በዓለም እየኖሩ የዓለም ክፍል አለመሆን
“ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።”—ዮሐንስ 15:19
1. ክርስቲያኖች ከዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን ዓይነት ነው? ይሁንና ዓለም ለእነርሱ ምን አመለካከት አለው?
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ‘ከዓለም አይደላችሁም’ ሲል ነግሯቸዋል። ስለ የትኛው ዓለም መናገሩ ነበር? ቀደም ሲል “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ብሎ አልነበረምን? (ዮሐንስ 3:16) የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በኢየሱስ ያመኑት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ደቀ መዛሙርቱ እንደመሆናቸው መጠን እነርሱ ራሳቸው እዚህ ላይ የተጠቀሰው ዓለም ክፍል እንደነበሩ ግልጽ ነው። ታዲያ አሁን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ከዓለም የተለዩ ስለመሆናቸው የተናገረው ለምንድን ነው? “ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” ያለውስ ለምን ነበር?—ዮሐንስ 15:19
2, 3. (ሀ) ክርስቲያኖች የየትኛው “ዓለም” ክፍል ሊሆኑ አይገባም? (ለ) ክርስቲያኖች የተለዩትን “ዓለም” አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
2 መልሱ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለም” (በግሪክኛ ኮስሞስ) የሚለውን ቃል የሚጠቀመው በተለያየ መንገድ ነው የሚል ነው። በፊተኛው ርዕስ ውስጥ እንደተብራራው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዓለም” የሚለው ቃል ጠቅላላውን የሰው ዘር የሚያመለክትባቸው አንዳንድ ቦታዎች አሉ። አምላክ የወደደውና ኢየሱስም የሞተለት ይህ ዓለም ነው። ይሁን እንጂ ዚ ኦክስፎርድ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቺያኒቲ እንደሚለው “በክርስትና ውስጥ ‘ዓለም’ የሚለው ቃል ከአምላክ የራቀንና የእርሱ ጠላት የሆነን ነገር ለማመልከት ያገለግልላል።” ይህ ምን ያህል እውነት ነው? ካቶሊካዊው ጸሐፊ ሮላን ሚንራት ሌ ክሬትየ ኤ ለ ሞንድ (ክርስቲያኖችና ዓለም) በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል:- “ዓለም የሚለው ቃል አሉታዊ በሆነ ትርጓሜው የሚያመለክተው . . . ከአምላክ ተጻራሪ የሆኑ ኃይሎች ተግባራቸውን የሚፈጽሙበትና የድል አድራጊውን የክርስቶስ አገዛዝ በመቃወም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለ የጠላት ኃይል ሆነው የሚደራጁበት ግዛት ነው።” ይህ “ዓለም” ከአምላክ የራቀው ኅብረተሰብ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች የዚህ ዓለም ክፍል አይደሉም፤ ደግሞም ይጠላቸዋል።
3 ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ገደማ እንደሚከተለው ብሎ ሲጽፍ በአእምሮው ይዞ የነበረው ይህንን ዓለም ነው:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፣ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።” (1 ዮሐንስ 2:15, 16) በተጨማሪም “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:19) ኢየሱስ ራሱ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ ጠርቶታል።—ዮሐንስ 12:31፤ 16:11
የዓለም ኃያላን መንግሥታት ዕድገት
4. የዓለም ኃይሎች ብቅ ያሉት እንዴት ነው?
4 ዛሬ ያለው ከአምላክ የራቀ ዓለም ብቅ ማለት የጀመረው በኖኅ ዘመን ከመጣው የጥፋት ውኃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር። በዚህ ጊዜ ብዙዎቹ የኖኅ ዝርያዎች ይሖዋ አምላክን ማምለክ አቁመው ነበር። በዚያ ዘመን ከተማ የገነባውና ‘ይሖዋን በመቃወም ኃያል አዳኝ’ የነበረው ናምሩድ ስሙ ገንኖ ነበር። (ዘፍጥረት 10:8-12 NW) በእነዚያ ዘመናት አብዛኛው የዚህ ዓለም ክፍል የተዋቀረው በትናንሽ የከተማ መንግሥታት ሲሆን እነዚህም አልፎ አልፎ አንዳቸው ከሌላው ጋር ጥምረት እየፈጠሩ እርስ በርሳቸው ይዋጉ ነበር። (ዘፍጥረት 14:1-9) አንዳንድ የከተማ መንግሥታት በሌሎች ላይ የበላይነት በመቀዳጀታቸው የየክልላቸው ኃያላን ሆኑ። ቀስ በቀስም ከክልሉ ኃያላን አንዳንዶቹ ታላላቅ የዓለም ኃያላን ሆኑ።
5, 6. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈራረቁት ሰባቱ የዓለም ኃያላን እነማን ናቸው? (ለ) እነዚህ የዓለም ኃያላን በምሳሌያዊ መንገድ እንዴት ተደርገው ተገልጸዋል? ሥልጣን ያገኙትስ ከማን ነው?
