የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

      በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ለአልኮል መጠጥ የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች አልፎ አልፎ ከጓደኞቻቸው ጋር መጠጣት ደስ ይላቸዋል። ሌሎች ደግሞ የአልኮል መጠጥ ጨርሶ አይጠጡም። እስኪሰክሩ ድረስ የሚጠጡ ሰዎችም አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኮል መጠጥ ምን ይላል?

      1. የአልኮል መጠጦችን መጠጣት ስህተት ነው?

      መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን አይከለክልም። እንዲያውም አምላክ ከሰጠን በርካታ ስጦታዎች መካከል “የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ” እንደሚገኝበት ይገልጻል። (መዝሙር 104:14, 15) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች የአልኮል መጠጥ ይጠጡ ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 5:23

      2. መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ ለሚጠጡ ሰዎች ምን ምክር ይሰጣል?

      ይሖዋ ከልክ በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል። (ገላትያ 5:21) ቃሉ “ብዙ የወይን ጠጅ እንደሚጠጡ . . . ሰዎች አትሁን” ይላል። (ምሳሌ 23:20) በመሆኑም ለብቻችን በምንጠጣበት ጊዜም እንኳ አስተሳሰባችን እስኪዛባ፣ ንግግራችንንና ድርጊታችንን መቆጣጠር እስኪያቅተን ወይም ጤናችን እስከሚጎዳ ድረስ መጠጣት አይኖርብንም። የምንጠጣውን መጠን መቆጣጠር የሚከብደን ከሆነ ከናካቴው መጠጥ ለማቆም መወሰን ሊያስፈልገን ይችላል።

      3. ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የሌሎችን ምርጫ እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      የአልኮል መጠጥ ከመጠጣት ወይም ካለመጠጣት ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ ሊያደርግ ይገባል። አንድ ሰው በልክ ለመጠጣት ከወሰነ ልንተቸው አይገባም፤ መጠጣት የማይፈልግንም ሰው እንዲጠጣ መጫን አይኖርብንም። (ሮም 14:10) የእኛ መጠጣት ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ከሆነ አለመጠጣትን እንመርጣለን። (ሮም 14:21⁠ን አንብብ።) ‘የራሳችንን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም እንፈልጋለን።’—1 ቆሮንቶስ 10:23, 24⁠ን አንብብ።

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ወይም ላለመጠጣት እንድትወስን አሊያም በምትጠጣው መጠን ላይ ገደብ እንድታበጅ የሚረዱህ እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ከመጠጥ ጋር የተያያዘ ችግር ካለብህ ምን ማድረግ እንደምትችል እንመረምራለን።

      4. የአልኮል መጠጥ መጠጣት ይኖርብህ እንደሆነና እንዳልሆነ ወስን

      ኢየሱስ የአልኮል መጠጥ ስለመጠጣት ምን አመለካከት ነበረው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ኢየሱስ የፈጸመውን የመጀመሪያ ተአምር እንመልከት። ዮሐንስ 2:1-11⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ይህ ተአምር ኢየሱስ ለአልኮል መጠጥም ሆነ የአልኮል መጠጥ ለሚጠጡ ሰዎች ስላለው አመለካከት ምን ይጠቁመናል?

      • ኢየሱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ስላላወገዘ ክርስቲያኖች የአልኮል መጠጥ ለሚጠጡ ሰዎች ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

      ክርስቲያኖች የአልኮል መጠጥ መጠጣት ቢችሉም እንዲህ ማድረጋቸው ጥሩ የማይሆንበት ጊዜ አለ። ምሳሌ 22:3⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም የሚከተሉት ሁኔታዎች ሰዎች ላለመጠጣት እንዲወስኑ ሊያደርጓቸው የሚችሉት ለምን እንደሆነ ተወያዩ፦

      • የሚያሽከረክሩ ወይም ማሽን ላይ የሚሠሩ ከሆነ

      • ነፍሰ ጡር ከሆኑ

      • ሐኪም የአልኮል መጠጥ እንዳይጠጡ ከነገራቸው

      • የሚጠጡትን መጠን መቆጣጠር የሚከብዳቸው ከሆነ

      • የአገሪቱ ሕግ የአልኮል መጠጥ እንዲጠጡ የማይፈቅድላቸው ከሆነ

      • የሚጠጣውን መጠን መቆጣጠር ስለሚከብደው ጨርሶ ላለመጠጣት ከወሰነ ሰው ጋር አብረው ሲሆኑ

      በሠርግ ድግስ ላይ ወይም በሌሎች ግብዣዎች ላይ የአልኮል መጠጥ ማቅረብ ይኖርብህ ይሆን? ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦችን ለማግኘት ቪዲዮውን ተመልከቱ።

      ቪዲዮ፦ የአልኮል መጠጥ ማቅረብ ይኖርብኝ ይሆን? (2:41)

      ሮም 13:13⁠ን እና 1 ቆሮንቶስ 10:31, 32⁠ን አንብቡ። እያንዳንዱን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባር ላይ ማዋልህ ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳህ እንዴት ነው?

