“ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ”
“እንግዲህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጉ።” በማቴዎስ 28:19 ላይ የሚገኘውን የኢየሱስን ትእዛዝ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በዚህ መልክ ተርጉሞታል። ሆኖም ይህ አተረጓጎም ትችት ተሰንዝሮበታል። ለምሳሌ ያህል አንድ አነስተኛ ሃይማኖታዊ መጽሔት “የግሪክኛው ጥቅስ ‘አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ ብለን እንድንተረጉም ብቻ ነው የሚያስችለን!” የሚል ሐሳብ ሰጥቷል። ይህ አባባል ትክክል ነውን?
“አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለው አተረጓጎም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከግሪክኛው ጥቅስ ቃል በቃል የተተረጎመ ነው። ታዲያ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን እያጠመቃችሁ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ብሎ ለመተርጎም የሚያስችል ምን መሠረት አለ? አገባቡ ትርጉሙን ይወስናል። “እያጠመቃችሁ” የሚለው አገላለጽ በግልጽ የሚያመለክተው ብሔራትን ሳይሆን ሰዎችን ነው። ጀርመናዊው ምሁር ሃንስ ብሩንስ እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “‘እያጠመቃችሁ’ የሚለው [ቃል] ብሔራትን የሚያመለክት አይደለም (ግሪክኛው ልዩነቱን ግልጽ ያደርገዋል) ከዚህ ይልቅ በየብሔራቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ያመለክታል።”
ከዚህም በተጨማሪ የኢየሱስ መመሪያ ሥራ ላይ የዋለበትንም መንገድ መመልከት ያስፈልጋል። ጳውሎስና በርናባስ በትንሹ እስያ በምትገኘው በደርቤን ከተማ ስላከናወኑት አገልግሎት እንዲህ የሚል እናነባለን:- “በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፣ . . . ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ።” (ሥራ 14:21) ጳውሎስና በርናባስ በደርቤ ከተማ ያሉትን ሰዎች ባጠቃላይ ሳይሆን በዚያች ከተማ የሚኖሩ የተወሰኑ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዳደረጉ ማስተዋል ያስፈልጋል።
በተመሳሳይ መንገድ የራእይ መጽሐፍ ስለ መጨረሻው ዘመን አስቀድሞ ሲናገር የአምላክ አገልጋዮች የሚሆኑት በየብሔራቱ ያሉ ሰዎች ባጠቃላይ ሳይሆኑ “ከሕዝብና [“ከብሔራትና፣” NW] ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ [“የተውጣጡ፣” NW] እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሆኑ ተናግሯል። (ራእይ 7:9፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ይህም በመሆኑ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ‘በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች’ ትክክለኛ ትርጉም መሆኑ ተረጋግጧል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16