አካሄድን ከአምላክ ጋር ማድረግ —የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች
“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል።”—ያዕቆብ 4:8
1, 2. ይሖዋን ማገልገል ትልቅ መብት ነው የምትሉት ለምንድን ነው?
ሰውየው ለዓመታት እስር ቤት ውስጥ ሲማቅቅ ቆይቷል። ከዚያም በአገሪቱ ገዥ ፊት እንዲቀርብ ተጠራ። ሁኔታዎቹ በቅጽበት ተለወጡ። እስረኛ የነበረው ሰው ሳይታሰብ በዘመኑ እጅግ ኃያል ለነበረው ንጉሠ ነገሥት አገልጋይ ሆነ። የቀድሞው እስረኛ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታና ልዩ ክብር ተሰጠው። በአንድ ወቅት በእግር ብረት ታስሮ የነበረው ዮሴፍ አሁን የንጉሥ ባለሟል ሆኗል!—ዘፍጥረት 41:14, 39–43፤ መዝሙር 105:17, 18
2 ዛሬ የሰው ልጆች ከግብጹ ፈርዖን የሚበልጥ ሥልጣን ያለውን አካል የማገልገል አጋጣሚ ተዘርግቶላቸዋል። በአጽናፈ ዓለም ላይ የበላይ የሆነው አካል ሁላችንም እንድናገለግለው ግብዣ ያቀርባል። እንዲህ ማድረግና ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ማዳበር እንዴት ያለ አስደናቂ መብት ነው! ታላቅ ኃይልና ግርማ እንዲሁም ፀጥታና እርጋታ፣ ውበትና ማራኪነት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከይሖዋ ጋር በተያያዘ መንገድ ተገልጸዋል። (ሕዝቅኤል 1:26–28፤ ራእይ 4:1–3) በሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ፍቅር ይንጸባረቃል። (1 ዮሐንስ 4:8) በፍጹም አይዋሽም። (ዘኁልቁ 23:19) እንዲሁም ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የሆኑትን በፍጹም አሳፍሯቸው አያውቅም። (መዝሙር 18:25 የ1980 ትርጉም) ከጽድቅ መስፈርቶቹ ጋር ተስማምተን የምንሄድ ከሆነ ከፊታችን የሚጠብቀንን የዘላለም ሕይወት በአእምሮአችን ይዘን በአሁኑ ጊዜ አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት ልንመራ እንችላለን። (ዮሐንስ 17:3) ማንኛውም ሰብዓዊ ገዥ ከእነዚህ በረከቶችና መብቶች ጋር በትንሹ እንኳ ሊወዳደር የሚችል ነገር ሊያቀርብ አይችልም።
3. ኖኅ ‘አካሄዱን ከእውነተኛው አምላክ ጋር ያደረገው’ በምን መንገድ ነው?
3 ጥንት የእምነት አባት የነበረው ኖኅ ከአምላክ ፈቃድና ዓላማ ጋር ተስማምቶ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:9) “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው” አንድም ሰው እንኳ ስለሌለ ኖኅ ቃል በቃል ከይሖዋ ጋር እንዳልሄደ የተረጋገጠ ነው። (ዮሐንስ 1:18) ከዚህ ይልቅ አምላክ አድርግ ያለውን በመታዘዝ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጓል። ኖኅ ሙሉ በሙሉ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ያደረ ሰው ስለነበረ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ሞቅ ያለና የተቀራረበ ዝምድና ሊመሠርት ችሏል። በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከይሖዋ ምክርና መመሪያ ጋር ተስማምተው በመኖር ልክ እንደ ኖኅ ‘አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር’ አድርገዋል። አንድ ሰው እንዲህ ያለውን አካሄድ የሚጀምረው እንዴት ነው?
ትክክለኛ እውቀት የግድ አስፈላጊ ነው
4. ይሖዋ ሕዝቡን የሚያስተምረው እንዴት ነው?
