የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 8/15 ገጽ 12-17
  • ሸክማቸው ለከበዳቸው ሰዎች የቀረበ ፍቅራዊ ግብዣ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሸክማቸው ለከበዳቸው ሰዎች የቀረበ ፍቅራዊ ግብዣ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ሸክማቸው የከበዳቸውና የደከማቸው’ ሰዎች
  • የችግሩ ዋነኛ መንስኤ
  • ኢየሱስ በአሁኑ ወቅት ያቀረበው ግብዣ
  • ዕረፍትና የሰውነት መታደስ
  • ማቴዎስ 11:28-30—“ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ”
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
  • “ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • ከውጥረት እፎይታ ለማግኘት የሚረዳ ተግባራዊ መፍትሔ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 8/15 ገጽ 12-17

ሸክማቸው ለከበዳቸው ሰዎች የቀረበ ፍቅራዊ ግብዣ

“እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።”—ማቴዎስ 11:28 አዓት

1. ኢየሱስ ሦስተኛ የስብከት ጉዞውን ባደረገበት ወቅት በገሊላ ውስጥ የተመለከተው ምን ነበር?

ኢየሱስ በ32 እዘአ መጀመሪያ ላይ በገሊላ አውራጃ ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የስብከት ሥራውን እያከናወነ ነበር። “በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፣ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ” በየከተማውና በየመንደሩ ዞረ። ይህን በሚያደርግበት ወቅት ብዙ ሕዝብ አየና “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።”—ማቴዎስ 9:35, 36

2. ኢየሱስ ሕዝቡን ይረዳ የነበረው እንዴት ነው?

2 ሆኖም ኢየሱስ ለእነዚህ ሰዎች ማዘን ብቻ ሳይሆን ከዚያ የበለጠ ነገር አድርጎላቸዋል። ደቀ መዛሙርቱን ‘የመከሩ ጌታ’ ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ እንዲጸልዩ ካዘዛቸው በኋላ ሕዝቡን እንዲረዱ ልኳቸዋል። (ማቴዎስ 9:38፤ 10:1) ከዚያም ሕዝቡ እውነተኛ እፎይታና መጽናናት የሚያገኝበትን መንገድ በተመለከተ ራሱ በቂ ማረጋገጫ ሰጣቸው። እጅግ አስደሳች የሆነውን የሚከተለውን ግብዣ አቀረበላቸው፦ “እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔም የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።”—ማቴዎስ 11:28, 29 አዓት

3. የኢየሱስ ግብዣ በአሁኑ ወቅትም ቢሆን አስደሳች የሆነው ለምንድን ነው?

3 ዛሬም አያሌ ሰዎች ሸክማቸው በጣም እንደከበዳቸው በሚሰማቸው ዘመን ውስጥ እንኖራለን። (ሮሜ 8:22፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) አንዳንዶች ለኑሮ የሚያደርጉት ሩጫ አብዛኛውን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ስለሚያሟጥጥባቸው ከቤተሰባቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ወይም ለሌላ ነገር የሚያውሉት ጊዜና ጉልበት የላቸውም። ብዙዎች ከባድ ሕመም፣ የሚደርሱባቸው መከራዎች፣ የመንፈስ ጭንቀትና ሌሎች አካላዊና ስሜታዊ ችግሮች ሸክም ሆነውባቸዋል። አንዳንዶች ሙሉ በሙሉ ተድላ በማሳደድ፣ በመብላትና በመጠጣት አልፎ ተርፎም ዕፅ በመውሰድ ከሚሰማቸው ጭንቀት እፎይታ ለማግኘት ይጥራሉ። ይህ በእርግጥ ተጨማሪ ችግሮችንና ጭንቀቶችን በመፍጠር የባሰ ወደ ተወሳሰበ ችግር ውስጥ እንደሚከታቸው የታወቀ ነው። (ሮሜ 8:6) የኢየሱስ ፍቅራዊ ግብዣ በዚያን ጊዜ አስደሳች የነበረውን ያህል በአሁኑ ወቅትም ቢሆን አስደሳች እንደሆነ አያጠራጥርም።

4. ከኢየሱስ ፍቅራዊ ግብዣ ለመጠቀም ከፈለግን የትኞቹን ጥያቄዎች መመርመር ይኖርብናል?

