የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 12/1 ገጽ 13-18
  • ‘በዓመፃ ገንዘብ ወዳጆችን አብጁ’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘በዓመፃ ገንዘብ ወዳጆችን አብጁ’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘የይሖዋ ቁርባን’
  • ለቤተ መቅደሱ የተደረጉ መዋጮዎች
  • በክርስትና ዘመን የነበረው ተገቢ የሆነ የሀብት አጠቃቀም
  • ታማኝ መጋቢ
  • የለጋስነት ምሳሌ
  • ‘በዓመፃ ገንዘብ ወዳጆችን አብጁ’
  • እውነተኛ የሆነውን ሀብት መፈለግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • የመንግሥቱ ሥራዎች ወጪ የሚሸፈንበት መንገድ
    የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
  • የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • የተትረፈረፈ ልግስና ደስታ ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 12/1 ገጽ 13-18

‘በዓመፃ ገንዘብ ወዳጆችን አብጁ’

“በእርሱ [በዓመፃ ገንዘብ] ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው።”—ሉቃስ 16:9, 10

1. ሙሴና የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ከወጡ በኋላ ይሖዋን ያወደሱት እንዴት ነበር?

1 በተአምር መዳን ማለት ምንኛ እምነት የሚያጠነክር አጋጣሚ ነው! እስራኤላውያንን ከግብፅ ያወጣቸው ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ሙሴና እስራኤላውያን፦ “ጉልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፣ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፣ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ” ብለው መዘመራቸው ምንም አያስደንቅም።—ዘጸአት 15:1, 2፤ ዘዳግም 29:2

2. የይሖዋ ሕዝቦች ከግብፅ ምን ይዘው ወጡ?

2 እስራኤላውያን አዲስ ያገኙት ነፃነት በግብፅ ከነበሩበት ሁኔታ እንዴት የተለየ ነው! አሁን ይሖዋን ያለ አንዳች እንቅፋት ሊያመልኩት ይችላሉ። እንዲሁም ከግብፅ የወጡት ባዶ እጃቸውን አይደለም። ሙሴ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “የእስራኤልም ልጆች . . . ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ። እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት የፈለጉትን እንዲሰጡአቸው ሞገስን ሰጠ። እነርሱም ግብፃውያንን በዘበዙ።” (ዘጸአት 12:35, 36) ነገር ግን ይህን ከግብፅ ያገኙትን ሀብት እንዴት ተጠቀሙበት? ይህ ሀብት ‘ይሖዋን ከፍ ከፍ ለማድረግ’ አገልግሏልን? ከእነሱ ምሳሌ ምን እንማራለን?—ከ1 ቆሮንቶስ 10:11 ጋር አወዳድር።

‘የይሖዋ ቁርባን’

3. እስራኤላውያን ወርቅን ለሐሰት አምልኮ መጠቀማቸው ይሖዋ ምን እርምጃ እንዲወስድ አደረገው?

3 አምላክ ለእስራኤላውያን የሚሰጣቸውን መመሪያዎች ለመቀበል ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ለ40 ቀናት በቆየበት ወቅት ታች ሆነው እሱን ይጠብቁ የነበሩት ሰዎች ተሰላቹ። ሕዝቡም በጆሮዎቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች በማምጣት የሚያመልኩት ምስል እንዲሠራላቸው አሮንን ጠየቁት። አሮን መሠዊያም ጭምር ሠራላቸው፤ በነጋታውም ማልደው ተነስተው በዚያ ቦታ መሥዋዕት አቀረቡ። ወርቃቸውን ለዚህ ነገር ማዋላቸው በነፃ አውጪያቸው ዘንድ አስወድዷቸዋልን? በፍጹም አላስወደዳቸውም! ይሖዋም ሙሴን “አሁንም ቁጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ” ሲል ተናገረው። ምንም እንኳን የዓመፁ ቀንደኛ መሪዎች ከአምላክ በመጣ መቅሰፍት ቢገደሉም ይሖዋ ሕዝቡን ከማጥፋት የተቆጠበው ሙሴ አጥብቆ ስለተማጸነው ብቻ ነው።—ዘጸአት 32:1-6, 10-14, 30-35

4. ‘የይሖዋ ቁርባን’ ምንድን ነበር? ይህን ቁርባን የሚያቀርቡትስ እነማን ነበሩ?

