-
“ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም”መጠበቂያ ግንብ—2002 | መስከረም 1
-
-
14. ስለ ደጉ ሳምራዊ በሚናገረው ምሳሌ ውስጥ ኢየሱስ መልእክቱን በግልጽ ለማስተላለፍ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” የሚወስደውን መንገድ መምረጡ ትርጉም ያለው የሚያደርገው ምንድን ነው?
14 ሁለተኛ፣ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚናገረውን ምሳሌ አስታውስ። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ምሳሌውን መናገር ጀመረ:- “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።” (ሉቃስ 10:30) ኢየሱስ መልእክቱን ለማስጨበጥ በምሳሌው ውስጥ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” የሚወስደውን መንገድ መጠቀም የፈለገው ሆን ብሎ ነው። ይህን ምሳሌ የተናገረው ከኢየሩሳሌም እጅግም በማትርቀው በይሁዳ ሆኖ ነው። ስለዚህም አድማጮቹ መንገዱን ጥሩ አድርገው የሚያውቁት መሆን አለበት። ይህ መንገድ በተለይ ለብቻው ለሚጓዝ ሰው በጣም አደገኛ ነው። መንገዱ ጠመዝማዛ በመሆኑ አድብተው ለሚዘርፉ ወንበዴዎች የተመቻቸ ነበር።
15. ስለ ደጉ ሳምራዊ ከሚናገረው ምሳሌ ውስጥ ካህኑና ሌዋዊው ላሳዩት ግዴለሽነት ማስተባበያ ማቅረብ የማይቻለው ለምንድን ነው?
15 ኢየሱስ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ” ብሎ መናገሩ ሌላም ትኩረት የሚስብ ነገር አለው። በታሪኩ መሠረት በመጀመሪያ አንድ ካህን ቀጥሎም አንድ ሌዋዊ በዚያ መንገድ ያለፉ ሲሆን አንዳቸውም ቢሆኑ ጉዳት ለደረሰበት ሰው የእርዳታ እጃቸውን አልዘረጉም። (ሉቃስ 10:31, 32) ካህናት ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ሲሆን ሌዋውያን ደግሞ በሥራ ያግዟቸው ነበር። በኢያሪኮና በኢየሩሳሌም መካከል ያለው ርቀት 23 ኪሎ ሜትር ብቻ በመሆኑ ብዙ ካህናትና ሌዋውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሥራ በማይኖራቸው ጊዜ ኢያሪኮ ይቀመጡ ነበር። በዚህም የተነሳ በዚያ መንገድ ላይ ካህን ወይም ሌዋዊ ሲያልፍ ማየት የተለመደ ነበር። በተጨማሪም ካህኑም ሆነ ሌዋዊው የተነሱት ‘ከኢየሩሳሌም’ እንደሆነ ልብ በል። ስለሆነም ከቤተ መቅደሱ እየተመለሱ ነበር።b በመሆኑም ‘ጉዳት የደረሰበትን ሰው ሳይረዱት የቀሩት የሞተ መስሏቸው ነው፤ ሬሳ መንካት ደግሞ ስለሚያረክስ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሰጡትን አገልግሎት ለጊዜውም ቢሆን ያስተጓጉልባቸው ነበር’ በማለት እነዚህ ሰዎች ላሳዩት ግዴለሽነት ማንም ማስተባበያ ማቅረብ አይችልም። (ዘሌዋውያን 21:1, 2፤ ዘኍልቍ 19:11, 16) ኢየሱስ ምሳሌውን የሚናገረው አድማጮቹ ከሚያውቁት ነገር ተነስቶ እንደነበር ይህ በግልጽ አያሳይምን?
-
-
“ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም”መጠበቂያ ግንብ—2002 | መስከረም 1
-
-
b ኢየሩሳሌም ከኢያሪኮ ይልቅ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ትገኝ ነበር። ስለዚህ በምሳሌው ውስጥ እንደተገለጸው አንድ ሰው “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” ጉዞ ሲያደርግ “ወረደ” ተብሎ መነገሩ ምክንያታዊ ነው።
-