5 የዓለም ኃያላን መንግሥታት ገዥዎችም የፈጸሙት ጭካኔ የሞላበት የኃይል ድርጊት እንደሚያረጋግጠው የናምሩድን ፈለግ በመከተል ይሖዋን ሳያመልኩ ቀርተዋል። እነዚህ የዓለም ኃያላን መንግሥታት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በአውሬዎች የተመሰሉ ሲሆን ባለፉት መቶ ዘመናት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የነበራቸው ስድስቱ የዓለም ኃይሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን። እነዚህም ግብጽ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክ እና ሮም ናቸው። ከሮም በኋላ ሰባተኛ የዓለም ኃይል እንደሚነሣ በትንቢት ተነግሯል። (ዳንኤል 7:3-7፤ 8:3-7, 20, 21፤ ራእይ 17:9, 10) ይህም የእንግሊዝን ግዛትና አጋሯን ዩናይትድ ስቴትስን የሚያቅፈው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ሲሆን፣ ከጊዜ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ በኃይል ከብሪታንያ ልቃ ተገኝታለች። የብሪታንያ ግዛት እያደገ መሄድ የጀመረው የሮማ ግዛት ርዝራዥ ጨርሶ ከጠፋ በኋላ ነው።a
6 ሰባቱ ተከታታይ የዓለም ኃያላን መንግሥታት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ እረፍት የለሽ ከሆነው ሰብዓዊ ባሕር ውስጥ በወጣ ባለ ሰባት ራስ አውሬ ራሶች ተመስለዋል። (ኢሳይያስ 17:12, 13፤ 57:20, 21፤ ራእይ 13:1) ለዚህ ገዥ ለሆነው አውሬ ሥልጣን የሚሰጠው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመልሳል:- “ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው።” (ራእይ 13:2) ይህ ዘንዶ ከሰይጣን ዲያብሎስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።—ሉቃስ 4:5, 6፤ ራእይ 12:9
መጪው የአምላክ መንግሥት አገዛዝ
7. ክርስቲያኖች ተስፋቸውን የጣሉት በማን ላይ ነው? ይህስ ከዓለም መንግሥታት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚነካው እንዴት ነው?
7 ክርስቲያኖች ወደ 2,000 ለሚጠጉ ዓመታት “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” እያሉ ሲጸልዩ ቆይተዋል። (ማቴዎስ 6:10) የይሖዋ ምሥክሮች በምድር ላይ እውነተኛ ሰላም ለማስፈን የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በቅርብ የሚከታተሉ እንደመሆናቸው መጠን ይህ ጸሎት በቅርቡ መልስ እንደሚያገኝና ይህ መንግሥት የምድርን ጉዳዮች መቆጣጠር እንደሚጀምር አጥብቀው ያምናሉ። (ዳንኤል 2:44) ለዚህ መንግሥት ያላቸው ታማኝነት ከዓለም መንግሥታት ጉዳዮች ገለልተኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
8. በመዝሙር 2 ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው መንግሥታት ለአምላክ መንግሥት አገዛዝ ምን ምላሽ ይሰጣሉ?