      አንድ ወንድም ምግብ ቤት ውስጥ የወይን ጠጅ መጠጣት እንደማይፈልግ ሲገልጽ። ከእሱ ጋር አብረው እየተመገቡ ያሉ ሁለት እህቶች የወይን ጠጅ እየጠጡ ነው

      እያንዳንዱ ክርስቲያን የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ወይም ላለመጠጣት የራሱን ውሳኔ ሊያደርግ ይገባል። የአልኮል መጠጥ የሚጠጡ ክርስቲያኖችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ላለመጠጣት ሊወስኑ ይችላሉ

      5. ምን ያህል እንደምትጠጣ ወስን

      የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ከወሰንክ ይህን ማስታወስ ይኖርብሃል፦ ይሖዋ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ባያወግዝም ከልክ በላይ መጠጣትን ያወግዛል። ለምን? ሆሴዕ 4:11, 18⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ከልክ በላይ መጠጣት ምን ጉዳት ያስከትላል?

      ከልክ በላይ እንዳንጠጣ ምን ይረዳናል? ልካችንን ወይም ገደባችንን ማወቅ ይኖርብናል። ምሳሌ 11:2⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • በምትጠጣው መጠን ላይ ገደብ ማስቀመጥህ ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?

      6. ከልክ በላይ የመጠጣት ልማድን ማሸነፍ

      ከልክ በላይ ይጠጣ የነበረ አንድ ሰው ይህን ልማድ እንዲያሸንፍ የረዳው ምንድን ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ ‘በሕይወቴ ተመረርኩ’ (6:32)

      ‘በሕይወቴ ተመረርኩ’ ከሚለው ቪዲዮ ላይ የተወሰዱ ትዕይንቶች፦ 1. ዲሚትሪ የአልኮል መጠጥ የያዘ ጠርሙስ ሲያይ 2. ዲሚትሪ፣ ባለቤቱና ሴት ልጃቸው መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ሲያነብቡ
      • በቪዲዮው ላይ ዲሚትሪ የአልኮል መጠጥ ሲጠጣ ምን ዓይነት ጠባይ ያሳይ ነበር?

      • የመጠጥ ሱሱን ወዲያው ማሸነፍ ችሏል?

      • በመጨረሻም ከአልኮል መጠጥ ሱስ መላቀቅ የቻለው እንዴት ነው?

      አንደኛ ቆሮንቶስ 6:10, 11⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ስካር እንደ ቀላል የሚታይ ጉዳይ ነው?

      • ከልክ በላይ የአልኮል መጠጥ ይጠጣ የነበረ ሰው ሊለወጥ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

      ማቴዎስ 5:30⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ‘እጅን መቁረጥ’ የሚለው አገላለጽ ይሖዋን ለማስደሰት ሲሉ መሥዋዕትነት መክፈልን ያመለክታል። የመጠጥ ሱስን ለማሸነፍ እየታገልክ ከሆነ ምን ማድረግህ ይረዳሃል?a

      አንደኛ ቆሮንቶስ 15:33⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ብዙ ከሚጠጡ ሰዎች ጋር ጓደኛ መሆንህ ምን ጉዳት ይኖረዋል?

      አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የአልኮል መጠጥ መጠጣት ስህተት ነው?”

      • ምን ብለህ ትመልሳለህ?

      ማጠቃለያ

      የአልኮል መጠጥ ይሖዋ ደስታ እንድናገኝ ሲል ከሰጠን ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው፤ ሆኖም ይሖዋ ከልክ በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል።

      ክለሳ

      • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኮል መጠጥ ምን ይላል?

      • ከልክ በላይ መጠጣት ምን ጉዳት ያስከትላል?

      • ሌሎች ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ምርጫ እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      ወጣቶች ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

      መጠጣት የሚያስከትለውን መዘዝ አስብ (2:31)

      ከልክ በላይ የመጠጣት ችግርን ለማስወገድ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?