4 ታዲያ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ‘የተጨነቁና የተጣሉ’ ሆነው እንዲታዩና ኢየሱስን እንዲያዝንላቸው ያደረገው ነገር ምንድን ነው? ግዴታ ሆኖባቸው የተሸከሟቸው ሸክሞች የትኞቹ ነበሩ? ኢየሱስ ያቀረበላቸው ግብዣስ የረዳቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ ሸክማቸው ለከበዳቸው ሰዎች ካቀረበላቸው ፍቅራዊ ግብዣ እንድንጠቀም ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ለእኛም በጣም ጠቃሚ ናቸው።

‘ሸክማቸው የከበዳቸውና የደከማቸው’ ሰዎች

5. ሐዋርያው ማቴዎስ ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ያጋጠመውን ይህን ድርጊት መዘገቡ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ያጋጠመውን ይህን ድርጊት የዘገበው ማቴዎስ ብቻ መሆኑ ተገቢ ነው። ሌዊ በመባል ጭምር የሚታወቀው ማቴዎስ ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረ እንደ መሆኑ መጠን በተለይ ሕዝቡ የተሸከመውን አንድ ሸክም በሚገባ ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 9:9፤ ማርቆስ 2:14) ዴይሊ ላይፍ ኢን ዘ ታይም ኦቭ ጂሰስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “[አይሁዳውያን] በገንዘብም ሆነ በሸቀጥ ወይም ግልጋሎት በመስጠት መልክ የሚከፍሏቸው ቀረጦች ከመጠን በላይ ከባድ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሁኔታውን ይበልጥ የሚያከብደው ለመንግሥትና ለሃይማኖት የሚከፍሏቸው ሁለት ዓይነት ቀረጦች አንድ ላይ መደራረባቸው ነው፤ ሁለቱም የሚጠይቁት ደግሞ ከፍተኛ ቀረጥ ነበር።”

6. (ሀ) በኢየሱስ ዘመን ይሠራበት የነበረው የቀረጥ አሰባሰብ ሥርዓት እንዴት ያለ ነበር? (ለ) ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንደዚያ ያለ መጥፎ ስም ያተረፉት ለምን ነበር? (ሐ) ጳውሎስ እንደሱ ክርስቲያን የሆኑትን ስለ ምን ነገር ማሳሰብ እንዳለበት ተሰምቶት ነበር?

6 በተለይ ይህን ሁሉ ሸክም ያደረገው በወቅቱ የነበረው የቀረጥ አሰባሰብ ሥርዓት ነበር። የሮም ባለ ሥልጣናት በየግዛቶቹ ውስጥ ቀረጥ የመሰብሰብ መብትን ለከፍተኛ ቀረጥ ሰብሳቢዎች አከፋፍለው ነበር። እነሱ በተራቸው ደግሞ ቀረጥ የመሰብሰቡን ተግባር እንዲቆጣጠሩ የአካባቢውን ሰዎች ይቀጥራሉ። ከላይ ወደ ታች እየሰፋ በሚሄደው የሥልጣን መዋቅር ውስጥ ያለ ሁሉ ራሱ ክፍያውን ወይም ድርሻውን ከፍ ለማድረግ ሙሉ መብት እንዳለው ይሰማው ነበር። ለምሳሌ ያህል ሉቃስ “ዘኬዎስ የሚባል ሰው [ነበረ]፣ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፣ ባለ ጠጋም ነበረ” በማለት ዘግቧል። (ሉቃስ 19:2) “የቀራጮች አለቃ” የነበረው ዘኬዎስና ሌሎች ከበታቹ የነበሩ ቀረጥ ሰብሳቢዎች የበለጸጉት ሕዝቡን በመበዝበር ሳይሆን አይቀርም። ይህ ዓይነቱ ሥርዓት የወለደው የሥልጣን ብልግና እንዲሁም ምግባረ ብልሹነት ሕዝቡ ቀረጥ ሰብሳቢዎችን እንደ ኃጢአተኞችና ጋለሞቶች እንዲመለከታቸው አድርጓል፤ ምናልባትም በዚህ ዓይነት መልኩ መታየታቸው ተገቢ ሳይሆን አይቀርም። (ማቴዎስ 9:10፤ 21:31, 32፤ ማርቆስ 2:15፤ ሉቃስ 7:34) ሕዝቡ ሸክሙን ለመሸከም እንደማይችሉ ተሰምቷቸው ስለ ነበር በሮም አገዛዝ ቀንበር ላይ ከማመፅ ይልቅ “ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፣ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን . . . ስጡ” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደእሱው ክርስቲያን የሆኑትን ማሳሰብ እንዳለበት የተሰማው መሆኑ አያስደንቅም።—ሮሜ 13:7፤ ከሉቃስ 23:2 ጋር አወዳድር።