8 አንዳንድ ብሔራት የሃይማኖት መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንደሚያከብሩ ይናገራሉ። ሆኖም ተግባራቸው ሲታይ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ እንደሆነና ኢየሱስን በምድር ላይ ሥልጣን ያለው ሰማያዊ ንጉሥ አድርጎ እንደሾመው አይቀበሉም። (ዳንኤል 4:17፤ ራእይ 11:15) አንድ ትንቢታዊ መዝሙር እንዲህ ይላል:- “የምድር ነገሥታት ተነሡ፣ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ [በኢየሱስ] ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ:- ማሰርያቸውን እንበጥስ፣ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል።” (መዝሙር 2:2, 3) መንግሥታት ብሔራዊ ሉዓላዊነታቸውን የሚገድብ መለኮታዊ “ማሰሪያ” ወይም “ገመድ” እንዲኖር አይፈልጉም። በመሆኑም ይሖዋ ለተመረጠው ንጉሡ ለኢየሱስ እንዲህ ይለዋል:- “ለምነኝ፣ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ። በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ [“ትሰባብራቸዋለህ፣” NW]። እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃም ትቀጠቅጣቸዋለህ።” (መዝሙር 2:8, 9) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሞተለት የሰው ዘር ዓለም ሙሉ በሙሉ ‘አይሰባበርም።’—ዮሐንስ 3:17
‘የአውሬውን’ “ምልክት” አለመቀበል
9, 10. (ሀ) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ምን ነገር ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል? (ለ) ‘የአውሬውን ምልክት’ መቀበል ምን ትርጉም አለው? (ሐ) የአምላክ አገልጋዮች የሚቀበሏቸው ምልክቶች ምንድን ናቸው?
9 ሐዋርያው ዮሐንስ የተቀበለው ራእይ እንደሚያሳየው ከአምላክ የራቀው የሰው ዘር ዓለም ፍጻሜው ሲቃረብ እንዲደረጉ የሚፈልጋቸው ነገሮች እንደሚጨምሩና “ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፣ . . . ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል” እንደሚያደርግ ያስጠነቅቃል። (ራእይ 13:16, 17) ይህ ምን ማለት ነው? በቀኝ እጅ ላይ ምልክት ማድረግ አንድን ነገር ከልብ መደገፍን ያሳያል። በግንባር ላይ ያለው ምልክትስ? ዚ ኤክስፖዚተርስ ግሪክ ቴስታመንት እንዲህ ይላል:- “ይህ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ምሳሌያዊ አገላለጽ በተዘዋዋሪ መንገድ በወታደሮችና በባሪያዎች ላይ በግልጽ የሚታይ ንቅሳት ወይም ምልክት የማድረግን ልማድ . . . ይበልጥ ደግሞ የአንድን አምላክ ስም የያዘ ክታብ ማንጠልጠል የመሰለውን ሃይማኖታዊ ልማድ የሚያመለክት ነው።” ብዙ ሰዎች በድርጊታቸውና በቃላቸው በምሳሌያዊ መንገድ ‘የአውሬው’ “ባሪያዎች” ወይም “ወታደሮች” እንደሆኑ አድርጎ የሚያሳውቃቸውን ይህን ምልክት ያደርጋሉ። (ራእይ 13:3, 4) የእነዚህን ሰዎች የወደፊት ዕጣ በሚመለከት ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንዲህ ይላል:- “የአምላክ ጠላቶች የአውሬው [ምልክት] ማለትም ስሙን የያዘው ምሥጢራዊ ቁጥር በግምባራቸውና በእጃቸው ላይ እንዲደረግ ይፈቅዳሉ። ይህን ማድረጋቸው ኢኮኖሚያዊና የንግድ ጠቀሜታ ያስገኝላቸዋል፤ ነገር ግን የአምላክን ቁጣ ስለሚያስከትልባቸው ከሺው ዓመት መንግሥት ውጭ ያደርጋቸዋል። ራእይ 13:16፤ 14:9፤ 20:4”
10 “ምልክቱን” እንድንቀበል የሚመጣብንን ግፊት መቋቋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ የሚሄድ ድፍረትና ጽናት ይጠይቃል። (ራእይ 14:9-12) ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ያለውን ጥንካሬ አሳይተዋል፤ ከዚህም የተነሣ ብዙውን ጊዜ ይጠላሉ ይነቀፋሉም። (ዮሐንስ 15:18-20፤ 17:14, 15) የአውሬውን ምልክት በመቀበል ፋንታ ኢሳይያስ እንዳለው “እኔ የእግዚአብሔር ነኝ” ብለው በምሳሌያዊ መንገድ በእጆቻቸው ላይ ይጽፋሉ። (ኢሳይያስ 44:5) ከዚህም በላይ በከሃዲ ሃይማኖት በሚፈጸመው ርኩሰት ‘ስለሚያዝኑና ስለሚተክዙ’ ይሖዋ የፍርድ እርምጃውን ሲያስፈጽም ለመትረፍ የሚበቁ መሆናቸውን የሚያሳይ ምሳሌያዊ ምልክት በግንባራቸው ላይ ይደረግላቸዋል።—ሕዝቅኤል 9:1-7
11. የአምላክ መንግሥት የምድርን አገዛዝ ሙሉ በሙሉ እስኪጨብጥ ድረስ ሰብዓዊ መንግሥታት እንዲገዙ የፈቀደላቸው ማን ነው?
