የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 44—የሐዋርያት ሥራ
ጸሐፊው:- ሉቃስ
የተጻፈበት ቦታ:- ሮም
ተጽፎ ያለቀው:- በ61 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ33–61 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ሉቃስ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው 42ኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ኢየሱስ እስካረገበት ጊዜ ድረስ ያለውን የኢየሱስን እንዲሁም የተከታዮቹን ሕይወት፣ ያከናወኗቸውን ተግባራትና አገልግሎታቸውን የሚዳስስ ዘገባ አቅርቧል። የሐዋርያት ሥራ በመባል የሚታወቀው 44ኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ጉባኤ ስለመቋቋሙ በመተረክ የጥንቱን ክርስትና ቀጣይ ታሪክ ይዘግባል። ከዚህም በተጨማሪ የምሥክርነቱ ሥራ መጀመሪያ በአይሁዳውያን ከዚያም በአሕዛብ መካከል እንዴት እንደተስፋፋ ይገልጻል። በመጀመሪያዎቹ 12 ምዕራፎች ውስጥ ያለው አብዛኛው ክፍል የጴጥሮስን እንቅስቃሴ፣ የቀሩት 16 ምዕራፎች ደግሞ ጳውሎስ ያከናወናቸውን ተግባራት የሚዳስሱ ናቸው። ሉቃስ፣ ከጳውሎስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለነበረው ሐዋርያው ባደረጋቸው በርካታ ጉዞዎች አብሮት ነበር።
2 መጽሐፉ የተጻፈው ለቴዎፍሎስ ነው። ቴዎፍሎስ “ክቡር” ተብሎ መጠራቱ የኃላፊነት ቦታ እንደነበረው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ይህ ቃል አክብሮትን ለመግለጽ የገባ ይሆናል። (ሉቃስ 1:3) መጽሐፉ የክርስቲያን ጉባኤን መቋቋምና እድገት በሚመለከት ትክክለኛ የሆነ ታሪካዊ ዘገባ ያቀርባል። ዘገባው፣ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እንደተገለጠላቸው በመተረክ ይጀምርና ከ33 እስከ 61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ድረስ ባሉት 28 የሚያህሉ ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙትን ጉልህ ክንውኖች ይዘግባል።
3 ከጥንትም ጀምሮ የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ የጻፈው የሉቃስ ወንጌል ጸሐፊ እንደሆነ ይታመናል። ሁለቱም መጻሕፍት የተጻፉት ለቴዎፍሎስ ነው። ሉቃስ፣ በወንጌሉ መደምደሚያ ላይ የገለጻቸውን ክንውኖች በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ ደግሞ ማውሳቱ ሁለቱም መጻሕፍት የአንድ ጸሐፊ ሥራዎች መሆናቸውን ያሳያል። ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ያጠናቀቀው ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በሮም ያደረገው የሁለት ዓመት ቆይታ ሊያበቃ አካባቢ በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሳይሆን አይቀርም። መጽሐፉ እስከዚህ ዓመት ድረስ የተከናወኑትን ነገሮች ስለሚያወሳ ከዚያ በፊት ሊጠናቀቅ አይችልም፤ እንዲሁም ጳውሎስ ለቄሣር ያቀረበው ይግባኝ ምን እንደደረሰ ሳይጠቅስ መደምደሙ በዚያ ዓመት እንደተጠናቀቀ ይጠቁማል።
