-
ምሥራቹ እየተሰበከ ያለው እንዴት ነው?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 21
ምሥራቹ እየተሰበከ ያለው እንዴት ነው?
በቅርቡ ይሖዋ እሱ ባቋቋመው መንግሥት አማካኝነት ችግሮቻችንን ሁሉ ያስወግድልናል። ይህ ሁሉም ሰው ሊያውቀው የሚገባ አስደሳች ዜና ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ ይህን መልእክት ለሌሎች እንዲናገሩ አዟል! (ማቴዎስ 28:19, 20) የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የሰጠውን ይህን ትእዛዝ እየፈጸሙ ያሉት እንዴት ነው?
1. በማቴዎስ 24:14 ላይ ያለው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) እኛ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ አስፈላጊ ሥራ መካፈል ያስደስተናል። በዓለም ዙሪያ ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ምሥራቹን እየሰበክን ነው! መጠነ ሰፊ የሆነውን ይህን ሥራ ለማከናወን ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግና በሚገባ የተደራጁ መሆን ያስፈልጋል። ያለይሖዋ እርዳታ ይህን ሥራ ማከናወን አይቻልም።
2. ለሰዎች ለመስበክ የትኞቹን ዘዴዎች እንጠቀማለን?
ሰዎችን በምናገኝባቸው ቦታዎች ሁሉ እንሰብካለን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም “ከቤት ወደ ቤት” እየሄድን ምሥራቹን እንናገራለን። (የሐዋርያት ሥራ 5:42) ይህ የስብከት ዘዴ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለማግኘት ያስችለናል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ቤታቸው ስለማይገኙ በሌሎች ቦታዎችም እንሰብካለን። ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዎች ለመናገር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች ሁሉ ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን።
3. ምሥራቹን የመስበክ ኃላፊነት ያለበት ማን ነው?
እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ምሥራቹን ለሌሎች የመናገር ኃላፊነት አለባቸው። ይህን ኃላፊነታችንን በቁም ነገር እንመለከተዋለን። አቅማችን እስከፈቀደው ድረስ ምሥራቹን ለመስበክ ጥረት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን የሰዎችን ሕይወት እንደሚያድን እንገነዘባለን። (1 ጢሞቴዎስ 4:16ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” ይላል፤ ስለዚህ ይህን ሥራ ስናከናውን ምንም ዓይነት ክፍያ አንቀበልም። (ማቴዎስ 10:7, 8) አንዳንዶች የምንሰብከውን መልእክት ባይቀበሉም መስበካችንን እንቀጥላለን። ምክንያቱም የስብከቱ ሥራ የአምልኳችን ክፍል ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ያስደስተዋል።
ጠለቅ ያለ ጥናት
የይሖዋ ምሥክሮች እያከናወኑ ስላሉት ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራና ይሖዋ ይህን ሥራ እየደገፈ ያለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
በዓለም ዙሪያ መስበክ፦ (ሀ) ኮስታ ሪካ፣ (ለ) ዩናይትድ ስቴትስ፣ (ሐ) ቤኒን፣ (መ) ታይላንድ፣ (ሠ) ያፕ፣ (ረ) ስዊድን
4. ሁሉም ሰዎች ምሥራቹ እንዲደርሳቸው ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን
የይሖዋ ምሥክሮች በሁሉም ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ ልዩ ጥረት ያደርጋሉ። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን ለመስበክ ከሚያደርጉት ጥረት ጋር በተያያዘ አንተን የሚያስገርምህ ምንድን ነው?
ማቴዎስ 22:39ን እና ሮም 10:13-15ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
የስብከቱ ሥራችን ሰዎችን እንደምንወድ የሚያሳየው እንዴት ነው?
ይሖዋ ምሥራቹን ለሚሰብኩ ሰዎች ምን አመለካከት አለው?—ሮም 10:15ን ተመልከት።
5. የምንሠራው ከአምላክ ጋር ነው
ብዙ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ሥራችንን የሚመራው ይሖዋ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ፖል የተባለ በኒው ዚላንድ የሚኖር ወንድም አንድ ቀን ከሰዓት ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል አንዲት ሴት አገኘ። ሴትየዋ በዚያኑ ዕለት ይሖዋ የሚለውን ስም ተጠቅማ ወደ አምላክ የጸለየች ሲሆን አንድ ሰው መጥቶ እንዲያነጋግራት አምላክን ለምናው ነበር። ፖል “ይህ ከሆነ ከሦስት ሰዓት በኋላ ወደ ቤቷ ሄድኩ” ሲል ተናግሯል።
አንደኛ ቆሮንቶስ 3:9ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ፖል እንዳጋጠመው ዓይነት ተሞክሮዎች ይሖዋ የስብከቱን ሥራ እየመራው እንዳለ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
የሐዋርያት ሥራ 1:8ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
የስብከቱን ሥራ ለመሥራት የይሖዋ እርዳታ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
ይህን ታውቅ ነበር?