11 አምላክ፣ የክርስቶስ ሰማያዊ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ምድርን ተቆጣጥሮ መግዛት እስኪጀምር ድረስ ሰብዓዊ መንግሥታት እንዲገዙ ፈቅዶላቸዋል። ፕሮፌሰር ኦስካር ኩልማን ዘ ስቴት ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ፖለቲካዊ መንግሥታት እንዲገዙ መለኮታዊ ፈቃድ ስለ ማግኘታቸው ጠቅሰዋል። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለመንግሥት የነበራቸው አመለካከት እርስ በርሱ የሚጣጣም ሳይሆን የሚጋጭ መስሎ የታየው መንግሥታት ‘ጊዜያዊ’ ናቸው በሚለው ውስብስብ ጽንሰ ሐሳብ ምክንያት ነው። መስሎ ታየ የሚለውን ሐሳብ ላሰምርበት እወዳለሁ። ‘ሰው ሁሉ ላሉት ኃይሎች ይገዛ . . .’ የሚለውን ሮሜ 13:1ን እና መንግሥትን ከባሕር በሚወጣ አውሬ የሚመስለውን ራእይ 13ን መጥቀሱ ብቻ ይበቃናል።”
“አውሬው” እና “ቄሣር”
12. የይሖዋ ምሥክሮች ሰብዓዊ መንግሥታትን በሚመለከት ምን ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት አላቸው?
12 በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ሁሉም ሰዎች የሰይጣን መሣሪያ ናቸው ብሎ መደምደም ስህተት ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አስተዋይ ሰው” መሆኑ እንደተጠቀሰለት እንደ አገረ ገዥው ሰርግዮስ ጳውሎስ ያሉ ብዙ ሰዎች በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመሩ መሆናቸውን አሳይተዋል። (ሥራ 13:7) አንዳንድ ገዥዎች ይሖዋንና ዓላማውን ባያውቁም እንኳ አምላክ በሰጣቸው ሕሊና በመመራት ለአናሳ ወገኖች መብት በድፍረት ተሟግተዋል። (ሮሜ 2:14, 15) መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለም” የሚለውን ቃል በሁለት ተጻራሪ መንገዶች እንደሚጠቀምበት አስታውስ፤ አንደኛው አምላክ የወደደውና እኛም ልንወደው የሚገባን የሰው ዘር ዓለም ሲሆን ሌላው ደግሞ ሰይጣን አምላኩ የሆነለትና እኛም ልንለየው የሚገባን ከአምላክ የራቀው የሰው ልጆች ዓለም ነው። (ዮሐንስ 1:9, 10፤ 17:14፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ያዕቆብ 4:4) በመሆኑም፣ የይሖዋ አገልጋዮች ለሰብዓዊ አገዛዝ ያላቸው አመለካከት ሚዛናዊ ነው። የአምላክ መንግሥት አምባሳደሮች ወይም መልእክተኞች ሆነን የምናገለግልና ሕይወታችንንም ለአምላክ የወሰን ሰዎች በመሆናችን ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ ነን። (2 ቆሮንቶስ 5:20) በአንጻሩ ደግሞ በሥልጣን ላይ ላሉት ሰዎች በሚገባ እንገዛለን።
13. (ሀ) ይሖዋ ሰብዓዊ መንግሥታትን የሚመለከታቸው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ለሰብዓዊ መንግሥታት የሚገዙት እስከ ምን ድረስ ነው?
