የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 4/1 ገጽ 27-29
  • የአንባብያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባብያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ታስታውሳለህን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • የቄሣርን ለቄሣር ማስረከብ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • በኢፍትሐዊነቱ አቻ የማይገኝለት የፍርድ ሂደት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ፍትሐዊ ነበር?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 4/1 ገጽ 27-29

የአንባብያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን በእማኝ ዳኝነት እንዲያገለግል ጥሪ ቢቀርብለት ምን ማድረግ ይገባዋል?

በአንዳንድ አገሮች ከሕዝብ የተውጣጡ ሰዎች የሚሳተፉበት እማኝ ዳኝነት የፍትሕ መዋቅሩ አካል ሆኖ ያገለግላል። ይህ አሠራር በሰፊው በተለመደበት አካባቢ የሚኖር አንድ ክርስቲያን በእማኝ ዳኝነት እንዲያገለግል ጥሪ ሲደርሰው ምን ምላሽ እንደሚሰጥ ራሱ መወሰን ይኖርበታል። ብዙ ክርስቲያኖች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎም በዱራ ሜዳ እንዲገኙ ከባቢሎን መንግሥት የመጣላቸውን መመሪያ መቀበላቸው እንዲሁም ዮሴፍና ማርያም የሮማ ባለ ሥልጣናትን ትእዛዝ ሰምተው ወደ ቤተ ልሔም መሄዳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በዚያ መገኘቱን እንደማይከለክሉ ያሳያል ብለው በቅን ሕሊና ደምድመዋል። (ዳንኤል 3:​1-12፤ ሉቃስ 2:​1-4) ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግምት ውስጥ ሊያስገቧቸው የሚችሉ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ።

እማኝ ዳኝነት በሁሉም አገሮች የተለመደ አሠራር አይደለም። በአንዳንድ አገሮች የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ክሶች የሚታዩት መንግሥት ባቆመው ዳኛ ወይም በዳኞች ቡድን [ፓነል] ነው። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ በሰፊው የተለመደው ባሕላዊ የመተዳደሪያ ደንብ [ያልተጻፈ ሕግ] ሆኖ እማኝ ዳኝነት የፍትሕ ሂደቱ አካል በመሆን ያገለግላል። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች እማኝ ዳኞች እንዴት እንደሚመረጡና ሥራቸው ምን እንደሆነ ያላቸው ግንዛቤ በጣም ውስን ነው። በመሆኑም ይህን ጉዳይ ጠቅለል አድርገን መመልከታችን ለእማኝ ዳኝነት የቀረበልህን ጥሪ ለመቀበል ወይም ላለመቀበል እንድትወስን ይረዳሃል።

የአምላክ ሕዝቦች ታላቁ ፈራጅ ይሖዋ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (ኢሳይያስ 33:​22) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ በሐቅ የሚሠሩና የማያዳሉ ተሞክሮ ያላቸው ወንዶች አለመግባባቶችን ለመፍታትና በሕጉ ላይ ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በዳኝነት ይቀመጡ ነበር። (ዘጸአት 18:​13-22፤ ዘሌዋውያን 19:​15፤ ዘዳግም 21:​18-21) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ዘመን የፍርድ ጉዳዮች የሚከናወኑት በአይሁዳውያኑ ከፍተኛ ሸንጎ በሳንሄድሪን ነበር። (ማርቆስ 15:​1፤ ሥራ 5:​27-34) የቀሩት አይሁዳውያን ከሕዝብ የተውጣጡ አባላት ባሉት እማኝ ዳኝነት ውስጥ የሚያገለግሉበት ዝግጅት አልነበረም።

