-
እናንት ወንዶች፣ ለክርስቶስ ራስነት ትገዛላችሁ?መጠበቂያ ግንብ—2010 | ግንቦት 15
-
-
እናንት ወንዶች፣ ለክርስቶስ ራስነት ትገዛላችሁ?
“የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ [ነው]።”—1 ቆሮ. 11:3
1. ይሖዋ የሁከት አምላክ እንዳልሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
“ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ያሉትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል” በማለት ራእይ 4:11 ይናገራል። ይሖዋ አምላክ፣ የሁሉም ነገር ፈጣሪ ስለሆነ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ነው፤ እንዲሁም በፍጥረታቱ ሁሉ ላይ ሥልጣን አለው። ይሖዋ “የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ” እንዳልሆነ መላእክቱን ካደራጀበት መንገድ በግልጽ መመልከት ይቻላል።—1 ቆሮ. 14:33፤ ኢሳ. 6:1-3፤ ዕብ. 12:22, 23
2, 3. (ሀ) ይሖዋ መጀመሪያ የፈጠረው ማንን ነው? (ለ) የአምላክ የበኩር ልጅ ከይሖዋ አንጻር ያለው ቦታ ምንድን ነው?
2 ማንኛውም ነገር ከመፈጠሩ በፊት አምላክ ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት ብቻውን ይኖር ነበር። አምላክ መጀመሪያ የፈጠረው “ቃል” ተብሎ የሚጠራውን መንፈሳዊ ፍጥረት ሲሆን ይህ ስም የተሰጠው የይሖዋ ቃል አቀባይ በመሆኑ ነው። ሌሎች ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና የመጡት “ቃል” በተባለው በዚህ አካል አማካኝነት ነው። ከጊዜ በኋላ ይህ መንፈሳዊ ፍጥረት ፍጹም ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ ይጠራ ጀመር።—ዮሐንስ 1:1-3, 14ን አንብብ።
3 ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክና የበኩር ልጁ ስላላቸው ቦታ ምን ይላሉ? ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ፣ የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ።” (1 ቆሮ. 11:3) ክርስቶስ በአባቱ የራስነት ሥልጣን ሥር ነው። የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጥረታት መካከል ሰላምና ሥርዓት እንዲሰፍን ከተፈለገ የራስነት ሥልጣን መኖሩ እንዲሁም ፍጥረታት ለዚህ ሥልጣን መገዛታቸው አስፈላጊ ነው። ‘ሌሎች ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት’ እንደሆነ የተነገረለት አካልም እንኳ ለአምላክ የራስነት ሥልጣን እንዲገዛ ይጠበቅበታል።—ቆላ. 1:16
4, 5. ኢየሱስ ከይሖዋ አንጻር ስላለው ቦታ ምን አመለካከት ነበረው?
4 ኢየሱስ ለይሖዋ የራስነት ሥልጣን ስለመገዛትና ወደ ምድር ስለመምጣት ምን ተሰምቶት ነበር? ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፦ “[ክርስቶስ ኢየሱስ] በአምላክ መልክ ይኖር የነበረ ቢሆንም ከአምላክ ጋር እኩል መሆንን ነጥቆ ሊወስደው እንደሚገባ ነገር አድርጎ አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ራሱን ባዶ አደረገ፤ እንደ ባሪያ ሆኖም በሰው አምሳል መጣ። ከዚህም በላይ በሰው አምሳል በመጣ ጊዜ ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል።”—ፊልጵ. 2:5-8
5 ኢየሱስ ምንጊዜም ለአባቱ ፈቃድ በትሕትና ይገዛ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በራሴ ተነሳስቼ አንድም ነገር ማድረግ አልችልም፤ . . . የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ መፈጸም ስለምፈልግ የምፈርደው የጽድቅ ፍርድ ነው።” (ዮሐ. 5:30) በተጨማሪም “ሁልጊዜ [አባቴን] ደስ የሚያሰኘውን [አደርጋለሁ]” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 8:29) ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ” ብሏል። (ዮሐ. 17:4) በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ኢየሱስ የአምላክን የራስነት ሥልጣን መቀበልና ለዚህ ሥልጣን መገዛት ምንም አላስቸገረውም።
የአምላክ ልጅ ለአባቱ መገዛቱ ጥቅም አስገኝቶለታል
6. ኢየሱስ ምን ግሩም ባሕርያት እንዳሉት አሳይቷል?