4 ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ያላቸውን ሀብት ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ የመጠቀም አጋጣሚ አግኝተዋል። ከተለያየ ነገር “የእግዚአብሔርን ቁርባን” አመጡ። ለማደሪያው ድንኳን ግንባታና ማስጌጫ በስጦታ ከቀረቡት ነገሮች መካከል ወርቅ፣ ብር፣ መዳብ፣ ሰማያዊ ግምጃ፣ የተለያየ ቀለም የተነከሩ ጨርቆች፣ የበግ ቁርበት፣ የአቆስጣ ቁርበትና የግራር እንጨት ይገኙበታል። ታሪኩ መዋጮውን ያደረጉት ሰዎች በነበራቸው ዝንባሌ ላይ እንድናተኩር ያደርገናል። “የልብ ፈቃድ ያለው የእግዚአብሔርን ቁርባን ያምጣ።” (ዘጸአት 35:5-9) እስራኤላውያን ለዚህ ጥሪ ከፍተኛ ምላሽ ሰጥተዋል። ስለሆነም አንድ ምሁር እንደተናገሩት የማደሪያው ድንኳን አሠራር “እጅግ ውብና ማራኪ ግርማ ሞገስ” ያለው ነበር።--ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

ለቤተ መቅደሱ የተደረጉ መዋጮዎች

5, 6. ከቤተ መቅደሱ ጋር በተያያዘ ዳዊት ሀብቱን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ሌሎችስ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?

5 ምንም እንኳን ቋሚ የሆነው የይሖዋ የአምልኮ ቤት ግንባታ ሲካሄድ አመራር ይሰጥ የነበረው የእስራኤሉ ንጉሥ ሰሎሞን ቢሆንም አባቱ ዳዊት ለዚህ ግንባታ ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል። ዳዊት ብዛት ያለው ወርቅ፣ ብር፣ መዳብ፣ ብረት፣ ጣውላና የከበሩ ድንጋዮችን አሰባስቧል። ዳዊት ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፦ “የአምላኬን ቤት ስለ ወደድሁ፣ ለመቅደሱ ካዘጋጀሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ። የቤቶቹ ግንብ ይለበጡበት ዘንድ . . . ሦስት ሺህ መክሊት ወርቅ፣ ሰባት ሺህም መክሊት ጥሩ ብር . . . ሰጥቻለሁ።” ዳዊት ሌሎችም ለጋሶች እንዲሆኑ አበረታቷል። የሰጡት ምላሽ በጣም ከፍተኛ ነበረ። ወርቁን፣ ብሩን፣ መዳቡን፣ ብረቱንና የከበሩ ድንጋዮችን በገፍ አመጡ። “በፍጹም ልባቸውም” ሕዝቡ “ለእግዚአብሔር በፈቃዳቸው” ስጦታ አቀረቡ።—1 ዜና መዋዕል 22:5፤ 29:1-9

6 እስራኤላውያን በዚህ የፈቃደኝነት መዋጮ አማካኝነት ለይሖዋ አምልኮ ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት ገልጸዋል። ዳዊት “ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው?” ሲል በትሕትና ጸልዮአል። ለምን? “ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፣ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና . . . እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ።”—1 ዜና መዋዕል 29:14, 17

7. ከአሞጽ ዘመን ምን የማስጠንቀቂያ ትምህርት እናገኛለን?

7 ይሁን እንጂ የእስራኤል ነገዶች የይሖዋን አምልኮ በአእምሮአቸውና በልባቸው ውስጥ በአንደኛ ቦታ ማስቀመጣቸውን ሳይቀጥሉ ቀርተዋል። የተከፋፈለችው እስራኤል በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በመንፈሳዊ ግዴለሽ በመሆኗ ጥፋተኛ ሆናለች። በሰሜን ያሉትን የአሥሩን ነገዶች የእስራኤል መንግሥት በተመለከተ ይሖዋ በአሞጽ አማካኝነት “በጽዮን ላሉ ዓለመኞች፣ በሰማርያም ተራራ ላይ ተዘልለው ለተቀመጡ . . . ወዮላቸው!” ሲል ተናግሯል። ‘ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ እንደሚተኙ፣ በምንጣፋቸውም ላይ ተደላድለው እንደተቀመጡ፣ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን እንደሚበሉ በፋጋ ወይን ጠጅ እንደሚጠጡ’ አድርጎ ገልጿቸዋል። ሆኖም የተንደላቀቀ አኗኗራቸው ከለላ አልሆነላቸውም። አምላክ እንዲህ ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጠ፦ “በምርኮ መጀመሪያ ይማረካሉ፣ ተደላድለው ከተቀመጡትም ዘንድ ዘፈን ይርቃል።” እስራኤላውያን በ740 ከዘአበ በአሦራውያን እጅ ተሠቃዩ። (አሞጽ 6:1, 4, 6, 7) ከጊዜ በኋላ ደቡባዊው የይሁዳ መንግሥትም በተመሳሳይ በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ውስጥ ወድቆ ነበር።—ኤርምያስ 5:26-29

