የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 9/15 ገጽ 21-26
  • ዛሬ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዛሬ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ የሚፈልገው ነገር
  • የፍቅር አስፈላጊነት
  • ፍቅራችንን የምናረጋግጥበት መንገድ
  • አዳጋች መስሎ የሚታይበት ምክንያት
  • ለኢየሱስ ፍቅር አጸፋውን ትመልሳለህን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • በልብ ላይ የተጻፈ የፍቅር ሕግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ፍቅርና ፍትሕ—በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • አምላክ ከሚወድዳቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነህን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 9/15 ገጽ 21-26

ዛሬ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

“ከደመናው:- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።”​—⁠ማቴዎስ 17:5

1. ሕጉ ዓላማውን ያከናወነው መቼ ነበር?

ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር ብዙ ገጽታዎች ያሉት ሕግ ሰጥቶ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እነሱን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፣ . . . የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና።” (ዕብራውያን 9:​10) ሕጉ እስራኤላውያን ቀሪዎች ኢየሱስ መሲህ ወይም ክርስቶስ መሆኑን እንዲቀበሉ በማድረግ ዓላማውን ፈጽሟል። በመሆኑም ጳውሎስ “ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና” በማለት ሊናገር ችሏል።​—⁠ሮሜ 10:4፤ ገላትያ 3:​19-25፤ 4:​4, 5

2. በሕጉ ሥር የነበሩት እነማን ነበሩ? ከሕጉ ነፃ የወጡትስ መቼ ነበር?

2 ታዲያ ዛሬ ሕጉ በእኛ ላይ አይሠራም ማለት ነውን? ቀድሞውኑም ቢሆን አብዛኛው የሰው ዘር በሕጉ ሥር እንዳልነበረ መዝሙራዊው ከተናገረው ሐሳብ ለመረዳት ይቻላል:- “[ይሖዋ] ቃሉን ለያዕቆብ፣ ሥርዓቱንና ፍርዱን ለእስራኤል ይናገራል። ለሌሎችም አሕዛብ ሁሉ እንዲህ አላደረገም፣ ፍርዱንም አልገለጠላቸውም።” (መዝሙር 147:​19, 20) አምላክ የኢየሱስን መሥዋዕት መሠረት በማድረግ አዲስ ቃል ኪዳን ባቋቋመ ጊዜ የእስራኤል ብሔር ጭምር ሕጉን ከመታዘዝ ግዴታ ነፃ ሆኗል። (ገላትያ 3:​13፤ ኤፌሶን 2:​15፤ ቆላስይስ 2:​13, 14, 16) ታዲያ ሕጉ መሥራቱን ካቆመ ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ሊያገለግሉት ከሚፈልጉ ሰዎች የሚጠብቅባቸው ነገር ምንድን ነው?

ይሖዋ የሚፈልገው ነገር

3, 4. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው መሠረታዊ ነገር ምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስን ፈለግ በቅርብ መከተል ያለብን ለምንድን ነው?

3 በኢየሱስ አገልግሎት መገባደጃ ዓመት ላይ ሐዋርያቱ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ አንድ ትልቅ ተራራ፣ ምናልባትም ወደ አርሞንዔም ተራራ ተረተር ሳይሆን አይቀርም፣ አብረውት ሄዱ። በዚያም ኢየሱስ ዕጹብ ድንቅ ክብር ተጎናጽፎ የሚያሳይ ትንቢታዊ ራእይ የተመለከቱ ሲሆን አምላክ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ብሎ ሲናገር ሰምተዋል። (ማቴዎስ 17:1-5) በመሠረቱ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ነገር ልጁን እንድንሰማ እንዲሁም ምሳሌውንና ትምህርቱን እንድንከተል ነው። (ማቴዎስ 16:​24) በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ “ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” ሲል ጽፏል።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:21

4 የኢየሱስን ፈለግ በቅርብ መከተል ያለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም እሱን በመምሰል ይሖዋ አምላክን መምሰል ስለምንችል ነው። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ኅልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዓመታት በሰማይ ከአባቱ ጋር አብሮ ስለኖረ አባቱን በቅርብ ያውቀዋል። (ምሳሌ 8:​22-31፤ ዮሐንስ 8:​23፤ 17:​5፤ ቆላስይስ 1:​15-17) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በታማኝነት አባቱን ወክሏል። “አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን [እናገራለሁ]” ብሏል። እንዲያውም ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ይሖዋን ይመስል ስለነበር “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ብሎ ሊናገር ችሏል።​—⁠ዮሐንስ 8:28፤ 14:9

5. ክርስቲያኖች በየትኛው ሕግ ሥር ናቸው? ይህስ ሕግ ተግባራዊ መሆን የጀመረው መቼ ነው?