4 አካሄዳችንን ከይሖዋ ጋር ለማድረግ በመጀመሪያ እሱን ልናውቀው ይገባል። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፤ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፣ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው:- ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።” (ኢሳይያስ 2:2, 3) አዎን፣ ይሖዋ በመንገዱ ለመሄድ የሚፈልጉትን ሁሉ እንደሚያስተምራቸው ልንተማመን እንችላለን። ይሖዋ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል፤ እንድናስተውለውም ይረዳናል። ይህን የሚያደርግበት አንዱ መንገድ በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 24:45–47) ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ባደረጉ ጽሑፎች፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዲሁም ያለ ምንም ክፍያ በሚሰጥ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዝግጅት አማካኝነት መንፈሳዊ ትምህርት ለመስጠት ‘ታማኙን ባሪያ’ ይጠቀምበታል። በተጨማሪም አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ሕዝቦቹ ቃሉን እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 2:10–16
5. ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት እጅግ ውድ ነገር የሆነው ለምንድን ነው?
5 የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምንም እንኳ ገንዘብ ባናወጣበትም እጅግ ውድ ነው። የአምላክን ቃል ስናጠና ስለ ራሱ ስለ አምላክ ማለትም ስለ ስሙ፣ ስለ ባሕርያቱ፣ ስለ ዓላማው እንዲሁም ከሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት እንማራለን። በተጨማሪም እንደሚከተሉት ላሉት የሕይወት መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚያረካ መልስ እናገኛለን:- በሕይወት የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዟል? የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው? ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? ከዚህም በላይ አምላክ ለእኛ ያለው ፈቃዱ ምን እንደሆነ ማለትም እሱን ሙሉ በሙሉ ለማስደሰት አካሄዳችን እንዴት መሆን እንዳለበት እንማራለን። መስፈርቶቹ ምክንያታዊ እንደሆኑና ከእነሱም ጋር ተስማምተን የምንኖር ከሆነ እጅግ እንደሚጠቅሙ እንማራለን። አምላክ ካላስተማረን በስተቀር እነዚህን ነገሮች ፈጽሞ ልናስተውል አንችልም።
6. ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ምን ዓይነት አካሄድ እንድንከተል ያስችለናል?
6 የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ኃይል ስላለው በሕይወታችን ውስጥ ለውጦች እንድናደርግ ይገፋፋናል። (ዕብራውያን 4:12) ቅዱሳን ጽሑፎች ምን እንደሚሉ ከመማራችን በፊት እንመላለስ የነበረው “በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ” ብቻ ነበር። (ኤፌሶን 2:2) ሆኖም ከአምላክ ቃል የሚገኘው ትክክለኛ እውቀት ‘በነገር ሁሉ ይሖዋን ደስ ለማሰኘት ለእርሱ እንደሚገባ ሆነን እንድንመላለስ’ ስለሚያስችለን የተለየ አካሄድ በዝርዝር ይገልጽልናል። (ቆላስይስ 1:10) አካሄዳችንን በመላው ጽንፈ ዓለም ውስጥ ዕጹብ ድንቅ ከሆነው አካል ማለትም ከይሖዋ ጋር ለማድረግ የመጀመሪያዎቹን እርምጃዎች መውሰዱ እንዴት የሚያስደስት ነው!—ሉቃስ 11:28
ሁለት አስፈላጊ እርምጃዎች —ራስን መወሰንና መጠመቅ
7. የአምላክን ቃል ስናጠና ሰብዓዊ አገዛዝን የሚመለከተው የትኛው እውነት ግልጽ ይሆናል?
7 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን ግንዛቤ እያደገ ሲሄድ የሰው ልጆችንና የራሳችንን ሕይወት የሚመለከቱ ጉዳዮችን በአምላክ ቃል መንፈሳዊ ብርሃን መመርመር እንጀምራለን። በዚህ ጊዜ አንድ አስፈላጊ እውነት ግልጽ ይሆናል። ይህ እውነት ከረዥም ጊዜ በፊት በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት የተገለጸ ሲሆን እንደሚከተለው ይላል:- “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” (ኤርምያስ 10:23) ሁላችንም የሰው ልጆች የአምላክ አመራር ያስፈልገናል።
8. (ሀ) ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ እንዲወስኑ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው? (ለ) በክርስትና ጎዳና ራስን ለአምላክ መወሰን ምን ትርጉም አለው?
