ጽናት
ሃይፖሜኖ የተባለው የግሪክኛ ግስ ቃል በቃል ሲተረጎም “እዚያው መቅረት ወይም ባሉበት መቆየት” ማለት ሲሆን በሉቃስ 2:43 እና በሥራ 17:14 ላይ “ቀረ” ተብሎ ተተርጉሟል። በተጨማሪም “ከአቋም ፍንክች አለማለትን፣ በአቋም መጽናትንና አለማወላወልን” የሚያመለክት ትርጉምም ስላለው ‘ጽናት’ ተብሎ ተተርጉሟል። (ማቴ 24:13) ሃይፖሜነ የተባለው ስም አብዛኛውን ጊዜ እንቅፋት፣ ስደት ወይም ፈተና ሲያጋጥም ተስፋ ሳይቆርጡ በድፍረት፣ በቆራጥነት ወይም በትዕግሥት “መጽናትን” ያመለክታል።
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች ከሚያጋጥሟቸው ነገሮች መካከል የሰዎች ግድ የለሽነት፣ ስድብ፣ ስም ማጥፋት፣ የከረረ ጥላቻ፣ ከቅርብ የቤተሰብ አባላት የሚደርስ ተቃውሞ፣ ግፍና እስራት ሌላው ቀርቶ ሞት ይገኙበታል። (ማቴ 5:10-12፤ 10:16-22፤ 24:9, 10, 39፤ ማር 13:9, 12, 13፤ ራእይ 13:10) እነዚህ ነገሮች ደግሞ ጽናት የሚጠይቁ ናቸው። አንድ ሰው ይህ በጣም አስፈላጊ ባሕርይ ከሌለው የዘላለም ሕይወት ሊያገኝ አይችልም። (ሮም 2:7፣ ዕብ 10:36፣ ራእይ 14:12) ምክንያቱም በአንድ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የደቀ መዝሙርነት ሕይወቱን መጀመሩ ሳይሆን እስከ መጨረሻው መጽናቱ ነው። ኢየሱስ እንዳለው “እስከ መጨረሻው የጸና ግን ይድናል።” (ማቴ 24:13) “ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ።”—ሉቃስ 21:19
‘የአምላክን ቃል’ ቶሎ ቢቀበሉም በውስጣቸው ሥር የማይሰድ ሰዎች ጽናት ይጎድላቸዋል። ብዙ ሳይቆይ መከራና ስደት ሲደርስባቸው ስለሚተዉት የአምላክን ሞገስና በረከት ያጣሉ። ‘ለአምላክ ቃል’ ጥልቅ የሆነ አድናቆት የሚያዳብሩ ግን ጸንተው ይቆማሉ። የሚደርስባቸውን መከራ፣ ችግርና ተስፋ አስቆራጭ ነገር ተቋቁመው የአምላክን መልእክት በታማኝነት ማወጃቸውን ስለሚቀጥሉ “በጽናት ፍሬ” ያፈራሉ።—ሉቃስ 8:11, 13, 15
ማዳበር የሚቻልበት መንገድ። እንደ ኢዮብ ያሉ ከክርስትና ዘመን በፊት የኖሩት ነቢያት እንዲሁም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስና ዮሐንስ ያሉ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች የተዉትን ጥሩ ምሳሌነት ማሰብና ታማኝ መሆናቸው ባስገኘላቸው ውጤት ላይ ማሰላሰል፣ መከራ በሚደርስብን ጊዜ ጸንተን እንድንቆም ያነሳሳናል። (2ቆሮ 6:3-10፤ 12:12፤ 2ተሰ 1:4፤ 2ጢሞ 3:10-12፤ ያዕ 5:10, 11፤ ራእይ 1:9) በተለይ ምንም እንከን ያልተገኘበት ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን ጽናት ምንጊዜም በትኩረት መመልከት ይኖርብናል።—ዕብ 12:2, 3፤ 1ጴጥ 2:19-24
በተጨማሪም ክርስቲያናዊ ተስፋችን ማለትም ከኃጢአት ተላቅቀን ለዘላለም የመኖር ተስፋችን ሁልጊዜ እንዲታየን ማድረግ አስፈላጊ ነው። አሳዳጆቻችን ቢገድሉን እንኳ ይህን ተስፋ ሊያሳጡን አይችሉም። (ሮም 5:4, 5፤ 1ተሰ 1:3፤ ራእይ 2:10) በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን መከራ ከዚህ ታላቅ ተስፋ ፍጻሜ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። (ሮም 8:18-25) ማንኛውም መከራ በወቅቱ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ከዘላለማዊነት ጋር ሲወዳደር “ጊዜያዊና ቀላል” ነው። (2ቆሮ 4:16-18) አንድ ሰው ፈተናዎች ጊዜያዊ መሆናቸውን ማሰቡና ክርስቲያናዊ ተስፋውን አጥብቆ መያዙ ተስፋ ቆርጦ ለይሖዋ አምላክ ያለውን ታማኝነት እንዳያጓድል ይጠብቀዋል።