13 ይህ ዓይነቱ ሚዛናዊ አቋም የይሖዋን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። ኃያላንም ሆኑ ትናንሽ መንግሥታት ሥልጣናቸውን አላግባብ ሲጠቀሙ፣ ሕዝቦቻቸውን ሲጨቁኑ ወይም አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎችን ሲያሳድዱ በአስፈሪ አራዊት ከሚመስላቸው ትንቢታዊ መግለጫ ጋር የሚስማማ ሥራ እየሠሩ ነው። (ዳንኤል 7:19-21፤ ራእይ 11:7) ይሁን እንጂ ብሔራዊ መንግሥታት በፍትሐዊ መንገድ ሕግንና ሥርዓትን በማስጠበቅ የአምላክን ዓላማ ሲያስፈጽሙ “የሕዝብ አገልጋዮቹ” እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ሮሜ 13:6 NW) ይሖዋ ሕዝቦቹ ሰብዓዊ መንግሥታትን እንዲያከብሩና እንዲገዙላቸው ይፈልጋል፤ ይሁን እንጂ ተገዥነታቸው ገደብ የለውም ማለት አይደለም። የአምላክ አገልጋዮች በአምላክ ሕግ ውስጥ የተከለከለውን ነገር እንዲያደርጉ ሲጠየቁ ወይም አምላክ አገልጋዮቹ እንዲያደርጉት ያዘዘውን ነገር እንዳያደርጉ ሲከለከሉ ሐዋርያት የወሰዱትን አቋም ይወስዳሉ፤ ይኸውም “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚል ነው።—ሥራ 5:29
14. ኢየሱስ ክርስቲያኖች ለሰብዓዊ መንግሥታት የሚያሳዩትን ተገዥነት እንዴት ገልጾታል? ጳውሎስስ?
14 ኢየሱስ “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ተከታዮቹ በመንግሥታትም ሆነ በአምላክ ፊት ግዴታ እንዳለባቸው መግለጹ ነበር። (ማቴዎስ 22:21) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። . . . በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቊጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ስለዚህ ስለ ቊጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና።” (ሮሜ 13:1, 4-6) ክርስቲያኖች ከመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥታት የሚያቀርቡትን ጥያቄ ማጤን አስፈልጓቸዋል። እነዚህን ጥያቄዎች መቀበል እምነታቸውን እንዳላሉ ሊያስቆጥርባቸው ይችል እንደሆነ ወይም ደግሞ ጥያቄዎቹ ተገቢ እንደሆኑና ተግተው ሊፈጽሟቸው የሚገባ መሆኑን ማስተዋል አስፈልጓቸዋል።
ትጉ ዜጎች
15. የይሖዋ ምሥክሮች ተግተው የቄሣርን ለቄሣር የሚያስረክቡት እንዴት ነው?
15 ፖለቲካዊ ‘የበላይ ባለ ሥልጣኖች’ አምላክ የፈቀደላቸውን ድርሻ ሲወጡ “አገልጋዮቹ” ይሆናሉ። ይህም ‘ክፉ የሚያደርጉትን መቅጣትና በጎ የሚያደርጉትን ማመስገንን’ ይጨምራል። (1 ጴጥሮስ 2:13, 14) የይሖዋ አገልጋዮች በሕግ የሚፈለግባቸውን ቀረጥ በወቅቱ በመክፈል ለቄሣር የሚገባውን ያስረክባሉ፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናቸው እስከሚፈቅድላቸው ድረስ “ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ” ናቸው። (ቲቶ 3:1) “በጎ ሥራ” አንዳንድ ድንገተኛ አደጋዎች ሲደርሱ ሌሎችን መርዳትን ይጨምራል። የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ አጋጣሚዎች ለሌሎች ሰዎች ስላሳዩት ደግነት ብዙዎች መስክረዋል።—ገላትያ 6:10
16. የይሖዋ ምሥክሮች ለመንግሥታትም ይሁን ለሌሎች ሰዎች በትጋት የሚያከናውኗቸው መልካም ሥራዎች ምንድን ናቸው?