ሌሎች አገሮች ግን ከሕዝብ የተውጣጡ አባላት ባሉት የእማኝ ዳኝነት ሥርዓት ይጠቀሙ ነበር። ሶቅራጥስ በ501 እማኝ ዳኞች ፊት ተከሶ ቀርቦ ነበር። በሮማ ሪፖብሊክም ውስጥ እማኝ ዳኝነት የነበረ ቢሆንም በኋላ በንጉሠ ነገሥታቱ የግዛት ዘመን እንዲቀር ተደርጓል። ከጊዜ በኋላ የእንግሊዙ ንጉሥ ሄንሪ ሦስተኛ ተከሳሹ በጎረቤቶቹ እንዲዳኝ ዝግጅት አድርገው ነበር። ከተከሳሹ ጋር ትውውቅ ስለሚኖራቸው ግለሰቡ በሌላ የፍርድ ሂደት ውስጥ ሙግት አለዚያም ትግል ገጥሞ ንጹሕ መሆኑን ለማረጋገጥ ከሚሞክር ይልቅ የእነርሱ ዳኝነት ይቀልለታል ተብሎ ይታሰብ ነበር። እየቆየ ሲሄድ የእማኝ ዳኝነቱ ሥርዓት ተቀየረና ከሕዝብ የተውጣጡ ሰዎች ያሉበት አንድ ቡድን ጉዳዩን ሰምቶ በማስረጃ ላይ የተደገፈ ብያኔ የሚያሳልፍበት ዝግጅት ሆነ። ማስረጃዎችን በተመለከተ አንድ ሙያውን የሚያውቅ ዳኛ ይመራቸው ነበር።

በዳኝነቱ ዓይነት፣ በአባላቱ ብዛትና በውሳኔው ሂደት ረገድ ልዩነት አለ። ለምሳሌ ያህል ከ12 እስከ 23 የሚደርሱ አባላት ያሉት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛው የእማኝ ዳኝነት [ግራንድ ጁሪ] ግለሰቡን በወንጀሉ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ማስረጃ መኖር አለመኖሩን ይገመግማል፤ ግለሰቡ ከወንጀል ነፃ ነው ወይም ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል የሚል ብያኔ አያስተላልፍም። በተመሳሳይም ከሕዝብ ባለ ሥልጣናት በተውጣጡ ሰዎች የሚዋቀረው የእማኝ ዳኝነት (የምርመራ ዳኝነት) [ኮሮነርስ ጁሪ] አባላቱ ወንጀል ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለውን ጉዳይ ለማጣራት ማስረጃዎችን ይመረምራሉ።

አብዛኞቹ ሰዎች ስለ እማኝ ዳኝነት ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጣላቸው ከሕዝብ መሃል ተውጣጥተው የተሰየሙ 12 ሰዎች የፍትሐ ብሔር ወይም የወንጀል ክሶችን በተመለከተ ምሥክሮችን ካዳመጡ በኋላ ግለሰቡ ጥፋተኛ ነው ወይም ነፃ ነው ብለው የሚፈርዱበት ዳኝነት ነው። ይህ ከከፍተኛው እማኝ ዳኝነት [ግራንድ ጁሪ] ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ የእማኝ ዳኝነት ሥርዓት [ፔቲት ጁሪ] ነው። በአብዛኛው ፍርድ ቤቱ በምርጫ ወቅት ድምፅ ለመስጠት ከተመዘገቡት መሐል የመንጃ ፈቃድ ያላቸውና የመሳሰሉትን ሰዎች በእማኝ ዳኝነት ለማገልገል እንዲቀርቡ ጥሪ ይልካል። በወንጀል ድርጊት የተከሰሱ ወይም የአእምሮ ሕሙማንና የመሳሰሉት ግለሰቦች ወዲያውኑ ውድቅ ሊደረጉ ይችላሉ። እንደየአገሩ ሕግ ቢለያይም ዶክተሮች፣ ቀሳውስት፣ ጠበቆች ወይም የትናንሽ ንግድ ባለቤቶች ከዚህ ኃላፊነት ነፃ ለመሆን ሊጠይቁ ይችላሉ። (አንዳንዶችም ከሕሊናቸው የተነሣ በእማኝ ዳኝነት ለማገልገል ስለማይፈቅዱ ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ።) ይሁንና ባለ ሥልጣኖች ሁሉም ሰው (በተወሰነ ዓመት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ቢደርሰውም እንኳ) በእማኝ ዳኝነት የማገልገል ኃላፊነቱን እንዲቀበል ለማስገደድ ሲሉ ከዚህ ኃላፊነት ነፃ የመውጣት ጥያቄዎችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ውድቅ እያደረጉ መጥተዋል።

