የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ወርቃማው ሕግ—በስፋት የሚታወቅ ትምህርት
    መጠበቂያ ግንብ—2001 | ታኅሣሥ 1
    • ወርቃማው ሕግ—በስፋት የሚታወቅ ትምህርት

      “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።”​—⁠ማቴዎስ 7:⁠12

      እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ክርስቶስ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በዝነኛ የተራራ ስብከቱ ላይ የተናገራቸው ናቸው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ባሉት ብዙ መቶ ዘመናት ይህንን ቀላል አነጋገር አስመልክቶ ብዙ ተብሏል፣ ብዙ ተጽፏል። እንደ አብነት ለመጥቀስ ያህል “የቅዱስ ጽሑፉ መሠረት፣” “አንድ ክርስቲያን ለባልንጀራው ማድረግ የሚጠበቅበትን ነገር ጠቅለል አድርጎ የሚገልጽ ሐሳብ፣” እና “መሠረታዊ የግብረገብ መመሪያ” ተብሎ ተወድሷል። በጣም የታወቀ ከመሆኑ የተነሣ ብዙውን ጊዜ ወርቃማው ሕግ እየተባለ ይጠራል።

      ይሁን እንጂ ስለ ወርቃማው ሕግ የሚነገረው ነገር ክርስቲያን ተብለው በሚጠሩት ሰዎች ዙሪያ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የአይሁድ እምነት፣ የቡድሃ እምነትና የግሪክ ፍልስፍና ይህን መሠረታዊ የግብረገብ እውነት በተለያዩ መንገዶች አብራርተውታል። በተለይ ግን በሩቅ ምሥራቅ ሕዝብ ዘንድ በስፋት የሚታወቀው አባባል፣ በምሥራቁ ዓለም እንደ ታላቅ የሃይማኖት ጠቢብና አስተማሪ የሚታየው ኮንፊሽየስ የተናገረው ነው። ኮንፊሽየስ ከጻፋቸው አራት መጽሐፎች መካከል አናሌክትስ በተባለው ሦስተኛ መጽሐፍ ውስጥ ይህ ሐሳብ ሦስት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ሁለቱ፣ ኮንፊሽየስ ተማሪዎቹ ለጠየቁት ጥያቄ “እንዲደረግባችሁ የማትፈልጉትን ነገር በሌሎች ላይ አታድርጉ” በማለት መልስ የሰጠባቸው አጋጣሚዎች ናቸው። በሌላ ወቅት ደግሞ ደዝጎንግ የተባለ ተማሪው “ሌሎች እንዲያደርጉብኝ የማልፈልገውን ነገር እኔም በእነርሱ ላይ ማድረግ አልፈልግም” ብሎ በኩራት ሲናገር አስተማሪው በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት በሚያደርግ መንገድ “ጥሩ ብለሃል፤ ሆኖም እስከ አሁን እንዲህ ማድረግ አልቻልክም” በማለት መልሶለታል።

      አንድ ሰው እነዚህን ቃላት ሲያነብ ኮንፊሽየስ ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ከአሉታዊ ድርጊት አኳያ እንደገለጻቸው መረዳት አያዳግተውም። በሁለቱ አነጋገሮች መካከል ያለው ግልጽ ልዩነት ኢየሱስ የተናገረው ወርቃማው ሕግ ለሌሎች መልካም በማድረግ አዎንታዊ እርምጃ መውሰድን የሚጠይቅ መሆኑ ነው። ሰዎች ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት፣ ሌሎችን ለመርዳት አንዳንድ ነገር በማድረግና በየዕለቱ በዚህ ደንብ በመመራት ኢየሱስ ከተናገረው አዎንታዊ ተግባር የሚጠይቅ አባባል ጋር በሚስማማ መንገድ ቢኖሩ ኖሮ ይህ ዓለም ከአሁኑ የተሻለ የሚሆን አይመስልህም? እንደዚያ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

      ሕጉ የተጠቀሰው በአዎንታዊ ጎኑም ይሁን በአሉታዊ ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ ዋናው ቁም ነገር በተለያዩ ዘመናትና አካባቢዎች የኖሩና የተለያየ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች ወርቃማው ሕግ በሚያስተላልፈው መልእክት ላይ ከፍተኛ እምነት መገንባታቸው ነው። ይህ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የጠቀሰው ሐሳብ በየትኛውም ቦታና በማንኛውም ዘመን የኖሩ ሰዎችን ሕይወት የሚነካ ዓለም በሰፊው የሚታወቅ ትምህርት መሆኑን የሚያሳይ ነው።

      እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ሰዎች እንዲያከብሩኝ፣ አድሎ እንዳይፈጽሙብኝ፣ እንዳይሸነግሉኝ እፈልጋለሁ? የዘር መድሎ፣ ወንጀልና ጦርነት በሌለበት ዓለም ውስጥ መኖር እፈልጋለሁ? እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለሌላው ስሜትና ደህንነት በሚያስብበት ቤተሰብ ውስጥ መኖር እፈልጋለሁ?’ እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ አልፈልግም የሚል ማን ይኖራል? የሚያሳዝነው ግን ይህን ሁኔታ ያገኙ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። እንዲያውም ለአብዛኞቹ እንዲህ ያሉትን ነገሮች ተስፋ ማድረግ ሕልም ሆኖ ይታያቸዋል።

      እየደበዘዘ የመጣው ወርቃማው ሕግ

      በታሪክ ውስጥ የሰዎች መብት ሙሉ በሙሉ ተረግጦ በሰብዓዊው ፍጥረት ላይ ወንጀል የተፈጸመባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች ተከስተዋል። ከእነዚህ መካከል በአፍሪካ የተካሄደው የባሪያ ንግድ፣ የናዚ የመግደያ ካምፖች፣ በኃይል የሚፈጸም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛና በየቦታው የተከሰቱት አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋዎች ይገኙበታል። የተፈጸሙት አሰቃቂ ድርጊቶች ለቁጥር የሚያታክቱ ናቸው።

      ዛሬ ያለው በቴክኖሎጂ የመጠቀ ዓለም ራስ ወዳድነት የተጠናወተው ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ሌሎች የሚያስቡት የራሳቸው ጥቅም ወይም መብቴ ነው የሚሉት ነገር እስካልተነካ ድረስ ብቻ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ብዙዎች ይህን ያህል ራስ ወዳድ፣ ጨካኝ፣ ስለሌላው ስሜት የማያስቡና የራሳቸው ጥቅም ብቻ የሚታያቸው የሆኑት ለምንድን ነው? ብዙዎች ወርቃማውን ሕግ የሚያውቁት ቢሆንም ከእውነታው የራቀና ጊዜ ያለፈበት አባባል እንደሆነ ተሰምቷቸው ችላ ስለሚሉት አይደለምን? የሚያሳዝነው ደግሞ በአምላክ እናምናለን የሚሉ ብዙ ሰዎች ያላቸው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አለመሆኑ ነው። ደግሞም ዛሬ ካለው አዝማሚያ አንጻር ሲታይ የሰዎች ራስ ወዳድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደሚሄድ መገመት አያዳግትም።

      ስለሆነም የሚከተሉትን በጣም ወሳኝ ጥያቄዎች መመርመሩ ተገቢ ነው:- በወርቃማው ሕግ መመራት ምን ይጠይቃል? ዛሬም በዚህ ሕግ የሚመሩ ሰዎች አሉ? መላው የሰው ዘር ከወርቃማው ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚኖርበት ጊዜስ ይመጣ ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች እውነተኛ መልስ ለማግኘት የሚከተለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

      [በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ኮንፊሽየስና ሌሎች ሰዎች ወርቃማውን ሕግ በተለያዩ መንገዶች አስተምረዋል

  • ወርቃማው ሕግ ዛሬም ይሠራል
    መጠበቂያ ግንብ—2001 | ታኅሣሥ 1
    • ወርቃማው ሕግ ዛሬም ይሠራል

      አብዛኛዎቹ ሰዎች ወርቃማውን ሕግ ኢየሱስ ያመነጨው የሥነ ምግባር ትምህርት እንደሆነ አድርገው ቢያስቡም ኢየሱስ ራሱ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም” በማለት ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 7:16

      አዎን፣ ወርቃማው ሕግ የሚል ስያሜ ያገኘውን ጨምሮ ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች በአጠቃላይ የመነጩት ኢየሱስን ወደ ምድር ከላከው ፈጣሪ ከይሖዋ አምላክ ነው።

