የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 21—መክብብ
ጸሐፊው:- ሰሎሞን
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ.ል.በፊት ከ1000 ቀደም ብሎ
የመክብብ መጽሐፍ የተጻፈው ከፍተኛ ለሆነ ዓላማ ነበር። ሰሎሞን፣ ለይሖዋ የተወሰነ ሕዝብ መሪ እንደመሆኑ መጠን እስራኤላውያን ከውሳኔያቸው ጋር በሚስማማ መንገድ ታማኝ ሆነው በአንድነት እንዲኖሩ የማድረግ ኃላፊነት ነበረበት። ይህንን ኃላፊነቱን በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙት ጥበብ ያዘሉ ምክሮች አማካኝነት ለመወጣት ጥረት አድርጓል።
2 ሰሎሞን፣ በመክብብ 1:1 ላይ ራሱን ‘ሰባኪው [“ሰብሳቢው፣”NW]’ በማለት ጠርቷል። በአማርኛ የተዘጋጀ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው መክብብ ማለት “ሰባኪ” ወይም “አስተማሪ” ማለት ነው። ይህ ቃል በዕብራይስጥ ቋንቋ ቆኸሌት ሲሆን በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጽሐፉ የሚጠራው በዚህ ስም ነው። ቆኸሌት ለተባለው የዕብራይስጥ ስም ይበልጥ ትክክለኛ የሆነው ትርጓሜ “ሰብሳቢው” የሚለው ሲሆን ይህም ለሰሎሞን ይበልጥ ተስማሚ የሆነ መጠሪያ ነው። ይህ አጠራር ሰሎሞን መጽሐፉን የጻፈበትን ዓላማ ያመለክታል።
3 ንጉሥ ሰሎሞን ሰብሳቢ የነበረው በምን መንገድ ነው? ሕዝቡንስ የሰበሰበው ለምን ዓላማ ነበር? ሰሎሞን የእስራኤላውያንና በመካከላቸው በጊዜያዊነት ይኖሩ የነበሩት መጻተኞች ሰብሳቢ ነበር። እነዚህን ሕዝቦች በሙሉ ወደ አምላኩ ወደ ይሖዋ አምልኮ ሰብስቧቸዋል። ቀደም ሲል በኢየሩሳሌም የይሖዋን ቤተ መቅደስ ሠርቶ ነበር። ቤተ መቅደሱ በተመረቀበት ጊዜም ሕዝቡን በሙሉ ወደ ይሖዋ አምልኮ ጠርቷቸዋል ወይም ሰብስቧቸዋል። (1 ነገ. 8:1 የ1954 ትርጉም) አሁን ደግሞ በመክብብ መጽሐፍ አማካኝነት ሕዝቦቹ ከዚህ ዓለም ከንቱና ፍሬ ቢስ ሥራ ርቀው ዋጋማ ለሆነ ሥራ እንዲሰባሰቡ ለማድረግ ፈልጓል።—መክ. 12:8-10
4 የመጽሐፉ ጸሐፊ ሰሎሞን መሆኑ በቀጥታ የተጠቀሰ ባይሆንም ይህንን በሚገባ የሚያረጋግጡ በርካታ ጥቅሶች አሉ። ሰብሳቢው ራሱን ሲያስተዋውቅ “የዳዊት ልጅ” እንዲሁም “በኢየሩሳሌም የእስራኤል ንጉሥ” እንደሆነ ገልጿል። ይህን ለማለት የሚችለው ንጉሥ ሰሎሞን ብቻ ነው። ምክንያቱም ከእርሱ በኋላ በኢየሩሳሌም የተነሱት ነገሥታት በሙሉ የገዙት በይሁዳ ብቻ ነበር። ከዚህም በላይ ሰብሳቢው “ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከገዙት ከማንኛቸውም ይልቅ ታላቅ ሆኛለሁ፤ ጥበብም በዝቶልኛል፤ በብዙ ጥበብና ዕውቀት ተመክሮም ዐልፌአለሁ” በማለት ጽፏል። (1:1, 12, 16) ይህ መግለጫ ከሰሎሞን ሁኔታ ጋር ይስማማል። መክብብ 12:9 “እርሱም በጥልቅ አሰበ፤ ተመራመረም፤ ብዙ ምሳሌዎችንም በሥርዐት አዘጋጀ” ይላል። ንጉሥ ሰሎሞን 3,000 ምሳሌዎችን ተናግሯል። (1 ነገ. 4:32) መክብብ 2:4-9 ጸሐፊው ስላከናወናቸው የግንባታ ሥራዎች ይኸውም ስለ ወይን እርሻው፣ ስለ አትክልት ቦታዎቹና ስለ መዝናኛ ስፍራዎቹ እንዲሁም ስለ መስኖዎቹ፣ ስለ ወንድና ሴት አገልጋዮቹ፣ ብርና ወርቅ ስለማከማቸቱና ስላደረጋቸው ሌሎች ነገሮች ይነግረናል። ሰሎሞን እነዚህን ነገሮች በሙሉ ፈጽሟል። የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብና ብልጽግና በተመለከተች ጊዜ “ግማሹን እንኳ አልነገሩኝም” ብላለች።—1 ነገ. 10:7