8 ይህንን ወሳኝ ሐቅ ማስተዋላችን መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር እንድንል ይገፋፋናል። ለአምላክ ያለን ፍቅር ደግሞ ሕይወታችንን ለእሱ እንድንወስን ያነሳሳናል። ራስን ለአምላክ መወሰን ማለት በጸሎት ወደ እርሱ መቅረብና በሕይወታችን ሙሉ እሱን ለማገልገልና በታማኝነት በመንገዶቹ ለመመላለስ ቃል መግባት ማለት ነው። እንዲህ በማድረግ መለኮታዊውን ፈቃድ ለመፈጸም ሙሉ በሙሉ ራሱን ለይሖዋ ያቀረበውን የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን።—ዕብራውያን 10:7
9. ግለሰቦች ሕይወታቸውን ለይሖዋ የሚወስኑት ለምንድን ነው?
9 ይሖዋ አምላክ ማንንም ሰው ቢሆን ራሱን እንዲወስን አይጫንም ወይም አያስገድድም። (ከ2 ቆሮንቶስ 9:7 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ አምላክ ማንም ሰው በጊዜያዊ ስሜት ተገፋፍቶ ሕይወቱን ለእሱ እንዲወስንለት አይፈልግም። አንድ ሰው ከመጠመቁ አስቀድሞ ደቀ መዝሙር መሆን አለበት፤ ይህ ደግሞ እውቀት ለማግኘት ልባዊ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ጳውሎስ ቀደም ሲል የተጠመቁትን ወንድሞች ‘ሰውነታቸውን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ ማለትም የማመዛዘን ችሎታቸውን በመጠቀም ቅዱስ አገልግሎት እንዲያከናውኑ’ ተማጽኗቸዋል። (ሮሜ 12:1) እኛም በተመሳሳይ ለይሖዋ አምላክ ራሳችንን የምንወስነው በማመዛዘን ችሎታችን በመጠቀም ነው። ራስን መወሰን ምንን እንደሚያካትት ከተማርንና ጉዳዩን በደንብ ከመረመርን በኋላ በፈቃደኝነትና በደስታ ሕይወታችንን ለአምላክ እንወስናለን።—መዝሙር 110:3 NW
10. ራስን መወሰን ከጥምቀት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
10 በመንገዶቹ ለመሄድ መወሰናችንን በጸሎት አማካኝነት በግል ቀርበን ለአምላክ ከገለጽንለት በኋላ ቀጣዩን እርምጃ እንወስዳለን። በውኃ በመጠመቅ ራሳችንን መወሰናችንን ይፋ እናደርጋለን። ይህም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቃል መግባታችንን ለሕዝብ የሚያሳውቅ ነው። ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ በዮሐንስ አማካኝነት በመጠመቅ ምሳሌ ትቶልናል። (ማቴዎስ 3:13–17) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ተከታዮቹን ደቀ መዛሙርት የማድረግና የማጥመቅ ተልዕኮ ሰጥቷቸዋል። ስለዚህ ራስን መወሰንና መጠመቅ አካሄዱን ከይሖዋ ጋር ለማድረግ ፍላጎት ያለው ማንኛውም ሰው ሊወስዳቸው የሚገቡ አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው።
11, 12. (ሀ) ጥምቀት ከሠርግ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና በአንድ ባልና ሚስት መካከል ከሚኖረው ዝምድና ጋር ምን ተመሳሳይነት አለው?