በክርስትና ዘመን የነበረው ተገቢ የሆነ የሀብት አጠቃቀም

8. በሀብት አጠቃቀም ረገድ ዮሴፍና ማርያም ምን ጥሩ ምሳሌ ትተዋል?

8 ከዚህ በተቃራኒው ግን በኋለኞቹ ዘመናት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች የነበሩበት አንፃራዊ የድህነት ሁኔታ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ከማሳየት አላገዳቸውም። ማርያምንና ዮሴፍን ተመልከቱ። ማርያምና ዮሴፍ አውግስጦስ ቄሣር ያወጣውን ድንጋጌ በመታዘዝ የቤተሰቦቻቸው የትውልድ ከተማ ወደሆነችው ወደ ቤተልሔም ሄዱ። (ሉቃስ 2:4, 5) ኢየሱስ የተወለደው እዚያ ሳሉ ነበር። ከአርባ ቀን በኋላ ዮሴፍና ማርያም ሕጉ የሚያዘውን የመንጻት መሥዋዕት ለማቅረብ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ሄዱ። ማርያም ሁለት የወፍ ጫጩቶችን ለመሥዋዕት ማቅረቧ ዝቅተኛ ኑሮ የነበራቸው መሆናቸውን የሚያመለክት ነው። እሷም ሆነች ዮሴፍ ለይሖዋ መሥዋዕት ላለማቅረብ ድህነታቸውን እንደሰበብ አድርገው አልተጠቀሙበትም። ከዚህ ይልቅ በታዛዥነት ያለቻቸውን አነስተኛ ነገር ተጠቅመውባታል።—ዘሌዋውያን 12:8፤ ሉቃስ 2:22-24

9-11. (ሀ) በማቴዎስ 22:21 ላይ ያሉት የኢየሱስ ቃላት ገንዘብን ስለምንጠቀምበት መንገድ ምን መመሪያ ይዘውልናል? (ለ) የመበለቲቱ አነስተኛ መዋጮ እንዲያው ከንቱ ያልነበረው ለምንድን ነው?

9 ከጊዜ በኋላ ፈሪሳውያንና የሄሮድስ ወገን ደጋፊዎች “እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን፤ ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ ልተፈቀደም?” የሚል ጥያቄ በማቅረብ ኢየሱስን ለማምታታት ሞክረው ነበር። የኢየሱስ መልስ አስተዋይነቱን አሳይቷል። ኢየሱስ ወደ ሰጡት ሳንቲም በማመልከት “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” አላቸው። እነሱም “የቄሣር ነው” አሉት። “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” በማለት ጥበብ ያለበት ማጠቃለያ ሰጠ። (ማቴዎስ 22:17-21) ኢየሱስ ሳንቲሙን ያሳተመው ባለ ሥልጣን ቀረጦች መከፈል አለባቸው ብሎ እንደሚጠብቅ ያውቅ ነበር። ሆኖም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን “የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር” ለመስጠት ጭምር እንደሚጥር ተከታዮቹም ሆኑ ጠላቶቹ በዚያ አጋጣሚ እንዲገነዘቡ አድርጓል። ይህም አንድ ሰው ያለውን ንብረት በአግባብ መጠቀምን ይጨምራል።

10 ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተመለከተው አንድ አጋጣሚ ይህን ያስረዳል። ‘የመበለቶችን ቤት የሚበሉትን’ ስግብግብ የሆኑ ጻፎች አወገዛቸው። ብዙም ሳይቆይ “ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ” በማለት ሉቃስ ይገልጻል። “አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል [ኢየሱስ] አየና፦ እውነት እላችኋለሁ፣ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጉድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ።” (ሉቃስ 20:46, 47፤ 21:1-4) አንዳንድ ሰዎች ቤተ መቅደሱ በከበሩ ድንጋዮች ያጌጠ መሆኑን ገለጹ። ኢየሱስ “ይህማ የምታዩት ሁሉ፣ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል” ሲል መለሰ። (ሉቃስ 21:5, 6) የዚያች መበለት አነስተኛ መዋጮ እንዲያው ከንቱ ነበርን? በፍጹም አልነበረም። በወቅቱ ይሖዋ ያቋቋመውን ዝግጅት ደግፋለች።

11 ኢየሱስ ለእውነተኛ ተከታዮቹ እንዲህ አላቸው፦ “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፣ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” (ሉቃስ 16:13) እንግዲያው በገንዘብ አጠቃቀማችን ረገድ ትክክለኛ ሚዛናዊነት ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?

