የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bsi08-1 ገጽ 20-22
  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 46—1 ቆሮንቶስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 46—1 ቆሮንቶስ
  • “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 16
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
“ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 16
bsi08-1 ገጽ 20-22

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 46​—⁠1 ቆሮንቶስ

ጸሐፊው:- ጳውሎስ

የተጻፈበት ቦታ:- ኤፌሶን

ተጽፎ ያለቀው:- በ55 ከክ.ል.በኋላ ገደማ

ቆሮንቶስ “የምሥራቁና የምዕራቡ ዓለም የብልግና መናኸሪያ የሆነች ስመ ጥር የፈንጠዝያ ከተማ” ነበረች።a ግሪክን በደቡብ በኩል ከሚገኘው ባሕረ ገብ መሬት ጋር በሚያገናኘው ጠባብ ምድር ላይ የምትገኘው የቆሮንቶስ ከተማ ወደ አሕጉሩ በሚወስደው ቁልፍ ቦታ ላይ ነበረች። በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን የከተማዋ ሕዝብ ብዛት ወደ 400,000 የሚጠጋ ሲሆን ከዚህ የሚበልጥ የሕዝብ ቁጥር የነበራቸው ሮም፣ እስክንድርያና በሶርያ የምትገኘው አንጾኪያ ብቻ ነበሩ። ከቆሮንቶስ በስተ ምሥራቅ የኤጂያን ባሕር፣ በስተ ምዕራብ ደግሞ የቆሮንቶስ ባሕረ ሰላጤና የአዮኒያን ባሕር ይገኛሉ። ስለዚህ የአካይያ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውና ክንክራኦስና ሊቆንየም የተባሉ ሁለት ወደቦች ያሏት ቆሮንቶስ የምትገኘው ለንግድ አመቺ በሆነ ቦታ ላይ ነበር። በተጨማሪም የግሪካውያን ትምህርት ማዕከል ነበረች። “የከተማዋ ብልጽግና ገንኖ ይነገር የነበረ ሲሆን ነዋሪዎቿም በብልግናና በልቅ አኗኗራቸው በሰፊው የሚታወቁ ነበሩ።”b አረማዊ ከሆኑት የከተማዋ ሃይማኖታዊ ልማዶች መካከል (የሮሟ ቬኑስ አቻ የሆነችው) የአፍሮዳይት አምልኮ ይገኝበት ነበር። የሥጋን ፍላጎት ማርካት የሚለው መርሕ የተገኘው የቆሮንቶስ ሰዎች ሲያካሂዱት ከነበረው አምልኮ ነው።

2 ሐዋርያው ጳውሎስ በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ የተጓዘው ወደዚህች የበለጸገችና በሥነ ምግባር ያዘቀጠች የሮማውያን ታላቅ ከተማ ነበር። በዚያ በቆየበት አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በከተማዋ አንድ የክርስቲያን ጉባኤ ተቋቁሟል። (ሥራ 18:1-11) ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ለመጀመሪያ ጊዜ ለነገራቸው ለእነዚህ አማኞች ከፍተኛ ፍቅር ነበረው! ጳውሎስ ከእነሱ ጋር የነበረውን መንፈሳዊ ትስስር አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “ምንም እንኳ በዐሥር ሺህ የሚቈጠሩ ሞግዚቶች በክርስቶስ ቢኖሯችሁም፣ ብዙ አባቶች ግን የሏችሁም፤ በወንጌል አማካይነት በክርስቶስ ኢየሱስ ወልጄአችኋለሁና።”—1 ቆሮ. 4:15

3 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ደህንነት በጥልቅ ያስብ የነበረ መሆኑ በሦስተኛ የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት የመጀመሪያውን ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው አነሳስቶታል። ጳውሎስ ቆሮንቶስን ለቅቆ ከሄደ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። ጊዜው 55 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሲሆን ጳውሎስ ያለው በኤፌሶን ነው። ጳውሎስ በአንጻራዊ ሁኔታ አዲስ ከነበረው የቆሮንቶስ ጉባኤ አንድ መልስ የሚያሻው ደብዳቤ የደረሰው ይመስላል። ከዚህም በላይ የሰማቸው ነገሮች ረብሸውታል። (7:1፤ 1:11፤ 5:1፤ 11:18) ሐዋርያው በሰማው ነገር በጣም ከማዘኑ የተነሳ እስከ 7ኛው ምዕራፍ መክፈቻ ድረስ ጥያቄያቸውን ስለያዘው ደብዳቤ ምንም አልጠቀሰም። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙት ክርስቲያን ባልንጀሮቹ እንዲጽፍላቸው ያስገደደው ስላሉበት ሁኔታ የሰማው ነገር ነበር።