11 ራስን በመወሰንና በመጠመቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ከጋብቻ ጋር የሚመሳሰልባቸው ሁኔታዎች አሉ። በብዙ አገሮች ከሠርጉ ቀን በፊት ደረጃ በደረጃ የሚከናወኑ በርካታ ነገሮች አሉ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ይተዋወቃሉ፣ ይቀራረባሉ፣ ይዋደዳሉ፣ ከዚያም ይተጫጫሉ። በትዳር ለመተሳሰርና ባልና ሚስት ሆነው ለመኖር እነርሱ በግላቸው ያደረጉት ውሳኔ በሠርጋቸው አማካኝነት ይፋ ይሆናል። የዚህን ልዩ ዝምድና መጀመር የሚያበስረው ሠርጋቸው ነው። ይህ ትዳራቸው የጀመረበት ቀን ነው። በተመሳሳይም ጥምቀት ለይሖዋ የተወሰንን ሆነን ለመመላለስ በሙሉ ልብ የምንከተለው የሕይወት ጎዳና መጀመሪያ ነው።
12 ሌላ ተመሳሳይ ሁኔታ ተመልከት። ከሠርጋቸው ቀን በኋላ የባልና ሚስቱ ፍቅር እየጠበቀና እየዳበረ ሊሄድ ይገባዋል። ከምንጊዜውም ይበልጥ እርስ በርሳቸው እየተቀራረቡ እንዲሄዱ ሁለቱም ባለ ትዳሮች የጋብቻ ዝምድናቸውን ጠብቀው ለማቆየትና ለማጠንከር ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ምንም እንኳ እኛ ከአምላክ ጋር ትዳር ባንመሠርትም ከተጠመቅን በኋላ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት ጠንክረን መሥራት አለብን። ፈቃዱን ለመፈጸም የምናደርገውን ጥረት ይመለከታል እንዲሁም ያደንቃል፤ ወደ እኛም ይቀርባል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” ሲል ጽፏል።—ያዕቆብ 4:8
የኢየሱስን ፈለግ መከተል
13. አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ስናደርግ የማንን ምሳሌ መከተል አለብን?
13 አካሄዳችንን ከይሖዋ ጋር ለማድረግ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልንን ምሳሌ መከተል አለብን። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ ፍጹም ሲሆን እኛ ግን ፍጹማን ባለመሆናችን እሱ የተወልንን ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ልንከተል አንችልም። ሆኖም ይሖዋ የተቻለንን ያህል እንድንጥር ይጠብቅብናል። ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች ጥረት በማድረግ ሊኮርጁአቸው የሚገቡ የኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት አምስት ገጽታዎች ቀጥለን እንመልከት።
14. የአምላክን ቃል ማወቅ ምንን ይጨምራል?
14 ኢየሱስ ትክክለኛና የተሟላ የአምላክ ቃል እውቀት ነበረው። ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ይጠቅስ ነበር። (ሉቃስ 4:4, 8) እርግጥ ነው በዘመኑ የነበሩት ክፉ ሃይማኖታዊ መሪዎችም ከቅዱሳን ጽሑፎች ይጠቅሱ ነበር። (ማቴዎስ 22:23, 24) ልዩነቱ ግን ኢየሱስ ቅዱሳን ጽሑፎች ምን እንደሚሉ በሚገባ ከማስተዋሉም በላይ በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ አድርጓቸዋል። የሕጉን ቃል ብቻ ሳይሆን የሕጉን መንፈስ ጭምር ያውቅ ነበር። እኛም የክርስቶስን ምሳሌ ስንከተል የአምላክን ቃል ለማስተዋል ማለትም ትርጉሙን ወይም መንፈሱን ለመረዳት መጣር አለብን። እንዲህ በማድረግ ‘የእውነትን ቃል በትክክል መጠቀም’ የምንችል መለኮታዊ ተቀባይነት ያገኘን ሠራተኞች እንሆናለን።—2 ጢሞቴዎስ 2:15 NW
15. ኢየሱስ ስለ አምላክ በመናገር ረገድ ምሳሌ የተወው እንዴት ነበር?