4 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑ ከጥንትም ጀምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ነገር ነው። አሁን ካሉት አንዳንድ በፓፒረስ የተዘጋጁ ጥንታዊ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተወሰኑ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በሦስተኛው ወይም በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተዘጋጀው ሚቺጋን ቁጥር 1571 (P38) እንዲሁም በሦስተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀው ቼስተር ቤቲ ቁጥር 1 (P45) የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ ሁለቱም ጥንታዊ ጽሑፎች የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ሌሎች ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ይሠራጭ እንደነበረና ጥንትም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ተካትቶ እንደነበር ይጠቁማሉ። ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ያሰፈረው ዘገባ በወንጌሉ ውስጥ በጉልህ ያየነውን ዓይነት ፍጹም ትክክለኛነት የተንጸባረቀበት ነው። ሰር ዊልያም ራምሴይ የሐዋርያት ሥራን ጸሐፊ “ከታላላቅ ታሪክ ጸሐፊዎች መካከል” የመደቡት ሲሆን ይህን አባባላቸውን ሲያብራሩም እንዲህ ብለዋል:- “ከታላላቅ ታሪክ ጸሐፊዎች የሚፈለገው ተቀዳሚና አቢይ ብቃት እውነተኝነት ነው። ታሪክ ጸሐፊው የሚናገረው ነገር እምነት የሚጣልበት ሊሆን ይገባል።”a
5 ሉቃስ በጻፋቸው መጻሕፍት ውስጥ የተንጸባረቀውን ትክክለኛነት በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሜድትራኒያን ባሕር ላይ የነበሩት የብሪታንያ የጦር መርከቦች አዛዥ ሆነው ያገለገሉት ኤድዊን ስሚዝ፣ መጋቢት 1947 በታተመው ዘ ረደር በተባለው መጽሔት ላይ ያሰፈሩትን ሐሳብ መጥቀስ ይቻላል:- “የጥንቶቹ መርከቦች የሚንቀሳቀሱት በመርከቢቱ የኋላ ክፍል በሁለቱም ወገን በሚገኙ ሁለት ትላልቅ መቅዘፊያዎች እንጂ እንደ ዘመናዊዎቹ መርከቦች በኋለኛው ክፍል ላይ በሚገኝ አንድ መቅዘፊያ አልነበረም፤ ቅዱስ ሉቃስ፣ መቅዘፊያዎቹን ሲጠቅስ ብዙ ቁጥር የተጠቀመው በዚህ ምክንያት ነው። [ሥራ 27:40 የ1879 ትርጉም] . . . ይህቺ መርከብ፣ መልካም ወደብ ከተባለው ሥፍራ ተነስታ መላጥያ ደሴት እስከደረሰችበት ጊዜ ድረስ ስለተከናወነው ነገር ቅዱስ ሉቃስ የሰጠው እያንዳንዱ መግለጫ ፍጹም ትክክለኛና አጥጋቢ መሆኑን ከመጽሐፉ ውጭ የተገኙ የገለልተኛ ወገን ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡ ካደረግነው ምርመራ ተረድተናል፤ መርከቧ በጉዞ ስላሳለፈችው ጊዜ ያሰፈረው ሐሳብም ከሸፈነችው ርቀት ጋር የሚመጣጠን ነው፤ በመጨረሻም ስለደረሱበት ቦታ የሰጠው መግለጫ ከቦታው ሁኔታ ጋር ፍጹም ተስማሚ ነው። ይህ ሁሉ ሉቃስ በዘገባው ላይ በገለጸው መሠረት በዚህ ጉዞ ላይ እንደነበረ ብቻ ሳይሆን የታዘባቸውና የተናገራቸው ነገሮች ሁሉ አስተማማኝና በከፍተኛ ደረጃ እምነት ሊጣልባቸው የሚችሉ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።”b
6 የአርኪኦሎጂ ግኝቶችም የሉቃስን ዘገባ ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የኤፌሶን ሰዎች በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ ዓመጽ ያስነሱበት ጥንታዊ የጨዋታ ማሳያ ሥፍራ እንዲሁም የአርጤምስ ቤተ መቅደስ በኤፌሶን በተደረጉ ቁፋሮዎች ተገኝተዋል። (ሥራ 19:27-41) ሉቃስ ስለ ተሰሎንቄ ባለ ሥልጣናት ሲናገር ‘የከተማው ባለ ሥልጣናት’ እንዲሁም ‘የከተማው ሹማምንት’ የሚለውን ማዕረግ መጠቀሙ ትክክል እንደሆነ የሚያረጋግጡ የተቀረጹ ጽሑፎች ተገኝተዋል። (17:6, 8) በመላጥያ የተገኙ ሁለት የተቀረጹ ጽሑፎች ሉቃስ፣ ፑፕልዮስን የመላጥያ “አለቃ” ብሎ መጥራቱ ትክክል እንደሆነም ያሳያሉ።—28:7c