      ከመጀመሪያም ቢሆን አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር ዓላማው እነርሱ ራሳቸው መያዝ በሚፈልጉበት መንገድ ሌሎችን እንዲይዙ ነበር። “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” በሚለው ጥቅስ ላይ እንደተንጸባረቀው ሰዎችን የፈጠረበት መንገድ ለሌሎች ደህንነት አሳቢ በመሆን ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። (ዘፍጥረት 1:​27) ይህም ማለት ሰዎች በሰላም፣ በደስታና በስምምነት ለዘላለም እንዲኖሩ አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ በተወሰነ መጠን ግሩም የሆኑ ባሕርያቱን አካፍሏቸዋል ማለት ነው። ከአምላክ ያገኙት ሕሊና ተገቢውን ሥልጠና ካገኘ እነርሱ ራሳቸው መያዝ በሚፈልጉበት መንገድ ሌሎችን እንዲይዙ ይመራቸዋል።

      ራስ ወዳድነት ነገሠ

      ታዲያ የሰው ልጅ ሕይወት ጅምሩ እንዲህ ያማረ ከነበረ ችግር የተፈጠረው ምኑ ላይ ነው? በአጭሩ መጥፎ የሆነ የራስ ወዳድነት ባሕርይ ብቅ በማለቱ ነው። ብዙ ሰዎች በዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምን እንዳደረጉ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ያውቃሉ። አዳምና ሔዋን የአምላክን መሠረታዊ የጽድቅ መስፈርቶች በሙሉ በሚቃወመው በሰይጣን ተገፋፍተው በራሳቸው ለመመራት ሲሉ በራስ ወዳድነት የአምላክን አገዛዝ አንቀበልም አሉ። ይህ የራስ ወዳድነትና የዓመፅ እርምጃቸው በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በዘሮቻቸው ሁሉ ላይ አሳዛኝ ውጤት አስከትሏል። ይህ ደግሞ ወርቃማው ሕግ ተብሎ የተጠራውን ትምህርት ችላ ማለት የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት በግልጽ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በዚህ ምክንያት “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።”​—⁠ሮሜ 5:​12

      በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች ለይሖዋ አምላክ ፍቅራዊ መንገዶች ጀርባቸውን ይስጡ እንጂ እሱ አልተዋቸውም። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ የሚመሩበትን ሕግ ሰጥቷቸው ነበር። ሕጉ እነርሱ ራሳቸው መያዝ በሚፈልጉበት መንገድ ሌሎችን እንዲይዙ አስተምሯቸዋል። ሕጉ ባሪያዎች፣ አባት የሌላቸው ልጆችና መበለቶች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚገልጽ መመሪያ ሰጥቷል። ድብደባ፣ አፈናና ስርቆት የፈጸሙ ሰዎች እንዴት መዳኘት እንዳለባቸው ይናገራል። ስለ ንጽሕና አጠባበቅ የተሰጡት ሕጎች ለሌሎች ጤንነት አሳቢነት ማሳየትን የሚያንጸባርቁ ነበሩ። ሌላው ቀርቶ ወሲባዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሕጎችም ተሰጥተዋል። ይሖዋ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሎ ለሕዝቡ በመናገር የሕጉን ፍሬ ነገር ጠቅለል አድርጎ ያስቀመጠ ሲሆን ኢየሱስም ከጊዜ በኋላ ይህን ሐሳብ ጠቅሶታል። (ዘሌዋውያን 19:​18፤ ማቴዎስ 22:​39, 40) ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ በእስራኤላውያን መካከል የሚኖሩ ስደተኞች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚገልጽ መመሪያ ይዞ ነበር። “በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች አውቃችኋልና” የሚል ትእዛዝ ነበረው። በሌላ አነጋገር እስራኤላውያን ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች ከልብ አሳቢነት እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸው ነበር።​—⁠ዘጸአት 23:​9፤ ዘሌዋውያን 19:​34፤ ዘዳግም 10:​19

      እስራኤላውያን ሕጉን በታማኝነት እስከተከተሉ ድረስ ይሖዋ ሕዝቡን ባርኳል። በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብሔሩ በልጽጎ የነበረ ሲሆን ሕዝቡም ተደስቶና ረክቶ ይኖር ነበር። ታሪካዊው ዘገባ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር። ይሁዳና እስራኤል . . . እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።”​—⁠1 ነገሥት 4:​20, 25

