የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ገለልተኛ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • ምዕራፍ 45. አንዲት እህት ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር አክብሮት በሚያሳይ መንገድ ቆማ፤ ሆኖም እንደ ሌሎቹ ተማሪዎች ብሔራዊ መዝሙር አልዘመረችም ወይም እጇን ደረቷ ላይ አላደረገችም

      ምዕራፍ 45

      ገለልተኛ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?

      ኢየሱስ ተከታዮቹ “የዓለም ክፍል” መሆን እንደሌለባቸው አስተምሯል። (ዮሐንስ 15:19) ይህም ገለልተኛ መሆንን ማለትም በዓለም የፖለቲካ ጉዳዮችና ጦርነቶች ላይ የትኛውንም ወገን አለመደገፍን ይጨምራል። እንደ እውነቱ ከሆነ ገለልተኛ መሆን ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። በዚህ አቋማችን ምክንያት ሰዎች ሊያሾፉብን ይችላሉ። ታዲያ ምንጊዜም ገለልተኛ በመሆን ለይሖዋ አምላክ ታማኝ እንደሆንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      1. እውነተኛ ክርስቲያኖች ለዓለም መንግሥታት ምን አመለካከት አላቸው?

      ክርስቲያኖች መንግሥትን ያከብራሉ። ኢየሱስ እንዳለው ‘የቄሳር የሆነውን ለቄሳር ለመስጠት’ ማለትም የአገሪቱን ሕጎች ለመታዘዝ ጥረት እናደርጋለን፤ ለምሳሌ ቀረጥ እንድንከፍል የሚያዝዙ ሕጎችን እንጠብቃለን። (ማርቆስ 12:17) መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም መንግሥታት እየገዙ ያሉት ይሖዋ እንዲገዙ ስለፈቀደላቸው እንደሆነ ያስተምራል። (ሮም 13:1) በመሆኑም መንግሥታት ያላቸው ሥልጣን ከአምላክ አንጻር ሲታይ አነስተኛ ወይም የተገደበ መሆኑን እንገነዘባለን። የሰው ልጆችን ችግሮች መፍታት የሚችለው አምላክና እሱ በሰማይ ያቋቋመው መንግሥት ብቻ እንደሆነ እናምናለን።

      2. ገለልተኛ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ፖለቲካ ውስጥ አንገባም። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ሕዝቡ እሱ የፈጸመውን ተአምር አይተው ሊያነግሡት በሞከሩ ጊዜ ፈቃደኛ አልሆነም። (ዮሐንስ 6:15) ለምን? ምክንያቱም በኋላ ላይ እንደተናገረው ‘መንግሥቱ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም።’ (ዮሐንስ 18:36) እኛም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ገለልተኛ መሆናችንን በተለያዩ መንገዶች እናሳያለን። ለምሳሌ ያህል፣ በጦርነት አንካፈልም። (ሚክያስ 4:3⁠ን አንብብ።) እንደ ባንዲራ ያሉ ብሔራዊ ዓርማዎችን የምናከብር ቢሆንም ለአምላክ የምንሰጠውን ዓይነት ክብር አንሰጣቸውም። (1 ዮሐንስ 5:21) በተጨማሪም የትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የፓርቲውን ዕጩ አንደግፍም ወይም አንቃወምም። በእነዚህና በሌሎች መንገዶች ለአምላክ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ታማኝ እንደሆንን እናሳያለን።

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      የገለልተኝነት አቋምን ሊፈትኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን እንመለከታለን፤ በተጨማሪም ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

      የገለልተኝነት አቋሙን የጠበቀ አንድ ሰው። ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ለሕዝቡ ለሚሰጡት ንግግር ምንም ትኩረት አይሰጥም

      3. እውነተኛ ክርስቲያኖች ገለልተኞች ናቸው

      ኢየሱስና ተከታዮቹ ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል። ሮም 13:1, 5-7⁠ን እንዲሁም 1 ጴጥሮስ 2:13, 14⁠ን አንብቡ። ከዚያም ቪዲዮውን ተመልከቱና በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ እውነተኛ ክርስቲያኖች ገለልተኞች ናቸው—ክፍል 1 (4:28)

      • ባለሥልጣናትን ልናከብር የሚገባው ለምንድን ነው?

