አምላክ
ማንኛውም የሚመለክ ነገር፣ አምላኪው ከራሱ አስበልጦና ቅዱስ አድርጎ እስከተመለከተው ድረስ አምላክ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። አንድ ሰው የገዛ ሆዱ እንኳ አምላክ ሊሆንበት ይችላል። (ሮም 16:18፤ ፊልጵ 3:18, 19) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ብዙ አማልክት (መዝ 86:8፤ 1ቆሮ 8:5, 6) የሚናገር ቢሆንም የብሔራት አማልክት ምንም እንደማይጠቅሙ ይናገራል።—መዝ 96:5፤ “GODS AND GODDESSES” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
የዕብራይስጡ ቃላት። “አምላክ” ተብለው ከተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቃላት መካከል አንዱ ኤል ሲሆን ትርጉሙም “ኃያል፣ ጠንካራ” ማለት ሳይሆን አይቀርም። (ዘፍ 14:18) ይህ ቃል ይሖዋን፣ ሌሎች አማልክትንና ሰዎችን ለማመልከት ተሠርቶበታል። በተጨማሪም ይህን ቃል ከሌሎች ቃላት ጋር በማቀናጀት የተሠራባቸው ብዙ ስሞች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል ኤልሳዕ (“አምላክ አዳኝ ነው” ማለት ነው) እና ሚካኤል (“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?”) የሚሉት ይገኙበታል። በአንዳንድ ቦታዎች ኤል ጠቃሽ አመልካች ተጨምሮለት (ሃ ኤል፣ ቃል በቃል “[እውነተኛው] አምላክ” ማለት ነው) ይሖዋን ከሌሎች አማልክት ለመለየት ይሠራበታል።—ዘፍ 46:3፤ 2ሳሙ 22:31፤ በባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) ገጽ 1567 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ መረጃ ተመልከት።
ኢየሱስ ክርስቶስ በኢሳይያስ 9:6 ላይ በትንቢት ኤል ጊብ ቦህር ማለትም “ኃያል አምላክ” ተብሎ ቢጠራም በዘፍጥረት 17:1 ላይ ይሖዋን ለማመልከት በተሠራበት ቃል ማለትም ኤል ሻዳይ [ሁሉን ቻይ አምላክ] በሚለው ስም ግን አልተጠራም።
ብዙ ቁጥርን የሚያመለክተው ኤሊም የሚለው ቃል እንደ ዘፀአት 15:11 (“አማልክት”) ባሉ ጥቅሶች ላይ ሌሎች አማልክትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። በተጨማሪም በመዝሙር 89:6 ላይ ግርማዊነትንና ክብርን ለማመልከት የገባው ቃል ብዙ ቁጥርን የሚያመለክት ነው፤ ጥቅሱ “ከአምላክ ልጆች [ቢ ቨነህ ኤሊም] መካከል እንደ ይሖዋ ያለ ማን ነው?” ይላል። እዚህ ላይና ሌሎች ብዙ ቦታዎች ላይ በብዙ ቁጥር የገባው ኤሊም የሚለው ቃል አንድን ግለሰብ እንደሚያመለክት ሌሎች ትርጉሞችም ያረጋግጣሉ፤ ለምሳሌ የግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ቃሉን ቴኦስ በተባለው ነጠላ ቁጥር የተረጎመው ሲሆን የላቲኑ ቩልጌት ደግሞ ዴዮስ ብሎ አስቀምጦታል።
ኤሎሂም (አማልክት) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ብርቱ ሁን” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው ቃል የተገኘ ይመስላል። ኤሎሂም በነጠላ ቁጥር ሲጻፍ ኤሎሃህ (አምላክ) ነው። ብዙ ቁጥርን የሚያመለክተው ይህ ቃል አንዳንድ ጊዜ ብዙ አማልክትን ለማመልከት የገባ ቢሆንም (ዘፍ 31:30, 32፤ 35:2) ብዙውን ጊዜ የሚሠራበት ግርማዊነትን፣ ክብርን ወይም ታላቅነትን ለማመልከት ነው። ኤሎሂም የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋን፣ መላእክትን፣ ጣዖታትን (አንድ ወይም ከአንድ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ) እንዲሁም ሰዎችን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ኤሎሂም ይሖዋን በሚያመለክትበት ጊዜ ግርማዊነትን፣ ክብርን ወይም ታላቅነትን በብዙ ቁጥር ለማመልከት ይሠራበታል። (ዘፍ 1:1) አሮን ኤምበር ይህን በማስመልከት የሚከተለውን ጽፈዋል፦ “ብሉይ ኪዳን በተጻፈበት ቋንቋ [ኤሎሂም] ብዙ ቁጥር አመልካች እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ይህን ቃል የሚከተለው ግስ ሁልጊዜ ነጠላ ቁጥር ያለው ሲሆን ለዚህ ስም የሚያገለግለውም ገላጭ ቃል ነጠላ ቁጥር መሆኑ ይህን ያሳያል (ለምሳሌ፣ የእስራኤልን አምላክ ለማመልከት ሲሠራበት)። . . . [ኤሎሂም] በብዙ ቁጥር የተጠቀሰው ታላቅነትን ወይም ግርማዊነትን ለማመልከት ሲሆን ‘ታላቅ አምላክ’ እንደማለት ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።”—ዚ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሴሜቲክ ላንጉዌጅስ ኤንድ ሊትሬቸርስ፣ 1905 ጥራዝ 21 ገጽ 208
ኤሎሂም የሚለው የማዕረግ ስም ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ያለውን ኃይል ያመለክታል። ይህ ቃል ስለ ፍጥረት በሚገልጸው ዘገባ ውስጥ 35 ጊዜ ብቻውን ተጠቅሷል፤ በነዚህ ቦታዎች ላይ እሱ ያደረጋቸውን ወይም የተናገራቸውን ነገሮች የሚገልጹት ግሶች በሙሉ የገቡት በነጠላ ቁጥር ነው። (ዘፍ 1:1–2:4) አምላክ ያለው ኃይል ስፍር ቁጥር የለውም።
መላእክትም በመዝሙር 8:5 ላይ ኤሎሂም ተብለዋል፤ ጳውሎስ በዕብራውያን 2:6-8 ይህን ጥቅስ መጥቀሱም ይህን ያረጋግጣል። በዘፍጥረት 6:2, 4፣ ኢዮብ 1:6 እና 2:1 ላይ እንደተጠቀሰው መላእክት ቤነህ ሃ ኤሎሂም፣ “የአምላክ ልጆች” (KJ)፣ “የእውነተኛው አምላክ ልጆች” (NW) ተብለው ተጠርተዋል። በከህለር እና ቦምጋርትነር (1958) የተዘጋጀው ሌክሲከን ኢን ቨተሪስ ቴስታሜንቲ ሊብሮስ ገጽ 134 ላይ “(በተናጠል) መለኮታዊ አካላት፣ አማልክት” ይላል። ገጽ 51 ላይ ደግሞ “አማልክት (በተናጠል)” ይልና ዘፍጥረት 6:2፣ ኢዮብ 1:6፣ 2:1 እና 38:7ን ይጠቅሳል። በመሆኑም ኤሎሂም በመዝሙር 8:5 ላይ “መላእክት” ወይም ‘እንደ አምላክ ያሉ’ ተብሎ ተተርጉሟል።
ኤሎሂም የሚለው ቃል የጣዖት አማልክትንም ለማመልከት ተሠርቶበታል። አንዳንድ ጊዜ ብዙ ቁጥርን የሚያመለክተው ይህ ቃል “አማልክት” የሚል ትርጉም ይኖረዋል። (ዘፀ 12:12፤ 20:23) በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ቃሉ የሚያመለክተው አንድን አምላክ (አንዲትን እንስት አምላክ) ብቻ ቢሆንም ክብርን ለማመልከት በብዙ ቁጥር ይሠራበታል። ይሁን እንጂ እነዚህ አማልክት ሥላሴዎች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው።—1ሳሙ 5:7ለ (ዳጎን)፣ 1ነገ 11:5 (“እንስት አምላክ” አስታሮት)፣ ዳን 1:2ለ (ማርዱክ)
በመዝሙር 82:1, 6 ላይ ኤሎሂም ሰዎችን ማለትም በእስራኤል የነበሩ ዳኞችን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ኢየሱስ ይህን መዝሙር ዮሐንስ 10:34, 35 ላይ ጠቅሶታል። የይሖዋ ቃል አቀባዮችና ወኪሎች በመሆናቸው አማልክት ተብለዋል። ሙሴም ለአሮንና ለፈርዖን እንደ “አምላክ” እንደሚሆን ተነግሮታል።—ዘፀ 4:16 ግርጌ፤ 7:1