አንድ ሰው በክርስትና ጎዳና ላይ በጽናት መጓዝ የሚችለው በራሱ ጥንካሬ ብቻ አይደለም። በመንፈሱና ከቅዱሳን መጻሕፍት በሚገኘው ማጽናኛ አገልጋዮቹን የሚያቆመውና የሚያበረታው ልዑሉ አምላክ ነው። አምላክ በእሱ ሙሉ በሙሉ ለሚታመኑ ሁሉ ‘ጽናት ይሰጣል።’ በመሆኑም ክርስቲያኖች አምላክ እንዲረዳቸውና የደረሰባቸውን መከራ እንዲወጡ የሚያስችላቸውን ጥበብ እንዲሰጣቸው መጸለይ ይችላሉ። (ሮም 15:4, 5፤ ያዕ 1:5) ማንም ሰው ሊወጣው የማይችለው ፈተና እንዲደርስበት ይሖዋ ፈጽሞ አይፈቅድም። አንድ ሰው የአምላክን እርዳታ ከጠየቀ እንዲሁም እምነት ሳያጣ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ የሚታመን ከሆነ ሁሉን የሚችለው አምላክ መጽናት እንዲችል መውጫ ያዘጋጅለታል።—1ቆሮ 10:13፤ 2ቆሮ 4:9
ክርስቲያኖች በመከራ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ሊያገኙ የሚችሉት ኃይል ገደብ የለሽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት እንድትቋቋሙ የአምላክ ታላቅ ኃይል የሚያስፈልጋችሁን ብርታት ሁሉ ይስጣችሁ” ሲል ጸልዮአል። (ቆላ 1:11) ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳቱና ከፍ ከፍ ብሎ በአብ ቀኝ መቀመጡ ይህ “ታላቅ ኃይል” የታየበት አንድ ምሳሌ ነው።—ኤፌ 1:19-21
ይሖዋ አምላክና ልጁ ሁላችንም እንዲሳካልን ይፈልጋሉ። ይህንንም ኢየሱስ ክርስቶስ በኤፌሶን፣ በሰምርኔስ፣ በጴርጋሞን፣ በትያጥሮን በሰርዴስ፣ በፊላደልፊያና በሎዶቅያ ለነበሩት የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ስለ መጽናት ከሰጠው ማበረታቻ መመልከት ይቻላል።—ራእይ 2:1-3, 8-10, 12, 13, 18, 19፤ 3:4, 5, 7, 10, 11, 14, 19-21
ስለ ፈተናዎች ትክክለኛ አመለካከት መያዝ። ክርስቲያኖች የዘላለም ሕይወት ማግኘት አለማግኘታቸው የተመካው በሚያሳዩት ጽናት እንደሆነ ስለሚያውቁ እንዲሁም ከአምላክ እርዳታ እንደሚያገኙ እርግጠኛ ስለሆኑ ፈተናና መከራ ሲደርስባቸው አይደናገጡም፤ እንዲሁም በትካዜ ከመዋጥ፣ ከማማረር፣ ወይም ከማጉረምረም ይርቃሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመከራ ውስጥ እያለንም እጅግ እንደሰት፤ ምክንያቱም መከራ ጽናትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ሮም 5:3) አንድ ክርስቲያን ፈተና ሲያጋጥመው በትዕግሥትና በሚያገኘው መለኮታዊ እርዳታ አማካኝነት በአቋሙ ሲጸና አንድ አስፈላጊ ባሕርይ ማለትም ጽናት እንዳለው ያሳያል፤ አንድ ሰው በመከራ ውስጥ ሳያልፍ ጽናት እንዳለው በትክክል ሊታወቅ አይችልም።
አንድ ሰው መከራ ሲደርስበት ከፈተናው ቶሎ ለመገላገል ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ አቋራጭ መንገዶችን ከመጠቀም ይልቅ ጽናት “ሥራውን ሙሉ በሙሉ” እንዲፈጽም መፍቀድ ይኖርበታል። በዚህ መንገድ እምነት የሚፈተንና የሚጣራ ከመሆኑም በላይ ጥንካሬው ይታያል። አንድ ክርስቲያን ያሉበት ድክመቶች በግልጽ እንዲታዩትና ጉድለቶቹን አስመልክቶ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ የሚያስችል አቋም እንዲኖረው ይረዳዋል። አንድ ሰው ፈተናዎችን በታማኝነትና በጽናት ማለፉ ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ይበልጥ ትዕግሥተኛ፣ አዛኝ፣ ሩኅሩኅ፣ ደግና አፍቃሪ እንዲሆን በማድረግ ባሕርይውን ይቀርጸዋል። ስለዚህ አንድ ሰው ጽናት “ሥራውን ሙሉ በሙሉ” እንዲፈጽም በመፍቀድ ይሖዋ አምላክ ከአገልጋዮቹ የሚፈልገውን ነገር በሟሟላት ረገድ ‘ምንም የማይጎድለው’ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።—ያዕ 1:2-4