      “ለአልኮል ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር” (መጠበቂያ ግንብ ጥር 1, 2010)

      ክርስቲያኖች መልካም ምኞታቸውን ለመግለጽ ጽዋቸውን ሊያነሱ ይገባል?

      “የአንባቢያን ጥያቄዎች” (መጠበቂያ ግንብ የካቲት 15, 2007)

      ‘ቀዳዳ በርሜል ነበርኩ’ የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ ከልክ በላይ የመጠጣት ችግር የነበረበት አንድ ሰው ይህን ልማዱን ያሸነፈው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

      “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” (መጠበቂያ ግንብ ግንቦት 1, 2012)

      a የአልኮል መጠጥ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ከሱሳቸው ለመላቀቅ የባለሙያ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ብዙ ሐኪሞች የመጠጥ ችግር የነበረባቸው ሰዎች ጨርሶ ባይጠጡ የተሻለ እንደሆነ ይመክራሉ።

  • አለባበሳችንና ውጫዊ ገጽታችን ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • ምዕራፍ 52. አንዲት ሴት የምትገዛውን ልብስ ስትመርጥ

      ምዕራፍ 52

      አለባበሳችንና ውጫዊ ገጽታችን ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

      ሁላችንም ከአለባበሳችንና ከውጫዊ ገጽታችን ጋር በተያያዘ የየራሳችን ምርጫ ይኖረናል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተላችን የራሳችንን ምርጫ መተው ሳያስፈልገን ይሖዋን ማስደሰት እንድንችል ይረዳናል። እስቲ ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

      1. ከአለባበሳችንና ከውጫዊ ገጽታችን ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ በየትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልንመራ ይገባል?

      “በልከኝነትና በማስተዋል፣ ተገቢ [የሆነ] ልብስ” መልበስ ይኖርብናል፤ በተጨማሪም “ለአምላክ ያደርን ነን የሚሉ [ሰዎች] ሊያደርጉት እንደሚገባ” ምንጊዜም ንጽሕናችንን መጠበቅ አለብን። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) የሚከተሉትን አራት መሠረታዊ ሥርዓቶች ልብ በል፦ (1) አለባበሳችን “ተገቢ” ሊሆን ይገባል። በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ እንዳየኸው የይሖዋ ሕዝቦች በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ረገድ የየራሳቸው ምርጫ አላቸው፤ ሆኖም ምርጫቸው የሚያመልኩትን አምላክ እንደሚያከብሩ የሚያሳይ ነው። (2) “በልከኝነት” መልበስ ሲባል የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ወይም ወደ ራሳችን ከልክ ያለፈ ትኩረት የሚስብ ልብስ ከመልበስ መቆጠብ ማለት ነው። (3) በየጊዜው የሚመጣውን እያንዳንዱን ፋሽን ባለመከተል ‘አስተዋይ’ እንደሆንን እናሳያለን። (4) ውጫዊ ገጽታችን ‘ለአምላክ ያደርን እንደሆንን’ ማለትም እውነተኛውን አምላክ እንደምናመልክ የሚያሳይ ሊሆን ይገባል።—1 ቆሮንቶስ 10:31

      2. አለባበሳችንን ስንመርጥ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ለምንድን ነው?

      የምንለብሰውን ልብስ የመምረጥ ነፃነት ቢኖረንም የእኛ ምርጫ በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማሰብ አለብን። ማንንም ቅር ላለማሰኘት፣ ከዚህ ይልቅ ‘ባልንጀራችንን የሚጠቅመውንና የሚያንጸውን ነገር በማድረግ ለማስደሰት’ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን።—ሮም 15:1, 2⁠ን አንብብ።

      3. አለባበሳችን ሌሎችን ወደ እውነተኛው አምልኮ ሊስብ የሚችለው እንዴት ነው?

