የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
‘የዓለም ክፍል አለመሆን’ሲባል ምን ማለት ነው?
በአራተኛው መቶ ዘመን በሺህ የሚቆጠሩ ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ ሰዎች ንብረታቸውን፣ ዘመዶቻቸውንና የቀድሞ ኑሯቸውን ትተው ከሰው ተለይተው ለመኖር ወደ ግብጽ ምድረ በዳዎች ሄዱ። እነዚህ ሰዎች አንኮራውያን ተብለው መጠራት ጀመሩ። ይህ ስያሜ የተገኘው “ራሴን አገለልኩ” የሚል ትርጉም ካለው አናኮርዮ ከተባለ የግሪክኛ ቃል ነው። ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች አግልለው ይኖሩ እንደነበረ አንድ ታሪክ ፀሐፊ ገልጿል። አንኮራውያን ራሳቸውን ከኅብረተሰቡ በማግለላቸው ‘የዓለም ክፍል አትሁኑ’ የሚለውን የክርስትና ትእዛዝ የፈጸሙ ይመስላቸው ነበር።—ዮሐንስ 15:19
መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ‘ከዓለም እድፍ እንዲጠብቁ’ ያዛል። (ያዕቆብ 1:27) ቅዱሳን ጽሑፎች “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” በማለት ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ። (ያዕቆብ 4:4) ታዲያ እንዲህ ሲባል ክርስቲያኖች ልክ እንደ አንኮራውያን ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች ማግለል ይኖርባቸዋል ማለት ነውን? ሃይማኖታዊ እምነታቸውን ከማይጋሩ ሰዎች ተለይተው መኖር አለባቸውን?
ክርስቲያኖች ፀረ ኅብረተሰብ አይደሉም
የዓለም ክፍል ያለመሆን ጽንሰ ሐሳብ ክርስቲያኖች ከአምላክ ከራቀው አጠቃላይ ማኅበረሰብ መለየት እንደሚገባቸው በሚያመለክቱ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ተብራርቷል። (ከ2 ቆሮንቶስ 6:14-17፤ ኤፌሶን 4:18፤ 2 ጴጥሮስ 2:20 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሀብትን፣ ዝናን፣ ተድላንና ፈንጠዝያን እንደማሳደድ ካሉት ከይሖዋ የጽድቅ መንገዶች ጋር የሚጋጩ ዝንባሌዎች፣ አነጋገሮችና ጠባዮች ይርቃሉ። (1 ዮሐንስ 2:15-17) በተጨማሪም ከጦርነትና ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆን ከዓለም ተለይተው ይኖራሉ።
ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ‘የዓለም ክፍል’ እንደማይሆኑ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ወደ አምላክ ሲጸልይ “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:14-16) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ፈጽሞ ከመገናኘት በመቆጠብ ፀረ ኅብረተሰቦች እንዲሆኑ እንዳልፈለገ ግልጽ ነው። እንዲያውም አንድ ክርስቲያን ራሱን ከሰዎች ቢያገል ‘በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት’ እንዲሰብክና እንዲያስተምር የተሰጠውን የሥራ ግዴታ መፈጸም አይችልም።—ሥራ 20:20፤ ማቴዎስ 5:16፤ 1 ቆሮንቶስ 5:9, 10
ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከዓለም እድፍ እንዲጠብቁ የተሰጣቸው ምክር ራሳቸውን ከሌሎች እንደሚበልጡ አድርገው እንዲመለከቱ ምክንያት አይሆናቸውም። ይሖዋን የሚወዱ ሁሉ ‘ራስን ከፍ ከፍ ማድረግን’ አጥብቀው ይጠላሉ። (ምሳሌ 8:13) ገላትያ 6:3 “አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል” ይላል። ራሳቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሁሉ ራሳቸውን ያታልላሉ። ምክንያቱም “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል።”—ሮሜ 3:23
‘ስለ ማንም ክፉ አትናገሩ’
በኢየሱስ ዘመን የሃይማኖታዊ ቡድኖቻቸው አባል ያልሆኑ ሰዎችን በሙሉ በንቀት የሚመለከቱ ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ፈሪሳውያን ይገኛሉ። ፈሪሳውያን የሙሴን ሕግና የወጋቸውን ዝርዝር ትእዛዛት ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። (ማቴዎስ 15:1, 2፤ 23:2) በርካታ የሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በጥንቃቄ በማከናወናቸው ይኩራሩ ነበር። ባገኙት እውቀትና ሃይማኖታዊ ማዕረግ የተነሣ ከሌሎች የበለጡ እንደሆኑ ይሰማቸው ነበር። “ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው” ሲሉ የነበራቸውን የግብዝነትና የንቀት ዝንባሌ ገልጸዋል።—ዮሐንስ 7:49
