  • ለማስተማር ሥራችሁ የማያቋርጥ ጥንቃቄ አድርጉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለማስተማር ሥራችሁ የማያቋርጥ ጥንቃቄ አድርጉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አስተማሪዎች
  • በሚገባ ተረድቶ ማመን
  • ለማስተማር ሥራችሁ ተጠንቀቁ
  • የአምላክ ቃል ተማሪዎች
  • ለምናስተምራቸው ሰዎች ፍቅርና አክብሮት ማሳየት
  • ለሚያስፈልጋቸው ነገር ንቁ መሆን
  • ግለት ይኑራችሁ!
  • ‘ለማስተማር ጥበብህ’ ትኩረት ስጥ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ‘ራስህንም የሚሰሙህንም አድን’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • በፍቅር በማስተማር ኢየሱስን ምሰሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ሰዎች የክርስቶስን ትእዛዛት እንዲጠብቁ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 3/15 ገጽ 10-15

ለማስተማር ሥራችሁ የማያቋርጥ ጥንቃቄ አድርጉ

“ለራስህና ለትምህርትህ [“ለማስተማር ሥራህ፣” የ“1980 ትርጉም”] ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።”—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​16

1, 2. በዛሬው ጊዜ ቀናተኛ አስተማሪዎች በአስቸኳይ የሚፈለጉት ለምንድን ነው?

“ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴዎስ 28:​19, 20) ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው በዚህ ትእዛዝ መሠረት ሁሉም ክርስቲያኖች አስተማሪዎች ለመሆን መጣር ይገባቸዋል። ጊዜው ከማለቁ በፊት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አምላክን እንዲያውቁ የሚረዱ ቀናተኛ አስተማሪዎች ይፈለጋሉ። (ሮሜ 13:​11) ሐዋርያው ጳውሎስ “ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና” ሲል አጥብቆ መክሯል። (2 ጢሞቴዎስ 4:​2) ይህ ደግሞ በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤ ውጪ ማስተማርን የሚጠይቅ ነው። እርግጥ የስብከቱ ተልእኮ ራሱ የአምላክን መልእክት ከማስታወቅ የበለጠ ነገር ያካትታል። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ከተፈለገ ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር ያሻል።

2 የምንኖረው ‘አስጨናቂ በሆነ ዘመን’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) የሰዎች አእምሮ በዓለማዊ ፍልስፍናዎችና በሐሰት ትምህርቶች ታጥቧል። የብዙዎች “አእምሮ ጨልሞአል፤” ‘የሐፍረት ስሜታቸውም ጠፍቷል።’ (ኤፌሶን 4:​18, 19 የ1980 ትርጉም) አንዳንዶች በከባድ የስሜት ቁስል ይሠቃያሉ። አዎን፣ ሰዎች ‘እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀዋል፤ ተጥለዋልም።’ (ማቴዎስ 9:​36) ይሁንና በጥሩ የማስተማር ችሎታ ተጠቅመን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አስፈላጊ ለውጦችን እንዲያደርጉ ልንረዳቸው እንችላለን።

በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አስተማሪዎች

3. (ሀ) ኢየሱስ የሰጠው የማስተማር ተልእኮ ምንን ይጨምራል? (ለ) በጉባኤ ውስጥ የማስተማር ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለው ማን ነው?

3 በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዝግጅት አማካኝነት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በግል ለሕይወታቸው መመሪያ የሚሆን ትምህርት በማግኘት ላይ ናቸው። ሆኖም ‘ሥርና መሠረታ​ቸው ጽኑ’ እንዲሆን እነዚህ አዳዲስ ሰዎች ከተጠመቁም በኋላ ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (ኤፌሶን 3:​17) በማቴዎስ 28:​19, 20 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ኢየሱስ የሰጠውን ተልእኮ በመፈጸም አዲሶችን ወደ ይሖዋ ድርጅት ስንመራ በጉባኤ ውስጥ ከሚሰጠው ትምህርት ተጠቃሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በኤፌሶን 4:​11-13 [NW] መሠረት ወንዶች “ቅዱሳንን ለመንፈሳዊ አገልግሎት በማስተካከል የክርስቶስን አካል ለመገንባት እረኞችና አስተማሪዎች” ሆነው እንዲያገለግሉ ተሹመዋል። አንዳንድ ጊዜ የማስተማር ሥራቸው ‘ፈጽመው እየታገሡ መዝለፍን፣ መገሠጽንና መምከርን’ ይጨምራል። (2 ጢሞቴዎስ 4:​2) የአስተማሪዎች የሥራ ድርሻ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሣ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ዝርዝር ላይ አስተማሪዎችን የጠቀሰው በቀጥታ ከሐዋርያትና ከነቢያት ቀጥሎ ነበር።​—⁠1 ቆሮንቶስ 12:​28