7. የሮማውያን የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች በሕዝቡ ላይ የነበረውን ሸክም ያከበዱት እንዴት ነው?

7 በተጨማሪም ጳውሎስ “መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” በማለት ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል። (ሮሜ 13:7) ሮማውያን በሚጠቀሙባቸው ጭካኔ የተሞላባቸውና ከባድ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎቻቸው የታወቁ ነበሩ። ብዙውን ጊዜ ሕዝቡን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ድብደባ፣ ግርፋት፣ ጽኑ እስራትና የሞት ቅጣት ይጠቀሙ ነበር። (ሉቃስ 23:32, 33፤ ሥራ 22:24, 25) የአይሁድ መሪዎችም እንኳ እነዚህን ቅጣቶች እንደ አስፈላጊነቱ የማስፈጸም ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:17፤ ሥራ 5:40) ይህ ዓይነቱ ሥርዓት በሥሩ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ የማያፈናፍን ከመሆኑም በላይ እጅግ የሚጨቁን እንደነበር አያጠራጥርም።

8. የሃይማኖት መሪዎች በሕዝቡ ላይ ሸክም ይጭኑ የነበረው እንዴት ነው?

8 ሆኖም ከሮም መንግሥት ቀረጦችና ሕጎች የሚከፋው በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በተራው ሕዝብ ላይ የጫኑት ሸክም ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ ሕዝቡ ‘ሸክማቸው እንደ ከበዳቸውና እንደ ደከማቸው’ ሲገልጽ በይበልጥ ያሳሰበው ይህ ሳይሆን አይቀርም። የሃይማኖት መሪዎች ለተጨቆኑት ሰዎች ተስፋና መጽናናትን ከመስጠት ይልቅ “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፣ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:4፤ ሉቃስ 11:46) ወንጌሎች እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች በተለይ ደግሞ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ትዕቢተኞች፣ አዘኔታ የሌላቸውና ግብዞች አድርገው እንደሚገልጿቸው ማንም መረዳት አያዳግተውም። ተራውን ሕዝብ እንዳልተማረና እንደ እርኩስ ነገር አድርገው በመመልከት ይንቁት ነበር፤ በመካከላቸው የነበሩትን የውጭ አገር ሰዎችም ይጸየፉ ነበር። እነሱ የነበራቸውን ዝንባሌ በተመለከተ እንዲህ የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል፦ “በዘመናችን ፈረስን ከአቅሙ በላይ የሚጭን ሰው በሕግ ይጠየቃል። ታዲያ ሃይማኖታዊ ሥልጠና በሌላቸው ተራ ሰዎች ላይ 613 ሕጎችን የሚጭንና ምንም እርዳታ ሳያደርግላቸው አምላክ የለሾች በማለት የሚያወግዛቸው ሰው ምን ሊደረግ ይገባል?” በሕዝቡ ላይ ተጭኖ የነበረው ትልቁ ሸክም ወግ እንደ ነበረ አያጠራጥርም።

የችግሩ ዋነኛ መንስኤ

9. በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሁኔታዎች በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ከነበሩት ሁኔታዎች ጋር የሚነጻጸሩት እንዴት ነው?

