የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • አምላክና ቄሣር
    መጠበቂያ ግንብ—1996 | ግንቦት 1
    • 11. ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከዓለማዊ ገዥዎች ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ግንኙነት በተመለከተ ምን ብሎ መክሯቸዋል?

      11 ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስ ከሞተ ከ20 ዓመት በኋላ በሮም ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ” ብሏቸዋል። (ሮሜ 13:1) ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ ጳውሎስ ሮም ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ታስሮ ከመገደሉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለቲቶ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፣ ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ [የቀርጤስ ክርስቲያኖችን] አሳስባቸው።”—ቲቶ 3:1, 2

      የ“በላይ ባለ ሥልጣኖች” ማን መሆናቸውን ደረጃ በደረጃ መረዳት

      12. (ሀ) ቻርልስ ቴዝ ራስል አንድ ክርስቲያን ከመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ሊኖረው የሚገባውን ትክክለኛ አቋም በተመለከተ ምን አመለካከት ነበረው? (ለ) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በጦር ሠራዊት ውስጥ ማገልገልን በተመለከተ ምን የተለያየ አመለካከት ነበራቸው?

      12 ገና በ1886 ቻርልስ ቴዝ ራስል ዘ ፕላን ኦቭ ዘ ኤጅስ (የዘመናት ቅያስ) በተባለው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፦ “ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያት ለምድራዊ ገዥዎች በምንም መንገድ እንቅፋት አልሆኑም። . . . ቤተ ክርስቲያን ሕጎችን እንድታከብር፣ ባለ ሥልጣኖችንም በያዙት የሥልጣን ቦታ የተነሣ እንድታከብር፣ . . . የሚገባቸውን ቀረጥ እንድትከፍልና ከአምላክ ሕግጋት ጋር የሚቃረን እስካልሆነ ድረስ (ሥራ 4:19፤ 5:29) የትኛውንም ሕግ ለመቀበል አሻፈረኝ ማለት እንደሌለባት አስተምረዋል። (ሮሜ 13:1-7፤ ማቴ. 22:21) ኢየሱስና ሐዋርያት እንዲሁም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳ ከዚህ ዓለም መንግሥታት ጉዳዮች ገለልተኞች የነበሩና በእነዚህ ጉዳዮች ፈጽሞ ያልተሳተፉ ቢሆንም ሁሉም ሕግ አክባሪዎች ነበሩ።” ይህ መጽሐፍ ሐዋርያው ጳውሎስ የጠቀሳቸው የ“በላይ ባለ ሥልጣኖች” ሰብዓዊ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች እንደሆኑ በትክክል አመልክቶ ነበር። (ሮሜ 13:1) በ1904 ዘ ኒው ክሪኤሽን (አዲስ ፍጥረት) የተባለው መጽሐፍ እውነተኛ ክርስቲያኖች “በዘመናችን በሕግ አክባሪነታቸው የላቀ ደረጃ ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆን እንዳለባቸውና የለውጥ አራማጆች፣ ጠበኞችና እንከን ፈላጊዎች መሆን እንደሌለባቸው” ገልጾ ነበር። አንዳንዶች ይህ ማለት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጦር ሠራዊቶች ውስጥ አገልግሎት እስከ መስጠት ደረጃ ድረስ ለመንግሥት ሙሉ በሙሉ መገዛት ማለት እንደሆነ አድርገው ተረድተው ነበር። ይሁን እንጂ ሌሎች ይህ ድርጊት ኢየሱስ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ሲል ከተናገረው አባባል ጋር ይጋጫል የሚል አመለካከት አድሮባቸው ነበር። (ማቴዎስ 26:52) ክርስቲያኖች ለበላይ ባለ ሥልጣኖች የሚያሳዩትን ተገዥነት በተመለከተ የተሰጠውን ሐሳብ ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ መረዳት ያስፈልግ እንደነበረ ከሁኔታው መገንዘብ ይቻላል።

      13. በ1929 የበላይ ባለ ሥልጣኖችን ማንነት በተመለከተ በነበረው አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ተደርጎ ነበር? ይህ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

