የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 43—ዮሐንስ
ጸሐፊው:- ሐዋርያው ዮሐንስ
የተጻፈበት ቦታ:- በኤፌሶን ወይም በአቅራቢያዋ
ተጽፎ ያለቀው:- በ98 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- መግቢያውን ሳይጨምር ከ29–33 ከክ.ል.በኋላ
የማቴዎስ፣ የማርቆስና የሉቃስ ወንጌሎች ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ሲሰራጩ ቆይተዋል፤ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም እነዚህ መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፉ መሆናቸውን አምነው በመቀበል ከፍተኛ ግምት ይሰጧቸው ነበር። የመጀመሪያው መቶ ዘመን መደምደሚያ ሲቃረብና ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ሰዎች ቁጥር ሲመናመን የሚከተሉት ጥያቄዎች ተነስተው ሊሆን ይችላል:- ገና በጽሑፍ ያልሰፈረ ዘገባ ይኖር ይሆን? የኢየሱስን አገልግሎት በሚመለከት ውድ የሆኑትን ተጨማሪ ዝርዝር ነገሮች አስታውሶ ሊዘግብ የሚችል ሰው ይኖር ይሆን? አዎን፣ ይህን ማድረግ የሚችል ሰው ነበር። አረጋዊው ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር በነበረው ቅርርብ በጣም ተባርኳል። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ከአምላክ በግ ጋር ከተዋወቁት የመጀመሪያዎቹ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት እንዲሁም ጌታ ከእሱ ጋር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ መጀመሪያ ከጋበዛቸው አራት ሰዎች አንዱ የነበረ ይመስላል። (ዮሐ. 1:35-39፤ ማር. 1:16-20) ኢየሱስ በአገልግሎት ባሳለፈው ጊዜ በሙሉ ሐዋርያው ዮሐንስ የቅርብ ወዳጁ የነበረ ከመሆኑም በላይ በመጨረሻው የማለፍ በዓል ወቅት ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ የተቀመጠውና “ኢየሱስ ይወደው የነበረ” የተባለው ደቀ መዝሙር እሱ ነበር። (ዮሐ. 13:23፤ ማቴ. 17:1፤ ማር. 5:37፤ 14:33) በጣም አሳዛኝ የነበረውን የኢየሱስ ሞት በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል፤ ኢየሱስ እናቱን እንዲንከባከብለት በአደራ የሰጠው በዚህ ጊዜ ነበር። እንዲሁም ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን የሚገልጽ ወሬ ሲሰሙ ሁኔታውን ለማጣራት ወደ መቃብሩ እየሮጡ በሄዱ ጊዜ ጴጥሮስን ቀድሞት የደረሰው ደቀ መዝሙር ዮሐንስ ነው።—ዮሐ. 19:26, 27፤ 20:2-4
2 ዮሐንስ፣ ወደ 70 ለሚጠጉ ዓመታት ባከናወነው አገልግሎት ተሞክሮ ማካበቱና ራእዮችን መመልከቱ እንዲሁም በፍጥሞ ደሴት ላይ ብቻውን ታስሮ በነበረበት ወቅት ሲያሰላስል መቆየቱ፣ ለረጅም ጊዜ በልቡ ይዞት የነበረውን ነገር በጽሑፍ ለማስፈር በሚገባ ዝግጁ እንዲሆን ረድቶታል። ዮሐንስ ውድና ሕይወት ሰጪ የሆኑትን ትምህርቶች እያስታወሰ በጽሑፍ ማስፈር እንዲችል መንፈስ ቅዱስ የረዳው ሲሆን ይህን ማድረጉም መጽሐፉን የሚያነብ ሁሉ ‘ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ ሆነ ያምን ዘንድ፣ አምኖም በስሙ ሕይወት እንዲኖረው’ ያስችላል።—20:31