9 በወቅቱ በሕዝቡ ላይ ተጭኖ የነበረው ገንዘብ ነክ ሸክም ከባድ ከመሆኑ የተነሣ ድህነት በጣም ተስፋፍቶ ነበር። እስራኤላውያን የሙሴ ሕግ የሚጠይቅባቸውን መጠነኛ ቀረጦች መክፈል ነበረባቸው። በሰሎሞን ዘመን ደግሞ ሕዝቡ እንደ ቤተ መቅደስ ግንባታና ሌሎች ሕንፃዎች ያሉ በጣም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ብሔራዊ ፕሮጄክቶችን አካሂደው ነበር። (1 ነገሥት 7:1–8፤ 9:17–19) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝቡ “በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር። በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር” በማለት ይነግረናል። (1 ነገሥት 4:20, 25) ለዚህ ልዩነት መንስኤ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

10. እስራኤላውያን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የደረሰባቸው ችግር መንስኤ ምን ነበር?

10 ሕዝቡ እውነተኛውን አምልኮ አጥብቆ እስከያዘበት ጊዜ ድረስ የይሖዋን ሞገስ አግኝቷል፤ በተጨማሪም በብሔር ደረጃ ከፍተኛ ወጪዎች ቢኖሩባቸውም ዋስትና ያለው ሕይወትና ብልጽግና በማግኘት ተባርከዋል። ሆኖም ይሖዋ ‘እኔን ከመከተል ብትመለሱ፣ የሰጠኋችሁንም ትእዛዝ ባትጠብቁ’ ከባድ ችግሮች ይገጥሟችኋል በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር። እንዲያውም ‘እስራኤላውያን በአሕዛብ መካከል ምሳሌና ተረት’ እንደሚሆኑ ተነግሯቸው ነበር። (1 ነገሥት 9:6, 7) የተፈጸመውም ልክ እንደዚሁ ነው። እስራኤል በውጭ አገር ሰዎች አገዛዝ ቀንበር ሥር ወደቀች፤ በአንድ ወቅት ገናና የነበረችው መንግሥት ቅኝ ግዛት ሆነች። መንፈሳዊ ግዴታዎቻቸውን ሳይፈጽሙ መቅረታቸው ያስከተለባቸው ጉዳት ምንኛ አስከፊ ነበር!

11. ኢየሱስ ሕዝቡ “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም” እንደነበር የተሰማው ለምንድን ነው?

11 ይህ ሁሉ ኢየሱስ ያያቸው ሰዎች ‘ተጨንቀውና ተጥለው’ እንደነበር ለምን እንደተሰማው እንድንረዳ ያስችለናል። እነዚህ እስራኤላውያን በአጠቃላይ ሲታይ ከአምላክ ሕጎች ጋር ተስማምተው ለመኖርና አምላካቸውን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ የሚጥሩ የይሖዋ ሕዝቦች ነበሩ። ሆኖም በፖለቲካና በንግድ ባለ ሥልጣናት ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው በነበሩ ከሃዲ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተበዝብዘዋል እንዲሁም ተንቀዋል። ማንም የሚያስብላቸውና የሚጠብቃቸው ስላልነበረ “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች” ሆነዋል። ያሉባቸውን ችግሮች ለመቋቋም እንዲችሉ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ ያቀረበላቸው ፍቅራዊና ደግነት የተሞላበት ግብዣ ምንኛ ወቅታዊ ነበር!

ኢየሱስ በአሁኑ ወቅት ያቀረበው ግብዣ

12. በአሁኑ ወቅት የአምላክ አገልጋዮችና ሌሎች ቅን አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የሚደርሱባቸው ተጽዕኖዎች የትኞቹ ናቸው?