      • ለእነሱ እንደምንገዛ ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

      በጦርነት ወቅት አንዳንድ አገሮች፣ ሁለቱንም ወገኖች እየደገፉ ገለልተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ። በእርግጥ ገለልተኛ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ዮሐንስ 17:16⁠ን አንብቡ። ከዚያም ቪዲዮውን ተመልከቱና በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ እውነተኛ ክርስቲያኖች ገለልተኞች ናቸው—ክፍል 2 (3:11)

      • ገለልተኛ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?

      ባለሥልጣናት ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጭ ነገር እንድናደርግ ቢጠይቁንስ? የሐዋርያት ሥራ 5:28, 29⁠ን አንብቡ። ከዚያም ቪዲዮውን ተመልከቱና በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ እውነተኛ ክርስቲያኖች ገለልተኞች ናቸው—ክፍል 3 (1:18)

      • ሰዎች ያወጡት ሕግ ከአምላክ ሕግ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ የትኛውን ሕግ ልንታዘዝ ይገባል?

      • ክርስቲያኖች ለባለሥልጣናት የማይታዘዙባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች መጥቀስ ትችላለህ?

      4. በሐሳብም ሆነ በድርጊት ገለልተኛ ሁን

      አንደኛ ዮሐንስ 5:21⁠ን አንብቡ። ከዚያም ቪዲዮውን ተመልከቱና በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ እውነተኛ ክርስቲያኖች ድፍረት ያስፈልጋቸዋል—የገለልተኝነት አቋም ለመጠበቅ (2:49)

      • በቪዲዮው ላይ አዬንጌ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ላለመሆን እንዲሁም ለባንዲራ ሰላምታ እንደመስጠት ባሉ ብሔራዊ ሥነ ሥርዓቶች ላለመካፈል የወሰነው ለምንድን ነው?

      • ያደረገው ውሳኔ ትክክል ይመስልሃል?

      የገለልተኝነት አቋማችንን ሊፈትኑ የሚችሉ ሌሎች ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ ከመጠበቂያ ግንብ የምናገኛቸው ትምህርቶች—በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የገለልተኝነት አቋማችሁን ጠብቁ (5:16)

      • የተለያዩ አገሮች የሚሳተፉበትን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስንመለከት ገለልተኝነታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

      • ፖለቲከኞች የሚያደርጉት ውሳኔ እኛን የሚነካን በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ገለልተኝነታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

      • የዜና ዘገባዎች ወይም አብረውን ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች በገለልተኝነት አቋማችን ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ?

      1. ምልክቶች ይዘው የተቃውሞ ሰልፍ የወጡ የተበሳጩ ሰዎች 2. በስፖርት ውድድር ላይ ባንዲራ ይዞ ድጋፉን እየገለጸ ያለ ሰው 3. አንድ ተማሪ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘምር 4. የጦር መሣሪያ የያዘ ወታደር 5. ሁለት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ሲከራከሩ 6. አንዲት ሴት ስትመርጥ

      ክርስቲያኖች በአስተሳሰብም ሆነ በድርጊት ገለልተኝነታቸውን መጠበቅ የሚኖርባቸው በየትኞቹ ሁኔታዎች ሥር ነው?

      አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “ለባንዲራ ሰላምታ የማትሰጠው ወይም ብሔራዊ መዝሙር የማትዘምረው ለምንድን ነው?”

      • ምን ብለህ ትመልሳለህ?

      ማጠቃለያ

      ክርስቲያኖች በሐሳባቸው፣ በንግግራቸውና በድርጊታቸው ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

      ክለሳ

      • ለመንግሥታት ምን የማድረግ ግዴታ አለብን?

      • ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

      • የገለልተኝነት አቋማችንን ሊፈትኑ የሚችሉ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      የገለልተኝነት አቋማችንን ለመጠበቅ ስንል ምን መሥዋዕትነት መክፈል ሊያስፈልገን ይችላል?

      ይሖዋ ፈጽሞ አላሳፈረንም (3:14)

      ቤተሰቦች ገለልተኝነታቸውን ለሚፈትኑ ሁኔታዎች አስቀድመው መዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?

