ሙታን የት ናቸው?
በምዕራብ አፍሪካ የሚገኘው የዩሩባ ሕዝብ “ምድር የገበያ ቦታ ናት፤ ሰማይ መኖሪያችን ነው” የሚል አባባል አለው። ይህ አመለካከት በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ ይስተጋባል። ይህ አባባል ምድር ለአጭር ጊዜ ደረስ ብለን እንደምንመለስበት የገበያ ቦታ ነች የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። በዚህ እምነት መሠረት በምንሞትበት ጊዜ ወደ ዋናው መኖሪያችን ወደ ሰማይ እንሄዳለን።
መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንዶች ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ያስተምራል። ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ . . . ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፣ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” ሲል ነግሯቸዋል።—ዮሐንስ 14:2, 3
የኢየሱስ አነጋገር ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ወይም ሰማይ የሰዎች መኖሪያ ነው ማለት አይደለም። በምድር ላይ ከመግዛት ጋር በተያያዘ ሁኔታ አንዳንዶች ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ። ይሖዋ አምላክ ሰብዓዊ መንግሥታት በምድር ላይ ያሉትን ጉዳዮች በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር እንደማይችሉ ያውቅ ነበር። ስለሆነም በመጨረሻ ምድርን የምትቆጣጠርና እሱ መጀመሪያ አቅዶት ወደነበረው ገነትነት የምትለውጥ ሰማያዊ መስተዳድር ወይም መንግሥት ለማቋቋም ዝግጅት አደረገ። (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ነው። (ዳንኤል 7:13, 14) ሌሎች ከእሱ ጋር አብረው እንዲገዙ ከሰዎች መካከል ይመረጣሉ። እነዚህ ወደ ሰማይ የሚወሰዱት “ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት” እንደሚሆኑና ‘በምድርም ላይ እንደሚነግሡ’ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል።—ራእይ 5:10
ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?
እነዚህ ሰማያዊ ገዥዎች ከሚኖራቸው ትልቅ ኃላፊነት አንጻር ስንመለከተው ጥብቅ የሆኑ ብቃቶችን ማሟላት የሚጠበቅባቸው መሆኑ አያስደንቅም። ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት ሊኖራቸውና እሱን ሊታዘዙ ይገባቸዋል። (ዮሐንስ 17:3፤ ሮሜ 6:17, 18) በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ማመን ይፈለግባቸዋል። (ዮሐንስ 3:16) ይሁን እንጂ ከዚህም የበለጠ ነገር ይፈለግባቸዋል። አምላክ በልጁ አማካኝነት የጠራቸውና የመረጣቸው መሆን አለባቸው። (2 ጢሞቴዎስ 1:9, 10፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) ከዚህም በላይ ደግሞ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ‘ዳግመኛ የተወለዱ’ የተጠመቁ ክርስቲያኖች መሆን አለባቸው። (ዮሐንስ 1:12, 13፤ 3:3–6) በተጨማሪም እስከ ሞት ድረስ ለአምላክ ፍጹም አቋማቸውን መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:11–13፤ ራእይ 2:10
ስፍር ቁጥር የሌላቸው በሕይወት ኖረው የሞቱ ሰዎች እነዚህን ብቃቶች አያሟሉም። ብዙዎቹ ስለ እውነተኛው አምላክ ለመማር ምንም አጋጣሚ አልነበራቸውም ለማለት ይቻላል። ሌሎች ደግሞ በፍጹም መጽሐፍ ቅዱስን አንብበው አያውቁም። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸው እውቀት በጣም ውስን ነው፤ አሊያም ደግሞ እስከ ጭራሹ ምንም አያውቁም። ዛሬ በምድር ላይ ካሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል እንኳን አምላክ ለሰማያዊ ሕይወት የመረጣቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው።
ስለዚህ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ትንሽ ነው። ኢየሱስ እነዚህን ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች “ታናሽ መንጋ” ሲል ጠርቷቸዋል። (ሉቃስ 12:32) ቆየት ብሎም በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት ‘ከምድር የተዋጁት’ ሰዎች ቁጥር 144,000 ብቻ እንደሚሆን ሐዋርያው ዮሐንስ ተገልጦለታል። (ራእይ 14:1, 3፤ 20:6) በምድር ላይ ከኖሩት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ብዛት ጋር ሲነጻጸር በእርግጥም ይህ ቁጥር ትንሽ ነው።