16 የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ያፈቅራሉ፤ ለሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ከሁሉ ይበልጥ የተሻለ ነገር ደግሞ አምላክ ጽድቅ የሰፈነበት “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ለማምጣት ስላለው ዓላማ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ መርዳት እንደሆነ ይሰማቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:13) የመጽሐፍ ቅዱስን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶች በማስተማርና በሥራ በመተርጎም ብዙዎቹን ከመጥፎ ድርጊት በማዳናቸው ለሰብዓዊው ኅብረተሰብ ጠቃሚ ሀብት ሆነዋል። የይሖዋ አገልጋዮች ለሕግ የሚታዘዙና ‘ክብር ለሚገባቸውም ክብርን የሚሰጡ’ በመሆናቸው ለመንግሥት ወኪሎች፣ ለባለ ሥልጣኖች፣ ለዳኞችና ለከተማ አስተዳዳሪዎች አክብሮት አላቸው። (ሮሜ 13:7) የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች በትምህርት ቤት ካሉ የልጆቻቸው አስተማሪዎች ጋር በደስታ የሚተባበሩ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ልጆቻቸው ለኅብረተሰቡ ሸክም ሳይሆኑ ኑሯቸውን መምራት ይችሉ ዘንድ ትምህርታቸውን በደንብ እንዲያጠኑ ይረዷቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 4:11, 12) በምሥክሮቹ ጉባኤዎች ውስጥ የዘር ጥላቻና የመደብ ልዩነት ቦታ የሌለው ከመሆኑም በላይ የቤተሰብን ሕይወት ለማጠናከሩ ጉዳይ ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ። (ሥራ 10:34, 35፤ ቆላስይስ 3:18-21) በመሆኑም ፀረ ቤተሰብ ናቸው ወይም ለማኅበረሰቡ ምንም እገዛ አያደርጉም የሚለው ክስ ሐሰት መሆኑን ድርጊታቸው ያረጋግጣል። በዚህ መንገድ ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት እውነት ሆነው ይገኛሉ:- “በጎ እያደረጋችሁ፣ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና።”—1 ጴጥሮስ 2:15
17. ክርስቲያኖች “በውጭ ባሉት ዘንድ በጥበብ” መመላለሳቸውን መቀጠል የሚችሉት እንዴት ነው?
17 ስለዚህ የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ‘የዓለም ክፍል ባይሆኑም’ የሚኖሩት በሰብዓዊ ኅብረተሰብ ዓለም ውስጥ በመሆኑ “በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ” መመላለሳቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 17:16፤ ቆላስይስ 4:5) ይሖዋ የበላይ ባለ ሥልጣኖች የእርሱ አገልጋዮች ሆነው መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ እስከፈቀደላቸው ድረስ ለእነርሱ ተገቢውን አክብሮት እናሳያለን። (ሮሜ 13:1-4) ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኞች ብንሆንም በተለይ የአምልኮ ነፃነትን ሊነካ የሚችል ውሳኔ ማድረግ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ “ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ” እንጸልያለን። ‘ሁሉም ዓይነት ሰዎች ይድኑ’ ዘንድ “እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር” እንዲህ ማድረጋችንን እንቀጥላለን።—1 ጢሞቴዎስ 2:1-4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 35 ተመልከት።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ ክርስቲያኖች የየትኛው “ዓለም” ክፍል ናቸው? የየትኛውስ “ዓለም” ክፍል ሊሆኑ አይችሉም?
◻ “የአውሬውን” “ምልክት” በእጅ ወይም በግንባር ላይ መቀበል ምን ትርጉም አለው? የይሖዋ የታመኑ አገልጋዮችስ ምን ምልክቶች አሏቸው?
◻ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰብዓዊ መንግሥታትን በሚመለከት ምን ሚዛናዊ አመለካከት አላቸው?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች ለሰብዓዊው ኅብረተሰብ ደህንነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
መጽሐፍ ቅዱስ ሰብዓዊ መንግሥታትን እንደ አምላክ አገልጋይም እንደ አውሬም አድርጎ ይገልጻቸዋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳዩ በመሆናቸው ለማኅበረሰባቸው ጠቃሚ ሀብት ናቸው