5 ኢየሱስን መስማትና እሱን መምሰል ምን ማድረግን ይጠይቃል? በአንድ ሕግ ሥር መሆን ማለት ነውን? ጳውሎስ “እኔ ራሴ ከሕግ በታች [አይደለሁም]” ሲል ጽፏል። እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ስለ “አሮጌው ቃል ኪዳን” ማለትም ከእስራኤላውያን ጋር ስለተደረገው የሕግ ቃል ኪዳን ነበር። ጳውሎስ “በክርስቶስ ሕግ በታች” መሆኑን ግን አምኗል። (1 ቆሮንቶስ 9:20, 21፤ 2 ቆሮንቶስ 3:​14) አሮጌው የሕግ ቃል ኪዳን ሲያበቃ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ ሊታዘዙት የሚገባውን “የክርስቶስን ሕግ” የያዘ “አዲስ ኪዳን” ተተካ።​—⁠ሉቃስ 22:​20፤ ገላትያ 6:​2፤ ዕብራውያን 8:​7-13

6. “የክርስቶስን ሕግ” እንዴት አድርጎ መግለጽ ይቻላል? የምንታዘዘውስ እንዴት ነው?

6 ይሖዋ “የክርስቶስን ሕግ” እንደ አሮጌው የሕግ ቃል ኪዳን በተለያዩ ክፍሎች ተደራጅቶ በአንቀጽ መልክ በጽሑፍ እንዲሰፍር አላደረገም። ይህ ለክርስቶስ ተከታዮች የተሰጠው አዲስ ሕግ አድርግ አታድርግ የሚሉ ዝርዝር ደንቦችን የያዘ አይደለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ስለ ልጁ ሕይወትና ትምህርት የሚናገሩ አራት ዘገባዎችን አጽፎልናል። ከዚህም በላይ አምላክ የግል ባሕርይን፣ የጉባኤ ጉዳዮችን፣ በቤተሰብ መካከል ሊኖር የሚገባውን መልካም ግንኙነትና ሌሎች ጉዳዮችን የሚመለከቱ መመሪያዎችን እንዲጽፉ ከኢየሱስ ቀደምት ተከታዮች መካከል አንዳንዶቹን በመንፈሱ መርቶ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 6:​18፤ 14:​26-35፤ ኤፌሶን 5:​21-33፤ ዕብራውያን 10:​24, 25) የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌና ትምህርቶች በሕይወታችን ላይ ተግባራዊ የምናደርግና የመጀመሪያው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን ምክር የምንከተል ከሆነ “የክርስቶስን ሕግ” እየታዘዝን ነው። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚጠይቀው ይህንን ነው።

የፍቅር አስፈላጊነት

7. ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የመጨረሻውን የማለፍ በዓል ባከበረበት ወቅት የእሱን ሕግ መሠረታዊ ነገር ያጎላው እንዴት ነበር?

7 ፍቅር በሕጉ ውስጥ የጎላ ስፍራ የነበረው ቢሆንም የክርስቶስ ሕግ እምብርት ወይም ምሰሶ ነው። ኢየሱስ በ33 እዘአ የዋለውን የማለፍ በዓል ለማክበር ከሐዋርያቱ ጋር በተገናኘበት ወቅት ይህን ሐቅ ጠበቅ አድርጎ ገልጾታል። ሐዋርያው ዮሐንስ በዚያ ልዩ ምሽት ስለተከናወኑ ነገሮች በሰጠው የማጠቃለያ ሐሳብ ላይ ኢየሱስ የተናገራቸው ከልብ የመነጩ ቃላት ፍቅርን የሚጠቅሱ 28 መግለጫዎች ይዘዋል። ይህ የእሱን ሕግ መሠረታዊ ነገር ወይም መንፈስ ለሐዋርያቱ አጉልቶላቸዋል። ዮሐንስ የዚያን ልዩ ምሽት ክንውኖች ሲያጠቃልል እንደሚከተለው ብሎ መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው:- “ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፣ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፣ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።”​—⁠ዮሐንስ 13:1

8. (ሀ) በሐዋርያቱ መካከል በየጊዜው ክርክር እንደነበር የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ትሕትናን የሚመለከት ትምህርት ለሐዋርያቱ ያስተማረው እንዴት ነበር?