      የሚያሳዝነው ግን የብሔሩ ሰላምና መረጋጋት ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። እስራኤላውያን አምላክ ሕግ ቢሰጣቸውም አልጠበቁትም። ከዚህ ይልቅ ራስ ወዳድነት ለሌሎች አሳቢነት እንዳያሳዩ እንቅፋት እንዲሆንባቸው ፈቀዱ። በዚህ ላይ የክህደት ጎዳናቸው ተጨምሮበት በግለሰብም ሆነ በብሔር ደረጃ ችግር ላይ ጥሏቸዋል። በመጨረሻም ይሖዋ በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን የይሁዳን መንግሥት፣ ኢየሩሳሌምን እንዲሁም ዕጹብ ድንቅ ውበት የነበረውን ቤተ መቅደስ ሳይቀር እንዲያጠፉ ፈቀደላቸው። ለምን? “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ቃሌን አልሰማችሁምና እነሆ፣ ልኬ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ ባሪያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፣ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፣ ለመደነቂያና ለማፍዋጫም ለዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ።” (ኤርምያስ 25:​8, 9) የይሖዋን ንጹሕ አምልኮ መተዋቸው እንዴት ያለ ጉዳት አስከትሎባቸዋል!

      ሊኮረጅ የሚገባው ምሳሌ

      በሌላ በኩል ኢየሱስ ክርስቶስ ወርቃማውን ሕግ በማስተማር ብቻ ሳይወሰን በዚያ በመመራት ረገድ ግሩም ምሳሌ ሆኗል። ለሌሎች ደህንነት ከልብ ያስብ ነበር። (ማቴዎስ 9:​36፤ 14:​14፤ ሉቃስ 5:​12, 13) አንድ ቀን ኢየሱስ ናይን በምትባል ከተማ አቅራቢያ ለቀብር ከሚሄዱ ሰዎች መካከል ልጅዋን በሞት በማጣትዋ ምክንያት ቅስሟ የተሰበረ አንዲት መበለት ተመለከተ። መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን ሲገልጽ “ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላት” ይላል። (ሉቃስ 7:​11-15) ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ የተባለው መዝገበ ቃላት “አዘነ” ተብሎ የተተረጎመው ሐረግ “አንጀቱ ተላወሰ” ማለት እንደሆነ ጠቅሷል። የልቧ ኃዘን ተሰምቶት ነበር። ይህ ደግሞ ኃዘኗን ለማቅለል አዎንታዊ እርምጃ እንዲወስድ አነሳስቶታል። ኢየሱስ ልጁን ከሞት አስነስቶ ‘ለእናቱ በሰጣት’ ጊዜ መበለቷ ምን ያህል ተደስታ ይሆን!

      በመጨረሻም ኢየሱስ ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ የሰው ዘር ከኃጢአትና ከሞት ባርነት እንዲላቀቅ ሥቃይ ለመቀበልና ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል። በወርቃማው ሕግ በመመራት ረገድ ከዚህ የላቀ ምን ምሳሌ ሊኖር ይችላል?​—⁠ማቴዎስ 20:​28፤ ዮሐንስ 15:​13፤ ዕብራውያን 4:​15

      በወርቃማው ሕግ የሚመሩ ሰዎች

      በዘመናችንስ በወርቃማው ሕግ የሚመሩ ሰዎች አሉ? አዎን፣ አሉ። ደግሞም እንዲህ የሚያደርጉት በሚመቻቸው ጊዜ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ጀርመን ሥር የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነትና ለባልንጀሮቻቸው ያላቸውን ፍቅር አጽንተው በመያዝ ወርቃማውን ሕግ ለመጣስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። ሕዝቡ አይሁዳውያንን እንዲጠላቸውና አድልዎ እንዲፈጸምባቸው መንግሥት ቅስቀሳ ቢያካሂድም የይሖዋ ምሥክሮች ወርቃማውን ሕግ ከመከተል ወደኋላ አላሉም። ሌላው ቀርቶ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ያለቻቸውን ምግብ በረሃብ ለሚሠቃዩ አይሁዳውያንና አይሁዳውያን ላልሆኑ እስረኞች በማካፈል አሳቢነት ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት መሣሪያ አንስተው ሌሎችን እንዲገድሉ ቢያዝዛቸውም ሌሎች እንዲገድሏቸው እንደማይፈልጉ ሁሉ እነርሱም ከመግደል ተቆጥበዋል። ደግሞስ እንደ ራሳቸው አድርገው የሚወድዷቸውን ሰዎች የሚገድሉበት ምን እጅ ይኖራቸዋል? ብዙዎቹ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ወደ ማጎሪያ ካምፖች ከመላካቸውም ባሻገር ተገድለዋል።​—⁠ማቴዎስ 5:​43-48