7 ከዚህም በተጨማሪ ሉቃስ እንደዘገበው ጴጥሮስ፣ እስጢፋኖስ፣ ቆርኔሌዎስ፣ ጠርጠሉስ፣ ጳውሎስና ሌሎችም ንግግሮቻቸውን ያቀረቡት በተለያየ መንገድ ነው። ጳውሎስ በተለያዩ አድማጮች ፊት የሰጣቸው ንግግሮችም እንኳ እንደ ሁኔታው በተለያየ መንገድ ቀርበዋል። ይህም ሉቃስ የጻፈው እሱ ራሱ የሰማውን ወይም በቦታው የነበሩ ሰዎች የነገሩትን ብቻ እንደሆነ ያሳያል። ሉቃስ የልብ ወለድ ጸሐፊ አልነበረም።
8 ስለ ሉቃስ የግል ሕይወት እምብዛም የሚታወቅ ነገር የለም። ሉቃስ ራሱ ሐዋርያ ባይሆንም ከሐዋርያት ጋር አብሮ ሠርቷል። (ሉቃስ 1:1-4) ሐዋርያው ጳውሎስ ሉቃስን ሦስት ጊዜ በስሙ ጠቅሶታል። (ቈላ. 4:10, 14፤ 2 ጢሞ. 4:11፤ ፊል. 24) ጳውሎስ፣ ሉቃስን ‘የተወደደው ሐኪም’ ሲል የጠራው ሲሆን ከእሱ ጋር ለተወሰኑ ዓመታት አብረው ቆይተዋል። በዘገባው ውስጥ ‘እነሱ’ እና “እኛ” የሚሉት መግለጫዎች እየተፈራረቁ መጠቀሳቸው፣ በጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞ ወቅት ሉቃስ በጢሮአዳ አብሮት እንደነበረና ጳውሎስ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ እሱ በፊልጵስዩስ ቆይቶ ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም ከዚያ በኋላ ጳውሎስ ችሎት ፊት ለመቅረብ ወደ ሮም በሄደበት ጊዜ እንደገና አብሮት እንደተጓዘ ይጠቁማል።—ሥራ 16:8, 10፤ 17:1፤ 20:4-6፤ 28:16
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
32 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛና በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ስለ መሆናቸው የወንጌል ዘገባዎች የሚሰጡትን ምሥክርነት ያጠናክራል። የጰንጠቆስጤ ዕለት እየተቃረበ ሲሄድ ጴጥሮስ “ስለ ይሁዳ፣ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ” የተናገራቸው ሁለት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን ተናገረ። (ሥራ 1:16, 20፤ መዝ. 69:25፤ 109:8) በተጨማሪም ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት በግርምት ለተዋጠው ሕዝብ የሚያዩት ነገር አስቀድሞ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን በመግለጽ “ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው” ሲል አስረድቷቸዋል።—ሥራ 2:16-21፤ ኢዩ. 2:28-32፤ በተጨማሪም የሐዋርያት ሥራ 2:25-28, 34, 35ን ከመዝሙር 16:8-11 እና 110:1 ጋር አወዳድር።
33 ጴጥሮስ፣ ከቤተ መቅደሱ ውጭ የተሰበሰቡትን ሌሎች ሰዎች ለማሳመን በድጋሚ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የጠቀሰ ሲሆን መጀመሪያ ሙሴ የተናገረውን ከጠቀሰ በኋላ “በርግጥም ከሳሙኤል ጀምሮ የተነሱት ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ጊዜያት ተናግረዋል” ብሏል። ከዚያም ጴጥሮስ በሳንሄድሪን ፊት በቀረበበት ወቅት መዝሙር 118:22ን በመጥቀስ እነሱ የናቁት ድንጋይ ማለትም ክርስቶስ “የማእዘን ራስ” እንደሆነ አስረድቷል። (ሥራ 3:22-24፤ 4:11) ፊልጶስ፣ በኢሳይያስ 53:7, 8 ላይ ያለው ትንቢት እንዴት ፍጻሜውን እንዳገኘ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ገልጾለታል፤ ይህ ሰው የእውቀት ብርሃን ስለበራለት በትሕትና ለመጠመቅ ጠይቋል። (ሥራ 8:28-35) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን አስመልክቶ ለቆርኔሌዎስ ሲናገር “ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል” ብሏል። (10:43) ግዝረትን በተመለከተ ውዝግብ በተነሣ ጊዜ ያዕቆብ “እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያቱም ቃል ከዚህ ጋር ይስማማል” በማለት ውሳኔውን በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል። (15:15-18) ሐዋርያው ጳውሎስም ከተመሳሳይ ምንጭ ማስረጃ እየጠቀሰ ተናግሯል። (26:22፤ 28:23, 25-27) ደቀ መዛሙርቱም ሆኑ አድማጮቻቸው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የአምላክ ቃል ክፍል እንደሆኑ አድርገው በሙሉ ልብ መቀበላቸው እነዚህ መጻሕፍት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ተቀባይነት ያላቸው ጽሑፎች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
34 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ስለ ክርስቲያን ጉባኤ አመሠራረትና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየታገዘ ስላደረገው እድገት በማብራራት ረገድ በጣም ጠቃሚ መጽሐፍ ነው። በዚህ አስደናቂ ዘገባ ውስጥ አምላክ ሕዝቦቹ ጭማሪ እንዲያገኙ በማድረግ እንደባረካቸው፣ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የነበራቸውን ድፍረትና ያገኙትን ደስታ፣ በስደት ወቅት ያለማወላወል የወሰዱትን አቋም እንዲሁም ይሖዋን ለማገልገል ራሳቸውን በፈቃደኝነት እንዳቀረቡ መመልከት እንችላለን፤ ጳውሎስ በባዕድ አገሮች እንዲያገለግልና ወደ መቄዶንያ እንዲሄድ ለቀረበለት ጥሪ የሰጠው ምላሽ እንዲህ ዓይነት የፈቃደኝነት መንፈስ እንደነበራቸው ምሳሌ የሚሆን ነው። (4:13, 31፤ 15:3፤ 5:28, 29፤ 8:4፤ 13:2-4፤ 16:9, 10) ዛሬ ያለው የክርስቲያን ጉባኤም በአንድነትና በፍቅር የተሳሰረ ከመሆኑም በላይ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” የመናገር የጋራ ግብ ያለው በመሆኑ ከጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ጋር ተመሳሳይ ነው።—2:11, 17, 45፤ 4:34, 35፤ 11:27-30፤ 12:25
35 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ የአምላክን መንግሥት የማወጁ ክርስቲያናዊ ሥራ እንዴት ሊከናወን እንደሚገባ ይጠቁማል። በዚህ ረገድ ጳውሎስ ራሱ እንደሚከተለው በማለት ምሳሌውን ትቷል:- “በአደባባይም ሆነ ከቤት ቤት በመዘዋወር፣ እናንተን ከማስተማርና ይጠቅማችኋል ብዬ ያሰብሁትን ከመስበክ ወደ ኋላ አላልሁም።” ጳውሎስ አክሎም ‘በሚገባ እንደመሠከረላቸው’ ወይም የተሟላ ምሥክርነት እንደሰጣቸው ተናግሯል። ‘የተሟላ ምሥክርነት መስጠት’ የሚለው ጭብጥ በመላው መጽሐፍ ውስጥ የተንጸባረቀ ሲሆን በተለይ ጳውሎስ በእስር ላይ ሆኖ እንኳ የስብከትና የማስተማር ሥራውን በሙሉ ልብ እንዳከናወነ በተገለጸባቸው በመጽሐፉ የመጨረሻ አንቀጾች ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል:- “እርሱም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ [‘የተሟላ ምሥክርነት እየሰጠ፣’ NW] ያብራራላቸው ነበር፤ ከሙሴ ሕግና ከነቢያትም በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ ሊያሳምናቸው ሞከረ።” እኛም እንደ ጳውሎስ ስለ መንግሥቱ የመስበክ ሥራችንን በአንድ ልብ የምናከናውን እንሁን!—20:20, 21 NW፤ 28:23፤ 2:40፤ 5:42፤ 26:22
