-
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
7. የአምላክ መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሩት ከየትኛውም መንግሥት የላቁ ሕጎች አሉት
መንግሥታት ለዜጎቻቸው ጥቅምና ጥበቃ ያስገኛሉ ብለው የሚያስቧቸውን ሕጎች ያወጣሉ። የአምላክ መንግሥትም ተገዢዎቹ ሊያከብሯቸው የሚገቡ ሕጎች አሉት። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ሁሉም ሰው አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር ደንቦች ቢከተል ዓለማችን ምን መልክ የሚኖራት ይመስልሃል?a
ይሖዋ የመንግሥቱ ተገዢዎች እነዚህን ሕጎች እንዲያከብሩ መጠበቁ ምክንያታዊ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
እነዚህን ሕጎች የማይታዘዙ ሰዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?—ቁጥር 11ን ተመልከት።
መንግሥታት ለዜጎቻቸው ጥበቃና ጥቅም የሚያስገኙ የተለያዩ ሕጎችን ያወጣሉ። የአምላክ መንግሥት ለተገዢዎቹ ጥበቃና ጥቅም የሚያስገኙ የላቁ ሕጎች አሉት
-
-
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ይላል?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 41
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ይላል?
ብዙ ሰዎች ስለ ፆታ ግንኙነት ማውራት ይከብዳቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ ሆኖም ጨዋነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ይናገራል። የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ እኛን የሚጠቅም መረጃ ይዟል። ይህ መሆኑ አያስገርምም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን ይሖዋ ያጻፈው መጽሐፍ ነው። ይሖዋ ደግሞ ለእኛ የተሻለውን ነገር ያውቃል። እሱን ለማስደሰትና ለዘላለም በደስታ ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል።
1. ይሖዋ ለፆታ ግንኙነት ምን አመለካከት አለው?
የፆታ ግንኙነት ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ ነው። ይሖዋ ትዳር የመሠረቱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ደስታ እንዲያገኙ ይፈልጋል። ይህ ስጦታ ባለትዳሮች ልጆች እንዲወልዱ ብቻ ሳይሆን አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ተፈጥሯዊ በሆነና እርካታ በሚያስገኝ መንገድ እንዲገልጹ ያስችላቸዋል። የአምላክ ቃል “ከወጣትነት ሚስትህ . . . ጋር ደስ ይበልህ” የሚለው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 5:18, 19) ይሖዋ ትዳር የመሠረቱ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ እንዲሆኑ ይፈልጋል፤ በመሆኑም ባለትዳሮች ምንዝር ከመፈጸም ሊርቁ ይገባል።—ዕብራውያን 13:4ን አንብብ።
2. የፆታ ብልግና ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሴሰኞች [የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች] የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ’ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የፆታ ብልግናን ለመግለጽ ፖርኒያ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅመዋል። ይህ ቃል (1) ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነትa (2) ግብረ ሰዶምን እና (3) ከእንስሳት ጋር የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት ያካትታል። ‘ከፆታ ብልግና መራቃችን’ ይሖዋን የሚያስደስት ከመሆኑም ሌላ እኛንም ይጠቅመናል።—1 ተሰሎንቄ 4:3
ጠለቅ ያለ ጥናት
ከፆታ ብልግና መራቅ የምትችለው እንዴት እንደሆነና የሥነ ምግባር ንጽሕናህን መጠበቅህ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልህ እንመለከታለን።
3. ከፆታ ብልግና ሽሽ
ዮሴፍ የተባለ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የሥነ ምግባር ንጽሕናውን ለመጠበቅ ብዙ ትግል አድርጓል። ዘፍጥረት 39:1-12ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ዮሴፍ የሸሸው ለምንድን ነው?—ቁጥር 9ን ተመልከት።
ዮሴፍ ያደረገው ነገር ትክክል ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የዮሴፍን ምሳሌ በመከተል ከፆታ ብልግና መሸሽ የሚችሉት እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ።
ይሖዋ ሁላችንም ከፆታ ብልግና እንድንርቅ ይፈልጋል። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:18ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
የፆታ ብልግና ወደመፈጸም ሊመሩ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?