      በሕዝባዊ ዝግጅቶች ወቅት የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ (4:25)

      ለአገር ከመዋጋት በላይ ክብር የሚያስገኝ ነገር አለ የምንለው ለምንድን ነው?

      “በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” (5:19)

      ከሥራ ምርጫ ጋር የተያያዘ ውሳኔ ስታደርግ የዓለም ክፍል እንዳልሆንክ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

      “እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋል” (መጠበቂያ ግንብ መጋቢት 15, 2006)

  • ስደትን በጽናት መቋቋም ትችላለህ
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች ተቃውሞ አልፎ ተርፎም ስደት ያጋጥማቸዋል። ታዲያ ይህ ሊያስደነግጠን ይገባል?

      1. ስደት እንደሚደርስብን የምንጠብቀው ለምንድን ነው?

      መጽሐፍ ቅዱስ “የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ኢየሱስ የሰይጣን ዓለም ክፍል ስላልነበር ስደት ደርሶበታል። እኛም የዓለም ክፍል ስላልሆንን መንግሥታትና የሃይማኖት ድርጅቶች ስደት ቢያደርሱብን አይገርመንም።—ዮሐንስ 15:18, 19

      2. ለስደት አስቀድመን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

      ከወዲሁ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ያስፈልገናል። በየዕለቱ ወደ ይሖዋ የምትጸልይበትና ቃሉን የምታነብበት ጊዜ መድብ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ተገኝ። እነዚህን ነገሮች ማድረግህ የቤተሰብ ተቃውሞን ጨምሮ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ዓይነት ስደት በድፍረት ለመቋቋም ብርታት ይሰጥሃል። በተደጋጋሚ ስደት የደረሰበት ሐዋርያው ጳውሎስ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 13:6

      አዘውትረን መስበካችንም ድፍረት ለማዳበር ይረዳናል። የስብከቱ ሥራ በይሖዋ እንድንታመንና የሰው ፍርሃትን እንድናሸንፍ ያሠለጥነናል። (ምሳሌ 29:25) ለመስበክ የሚያስፈልግህን ድፍረት ከወዲሁ ካዳበርክ መንግሥት በሥራችን ላይ እገዳ በሚጥልበት ጊዜም መስበክህን ለመቀጠል ዝግጁ ትሆናለህ።—1 ተሰሎንቄ 2:2

      3. ስደትን በጽናት መቋቋማችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

      እርግጥ ነው፣ ስደት በራሱ የሚያስደስት ነገር አይደለም፤ ሆኖም ስደትን በተሳካ ሁኔታ ስንወጣ እምነታችን ይበልጥ ይጠናከራል። ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነ በሚሰማን ጊዜ የይሖዋን እርዳታ ማየት ስለምንችል ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን። (ያዕቆብ 1:2-4⁠ን አንብብ።) ይሖዋ መከራ ሲደርስብን ሲያይ የሚያዝን ቢሆንም በጽናት መወጣታችን ያስደስተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ነገር በማድረጋችሁ መከራ ሲደርስባችሁ ችላችሁ ብታሳልፉ . . . ይህ አምላክ ደስ የሚሰኝበት ነገር ነው” ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:20) ይሖዋ በታማኝነት የሚጸኑ አገልጋዮቹን በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ በማድረግ ይክሳቸዋል፤ በዚያን ጊዜ እውነተኛውን አምልኮ የሚቃወም ማንም አይኖርም።—ማቴዎስ 24:13

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      ስደት ቢደርስብህም ለይሖዋ ታማኝ መሆን ትችላለህ የምንልበትን ምክንያትና እንዲህ ማድረግህ የሚያስገኝልህን በረከት እንመለከታለን።

      ወላጆቿ ቢቃወሟትም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እየሄደች ያለች ሴት

      4. ከቤተሰብህ የሚደርስብህን ተቃውሞ መቋቋም ትችላለህ

      ኢየሱስ በግልጽ እንደተናገረው ቤተሰባችን ይሖዋን ለማገልገል ያደረግነውን ውሳኔ ሊቃወም ይችላል። ማቴዎስ 10:34-36⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • አንድ ሰው ይሖዋን ለማገልገል ሲወስን ከቤተሰቡ ምን ሊያጋጥመው ይችላል?