3 በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበሩት ክርስቲያኖች የዚህ ዘገባ ጸሐፊ ዮሐንስ መሆኑን አምነው ከመቀበላቸውም በላይ መጽሐፉ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑ ምንም እንደማያጠያይቅ እርግጠኞች ነበሩ። በሁለተኛው መቶ ዘመን ማብቂያና በሦስተኛው መቶ ዘመን መባቻ አካባቢ የኖሩት የእስክንድርያው ክሌመንት፣ ኢራንየስ፣ ተርቱሊያንና ኦሪጀን የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ዮሐንስ መሆኑን መሥክረዋል። ከዚህም በላይ በራሱ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ጸሐፊው እሱ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ጸሐፊው አይሁዳዊ እንደሆነና የአይሁዳውያንን ባሕልም ሆነ የምድራቸውን አቀማመጥ በሚገባ እንደሚያውቅ በግልጽ መመልከት ይቻላል። (2:6፤ 4:5፤ 5:2፤ 10:22, 23) ጸሐፊው ያሰፈረውን ዘገባ በቅርብ እንደሚያውቀው ከጽሑፉ መረዳት የሚቻል ሲሆን ይህም ወንጌሉን የጻፈው ግለሰብ ሐዋርያ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ለየት ባሉ አጋጣሚዎች ከኢየሱስ ጋር ይሆኑ ከነበሩት ሦስት ሐዋርያት ማለትም ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብ እና ከዮሐንስ መካከል አንዱ እንደሆነ ይጠቁማል። (ማቴ. 17:1፤ ማር. 5:37፤ 14:33) ከእነዚህ ሦስት ሐዋርያት መካከል ያዕቆብ (የዘብዴዎስ ልጅ) የዮሐንስ ወንጌል ከመጻፉ ከረጅም ጊዜ በፊት ማለትም በ44 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ በቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ስለተገደለ ጸሐፊው እሱ ሊሆን አይችልም። (ሥራ 12:2) ጴጥሮስ ደግሞ በዮሐንስ 21:20-24 ላይ ከዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ጋር እንደነበረ ስለተገለጸ እሱም ይህን ወንጌል አልጻፈውም።
4 በእነዚህ የመደምደሚያ ቁጥሮች ላይ ጸሐፊው “ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር” ተብሎ ተገልጿል፤ በዚህ ወንጌል ውስጥ የሐዋርያው ዮሐንስ ስም አንድም ጊዜ ባይጠቀስም ከላይ እንዳለው ያሉ አነጋገሮች በተደጋጋሚ ጊዜያት ተመዝግበው እናገኛለን። ከላይ ያለው ጥቅስ ላይ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ሲናገር “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ?” እንዳለ ተጠቅሷል። (ዮሐ. 21:20, 22) ይህ አባባል ደቀ መዝሙሩ ከጴጥሮስም ሆነ ከሌሎቹ ሐዋርያት የበለጠ ዕድሜ እንደሚኖር ይጠቁማል። እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ይስማማሉ። ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ መምጣት የሚገልጸውን ራእይ ከተቀበለ በኋላ አስገራሚ የሆነውን ትንቢት ሲደመድም “አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ና” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው።—ራእይ 22:20
5 ዮሐንስ የጻፋቸው መጻሕፍት ወንጌሉን መቼ እንደጻፈው ባይገልጹም ወንጌሉን የጻፈው በፍጥሞ ደሴት በግዞት ቆይቶ ሲመለስ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። (ራእይ 1:9) ከ96-98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የገዛው የሮማው ንጉሠ ነገሥት ኔርቫ፣ ከእሱ በፊት በነበረው በደሚሻን ግዛት ማብቂያ አካባቢ በግዞት ላይ ከነበሩት መካከል ብዙዎቹን ወደ አገራቸው መልሷቸው ነበር። ዮሐንስ፣ በ98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ወንጌሉን ከጻፈ በኋላ በንጉሠ ነገሥት ትራጃን ሦስተኛ የግዛት ዓመት ማለትም በ100 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኤፌሶን በሰላም ሕይወቱ እንዳለፈ ይታመናል።