15 ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰማያዊ አባቱ ለሌሎች ይናገር ነበር። ኢየሱስ ከአምላክ ቃል ያገኘውን እውቀት ለራሱ ብቻ ይዞ ዝም አላለም። በሄደበት ሁሉ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለሌሎች ይናገር ስለነበር ጠላቶቹ እንኳን ሳይቀሩ “መምህር” ብለው ጠርተውታል። (ማቴዎስ 12:38) ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አካባቢ፣ በምኩራብ፣ በከተማና በገጠር ለሕዝብ ሰብኳል። (ማርቆስ 1:39፤ ሉቃስ 8:1፤ ዮሐንስ 18:20) ኢየሱስ ያስተማረው በርኅራኄና በደግነት ሲሆን ለሚረዳቸውም ሰዎች ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ማቴዎስ 4:23) የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉ ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክና አስደናቂ ስለሆኑት ዓላማዎቹ ሌሎችን ለማስተማር የሚያስችሏቸው ብዙ ቦታዎችና ዘዴዎች አሏቸው።
16. ኢየሱስ ከመሰል የይሖዋ አምላኪዎች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ያህል የተቀራረበ ነበር?
16 ኢየሱስ ይሖዋን ከሚያመልኩ ሌሎች ሰዎች ጋር የጠበቀ ትስስር ነበረው። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለተሰበሰበ ሕዝብ በሚናገርበት ጊዜ እናቱና የማያምኑ ወንድሞቹ ከእሱ ጋር ለመነጋገር መጡ። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “አንዱም:- እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል አለው። እርሱ ግን ለነገረው መልሶ:- እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? አለው። እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ:- እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና።” (ማቴዎስ 12:47–50) ይህ ማለት ግን ኢየሱስ ቤተሰቡን አግልሏል ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ቀጥሎ የተከናወኑ ነገሮች እንዲህ እንዳላደረገ ያሳያሉ። (ዮሐንስ 19:25–27) ይሁንና ይህ ታሪክ ኢየሱስ ለመሰል አማኞች ያለውን ፍቅር የሚያጎላ ነው። በተመሳሳይም ዛሬ አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር የሚያደርጉ ሰዎች የሌሎች የይሖዋ አገልጋዮችን ወዳጅነት ይፈልጋሉ፤ እንዲሁም ለእነሱ ያላቸውን ፍቅር ለማሳደግ ይጥራሉ።—1 ጴጥሮስ 4:8
17. ኢየሱስ የሰማያዊ አባቱን ፈቃድ ማድረግን በተመለከተ እንዴት ይሰማው ነበር? ይህስ እኛን እንዴት ሊነካን ይገባል?
17 ኢየሱስ መለኮታዊውን ፈቃድ በማድረግ ለሰማያዊ አባቱ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። ኢየሱስ ይሖዋን በሁሉም መስክ ታዝዟል። “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) በተጨማሪም ክርስቶስ “እኔ [አምላክን] ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:29) ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱን እጅግ ከመውደዱ የተነሣ “ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ [ሆኗል]።” (ፊልጵስዩስ 2:8) ይሖዋ ደግሞ ከእሱ ከራሱ ቀጥሎ ከፍተኛ የሥልጣንና የክብር ቦታ በመስጠት በአጸፋው ኢየሱስን ባርኮታል። (ፊልጵስዩስ 2:9–11) የአምላክን ትእዛዛት በመጠበቅና ፈቃዱን በማድረግ እንደ ኢየሱስ ለአምላክ ያለንን ፍቅር እናሳያለን።—1 ዮሐንስ 5:3
18. የጸሎትን ጉዳይ በተመለከተ ኢየሱስ ምሳሌ የተወው በምን መንገድ ነው?
18 ኢየሱስ የጸሎት ሰው ነበር። በተጠመቀ ጊዜ ጸልዮአል። (ሉቃስ 3:21) አሥራ ሁለት ሐዋርያቱን ከመምረጡ በፊት ሌሊቱን በሙሉ ሲጸልይ አድሯል። (ሉቃስ 6:12, 13) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት እንደሚጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ሉቃስ 11:1–4) ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለደቀ መዛሙርቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:1–26) ጸሎት የኢየሱስ ሕይወት አቢይ ክፍል ነበረ፤ እኛም የእሱ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ጸሎት የሕይወታችን አቢይ ክፍል ሊሆን ይገባል። ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ጋር በጸሎት መነጋገር እንዴት ያለ ክብር ነው! ከዚህም በላይ ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ ይሰጣል። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።”—1 ዮሐንስ 5:14, 15
19. (ሀ) የትኞቹን የኢየሱስ ባሕርያት ልንኮርጅ ይገባል? (ለ) የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት ከማጥናት ጥቅም ማግኘት የምንችለው በምን መንገዶች ነው?