36 ጳውሎስ ከኤፌሶን ለመጡት የበላይ ተመልካቾች የሰጠው ምክር ዛሬ ላሉት የበላይ ተመልካቾች ብዙ ጠቃሚ ትምህርት ይዟል። እነዚህ የበላይ ተመልካቾች በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ እንደመሆናቸው መጠን ‘ለራሳቸውና ለመንጋው መጠንቀቃቸው’ በጣም አስፈላጊ ነው፤ መንጋውን በርኅራኄ መጠበቅና ሊያጠፏቸው ከሚፈልጉ ነጣቂ ተኩላዎች በጎቹን መታደግ አለባቸው። ይህ ደግሞ ቀላል ኃላፊነት አይደለም! የበላይ ተመልካቾች ንቁ ሆነው ሊኖሩና ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት መግለጫ በሆነው በቃሉ ራሳቸውን ሊገነቡ ይገባል። እነዚህ እረኞች ደካማ የሆኑትን ለመርዳት ሲተጉ “‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው’ ያለውን የጌታ የኢየሱስን ቃል” ሊያስታውሱ ይገባል።—20:17-35
37 ጳውሎስ የሰጣቸው ሌሎች ትምህርቶችም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በግልጽ የሚያብራሩ ናቸው። በአርዮስፋጎስ፣ ለኢስጦኢኮችና ለኤፊቆሮሳውያን ባደረገው ንግግር ላይ ያቀረበውን አሳማኝ ሐሳብ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በመጀመሪያ “ለማይታወቅ አምላክ” የሚለውን በመሠዊያ ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ በመጥቀስ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን የፈጠረው የሰማይና የምድር ጌታ የሆነው እውነተኛው አንድ አምላክ ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ እንዳልሆነ’ ለማስረዳት ተጠቅሞበታል። ከዚያም “እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን” የሚለውን የባለቅኔዎቻቸውን አባባል በመጥቀስ ሕይወት አልባ ከሆኑ የወርቅ፣ የብር ወይም የድንጋይ ጣዖታት እንደመጡ አድርገው ማሰባቸው ሞኝነት እንደሚሆን አስረድቷቸዋል። በዚህ መንገድ ጳውሎስ ሕያው የሆነውን አምላክ ሉዓላዊነት በጥበብ ነግሯቸዋል። ስለ ትንሣኤ የገለጸው በመደምደሚያው ላይ ሲሆን ያኔም ቢሆን የክርስቶስን ስም አልጠቀሰም። የእውነተኛውን አንድ አምላክ ሉዓላዊነት እንዲገነዘቡ ያደረገ ሲሆን በዚህም የተነሣ አንዳንዶች አማኞች ሆነዋል።—17:22-34
38 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ‘ቅዱሳት መጻሕፍትን ሁሉ’ አዘውትሮ በትጋት ማጥናትን ያበረታታል። ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ በቤርያ በሰበከበት ጊዜ በዚያ የነበሩት አይሁዳውያን “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት [በመቀበላቸው]” “አስተዋዮች” ተብለው ተመስግነዋል። (17:11) እንደዚያ ጊዜ ሁሉ ዛሬም የይሖዋ መንፈስ ካደረበት ጉባኤው ጋር ሆነን ቅዱሳን መጻሕፍትን በዚህ መልኩ በጉጉት ብንመረምር ጽኑ እና ጠንካራ እምነት በማግኘት እንባረካለን። አንድ ሰው መለኮታዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በግልጽ መገንዘብ የሚችለው ይህን የመሰለ ጥናት ሲያካሂድ ነው። ከእነዚህ ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዱ በሐዋርያት ሥራ 15:29 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። እዚህ ጥቅስ ላይ፣ ከሐዋርያትና በኢየሩሳሌም ከነበሩ ሽማግሌዎች የተውጣጣው የአስተዳደር አካል መንፈሳዊ እስራኤላውያን የመገረዝ ግዴታ እንደሌለባቸው ከገለጸ በኋላ ከጣዖት፣ ከደምና ከዝሙት እንዲርቁ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል።
