የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ijwbq ርዕስ 149
  • “ዓይን ስለ ዓይን” ሲባል ምን ማለት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ዓይን ስለ ዓይን” ሲባል ምን ማለት ነው?
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
  • “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ዓላማው ምን ነበር?
  • “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ በክርስቲያኖች ላይ ይሠራል?
  • “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለውን ሕግ በተመለከተ የተሳሳቱ አመለካከቶች
  • ስለ ዓይን የተሰጠ ጥበብ ያዘለ ምክር
    ንቁ!—2012
  • ጤናማ ዓይን ይኑራችሁ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2004
  • ሌላኛውን ጉንጭ ማዞር ሲባል ምን ማለት ነው?
    ንቁ!—2010
  • ዓይን ለዓይን ለመተያየት በመጣር ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2006
ለተጨማሪ መረጃ
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ijwbq ርዕስ 149
የአንድ ሰው ዓይን

“ዓይን ስለ ዓይን” ሲባል ምን ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ትእዛዝ አምላክ በሙሴ በኩል ለጥንት እስራኤላውያን ከሰጣቸው ሕግ አንዱ ነው፤ ኢየሱስም በተራራው ስብከቱ ላይ ጠቅሶታል። (ማቴዎስ 5:38፤ ዘፀአት 21:24, 25፤ ዘዳግም 19:21) ይህ ሕግ ለጥፋተኞች የሚሰጠው ፍርድ ከጥፋታቸው ጋር የሚመጣጠን መሆን እንዳለበት ያሳያል።a

ይህ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆነው አንድ ሰው በሌላው ላይ ሆን ብሎ ጉዳት ሲያደርስ ነው። እንደዚህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽምን ሰው በተመለከተ የሙሴ ሕግ እንዲህ ይላል፦ “ስብራት ስለ ስብራት፣ ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ ይሁን፤ በሰውየው ላይ ያደረሰው ዓይነት ጉዳት በእሱ ላይ እንዲደርስ ይደረግ።”—ዘሌዋውያን 24:20

  • “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ዓላማው ምን ነበር?

  • “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ በክርስቲያኖች ላይ ይሠራል?

  • “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለውን ሕግ በተመለከተ የተሳሳቱ አመለካከቶች

  • ኢየሱስ የተሳሳተውን አመለካከት አርሟል

“ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ዓላማው ምን ነበር?

“ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ሰዎች ሲበደሉ የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ የሚፈቅድ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ፣ የተሾሙ ዳኞች በጣም ጥብቅ ወይም ልል ሳይሆኑ ተገቢ የሆነ የቅጣት ፍርድ እንዲያስተላልፉ የሚረዳ ነው።

ከዚህም ሌላ ሕጉ በሌሎች ላይ ሆን ብለው ጉዳት ለሚያደርሱ ወይም ይህን ለማድረግ ለሚያሴሩ ሰዎች እንደ ማስጠንቀቂያ ያገለግል ነበር። ሕጉ እንዲህ ይላል፦ “ሌሎችም ይህን [አምላክ የወሰደውን ፍትሐዊ እርምጃ] ሲሰሙ ይፈራሉ፤ በመካከልህም እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ፈጽሞ ዳግመኛ አያደርጉም።”—ዘዳግም 19:20

“ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ በክርስቲያኖች ላይ ይሠራል?

አይሠራም፤ ክርስቲያኖች በዚህ ሕግ እንዲመሩ አይጠበቅባቸውም። “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ደንብ የሙሴ ሕግ ክፍል ሲሆን የሙሴ ሕግ ደግሞ ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ ሲሞት ተወግዷል።—ሮም 10:4

ያም ቢሆን ሕጉ ስለ አምላክ አስተሳሰብ ለማወቅ ያስችለናል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለፍትሕ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ እንማራለን። (መዝሙር 89:14) እንዲሁም ከፍትሕ ጋር በተያያዘ የአምላክ መሥፈርት ምን እንደሆነ ይኸውም ጥፋት የሠሩ ሰዎች “በተገቢው መጠን” መቀጣት እንዳለባቸው ይጠቁማል።—ኤርምያስ 30:11

