የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 5/15 ገጽ 26-27
  • ይሖዋን ለማገልገል ዕድሜዋ አላለፈም ነበር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋን ለማገልገል ዕድሜዋ አላለፈም ነበር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ከመቅደስ አትለይም ነበር”
  • ያልተጠበቀ በረከት
  • የሐና መልካም ምሳሌ
  • ሐና
    ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል
  • አንዲት አስተማሪ የነበራትን አመለካከት ለወጠች
    ንቁ!—2009
  • ላትቪያ ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • በእርጅና ዘመን በመንፈሳዊ ማፍራት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 5/15 ገጽ 26-27

ይሖዋን ለማገልገል ዕድሜዋ አላለፈም ነበር

በዕድሜ የገፉ ብዙ ሰዎች የቀረው የሕይወታቸው ዘመን ለመደሰት ምንም ተስፋ እንዳልያዘላቸው ይሰማቸዋል። አንድ በዕድሜ የገፉ እውቅ ተዋናይ እንኳን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “ሕይወቴን አዘበራርቄዋለሁ፤ ከአሁን በኋላ ለማስተካከል ጊዜው አልፏል . . . አንዳንዴ ብቻዬን ስጓዝ ያሳለፍኩትን ጊዜ መለስ ብዬ እቃኘዋለሁ፤ ግን ባለፈው አኗኗሬ አልደሰትም . . . በሄድኩበት ቦታ ሁሉ እረፍት የለኝም፤ ተረጋግቼ አንድ ቦታ ለመቀመጥ አልቻልኩም።”

ከ2,000 ዓመታት በፊት ትኖር የነበረች አንዲት አረጋዊት ግን እንዲህ ዓይነት ችግር አልነበረባትም። የ84 ዓመት መበለት ብትሆንም ንቁ፣ ደስተኛና በልዩ መንገድ የአምላክን ሞገስ ያገኘች ሴት ነበረች። ሐና ትባል ነበር። ደስተኛ ያደረጋት ልዩ ምክንያት ነበራት። ይህ ምን ነበር?

“ከመቅደስ አትለይም ነበር”

የወንጌል ጸሐፊ የነበረው ሉቃስ ከሐና ጋር ያስተዋውቀናል። በእስራኤል ውስጥ “ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች” ይላል። ነቢይት እንደመሆኗ መጠን በተለየ መንገድ የአምላክን መንፈስ ቅዱስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ስጦታ ያገኘች ሴት ነበረች። ሐና በተለይ በአንድ ልዩ አጋጣሚ ላይ ትንቢት ለመናገር ትልቅ መብት አግኝታ ነበር።

ሉቃስ እንዲህ ብሏል፦ “እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርስዋም ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ሆና በጣም አርጅታ ነበር።” (ሉቃስ 2:36, 37) ሐና መበለት የሆነቸው ገና ወጣት እያለች ይመስላል። በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ባል የሞተባቸው ክርስቲያን ሴቶች የሚወዱትን ባል በሞት ማጣት ምን ያህል ቅስም የሚሰብር እንደሆነ ያውቁታል። በጊዜያችን እንደሚገኙት ብዙ አምላካዊ ሴቶች ሁሉ ሐናም ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ለአምላክ የምታቀርበውን አገልግሎት እንዲገታባት አልፈቀደችም።

ሐና በኢየሩሳሌም ከሚገኘው “መቅደስ ተለይታ እንደማታውቅ” ሉቃስ ይነግረናል። (ሉቃስ 2:37) በአምላክ ቤት ከማገልገል የሚገኘውን በረከት ከልቧ ታደንቅ ነበር። እንደ እስራኤላዊው መዝሙራዊ ዳዊት ይሖዋን የምትለምነው አንድ ነገር ብቻ እንደነበራት በአድራጎቷ አሳይታለች። ይህስ ምን ነበር? ዳዊት እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “እግዚአብሔርን አንድ ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፣ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ ነው።” (መዝሙር 27:4) በዚህ ረገድም ሐና አዘውትረው በይሖዋ የአምልኮ ቦታ በመገኘታቸው እንደሚደሰቱት ክርስቲያን ሴቶች ነበረች።

ሐና ለይሖዋ ቀንና ሌሊት የተቀደሰ አገልግሎት አቅርባለች። ይህንንም ያደረገችው ሐዘኗንና ውስጣዊ ምኞቷን በሚገልጽ “ጾምና ጸሎት” ነበር። (ሉቃስ 2:37) ለአያሌ መቶ ዘመናት የቆየው የአይሁድ በአሕዛብ ግዛት ሥር መውደቅና ወደ ክህነቱና ወደ ቤተ መቅደሱ እንኳን ሳይቀር የዘለቀው መንፈሳዊ ብክለት ለሐና ወደ ይሖዋ በጾምና በጸሎት መቅረብ ምክንያት ሳይሆናት አልቀረም። ደስተኛ የምትሆንበትም ምክንያት ነበራት። በተለይ በእውነትም ታሪካዊ በነበረው ቀን በ2 ከዘአበ ላይ በተፈጸመው እንግዳ ነገር የምትደሰትበት ምክንያት ነበራት።