ለእማኝ ዳኝነት እንዲቀርቡ ጥሪ የደረሳቸው ሁሉ ለፍርድ ይቀመጣሉ ማለት አይደለም። ለእማኝ ዳኝነት ተጠርተው ከመጡት ብዙ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ችሎት ተቀምጠው አንድን ጉዳይ እንዲያዩ ይመረጣሉ። ከዚያም ዳኛው ከሳሹንና ተከሳሹን እንዲሁም ጠበቆቻቸውን ካስታወቁ በኋላ ጉዳዩ ምን እንደሆነ ይገልጻሉ። ዳኛውና ጠበቃዎቹ አንድ ላይ ሆነው የእያንዳንዱን እማኝ ዳኛ ብቃት ይገመግማሉ። ከሚታየው ጉዳይ አንጻር በችሎቱ ለመቀመጥ ሕሊናው የማይፈቅድለት ሰው ካለ አቋሙን ማሳወቅ ያለበት በዚህ ጊዜ ነው።

ከእማኝ ዳኞቹ መካከል አንዳንዶቹ ይቀነሱና ጉዳዩን ለማየት የሚያስፈልጉትን ያህል ሰዎች ብቻ ይቀራሉ። ዳኛው ከጉዳዩ ጋር በሆነ መልኩ ግንኙነት ይኖራቸውና አድሎ ይፈጽማሉ ተብለው የሚጠረጠሩትን ሰዎች ያሰናብታሉ። በተጨማሪም በሁለቱም ወገኖች በኩል የሚቆሙት ጠበቃዎችም የተወሰኑ የእማኝ ዳኝነት አባላትን የመቀነስ ሥልጣን አላቸው። ከእማኝ ዳኞቹ ቡድን የተሰናበቱት ሰዎች ይመለሱና ጥሪ ደርሷቸው ከመጡት ብዙ ሰዎች ጋር ተቀላቅለው እንደገና ሌላ ጉዳይ ለማየት እስኪመረጡ ድረስ ይጠብቃሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህን አጋጣሚ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምሥክርነት ለመስጠት ይጠቀሙበታል። አንድ ግለሰብ በእማኝ ዳኝነት ተቀምጦ ሠራም አልሠራ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ የሥራ ጊዜው ያበቃል።

ክርስቲያኖች ‘በሌሎች ጉዳይ ሳይገቡ’ ‘ስለ ራሳቸው ጉዳይ ብቻ ሊጠነቀቁ’ ይገባል። (1 ተሰሎንቄ 4:​11፤ 1 ጴጥሮስ 4:​15) አንድ አይሁዳዊ ውርስን በሚመለከት እንዲፈርድለት በጠየቀው ጊዜ ኢየሱስ “አንተ ሰው፣ ፈራጅና አካፋይ በላያችሁ እንድሆን ማን ሾመኝ?” ሲል መልሶለታል። (ሉቃስ 12:​13, 14) ኢየሱስ የመጣው ስለ ሕግ ጉዳዮች ለመዳኘት ሳይሆን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማወጅ ነበር። (ሉቃስ 4:​18, 43) ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ ሰውዬው በአምላክ ሕግ ውስጥ የሰፈረውን ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ዘዴ እንዲጠቀም አነሳስቶት ሊሆን ይችላል። (ዘዳግም 1:​16, 17) እነዚህ ነገሮች እውነት ቢሆኑም ትእዛዝ ተቀብሎ ለእማኝ ዳኝነት መቅረብና ራስን በሌሎች ጉዳይ ማስገባት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ይህ ሁኔታው ይበልጥ ከዳንኤልና ከሦስቱ ጓደኞቹ ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። የባቢሎን መንግሥት በዱራ ሜዳ እንዲገኙ አዝዟቸው ነበር፤ ይህን በማድረጋቸው የአምላክን ሕግ አልጣሱም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ከዚያ በኋላ ያደረጉት ነገር ግን ራሱን የቻለ ጉዳይ ነው።​—ዳንኤል 3:​16-​18