ከፆታ ብልግና መሸሽ የምትችለው እንዴት ነው?
4. ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ትችላለህ
የፆታ ብልግና እንድንፈጽም የሚደረግብንን ጫና መቋቋም ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ የታየው ወንድም፣ የሚያስባቸውና የሚያደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች ለባለቤቱ ያለውን ታማኝነት እንዲያጓድል ሊያደርጉት እንደሚችሉ ሲገነዘብ ምን አደረገ?
ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ አስተሳሰባቸው ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን ለማድረግ መታገል ሊያስፈልጋቸው ይችላል። የብልግና ሐሳቦችን እንዳታውጠነጥን ምን ይረዳሃል? ፊልጵስዩስ 4:8ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ስለ ምን ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል?
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና በይሖዋ አገልግሎት በትጋት መካፈላችን ኃጢአት ለመፈጸም ስንፈተን የሚረዳን እንዴት ነው?
5. ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መከተላችን ይጠቅመናል
ይሖዋ ለእኛ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነና እንዲህ ማድረጋችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን ገልጾልናል። ምሳሌ 7:7-27ን አንብቡ ወይም ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ወጣት ራሱን ፈተና ውስጥ ያስገባው እንዴት ነው?—ምሳሌ 7:8, 9ን ተመልከት።
ምሳሌ 7:23, 26 ላይ እንደተገለጸው የፆታ ብልግና መፈጸም አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቃችን ከየትኞቹ ችግሮች ያድነናል?
የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቃችን ለዘላለም በደስታ ለመኖር የሚያስችለን እንዴት ነው?
አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን አስመልክቶ የሚናገረው ሐሳብ ፍቅር የጎደለው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ሁሉም ሰው ለዘላለም በደስታ እንዲኖር ይፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር አለብን። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በዚህ ጥቅስ መሠረት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ግብረ ሰዶም ብቻ ነው?
አምላክን ለማስደሰት ሁላችንም የተለያዩ ለውጦች ማድረግ ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ የምናደርገው ጥረት የሚያስቆጭ ነው? መዝሙር 19:8, 11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ ያወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምክንያታዊ ወይም ተገቢ ይመስሉሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ይሖዋ ብዙዎች እሱ ካወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር እንዲችሉ ረድቷል። አንተንም ሊረዳህ ይችላል
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ማንም ሰው ከፈለገው ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይችላል። ዋናው ነገር መዋደዳቸው ነው።”
አንተ ምን ትላለህ?
ማጠቃለያ
የፆታ ግንኙነት ትዳር በመሠረቱ ወንድና ሴት መካከል ብቻ ሊፈጸም የሚገባ የይሖዋ ስጦታ ነው።
ክለሳ
የፆታ ብልግና ምን ነገሮችን ያካትታል?
ከፆታ ብልግና እንድንርቅ ምን ይረዳናል?
ይሖዋ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
ምርምር አድርግ
አምላክ አብረው መኖር የሚፈልጉ ወንድና ሴት ትዳር እንዲመሠርቱ የሚፈልገው ለምንድን ነው?
“መጽሐፍ ቅዱስ ሳይጋቡ አብሮ መኖርን በተመለከተ ምን ይላል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም የሚያስተምረው ትምህርት ጥላቻን የሚያስፋፋ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
አምላክ ከማንኛውም ዓይነት የፆታ ብልግና ጋር በተያያዘ ያወጣው ሕግ ጥበቃ የሚያስገኝልን እንዴት ነው?