12 ዛሬ ያሉት ነገሮች ከዚህ ሁኔታ ጋር በብዙ መንገዶች ይመሳሰላሉ። በንግድ ሥራዎች ሐቀኛ ለመሆን የሚጥሩ ቅን አስተሳሳብ ያላቸው ሰዎች ይህ የረከሰ የነገሮች ሥርዓት የሚያሳድራቸው ተጽዕኖዎችና የሚጠይቃቸው ነገሮች መሸከም ከሚችሉት በላይ ሆኖባቸዋል። ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሰዎችም እንኳ ከዚህ ሁኔታ ነጻ አይደሉም። አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቢፈልጉም እንኳ ይህን ማድረግ ይበልጥ እየከበዳቸው እንደመጣ ያሉት ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ሸክም እንደ በዛባቸው፣ እንደ ደከማቸውና እንደዛሉ ይሰማቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገው ቢተዉና ወደ አንድ ቦታ ሄደው ከሰው ፊት ቢሰወሩ ከጭንቀታቸው እፎይታ የሚያገኙ ይመስላቸዋል። እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃልን? አንድ የምትቀርበው ሰው በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ታውቃለህን? በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ኢየሱስ ያቀረበው እጅግ አስደሳች የሆነ ግብዣ ለእኛ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

13. ኢየሱስ መጽናናትና ዕረፍት እንድናገኝ ሊረዳን እንደሚችል እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ ፍቅራዊ ግብዣውን ከማቅረቡ በፊት “ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፣ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም” በማለት ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 11:27) የኢየሱስን ግብዣ ተቀብለን ደቀ መዛሙርቱ ከሆንን በኢየሱስና በአባቱ መካከል ባለው በዚህ የተቀራረበ ዝምድና ምክንያት “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ የግል ዝምድና መመሥረት እንደምንችል እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 1:3፤ ከዮሐንስ 14:6 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በተጨማሪ ‘ሁሉ ነገር ስለ ተሰጠው’ ሸክሞቻችንን ለማቃለል የሚያስችል ኃይልና ሥልጣን ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ሸክሞቹ ምን ምን ናቸው? ብልሹ የሆኑት ፖለቲካዊ፣ የንግድና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችም ሆኑ የወረስነው ኃጢአትና አለፍጽምና የሚያመጧቸው ሸክሞች ናቸው። ይህ ከጅምሩ እንኳ ምንኛ የሚያበረታታና የሚያጽናና ሐሳብ ነው!

14. ኢየሱስ እረፍት ሊያመጣልን የሚችለው ከየትኛው ሸክም ነው?

14 ከዚያም ኢየሱስ “እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:28 አዓት) ኢየሱስ ይህን ሲል ከባድ ሥራ መሥራትን ማውገዙ እንዳልነበረ የተረጋገጠ ነው፤ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ የተሰጣቸውን ሥራ ጠንክረው እንዲሠሩ ደቀ መዛሙርቱን ያሳስባቸው ነበር። (ሉቃስ 13:24) ይሁን እንጂ “የደከማችሁ” (“ከባድ ሥራ መሥራት” ኪንግደም ኢንተርሊኒየር) የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ ምንም እርባና ሳይኖረው ለረጅም ጊዜ የሚሠራ አድካሚ የሆነ የጉልበት ሥራን ያመለክታል። በተጨማሪም “ሸክማችሁ የከበደ” የሚለው ሐረግ ከአቅም በላይ መሸከም የሚል ትርጉም አለው። አንድን የተቀበረ ሀብት ለማግኘት የሚቆፍር ሰውን በካምፕ ውስጥ ለቅጣት ጉድጓድ ከሚቆፍር ሰው ጋር በማወዳደር ልዩነቱን ለማየት ይቻላል። ሁለቱም ተመሳሳይ የሆነ አድካሚ ሥራ እየሠሩ ናቸው። አንደኛው ሥራውን የሚያከናውነው በጉጉት ሲሆን ሌላው ደግሞ ማለቂያ የሌለው የሚያሰለች ነገር ሆኖበታል። ለዚህ ልዩነት ምክንያት የሆነው ሥራው ዓላማ ያለው ወይም ዓላማ የሌለው መሆኑ ነው።

15. (ሀ) በትከሻችን ላይ ከባድ ሸክም እንደተሸከምን ከተሰማን ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል? (ለ) የሸክሞቻችንን ምንጭ በተመለከተ ምን ሊባል ይቻላል?