4 ይሁን እንጂ ጳውሎስ አንደኛ ቆሮንቶስን የጻፈው በኤፌሶን መሆኑን እንዴት እናውቃለን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሐዋርያው ደብዳቤውን ሲደመድም በላከው ሰላምታ ላይ አቂላንና ጵርስቅላን ጨምሮ ጠቅሷል። (16:19) የሐዋርያት ሥራ 18:18, 19 አቂላና ጵርስቅላ ከቆሮንቶስ ወደ ኤፌሶን ተዛውረው እንደነበር ይገልጻል። አቂላና ጵርስቅላ በኤፌሶን የነበሩ መሆናቸውና ጳውሎስ በአንደኛ ቆሮንቶስ መደምደሚያ በላከው ሰላምታ ላይ እነሱንም መጥቀሱ ደብዳቤውን የጻፈው በኤፌሶን ሳለ መሆኑን ያሳያል። ከዚህም በላይ በ1 ቆሮንቶስ 16:8 ላይ የሚገኘው “ነገር ግን እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቆያለሁ” የሚለው የጳውሎስ አነጋገር ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ለመሆን ያስችለናል። ስለዚህ ጳውሎስ አንደኛ ቆሮንቶስን የጻፈው ኤፌሶንን ለቅቆ ከመሄዱ ከጥቂት ጊዜ በፊት እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

5 አንደኛና ሁለተኛ ቆሮንቶስ ትክክለኛ ዘገባዎች መሆናቸው የሚያጠያይቅ አይደለም። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እነዚህን ደብዳቤዎች ጳውሎስ እንደጻፋቸውና ትክክል እንደሆኑ አምነው በመቀበል ከሌሎቹ መጻሕፍት መካከል አካተዋቸዋል። እንዲያውም አንደኛ ቆሮንቶስ በ95 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ከሮም ወደ ቆሮንቶስ በተላከ አንድ ደብዳቤ ላይ ቢያንስ ለስድስት ጊዜ ያህል በቀጥታና በተዘዋዋሪ እንደተጠቀሰና መጽሐፉ አንደኛ ቀለሜንጦስ ተብሎ ይጠራ እንደነበር ይነገርለታል። የደብዳቤው ጸሐፊ ስለ አንደኛ ቆሮንቶስ እንደሚናገር በሚያሳይ መንገድ “የተባረከውን ሐዋርያ የጳውሎስን መልእክት ተቀበሉ” ሲል አንባቢዎቹን አሳስቧል።c ሰማዕቱ ጀስቲን፣ አቴናጎራስ፣ ኢረኒየስና ተርቱሊያን ከአንደኛ ቆሮንቶስ በቀጥታ ጠቅሰው ጽፈዋል። አንደኛና ሁለተኛ ቆሮንቶስን የሚያካትቱት የጳውሎስ መልእክቶች “አንድ ላይ ተሰብስበው የታተሙት በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ” እንደነበር የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አለ።d

6 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ በቆሮንቶስ ጉባኤ የነበረውን ሁኔታ በቅርበት ለማወቅ ያስችለናል። እነዚህ ክርስቲያኖች ችግሮች ተጋርጠውባቸው ነበር፤ እንዲሁም መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ነበሯቸው። አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ሰዎችን መከተል በመጀመራቸው በጉባኤው ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር። እጅግ አሳፋሪ የሆነ የጾታ ብልግና ተፈጽሞ ነበር። አንዳንዶች የሚኖሩት በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ከማያምነው የትዳር ጓደኛቸው ጋር መኖራቸውን ይቀጥሉ ወይስ ይለያዩ? ለጣዖት የተሰዋ ሥጋ መብላትን በተመለከተስ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ሥጋውን መብላት ይችሉ ይሆን? የቆሮንቶስ ሰዎች የጌታ እራት በዓል አከባበርን ጨምሮ ስብሰባዎቻቸውን ስለሚያከናውኑበት መንገድ ምክር ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። ሴቶች በጉባኤ ውስጥ ያላቸው ቦታ ምን መሆን አለበት? ይባስ ብሎ በትንሣኤ የማያምኑ ሰዎችም በመካከላቸው ይገኙ ነበር። ያም ሆነ ይህ በርካታ ችግሮች ነበሩባቸው። ይሁንና የሐዋርያው ጳውሎስ ዋነኛ ትኩረት ያረፈው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን መንፈሳዊነት መልሶ በመገንባቱ ላይ ነበር።