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤሎሂም በአብዛኛው ሃ የሚለው ጠቃሽ አመልካች ከፊቱ ይገባለታል። (ዘፍ 5:22) ሃ ኤሎሂም የሚለውን ቃል አጠቃቀም አስመልክተው ዞረል እንዲህ ብለዋል፦ “በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተለይ አንዱን እውነተኛ አምላክ ማለትም ጃህቨን ለማመልከት የተሠራበት ቃል ይህ ነው፤ . . . ‘ጃህቨ [አንዱ እውነተኛ] አምላክ ነው’ ዘዳ 4:35, 39፤ ኢያሱ 22:34፤ 2ሳሙ 7:28፤ 1ነገ 8:60 ወዘተ።”—ሌክሲከን ሂብራይኩም ቨተሪስ ቴስታሜንቲ፣ ሮም፣ 1984 ገጽ 54፤ ቅንፉን ያስገቡት ጸሐፊው ናቸው።
የግሪክኛው ቃል። በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ውስጥ ኤል እና ኤሎሂም የሚሉት ቃላት በአብዛኛው የተተረጎሙት ቴኦስ በሚለው የግሪክኛ ቃል ነው፤ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም “አምላክን” ለማመልከት የተሠራበት ቃል ቴኦስ ነው።
እውነተኛው አምላክ ይሖዋ። እውነተኛው አምላክ ስም የሌለው አምላክ አይደለም። ስሙ ይሖዋ ነው። (ዘዳ 6:4፤ መዝ 83:18) አምላክ የተባለው ፈጣሪ ስለሆነ ነው። (ዘፍ 1:1፤ ራእይ 4:11) እውነተኛው አምላክ በእውን ያለና (ዮሐ 7:28) አካል ያለው (ሥራ 3:19፤ ዕብ 9:24) ነው፤ ሕይወት ያለው ሕግ ሰጪ ሳይኖር ነገሮች በአጋጣሚ እንዲከሰቱ የሚያደርግ ሕያው ያልሆነ ኃይል አይደለም። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና የ1956 እትም (ጥራዝ 12 ገጽ 743) “ጎድ” በሚለው ርዕስ ሥር የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሯል፦ “ክርስቲያኖች፣ የመሐመድ ተከታዮችና አይሁዳውያን ከሁሉ በላይ የሆነና ሁሉን ነገር የፈጠረ እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት አካል፤ በጥቅሉ ሲታይ ዛሬ ያለው የሠለጠነ ዓለም መንፈሳዊ አካል የሆነ፣ በራሱ ሕልውና ያለው፣ ዘላለማዊ፣ የማንም ጥገኛ ያልሆነ፣ ሁሉን ቻይ እንዲሁም በተለያየ ቅርጽና መልክ ከሠራቸው፣ ከሚጠብቃቸውና ከሚቆጣጠራቸው ፍጥረታት ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት አካል። ከሰው በላይ የሆነ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪና ገዢ አለ የሚለው ሐሳብ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ምንጊዜም የነበረ ይመስላል።”
“ሕያው አምላክ” መኖሩን የሚያሳዩ ማስረጃዎች። በግዙፍና በረቂቅ ፍጥረታት ውስጥ የሚታየው ሥርዓት፣ ኃይልና ውስብስብነት እንዲሁም አምላክ በታሪክ ዘመናት በሙሉ ለሕዝቡ ሲል ያደረጋቸው ነገሮች የአምላክን መኖር ያረጋግጣሉ። ሳይንቲስቶች “የመለኮታዊ ፍጥረት መጽሐፍ” የሚባለውን የፍጥረት ሥራ በመመልከት ብዙ ነገር ሊማሩ ይችላሉ። አንድ ሰው ከአንድ መጽሐፍ ትምህርት ሊያገኝ የሚችለው ደራሲው የማሰብ ችሎታውን ተጠቅሞ በሚገባ ካዘጋጀው ብቻ ነው።