6 መጽሐፉ የተጻፈው በኤፌሶን ወይም በአቅራቢያዋ መሆኑን በተመለከተ ታሪክ ጸሐፊው ዩሲቢየስ (260-342 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ)፣ ኢራንየስን እንደ ዋቢ በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “የጌታ ደቀ መዝሙር የሆነውና ወደ ጌታ ደረት ጠጋ ብሎ ያናገረው ዮሐንስ፣ በእስያ በምትገኘው በኤፌሶን ሳለ ወንጌሉን ጽፏል።”a ዮሐንስ በወንጌሉ ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ የኢየሱስን ተቃዋሚዎች “ፈሪሳውያን” እንዲሁም “የካህናት አለቆች” እያለ ከመጥራት ይልቅ “አይሁድ” በሚለው የወል ስም መጠቀሙ፣ መጽሐፉን በፓለስቲና ሆኖ እንዳልጻፈው የሚገልጸውን ሐሳብ የሚደግፍ ነው። (ዮሐ. 1:19፤ 12:9) ከዚህም በተጨማሪ የገሊላ ባሕር የጥብርያዶስ ባሕር በሚለው የሮማውያን ስያሜ ተጠርቷል። (6:1፤ 21:1) ዮሐንስ፣ አይሁዳውያን ላልሆኑት ሰዎች በማሰብ ስለ አይሁዳውያን በዓላት አስፈላጊውን ማብራሪያ ሰጥቷል። (6:4፤ 7:2፤ 11:55) በግዞት የቆየባት ፍጥሞ የተባለችው ደሴት የምትገኘው በኤፌሶን አቅራቢያ ነበር፤ ራእይ ምዕራፍ 2 እና 3 እንደሚያሳየው ዮሐንስ፣ ስለ ኤፌሶንና በትንሿ እስያ ስለነበሩት ሌሎች ጉባኤዎች ያውቅ ነበር።
7 የዮሐንስን ወንጌል ትክክለኛነት በ20ኛው መቶ ዘመን የተገኙ ጥንታዊ ጽሑፎች ይመሠክራሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ በግብጽ የተገኘውና በአሁኑ ጊዜ ፓፓይረስ ራይላንድስ 457 (P52) በመባል የሚታወቀው የዮሐንስ ወንጌል ቁራጭ ሲሆን ዮሐንስ 18:31-33, 37, 38ን ይዟል፤ ይህ ቁራጭ በማንቸስተር፣ እንግሊዝ ጆን ራይላንድስ በተባለው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል።b ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ስለመሆኑ የሚነገረውን ወግ በማረጋገጥ በኩል ይህ ግኝት ስላለው ድርሻ ሟቹ ሰር ፍሬድሪክ ኬንየን ዘ ባይብል ኤንድ ሞደርን ስኮላርሺፕ፣ 1949 በተባለው መጽሐፋቸው ገጽ 21 ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ቁራጭ ትንሽ ቢሆንም የዮሐንስ ወንጌል ጥንታዊ ቅጂ ከ130-150 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ ምናልባት አሁን በተገኘበት የሮም ግዛት በነበረችው ግብጽ ውስጥ በብዛት ተሠራጭቶ እንደነበር የሚጠቁም በቂ ማስረጃ ነው። ይህ ወንጌል ከተዘጋጀበት አካባቢ ተነሥቶ ወደ ሌሎች ቦታዎች ለመሠራጨት በጣም አጭር ጊዜ እንደወሰደበት ብናስብ እንኳ ወንጌሉ፣ በብዙዎች ዘንድ እንደሚታመነው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የመደምደሚያ አሥር ዓመት መጻፉን ይጠቁመናል፤ በመሆኑም የዚህን አባባል እውነተኝነት የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም።”
8 የዮሐንስ ወንጌል መግቢያ አስገራሚ ነው፤ ወንጌሉ፣ “በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር” በነበረው በቃል ሁሉም ነገር እንደተፈጠረ በመግለጽ ይጀምራል። (1:2) ዮሐንስ፣ በአብና በወልድ መካከል ስላለው ውድ ዝምድና ከገለጸ በኋላ ኢየሱስ ያደረጋቸውንና ያስተማራቸውን ነገሮች አስገራሚ በሆነ መንገድ መግለጹን ይቀጥላል። መግለጫዎቹ በተለይ በአምላክ ታላቅ ዝግጅት ውስጥ ያለውን ሁሉንም ነገር በሚያስተሳስረው በፍቅር ላይ ያተኮሩ ናቸው። ስለ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት የሚገልጸው ይህ ዘገባ፣ ከ29-33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሲሆን ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ስላከበራቸው አራት የፋሲካ በዓላትም ይጠቅሳል። ይህም ኢየሱስ በምድር ላይ ያገለገለው ለሦስት ዓመት ተኩል እንደነበር የሚጠቁም አንድ ማስረጃ ነው። ሦስቱ በዓላት የፋሲካ በዓል ተብለዋል። (2:13፤ 6:4፤ 12:1፤ 13:1) አንዱ ደግሞ “የአይሁድ በዓል” ተብሎ ተጠርቷል፤ ሆኖም ይህ ሐሳብ ኢየሱስ “ከአራት ወር በኋላ መከር ይደርሳል” ብሎ እንደተናገረ ከተገለጸ በኋላ ብዙም ሳይርቅ መጠቀሱ፣ ይህ በዓል በመከር ወቅት መጀመሪያ ላይ የሚከበረው የፋሲካ በዓል መሆኑን ይጠቁማል።—4:35፤ 5:1c
