የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • “የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ”
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
    • 11. ሽማግሌዎቹ ለጳውሎስ ምን ምክር ሰጡት? ሆኖም ጳውሎስ ለማድረግ ፈቃደኛ የሚሆናቸው ወይም የማይሆናቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

      11 በጳውሎስ ላይ የተወራው ነገር ትክክል ባይሆንም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በሰሙት ነገር ተረብሸዋል። በመሆኑም ሽማግሌዎቹ እንዲህ የሚል ምክር ሰጡት፦ “ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። እነዚህን ሰዎች ይዘህ በመሄድ ከእነሱ ጋር የመንጻት ሥርዓት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ክፈልላቸው። ይህን ካደረግክ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ሕጉን እያከበርክ በሥርዓት እንደምትኖር ሁሉም ሰው ያውቃል።”c—ሥራ 21:23, 24

      12. ጳውሎስ የኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች ምክር ሲሰጡት እሺ ባይና ተባባሪ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

      12 ጳውሎስ የችግሩ ዋና መንስኤ ስለ እሱ የተወራው አሉባልታ ሳይሆን አይሁዳውያን አማኞች ለሙሴ ሕግ ያላቸው ቅንዓት እንደሆነ በመግለጽ መቃወም ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ያወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ ሽማግሌዎቹ ያሉትን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል። ቀደም ሲል “እኔ ራሴ በሕግ ሥር ባልሆንም እንኳ በሕግ ሥር ያሉትን እማርክ ዘንድ በሕግ ሥር ላሉት በሕግ ሥር እንዳለሁ ሆንኩ” በማለት ጽፎ ነበር። (1 ቆሮ. 9:20) በዚህ ወቅት ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር “በሕግ ሥር” እንዳለ ሆኗል። ከሽማግሌዎች ጋር በመተባበርና እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ከማለት በመቆጠብ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።—ዕብ. 13:17

      ምስሎች፦ 1. ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ያሉ ሽማግሌዎች የሚሰጡትን መመሪያ ሲያዳምጥ። 2. በዘመናችን ሽማግሌዎች ስብሰባ ሲያደርጉ፤ ሽማግሌዎቹ እጃቸውን ሲያወጡ አንድ ወንድም ትኩር ብሎ እየተመለከታቸው ነው።

      ጳውሎስ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ የሌሎችን ሐሳብ ይቀበል ነበር። አንተስ?

      የሮም ሕግና የሮም ዜጎች

      የሮም ባለሥልጣናት በቅኝ ተገዢዎቻቸው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ውስጥ ያን ያህል ጣልቃ አይገቡም። በጥቅሉ ሲታይ አይሁዳውያን የሚተዳደሩት በራሳቸው ሕግ ነበር። የሮም ባለሥልጣናት በጳውሎስ ጉዳይ ጣልቃ የገቡት፣ ሐዋርያው ቤተ መቅደሱ ውስጥ በመታየቱ የተፈጠረው ሁከት የከተማዋን ሰላም እንዳያደፈርስ ስለሰጉ ብቻ ነው።

      የሮም ዜግነት የሌለው ሰው በሮም ግዛት ውስጥ ያለው መብት ውስን ነበር። ባለሥልጣናቱ የሮም ዜግነት ያላቸውን ሰዎች የሚይዙበት መንገድ ግን ይለያል።f የሮም ዜግነት የሚያስገኛቸው መብቶች አሉ፤ እነዚህ መብቶች በመላው የሮም ግዛት ውስጥ ይከበሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንድን ሮማዊ ያለፍርድ ማሰር ወይም መደብደብ በሕግ የተከለከለ ነው፤ ይህ ሕጋዊ መብት የሌላቸው ባሪያዎች ብቻ ናቸው። በተጨማሪም የሮም ዜግነት ያላቸው ሰዎች፣ አንድ የአውራጃ ገዢ በትክክል እንዳልፈረደላቸው ከተሰማቸው በሮም ለሚገኘው ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ የማለት መብት ነበራቸው።

      የሮም ዜግነት ማግኘት የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች ነበሩ። የመጀመሪያው በመወለድ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ንጉሠ ነገሥታት፣ የሮም ዜግነትን ለግለሰቦች ወይም በአንድ ከተማ አሊያም አውራጃ ውስጥ ለሚኖሩ ነፃ ሰዎች በሙሉ ይሰጣሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ለሮም መንግሥት ለሰጡት አገልግሎት ወሮታ ለመክፈል ነው። አንድ ባሪያ፣ የሮም ዜጋ ከሆነ ሰው ነፃነቱን በገንዘብ ከገዛ ወይም ሮማዊው ነፃ ካወጣው የሮም ዜግነት ያገኛል፤ በሮማውያን ሠራዊት ውስጥ ሲያገለግል ቆይቶ በጡረታ የተገለለ ወታደርም የሮም ዜግነት ያገኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሮም ዜግነትን መግዛት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች የነበሩ ይመስላል። ሮማዊው ሻለቃ ቀላውዴዎስ ሉስዮስ ጳውሎስን “እኔ ይህን የዜግነት መብት የገዛሁት ብዙ ገንዘብ አውጥቼ ነው” ብሎታል። በምላሹም ጳውሎስ “እኔ ግን በመወለድ አገኘሁት” ብሏል። (ሥራ 22:28) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ከጳውሎስ ወንድ ቅድመ አያቶች አንዱ በሆነ መንገድ የሮም ዜግነት አግኝቶ መሆን አለበት፤ ዜግነቱን ያገኘው እንዴት እንደሆነ ግን በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም።

      f በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ይሁዳ ውስጥ የሮም ዜግነት ያላቸው ብዙ ሰዎች የነበሩ አይመስልም። በሮም ቅኝ ግዛቶች ውስጥ ለሚኖሩ ለሁሉም ሰዎች የዜግነት መብት የተሰጠው በሦስተኛው መቶ ዘመን ነው።

  • “የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ”
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
    • c አንዳንድ ምሁራን፣ እነዚህ ሰዎች የናዝራዊነት ስእለት እንደነበረባቸው ይናገራሉ። (ዘኁ. 6:1-21) እርግጥ ነው፣ ይህን ስእለት የሚያካትተው የሙሴ ሕግ አሁን ተሽሯል። ይሁንና እነዚህ ሰዎች የተሳሉት ለይሖዋ በመሆኑ ጳውሎስ ስእለቱን መፈጸማቸው ስህተት እንዳልሆነ አስቦ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የሰዎቹን ወጪ መክፈሉና አብሯቸው መሄዱ ምንም ስህተት የለውም። ሰዎቹ የተሳሉት ምን ዓይነት ስእለት እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። ይሁንና ብዙውን ጊዜ ናዝራውያን ከኃጢአት ለመንጻት የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል፤ የሰዎቹ ስእለት ምንም ዓይነት ይሁን፣ ጳውሎስ እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ለማቅረብ እንደማይስማማ ጥያቄ የለውም። ፍጹም የሆነው የክርስቶስ መሥዋዕት ከቀረበ ወዲህ የእንስሳት መሥዋዕቶች ኃጢአትን ማስተሰረይ አይችሉም። ጳውሎስ ያደረገው ነገር ምንም ይሁን ምን፣ ሕሊናውን የሚያስጥስ ነገር ለማድረግ እንደማይስማማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