      አሁን ይህን ርዕስ በምታነብበት ጊዜ እንኳን ወርቃማው ሕግ ተግባራዊ በመሆኑ ምክንያት በተደረገ ዝግጅት እየተጠቀምህ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ዛሬ ብዙ ሰዎች በተስፋ መቁረጥና ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮቻቸው ምክንያት እንደሚሠቃዩ ይገነዘባሉ። ስለዚህ ሌሎች ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ተስፋና ተግባራዊ ሊሆን ስለሚችለው መመሪያ እንዲማሩ ለመርዳት በፈቃደኝነት በጎ ሥራ እየሠሩ ነው። ይህ ሁሉ ከዚህ በፊት ተደርጎ በማያውቅ መጠን በመከናወን ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የማስተማር ሥራ አካል ነው። ምን ውጤት አስገኝቷል? በኢሳይያስ 2:​2-4 ላይ በትንቢት እንደተነገረው “ብዙዎች አሕዛብ” እንዲያውም አሁን ቁጥራቸው በዓለም ዙሪያ ከስድስት ሚልዮን በላይ የሆነ ሰዎች ‘የይሖዋን መንገድ ተምረዋል፣ በጎዳናውም ይሄዳሉ።’ በምሳሌያዊ መንገድ “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውን ማጭድ ለማድረግ” እንዴት እንደሚቀጠቅጡ ተምረዋል። በእነዚህ አስጨናቂ ቀናት ውስጥ ሰላምና ደህንነት አግኝተዋል።

      አንተስ?

      እስቲ ለአንድ አፍታ በሰይጣን ዲያብሎስ ገፋፊነት በኤደን ገነት ውስጥ ከተፈጸመው ዓመፅ ወዲህ የሰው ልጅ ወርቃማውን ሕግ ገሸሽ በማድረጉ ምክንያት የደረሰበትን መከራና ሥቃይ አስብ። ይሖዋ በቅርቡ ሁኔታውን የመለወጥ ዓላማ አለው። እንዴት? “ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ።” (1 ዮሐንስ 3:​8) የዲያብሎስ ሥራ የሚፈርሰው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ማለትም ጥበቡና ችሎታው ባለውና ወርቃማውን ሕግ ባስተማረው እንዲሁም በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ባደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው።​—⁠መዝሙር 37:​9-11፤ ዳንኤል 2:​44

      የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም። ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፣ ዘሩም በበረከት ይኖራል” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 37:​25, 26) ዛሬ አብዛኛው ሰው ለሌላው ‘ከመራራትና ከማበደር’ ይልቅ መቀበልና መንጠቅ የሚቀናው ሆኗል ቢባል አትስማማም? በግልጽ እንደሚታየው ወርቃማውን ሕግ መከተል አንድ ሰው አሁንም ሆነ በመጪው የአምላክ መንግሥት ሥር በረከት እንዲያገኝ ስለሚያስችለው ወደ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ይመራል ለማለት ይቻላል። የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ የሚታየውን የራስ ወዳድነትና የክፋት ርዝራዥ ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ በማስወገድ ብልሹ የሆነውን የአሁኑን ሰብዓዊ አገዛዝ አምላክ በሚያቋቁመው አዲስ ሥርዓት ይተካዋል። በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ በወርቃማው ሕግ መመራት የሚያስገኘውን ደስታ ያጣጥማሉ።​—⁠መዝሙር 29:​11፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

      [በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ኢየሱስ ወርቃማውን ሕግ በማስተማር ብቻ ሳይወሰን ተግባራዊ በማድረግም ግሩም ምሳሌ ትቷል

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ወርቃማውን ሕግ መከተል ወደ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ይመራል

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