4. የማስተማር ችሎታ ጳውሎስ በዕብራውያን 10:​24, 25 ላይ የሰጠውን ማሳሰቢያ ለመታዘዝ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

4 እርግጥ ነው፣ ሁሉም ክርስቲያኖች ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ሆነው ያገለግላሉ ማለት አይደለም። ሆኖም ሁሉም ክርስቲያኖች አንዳቸው ሌላውን ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ’ እንዲያነቃቁ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (ዕብራውያን 10:​24, 25) በስብሰባዎች ላይ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሌሎችን ሊገነቡና ሊያበረታቱ የሚችሉ በደንብ ዝግጅት የተደረገባቸውና ከልብ የመነጩ ሐሳቦችን መስጠት ይጠይቃል። በተጨማሪም ተሞክሮ ያካበቱ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከአዲሶች ጋር በመስክ አገልግሎት በሚሠማሩበት ጊዜ እውቀታቸውንና ተሞክሯቸውን በማካፈል ‘ለመልካም ሥራ ሊያነቃቋቸው’ ይችላሉ። በእነዚህም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ ሌሎች ጊዜያት ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ማካፈል ይቻላል። ለምሳሌ ያህል የጎለመሱ ሴቶች “በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ” እንዲሆኑ ተመክረዋል።​—⁠ቲቶ 2:​3

በሚገባ ተረድቶ ማመን

5, 6. (ሀ) እውነተኛው ክርስትና ከሐሰት አምልኮ የሚለየው እንዴት ነው? (ለ) አዲሶች የጥበብ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ሽማግሌዎች ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

5 በመሆኑም እውነተኛ ክርስትና የአባላቶቻቸውን አስተሳሰብ ለመቆጣጠር ከሚጥሩት ሐሰተኛ ሃይማኖቶች ፍጹም የተለየ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጨቋኝ በሆኑ ሰው ሠራሽ ወጎች አማካኝነት እያንዳንዱን የሰዎች ሕይወት ዘርፍ ለማለት ይቻላል ለመቆጣጠር ይሞክሩ ነበር። (ሉቃስ 11:​46) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ ነገር አድርገዋል።

6 ይሁን እንጂ እውነተኛ አምልኮ “በማመዛዘን ችሎታችን” ተጠቅመን የምናቀርበው “ቅዱስ አገልግሎት” ነው። (ሮሜ 12:​1) የይሖዋ አገልጋዮች ‘ተረድተውት ያመኑ’ ሰዎች ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​14) አንዳንድ ጊዜ የመሪነቱን ቦታ የያዙ ወንድሞች ጉባኤው የተስተካከለ አሠራር እንዲኖረው ለማድረግ ሲሉ አንዳንድ መመሪያዎችንና ሥርዓቶችን ማውጣት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ሆኖም ለክርስቲያን ባልደረቦቻቸው ውሳኔ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ‘መልካሙንና ክፉውን እንዲለዩ’ ያስተምሯቸዋል። (ዕብራውያን 5:​14) ሽማግሌዎች ይህንን የሚያደርጉት በመጀመሪያ ደረጃ “በእምነትና . . . በመልካም ትምህርት ቃል” ጉባኤውን በመመገብ ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​6

ለማስተማር ሥራችሁ ተጠንቀቁ

7, 8. (ሀ) መጠነኛ ችሎታ ያላቸው ሰዎች አስተማሪዎች በመሆን ሊያገለግሉ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ውጤታማ አስተማሪ ለመሆን የግል ጥረት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

7 ይሁንና ወደ አጠቃላዩ የማስተማር ተልእኳችን መለስ እንበል። በዚህ ሥራ መካፈል ልዩ ጥበብ፣ ትምህርት ወይም ችሎታ ይጠይቃልን? ላይጠይቅ ይችላል። ይህ ዓለም አቀፋዊ የማስተማር ሥራ እየተከናወነ ያለው መጠነኛ ችሎታ ባላቸው ተራ ግለሰቦች ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:​26-29) ጳውሎስ “የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ [አገልግሎቱ] በሸክላ ዕቃ [ፍጹም ባልሆነው ሥጋችን] ውስጥ አለን” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 4:​7) በዓለም ዙሪያ የሚካሄደው ይህ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ያገኘው ከፍተኛ ስኬት የይሖዋ መንፈስ ላለው ኃይል ምሥክር ነው!

