-
ስማችሁ “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ ተጽፏል?መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022 | መስከረም
-
-
የሕይወት ትንሣኤ እና የፍርድ ትንሣኤ
13-14. (ሀ) ከዚህ ቀደም፣ በዮሐንስ 5:29 ላይ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ የምንረዳው እንዴት ነበር? (ለ) እነዚህን ቃላት በተመለከተ ምን ነገር ልብ ማለት ይኖርብናል?
13 ኢየሱስም በምድር ላይ ትንሣኤ ስለሚያገኙ ሰዎች ተናግሯል። ለምሳሌ እንዲህ ብሏል፦ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።” (ዮሐ. 5:28, 29) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
14 ከዚህ ቀደም፣ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ከሞት ከተነሱ በኋላ የሚያደርጉትን ነገር እንደሚያመለክት እናስብ ነበር፤ ይህም ሲባል አንዳንዶች ከሞት ተነስተው መልካም እንደሚሠሩ፣ ሌሎች ደግሞ ከሞት ተነስተው ክፉ እንደሚሠሩ እናስብ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ከመታሰቢያ መቃብር የወጡ ሰዎች መልካም እንደሚሠሩ ወይም ክፉ እንደሚሠሩ እንዳልተናገረ ልብ በሉ። ከዚህ ይልቅ የተጠቀመበት ግስ አላፊ ጊዜን የሚያመለክት ነው። “መልካም የሠሩ” እና “ክፉ የሠሩ” በማለት ተናግሯል። ይህም፣ መልካም ወይም ክፉ የሠሩት ከመሞታቸው በፊት እንደሆነ ይጠቁማል። ይህ ሐሳብ ምክንያታዊ አይደለም? ደግሞም ማንም ሰው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ክፉ እንዲሠራ አይፈቀድለትም። ስለዚህ ትንሣኤ ያገኙት ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ክፉ የሠሩት ከመሞታቸው በፊት መሆን አለበት። ታዲያ ኢየሱስ ስለ “ሕይወት ትንሣኤ” እና ስለ “ፍርድ ትንሣኤ” የተናገረውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል?
15. ‘የሕይወት ትንሣኤ’ የሚያገኙት እነማን ናቸው? ለምንስ?
15 ከመሞታቸው በፊት መልካም የሠሩ ጻድቃን ‘የሕይወት ትንሣኤ’ ያገኛሉ፤ ምክንያቱም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሯል። ይህም ሲባል በዮሐንስ 5:29 መሠረት ትንሣኤ የሚያገኙት “መልካም የሠሩ” ሰዎችና በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ የተጠቀሱት ትንሣኤ የሚያገኙ “ጻድቃን” አንድ ዓይነት ናቸው። ይህ ማብራሪያ በሮም 6:7 ላይ ካለው ሐሳብ ጋር ይስማማል፤ ጥቅሱ “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል” ይላል። እነዚህ ጻድቃን ሲሞቱ ኃጢአታቸው ተሰርዞላቸዋል፤ ያስመዘገቡት የታማኝነት ታሪክ ግን አልተሰረዘም። (ዕብ. 6:10) እርግጥ ትንሣኤ ያገኙት ጻድቃን ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ እንደተጻፈ እንዲቀጥል ከፈለጉ ታማኝነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
16. ‘የፍርድ ትንሣኤ’ ምን ያመለክታል?
16 ከመሞታቸው በፊት ክፉ ስለሠሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ሲሞቱ ኃጢአታቸው የተሰረዘላቸው ቢሆንም የታማኝነት ታሪክ አላስመዘገቡም። ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ አልተጻፈም። በመሆኑም ትንሣኤ የሚያገኙት “ክፉ የሠሩ” ሰዎች በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ ከተጠቀሱት ትንሣኤ የሚያገኙ “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ጋር አንድ ዓይነት ናቸው። እነዚህ ሰዎች የሚያገኙት ትንሣኤ ‘የፍርድ ትንሣኤ’ ይሆናል።c ይህም ሲባል ኢየሱስ እነዚህን ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ይገመግማቸዋል ማለት ነው። (ሉቃስ 22:30) ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ መጻፍ የሚገባው መሆኑን ለመወሰን ጊዜ ይወስዳል። እነዚህ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የሚጻፈው የቀድሞውን ክፉ አኗኗራቸውን ከተዉና ራሳቸውን ለይሖዋ ከወሰኑ ብቻ ነው።
-
-
ስማችሁ “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ ተጽፏል?መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022 | መስከረም
-
-
c ከዚህ ቀደም፣ እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው “ፍርድ” የሚለው ቃል እነዚህ ሰዎች እንደሚፈረድባቸው ወይም አሉታዊ ፍርድ እንደሚሰጣቸው እንደሚያመለክት ገልጸን ነበር። እርግጥ “ፍርድ” የሚለው ቃል ይህን ትርጉም ሊያስተላልፍ ይችላል። ሆኖም በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ “ፍርድ” የሚለውን ቃል ጠቅለል ባለ መልኩ ማለትም የግምገማ ወይም የፈተና ሂደትን ለማመልከት የተጠቀመበት ይመስላል፤ አንድ የግሪክኛ መዝገበ ቃላት፣ ይህ ቃል ‘የአንድን ሰው ምግባር መፈተንን’ ሊያመለክት እንደሚችል ይገልጻል።
-