9 “የዮሐንስ ወንጌል” በአብዛኛው ሌሎቹን የወንጌል ዘገባዎች የሚያሟላ ሐሳብ የያዘ ነው፤ ከወንጌሉ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆነው በቀሩት ሦስት ወንጌሎች ውስጥ የማይገኝ አዲስ ሐሳብ ነው። ያም ሆኖ ግን ዮሐንስ ወንጌሉን ሲደመድም እንዲህ ብሏል:- “ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሁሉም ነገር ቢጻፍ፣ ለተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ዓለም በቂ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።”—21:25
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
30 “የዮሐንስ ወንጌል”፣ ቃል ተብሎ ስለሚጠራውና በኋላ ክርስቶስ ስለሆነው የአምላክ ልጅ በጣም ግልጽና አስደሳች ሐሳብ ይዟል፤ ይህ ወንጌል በመንፈስ የተቀባውን የአምላክ ልጅ በተመለከተ ጥልቀት ያለው አሳማኝ ማብራሪያ የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ ስለተናገራቸውና ስላከናወናቸው ነገሮች በዝርዝር ይገልጽልናል። ዮሐንስ ቀለል ያሉ ቃላትን መጠቀሙና ያልተወሳሰበ የአጻጻፍ ስልት መከተሉ ‘ያልተማረ ተራ ሰው’ መሆኑን የሚጠቁም ቢሆንም የተጠቀመባቸው መግለጫዎች ኃይል አላቸው። (ሥራ 4:13) ወንጌሉ በአብና በወልድ መካከል ስላለው የጠበቀ ፍቅር እንዲሁም ከእነሱ ጋር በመተባበር የሚገኘውን የተባረከ ፍቅራዊ ዝምድና በመግለጽ ረገድ አቻ አይገኝለትም። ዮሐንስ ‘ከፍቅር’ እና ‘ከመውደድ’ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ቃላት ሌሎቹ ሦስት ወንጌሎች አንድ ላይ ቢደመሩ እንኳን በማይተካከሉት መጠን ተጠቅሞባቸዋል።
31 ቃልና አብ ከመጀመሪያው አንስቶ ግሩም ግንኙነት ነበራቸው። በአምላክ መመሪያ መሠረት “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን።” (ዮሐ. 1:14) ከዚያም ኢየሱስ፣ የአባቱን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ እንደሚታዘዝ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በሙሉ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (4:34፤ 5:19, 30፤ 7:16፤ 10:29, 30፤ 11:41, 42፤ 12:27, 49, 50፤ 14:10) በእሱና በአባቱ መካከል ስላለው የጠበቀ ዝምድና የሰጣቸው ሐሳቦች በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ልብ የሚነካ ጸሎት አስደናቂ በሆነ መንገድ ይደመደማሉ፤ ኢየሱስ በዚህ ጸሎት ላይ አባቱ በምድር ላይ እንዲሠራው የሰጠውን ሥራ እንደፈጸመ ከገለጸ በኋላ እንዲህ በማለት አክሎ ተናግሯል:- “እንግዲህ አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ።”—17:5
32 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ስለነበረው ግንኙነትስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱም ሆኑ መላው የሰው ዘር የአምላክን በረከት የሚያገኙበት መሥመር በመሆን የሚጫወተው ሚና በተደጋጋሚ ጊዜ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። (14:13, 14፤ 15:16፤ 16:23, 24) ኢየሱስ “የእግዚአብሔር በግ፣” “የሕይወት እንጀራ፣” “የዓለም ብርሃን፣” “መልካም እረኛ፣” “ትንሣኤና ሕይወት፣” ‘መንገድ፣ እውነትና ሕይወት፣’ እንዲሁም “እውነተኛው የወይን ተክል” ተብሎ ተጠርቷል። (1:29፤ 6:35፤ 8:12፤ 10:11፤ 11:25፤ 14:6፤ 15:1) ኢየሱስ፣ ከእውነተኛ ተከታዮቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአብም ጋር ስላለው አስደናቂ አንድነት የገለጸው ስለ “እውነተኛው የወይን ተክል” በተናገረው በዚሁ ምሳሌ ላይ ነው። ተከታዮቹ ብዙ ፍሬ ቢያፈሩ አባቱ ይከበራል። ኢየሱስ “አብ እንደ ወደደኝ ሁሉ እኔም ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ” ሲል መክሯል።—15:9