ታማኝ መጋቢ

12-14. (ሀ) ክርስቲያኖች በተገቢው መንገድ መያዝ ያለባቸው የትኛውን ሀብት ነው? (ለ) ዛሬ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች መጋቢነታቸውን በታማኝነት የሚያከናውኑት በምን ጥሩ መንገዶች ነው? (ሐ) ዛሬ ያለውን የአምላክ ሥራ ለመደገፍ የሚውለው ገንዘብ የሚመጣው ከየት ነው?

12 ሕይወታችንን ለይሖዋ ስንወስን ያለን ማንኛውም ነገር፣ ያለን አንጡራ ሀብት በሙሉ የእሱ ነው ማለታችን ነው። ታዲያ ያለንን ነገር እንዴት መጠቀም ይኖርብናል? የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት ወንድም ሲ ቲ ራስል በጉባኤ ውስጥ ያለውን ክርስቲያናዊ አገልግሎት አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው ጊዜውን፣ ጉልበቱን፣ ገንዘቡንና የመሳሰሉትን በሚገባ እንዲይዝ በጌታ እንደተሾመ አድርጎ ራሱን መቁጠር አለበት፤ እንዲሁም እያንዳንዱ እነዚህን ተሰጥኦዎቹን አቅሙ በፈቀደለት መጠን ለጌታ ክብር ሊጠቀምባቸው መጣር አለበት።”—ዘ ኒው ክሬሽን ገጽ 345

13 “በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል” በማለት 1 ቆሮንቶስ 4:2 ይገልጻል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንድ ዓለም አቀፍ አካል በመሆን የማስተማር ችሎታቸውን በሚገባ በማሻሻልና ጊዜያቸውን በተቻላቸው መጠን ለክርስቲያናዊ አገልግሎት በማዋል ከላይ ካለው መግለጫ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ ይጥራሉ። ከዚህም በላይ የፈቃደኛ ሠራተኞች ቡድኖች የአካባቢ የሕንፃ ሥራ ኮሚቴ በሚሰጠው መመሪያ ሥር በመሆን ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በፈቃደኝነት በመስጠት ለአምልኮ የሚያገለግሉ ግሩም የሆኑ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ይሠራሉ። በዚህ ሁሉ ይሖዋ በጣም ይደሰታል።

14 ይህን በጣም ሰፊ የማስተማር ዘመቻና የግንባታ ሥራ ለማገዝ የሚውለው ገንዘብ የሚገኘው ከየት ነው? የማደሪያው ድንኳን በተሠራበት ጊዜ እንደነበረው ፈቃደኛ ልብ ካላቸው ሰዎች ነው። እኛ በየግል በዚህ ተካፋይ ነንን? ገንዘባችንን የምንጠቀምበት መንገድ የይሖዋ አገልግሎት ለእኛ ከሁሉ የበለጠ ቦታ እንዳለው ያሳያልን? ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ታማኝ መጋቢዎች እንሁን።

የለጋስነት ምሳሌ

15, 16. (ሀ) በጳውሎስ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ለጋስነት ያሳዩት እንዴት ነበር? (ለ) ይህን አሁን የምናጠናውን ትምህርት እንዴት አድርገን መመልከት ይኖርብናል?

15 ሐዋርያው ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ ስላሉት ክርስቲያኖች የለጋስነት መንፈስ ጽፏል። (ሮሜ 15:26) ራሳቸው ችግረኞች ቢሆኑም እንኳን ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ወዲያው አዋጥተዋል። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችም ትርፋቸውን በመስጠት የሌሎችን ጉድለት ለማሟላት በተመሳሳይ በልግስና እንዲሰጡ አበረታቷቸዋል። ጳውሎስ በግድ ገንዘብ ያስከፍል ነበር ብሎ ማንም ሊከሰው አይችልም። “በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፣ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል። እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” ሲል ጽፏል።—2 ቆሮንቶስ 8:1-3, 14፤ 9:5-7, 13

16 ወንድሞቻችንና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ዛሬ ላለው ዓለም አቀፍ የመንግሥቱ ሥራ በልግስና የሚያደርጉት መዋጮ ይህን መብት ምን ያህል ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን እንዳሳሰባቸው ሁሉ እኛም ይህን ሐሳብ እንደማሳሰቢያ አድርገን ብንወስደው ጥሩ ነው።

17. ጳውሎስ በምን ዓይነት መንገድ እንዲያዋጡ አበረታቷል? ይህስ ዛሬ ሊሠራበት ይችላልን?