ይሖዋ በድን ከሆኑት የብሔራት አማልክት በተቃራኒ “ሕያው አምላክ” ነው። (ኤር 10:10፤ 2ቆሮ 6:16) ስለ ታላቅነቱና ስለ ሥራዎቹ የሚመሠክሩ ነገሮችን የትም ቦታ ማግኘት እንችላለን። “ሰማያት የአምላክን ክብር ይናገራሉ፤ ጠፈርም የእጆቹን ሥራ ያውጃል።” (መዝ 19:1) ሰዎች አምላክ የለም ለማለት የሚያበቃ ምክንያት ወይም ሰበብ የላቸውም፤ ምክንያቱም “ስለ አምላክ ሊታወቅ የሚችለው ነገር በእነሱ ዘንድ በግልጽ የታወቀ ነው፤ ይህም የሆነው አምላክ ይህን ግልጽ ስላደረገላቸው ነው። የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል፤ ስለሆነም የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም።”—ሮም 1:18-20
ይሖዋ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንደሚኖር (መዝ 90:2, 4፤ ራእይ 10:6) የዘላለም ንጉሥ፣ የማይጠፋ፣ የማይታይና እሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ተገልጿል። (1ጢሞ 1:17) ከእሱ በፊት አምላክ ኖሮ አያውቅም።—ኢሳ 43:10, 11
አቻ የሌለው ግን የሚቀረብ። እውነተኛው አምላክ አቻ የሌለውና የሰው አእምሮ ሙሉ ለሙሉ ሊረዳው የማይችል ነው። ማንኛውም ፍጡር ከፈጣሪው ጋር ሊተካከልም ሆነ የእሱን አሠራር ሙሉ ለሙሉ ሊረዳ አይችልም። (ሮም 11:33-36) ይሁን እንጂ ሰዎች ሊያገኙትና ሊቀርቡት ይችላሉ፤ እንዲሁም አምላኪዎቹ ደህንነታቸው እንዲጠበቅና ደስተኛ እንዲሆኑ ሲል የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ያቀርባል። (ሥራ 17:26, 27፤ መዝ 145:16) ለፍጥረታቱ መልካም ነገር የመስጠት ከፍተኛ ችሎታና ፈቃደኝነት እንዳለው የሚከተለው ጥቅስ ያረጋግጣል፦ “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት ሲሆን እሱ ደግሞ ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም።” (ያዕ 1:17) ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ያወጣቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች ሳይጥስ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ነው። (ሮም 3:4, 23-26) በመሆኑም ሁሉም ፍጥረታቱ እሱ ራሱ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንጊዜም እንደሚያከብር ስለሚያውቁ ሙሉ በሙሉ ሊተማመኑበት ይችላሉ። እሱ አይለወጥም፤ (ሚል 3:6) መሠረታዊ ሥርዓቶቹን የሚያስፈጽምበት መንገድም ‘አይለዋወጥም።’ በእሱ ዘንድ አድልዎ የለም፤ (ዘዳ 10:17, 18፤ ሮም 2:11) ፈጽሞ ሊዋሽ አይችልም።—ዘኁ 23:16, 19፤ ቲቶ 1:1, 2፤ ዕብ 6:17, 18
ባሕርያቱ። እውነተኛው አምላክ የሚገኘው በሁሉም ቦታ አይደለም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ መኖሪያ ቦታ እንዳለው ይናገራል። (1ነገ 8:49፤ ዮሐ 16:28፤ ዕብ 9:24) ዙፋኑ በሰማይ ነው። (ኢሳ 66:1) ሁሉን ቻይ አምላክ እንደመሆኑ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው። (ዘፍ 17:1፤ ራእይ 16:14) “በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው፤” በተጨማሪም “ከመጀመሪያ መጨረሻውን” የሚናገር አምላክ ነው። (ዕብ 4:13፤ ኢሳ 46:10, 11፤ 1ሳሙ 2:3) ኃይሉና እውቀቱ ከፍተኛ ስለሆነ መላውን ጽንፈ ዓለም መመልከት ይችላል።—2ዜና 16:9፤ መዝ 139:7-12፤ አሞጽ 9:2-4