5 ሰብሳቢው “በኢየሩሳሌም” ንጉሥ እንደነበረ ስለተጠቀሰ መክብብ የተጻፈው በኢየሩሳሌም መሆኑን ማወቅ ይቻላል። መክብብ የተጻፈው ሰሎሞን በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጹትን በርካታ ሥራዎች አከናውኖ ከጨረሰ በኋላ እና የ40 ዓመት የንግሥና ዘመኑን ሊያገባድድ አካባቢ፣ ይኸውም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1000 ቀደም ብሎ መሆን አለበት። ይህ የሆነው ግን ወደ ጣዖት አምልኮ ከመግባቱ በፊት መሆን ይኖርበታል። በዚህ ጊዜ ሰዎች ስለተሰማሩባቸው የተለያዩ የሥራ መስኮችና ሞያዎች እንዲሁም ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት ስለሚያደርጉት ጥረት ሰፋ ያለ እውቀት አካብቷል። ሰሎሞን መክብብን በጻፈበት ወቅት የአምላክ ሞገስ ስላልተለየው በአምላክ መንፈስ መሪነት ሊጽፍ ይችል ነበር።
6 የመክብብ መጽሐፍ “የእግዚአብሔር መንፈስ [ያለበት]” መሆኑን እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም አንድም ጊዜ ስለማይጠቅስ በመንፈስ የተጻፈ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ያድርባቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፉ እውነተኛውን አምልኮ የሚደግፍ ከመሆኑም በላይ “እውነተኛው አምላክ” [NW] የሚል ትርጉም ያለውን ሃኤሎሂም የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ጊዜያት ይጠቅሳል። በተጨማሪም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ከመክብብ በቀጥታ የጠቀሱበት ጊዜ ባለመኖሩ የመክብብ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ስለመሆኑ ሌላ ተቃውሞ ይነሳ ይሆናል። ይሁን እንጂ በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጹት ትምህርቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሌሎቹ የቅዱስ ጽሑፉ ክፍሎች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማሙ ናቸው። የክላርክ ኮሜንታሪ 3ኛ ጥራዝ ገጽ 799 እንዲህ ይላል:- “ኮኸሌት ወይም [መክብብ] የተባለው መጽሐፍ ሁሉን በሚችለው አምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆኑ በአይሁዳውያንም ሆነ በክርስትና እምነት ዘንድ መቼም ቢሆን ተቀባይነት አግኝቷል።”