የአምላክ አገልጋዮች ከሙሴ ሕግ ነፃ ከተደረጉም በኋላ በተለያዩ አገሮች ውስጥ በመንግሥታዊ የፍርድ አካላት ፊት ለመቅረብ ተገደው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ውስጥ የነበሩት “ቅዱሳን” አለመግባባቶቻቸውን በጉባኤ ውስጥ እንዲፈቱ አበረታቷቸው ነበር። ጳውሎስ ከጉባኤ ውጭ የነበሩትን የሕግ አካላት “ዓመፀኞች” ብሎ ቢጠራቸውም ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ባሉ የፍርድ ጉዳዮች ለመዳኘት ሥልጣን እንዳላቸው አልካደም። (1 ቆሮንቶስ 6:​1) የሮማውያንን የፍትሕ ሥርዓት በመጠቀም ስለ መብቱ ከመከራከሩም በላይ ጉዳዩ በቄሣር ዘንድ እንዲታይለት ይግባኝ ጠይቋል። ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉ የፍርድ አካላት ጨርሶ ስህተት ናቸው ማለት አይደለም።​— ሥራ 24:​10፤ 25:​10, 11

ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ያሉት የፍርድ አካላት ‘በበላይ ያሉት ባለ ሥልጣኖች’ ክፍል ናቸው። ይህን ‘አንጻራዊ የሆነ ሥልጣናቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው፤’ ሕግ ያወጣሉ፣ ያወጡትንም ሕግ ያስፈጽማሉ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና።” ክርስቲያኖች ባለ ሥልጣኖች ሕጋዊ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ‘አይቃወሟቸውም፤’ ምክንያቱም እነርሱን ‘በመቃወም’ ቅጣት እንዲደርስባቸው አይፈልጉም።​—ሮሜ 13:​1-4፤ ቲቶ 3:​1

ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ሚዛናዊ የሆነ አቋም ለመያዝ ቄሣር ከእነርሱ የሚጠይቃቸውን አንዳንድ ነገሮች መፈጸም ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል መክሯል:- “ለሁሉ [ለሁሉም የበላይ ባለ ሥልጣናት] የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፣ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ።” (ሮሜ 13:​7) እዚህ ላይ የገንዘብ ቀረጥ መክፈልን በተመለከተ ምንም የማያሻማ መመሪያ ተቀምጧል። (ማቴዎስ 22:​17-21) ቄሣር ነዋሪዎቹ መንገድ እንዲያጸዱ ወይም ቄሣር ሊያከናውናቸው የሚገቡ ተግባራት ሆነው ጊዜና ጥረት የሚጠይቁ ሥራዎችን እንዲሠሩ ቢያዝ ይህን ትእዛዝ ለመቀበልና ላለመቀበል እያንዳንዱ ክርስቲያን መወሰን ይችላል።​— ማቴዎስ 5:​41

አንዳንድ ክርስቲያኖች በእማኝ ዳኝነት ማገልገል የቄሣርን ለቄሣር ማስረከብ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውታል። (ሉቃስ 20:​25) የእማኝ ዳኝነት ሥራ ግራና ቀኝ ማስረጃዎችን አይቶ በእውነታዎች ወይም በሕግ ላይ ተመሥርቶ አስተያየት መስጠትን የሚጠይቅ ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል በከፍተኛ የእማኝ ዳኝነት [ግራንድ ጁሪ] ውስጥ አባላቱ ከማስረጃዎቹ ተነስተው ሰውዬው ፍርድ ፊት መቅረብ ይገባውና አይገባው እንደሆነ ይወስናሉ፤ ወንጀለኛ ነው ወይም ወንጀለኛ አይደለም ብለው ግን አይወስኑም። ስለተለመደው የፍርድ ሂደትስ ምን ማለት ይቻላል? ጉዳዩ የፍትሐ ብሔር ክስ ከሆነ እማኝ ዳኝነቱ የጉዳት ካሳ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ እንዲከፈል ይወስን ይሆናል። ወንጀል ነክ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ ግለሰቡ በወንጀሉ ተጠያቂ ነው ብሎ ለመወሰን የሚያስችል ማስረጃ መኖር አለመኖሩን ይመረምራሉ። አንዳንድ ጊዜ በሕጉ ውስጥ የተደነገገው የትኛው አንቀጽ ሊተገበር እንደሚገባ የውሳኔ ሐሳብ ይሰጣሉ። ከዚያ በኋላ መንግሥት ያለውን ሥልጣን በመጠቀም ‘ክፉ አድራጊውን’ ‘ይበቀለዋል’ ወይም ‘ይቀጣዋል።’​— 1 ጴጥሮስ 2:​14