ወደ ሰማይ የማይሄዱት ሰዎች
ወደ ሰማይ የማይሄዱት ሰዎች ምን ይሆናሉ? አንዳንድ ሃይማኖቶች እንደሚያስተምሩት በዘላለማዊ የሥቃይ ሥፍራ እየተሠቃዩ ነውን? ይሖዋ የፍቅር አምላክ ስለሆነ በፍጹም ይህ ሊሆን አይችልም። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን እሳት ውስጥ አይጨምሩም፤ እንግዲያው ይሖዋም ሰዎችን በዚህ መንገድ አያሠቃይም።—1 ዮሐንስ 4:8
ሞተው ካሉት ሰዎች መካከል እጅግ የሚልቁት ወደፊት በምድራዊ ገነት ውስጥ ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ ይጠብቃቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ምድርን የፈጠራት ‘መኖሪያ እንድትሆን’ ነው ይላል። (ኢሳይያስ 45:18) መዝሙራዊው “የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 115:16) የሰው ልጆች የዘለቄታ መኖሪያ ሰማይ ሳይሆን ምድር ነች።
ኢየሱስ “በመቃብር ያሉት ሁሉ [“የሰው ልጅ” የሆነውን የኢየሱስን] ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል” ሲል ትንቢት ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:27–29) ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስም “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ . . . ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” ሲል ይህን አረጋግጧል። (ሥራ 24:15) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሳለ ንስሐ ለገባው ክፉ አድራጊ በትንሣኤ አማካኝነት በምድራዊት ገነት ውስጥ ሕይወት የማግኘት ተስፋ ሰጥቶታል።—ሉቃስ 23:43
ሆኖም በምድር ላይ ለሚኖረው ሕይወት ትንሣኤ የሚያገኙት ሙታን አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? ኢየሱስ ሲያገለግል ያጋጠመው አንድ ሁኔታ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳናል። ኢየሱስ ወዳጁ አልዓዛር ሞቶ ነበር። ኢየሱስ ሊያስነሣው ከመሄዱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው።” (ዮሐንስ 11:11) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ሞትን ምንም ዓይነት ሕልም ከማይታይበት ድብን ካለ እንቅልፍ ጋር አነጻጽሮታል።
በሞት ማንቀላፋት
በሞት ማንቀላፋት ከሚለው ከዚህ ሐሳብ ጋር ሌሎች ጥቅሶችም ይስማማሉ። እነዚህ ጥቅሶች ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ከእነሱ ተለይታ ወደ መንፈሳዊው ዓለም የምትሄድ የማትሞት ነፍስ አለቻቸው ብለው አያስተምሩም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ . . . ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፣ . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል [በመቃብር] ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና” ይላል። (መክብብ 9:5, 6, 10) ከዚህም በላይ መዝሙራዊው፣ ሰው “ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል” ሲል ተናግሯል።—መዝሙር 146:4
እነዚህ ጥቅሶች በሞት ያንቀላፉ ሰዎች ሊያዩን ወይም ሊሰሙን እንደማይችሉ ግልጽ ያደርጉልናል። በሞት ያንቀላፉ ሰዎች በረከትም ሆነ ጥፋት ሊያመጡ አይችሉም። በሰማይ ወይም ከቀድሞ አባቶች ጋር እየኖሩ አይደሉም። እነሱ በድንና ከሕልውና ውጭ ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ በሞት ያንቀላፉትና በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ ያሉት አምላክ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ ይቀሰቀሳሉ። ከአካባቢ መበከል፣ የሰው ልጅ አሁን እየደረሰበት ካለው ችግርና መከራ የጸዳች ምድር ትሆናለች። ይህ ምንኛ የሚያስደስት ጊዜ ይሆናል! መዝሙር 37:29 “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል ዋስትና ስለሚሰጠን በዚያች ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይጠብቃቸዋል።
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙታንን ማምለክ ተውኩ
