የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • jy ምዕ. 77 ገጽ 180-ገጽ 181 አን. 1
  • ኢየሱስ ሀብትን በተመለከተ ምክር ሰጠ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኢየሱስ ሀብትን በተመለከተ ምክር ሰጠ
  • ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የውርስ ጥያቄ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ዝነኛ ስብከት
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • ‘በአምላክ ዘንድ ሀብታም’ ነህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ታዋቂው የተራራ ስብከት
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
ለተጨማሪ መረጃ
ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
jy ምዕ. 77 ገጽ 180-ገጽ 181 አን. 1
አንድ ሀብታም ሰው ስላከማቸው ሀብት እያሰበ ሲደሰት

ምዕራፍ 77

ኢየሱስ ሀብትን በተመለከተ ምክር ሰጠ

ሉቃስ 12:1-34

  • የሀብታሙ ሰው ምሳሌ

  • ኢየሱስ ስለ ቁራዎችና ስለ አበቦች ተናገረ

  • መንግሥቱን የሚወርስ “ትንሽ መንጋ”

ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት እየተመገበ ሳለ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ደጅ ተሰብስቦ እየጠበቀው ነው። በገሊላም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። (ማርቆስ 1:33፤ 2:2፤ 3:9) በይሁዳ ብዙዎች ሊያዩትና የሚናገረውን ሊሰሙ ፈልገዋል፤ እነዚህ ሰዎች፣ አብረውት እየተመገቡ ካሉት ፈሪሳውያን በጣም የተለየ አመለካከት አላቸው።

ኢየሱስ መጀመሪያ የተናገረው ነገር ለደቀ መዛሙርቱ ልዩ ትርጉም አለው፤ “ከፈሪሳውያን እርሾ ይኸውም ከግብዝነት ተጠንቀቁ” አላቸው። ኢየሱስ ይህን ማስጠንቀቂያ ከዚህ ቀደምም ሰጥቷል፤ ሆኖም በምሳ ግብዣው ላይ የተመለከተው ነገር ይህ ምክር ወቅታዊ መሆኑን ይጠቁማል። (ሉቃስ 12:1፤ ማርቆስ 8:15) ፈሪሳውያን ሃይማኖተኛ በመምሰል ክፋታቸውን ለመሸፈን ቢሞክሩም አደገኛ መሆናቸው መጋለጥ አለበት። ኢየሱስ “የተሰወረ መገለጡ፣ ሚስጥር የሆነም መታወቁ አይቀርም” በማለት አብራራ።—ሉቃስ 12:2

ከተሰበሰቡት ሰዎች ብዙዎቹ በገሊላ ሲያስተምር ሰምተውት የማያውቁ የይሁዳ ነዋሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። በመሆኑም ቀደም ሲል የተናገራቸውን ጠቃሚ ሐሳቦች ደገመ። አድማጮቹን በሙሉ “ሥጋን የሚገድሉትን ከዚያ በላይ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ” በማለት አሳሰባቸው። (ሉቃስ 12:4) ተከታዮቹ፣ አምላክ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚሰጣቸው መተማመናቸው አስፈላጊ መሆኑን በድጋሚ ጠበቅ አድርጎ ገለጸ። በተጨማሪም የሰውን ልጅ እንደሚደግፉ ማሳየትና አምላክ እንደሚረዳቸው መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል።—ማቴዎስ 10:19, 20, 26-33፤ 12:31, 32

ከዚያም ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው “መምህር፣ ወንድሜ ውርሳችንን እንዲያካፍለኝ ንገረው” በማለት በወቅቱ ያሳሰበውን ነገር ገለጸ። (ሉቃስ 12:13) ሕጉ የበኩር ልጅ ከውርሱ ሁለት እጥፍ እንደሚወስድ ስለሚናገር በዚህ ረገድ ውዝግብ ሊፈጠር አይገባም። (ዘዳግም 21:17) ሆኖም ይህ ሰው ከሕጋዊ ድርሻው የበለጠ ማግኘት የፈለገ ይመስላል። ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ውስጥ እጁን ባለማስገባት የጥበብ እርምጃ ወስዷል። “አንተ ሰው፣ በእናንተ መካከል ፈራጅና ዳኛ እንድሆን ማን ሾመኝ?” ሲል ጠየቀው።—ሉቃስ 12:14