8 የሆነ ሆኖ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ” ለመሆን የግል ጥረት ማድረግ ያሻል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​15) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል መክሮታል:- “ለራስህና ለትምህርትህ [“ለማስተማር ሥራህ፣” የ1980 ትርጉም] ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።” (1 ጢሞቴዎስ 4:​16) አንድ ሰው በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤ ውጪ ለሚያከናውነው የማስተማር ሥራ ጥንቃቄ የሚያደርገው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ የተወሰኑ ችሎታዎችን ማዳበር ወይም የማስተማር ዘዴዎችን ማጥናት ይጠይቃልን?

9. ከተፈጥሯዊ ችሎታ ይልቅ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

9 ኢየሱስ በታዋቂው የተራራ ስብከቱ ላይ በላቁ የማስተማር ዘዴዎች እንደተጠቀመ የተረጋገጠ ነው። ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ “ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ።” (ማቴዎስ 7:​28) እርግጥ ማናችንም ብንሆን እንደ ኢየሱስ ልናስተምር አንችልም። ይሁን እንጂ ውጤታማ አስተማሪዎች ለመሆን የግድ አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪዎች መሆን አያስፈልገንም። ኢዮብ 12:​7 እንደሚለው ‘እንስሶች’ እና “የሰማይ ወፎች” እንኳ ያለ አንደበት ሊያስተምሩ ይችላሉ! ካለን ማንኛውም ዓይነት ተፈጥሯዊ ችሎታ ወይም ክህሎት በተጨማሪ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ምን ዓይነት ሰዎች ነን ይኸውም ተማሪዎቻችን ሊኮርጁአቸው የሚችሏቸው ምን ባህርያትና ምን መንፈሳዊ ልማዶች አዳብረናል የሚለው ነው።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​11፤ ሉቃስ 6:​40

የአምላክ ቃል ተማሪዎች

10. ኢየሱስ የአምላክ ቃል ተማሪ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ የተወው እንዴት ነበር?

10 በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን እውነት የሚያስተምር አንድ ውጤታማ አስተማሪ የአምላክ ቃል ተማሪ መሆን አለበት። (ሮሜ 2:​21) ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት ወደ ግማሽ ከሚጠጉት በቀጥታ ይጠቅስ ወይም ሐሳባቸውን ይገልጽ ነበር።a በ12 ዓመት ዕድሜው “በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም” መገኘቱ የአምላክን ቃል ጠንቅቆ ያውቅ እንደነበር ያረጋግጣል። (ሉቃስ 2:​46) ኢየሱስ ትልቅ ሰው ከሆነም በኋላ የአምላክ ቃል ከሚነበብበት ምኩራብ አይጠፋም ነበር።​—⁠ሉቃስ 4:​16

11. አንድ አስተማሪ ምን ጥሩ የጥናት ልማድ ሊያዳብር ይገባል?

11 የአምላክን ቃል በጉጉት ታነብባለህን? የአምላክን ቃል በጥልቅ መመርመር ‘ይሖዋን መፍራትን ለማስተዋልና የአምላክን እውቀት ለማግኘት’ ያስችልሃል። (ምሳሌ 2:​4, 5) ስለዚህ ጥሩ የጥናት ልማድ አዳብር። በየቀኑ ከአምላክ ቃል የተወሰነ ክፍል ለማንበብ ጥረት አድርግ። (መዝሙር 1:​2) እያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትም እንደደረሰህ የማንበብ ልማድ ይኑርህ። የጉባኤ ስብሰባዎችን ትኩረት ሰጥተህ ተከታተል። ጥልቅ ምርምር ማድረግን ተማር። ‘ሁሉን ነገር በጥንቃቄ የመመርመር’ ልማድ ካዳበርክ በምታስተምርበት ጊዜ ነገሮችን ከማጋነን ወይም ትክክል ያልሆነ ነገር ከመናገር ልትቆጠብ ትችላለህ።​—⁠ሉቃስ 1:​3

ለምናስተምራቸው ሰዎች ፍቅርና አክብሮት ማሳየት

12. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን አመለካከት ነበረው?