7 በብልጽግናዋና ልቅ በሆነ ሥነ ምግባሯ በምትታወቀው በጥንቷ ቆሮንቶስ ከተማ በሚገኘው ጉባኤ ውስጥም ይሁን ከጉባኤ ውጭ የነበረው ሁኔታ ከጊዜያችን ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፋቸው ቁም ነገር ያዘሉ ምክሮች ትኩረታችንን ይስቡታል። ጳውሎስ የተናገራቸው ነገሮች ለዘመናችን ከፍተኛ ትርጉም ስላላቸው በቆሮንቶስ ለነበሩት የተወደዱ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ የጻፈውን የመጀመሪያ ደብዳቤ በጥሞና መመርመራችን በእርግጥም ጠቃሚ ነው። አሁን፣ በዚያን ወቅት የነበረውን ሁኔታ መለስ ብለህ ለመቃኘት ሞክር። ጳውሎስ በቀድሞዋ ቆሮንቶስ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያን ወንድሞቹ የጻፈው መልእክት ያለውን ጠቀሜታ ስንመረምር በትኩረት ተከታተል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችም ይህን አድርገው እንደነበር ጥርጥር የለውም።

ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት

23 ይህ የሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ በርካታ ጥቅሶችን የያዘ በመሆኑ ስለ እነዚህ ቅዱሳን መጽሐፍት ያለንን ግንዛቤ ለማስፋት እጅግ ይጠቅመናል። ጳውሎስ በአሥረኛው ምዕራፍ ላይ ሙሴ ይመራቸው የነበሩት እስራኤላውያን ከመንፈሳዊው ዓለት ማለትም ከክርስቶስ መጠጣታቸውን አመልክቷል። (1 ቆሮ. 10:4፤ ዘኍ. 20:11) በመቀጠልም እነዚህን እስራኤላውያን ምሳሌ አድርጎ በመጥቀስ ክፉ ምኞት ስለሚያስከትላቸው አስከፊ መዘዞች ከተናገረ በኋላ “ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ” ብሏል። መቼም ቢሆን ፈጽሞ አንወድቅም ብለን በማሰብ በራሳችን አንመካ! (1 ቆሮ. 10:11, 12፤ ዘኍ. 14:2፤ 21:5፤ 25:9) ጳውሎስ እንደገና ከሕጉ አንድ ምሳሌ ጠቀሰ። በእስራኤል ይቀርብ ስለነበረው የኅብረት መሥዋዕት በማውሳት የጌታን እራት የሚካፈሉ ሰዎች ከይሖዋ ማዕድ የሚካፈሉት እንደሚገባ ተዘጋጅተው መሆን እንዳለበት ገልጿል። ከዚያም በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ማንኛውንም ዓይነት ሥጋ መብላት ትክክል መሆኑን ለማስረዳት ሲል መዝሙር 24:1ን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “ምድርና በእርስዋ የሞላባት ሁሉ የጌታ ነው።”—1 ቆሮ. 10:18, 21, 26፤ ዘፀ. 32:6፤ ዘሌ. 7:11-15

24 ጳውሎስ ‘አምላክ ለሚወዱት ያዘጋጃቸው’ ነገሮች እጅግ ብልጫ እንዳላቸውና በዚህ ዓለም የሚገኙ “ጥበበኞች አሳብ” ከንቱ መሆኑን ለማስረዳትም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሷል። (1 ቆሮ. 2:9፤ 3:20፤ ኢሳ. 64:4፤ መዝ. 94:11) ጳውሎስ “ክፉን ከመካከልህ አስወግድ” የሚለውን የይሖዋን ሕግ በምዕራፍ 5 ላይ ኃጢአተኛውን ከጉባኤ ስለ ማስወገድ ለሰጠው መመሪያ ድጋፍ አድርጎ ጠቅሷል። (ዘዳ. 17:7) ጳውሎስ አገልግሎቱን ብቻ እያከናወነ ለኑሮ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሌሎች እንዲያሟሉለት የመጠየቅ መብት እንደነበረው ሲያብራራ፣ የሚሠሩ እንስሳት እንዳይበሉ ተብሎ አፋቸው መታሰር እንደሌለበትና በመቅደስ የሚያገለግሉ ሌዋውያን ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ውስጥ ድርሻቸውን እንደሚወስዱ የሚገልጹትን በሙሴ ሕግ ውስጥ የሰፈሩትን ሐሳቦች ጠቅሷል።—1 ቆሮ. 9:8-14፤ ዘዳ. 25:4፤ 18:1