8 ኢየሱስ ሐዋርያቱ ለሥልጣንና ለደረጃ የነበራቸውን ከልክ ያለፈ ፍላጎት እንዲያሸንፉ ለመርዳት ያደረገው ጥረት ውጤት ባያስገኝም ለእነርሱ የነበረው ፍቅር ግን አልቀነሰም። ኢየሩሳሌም ከመድረሳቸው ከወራት በፊት ‘ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?’ በሚል ተከራክረው ነበር። እንዲሁም የማለፍ በዓልን ለማክበር ወደ ከተማዋ ከመግባታቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት ለሥልጣን የሚያደርጉት ሽኩቻ እንደገና ተቀስቅሶ ነበር። (ማርቆስ 9:​33-37፤ 10:​35-45) ለመጨረሻ ጊዜ አንድ ላይ ሆነው የሚያሳልፉትን የማለፍ በዓል ለማክበር በደርብ ላይ ወዳለው ክፍል ከገቡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከተከሰተው ሁኔታ ለመመልከት እንደሚቻለው ይህ ቀጣይ የሆነ ችግር ነበር። በዚያን ጊዜ የሌሎችን እግር በማጠብ ባሕላዊውን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ለማሳየት የሚያስችላቸውን አጋጣሚ አልተጠቀሙበትም። ኢየሱስ ስለ ትሕትና ሊያስተምራቸው በመፈለግ እግራቸውን አጠበላቸው።​—⁠ዮሐንስ 13:​2-15፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​9, 10

9. ኢየሱስ የመጨረሻውን የማለፍ በዓል ተከትሎ ለተከሰተው ሁኔታ እልባት የሰጠው እንዴት ነበር?

9 ይህ ትምህርት ቢሰጣቸውም የማለፍ በዓል ከተከበረና ኢየሱስ እየቀረበ ላለው ሞቱ የመታሰቢያ በዓል ካቋቋመ በኋላ ምን እንደ ተከሰተ ተመልከት። የሉቃስ ወንጌል ዘገባ “ደግሞም ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ” ይላል። ኢየሱስ በሐዋርያቱ ከመናደድ ብሎም ከመገሰጽ ይልቅ የሥልጣን ጥመኞች ከሆኑት ከዚህ ዓለም ገዥዎች የተለዩ መሆን እንዳለባቸው በደግነት መከራቸው። (ሉቃስ 22:24-27) ከዚያም ለክርስቶስ ሕግ የማዕዘን ድንጋይ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ነገር ተናገረ:- “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።”​—⁠ዮሐንስ 13:34

10. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ትእዛዝ ሰጥቷል? ይህስ ትእዛዝ ምንን ይጨምራል?

10 ኢየሱስ በዚያኑ ዕለት ምሽት የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር እስከ ምን ድረስ ሊሄድ እንደሚገባ ገልጿል። እንዲህ ብሏል:- “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” (ዮሐንስ 15:12, 13) ኢየሱስ ተከታዮቹ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለመሰል አማኞች ሲሉ ለመሞት ፈቃደኞች መሆን አለባቸው ማለቱ ነበርን? ኢየሱስ ይህን በተናገረበት ወቅት አብሮ የነበረው ዮሐንስ አባባሉን የተረዳው እንደዚያ መሆኑን ከጊዜ በኋላ ከጻፈው ነገር ለመመልከት ይቻላል:- “እርሱ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል።”​—⁠1 ዮሐንስ 3:16

11. (ሀ) የክርስቶስን ሕግ የምንፈጽመው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?