15 ‘ሸክምህ እንደ ከበደህና እንደ ደከመህ’ ማለትም ጊዜህንና ጉልበትህን የሚያሟጥጡ ከመጠን በላይ የሆኑ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ይሰማሃልን? የተሸከምሃቸው ሸክሞች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ ይሰማሃልን? እንደዚህ ከሆነ ‘የምደክመው ለምንድን ነው? የተሸከምሁት ምን ዓይነት ሸክም ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ ከ80 ዓመት በፊት ይህን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “በሕይወት ውስጥ ያሉትን ሸክሞች ብንመረምራቸው በሁለት ክፍሎች ይመደባሉ፤ እነርሱም በገዛ ራሳችን የምንፈጥራቸው እና የትም የማንሸሻቸው ሸክሞች ብለን ልንጠራቸው እንችላለን። ይህም ሲባል በገዛ ራሳችን የምንፈጥራቸው ሸክሞች እና ወደድንም ጠላንም የግድ የምንሸከማቸው ሸክሞች ይኖራሉ ማለት ነው።” ከዚያም “ብዙዎቻችን ራሳችንን በአንክሮ ከመረመርን በኋላ ከሸክሞቻችን ውስጥ አብዛኞቹን ራሳችን እንደፈጠርናቸው ስንገነዘብ ይገርመን ይሆናል” በማለት አክለው ተናግረዋል።

16. ሳናስተውል በራሳችን ላይ ልንጭናቸው የምንችላቸው ሸክሞች የትኞቹ ናቸው?

16 ራሳችን ልንፈጥራቸው ከምንችላቸው ሸክሞች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? በአሁኑ ወቅት የምንኖረው ቁሳዊ አስተሳሰብ በተጠናወተው፣ ተድላ ወዳድና ምግባረ ብልሹ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች እንኳ የዓለማውያንን አለባበስና አኗኗር እንዲከተሉ የማያቋርጥ ግፊት ይደርስባቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘የሥጋ ምኞትን፣ የዓይን አምሮትንና በገንዘብ መመካትን’ በተመለከተ ጽፏል። (1 ዮሐንስ 2:16) እነዚህ ነገሮች በቀላሉ ሊያጠቁን የሚችሉ ኃይለኛ ተጽዕኖዎች ናቸው። አንዳንዶች ዓለማዊ ተድላዎችን አግኝተው ለመደሰት ወይም ከፍ ያለ የኑሮ ደረጃ ላይ ለመድረስ ሲሉ በዕዳ ውስጥ ለመዘፈቅ ፈቃደኛ እንደሆኑ ተስተውሏል። ከዚያም ዕዳቸውን ለመክፈል የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ብዙ ሰዓት መሥራት ወይም በርካታ ሥራ መያዝ እንዳለባቸው ይገነዘባሉ።

17. አንድ ሰው ሸክሙን መሸከምን ይበልጥ ከባድ የሚያደርግበት ምንድን ነው? ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