እውነተኛው አምላክ መንፈሳዊ አካል እንጂ ሥጋዊ አካል የለውም፤ (ዮሐ 4:24፤ 2ቆሮ 3:17) ያም ቢሆን ልክ እንደ ሰዎች የማየትና ሌሎች ነገሮችን የማድረግ ችሎታ እንዳለው ተደርጎ ተገልጿል። በመሆኑም በምሳሌያዊ ሁኔታ “ክንድ” (ዘፀ 6:6)፣ “ዓይን” እና “ጆሮ” እንዳለው ተናግሯል፤ (መዝ 34:15) በተጨማሪም የሰውን ዓይንና ጆሮ የፈጠረው እሱ በመሆኑ ማየትና መስማት እንደሚችል ገልጿል።—መዝ 94:9
ከአምላክ ባሕርያት መካከል ዋነኞቹ ፍቅር (1ዮሐ 4:8)፣ ጥበብ (ምሳሌ 2:6፤ ሮም 11:33)፣ ፍትሕ (ዘዳ 32:4፤ ሉቃስ 18:7, 8) እና ኃይል (ኢዮብ 37:23፤ ሉቃስ 1:35) ናቸው። እሱ የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም። (1ቆሮ 14:33) እጅግ ቅዱስና ንጹሕ (ኢሳ 6:3፤ ዕን 1:13፤ ራእይ 4:8)፣ ደስተኛ (1ጢሞ 1:11)፣ እንዲሁም መሐሪ (ዘፀ 34:6፤ ሉቃስ 6:36) ነው። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሌሎች በርካታ ባሕርያቱም ተጠቅሰዋል።
ሥልጣኑ። ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታና የዘላለም ንጉሥ ነው። (መዝ 68:20፤ ዳን 4:25, 35፤ ሥራ 4:24፤ 1ጢሞ 1:17) ዙፋኑ የመጨረሻውን ከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ያመለክታል። (ሕዝ 1:4-28፤ ዳን 7:9-14፤ ራእይ 4:1-8) እሱ ግርማዊ (ዕብ 1:3፤ 8:1)፣ ባለ ግርማ አምላክ፣ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ነው። (1ሳሙ 4:8፤ ኢሳ 33:21) የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነው።—ኢዮብ 33:4፤ መዝ 36:9፤ ሥራ 17:24, 25
ጽድቁና ክብሩ። እውነተኛው አምላክ ጻድቅ አምላክ ነው። (መዝ 7:9) እሱ ክብር የተጎናጸፈ አምላክ ነው። (መዝ 29:3፤ ሥራ 7:2) ከማንም በላይ ግርማዊ የሆነ (ዘዳ 33:26)፣ ግርማና ብርታት (መዝ 93:1፤ 68:34) እንዲሁም ሞገስ የተላበሰ ነው። (መዝ 104:1፤ 1ዜና 16:27፤ ኢዮብ 37:22፤ መዝ 8:1) “ሥራው ግርማና ውበት የተላበሰ ነው።” (መዝ 111:3) ንግሥናው ታላቅ ክብር የተላበሰ ነው።—መዝ 145:11, 12
ዓላማው። አምላክ ያወጣው ዓላማ መፈጸሙ አይቀርም፤ ሊቀለብሰው የሚችል አካል የለም። (ኢሳ 46:10፤ 55:8-11) ዓላማውም በኤፌሶን 1:9, 10 ላይ እንደተገለጸው “ሁሉንም ነገሮች ማለትም በሰማያት የሚሆኑ ነገሮችንና በምድር የሚሆኑ ነገሮችን በክርስቶስ አንድ ላይ ለመሰብሰብ ነው።” የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ በክርስቶስ አማካኝነት ከአምላክ ጋር ስምምነት ይፈጥራሉ። (ከማቴ 6:9, 10 ጋር አወዳድር።) ከይሖዋ በፊት ምንም ነገር ስላልነበረ ከእሱ የሚቀድም የለም። (ኢሳ 44:6) እሱ ፈጣሪ በመሆኑ ከየትኛውም አምላክ በፊት ነበር፤ ‘ከእሱ በኋላም አምላክ አይኖርም።’ ምክንያቱም ሰዎች ትንቢት ሊናገር የሚችል ሕያው አምላክ ሊሠሩ አይችሉም። (ኢሳ 43:10፤ 46:9, 10) አልፋና ኦሜጋ (ራእይ 22:13) እንደመሆኑ መጠን ሁሉን ቻይ አምላክ እሱ ብቻ ነው፤ በአምላክነቱ ላይ የተነሳው ጥያቄ በተሳካ ሁኔታ እንዲቋጭ በማድረግ ሁሉን ቻይ አምላክ እሱ ብቻ መሆኑ ለዘላለም እንዲረጋገጥ ያደርጋል። (ራእይ 1:8፤ 21:5, 6) ዓላማውን ወይም ቃል ኪዳኑን ፈጽሞ አይረሳም ወይም ሳይፈጽም አይቀርም፤ ይህም እምነት የሚጣልበት አምላክ እንዲሆን ያደርገዋል።—መዝ 105:8