33 ከዚያም እነዚህ የተወደዱ ሰዎችና ‘የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእሱ የሚያምኑ’ በእውነት ቃል ተቀድሰው ከእሱና ከአባቱ ጋር አንድ እንዲሆኑ ወደ ይሖዋ አጥብቆ ጸልዮአል! በእርግጥም ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት መደምደሚያ ላይ የአገልግሎቱ ዋነኛ ዓላማ ግሩም በሆነ መንገድ ተገልጿል:- “ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ።”—17:20, 26
34 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በዓለም ውስጥ ትቷቸው ሊሄድ ቢሆንም ያለ ረዳት ሊተዋቸው አላሰበም፤ ‘የእውነትን መንፈስ’ ይሰጣቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከዓለም ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ወቅታዊ ምክር ሰጥቷቸዋል፤ “የብርሃን ልጆች” እንደመሆናቸው መጠን ዓለምን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ ነግሯቸዋል። (14:16, 17፤ 3:19-21፤ 12:36) ኢየሱስ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” ብሏል። በአንጻሩ ደግሞ ለጨለማ ልጆች “እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። . . . በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም” ብሏቸዋል። እንግዲያውስ ዘወትር በእውነት ለመጽናት ማለትም ‘አብን በመንፈስና በእውነት’ ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ እንዲሁም “አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ከሚሉት የኢየሱስ ቃላት ብርታት እናግኝ።—8:31, 32, 44፤ 4:23፤ 16:33
35 ይህ ሁሉ ትምህርት ከአምላክ መንግሥት ጋርም የተያያዘ ነው። ኢየሱስ ለፍርድ በቀረበበት ጊዜ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” በማለት ተናግሯል። ከዚያም ጲላጦስ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ መናገርህ ትክክል ነው [“አንተ ትላለህ፣” የ1954 ትርጉም] የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል” ብሏል። (18:36, 37) በእርግጥም ኢየሱስን የሚሰሙ እንዲሁም ከንጉሡ ጋር በአንድነት ‘ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት’ ‘ዳግመኛ የተወለዱ’ ደስተኞች ናቸው። ንጉሥ የሆነውን እረኛ ድምፅ በመስማት የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት “ሌሎች በጎች” ደስተኞች ናቸው። በእርግጥም የዮሐንስ ወንጌል ‘ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ ሆነ እናምን ዘንድ፣ አምነንም በስሙ ሕይወት እንዲኖረን’ ስለተጻፈ አመስጋኝ እንድንሆን የሚገፋፋን ምክንያት አለን።—3:3, 5፤ 10:16፤ 20:31
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዚ ኤክለሲያስቲካል ሂስትሪ፣ ዩሲቢየስ V, VIII, 4
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 323
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 57-58