በሳምንቱ መሃል በምናደርገው ስብሰባ ላይ እንዴት መስበክ እንዳለብን የሚያሳይ ሥልጠና ይሰጠናል። በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ የምታውቅ ከሆነ ስለሚሰጠው ሥልጠና ምን ተሰማህ?
6. አምላክ እንድንሰብክ የሰጠንን ትእዛዝ እንፈጽማለን
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተቃዋሚዎች የኢየሱስ ተከታዮች የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ ለማስቆም ጥረት አድርገው ነበር። በዚያን ጊዜ የነበሩት ክርስቲያኖች ‘ምሥራቹ በሕግ የጸና እንዲሆን በማድረግ’ የመስበክ መብታቸውን ለማስጠበቅ ሞክረዋል። (ፊልጵስዩስ 1:7) በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም እንዲህ ያደርጋሉ።a
የሐዋርያት ሥራ 5:27-42ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሰዎች ቤት እየሄዱ የሚሰብኩት ለምንድን ነው?”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ማጠቃለያ
ኢየሱስ ተከታዮቹን ለሁሉም ብሔራት ምሥራቹን እንዲሰብኩ አዟቸዋል። ይሖዋ ሕዝቦቹ ይህን ሥራ እንዲያከናውኑ እየረዳቸው ነው።
ክለሳ
ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ እየተሰበከ ያለው እንዴት ነው?
ምሥራቹን መስበካችን ሰዎችን እንደምንወድ የሚያሳየው እንዴት ነው?
የስብከቱ ሥራ አስደሳች እንደሆነ ይሰማሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ምርምር አድርግ
የይሖዋ ምሥክሮች በትላልቅ ከተሞች ለሚኖሩ ሰዎች የሚሰብኩት እንዴት ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች ለስደተኞች ለመስበክ ምን ጥረት አድርገዋል?
ሕይወቷን ሙሉ በስብከቱ ሥራ ያሳለፈች አንዲት ሴት ይህ ሥራ የሚያስደስታት ለምን እንደሆነ ስትናገር ተመልከት።
በፍርድ ቤት ያገኘናቸው አንዳንድ ድሎች የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት የረዱን እንዴት ነው?
“የመንግሥቱ ሰባኪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይላቸው አደረጉ” (የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! ምዕራፍ 13)
a ለሰዎች እንድንሰብክ ያዘዘን አምላክ ነው። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን ለመስበክ የባለሥልጣናት ፈቃድ አያስፈልጋቸውም።
-
-
ጥምቀት—ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግብ!ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 23
ጥምቀት—ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግብ!
ኢየሱስ ክርስቲያኖች መጠመቅ እንዳለባቸው አስተምሯል። (ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ።) ይሁንና ጥምቀት ምንድን ነው? በተጨማሪም አንድ ሰው እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ ይኖርበታል?
1. ጥምቀት ምንድን ነው?
“መጠመቅ” የሚለው ቃል ውኃ ውስጥ “መጥለቅ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የተወሰደ ነው። ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ከጠለቀ በኋላ “ከውኃው እንደወጣ” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማርቆስ 1:9, 10) በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚጠመቁት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመግባት ወይም በመጥለቅ ነው።
2. አንድ ሰው መጠመቁ ምን ያሳያል?
አንድ ሰው መጠመቁ ሕይወቱን ለይሖዋ አምላክ ለመስጠት እንደወሰነ ያሳያል። ግለሰቡ ይህን ውሳኔ የሚያደርገው እንዴት ነው? ከመጠመቁ በፊት በግሉ ወደ ይሖዋ በመጸለይ እሱን ለዘላለም ማገልገል እንደሚፈልግ ይነግረዋል። ይሖዋን ብቻ ለማምለክና በሕይወቱ ውስጥ ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ ለመስጠት ቃል ይገባል። ‘ራሱን ለመካድ’ እንዲሁም የኢየሱስን ትምህርትና ምሳሌ ‘ያለማቋረጥ ለመከተል’ ይወስናል። (ማቴዎስ 16:24) ሕይወቱን ለአምላክ ለመስጠት መወሰኑና መጠመቁ ከይሖዋና ከሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለዋል።
3. አንድ ሰው ለጥምቀት ብቁ እንዲሆን ምን ማድረግ ይኖርበታል?
ከመጠመቅህ በፊት ስለ ይሖዋ መማርና በእሱ ላይ ጠንካራ እምነት መገንባት ይኖርብሃል። (ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።) እውቀትህና እምነትህ እያደገ ሲሄድ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርም ይጨምራል። ይህ ደግሞ ስለ እሱ ለመስበክና እሱ ባወጣቸው መሥፈርቶች ለመመራት እንድትነሳሳ ያደርግሃል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2፤ 1 ዮሐንስ 5:3) አንድ ሰው ‘ለይሖዋ በሚገባ ሁኔታ መመላለስና እሱን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት’ ሲችል ሕይወቱን ለአምላክ ለመስጠትና ለመጠመቅ መወሰኑ አይቀርም።—ቆላስይስ 1:9, 10a
ጠለቅ ያለ ጥናት
ከኢየሱስ ጥምቀት ምን ትምህርት እንደምናገኝና አንድ ሰው ለዚህ ወሳኝ እርምጃ መዘጋጀት የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
4. ከኢየሱስ ጥምቀት ትምህርት ማግኘት እንችላለን
ስለ ኢየሱስ ጥምቀት ይበልጥ ለማወቅ ማቴዎስ 3:13-17ን አንብቡ። ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ የተጠመቀው በሕፃንነቱ ነው?