7 በዓለም ጥበብ ተመርተው “መጽሐፍ ቅዱስን የሚገመግሙ ሰዎች” መጽሐፉ የተጻፈበት ቋንቋም ሆነ በውስጡ የያዘው መመሪያ ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት እንጂ በዚያ ዘመን የሚታወቅ ሊሆን ስለማይችል የመክብብን መጽሐፍ ሰሎሞን እንዳልጻፈው ወይም መጽሐፉ ‘የቅዱሳን መጻሕፍት’ ክፍል እንዳልሆነ ይናገራሉ። ሰሎሞን ቀስ በቀስ እያስፋፋው ከሄደው ዓለም አቀፍ ንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም ሊጎበኙት ከሚመጡ ታላላቅ ሰዎችና የውጭ አገር ሰዎች ምን ያህል ሰፊ እውቀት ሊያካብት እንደሚችል አላስተዋሉም። (1 ነገ. 4:30, 34፤ 9:26-28፤ 10:1, 23, 24) ኤፍ ሲ ኩክ ባይብል ኮሜንታሪ በተባለው መጽሐፋቸው በጥራዝ 4 ገጽ 622 ላይ “የታላቁ ዕብራዊ ንጉሥ የዕለት ተዕለት ሥራዎችና የመረጣቸው እንቅስቃሴዎች ከተለመደው የዕብራውያን አኗኗር፣ አስተሳሰብና ቋንቋ ልቆ እንዲሄድ አድርገውታል” ሲሉ ጽፈዋል።
8 ይሁን እንጂ የመክብብ መጽሐፍ የአምላክ ቃል ክፍል መሆኑን ለማረጋገጥ የውጭ ማስረጃዎችን መጥቀስ የግድ አስፈላጊ ነው? መጽሐፉን ራሱን ብንመረምረው እርስ በርሱ ስምምነት ያለው ከመሆኑም በላይ ከሌሎቹ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የሚጣጣም መሆኑን ማረጋገጥ እንችላለን።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
15 መክብብ የሕይወትን አሉታዊና አሳዛኝ ገጽታዎች የሚያጎላ ሳይሆን አስደሳች የሆነና ውድ መለኮታዊ ጥበብ የሚገኝበት መጽሐፍ ነው። ሰሎሞን ከንቱ የሚላቸውን በርካታ ሥራዎች በዘረዘረበት ወቅት በኢየሩሳሌም፣ በሞሪያ ተራራ ላይ የተሠራውን የይሖዋን ቤተ መቅደስም ሆነ ንጹሑን የይሖዋ አምልኮ በዚህ ዝርዝር ውስጥ አላካተታቸውም። የአምላክ ስጦታ የሆነው ሕይወት ከንቱ ነው አላለም፤ ከዚህ ይልቅ የሰው ልጅ ሕይወት የተሰጠው ተደስቶ እንዲኖርና መልካም እንዲያደርግ መሆኑን ገልጿል። (3:12, 13፤ 5:18-20፤ 8:15) አደገኛ ብሎ የጠቀሳቸው የሥራ ዓይነቶች አምላክን ግምት ውስጥ የማያስገቡት ናቸው። አንድ አባት ለልጁ ሀብት ያከማች ይሆናል፤ ሆኖም ድንገተኛ አደጋ ያከማቸውን በሙሉ ያጠፋበትና ለልጁ ምንም አይቀርለትም። ከዚህ ይልቅ ዘላቂነት ያለው መንፈሳዊ ሀብት ቢያቆይለት በጣም የተሻለ ይሆን ነበር። ብዙ ሀብት ካካበቱ በኋላ በሀብቱ መደሰት አለመቻልም ትልቅ ጉዳት ነው። ዓለማዊ ሀብት ያካበቱ ሰዎች ወደመጡበት በሞት ‘ሲመለሱ’ ምንም ነገር ይዘው መሄድ ስለማይችሉ አሳዛኝ ሁኔታ ይገጥማቸዋል።—5:13-15፤ 6:1, 2
16 ክርስቶስ ኢየሱስ በማቴዎስ 12:42 ላይ ራሱን “ከሰሎሞን የሚበልጥ” ሲል ጠርቷል። ሰሎሞን ለኢየሱስ ጥላ ስለነበረ በቆኸሌት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት የሰሎሞን ቃላት ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር ይስማሙ ይሆን? በሁለቱ መካከል ብዙ ተመሳሳይ ሐሳቦችን እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” በማለት የአምላክ ሥራ ሰፊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ዮሐ. 5:17) ሰሎሞንም እንደሚከተለው በማለት ስለ አምላክ ሥራዎች ተናግሯል:- “እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ አየሁ። ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ማንም ሊያውቅ አይችልም፤ ሰው ለመመርመር ብዙ ቢጥርም፣ ትርጒሙን ማግኘት አይችልም፤ ጠቢብም እንኳ ዐውቀዋለሁ ቢል፣ ፈጽሞ ሊገነዘበው አይችልም።”—መክ. 8:17
