ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
ለመጨረሻ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ የታየባቸው ጊዜያትና የ33 እዘአ የጴንጤቆስጤ ዕለት
አንድ ወቅት ላይ ኢየሱስ ከአሥራ አንዱ ሐዋርያቱ ጋር በገሊላ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ እንዲገናኙ ዝግጅት አደረገ። ሌሎች ደቀመዛሙርትም ስለ ስብሰባው ተነግሯቸው ኖሮ ከ500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተሰበሰቡ። ኢየሱስ ተገልጦ ሊያስተምራቸው ሲጀምር እንዴት ዓይነት አስደሳች ስብሰባ ሆነላቸው!
ኢየሱስ ከተናገራቸው ነገሮች መካከል አምላክ በሰማይና በምድር ሥልጣን እንደሰጠው የሚገልጽ ነበር። “ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው” በማለት በጥብቅ አሳሰባቸው።
እስቲ አስበው! ደቀመዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንዲካፈሉ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ሳይቀሩ ይህንን ትዕዛዝ ተቀብለዋል። ተቃዋሚዎች የስብከትና ደቀመዛሙርት የማድረግ ሥራቸውን ለማስቆም ይጥራሉ። ኢየሱስ ግን “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ያጽናናቸዋል። አገልግሎታቸውን እንዲፈጽሙ ለመርዳት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከደቀመዛሙርቱ ጋር ይሆናል።
ከትንሣኤው በኋላ ኢየሱስ ሕያው መሆኑን ለ40 ቀን ያህል ያሳያቸዋል። በእነዚህ በተገለጠባቸው ጊዜያት ስለ አምላክ መንግሥትና የሱ ደቀመዛሙርት እንደመሆናቸው መጠን ኃላፊነቶቻቸው ምን እንደሆኑ በማሳሰብ ያስተምራቸዋል። በአንድ ወቅት ላይ የማያምን ለነበረው ግማሽ ወንድሙ ለሆነው ለያዕቆብም ይገለጥለትና እሱ በእርግጥም ክርስቶስ መሆኑን ያሳምነዋል።
ሐዋርያቱ ገና በገሊላ ሳሉ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ ሳይነግራቸው አልቀረም። እዚያ ባገኛቸው ጊዜ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ። ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” ይላቸዋል።
ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር እንደገና ይገናኝና በደብረዘይት አቀበት እስከሚገኘው እስከ ቢታንያ ድረስ ከከተማ አውጥቶ ይወስዳቸዋል። የሚገርመው ነገር ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደሚሄድ ብዙ ቢነግራቸውም መንግሥቱ በምድር ላይ ትቋቋማለች ብለው ገና ያምናሉ። ስለዚህም “ጌታ ሆይ በዚህ ወራት ለእሥራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት።
የተሳሳተ ግንዛቤያቸውን ለማረም እንደገና ከመሞከር ይልቅ “አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጠም” በማለት ይመልስላቸዋል። ከዚያም ሊሠሩት ስለሚገባው ሥራ በድጋሚ ጠበቅ በማድረግ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ። በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ይላቸዋል።
ገና እየተመለከቱት ሳሉም ኢየሱስ ወደ ሰማይ መውጣት ይጀምራል። ደመናም ተቀብላ ከዓይናቸው ትሰውረዋለች። ለብሶት የነበረውን ሥጋዊ አካል ትቶ መንፈሳዊ አካል በመሆን ወደ ሰማይ አረገ። አሥራ አንዱ ገና ወደ ሰማይ ሲመለከቱ ሁለት ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሰዎች ባጠገባቸው ቆሙ። እነዚህ ሥጋዊ አካል ለብሰው የተገለጡ መላእክት “የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ (በዚሁ ዓይነት) ይመጣል” አሏቸው።
ኢየሱስ ምድርን የለቀቀበት ሁኔታ ሕዝብ ሳያውቅና ታማኝ ተከታዮቹ ብቻ እየተመለከቱ ነው። ስለዚህ በተመሳሳይ ሁኔታ ሕዝብ በማያውቅበትና የሱ ታማኝ ተከታዮች ብቻ መመለሱንና በመንግሥት ሥልጣን ላይ መገኘትን እንደጀመረ ሊያስተውሉ በሚችሉበት ሁኔታ ይመለሳል።
አሁን ደቀመዛሙርቱ የደብረዘይትን ተራራ ወርደው የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግረው እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ይመለሳሉ። ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት እዚያው ይቆያሉ። ከአሥር ቀናት በኋላ የ33 እዘአ የአይሁድ በዓለ ሃምሳ ዕለት 120 የሚያህሉ ደቀመዛሙርት በኢየሩሳሌም በሰገነት ላይ ተሰብስበው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ ዐውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣና ቤቱን ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው። በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው። መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሣኖች ይናገሩ ጀመር። ይህ ኢየሱስ ተስፋ የሰጠው የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ነው።—ማቴዎስ 28:16-20፤ ሉቃስ 24:49-52፤ 1 ቆሮንቶስ 15:5-7፤ ሥራ 1:3-15፤ 2:1-4
◆ በገሊላ ተራራ ላይ ኢየሱስ የመሰነባበቻ ትዕዛዝ የሰጠው ለማነው? እነዚህ ትእዛዞችስ ምንድናቸው?
◆ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ ምን ማጽናኛ ሰጣቸው? ከእነሱ ጋር የሚኖረውስ እንዴት ነው?
◆ ከትንሣኤው በኋላ ኢየሱስ ለምን ያህል ጊዜ ታያቸው? ምንስ ያስተምራቸዋል?
◆ ከኢየሱስ ሞት በፊት ደቀመዝሙር ላልነበረው ለማነው ኢየሱስ የተገለጠለት?
◆ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ምን ሁለት የመጨረሻ ስብሰባዎች አደረገ? በእነዚህ ሁለት ወቅቶችስ ምን ተፈጸመ?
◆ ኢየሱስ በሄደበት በዚያው መንገድ የሚመለሰው እንዴት ነው?
◆ በ33 እዘአ ጴንጠቆስጤ ዕለት ምን ሆነ?