      ምሳሌ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ ይሖዋ ተቀብሎናል (5:13)

      • የቤተሰብህ አባል ወይም ጓደኛህ ይሖዋን ለማገልገል ያደረግከውን ውሳኔ ቢቃወም ምን ታደርጋለህ?

      መዝሙር 27:10⁠ን እና ማርቆስ 10:29, 30⁠ን አንብቡ፤ እያንዳንዱን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ከቤተሰቦችህ ወይም ከጓደኞችህ ተቃውሞ ሲያጋጥምህ የሚረዳህ እንዴት ነው?

      5. ስደት ቢኖርም ይሖዋን ማገልገልህን ቀጥል

      ተቃውሞ እያለም ይሖዋን ማገልገል ድፍረት ይጠይቃል። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ ስደትን በድፍረት መቋቋም (6:27)

      • በዚህ ቪዲዮ ላይ ከተጠቀሱት ወንድሞችና እህቶች ምሳሌ ምን ማበረታቻ አግኝተሃል?

      የሐዋርያት ሥራ 5:27-29⁠ን እና ዕብራውያን 10:24, 25⁠ን አንብቡ። እያንዳንዱን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • በስብከቱ ሥራችን ወይም በስብሰባዎቻችን ላይ እገዳ ቢጣልም እንኳ በእነዚህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላችንን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      6. ይሖዋ መጽናት እንድትችል ይረዳሃል

      በዓለም ዙሪያ ያሉ በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስደት ቢደርስባቸውም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ምን እንደረዳቸው ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ። ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ ይሖዋ አምላክ ብርታት ይሰጠኛል (3:40)

      • በቪዲዮው ላይ የታዩትን ወንድሞችና እህቶች እንዲጸኑ የረዳቸው ምንድን ነው?

      ሮም 8:35, 37-39⁠ን እንዲሁም ፊልጵስዩስ 4:13⁠ን አንብቡ። እያንዳንዱን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ይህ ጥቅስ ማንኛውንም ፈተና በጽናት መቋቋም እንደምትችል እርግጠኛ እንድትሆን የሚረዳህ እንዴት ነው?

      ማቴዎስ 5:10-12⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ስደት ቢደርስብህም ደስተኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

      በእምነታቸው ምክንያት ስደት የደረሰባቸውና የታሰሩ በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች

      በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች ተቃውሞን በጽናት ተቋቁመዋል። አንተም መቋቋም ትችላለህ!

      አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ስደትን መቋቋም ይከብደኛል።”

      • እነዚህ ሰዎች ስደትን በጽናት መቋቋም እንደሚችሉ እርግጠኛ እንዲሆኑ ለመርዳት የትኞቹን ጥቅሶች ልትጠቀም ትችላለህ?

      ማጠቃለያ

      ይሖዋ ስደትን ተቋቁመን እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። በእሱ እርዳታ ጸንተን መቀጠል እንችላለን!

      ክለሳ

      • ክርስቲያኖች ስደት እንደሚደርስባቸው መጠበቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?

      • ከወዲሁ ራስህን ለስደት ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

      • ማንኛውም ፈተና ቢያጋጥምህ ይሖዋን ማገልገልህን መቀጠል እንደምትችል እርግጠኛ እንድትሆን የሚረዳህ ምንድን ነው?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      አንድ ወጣት ወንድም ገለልተኛ በመሆኑ ምክንያት በታሰረበት ወቅት ይሖዋ የረዳው እንዴት ነው?

      ስደትን በጽናት መቋቋም (2:34)

      አንድ ባልና ሚስት ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት እንዲያገለግሉ የረዳቸው ምንድን ነው?

      የተለያዩ ለውጦች ቢያጋጥሙም ይሖዋን ማገልገል (7:11)

      ስደትን በድፍረት መጋፈጥ የምትችለው እንዴት ነው?

      “ከአሁኑ ለስደት ተዘጋጁ” (መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 2019)

      ከቤተሰብ ለሚደርስብን ተቃውሞ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ መወጣት የምንችለውስ እንዴት ነው?

      “ሰላምን ሳይሆን ሰይፍን የሚያመጣው እውነት” (መጠበቂያ ግንብ ጥቅምት 2017)

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