“የያዙኝ በአክብሮት ነበር” የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ ግብረ ሰዶማዊ የነበረ አንድ ሰው አምላክን ለማስደሰት ሲል አኗኗሩን እንዲቀይር ያነሳሳው ምን እንደሆነ ተመልከት።
a በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የፆታ ግንኙነት በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ ግንኙነትን፣ የሌላን ግለሰብ የፆታ ብልት ማሻሸትንና እንዲህ የመሳሰሉ ሌሎች ድርጊቶችን ያካትታል።
-
-
ከባድ ኃጢአት ብትፈጽም ምን ማድረግ ይኖርብሃል?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ይሖዋን ከልብ የምትወድና እሱን ላለማሳዘን የቻልከውን ያህል ጥረት የምታደርግ ቢሆንም አልፎ አልፎ ስህተት መሥራትህ አይቀርም። ይሁንና አንዳንድ ስህተቶች ከሌሎቹ የበለጠ ክብደት አላቸው። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ከባድ ኃጢአት ከፈጸምክ ይሖዋ ለአንተ ያለው ፍቅር እንደማይለወጥ እንዲሁም ይቅር ሊልህና ሊረዳህ ፈቃደኛ እንደሆነ አስታውስ።
1. ይሖዋ ይቅር እንዲለን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ከባድ ኃጢአት እንደፈጸሙ ሲገነዘቡ ከልብ እንደሚያዝኑ የታወቀ ነው። ይሁንና ይሖዋ ለሕዝቡ የገባውን ቃል ማስታወሳቸው ያጽናናቸዋል። ይሖዋ “ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል” ብሏል። (ኢሳይያስ 1:18) ከልባችን ንስሐ ከገባን ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር ይለናል። ንስሐ እንደገባን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በፈጸምነው ኃጢአት ከልብ ማዘን፣ መጥፎ ድርጊታችንን ማቆምና ይሖዋ ይቅር እንዲለን መለመን ይኖርብናል። ከዚያም ኃጢአት ወደመፈጸም የመራንን የተሳሳተ አስተሳሰብ ወይም ልማድ ለማስወገድ እንዲሁም ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው።—ኢሳይያስ 55:6, 7ን አንብብ።
2. ኃጢአት ስንሠራ ይሖዋ በሽማግሌዎች አማካኝነት የሚረዳን እንዴት ነው?
ይሖዋ ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን ‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንድንጠራ’ ነግሮናል። (ያዕቆብ 5:14, 15ን አንብብ።) እነዚህ የተሾሙ ወንዶች ይሖዋንና ሕዝቦቹን ይወዳሉ። በተጨማሪም ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ማደስ እንዲችሉ ለመርዳት በቂ ሥልጠና አግኝተዋል።—ገላትያ 6:1
ከባድ ኃጢአት ስንፈጽም ሽማግሌዎች የሚረዱን እንዴት ነው? ሁለት ወይም ሦስት ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው እርማት ይሰጡናል። በተጨማሪም ዳግመኛ ኃጢአት ከመፈጸም እንድንርቅ የሚረዳ ጠቃሚ ሐሳብ ወይም ማበረታቻ ያካፍሉናል። ሽማግሌዎች ጉባኤውን ከጎጂ ተጽዕኖ ለመጠበቅ ሲሉ፣ ከባድ ኃጢአት ፈጽመው ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ከጉባኤው እንዲወገዱ ያደርጋሉ።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ከባድ ኃጢአት ስንፈጽም ይሖዋ ስለሚሰጠን እርዳታ ያለህን ግንዛቤና አድናቆት እንድታሳድግ የሚረዳ ሐሳብ እንመለከታለን።
3. ኃጢአታችንን መናዘዛችን ፈውስ እንድናገኝ ይረዳናል
ማንኛውንም ኃጢአት ስንፈጽም ይሖዋን ስለምናሳዝን ኃጢአታችንን ለእሱ መናዘዛችን ተገቢ ነው። መዝሙር 32:1-5ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
የፈጸምነውን ኃጢአት ከመሸፋፈን ይልቅ ለይሖዋ መናዘዛችን የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?