የተጠመቀው እንዴት ነው? እንዲሁ ውኃ በመረጨት ነው?
ኢየሱስ በምድር ላይ አምላክ የሰጠውን ልዩ ተልእኮ ማከናወን የጀመረው ከተጠመቀ በኋላ ነው። ሉቃስ 3:21-23ን እና ዮሐንስ 6:38ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሰጠው ለየትኛው ሥራ ነው?
5. ጥምቀት ሊደረስበት የሚችል ግብ ነው
ሕይወትህን ለአምላክ ስለ መወሰንና ስለ መጠመቅ ስታስብ መጀመሪያ ላይ ፍርሃት ሊያድርብህ ይችላል። ሆኖም ይሖዋን ይበልጥ እያወቅከው ስትሄድ ይህን ትልቅ ውሳኔ ለማድረግ ብቁ እንደሆንክ ይሰማሃል። ይህን ውሳኔ ያደረጉ ሰዎችን ተሞክሮ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ።
ዮሐንስ 17:3ን እና ያዕቆብ 1:5ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
አንድ ሰው ለመጠመቅ ብቁ እንዲሆን ምን ሊረዳው ይችላል?
ሀ. ለዘላለም ልናገለግለው እንደምንፈልግ ለይሖዋ በጸሎት በመንገር ሕይወታችንን ለእሱ ለመስጠት እንወስናለን
ለ. ስንጠመቅ ሕይወታችንን ለአምላክ ለመስጠት እንደወሰንን ለሌሎች እናሳያለን
6. ስንጠመቅ የይሖዋ ቤተሰብ አባል እንሆናለን
ስንጠመቅ አንድነት ያለው ዓለም አቀፍ ቤተሰብ አባል እንሆናለን። ያደግንበት ቦታ ወይም የኋላ ታሪካችን የተለያየ ቢሆንም የምናምንባቸው ነገሮችም ሆኑ የምንመራባቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተመሳሳይ ናቸው። መዝሙር 25:14ን እና 1 ጴጥሮስ 2:17ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ጥምቀት አንድ ሰው ከይሖዋ ጋርም ሆነ ከሌሎች የይሖዋ አገልጋዮች ጋር ባለው ዝምድና ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ለመጠመቅ ዝግጁ አይደለሁም።”
አንተስ እንዲህ ይሰማሃል? ያም ሆኖ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ መጣጣርህ አስፈላጊ እንደሆነ ታምናለህ?
ማጠቃለያ
ኢየሱስ ክርስቲያኖች መጠመቅ እንዳለባቸው አስተምሯል። አንድ ሰው እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት መገንባት፣ በእሱ መሥፈርቶች መመራትና ሕይወቱን ለእሱ ለመስጠት መወሰን አለበት።
ክለሳ
ጥምቀት ምንድን ነው? መጠመቅ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
አንድ ሰው መጠመቁ ምን ያሳያል?
አንድ ሰው ሕይወቱን ለአምላክ ለመስጠት ከመወሰኑና ከመጠመቁ በፊት የትኞቹን ነገሮች ማድረግ አለበት?
ምርምር አድርግ
ጥምቀት ምንድን ነው? ብዙዎች ስለ ጥምቀት ምን የተሳሳተ አመለካከት አላቸው?
ለመጠመቅ የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ማሟላት የሚቻለው እንዴት ነው?
አንድ ሰው ለመጠመቅ የተነሳሳበትን ምክንያት አስመልክቶ ምን እንዳለ አንብብ።
“እውነቱ ምን እንደሆነ ራሴ እንዳረጋግጥ ፈልገው ነበር” (መጠበቂያ ግንብ የካቲት 1, 2013)
ጥምቀት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግብ የሆነው ለምንድን ነው? እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ መዘጋጀት የምትችለውስ እንዴት ነው?
“መጠመቅ ይኖርብኝ ይሆን?” (ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 37)
a አንድ ሰው ከዚህ በፊት በሌላ ሃይማኖት ውስጥ ተጠምቆ የነበረ ቢሆንም እንኳ እንደገና መጠመቅ ያስፈልገዋል። ለምን? ምክንያቱም ቀደም ሲል የተጠመቀበት ሃይማኖት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አያስተምርም።—የሐዋርያት ሥራ 19:1-5ን እና ምዕራፍ 13ን ተመልከት።
-