11 ስለዚህ ሌሎችን ስለ ኢየሱስ በማስተማር ብቻ የክርስቶስን ሕግ ማሟላት አይቻልም። የኢየሱስን የአኗኗር ዘይቤ ልንከተልና የእሱን ዓይነት ጠባይ ልናሳይ ይገባል። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ በንግግሮቹ ላይ ውብና የተመረጡ ቃላትን ተጠቅሟል። ይሁንና በምሳሌም አስተምሯል። ኢየሱስ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር የነበረ ቢሆንም አባቱን በምድር ላይ ለማገልገልና እንዴት መኖር እንዳለብን ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ ሲያገኝ ተጠቅሞበታል። ትሑት፣ ደግና አሳቢ የነበረ ሲሆን ሸክማቸው የከበዳቸውንና የተጨቆኑትን ይረዳ ነበር። (ማቴዎስ 11:​28-30፤ 20:​28፤ ፊልጵስዩስ 2:​5-8፤ 1 ዮሐንስ 3:​8) እንዲሁም ኢየሱስ እሱ እንደወደዳቸው ተከታዮቹ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ አሳስቧቸዋል።

12. የክርስቶስ ሕግ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር አይቀንሰውም ብሎ ለመናገር የሚቻለው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋን ውደድ የሚለው የሕጉ ፊተኛ ትእዛዝ በክርስቶስ ሕግ ውስጥ ምን ቦታ አለው? (ማቴዎስ 22:​37, 38፤ ገላትያ 6:​2) ሁለተኛ ደረጃ? በፍጹም! ለይሖዋና ለመሰል ክርስቲያኖች ያለን ፍቅር ፈጽሞ የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። አንድ ሰው ወንድሙን ሳይወድ ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር ሊኖረው እንደማይችል ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው ብሎ ከተናገረው ለመመልከት ይቻላል:- “ማንም:- እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?”​—⁠1 ዮሐንስ 4:20፤ ከ1 ዮሐንስ 3:​17, 18 ጋር አወዳድር።

13. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የሰጣቸውን አዲስ ትእዛዝ መታዘዛቸው ምን ውጤት አስገኝቶ ነበር?

13 ኢየሱስ እርሱ እንደወደዳቸው ተከታዮቹ እርስ በርስ እንዲዋደዱ የሰጣቸው አዲስ ትእዛዝ የሚያስገኘውን ውጤት ገልጿል። “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) ኢየሱስ ከሞተ ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ ይኖር የነበረው ተርቱሊያን የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች የነበራቸው የወንድማማች መዋደድ ይህን የመሰለ ውጤት ማስገኘቱን ተናግሯል። ተርቱሊያን ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮችን አስመልክተው ‘እንዴት እንደሚዋደዱና አንዳቸው ለሌላው ለመሞት እንኳን ዝግጁ እንደሆኑ ተመልከቱ’ ብለው ይናገሩ እንደነበር ጠቅሷል። ራሳችንን ‘የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኔን የሚያረጋግጠውን ይህን የመሰለውን ፍቅር ለመሰል ክርስቲያኖች አሳያለሁን?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

ፍቅራችንን የምናረጋግጥበት መንገድ

14, 15. የክርስቶስን ሕግ መታዘዝን ከባድ ሊያደርገው የሚችለው ምን ሊሆን ይችላል? ሆኖም እንዲህ እንድናደርግ ምን ሊረዳን ይችላል?

14 የይሖዋ አገልጋዮች የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር ማሳየታቸው የግድ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ የራስ ወዳድነት ባሕርይ ለሚታይባቸው መሰል ክርስቲያኖች ፍቅር ማሳየት ይከብድሃልን? ቀደም ሲል ሐዋርያቱ እንኳ ሳይቀሩ እንደ ተከራከሩና የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት እንደሞከሩ ተመልክተናል። (ማቴዎስ 20:​20-24) የገላትያ ሰዎችም በመካከላቸው ጥል ተነስቶ ነበር። ጳውሎስ ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ የሕግ ፍጻሜ መሆኑን ከገለጸ በኋላ “ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። ጳውሎስ የሥጋ ሥራዎችን ከመንፈስ ፍሬዎች ጋር ካነጻጸረ በኋላ “እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ” የሚለውን ማሳሰቢያ አክሏል። ከዚያም ሐዋርያው “እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ” ሲል አጥብቆ መክሯል።​—⁠ገላትያ 5:14-6:2