      ሁሌም ሥርዓታማ አለባበስ እንዲኖረን ጥረት ብናደርግም በተለይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝና በስብከቱ ሥራ ስንካፈል ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት እንሰጣለን። አለባበሳችን ሰዎች በያዝነው አስፈላጊ መልእክት ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ እንቅፋት እንዲሆንባቸው አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ‘የአዳኛችን ትምህርት ውበት እንዲጎናጸፍ’ በማድረግ ሰዎችን ወደ እውነት የሚስብ ሊሆን ይገባል።—ቲቶ 2:10

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ አለባበስና ውጫዊ ገጽታ እንዲኖረን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

      ሁለት ወንዶች ዳኛ ፊት ቆመው። አንደኛው ሙሉ ልብስ ለብሷል፤ ሌላኛው ደግሞ የተቀዳደደና የተዝረከረከ ልብስ እንዲሁም ኮፍያ አድርጓል

      አለባበሳችን ሥልጣን ላላቸው ሰዎች አክብሮት እንዳለን ወይም እንደሌለን ሊጠቁም ይችላል። ይሖዋ የልባችንን የሚያውቅ ቢሆንም ለእሱ አክብሮት እንዳለን በአለባበሳችንም ማሳየት አለብን

      4. ጥሩ አለባበስ ለይሖዋ አክብሮት እንዳለን ያሳያል

      ለአለባበሳችን ትኩረት የምንሰጥበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? መዝሙር 47:2⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • አለባበሳችን ሰዎች ለይሖዋ ባላቸው አመለካከት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ማወቃችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

      • በስብሰባዎች ላይ ስንገኝና በስብከቱ ሥራ ስንካፈል ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

      5. ከአለባበስና ከውጫዊ ገጽታ ጋር በተያያዘ ጥሩ ምርጫ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

      ቪዲዮውን ተመልከቱ።

      ቪዲዮ፦ “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” (10:18)

      ልብሶቻችን ውድ ሆኑም አልሆኑ ንጹሕና ለሁኔታው ተስማሚ መሆን አለባቸው። አንደኛ ቆሮንቶስ 10:24⁠ን እና 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10⁠ን አንብቡ። ከዚያም የሚከተሉትን ዓይነት ልብሶች መልበስ የሌለብን ለምን እንደሆነ ተወያዩ፦

      • የቆሸሸና የተዝረከረከ

      • የተጣበቀ፣ ሰውነትን የሚያሳይ ወይም የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ

      እኛ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ሕጉ የይሖዋን አመለካከት ለማወቅ ይረዳናል። ዘዳግም 22:5⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ወንዶች ሴት የሚያስመስል፣ ሴቶች ደግሞ ወንድ የሚያስመስል ልብስ መልበስ የሌለባቸው ለምንድን ነው?

      አንደኛ ቆሮንቶስ 10:32, 33⁠ን እንዲሁም 1 ዮሐንስ 2:15, 16⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • አለባበሳችን በጉባኤያችን ወይም በአካባቢያችን ያሉ አንዳንድ ሰዎችን ቅር የሚያሰኝ መሆን አለመሆኑን ማሰባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      • አንተ በምትኖርበት አካባቢ የተለመደው ምን ዓይነት አለባበስ ነው?

      • ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ለክርስቲያኖች ተገቢ ያልሆኑ ይመስሉሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

      በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያላቸው የተለያዩ አለባበሶች አሉ

      በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙና የተለያየ ዘር ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ለክርስቲያኖች ተገቢ የሆነ የተለያየ ልብስ ለብሰው፤ የፀጉር አያያዛቸውም የተለያየ ነው

      አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “የፈለግኩትን ልብስ መልበስ መብቴ ነው።”

      • አንተ በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

      ማጠቃለያ

      በአለባበስ ረገድ ጥሩ ምርጫ ማድረጋችን ለይሖዋም ሆነ ለሰዎች አክብሮት እንዳለን ያሳያል።

      ክለሳ

      • ይሖዋ በአለባበስ ረገድ ጥሩ ምርጫ እንድናደርግ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

      • ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ በየትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልንመራ ይገባል?

      • አለባበሳችን ሌሎች ለእውነተኛው አምልኮ ባላቸው አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      አለባበስህ ለሌሎች ምን መልእክት ያስተላልፋል?

      “አለባበሴ እንዴት ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      ከመነቀስህ በፊት ቆም ብለህ ማሰብህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንቅሳት ምን ይላል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱህ ሌሎች መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

      “አለባበሳችሁ አምላክን ያስከብራል?” (መጠበቂያ ግንብ መስከረም 2016)

      አምላክን ማስደሰት ትፈልግ የነበረች አንዲት ሴት ሌሎች በአለባበስ ረገድ ያደረጉትን ምርጫ እንድታከብር የረዳት ምንድን ነው?

      “የሰዎች አለባበስና የፀጉር አያያዝ መሰናክል ሆኖብኝ ነበር” (ንቁ! ላይ የወጣ ርዕስ)

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