“ልጅ በነበርኩበት ጊዜ አባቴ ለሞተው አባቱ ዘወትር መሥዋዕት በሚያቀርብበት ወቅት እረዳው ነበር። አንድ ጊዜ አባቴ በጠና ከታመመ በኋላ ከበሽታው ያገግማል። ስለሆነም ለዚህ ያለውን አድናቆት ለመግለጽ ለሞተው አባቱ የፍየል፣ የስኳር ድንች፣ የኮላ ፍሬዎችና የአረቄ መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚኖርበት አንድ ደብተራ ይነግረዋል። በተጨማሪም ሌላ በሽታና መቅሰፍት እንዳይመጣበት የቀድሞ አባቶቹን መለማመን እንዳለበት ምክር ይሰጠዋል።”
“እናቴም በአያቴ መቃብር ላይ ለሚቀርበው መሥዋዕት የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ገዛዛች። በአካባቢው ልማድ መሠረት መቃብሩ ያለው ልክ ከቤታችን አጠገብ ነው።”
“ወዳጆቻችን፣ ዘመዶቻችንና ጎረቤቶቻችን በሙሉ መሥዋዕቱ በሚቀርብበት ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ ተጋበዙ። አባቴ ለሥነ ሥርዓቱ የሚስማማ ያሸበረቀ ልብስ ለብሶ ከዚህ በፊት ለመሥዋዕት የቀረቡ በርካታ ፍየሎች ጭንቅላት በመደዳ ወደ ተቀመጠበት ቅዱስ ሥፍራ ፊቱን መልሶ አንድ ወንበር ላይ ተቀመጠ። የእኔ ሥራ ከጠርሙሱ ውስጥ የወይን ጠጅ በብርጭቆ እየቀዳሁ ለአባቴ መስጠት ነበር። እሱ ደግሞ በተራው ለመሥዋዕት እንዲሆን መሬት ላይ ያፈስሰዋል። አባቴ ሦስት ጊዜ የአባቱን ስም በመጥራት ወደፊት ከሚመጣ መቅሰፍት እንዲጠብቀው ጸለየ።”
“የኮላ ፍሬዎች ለመሥዋዕት ቀረቡ፣ እንዲሁም በግ ታረዶ ከተቀቀለ በኋላ እዚያ የተገኙት ሁሉ በሉ። እኔም ከበላሁ በኋላ ሲዘፈንና ከበሮ ሲመታ አብሬ ጨፈርኩ። አባቴ ምንም እንኳን እንዳረጀ ቢያስታውቅበትም ጥሩ አድርጎ ጨፈረ። የቀድሞ አባቶቹ በዚያ የተገኙትን ሁሉ እንዲባርኩ በየጣልቃው ይጸልይ ነበር። በዚህ ጊዜ እኔን ጨምሮ በዚያ ያሉት ሰዎች በሙሉ አይሲ ማለትም ‘አሜን’ በማለት እንመልስ ነበር። አባቴ እኔ አድጌ ለሞቱ የቀድሞ አባቶቻችን መሥዋዕት ለማቅረብ የምችልበትን ጊዜ በጉጉትና በናፍቆት ይጠብቅ እንደነበረ ለማስተዋል ችያለሁ።”
“ምንም እንኳን ብዙ መሥዋዕት ቢቀርብም በቤተሰቡ ውስጥ ግን ሰላም ሊኖር አልቻለም። እናቴ ከሞት የተረፉ ሦስት ወንዶች ልጆች ቢኖሯትም ከወለደቻቸው ሦስት ሴቶች ልጆች መካከል ግን አንዳቸውም ቢሆኑ ረዘም ላለ ጊዜ በሕይወት አልቆዩም። ሁሉም የሞቱት በሕፃንነታቸው ነው። እናቴ እንደገና ስትፀንስ ሕፃኑ በደህና እንዲወለድ አባቴ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት መሥዋዕት አቀረበ።”
“እናቴ ሌላ ሴት ልጅ ወለደች። ከሁለት ዓመት በኋላ ሕፃኗ ታመመችና ሞተች። አባቴ ደብተራውን ሲያማክር ልጅቷ እንድትሞት ያደረጋት ጠላት እንደሆነ ይነግረዋል። ደብተራውም የልጅቷ ‘ነፍስ’ አጸፋውን ለመመለስ እንድትችል የማገዶ እንጨት፣ አንድ ጠርሙስ አረቄና አንድ የውሻ ቡችላ መሠዋት ያስፈልጋል አለ። የማገዶው እንጨት በመቃብሩ ላይ የሚደረግ ነው፤ አረቄው በመቃብሩ ላይ የሚረጭ ሲሆን የውሻ ቡችላው ደግሞ በመቃብሩ አጠገብ ከነሕይወቱ የሚቀበር ነው። ይህም የሞተችው ልጅ ነፍስ ገዳይዋን እንድትበቀል ያነቃታል ተብሎ ይታመናል።”
“እኔ አንዱን ጠርሙስ አረቄና የማገዶውን እንጨት ይዤ ወደ መቃብሩ ስሄድ አባቴ ደግሞ የውሻ ቡችላውን ይዞ ሄደ። ከዚያም ደብተራው በሰጠው መመሪያ መሠረት ቀበረው። ሁላችንም የሞተችው ልጅ ነፍስ በሰባት ቀን ውስጥ በለጋ ዕድሜዋ እንድትቀጭ ያደረጋትን ሰው ታጠፋለች ብለን አምነን ነበር። ሁለት ወር አለፈ፤ ነገር ግን በአካባቢው ምንም ሰው አልሞተም። በጣም ግራ ተጋባሁ።”
“በዚያን ጊዜ የ18 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮችን አገኘሁ። እነሱም ሙታን በሕያዋን ላይ ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ሊያደርጉባቸው እንደማይችሉ ከቅዱሳን ጽሑፎች አውጥተው አሳዩኝ። የአምላክ ቃል እውቀት በልቤ ውስጥ ሥር እየሰደደ ሲሄድ አባቴ ለሙታን መሥዋዕት ሊያቀርብ በሚሄድበት ጊዜ ከእንግዲህ ወዲህ አብሬው ልሄድ እንደማልችል ነገርኩት። በመጀመሪያ ጊዜ አብሬህ አልሄድም ስላልኩት በጣም ተናድዶ ነበር። ነገር ግን አዲስ ያገኘሁትን እምነቴን ለመተው ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ ሲመለከት ይሖዋን ማምለኬን አልተቃወመም።”
“ሚያዝያ 18, 1948 ራሴን ለአምላክ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሊረዱም ሆነ ሊጎዱ የማይችሉትን የሞቱ የቀድሞ አባቶችን ከማምለክ እንዲላቀቁ ሌሎችን በመርዳት በብዙ ደስታና እርካታ ይሖዋን ማገልገሌን ቀጥያለሁ።”—ከናይጄሪያ ቤኒን ሲቲ በጄ ቢ ኦሚግቢ የተጻፈ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገነት በሆነች ምድር ላይ ሙታን ትንሣኤ በሚያገኙበት ጊዜ ታላቅ ደስታ ይሆናል