15 ይሖዋ የክርስቶስን ሕግ እንድንታዘዝ መጠየቁ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ነውን? በንግግራቸው ላቆሰሉንና ስሜታችንን ለጎዱን ሰዎች ደግነት ማሳየቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ‘እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን የምንመስል እንድንሆንና በፍቅር እንድንመላለስ’ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። (ኤፌሶን 5:1, 2) ‘ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ እንዲሞት በመላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳየንን’ አምላክ ምሳሌ በመከተል መቀጠል ይገባናል። (ሮሜ 5:8) የበደሉንን ጨምሮ ሌሎችን ለመርዳት ቅድሚያውን በመውሰድ አምላክን እየኮረጅንና የክርስቶስን ሕግ እየታዘዝን መሆናችንን በማወቅ እርካታ ልናገኝ እንችላለን።

16. ለአምላክና ለክርስቶስ ያለንን ፍቅር ልናረጋግጥ የምንችለው እንዴት ነው?

16 ፍቅር እንዳለን የምናረጋግጠው በምንናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን በምናደርገው ነገር ጭምር መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። ከጉዳዩ ክብደት የተነሣ በአንድ ወቅት ኢየሱስ እንኳ ለመቀበል የከበደው የአምላክ ፈቃድ ክፍል ነበር። ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ” ሲል ጸልዮአል። ነገር ግን ወዲያውኑ “የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ” ሲል አክሏል። (ሉቃስ 22:42) ኢየሱስ ብዙ ስቃይ ቢደርስበትም የአምላክን ፈቃድ ፈጽሟል። (ዕብራውያን 5:​7, 8) ታዛዥነት የፍቅራችን ማረጋገጫ ሲሆን የአምላክ መንገድ ከሁሉ የተሻለ መሆኑን መገንዘባችንን ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:3) ኢየሱስ ደግሞ ሐዋርያቱን “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” ብሎ ነግሯቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 14:15

17. ኢየሱስ ለተከታዮቹ የትኛውን ልዩ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል? በዛሬው ጊዜ በምንገኘውስ ላይ እንደሚሠራ እንዴት እናውቃለን?

17 ክርስቶስ ተከታዮቹ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ከማዘዝ በተጨማሪ ምን ልዩ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል? በሰጣቸው ስልጠና መሠረት የስብከቱን ሥራ እንዲሠሩ አዝዟቸዋል። ጴጥሮስ “ለሕዝብም እንድንሰብክና . . . እንመሰክር ዘንድ አዘዘን” ብሏል። (ሥራ 10:42) ኢየሱስ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ቀጥተኛ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሥራ 1:​8) ኢየሱስ እነዚህን የመሰሉት መመሪያዎች በዚህ ‘በፍጻሜ ዘመን’ በሚገኙ ተከታዮቹም ላይ እንደሚሠሩ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ዳንኤል 12:​4፤ ማቴዎስ 24:14) ምሥራቹን እንድንሰብክ የአምላክ ፈቃድ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ሆኖም አንዳንዶች አምላክ ይህን ሥራ እንድንሠራ መጠየቁ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ነው ብለው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም በእርግጥ ከአቅማችን በላይ ነውን?

አዳጋች መስሎ የሚታይበት ምክንያት

18. ይሖዋ የሚፈልግብንን ነገር በማድረጋችን ስቃይ ሲደርስብን ምንን ማስታወስ አለብን?

18 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በታሪክ ዘመናት በሙሉ ይሖዋ የተለያዩ መሥፈርቶችን በማውጣት ሰዎች እንዲያሟሏቸው ሲጠብቅባቸው ቆይቷል። እንዲያደርጉ የሚፈለግባቸው ነገር የተለያየ እንደነበር ሁሉ የደረሰባቸውም የፈተና ዓይነት የተለያየ ነበር። የአምላክ ውድ ልጅ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ፈተና ሥር ያለፈ ሲሆን አምላክ የሚፈልገውን በማድረጉም እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ተገድሏል። ይሖዋ የሚፈልግብንን ነገር በማድረጋችን ስቃይ ቢደርስብን ለደረሰብን መከራ በኃላፊነት የሚጠየቀው እሱ እንዳልሆነ ማስታወስ አለብን። (ዮሐንስ 15:​18-20፤ ያዕቆብ 1:​13-15) የሰይጣን ዓመፅ ኃጢአት፣ መከራና ሞት ያስከተለ ሲሆን ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚፈልገውን ነገር መፈጸምን አስቸጋሪ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን የሚፈጥረውም እሱ ራሱ ነው።​—⁠ኢዮብ 1:​6-19፤ 2:​1-8

19. አምላክ በልጁ በኩል ያዘዘንን ማድረጉ መብት የሆነው ለምንድን ነው?