17 አንድ ሰው ሌሎች ያሏቸውን አንዳንድ ነገሮች ማግኘት ወይም ሌሎች የሚያደርጉትን አንዳንድ ነገር ማድረግ ስሕተት አይደለም ብሎ ሊያስብ ቢችልም በራሱ ላይ አላስፈላጊ የሆነ ሸክም ጨምሮ እንደሆነና እንዳልሆነ ራሱን መመርመሩ በጣም ጥሩ ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:23) አንድ ግለሰብ መሸከም የሚችለው የአቅሙን ያህል ብቻ ስለሆነ ሌላ ሸክም ሲሸከም አንድ ነገር መተው አለበት። ብዙውን ጊዜ በመጀመሪያ የሚተዉት ለመንፈሳዊ ደኅንነታችን በጣም አስፈላጊ የሆኑት የግል ጥናት፣ በስብሰባ ላይ መገኘትና የመስክ አገልግሎት ናቸው። ይህም መንፈሳዊ ጥንካሬ ያሳጣል፤ መንፈሳዊ ጥንካሬ ማጣት ደግሞ ሸክሙን መሸከምን ይበልጥ ከባድ እንዲሆን ያደርጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋል” ሲል ያስጠነቀቀው እንዲህ ዓይነቱን አደጋ ነው። (ሉቃስ 21:34, 35፤ ዕብራውያን 12:1) አንድ ሰው ሸክሙ ከከበደውና ከደከመ ከፊቱ የተደቀነበትን ወጥመድ ለይቶ ለማወቅና ከወጥመዱ ለመዳን ይቸገራል።

ዕረፍትና የሰውነት መታደስ

18. ኢየሱስ ወደ እርሱ ለሚመጡት ያቀረበላቸው ግብዣ ምንድን ነው?

18 ስለዚህ ኢየሱስ በፍቅር “ወደ እኔ ኑ፣ . . . እኔም አሳርፋችኋለሁ” በማለት መፍትሔውን ገልጿል። (ማቴዎስ 11:28) እዚህ ላይ የተጠቀሰው “አሳርፋችኋለሁ” የሚለው ቃልና በቁጥር 29 ላይ “ዕረፍት ታገኛላችሁ” የሚሉት ቃላት የሴፕቱጀንት ትርጉም “ሰንበት”ን ወይም “ሰንበት መጠበቅ”ን ለማመልከት የገባውን የዕብራይስጥ ቃል ለመተርጎም ከተጠቀመበት ተመሳሳይ የግሪክኛ ቃል የመጡ ናቸው። (ዘጸአት 16:23) ስለዚህ ኢየሱስ ወደ እርሱ የሚመጡ ምንም ሥራ አይኖራቸውም የሚል ተስፋ አልሰጠም፤ ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚስማማ ሥራ ለመሥራት የተዘጋጁ እንዲሆኑ ዕረፍት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።

19. አንድ ሰው ‘ወደ ኢየሱስ የሚመጣው’ እንዴት ነው?

19 ታዲያ አንድ ሰው ‘ወደ ኢየሱስ የሚመጣው’ እንዴት ነው? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ የመከራውንም እንጨት ተሸክሞ ያለማቋረጥ ይከተለኝ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 16:24 አዓት) ስለዚህ ወደ ኢየሱስ መምጣት ለአምላክና ለክርስቶስ ፈቃድ ራስን ማስገዛትንና የተወሰነ የኃላፊነት ሸክምን ያለማቋረጥ መሸከምን ያመለከታል። ይህ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር የሚጠይቅብን ነውን? ለዚህ የሚከፈለው ዋጋ ከመጠን በላይ ነውን? እስቲ ኢየሱስ ለደከማቸው ሰዎች ፍቅራዊ ግብዣ ካቀረበ በኋላ የተናገረውን እንመልከት።

ታስታውሳለህን?

◻ በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ሸከማቸው የከበዳቸው በምን በምን መንገዶች ነበር?

◻ የሕዝቡ ችግር ዋነኛ መንስኤ ምን ነበር?

◻ ከአቅማችን በላይ የሆነ ሸክም እንደተሸከምን ከተሰማን ራሳችንን መመርመር ያለብን እንዴት ነው?

◻ ሳናስተውል በራሳችን ላይ ልንጭናቸው የምንችላቸው ሸክሞች የትኞቹ ናቸው?

◻ ኢየሱስ ቃል የገባልንን ዕረፍት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በራሳችን ላይ ልንጭናቸው የምንችላቸው አንዳንድ ሸክሞች የትኞቹ ናቸው?

[ምንጭ]

Courtesy of Bahamas Ministry of Tourism

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