17 ጳውሎስ ወንድሞች በአሰጣጣቸው ረገድ አንድ ወጥ የሆነ አሠራር እንዲከተሉ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። እንዲህ አለ፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ።” (1 ቆሮንቶስ 16:1, 2) በጉባኤም ሆነ በቀጥታ በአቅራቢያችን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ አማካኝነት ለምናደርገው መዋጮ ይህ ለእኛም ሆነ ለልጆቻችን እንደ ምሳሌ ሊያገለግል ይችላል። በአንዲት የምሥራቅ አፍሪካ ከተማ እንዲሰብኩ የተመደቡ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ እንዲገኙ ጋበዙ። ይህ የመጀመሪያው ስብሰባ እንዳበቃ “ለመንግሥቱ ሥራ የሚሆን መዋጮ” የሚል ምልክት በተለጠፈበት ሣጥን ውስጥ ቀስ ብለው በዘዴ የተወሰኑ ሳንቲሞችን ጨመሩ። በስብሰባው ላይ የተገኙ ሌሎችም እንዲሁ አደረጉ። እነዚህ አዲሶች የክርስቲያን ጉባኤ ሆነው ከተደራጁ በኋላ የክልል የበላይ ተመልካች ሲጎበኛቸው ሳያቋርጡ ለሚያደርጉት መዋጮ አመሰገናቸው።—መዝሙር 50:10, 14, 23

18. በችግር ላይ ያሉ ወንድሞቻችንን ልንረዳ የምንችለው እንዴት ነው?

18 እኛም ያለንን ሀብት የተፈጥሮ አደጋ የደረሰባቸውንና በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙትን ለመርዳት ለመጠቀም የምንችልበት አጋጣሚ አለን። ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብጥብጥ ወዳጥለቀለቀው የዓለም ክፍል ወደ ምሥራቅ አውሮፓ የእርዳታ ቁሳቁሶች መላካቸውን ስናነብ በጣም ተደስተናል! የተደረጉት የቁሳቁስም ሆነ የገንዘብ መዋጮዎች ወንድሞቻችን ያላቸውን ለጋስነት እንዲሁም ችግር ከደረሰባቸው ክርስቲያኖች ጋር ያላቸውን አንድነትና ኅብረት አሳይተዋል።—2 ቆሮንቶስ 8:13, 14

19. በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉትን ለማበረታታት ምን ተግባራዊ የሆኑ ነገሮችን ልናደርግ እንችላለን?

19 አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ሚስዮናውያንና የቤቴል ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሠማርተው ያሉ ወንድሞቻችን የሚያከናውኑትን ሥራ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን፤ አይደለም እንዴ? ሁኔታዎቻችን በሚፈቅዱልን መጠን በቀጥታ አንዳንድ ቁሳዊ ድጋፍ ልናደርግላቸው እንችል ይሆናል። ለምሳሌ ያክል የክልል የበላይ ተመልካች ጉባኤያችሁን በሚጎበኝበት ጊዜ የሚያርፍበት ክፍል ልትሰጡት፣ ምግብ ልትጋብዙት ወይም ለመጓጓዣ ወጪው የሚሆን ድጋፍ ልታደርጉለት ትችሉ ይሆናል። አገልጋዮቹ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው የሚፈልገው ሰማያዊ አባታችን እንዲህ ዓይነቱን ለጋስነት በቸልታ አያልፈውም። (መዝሙር 37:25) ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ቀለል ያሉ ምግቦችን ብቻ የመጋበዝ አቅም የነበረው አንድ ወንድም ተጓዥ የበላይ ተመልካቹንና ሚስቱን ቤቱ ጋበዛቸው። ባልና ሚስቱ ወደ ማታ ጊዜ ለሚደረገው የመስክ አገልግሎት ሲወጡ ወንድም ለእንግዶቹ አንድ ፖስታ ሰጣቸው። በፖስታው ውስጥ (አንድ የአሜሪካ ዶላር የሚሆን) የባንክ ኖትና “ለሻይ ወይም ለአንድ ጋሎን ቤንዚን ብትሆናችሁ ብዬ ነው” የሚል በእጅ የተጻፈ ማስታወሻ ነበረበት። ትሕትና የተሞላበት እንዴት ያለ ግሩም የአድናቆት መግለጫ ነው!