12 ሌላው አስፈላጊ ባህርይ ለምናስተምራቸው ሰዎች ሊኖረን የሚገባው ተገቢ ዝንባሌ ነው። ፈሪሳውያን ኢየሱስን ያዳምጡ የነበሩ ሰዎችን ይንቁ ነበር። “ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው” ይሉ ነበር። (ዮሐንስ 7:​49) ሆኖም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የጠለቀ ፍቅርና አክብሮት ነበረው። እንዲህ ብሏል:- “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፣ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።” (ዮሐንስ 15:​15) ይህ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማስተማር እንቅስቃሴያቸውን እንዴት ማከናወን እንደሚገባቸው ያሳያል።

13. ጳውሎስ ስለሚያስተምራቸው ሰዎች እንዴት ይሰማው ነበር?

13 ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ከተማሪዎቹ ጋር የነበረው ግንኙነት ሞቅ ያለ የወዳጅነት ስሜት የሚንጸባረቅበት ነበር። የቆሮንቶስ ሰዎችን “በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም፤ እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና” ብሏቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 4:​15) ጳውሎስ የሚያስተምራቸውን ሰዎች እያለቀሰ የመከረበትም ጊዜ ነበር! (ሥራ 20:​31) በተጨማሪም ከፍተኛ ትዕግሥትና ደግነት አሳይቷል። ስለዚህም የተሰሎንቄን ሰዎች “ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፣ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን” ሊላቸው ችሏል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 2:​7

14. ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን በግል አሳቢነት ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

14 የኢየሱስንና የጳውሎስን ምሳሌ ትከተላለህን? ተማሪዎቻችንን ከልብ መውደዳችን በተፈጥሮ ሊኖረን የሚችለውን ማንኛውም ዓይነት ጉድለት በእጅጉ ሊያካክስ ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ከልብ እንደምናስብላቸው ይሰማቸዋልን? አብረናቸው ጊዜ በማሳለፍ እነሱን በደንብ ለማወቅ ጥረት እናደርጋለንን? አንዲት ተማሪ መንፈሳዊ እድገት እንድታደርግ ለመርዳት የተቸገረች አንዲት ክርስቲያን እህት “የሚያሳስብሽ ነገር አለ?” ስትል ተማሪዋን በደግነት ጠየቀቻት። ሴትየዋ የሚያሳስቧትንና የሚያስጨንቋትን በርካታ ነገሮች በመዘርዘር የልቧን አውጥታ መናገር ጀመረች። ይህ ፍቅራዊ ውይይት የሴትየዋ ሕይወት እንዲለወጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አደረገ። እነዚህን በመሳሰሉ ጊዜያት ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች እንዲሁም የሚያጽናኑና የሚያበረታቱ ቃላት መናገር ተገቢ ነው። (ሮሜ 15:​4) ይሁንና ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ነገር አለ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ፈጣን እድገት እያደረገ ቢሆንም ገና ያላስወገዳቸው ክርስቲያናዊ ያልሆኑ የአኗኗር ዘይቤዎች ይኖሩት ይሆናል። ስለዚህ ከግለሰቡ ጋር ከገደብ ያለፈ ማኅበራዊ ቅርርብ መፍጠር ጥበብ አይሆንም። ተገቢ የሆኑ ክርስቲያናዊ ገደቦች ሊከበሩ ይገባል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​33

15. ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን አክብሮት ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ለተማሪዎቻችን ያለን አክብሮት የግል ሕይወታቸውን ለመቆጣጠር ከመሞከር መቆጠብንም ይጨምራል። (1 ተሰሎንቄ 4:​11) ለምሳሌ ያህል በሕግ ካላገባችው ሰው ጋር አብራ የምትኖር አንዲት ሴት እናስጠና ይሆናል። ምናልባትም ልጆች ወልደው ይሆናል። የአምላክን ትክክለኛ እውቀት በማግኘቷ በይሖዋ ፊት ያላትን አቋም ለማስተካከል ትፈልጋለች። (ዕብራውያን 13:​4) ታዲያ ሰውየውን ታግባው ወይስ ትለያይ? ምናልባት እኛ ለመንፈሳዊ ነገሮች እምብዛም ወይም ምንም ፍላጎት የሌለውን ሰው ማግባት ለወደፊት እድገቷ ጋሬጣ ይሆንባታል የሚል ጽኑ እምነት ይኖረን ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ለልጆቿ ደኅንነት በመስጋት ብታገባው ይሻላል ብለን እናስብ ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ በአንድ ተማሪ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ በመግባት እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ አስተያየታችንን ለመስጠት መሞከር አክብሮትና ፍቅር የጎደለው ድርጊት ነው። ደግሞም ውሳኔዋ የሚያስከትለውን ውጤት መቀበል ያለባት ራሷ ነች። ታዲያ እንዲህ ያለችው ተማሪ ‘የማስተዋል ችሎታዋን’ ተጠቅማ ምን ማድረግ እንዳለባት የራሷን ውሳኔ እንድትወስን ማሠልጠኑ የተሻለ አይሆንም?​—⁠ዕብራውያን 5:​14 NW

16. ሽማግሌዎች ለአምላክ መንጋ ፍቅርና አክብሮት ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?

16 በተለይ የጉባኤ ሽማግሌዎች መንጋውን በፍቅርና በአክብሮት መያዛቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ ለፊልሞና ሲጽፍ “የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፣ . . . ስለ ፍቅር እለምናለሁ” ብሏል። (ፊልሞና 8, 9) አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ቅስም የሚሰብሩ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ያስፈልግም ይሆናል። ጳውሎስ “በሃይማኖት ጤናሞች እንዲሆኑ [ጥፋተኞችን] በብርቱ ውቀሳቸው” በማለት ቲቶን አጥብቆ አሳስቦታል። (ቲቶ 1:​13) ያም ሆኖ ግን የበላይ ተመልካቾች ጉባኤውን ደግነት በጎደላቸው ቃላት ላለመናገር ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። ጳውሎስ “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም” ሲል ጽፏል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:​24፤ መዝሙር 141:​3

17. ሙሴ ምን ስህተት ሠራ? ሽማግሌዎችስ ከዚህ ምን ሊማሩ ይችላሉ?

17 የበላይ ተመልካቾች የሚንከባከቡት “የእግዚአብሔርን መንጋ” መሆኑን ምንጊዜም መዘንጋት የለባቸውም። (1 ጴጥሮስ 5:​2 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ሙሴ ትሑት የነበረ ቢሆንም ይህን ባህርዩን ለጥቂት ጊዜ አጥቶ ነበረ። እስራኤላውያን “መንፈሱን አስመርረዋታልና፤ . . . በከንፈሮቹም በስንፍና ተናገረ።” (መዝሙር 106:​33) ምንም እንኳ መንጋው ጥፋተኛ ቢሆንም በዚያ መንገድ መያዙ አምላክን ቅር አሰኝቶታል። (ዘኁልቁ 20:​2-12) ዛሬም ሽማግሌዎች ተመሳሳይ የሆነ ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው መንጋውን በጥልቅ ማስተዋልና በደግነት ለማስተማርና ለማሠልጠን ጥረት ማድረግ አለባቸው። ወንድሞቻችን የተሻለ ምላሽ የሚሰጡት የመስተካከል ተስፋ እንደሌላቸው ጥፋተኞች ሲቆጠሩ ሳይሆን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ግለሰቦች በአሳቢነት ሲያዙ ነው። ሽማግሌዎች እንደሚከተለው ብሎ የተናገረውን የጳውሎስን ዓይነት አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ያስፈልጋቸዋል:- “የምናዛችሁንም አሁን እንድታደርጉ ወደ ፊትም ደግሞ እንድታደርጉ ስለ እናንተ በጌታ ታምነናል።”​—⁠2 ተሰሎንቄ 3:​4

ለሚያስፈልጋቸው ነገር ንቁ መሆን

18, 19. (ሀ) ችሎታቸው ውስን የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ለሚያስፈልጋቸው ነገር ምን ምላሽ መስጠት አለብን? (ለ) በተወሰኑ ጉዳዮች ረገድ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