አንድ ክርስቲያን አንድን ዓይነት ጉዳይ በእማኝ ዳኝነት ለማየት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት ቢሰማውስ? መጽሐፍ ቅዱስ በእማኝ ዳኝነት ስለማገልገል የሚናገረው ነገር ስለሌለ ‘ሃይማኖቴ በማንኛውም የእማኝ ዳኝነት ሥራ መሳተፍን አይፈቅድም’ ማለት አይችልም። አንድን የተወሰነ ጉዳይ በእማኝ ዳኝነት ለማየት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት ሊገልጽ ይችል ይሆናል። ምናልባት ጉዳዩ የጾታ ብልግናን፣ ውርጃን፣ ነፍስ ግድያን ወይም ግለሰቡ በመንግሥት ሕግ ብቻ ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘው እውቀት የሚመራባቸውን ሌሎች ጉዳዮች የሚመለከት ሲሆን ይህን አቋሙን ሊገልጽ ይችል ይሆናል። ነገር ግን እርሱ የተመረጠበት ክስ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን የማይጨምር ሊሆን ይችላል።

አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ዳኞቹ ያሳለፉት ውሳኔ እርሱንም በኃላፊነት የሚያስጠይቀው እንደሆነና አንዳልሆነ ያስባል። (ከዘፍጥረት 39:​17-20 እና ከ1 ጢሞቴዎስ 5:​22 ጋር አወዳድር።) ግለሰቡ በስህተት ወንጀለኛ ሆኖ ተገኝቷል ተብሎ ቢበየንበትና በሞት ቢቀጣ በእማኝ ዳኝነት የሚያገለግለው ክርስቲያን በደም ዕዳ ተጠያቂ ይሆናልን? (ዘጸአት 22:​2፤ ዘዳግም 21:​8፤ 22:​8፤ ኤርምያስ 2:​34፤ ማቴዎስ 23:​35፤ ሥራ 18:​6) ኢየሱስ ተከሶ በቀረበበት ጊዜ ጲላጦስ ‘ከእርሱ ደም ንጹህ ለመሆን’ ፈልጎ ነበር። አይሁዳውያኑ ቀበል አድርገው “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለዋል።​— ማቴዎስ 27:​24, 25

አንድ ክርስቲያን በእማኝ ዳኝነት እንዲያገለግል ከመንግሥት የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ከቀረበ በኋላ የዳኛውን ውትወታ ወደጎን በመተው በሕሊናው ምክንያት በአንድ የተወሰነ ጉዳይ ውስጥ ከመግባት ወደ ኋላ ቢል እርምጃው የሚያስከትለውን ውጤት ለመቀበል ዝግጁ መሆን ይኖርበታል። ቅጣቱ የገንዘብ መቀጮ ወይም መታሰር ሊሆን ይችላል።​— 1 ጴጥሮስ 2:​19

ለማጠቃለል ያህል በእማኝ ዳኝነት እንዲያገለግል የተጠራ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘው ግንዛቤና በገዛ ሕሊናው በመመራት ምን ማድረግ እንዳለበት መወሰን ይኖርበታል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በእማኝ ዳኝነት ለማገልገል ቀርበው በአንዳንድ ጉዳዮች ውስጥ ገብተው ሠርተዋል። ሌሎች ደግሞ እንዲህ ከማድረግ ቅጣቱን መቀበልን መርጠዋል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ምን ማድረግ እንዳለበት ራሱ መወሰን የሚኖርበት ሲሆን ሌሎች ባደረገው ውሳኔ ሊነቅፉት አይገባም።​— ገላትያ 6:​5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