-
ለንጉሥ የሚቀርቡ ስጦታዎችመጠበቂያ ግንብ—2015 | መጋቢት 1
-
-
ለንጉሥ የሚቀርቡ ስጦታዎች
“ኮከብ ቆጣሪዎች ከምሥራቅ አገር ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው . . . ወርቅ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ በስጦታ መልክ አቀረቡለት።”—ማቴዎስ 2:1, 11
ለአንድ የተከበረ ሰው ስጦታ መስጠት ብትፈልግ ምን ትመርጥ ነበር? በጥንት ዘመን አንዳንድ ቅመሞች የወርቅን ያህል ውድ ነበሩ፤ እንዲሁም ለነገሥታት በስጦታነት ከሚቀርቡት የከበሩ ነገሮች መካከል ይገኙበት ነበር።a ኮከብ ቆጣሪዎቹ ደስ የሚል መዓዛ ያላቸው ሁለት ቅመሞችን ‘ለአይሁድ ንጉሥ’ በስጦታነት ያቀረቡት ለዚህ ነው።—ማቴዎስ 2:1, 2, 11
የበለሳን ዘይት
በተጨማሪም ንግሥት ሳባ ሰለሞንን በጎበኘችበት ወቅት ለንጉሡ ስላመጣቻቸው ነገሮች ሲገልጽ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ቅመማ ቅመምና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰሎሞን እንደሰጠችው ዐይነት ቅመማ ቅመም ያለ ከቶ አልነበረም።”b (2 ዜና መዋዕል 9:9) ሌሎች ነገሥታትም ለሰለሞን የበለሳን ዘይት ገጸ በረከት አድርገው ልከውለታል።—2 ዜና መዋዕል 9:23, 24
እንዲህ ዓይነቶቹ ቅመሞችና ተዛማጅነት ያላቸው ምርቶች በጥንት ዘመን በጣም ከፍ ተደርገው የሚታዩት እንዲሁም ውድ የነበሩት ለምንድን ነው? ለተለያዩ አስፈላጊ ዓላማዎች ይውሉ ስለነበር ነው፤ ለምሳሌ ውበትን ለመጠበቅና አስከሬን ለማዘጋጀት ያገለግሉ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። (“ቅመማ ቅመሞች በጥንት ዘመን የነበራቸው ጥቅም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ቅመሞች በጣም ተፈላጊ የነበሩ ከመሆኑም ሌላ እነሱን ማጓጓዝና መሸጥ ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ ዋጋቸው ውድ ነበር።
የአረቢያን በረሃ ማቋረጥ
ብርጉድ
በጥንት ዘመን ቅመም የሚገኝባቸው አንዳንድ ተክሎች በዮርዳኖስ ሸለቆ ይበቅሉ ነበር። ሌሎቹ ቅመሞች የሚመጡት ግን ከውጭ አገር ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ የቅመማ ቅመም ምርቶች ተጠቅሰዋል። በጣም ከሚታወቁት መካከል የሳሮን አበባ፣ እሬት፣ በለሳን፣ ቀረፋ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ ይገኙበታል። ከእነዚህ ሌላ ደግሞ እንደ ከሙን፣ ኮሰረትና እንስላል ያሉ የተለመዱ የምግብ ማጣፈጫዎች ተጠቅሰዋል።
እነዚህን ቅመሞች የሚያስመጡት ከየት ነበር? እሬት፣ ብርጉድና ቀረፋ የሚመጡት ከአሁኗ ሕንድ፣ ስሪ ላንካና ቻይና ነበር። እንደ ከርቤና ነጭ ዕጣን ያሉት ቅመሞች የሚገኙት ከደቡብ አረቢያ አንስቶ በአፍሪካ እስካለችው ሶማሊያ ድረስ ባለው በረሃማ አካባቢ ከሚበቅሉ ዛፎችና ቁጥቋጦዎች ነው። ናርዶስ ደግሞ በሂማላያ አካባቢ ብቻ የሚገኝ የሕንድ ምርት ነበር።
የሳሮን አበባ
ብዙ የቅመማ ቅመም ምርቶች ወደ እስራኤል የሚላኩት በአረቢያ በኩል ነበር። አረቢያ በሁለተኛውና በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. “በምሥራቅና በምዕራብ መካከል ሸቀጦችን የማጓጓዙን ሥራ መቆጣጠር” የቻለችበት አንዱ ምክንያት ይህ እንደሆነ ዘ ቡክ ኦቭ ስፓይስስ (የቅመማ ቅመም መጽሐፍ) የተባለ ጽሑፍ ገልጿል። በደቡብ እስራኤል በሚገኘው በኔጌቭ ያሉት ጥንታዊ ከተሞች፣ ምሽጎችና የሲራራ ነጋዴዎች ማረፊያ የነበሩ ሰፈሮች የቅመማ ቅመም ሻጮች ለጉዞ ይጠቀሙበት የነበረውን መንገድ ለማወቅ ያስችሉናል። በተጨማሪም እነዚህ ቦታዎች “ከደቡብ አረቢያ እስከ ሜድትራንያን ይካሄድ የነበረውን እጅግ አትራፊ የሆነ . . . ንግድ” እንደሚያሳዩ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ማዕከል ዘግቧል።
“መጠናቸው ትንሽ፣ ዋጋቸው ከፍ ያለ እንዲሁም በሸማቾች ዘንድ ሁልጊዜ ተፈላጊ የነበሩት ቅመማ ቅመሞች በተለይ በንግድ ሸቀጥነታቸው ተመራጭ ነበሩ።” —የቅመማ ቅመም መጽሐፍ
እነዚህን ደስ የሚል መዓዛ ያላቸው ቅመማ ቅመሞች የጫኑ ሲራራ ነጋዴዎች አረቢያን በማቋረጥ እስከ 1,800 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት አዘውትረው ይጓዙ ነበር። (ኢዮብ 6:19) መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ሽቶ፣ በለሳን ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው” ከገለዓድ ወደ ግብፅ ስለወረዱ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ይናገራል። (ዘፍጥረት 37:25) የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸውን ዮሴፍን ለባርነት የሸጡት ለእነዚህ ነጋዴዎች ነው።
-