25 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ በመንፈስ አነሳሽነት ካሰፈራቸው ትምህርቶች ከፍተኛ ጥቅም እናገኛለን! እርስ በርስ መከፋፈልንና ሰዎችን መከተልን በመቃወም በተሰጠው ምክር ላይ አሰላስል። (ምዕራፍ 1-4) ተከስቶ ስለነበረው የጾታ ብልግና እንዲሁም ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው በጎ ሥነ ምግባርና ንጽሕና እንዴት ጎላ አድርጎ እንደገለጸ አስታውስ። (ምዕራፍ 5, 6) ነጠላነትን፣ ጋብቻንና መለያየትን በሚመለከት በመንፈስ አነሳሽነት ስለሰጠው ምክር አስብ። (ምዕራፍ 7) ሐዋርያው ለጣዖት የተሠዋ ምግብን በሚመለከት የተናገረውን እንዲሁም ሌሎችን አለማሰናከላችንና ጣዖት አምላኪዎች ከመሆን መቆጠባችን ያለውን አስፈላጊነት ጠንከር አድርጎ የገለጸው እንዴት እንደሆነ አሰላስል። (ምዕራፍ 8-10) በተገቢው መንገድ ለሥልጣን ስለ መገዛት፣ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዲሁም ፍቅር ጽኑና የማይወድቅ ስለመሆኑ የተሰጡትን ጠቃሚ ምክሮች መለስ ብለህ ቃኝ። በተጨማሪም ሐዋርያው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሊታይ ስለሚገባው ሥርዓት በአጽንኦት ተናግሯል! (ምዕራፍ 11-14) በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ ትንሣኤን በመደገፍ ግሩም የመከላከያ ሐሳብ አቅርቧል! (ምዕራፍ 15) ጳውሎስ እነዚህንና ሌሎች ነገሮችን ጽፏል፤ ይህ ደግሞ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው!

26 ይህ ደብዳቤ ክብራማ ስለሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት ያለንን እውቀት በእጅጉ ያሰፋልናል። ኃጢአተኛ ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት እንደማይገቡ ጥብቅ የሆነ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፤ እንዲሁም አንድን ሰው ለአምላክ መንግሥት ብቁ እንዳይሆን የሚያደርጉት መጥፎ ድርጊቶች ምን እንደሆኑ ይዘረዝራል። (1 ቆሮ. 6:9, 10) ከሁሉ በላይ ግን በትንሣኤና በአምላክ መንግሥት መካከል ስላለው ግንኙነት ያስረዳል። ይህ ደብዳቤ የትንሣኤ ‘በኩር’ የሆነው ክርስቶስ፣ አምላክ ‘ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስኪያደርግለት ድረስ እንደሚነግሥ’ ይናገራል። ከዚያም ሞትን ጨምሮ ጠላቶቹ በሙሉ ከተገዙለት በኋላ ‘አምላክ ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ መንግሥቱን ለአባቱና ለአምላኩ መልሶ ያስረክባል።’ በመጨረሻም በኤደን በተሰጠው የመንግሥቱ ተስፋ መሠረት ክርስቶስና በትንሣኤ የተነሱት መንፈሳዊ ወንድሞቹ የእባቡን ራስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቀጠቅጣሉ። ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የማይጠፋ ማለትም የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት ለመውረስ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች በእርግጥም እጅግ ታላቅ ተስፋ አላቸው። በተጨማሪም ጳውሎስ የትንሣኤን ተስፋ መሠረት በማድረግ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል:- “ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።”—1 ቆሮ. 15:20-28, 58፤ ዘፍ. 3:15፤ ሮሜ 16:20

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ሃሊስ ባይብል ሃንድቡክ፣ 1988፣ ኤች ኤች ሃሊ፣ ገጽ 593

b በስሚዝ የተዘጋጀው ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል፣ 1863፣ ጥራዝ 1 ገጽ 353

c ዚ ኢንተርፕሪተርስ ባይብል፣ ጥራዝ 10፣ 1953 ገጽ 13

d ዚ ኢንተርፕሪተርስ ባይብል፣ ጥራዝ 9፣ 1954 ገጽ 356

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