ያልተጠበቀ በረከት

በዚህ ታላቅ ትርጉም በነበረው ቀን ላይ ሕጻኑን ኢየሱስን እናቱ ማሪያምና አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ ይዘውት ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ነበር። በዕድሜ የገፋው ስምዖን ሕጻኑን አይቶ በዚያ አጋጣሚ ትንቢታዊ ቃላትን ተናገረ። (ሉቃስ 2:25–35) ሐና እንደተለመደው በመቅደሱ ተገኝታ ነበር። “በዚያችም ሰዓት” ይላል ሉቃስ ‘ቀረበች’። (ሉቃስ 2:38) በእርጅና የደከሙት አይኖቿ ወደፊት መሲሕ የሚሆነውን ሕጻን ሲመለከቱ ሐና እንዴት በደስታ ተውጣ ይሆን!

ከዚያ አርባ ቀናት ቀደም ብሎ የአምላክ መልአክ ለእረኞች እንደሚከተለው ባሉ አስገራሚ ቃላት ተናግሯቸው ነበር፦ “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” ብዙ የሰማይ ሠራዊት ይሖዋን በማመስገን፦ “ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።” (ሉቃስ 2:8–14) በተመሳሳይ ሐናም ወደፊት መሲሕ ስለሚሆነው ሕጻን ለመመሥከር ተገፋፋች።

ሐና ሕጻኑን ኢየሱስን በማየት “እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ [ነፃ መውጣት አዓት] ለሚጠባበቁት ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።” (ሉቃስ 2:38) ሕጻኑን ኢየሱስን በቤተ መቅደስ ለማየት እንደታደለው አረጋዊ ስምዖን ሁሉ እርሷም ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተሰጠበትን ነፃ አውጪ ለማየት ስትጓጓ፣ ስትጸልይና ስትጠባበቅ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ኢየሱስ የመሆኑን ምሥራች ለብቻዋ ልትይዘው የማትችለው ደስታ ነበር።

ምንም እንኳ ሐና ኢየሱስ እስኪያድግ ድረስ በሕይወት እኖራለሁ ብላ ልትጠብቅ ባትችልም ምን አደረገች? ይህ ወደፊት የሚመጣ መሲሕ ሕዝቡን ነፃ ስለማውጣቱ ለሌሎች በደስታ መሠከረች።

የሐና መልካም ምሳሌ

በዓለም ላይ ከሚገኙ ሃይማኖታዊ ሰዎች መካከል በሰማኒያ አራት ዓመታቸው ይህንን ዓይነት ምሥክርነት የሚሰጡ ወይም ደግሞ ቀንና ሌሊት በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምን ያህል ይገኛሉ? ከዚያ ቀደም ብለው ጡረታ እንደሚጠይቁ የታወቀ ነው። ሐናና ስምዖን ግን ከዚህ የተለዩ ነበሩ። አረጋውያን ለሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ መልካም ምሳሌ ትተዋል። የይሖዋን የአምልኮ ቦታ በእርግጥ ይወዱ ነበር። ይሖዋንም በሙሉ ልባቸው አወድሰውታል።

ሐና ለአምላክ አክብሮት ያላት መበለት እንዴት መሆን እንዳለባት ትልቅ ምሳሌ ትታለች። እንዲያውም ሉቃስ ስለዚህች ትሑት መበለት የሰጠው መግለጫ በ1 ጢሞቴዎስ 5:3–16 ላይ ከተገለጸው ምስጋና የሚገባቸው መበለቶች ብቃት ጋር በትክክል ይስማማል። በዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደዚህ ዓይነት መበለት ‘ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ የምትኖር’ “የአንድም ባል ሚስት የነበረች” እና ‘መልካም ሥራ በማድረግ የምትተጋ’ መሆን እንዳለባት ተናግሯል።

ዛሬ በምድር ዙሪያ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ቀንና ሌሊት ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡ ታማኝ አረጋዊያን መበለቶችን እናገኛለን። በመካከላችን እነዚህን ዘመናዊ ‘ሐናዎች’ በማግኘታችን እንዴት ደስ ይለናል!

ዕድሜያቸው የገፋ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ለአምለክ ራሳቸውን ሲወስኑና ይህንንም በውሃ ጥምቀት ሊያሳዩ ይችላሉ። አረጋውያን ይሖዋን ለማገልገልና አሁን በሰማይ ስለተቋቋመችውና በቅርቡም ለታዛዥ የሰው ልጆች የተትረፈረፉ በረከቶችን ስለምታመጣው የይሖዋ መንግሥት ለመናገር ዕድሜያቸው ገና አላለፈም። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ሐና በልዩ መንገድ እንደተባረከች ሁሉ አሁንም ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡ አረጋውያን የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ሊያገኙ ይችላሉ። ይሖዋን ለማገልገልና ቅዱሱን ስሙን ለማወደስ ሐና ዕድሜዋ አላለፈባትም። የእነርሱም ሁኔታ ከእርሷ ያልተለየ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