17 ኢየሱስም ሆነ ሰሎሞን እውነተኛ አምላኪዎች በአንድነት እንዲሰበሰቡ አበረታተዋል። (ማቴ. 18:20፤ መክ. 4:9-12፤ 5:1) ኢየሱስ “የዓለም መጨረሻ” እና “የአሕዛብ ዘመን” በማለት የተናገረው ሐሳብ ሰሎሞን “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው” በማለት ከተናገረው ጋር ይስማማል።—ማቴ. 24:3፤ ሉቃስ 21:24፤ መክ. 3:1
18 ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቁሳዊ ሀብት ማሳደድ በሰዎች ላይ ስለሚያስከትለው አደጋ በማስጠንቀቅ ረገድ የሰሎሞንን ሐሳብ ደግፈዋል። ሰሎሞን፣ “ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት [ስለምትጠብቅ]” እውነተኛ ከለላ እንደምታስገኝ ተናግሯል። ኢየሱስም “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” ብሏል። (መክ. 7:12፤ ማቴ. 6:33) በመክብብ 5:10 ላይ “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም፤ ይህም ከንቱ ነው” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። ይህም ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 6:6-19 ላይ “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው” ሲል ከሰጠው ምክር ጋር በጣም ይመሳሰላል። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ረገድም ይህን ዓይነት ተመሳሳይ ዘገባ ማግኘት ይቻላል።—መክ. 3:17—ሥራ 17:31፤ መክ. 4:1—ያዕ. 5:4፤ መክ. 5:1, 2—ያዕ. 1:19፤ መክ. 6:12—ያዕ. 4:14፤ መክ. 7:20—ሮሜ 3:23፤ መክ. 8:17—ሮሜ 11:33
19 በምድራዊ ሕይወቱ የንጉሥ ሰሎሞን ዝርያ የሆነው የአምላክ ውድ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በንጉሣዊ አገዛዙ በምድር ላይ አዲስ ኅብረተሰብ እንዲመሠረት ያደርጋል። (ራእይ 21:1-5) ሰሎሞን፣ ለክርስቶስ መንግሥት ጥላ በሆነው መንግሥቱ ሥር ለነበሩት ተገዥዎች አመራር ለመስጠት ሲል የጻፈው መጽሐፍ በክርስቶስ ኢየሱስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት ተስፋ ለሚያደርጉ ሁሉ በጣም ይጠቅማቸዋል። በዚህ መንግሥት ግዛት ሥር የሰው ልጆች ሰብሳቢው በተናገራቸው ጥበብ ያዘሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች እየተመሩ የአምላክ ስጦታ በሆነው ሕይወት ለዘላለም ይደሰታሉ። በአምላክ መንግሥት ሥር መኖር የሚያመጣውን ደስታ በተሟላ ሁኔታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ አምልኮ የምንሰባሰብበት ጊዜ አሁን ነው።—መክ. 3:12, 13፤ 12:13, 14