39 እነዚያ የጥንት ደቀ መዛሙርት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን ቅዱሳን መጻሕፍት በሚገባ በማጥናታቸው እንደ አስፈላጊነቱ ጥቅሶችን መጥቀስና የተማሩትን በሥራ ማዋል ችለው ነበር። ያገኙት ትክክለኛ እውቀትና የአምላክ መንፈስ ከባድ ስደቶችን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ሰጥቷቸዋል። ጴጥሮስና ዮሐንስ የስብከቱን ሥራ ለሚቃወሙት መሪዎች እንደሚከተለው ብለው በድፍረት በመናገር ለሁሉም ታማኝ ክርስቲያኖች የሚሆን ምሳሌ ትተዋል:- “ከእግዚአብሔር ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ይገባ እንደሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም።” ከዚያም ሐዋርያት፣ በኢየሱስ ስም ማስተማራቸውን እንዲያቆሙ “በጥብቅ” ባዘዛቸው በሳንሄድሪን ፊት ድጋሚ በቀረቡ ጊዜ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ሲሉ ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥተዋል። ይህ ድፍረት የተሞላበት ንግግር ለገዥዎቹ ጥሩ ምሥክርነት የሰጠ ሲሆን ታዋቂ የሕግ አስተማሪ የሆነው ገማልያል ሃይማኖታዊ ነፃነትን በመደገፍ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውንና ለሐዋርያቱ መፈታት ምክንያት የሆነውን ሐሳብ እንዲሰነዝር አድርጎታል።—4:19, 20፤ 5:28, 29, 34, 35, 38, 39
40 በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ቦታ የተሰጠው፣ ይሖዋ ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ ያለው ክብራማ ዓላማ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ጎልቶ ይታያል። በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ኢየሱስ ከማረጉ በፊት በነበሩት 40 ቀናት ውስጥ “ስለ እግዚአብሔር መንግሥት” እንደተናገረ ተገልጿል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መንግሥቱ መልሶ መቋቋም ላነሱት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ በመጀመሪያ እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቹ ሊሆኑ እንደሚገባ ነግሯቸዋል። (1:3, 6, 8) ደቀ መዛሙርቱም ከኢየሩሳሌም ጀምረው ስለ አምላክ መንግሥት በድፍረት ሰብከዋል። በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ላይ በደረሰው ስደት ምክንያት እስጢፋኖስ በድንጋይ ሲወገር ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት ወደ አዳዲስ ክልሎች ተበታተኑ። (7:59, 60) ፊልጶስ በሰማርያ “ስለ እግዚአብሔር መንግሥት” እንደሰበከና ብዙ ፍሬ እንዳገኘ እንዲሁም ጳውሎስና የአገልግሎት ባልደረቦቹ በእስያ፣ በቆሮንቶስ፣ በኤፌሶንና በሮም ‘የእግዚአብሔርን መንግሥት’ እንዳወጁ ተገልጿል። እነዚህ ሁሉ የጥንት ክርስቲያኖች አለማወላወል በይሖዋና የብርታት ምንጭ በሆነው በመንፈሱ በመተማመን ረገድ ድንቅ ምሳሌ ትተዋል። (8:5, 12፤ 14:5-7, 21, 22፤ 18:1, 4፤ 19:1, 8፤ 20:25፤ 28:30, 31) እኛም ሊዳፈን ያልቻለውን የእነሱን ቅንዓትና ድፍረት መመልከታችንና ይሖዋ ጥረታቸውን ምን ያህል አብዝቶ እንደባረከላቸው ማስተዋላችን ‘ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በመመስከሩ’ ሥራ ታማኞች እንድንሆን ግሩም ማበረታቻ ይሆነናል።—28:23
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሴንት ፖል ዘ ትራቭለር፣ 1895 ገጽ 4
b በሐምሌ 22, 1947 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ገጽ 22-23 ላይ ወጥቷል፤ በተጨማሪም የሚያዝያ 8, 1971 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ገጽ 27-28ን ተመልከት።
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1 ገጽ 153-154, 734-735፤ ጥራዝ 2 ገጽ 748