ኃጢአታችንን ለይሖዋ ከመናዘዝ በተጨማሪ የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቃችን እረፍት ያስገኝልናል። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ ሽማግሌዎች ካነንን ወደ ይሖዋ እንዲመለስ የረዱት እንዴት ነው?
የፈጸምነውን ኃጢአት ለሽማግሌዎች በግልጽና በሐቀኝነት መናገራችን አስፈላጊ ነው፤ ዋነኛ ዓላማቸው እኛን መርዳት ነው። ያዕቆብ 5:16ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ሐቀኛ መሆናችን ሽማግሌዎች እኛን መርዳት ቀላል እንዲሆንላቸው የሚያደርገው እንዴት ነው?
ኃጢአትህን ተናዘዝ፣ ለሽማግሌዎች በሐቀኝነት ተናገር እንዲሁም ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የሚያደርግልህን እርዳታ ተቀበል
4. ይሖዋ ለኃጢአተኞች ምሕረት ያደርጋል
ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ፈቃደኛ ካልሆነ ከጉባኤው ይወገዳል። እንዲህ ካለው ሰው ጋር ጊዜ አናሳልፍም። አንደኛ ቆሮንቶስ 5:6, 11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው ሁሉ ንስሐ ከማይገባ ኃጢአተኛ ጋር ጊዜ ማሳለፍም በጉባኤ ውስጥ ባሉት ላይ ምን ጉዳት ይኖረዋል?
ይሖዋ ፍጹም ላልሆኑ ኃጢአተኞች ምሕረት ያሳያል፤ ሽማግሌዎችም ከጉባኤ የተወገዱትን ለመርዳት ጥረት በማድረግ የእሱን ምሳሌ ይከተላሉ። ብዙዎች የተሰጣቸው ተግሣጽ ቢያሳዝናቸውም ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ስለረዳቸው ወደ ጉባኤው ተመልሰዋል።—መዝሙር 141:5
• ይሖዋ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችን የሚይዝበት መንገድ ፍትሐዊ፣ መሐሪና አፍቃሪ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
5. ንስሐ ከገባን ይሖዋ ይቅር ይለናል
ኢየሱስ፣ ይሖዋ ንስሐ ለገባ ኃጢአተኛ ያለውን አመለካከት የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሯል። ሉቃስ 15:1-7ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይህ ጥቅስ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምርሃል?
ሕዝቅኤል 33:11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ንስሐ መግባት የትኛውን አስፈላጊ እርምጃ መውሰድን ይጨምራል?
ልክ እንደ አንድ እረኛ ይሖዋም ለበጎቹ ከልብ ያስባል
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “የፈጸምኩትን ኃጢአት ለሽማግሌዎች ብናገር ከጉባኤ እወገዳለሁ ብዬ እፈራለሁ።”
እንዲህ ለሚሰማው ሰው ምን ልትለው ትችላለህ?
ማጠቃለያ
ከባድ ኃጢአት ስንፈጽም ከልባችን ካዘንን እና መጥፎ ድርጊታችንን ለመተው ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን ይሖዋ ይቅር ይለናል።
ክለሳ
ኃጢአታችንን ለይሖዋ መናዘዛችን ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?
ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲል ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን የሽማግሌዎችን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
ምርምር አድርግ
አንድ ሰው በኢሳይያስ 1:18 ላይ የተገለጸውን የይሖዋን ምሕረት በሕይወቱ ማየት የቻለው እንዴት ነው?
ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸሙትን የሚረዱት እንዴት ነው?
ሽማግሌዎች ንስሐ ላልገቡ ኃጢአተኞች ፍቅርና ምሕረት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
“ወደ ይሖዋ መመለስ ነበረብኝ” የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ ከእውነት ርቆ የነበረ አንድ ሰው ይሖዋ ወደ ራሱ መልሶ እንደሳበው የተሰማው ለምን እንደሆነ ተመልከት።
-