እንዲያውም ፈሪሳውያን ያልሆኑ ሰዎችን የሚጠሩበት የንቀት ስያሜ ነበራቸው። አምሃሬትስ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ተራዎቹን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያመለክት የንቀት ወይም የውርደት ትርጉም የሌለው ቃል ነበር። በኋላ ግን እብሪተኞቹ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች አምሃሬትስ የሚለውን ቃል ትርጉም ለውጠው የስድብ ቃል አድርገውታል። ሌሎች ቡድኖችም፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሳይቀሩ፣ ከራሳቸው የተለየ እምነት ያላቸውን ሰዎች “አረመኔ” የሚለውን በመሰሉ የንቀት ስሞች ይጠራሉ።
ይሁን እንጂ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ክርስትናን ያልተቀበሉ ሰዎችን እንዴት ይመለከቱ ነበር? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማያምኑ ሰዎችን “በየዋህነት” እንዲይዙና ‘በጥልቅ እንዲያከብሩ’ ተመክረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:25፤ 1 ጴጥሮስ 3:15) በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ሰዎች በቀላሉ የሚቀርቡት ሰው ነበር እንጂ እብሪተኛ አልነበረም። ራሱን ከሌሎች አስበልጦ የሚመለከት ሳይሆን ትሑትና ሌሎችን የሚያንጽ ሰው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:22, 23) ጳውሎስ በመንፈስ ተነድቶ ለቲቶ በጻፈው መልእክት ላይ ክርስቲያኖች “ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ” መክሯል።—ቲቶ 3:2 የ1980 ትርጉም
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የማያምኑ” የሚለው ቃል ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችን ለማመልከት የተሠራበት ጊዜ አለ። ቢሆንም “የማያምኑ” የሚለው ቃል አንድን የተወሰነ ወገን የሚያመለክት ስያሜ ሆኖ ያገለገለበት ጊዜ የለም። ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችን ለማዋረድ ወይም ለማጥላላት ተሠርቶበት እንደማያውቅ የተረጋገጠ ነው። ምክንያቱም ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይጻረራል። (ምሳሌ 24:9) በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች ለማያምኑ ሰዎች የጥላቻ ወይም የንቀት ዝንባሌ አያሳዩም። ምሥክር ያልሆኑ ዘመዶቻቸውን ወይም ጎረቤቶቻቸውን በሚያናንቁ ወይም በሚያጥላሉ ስያሜዎች መጥራትን እንደ ብልግና ይቆጥራሉ። “የጌታ ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር” መሆን ያስፈልገዋል የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ።—2 ጢሞቴዎስ 2:24
“ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ”
ከዓለም ጋር፣ በተለይም ለአምላካዊ የሥነ ምግባር ደንቦች ከፍተኛ ንቀት ካላቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ እጅግ አደገኛ መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው። (ከ1 ቆሮንቶስ 15:33 ጋር አወዳድር።) ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ” ብሎ ሲመክር “ሁሉ” የሚለው ቃል ክርስቲያናዊ እምነቶችን የማይጋሩ ሰዎችን ይጨምራል። (ገላትያ 6:10) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከማያምኑ ሰዎች ጋር በአንድ ገበታ የተመገቡባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ግልጽ ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:27) ስለዚህ ዛሬም ቢሆን ክርስቲያኖች የማያምኑ ሰዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መልካም ነገር ያደርጉላቸዋል።—ማቴዎስ 22:39
አንድን ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ስለማያውቅ ብቻ ሥነ ምግባር እንደጎደለው ወይም ጨዋ እንዳልሆነ መቁጠር ትክክል አይደለም። ሰዎችና ሁኔታዎች ይለያያሉ። በዚህ የተነሣ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከማያምኑ ሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት እስከምን ደረጃ መሆን እንዳለበት ራሱ መወሰን ይኖርበታል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን አንኮራውያን እንዳደረጉት ራሱን ከሌሎች ማግለሉ ወይም እንደ ፈሪሳውያን ራሱን ከሌሎች አስበልጦ መመልከቱ አስፈላጊም፣ ቅዱስ ጽሑፋዊም አይሆንም።