18 አንድ ውጤታማ አስተማሪ የተማሪዎቹን አቅምና ችሎታ ግምት ውስጥ ያስገባል። (ከዮሐንስ 16:​12 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ ስለ መክሊቶቹ በተናገረው ምሳሌ ላይ ጌታው “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ” መብት ሰጥቶ ነበር። (ማቴዎስ 25:​15) እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ስንመራ ተመሳሳይ መሠረታዊ ሥርዓት ልንከተል እንችላለን። እርግጥ አንድን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ምክንያታዊ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቁ የሚፈለግ ነገር ነው። ይሁንና ጥሩ የማንበብ ወይም አዳዲስ ሐሳቦችን ቶሎ የመቀበል ችሎታ ያላቸው ሁሉም አለመሆናቸው ሊስተዋል ይገባል። ስለዚህ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች በጥናታቸው በፍጥነት የመግፋት ችግር ሲኖርባቸው ከአንድ ነጥብ ወደ ሌላው ነጥብ መቼ መሸጋገር እንዳለብን ለመወሰን የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም አስፈላጊ ነው። ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር የሚጠናውን ጽሑፍ በተወሰነ ፍጥነት አጥንቶ መሸፈኑ ሳይሆን ተማሪዎቹ የሚማሩትን ነገር እንዲያስተውሉ መርዳቱ ነው።​—⁠ማቴዎስ 13:​51

19 ሥላሴን ወይም ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን በመሳሰሉ ጉዳዮች ረገድ ችግር ስላለባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ተመሳሳይ ነገር ለመናገር ይቻላል። በጥናታችን ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የምርምር ጽሑፎችን መጠቀሙ በአጠቃላይ ሲታይ አስፈላጊ ባይሆንም ጠቃሚነቱ አመዝኖ ከተገኘ ግን አልፎ አልፎ እንዲህ ልናደርግ እንችላለን። የአንድ ተማሪ እድገት ሳያስፈልግ እንዳይጓተት ለማድረግ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም አስፈላጊ ነው።

ግለት ይኑራችሁ!

20. ጳውሎስ ግለትና እምነት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ በማስተማር ምሳሌ የተወው እንዴት ነበር?

20 ጳውሎስ “በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ” ብሏል። (ሮሜ 12:​11) አዎን፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራም ሆነ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ክፍል ስናቀርብ ቅንዓትና ግለት ሊኖረን ይገባል። ጳውሎስ የተሰሎንቄን ሰዎች “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና” ብሏቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 1:​5) በመሆኑም ጳውሎስና አጋሮቹ ‘የአምላክን ወንጌል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳቸውንም’ አካፍለዋቸዋል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 2:​8

21. ለማስተማር ሥራችን ያለንን የጋለ ስሜት ጠብቀን ለማቆየት የምንችለው እንዴት ነው?

21 እውነተኛ ግለት የሚመጣው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን የምንናገረውን ነገር መስማት እንደሚያስፈልጋቸው በጽኑ የምናምን ከሆነ ነው። ማንኛውንም የማስተማር ሥራ እንደ አሰልቺ ነገር አድርገን መመልከት የለብንም። ጸሐፊው ዕዝራ በዚህ ረገድ ለማስተማር ሥራው ትኩረት ሰጥቶ ነበር። “የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” (ዕዝራ 7:​10) እኛም በተመሳሳይ በጥንቃቄ በመዘጋጀትና የትምህርቱን አስፈላጊነት በማጉላት እንዲህ ልናደርግ ይገባል። እምነት እንዲጨምርልን ወደ ይሖዋ እንጸልይ። (ሉቃስ 17:​5) የምናሳየው ግለት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለእውነት ልባዊ ፍቅር እንዲያዳብሩ ሊረዳቸው ይችላል። እርግጥ የማስተማር ሥራችን የተወሰኑ የማስተማር ዘዴዎችን መጠቀምን የሚጠይቅ ነው። በሚቀጥለው ርዕሳችን ላይ አንዳንዶቹን እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 1071ን ተመልከት።

ታስታውሳለህን?

◻ በዛሬው ጊዜ ችሎታ ያላቸው ክርስቲያን አስተማሪዎች የሚፈለጉት ለምንድን ነው?

◻ ምን ዓይነት ጥሩ የጥናት ልማድ ልናዳብር እንችላለን?

◻ ለምናስተምራቸው ሰዎች ፍቅርና አክብሮት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ለሚያስፈልጋቸው ነገር ምላሽ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

◻ ሌሎችን በምናስተምርበት ወቅት ግለትና እምነት አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩ አስተማሪዎች ራሳቸውም የአምላክ ቃል ተማሪዎች ናቸው

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ የግል አሳቢነት አሳዩ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