-
ይህን ያውቁ ኖሯል?መጠበቂያ ግንብ—2010 | መጋቢት 1
-
-
ጳውሎስ በሮማውያን ከመያዙ ጋር በተያያዘ የተጠቀሱት “ነፍሰ ገዳዮች” እነማን ነበሩ?
▪ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደሚናገረው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሁካታ በተፈጠረበት ወቅት የሮም ጦር አዛዥ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “አራት ሺህ ነፍሰ ገዳዮችን” በመምራት ዓመፅ ያስነሳው ሰው ስለመሰለው በጥበቃ ሥር እንዲሆን አደረገው። (የሐዋርያት ሥራ 21:30-38) ስለ እነዚህ ነፍሰ ገዳዮች ምን የሚታወቅ ነገር አለ?
“ነፍሰ ገዳዮች” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሲካሪ ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ሲሆን “ሲካ የሚጠቀሙ” ወይም ጩቤ የሚጠቀሙ የሚል ትርጉም አለው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ፍላቭየስ ጆሴፈስ የተባለ ታሪክ ጸሐፊ ሲካሪ ስለተባሉት ሰዎች ሲገልጽ በፖለቲካዊ ዓላማ ተነሳስተው ግድያ ለመፈጸም የተደራጁና የሮም የምንጊዜም ጠላት የነበሩ አክራሪ የአይሁድ ዓማፂ ቡድኖች እንደሆኑ ተናግሯል።
ጆሴፈስ እንደገለጸው ሲካሪዎች “በጠራራ ፀሐይ ከተማ ውስጥ ሰዎችን ይገድሉ ነበር፤ አብዛኛው ጊዜ ይህን የሚያደርጉት በበዓል ቀናት ሲሆን ጠላቶቻቸውን ለመውጋት የሚጠቀሙባቸውን ጩቤዎች ልብሳቸው ውስጥ በመሸሸግና ከሕዝቡ ጋር በመቀላቀል ነው።” እነዚህ ሲካሪዎች የወጉት ሰው ሲሞት ማንም ሰው እንዳይጠረጥራቸው ለማድረግ ሲሉ በሰውየው ሞት እንደተናደዱ ለማስመሰል ይሞክራሉ። ጆሴፈስ እነዚህ ሲካሪዎች ቆየት ብሎ ማለትም ከ66 እስከ 70 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት አይሁዳውያን በሮማውያን ላይ ላስነሱት ዓመፅ ትልቅ ሚና ተጫውተው እንደነበር አክሎ ተናግሯል። በመሆኑም ጳውሎስን የያዘው ሮማዊ የጦር አዛዥ የዚህ ቡድን መሪ ብሎ የጠረጠረውን ሰው በቁጥጥር ሥር የማዋል ከፍተኛ ጉጉት ነበረው።
-
-
ይህን ያውቁ ኖሯል?መጠበቂያ ግንብ—2010 | መጋቢት 1
-
-
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ሠዓሊ አንድን ነፍሰ ገዳይ በሥዕሉ እንዳስቀመጠው
-