19 ይሖዋ በልጁ በኩል በዚህ የፍጻሜ ዘመን የሚገኙ አገልጋዮቹ ለሰው ልጆች ስቃይና መከራ ብቸኛው መፍትሔ የመንግሥቱ አገዛዝ መሆኑን በምድር ዙሪያ እንዲያውጁ አመራር በመስጠት ላይ ይገኛል። ይህ የአምላክ መንግሥት ጦርነትን፣ ወንጀልን፣ ድህነትን፣ እርጅናን፣ በሽታንና ሞትን ጨምሮ በምድር ላይ ያሉትን ችግሮች በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል። በተጨማሪም መንግሥቱ ሙታን ሳይቀር የሚነሱባት ክብራማ የሆነች ገነታዊ ምድር ያስገኛል። (ማቴዎስ 6:​9, 10፤ ሉቃስ 23:​43፤ ሥራ 24:​15፤ ራእይ 21:​3, 4) እነዚህን ስለ መሳሰሉ ነገሮች የሚናገረውን ምሥራች ማወጅ እንዴት ያለ መብት ነው! ስለዚህ ይሖዋ እንድናደርግ የሚጠይቀን ነገር ምንም ችግር እንደሌለበት በግልጽ ለማየት ይቻላል። ተቃውሞ ሊያጋጥመን ቢችልም ተጠያቂዎቹ ሰይጣን ዲያብሎስና በቁጥጥሩ ሥር ያለው ዓለም ናቸው።

20. ዲያብሎስ የሚያመጣውን ማንኛውንም ፈተና ልንቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

20 ሰይጣን ዲያብሎስ የሚያመጣብንን ማንኛውንም ፈተና በተሳካ ሁኔታ መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” የሚሉትን ቃላት በማስታወስ ነው። (ምሳሌ 27:​11) ኢየሱስ ደህንነት ያለበትን ሰማያዊ ሕይወት ትቶ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ወደዚች ምድር በመምጣት ይሖዋ ለሰይጣን ስድብ ምላሽ እንዲሰጥ አስችሎታል። (ኢሳይያስ 53:​12፤ ዕብራውያን 10:​7) ኢየሱስ ሰው በነበረበት ጊዜ ያጋጠመውን ማንኛውንም ፈተና፣ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቃይቶ መሞትን እንኳ ሳይቀር በጽናት አልፏል። ኢየሱስን ምሳሌያችን አድርገን ከተከተልነው በመከራ ልንጸናና ይሖዋ የሚፈልግብንን ነገር ልናደርግ እንችላለን።​—⁠ዕብራውያን 12:​1-3

21. ይሖዋና ልጁ ስላሳዩህ ፍቅር ምን ይሰማሃል?

21 አምላክና ልጁ የላቀ ፍቅር አሳይተውናል። በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ታዛዥ የሰው ልጆች በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሊኖራቸው ችሏል። ስለዚህ ተስፋችንን ምንም ነገር እንዲያጨልምብን አንፍቀድ። ከዚያ ይልቅ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ስለ ወደደኝ ለእኔ ራሱን አሳልፎ ሰጠ’ ሲል እንደ ተናገረው እንደ ጳውሎስ ኢየሱስ ላስገኘልን መብት በግለሰብ ደረጃ ልባዊ አድናቆት ይኑረን። (ገላትያ 2:20 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እንዲሁም ፈጽሞ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ለማይጠብቅብን ለአፍቃሪው አምላካችን ለይሖዋ ልባዊ አመስጋኝነታችንን የምናሳይ እንሁን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ዛሬ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

◻ ክርስቶስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ የፍቅርን አስፈላጊነት ያጎላው እንዴት ነበር?

◻ አምላክን እንደምንወድድ እንዴት ልናረጋግጥ እንችላለን?

◻ ይሖዋ የሚፈልግብንን ነገር ማድረጉ መብት የሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ምን ትምህርት ሰጥቷል?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተቃውሞ ቢያጋጥመንም ምሥራቹን ለሌሎች ማካፈሉ አስደሳች መብት ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