      13 በ1929፣ የተለያዩ መንግሥታት አምላክ ያዘዛቸውን ነገሮች የሚከለክሉ ወይም የአምላክ ሕጎች የሚከለክሏቸውን ነገሮች እንዲደረጉ የሚያዙ ሕጎችን ማውጣት በጀመሩበት ወቅት የበላይ ባለ ሥልጣኖች የተባሉት ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን አለባቸው ተባለ።b ይህም የይሖዋ አገልጋዮች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊትና ጦርነቱ ይካሄድ በነበረበት ቀውጢ ወቅት እንዲሁም እርስ በርስ ተፈራርቶ የመኖርና የወታደራዊ ዝግጁነት መርሆ ያራምድ በነበረው በቀዝቃዛው ጦርነት መጀመሪያ ላይ የነበራቸው አመለካከት ነበር። ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት የይሖዋንና የክርስቶስን የበላይነት ከፍ ከፍ ያደረገው ይህ አመለካከት በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት በሙሉ የአምላክ ሕዝቦች የገለልተኝነት አቋማቸውን አጥብቀው እንደያዙ ለመቀጠል እንደረዳቸው መገንዘብ እንችላለን።

      አንፃራዊ ተገዥነት

      14. በ1962 በሮሜ 13:1, 2 እና ከዚህ ጋር በተያያዙ ሌሎች ጥቅሶች ላይ ተጨማሪ የእውቀት ብርሃን የፈነጠቀው እንዴት ነው?

      14 በ1961 የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ተተርጉሞ አለቀ። የትርጉም ሥራው ቅዱሳን ጽሑፎች የተጻፉበትን ሥነ ጽሑፋዊ ቋንቋ በጥልቀት መመርመርን የሚጠይቅ ነበር። በሮሜ ምዕራፍ 13 ላይ ብቻ ሳይሆን በቲቶ 3:1, 2 እና በ1 ጴጥሮስ 2:13, 17 ምንባቦች ላይ ያሉት ቃላት በትክክል በመተርጎማቸው የ“በላይ ባለ ሥልጣኖች” የሚለው አነጋገር የሁሉ የበላይ ባለ ሥልጣን የሆነውን ይሖዋንና ልጁን ኢየሱስን ሳይሆን ሰብዓዊ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችን የሚያመለክት እንደሆነ መረዳት ተችሏል። በ1962 መገባደጃ ላይ የሮሜ ምዕራፍ 13ን ትክክለኛ ማብራሪያ የያዙና በሲ ቲ ራስል ዘመን ከነበረው ይበልጥ ግልጽ የሆነ አመለካከት የሠፈረባቸው የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶች ወጡ። እነዚህ ርዕሶች ክርስቲያኖች ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙት ፍጹም በተሟላ መንገድ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። አንፃራዊ መሆን አለበት፤ የአምላክ አገልጋዮች ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙት ከአምላክ ሕጎች ጋር የሚያጋጫቸው እስካልሆነ ድረስ ብቻ ነው። በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡ ሌሎች ርዕሶችም ይህን አስፈላጊ ነጥብ ጠበቅ አድርገው ገልጸውታል።c

      15, 16. (ሀ) ሮሜ ምዕራፍ 13ን በተመለከተ የተገኘው አዲስ እውቀት ምን የተሻለ ሚዛናዊ አመለካከት አስገኝቷል? (ለ) መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?

      15 ሮሜ ምዕራፍ 13ን በትክክል ለመረዳት ቁልፍ ሆኖ ያገለገለው ይህ ማብራሪያ የይሖዋ ሕዝቦች በቅዱስ ጽሑፉ ላይ ለሰፈሩት ወሳኝ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸውን አቋም ሳያላሉ ለፖለቲካ ባለ ሥልጣኖች ሚዛናዊ የሆነ አክብሮት እንዲሰጡ አስችሏቸዋል። (መዝሙር 97:11፤ ኤርምያስ 3:15) ከአምላክ ጋር ስላላቸው ዝምድናና ከመንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል። የቄሣርን ለቄሣር ሲያስረክቡ የአምላክን ለአምላክ የማስረከብ ኃላፊነታቸውን ችላ እንዳይሉ አድርጓቸዋል።

  • አምላክና ቄሣር
    መጠበቂያ ግንብ—1996 | ግንቦት 1
    • ፕሮፌሰር ኤፍ ኤፍ ብሩስ ሮሜ ምዕራፍ 13ን ሲያብራሩ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በዚህ ምዕራፍ ዙሪያ ያለው ሐሳብና ከዚህ ጋር ዝምድና ያላቸው የሐዋርያት ጽሑፎች የያዙት ሐሳብ እንደሚያሳዩት መንግሥት የማዘዝ መብት ያለው በመለኮታዊ ፈቃድ ከተቋቋመበት ዓላማ ጋር በሚያያዙ ጉዳዮች ረገድ ብቻ ነው። በተለይ መንግሥት ለአምላክ ብቻ ሊሰጥ የሚገባውን የታማኝነት አቋም ለራሱ በሚጠይቅበት ጊዜ ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል፤ ደግሞም ሊገጥመው ይገባል።”

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