ከዚያም ለአድማጮቹ ሁሉ የሚከተለውን ምክር ሰጠ፦ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም፤ ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ተጠበቁ።” (ሉቃስ 12:15) አንድ ሰው ምንም ያህል ቁሳዊ ሀብት ቢያካብት ሁሉንም ትቶ መሞቱ አይቀርም። ኢየሱስ ይህን ሐቅ ለማጉላት ሲል በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ማትረፍ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ የማይረሳ ምሳሌ ተናገረ፦

“አንድ ሀብታም ሰው መሬቱ ብዙ ምርት አስገኘለት። በመሆኑም ‘ምርቴን የማከማችበት ቦታ ስለሌለኝ ምን ባደርግ ይሻላል?’ ብሎ በልቡ ማሰብ ጀመረ። ከዚያም እንዲህ አለ፦ ‘እንዲህ አደርጋለሁ፦ ያሉኝን ጎተራዎች አፈርስና ትላልቅ ጎተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም እህሌንና ንብረቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም “ነፍሴ ሆይ፣ ለብዙ ዘመን የሚበቃ የተከማቸ ሀብት አለሽ፤ እንግዲህ ዘና በይ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’ አምላክ ግን ‘አንተ ማስተዋል የጎደለህ፣ በዚህች ሌሊት ሕይወትህን ይፈልጓታል። ታዲያ ያከማቸኸው ነገር ለማን ይሆናል?’ አለው። ለራሱ ሀብት የሚያከማች በአምላክ ዘንድ ግን ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”—ሉቃስ 12:16-21

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ሆኑ የሚያዳምጡት ሌሎች ሰዎች ሀብትን በማሳደድ ወይም በማከማቸት ወጥመድ ሊያዙ ይችላሉ። አሊያም ደግሞ የኑሮ ጭንቀት፣ ሙሉ ትኩረታቸውን በይሖዋ አገልግሎት ላይ እንዳያደርጉ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በተራራ ስብከቱ ላይ የሰጠውን ግሩም ምክር ደገመው፦

“ስለ ሕይወታችሁ ምን እንበላለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ። . . . ቁራዎችን ተመልከቱ፦ አይዘሩም፣ አያጭዱም እንዲሁም የእህል ማከማቻ ወይም ጎተራ የላቸውም፤ ሆኖም አምላክ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከወፎች እጅግ የላቀ ዋጋ የላችሁም? . . . እስቲ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፦ አይለፉም ወይም አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ያን ያህል ክብር የነበረው ሰለሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም። . . . ስለዚህ ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት ነገር ከልክ በላይ አታስቡ፤ እንዲሁም አትጨነቁ፤ . . . አባታችሁ እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። . . . ዘወትር መንግሥቱን ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ይሰጧችኋል።”—ሉቃስ 12:22-31፤ ማቴዎስ 6:25-33

የአምላክን መንግሥት እንዲፈልጉ የታዘዙት እነማን ናቸው? ይህን የሚያደርጉት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ታማኝ ሰዎች እንደሆኑ ኢየሱስ ገልጿል፤ እነዚህን ሰዎችም “ትንሽ መንጋ” ብሏቸዋል። ቁጥራቸው 144,000 ብቻ እንደሚሆን ከጊዜ በኋላ ታወቀ። እነዚህ ሰዎች ምን ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል? ኢየሱስ “አባታችሁ መንግሥት ሊሰጣችሁ ወስኗል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። እነዚህ ሰዎች በምድር ሀብት በማከማቸት ላይ ትኩረት አያደርጉም፤ በምድር የሚገኝን ሀብት ሌቦች ሊሰርቁት ይችላሉ። ልባቸው ያረፈው ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ሲገዙ በሚያገኙት “የማያልቅ ውድ ሀብት” ላይ ነው።—ሉቃስ 12:32-34

  • ኢየሱስ ውርስን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ምን መልስ ሰጠ?

  • ኢየሱስ የተጠቀመበት ምሳሌ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

  • ኢየሱስ ከእሱ ጋር በመንግሥቱ የሚሆኑትን አስመልክቶ ምን ተናገረ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