ሐሳቡን የሚገልጽ አምላክ። አምላክ ለፍጥረታቱ እጅግ ታላቅ ፍቅር ስላለው እሱንና ዓላማዎቹን ማወቅ የሚችሉበት በርካታ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። በምድር ላይ ያሉ ሰዎች የራሱን ድምፅ በሦስት የተለያዩ አጋጣሚዎች እንዲሰሙ አድርጓል። (ማቴ 3:17፤ 17:5፤ ዮሐ 12:28) በመላእክት በኩል (ሉቃስ 2:9-12፤ ሥራ 7:52, 53)፣ መመሪያዎችን በሰጣቸውና ራእይ እንዲያዩ ባደረጋቸው እንደ ሙሴ ባሉ ሰዎች አማካኝነት በተለይ ደግሞ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሐሳቡን ገልጿል። (ዕብ 1:1, 2፤ ራእይ 1:1) ለሕዝቡ ሐሳቡን ለመግለጽ የተጠቀመበት በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ ሕዝቦቹ በሚገባ የታጠቁ አገልጋዮቹ እንዲሆኑና በሕይወት መንገድ እንዲጓዙ አስችሏቸዋል።—2ጴጥ 1:19-21፤ 2ጢሞ 3:16, 17፤ ዮሐ 17:3
ከብሔራት አማልክት ጋር ሲነጻጸር። ታላቅ ግርማ የተላበሱትን የሰማይ አካላት የፈጠረው እውነተኛው አምላክ ያለው ግርማና ክብር በሰው ዓይን ሊታይ አይችልም፤ ምክንያቱም ‘ማንም ሰው አይቶት በሕይወት መኖር አይችልም።’ (ዘፀ 33:20) የአምላክን ፊት ቃል በቃል የማየት ችሎታ ያላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት የሆኑት መላእክት ብቻ ናቸው። (ማቴ 18:10፤ ሉቃስ 1:19) ይሁን እንጂ ሰዎች እንዲህ ያለውን አጋጣሚ አላገኙም። ይሁን እንጂ በፍቅራዊ ደግነቱ ተነሳስቶ በቃሉና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን በመግለጥ ያሉትን ግሩም ባሕርያት ሰዎች እንዲያውቁ አድርጓል።—ማቴ 11:27፤ ዮሐ 1:18፤ 14:9
አምላክ፣ እሱን ማየት የሚያሳድረውን ስሜት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ገልጾልናል። ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው ነገር አምላክን የማየት ያህል ነበር፤ በሌላ አባባል አምላክን በዙፋኑ ላይ ማየት ምን ስሜት እንደሚያሳድር የሚገልጽ ነው። አምላክ የሰው ዓይነት ገጽታ የለውም፤ ምክንያቱም የሆነ ቅርጽ ወይም መልክ ይዞ ለሰው ልጆች ተገልጦ አያውቅም፤ እንዲያውም ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ እንደገለጸው “በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም።” (ዮሐ 1:18) ከዚህ ይልቅ አምላክ የታየው ዓይን እንደሚስብና በአድናቆት እንደሚያፈዝ በደንብ የተወለወለ፣ እጅግ የሚያብረቀርቅ፣ የሚያምርና ውድ የሆነ ዕንቁ ሆኖ ነው። አምላክ “የኢያስጲድ ድንጋይና የሰርድዮን ድንጋይ ዓይነት መልክ ነበረው፤ በዙፋኑም ዙሪያ መረግድ የሚመስል ቀስተ ደመና ነበር።” (ራእይ 4:3) በመሆኑም አምላክ መልኩ የሚያምርና ለማየት የሚያስደስት ሲሆን ያየው ሁሉ በአድናቆት ይዋጣል። ዙፋኑም ግርማ የተላበሰ፣ ፀጥታና እርጋታ የሰፈነበት ነው። መረግድ የሚመስለው ቀስተ ደመና ከባድ ማዕበል ካለፈ በኋላ የሚኖረውን ፀጥታ ያስታውሳል።—ከዘፍ 9:12-16 ጋር አወዳድር።
በእርግጥም እውነተኛው አምላክ፣ ብዙ ጊዜ የሚያስፈራ ፊት ያላቸው፣ ቁጡ፣ ጨካኝ፣ አዘኔታ የሌላቸው፣ ምሕረት የለሽ፣ የሚወዱትም ሆነ የሚጠሉት ነገር የማይታወቅ፣ አስፈሪና አረመኔ እንዲሁም በምድር ያሉ ፍጥረታትን በማሠቃየት የሚደሰቱ እንደሆኑ ተደርገው ከሚገለጹት የብሔራት አማልክት ምንኛ የተለየ ነው!