6 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ብዙ ግሩም ባሕርያት እንዳሉት አሳይቷል። ለአባቱ የነበረውን ጥልቅ ፍቅር እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። “እኔ አብን [እወደዋለሁ]” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 14:31) ኢየሱስ ለሰዎችም ታላቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ማቴዎስ 22:35-40ን አንብብ።) ኢየሱስ ደግና አሳቢ እንጂ ኃይለኛ ወይም ሥልጣኑን አላግባብ የሚጠቀም ሰው አልነበረም። እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ምክንያቱም ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነው።” (ማቴ. 11:28-30) በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ በግ መሰል ሰዎች በተለይም በደል የደረሰባቸውና የተጨቆኑ ሰዎች አስደሳች የሆነው የኢየሱስ ባሕርይና መንፈስን የሚያድሰው መልእክቱ ያጽናናቸው ነበር።
7, 8. ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት በሕጉ መሠረት ምን እንድታደርግ አይፈቀድላትም ነበር? ኢየሱስ ግን ይህችን ሴት የያዛት እንዴት ነበር?
7 ኢየሱስ ሴቶችን የያዘበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በታሪክ ዘመናት ሁሉ በርካታ ወንዶች ሴቶችን ሲጨቁኗቸው ኖረዋል። በጥንቷ እስራኤል የነበሩት የሃይማኖት መሪዎችም ሴቶችን የሚይዙት በዚህ መንገድ ነበር። ኢየሱስ ግን ለሴቶች አክብሮት ነበረው። ለ12 ዓመት ደም ሲፈሳት ለኖረች አንዲት ሴት ያደረገው ነገር ይህን በግልጽ ያሳያል። ይህች ሴት ከሐኪም ወደ ሐኪም በመሄድ “ብዙ ተሠቃይታ” የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለመዳን ስትል ያላትን ጥሪት ሁሉ ብትጨርስም “ሕመሙ ባሰባት” እንጂ አልተሻላትም። በሕጉ መሠረት ይህች ሴት ርኩስ እንደሆነች ተደርጋ ትታይ ነበር። እሷን የሚነካ ማንኛውም ሰውም ርኩስ ይሆን ነበር።—ዘሌ. 15:19, 25
8 ይህች ሴት ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን እንደሚፈውስ ስትሰማ “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ስላሰበች እሱን ከከበበው ሕዝብ ጋር ተቀላቀለች። ኢየሱስን ስትነካው ወዲያውኑ ዳነች። ኢየሱስ ሴትየዋ ልብሱን መንካት እንዳልነበረባት ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን ይህን በማድረጓ አልወቀሳትም። እንዲያውም ደግነት አሳይቷታል። ለበርካታ ዓመታት በሕመም ስትሠቃይ በመኖሯ ስሜቷ ምን ያህል እንደተደቆሰና እርዳታ ለማግኘት ምን ያህል እንደጓጓች ተረድቶ ነበር። ኢየሱስ ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፣ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም እረፊ” አላት።—ማር. 5:25-34
9. ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ልጆች ወደ እሱ እንዳይቀርቡ በተከላከሉ ጊዜ ምን አደረገ?