“ዓይን ስለ ዓይን” የሚለውን ሕግ በተመለከተ የተሳሳቱ አመለካከቶች

የተሳሳተ አመለካከት፦ “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ነው።

እውነታው፦ ሕጉ ፍትሕ እንዲፈጸም ሲባል ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ቅጣት እንዲበየን አይፈቅድም። ከዚህ ይልቅ በሕጉ መሠረት፣ ቅጣት ከመበየኑ በፊት ብቃት ያላቸው ዳኞች ጉዳዩን መመርመር እንዲሁም ጥፋቱ ሆን ተብሎ የተሠራ መሆን አለመሆኑን ማጣራት ይኖርባቸዋል፤ ሕጉ በትክክል ተግባራዊ ሆኗል ሊባል የሚችለው እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው። (ዘፀአት 21:28-30፤ ዘኁልቁ 35:22-25) “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ከተፈጸመው ጥፋት ጋር የማይመጣጠን ቅጣት እንዳይተላለፍ ይረዳል።

የተሳሳተ አመለካከት፦ “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ሕግ ማብቂያ የሌለው በቀልን ያበረታታል።

እውነታው፦ የሙሴ ሕግ “የሕዝብህን ልጆች አትበቀል፤ በእነሱም ላይ ቂም አትያዝ” ይላል። (ዘሌዋውያን 19:18) ሕጉ ሰዎች የራሳቸውን የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ ከማበረታታት ይልቅ በአምላክና ፍትሕን ለማስፈን ሲል ባቋቋመው የሕግ ሥርዓት ላይ እንዲተማመኑ ያበረታታ ነበር።—ዘዳግም 32:35

ኢየሱስ የተሳሳተውን አመለካከት አርሟል

ኢየሱስ “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለውን ሕግ አንዳንዶች በተሳሳተ መንገድ እንደተረዱት አውቆ ነበር። በመሆኑም እንዲህ በማለት አርሟቸዋል፦ “‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ክፉን ሰው አትቃወሙት፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት።”—ማቴዎስ 5:38, 39

ኢየሱስ “እንደተባለ ሰምታችኋል” ማለቱን ልብ እንበል። ኢየሱስ ይህን ሲል፣ አጸፋ መመለስ ተገቢ እንደሆነ ስለሚያስተምሩ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች መናገሩ ሳይሆን አይቀርም። አዳም ክላርክ የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “አይሁድ ይህን ሕግ [ዓይን ስለ ዓይን የሚለውን] . . . የግል ቅራኔዎቻቸውንና በቂም በቀል መንፈስ ተነሳስተው የሚፈጽሟቸውን የተለያዩ የግፍ ተግባሮች ተገቢ አስመስለው ለማቅረብ እንደ ምክንያት አድርገው ሳይጠቀሙበት አልቀሩም።” እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በቀልን በማበረታታት የአምላክን ሕግ አጣመዋል።—ማርቆስ 7:13

ከእነዚህ ሰዎች በተቃራኒ ኢየሱስ በአምላክ ሕጎች ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ባሕርይ ፍቅር መሆኑን ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “‘አምላክህን ይሖዋን . . . ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል። መላው ሕግም ሆነ የነቢያት ቃል በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተመሠረቱ ናቸው።” (ማቴዎስ 22:37-40) ኢየሱስ የእውነተኛ ተከታዮቹ መለያ እንደሚሆን የጠቀሰው ፍቅርን እንጂ በቀልን አይደለም።—ዮሐንስ 13:34, 35

a ይህ መሠረታዊ ሐሳብ፣ አንዳንድ ጊዜ በላቲን ሌክስ ታሊዮኒስ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በአንዳንድ የጥንት ማኅበረሰቦች የሕግ ሥርዓት ውስጥም ይገኛል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