‘እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ።’ “ብዙ ‘አማልክት’ እና ብዙ ‘ጌቶች’ እንደመኖራቸው መጠን በሰማይም ሆነ በምድር አማልክት ተብለው የሚጠሩ ቢኖሩም እንኳ እኛ ግን ሁሉም ነገር ከእሱ የሆነ እኛም ለእሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን።” (1ቆሮ 8:5, 6) ይሖዋ ሁሉን ቻይ፣ እሱ ብቻ እውነተኛ የሆነ አምላክ እንዲሁም እሱ ብቻ ሊመለክ የሚገባው አምላክ ነው። (ዘፀ 20:5) አገልጋዮቹ በሚያደርጉት ነገርም ሆነ በልባቸው ውስጥ ለአምላክ ተገቢውን ቦታ መስጠት ይኖርባቸዋል፤ ይህን ቦታ ለሌሎች አማልክት መስጠት አይኖርባቸውም። አገልጋዮቹ በመንፈስና በእውነት እንዲያመልኩት ይፈልጋል። (ዮሐ 4:24) ማክበርና መፍራት የሚገባቸው እሱን ብቻ ነው።—ኢሳ 8:13፤ ዕብ 12:28, 29
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አማልክት” ተብለው ከተጠሩ ኃያላን መካከል “አምላክ የሆነው” ኢየሱስ ክርስቶስ ይገኝበታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ራሱ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐ 1:18፤ ሉቃስ 4:8፤ ዘዳ 10:20) መላእክትም ‘እንደ አምላክ ያሉ’ ናቸው፤ ይሁን እንጂ አንድ መልአክ “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው! . . . ለአምላክ ስገድ!” በማለት ዮሐንስ እንዳያመልከው ተከላክሏል። (መዝ 8:5፤ ዕብ 2:7፤ ራእይ 19:10) በዕብራውያን መካከል ይኖሩ የነበሩ ኃያላን ሰዎች “አማልክት” ተብለዋል (መዝ 82:1-7)፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች አማልክት ተብለው ቢጠሩም የአምላክ ዓላማ ሰዎች እንዲመለኩ አይደለም። ጴጥሮስ፣ ቆርኔሌዎስ ሊሰግድለት ሲል “ተነስ፣ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” በማለት ከልክሎታል። (ሥራ 10:25, 26) የሰው ልጆች በኤደን ዓመፅ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የሠሯቸውና ያበጇቸው የሐሰት አማልክት መመለክ አይገባቸውም። የሙሴ ሕግ ከይሖዋ ርቆ እነሱን ማምለክ ተገቢ እንዳልሆነ በጥብቅ ያስጠነቅቃል። (ዘፀ 20:3-5) እውነተኛ አምላክ የሆነው ይሖዋ ከንቱ የሆኑት የሐሰት አማልክት የእሱ ተቀናቃኝ ሆነው እንዲቀጥሉ አይፈቅድላቸውም።—ኤር 10:10, 11
ክርስቶስ የአምላክ ተቃዋሚ የሆነን ማንኛውንም ኃይልና ሥልጣን ከሚያጠፋበት የሺህ ዓመት ግዛት በኋላ መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ ያስረክባል፤ ከዚያም አባቱ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ይሆናል። (ሮም 8:33፤ 1ቆሮ 15:23-28) በመጨረሻ ሕያዋን ሁሉ የአምላክን ሉዓላዊነት ተቀብለው ስሙን ለዘላለም ያወድሳሉ።—መዝ 150፤ ፊልጵ 2:9-11፤ ራእይ 21:22-27፤ “ይሖዋ” የሚለውን ተመልከት።