-
ይሖዋ ረዳታችን ነውመጠበቂያ ግንብ—2004 | ታኅሣሥ 15
-
-
20, 21. ሐዋርያው ጳውሎስ ከሮም በመጡ ወንድሞች የተጽናናው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር?
20 በተለይ ደግሞ የይሖዋ አገልጋዮች አንዳቸው ሌላውን ለማበረታታትና ለማጽናናት ስላደረጉት ጥረት የሚያወሱ ዘገባዎች ልብ የሚነኩ ናቸው። ከሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወት ጋር የተያያዘ አንድ ምሳሌ ተመልከት። ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም እያመራ በነበረበት ወቅት የአፍያን መንገድ ተብሎ በሚታወቀው የሮማውያን አውራ ጎዳና ላይ ተጉዞ ነበር። የጉዞው የመጨረሻ ክፍል ረግረጋማ በሆነ ረባዳ መሬት ላይ መጓዝ ስለሚጠይቅ አስቸጋሪ ነበር።a የሮም ጉባኤ ወንድሞች ጳውሎስ ወደዚያ እየመጣ መሆኑን ሰምተው ነበር። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን? በሞቀ ቤታቸው ቁጭ ብለው የጳውሎስን ወደ ሮም መምጣት ይጠባበቁ ይሆን?
21 ከጳውሎስ ጋር አብሮ ተጉዞ የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው ሉቃስ “በዚያ [በሮም] የነበሩ ወንድሞችም መምጣታችንን ስለሰሙ፣ እስከ አፍዩስ ፋሩስ፣ እንዲሁም ‘ሦስት ማደሪያ’ እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን ወጡ” በማለት የነበረውን ሁኔታ ገልጾልናል። ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ማየት ትችላለህ? በሮም የሚኖሩ በርካታ ወንድሞች ጳውሎስ እየመጣ መሆኑን ሰምተው ስለነበር እርሱን ለመቀበል ተጉዘዋል። ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ ከሮም 74 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአፍዩስ ገበያ የሚባለው የታወቀ ጣቢያ ድረስ መጥተው የጠበቁት ሲሆን የቀሩት ደግሞ ከከተማዋ 58 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሦስት ማደሪያ የሚባለው ጣቢያ ድረስ መጥተዋል። ጳውሎስ ሲያያቸው ምን ተሰማው? ሉቃስ “ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም” በማለት ዘግቧል። (የሐዋርያት ሥራ 28:15) እስቲ አስበው፣ ጳውሎስ ያንን ሁሉ መንገድ ተጉዘው የመጡትን ወንድሞች ማየቱ በራሱ እንዲበረታታና እንዲጽናና አስችሎታል! ጳውሎስ እንዲህ የመሰለ ድጋፍ በማግኘቱ ያመሰገነው ማንን ነበር? የመጽናኛው ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ነበር።
-
-
ይሖዋ ረዳታችን ነውመጠበቂያ ግንብ—2004 | ታኅሣሥ 15
-
-
a ተመሳሳይ ጉዞ አድርጎ የነበረው ሮማዊው ባለቅኔ ሆራስ (65-68 ከክርስቶስ ልደት በፊት) መንገዱ አስቸጋሪ መሆኑን ጽፏል። ሆራስ፣ አፍዩስ የሚባለው የገበያ ቦታ “በመርከበኞችና ስግብግብ በሆኑ ባለ መጠጥ ቤቶች የተጨናነቀ” እንደሆነ ገልጿል። “አስቸጋሪ ስለሆኑት ትንኞችና እንቁራሪቶች” እንዲሁም “ጣዕሙ ደስ ስለማይለው” ውኃ አማርሮ ተናግሯል።
-