19 የኢየሱስ ክርስቶስን ምድራዊ ሕይወትና አገልግሎት በጥልቅ በመመርመር ብዙ መማር ይቻላል! ኢየሱስ ያንጸባረቃቸውን እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄ፣ ደግነት፣ ጥንካሬ፣ ሚዛናዊነት፣ ምክንያታዊነት፣ ትሕትና፣ ድፍረትና ለጋስነት ስለ መሳሰሉት ባሕርያት አሰላስሉ። ስለ ኢየሱስ ይበልጥ ባወቅን መጠን የእሱ ተከታዮች ለመሆን ያለን ፍላጎትም የዚያኑ ያህል እያደገ ይሄዳል። በተጨማሪም ስለ ኢየሱስ ያለን እውቀት ይበልጥ ወደ ይሖዋ ያቀርበናል። ምክንያቱም ኢየሱስ የሰማያዊ አባቱ ፍጹም ነጸብራቅ ነበር። ይሖዋን በቅርብ ያውቀው ስለነበር “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ብሎ ለመናገር ችሏል።—ዮሐንስ 14:9
አምላክ እንደሚደግፋችሁ ትምክህት ይኑራችሁ
20. አካሄዳችንን ከይሖዋ ጋር በማድረግ በትምክህት መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?
20 ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ በእግራቸው መሄድ ሲማሩ እርምጃዎቻቸው የተስተካከሉ አይደሉም። ተማምኖ መራመድን የሚማሩት እንዴት ነው? ልምምድና ጥረት በማድረግ ብቻ ነው። አካሄዳቸውን ከይሖዋ ጋር ያደረጉ ሰዎች በትምክህትና በተስተካከለ እርምጃ ለመመላለስ ይፈልጋሉ። ይህም ቢሆን ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ አካሄድን ከአምላክ ጋር ለማድረግ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን አመልክቷል:- “እንግዲህ በቀረውስ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፣ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፣ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን እንመክራችሁማለን።”—1 ተሰሎንቄ 4:1
21. አካሄዳችንን ከይሖዋ ጋር ስናደርግ ምን በረከቶችን ለማግኘት እንችላለን?
21 ሙሉ በሙሉ ለእሱ ያደርን ከሆንን አምላክ ከእሱ ጋር መመላለሳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። (ኢሳይያስ 40:29–31) ይህ ዓለም የሚሰጠው ማንኛውም ነገር አምላክ በመንገዱ ለሚመላለሱ ሰዎች ከሚያወርድላቸው በረከቶች ጋር በፍጹም ሊወዳደር አይችልም። እሱ ‘የሚረባንን ነገር የሚያስተምረንና በምንሄድበት መንገድ የሚመራን ነው። ትእዛዛቱን ብንሰማ ሰላማችን እንደ ወንዝ ጽድቃችንም እንደ ባሕር ሞገድ ይሆናል።’ (ኢሳይያስ 48:17, 18) አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር እንድናደርግ የቀረበልንን ግብዣ በመቀበልና ይህንም በታማኝነት በመፈጸም ከእሱ ጋር ለዘላለም ሰላም ሊኖረን ይችላል።
[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]
◻ አካሄድን ከእውነተኛው አምላክ ጋር ማድረግ ክብር የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ማጥናት፣ ራስን መወሰንና መጠመቅ አካሄድን ከይሖዋ ጋር ለማድረግ የሚወሰዱ የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች የሆኑት ለምንድን ነው?
◻ የኢየሱስን ፈለግ ልንከተል የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ አካሄዳችንን ከእሱ ጋር አድርገን በምንመላለስበት ጊዜ እንደሚደግፈን እንዴት እናውቃለን?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ማጥናት፣ ራስን መወሰንና መጠመቅ አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ለማድረግ የምንወስዳቸው የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች ናቸው