20. የትኛውን መብትና ኃላፊነት ቸል ማለት አንፈልግም?

20 የይሖዋ ሕዝብ በመንፈሳዊ ተባርኳል! አዲስ የወጡ ጽሑፎችን፣ ግሩም የሆኑ ትምህርቶችንና ተግባራዊ ምክሮችን በምናገኝባቸው የክልልና የወረዳ ስብሰባዎቻችን ላይ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ግብዣ ይቀርብልናል። ለምናገኛቸው መንፈሳዊ በረከቶች ልባችን በአድናቆት ሲሞላ የአምላክን መንግሥት ፍላጎት በዓለም ዙሪያ ለማስፋፋት የሚውል የገንዘብ መዋጮ የማድረግ መብትና ኃላፊነት እንዳለን አንዘነጋም።

‘በዓመፃ ገንዘብ ወዳጆችን አብጁ’

21, 22. “የዓመፃ ገንዘብ” በቅርቡ ምን ይደርስበታል? ይህስ አሁኑኑ ምን እንድናደርግ ይጠይቅብናል?

21 በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን አምልኮ እንደምናስቀድም ልናሳይ የምንችልባቸው በጣም ብዙ መንገዶች አሉ፤ በተለይም ይህን የምናሳይበት ዋነኛው መንገድ “የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፣ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ” የሚለውን የኢየሱስን ምክር መከተልን የሚጨምር ነው።—ሉቃስ 16:9

22 ኢየሱስ የዓመፃ ገንዘብ ከንቱ እንደሚሆን እንደተናገረ ልብ በሉ። አዎን፣ የዚህ ሥርዓት ገንዘብ ዋጋቢስ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። “ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጉድፍ ይሆናል” ሲል ሕዝቅኤል ትንቢት ተናግሯል። “በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም።” (ሕዝቅኤል 7:19) ይህ ሁኔታ እስከሚከሰት ድረስ ቁሳዊ ንብረቶቻችንን የምንጠቀምበትን መንገድ በተመለከተ ጥበብና ማስተዋል ማሳየት አለብን። ይህ ከሆነ ኢየሱስ “እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፣ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? . . . ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” ሲል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሳንከተል መቅረታችን ያስከተለብንን ሁኔታ ወደኋላ ተመልሰን በቁጭት አንመለከተውም።—ሉቃስ 16:11-13

23. በጥበብ ልንጠቀምበት የሚገባን ነገር ምንድን ነው? ሽልማታችንስ ምን ይሆናል?

23 እንግዲያው ሁላችንም የይሖዋን አምልኮ በሕይወታችን ውስጥ በአንደኛ ቦታ እንድናስቀምጥና በንብረታችን በጥበብ እንድንጠቀም የተሰጡንን እነዚህን ማሳሰቢያዎች ሰምተን በታማኝነት እንከተል። እንዲህ ካደረግን ገንዘብ ዋጋ ቢስ በሚሆንበት ጊዜ በሰማያዊቷ መንግሥት ውስጥ ወይም በምድር ላይ ከሚገኝ ዘላለማዊ ሕይወት ተስፋ ጋር “በዘላለም ቤቶች” እንደሚቀበሉን ተስፋ ከሰጡን ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት ልናበጅ እንችላለን።—ሉቃስ 16:9

ታስታውሳለህን?

◻ ለማደሪያው ድንኳን ሥራ እንዲያዋጡ ይሆዋ ላቀረበው ጥሪ እስራኤላውያን እንዴት ያለ ምላሽ ሰጡ?

◻ የመበለቲቱ መዋጮ ከንቱ ያልነበረው ለመንድን ነው?

◻ ክርስቲያኖች ሀብታቸውን የሚጠቀሙበትን መንገድ በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለባቸው?

◻ በገንዘብ እጠቃቀማቸን ረገድ ከቁጭት ልንድን የምንቸለው እንዴት ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመበለቲቱ መዋጮ ምንም እንኳ እነስተኛ ቢሆንም ከንቱ እልነበረም

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መዋጮዎቻችን ዓለም አቀፍ የመንግሥቱን ሥራ ያግዛሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