9 ልጆችም እንኳ ከኢየሱስ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። በአንድ ወቅት ሰዎች ልጆችን ወደ ኢየሱስ ይዘው በመጡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ልጆቹ እንዲያስቸግሩት እንደማይፈልግ በማሰብ ሰዎቹን ገሠጿቸው። ኢየሱስ ግን ልጆቹ እንደሚያስቸግሩት አልተሰማውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ይህን ሲያይ [ደቀ መዛሙርቱን] ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፦ ‘ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነው።’” “ልጆቹንም አቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ይባርካቸው ጀመር።” ኢየሱስ ልጆችን የሚያቀርበው የግድ ሆኖበት አልነበረም፤ እንዲያውም ሞቅ ባለ ስሜት ተቀብሏቸዋል።—ማር. 10:13-16
10. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ያሳያቸውን ባሕርያት ያዳበረው እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ያሳያቸውን ባሕርያት ያዳበረው እንዴት ነው? ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ በቆየባቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዘመናት የአባቱን ባሕርያት ያስተዋለ ከመሆኑም ሌላ አባቱ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በመመልከት ትምህርት ይቀስም ነበር። (ምሳሌ 8:22, 23, 30ን አንብብ።) ኢየሱስ በሰማይ በነበረበት ወቅት ይሖዋ በሁሉም ፍጥረታቱ ላይ የራስነት ሥልጣኑን በፍቅር የሚጠቀምበት እንዴት እንደሆነ የተመለከተ ሲሆን እሱም የአባቱን ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ተከትሏል። ኢየሱስ ለአባቱ ሥልጣን ተገዢ ባይሆን ኖሮ የእሱን ምሳሌ ለመከተል ይነሳሳ ነበር? የአምላክ ልጅ ለአባቱ ሥልጣን መገዛት የሚያስደስተው ሲሆን ይሖዋም እንዲህ ዓይነት ልጅ ስላለው ደስተኛ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የሰማይ አባቱን ግሩም ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። በሰማይ ባለው መንግሥት ላይ እንዲገዛ አምላክ ለሾመው ንጉሥ ማለትም ለክርስቶስ መገዛታችን እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው!
የክርስቶስን ባሕርያት አንጸባርቁ
11. (ሀ) ማንን ለመምሰል ጥረት ማድረግ አለብን? (ለ) በተለይ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶች ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው?
11 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ በተለይም ወንዶች የክርስቶስን ባሕርያት ለማንጸባረቅ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ” እንደሆነ ይናገራል። ክርስቶስ የእሱ ራስ የሆነውን እውነተኛውን አምላክ እንደመሰለ ሁሉ ክርስቲያን ወንዶችም ራሳቸው የሆነውን ክርስቶስን ለመምሰል መጣር ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ሲሆን ይህንን አድርጓል። “እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ” በማለት የእምነት ባልንጀሮቹን መክሯቸዋል። (1 ቆሮ. 11:1) ሐዋርያው ጴጥሮስም እንዲህ ብሏል፦ “የተጠራችሁት በዚህ ጎዳና እንድትሄዱ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስም እንኳ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል።” (1 ጴጥ. 2:21) በተለይ ወንዶች ክርስቶስን እንድንመስል ለተሰጠን ምክር ትኩረት እንዲሰጡት የሚያነሳሳቸው ሌላም ምክንያት አለ። ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች የሚሆኑት እነሱ ናቸው። ኢየሱስ ይሖዋን በመምሰሉ ይደሰት እንደነበረ ሁሉ ክርስቲያን ወንዶችም ክርስቶስን በመምሰልና ባሕርያቱን በማንጸባረቅ ሊደሰቱ ይገባል።
12, 13. ሽማግሌዎች በአደራ የተሰጧቸውን በጎች እንዴት ሊይዟቸው ይገባል?
12 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች የክርስቶስን አርዓያ ለመከተል ጥረት የማድረግ ግዴታ አለባቸው። ጴጥሮስ ለሽማግሌዎች የሚከተለውን ጥብቅ ምክር ሰጥቷቸዋል፦ “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ፤ በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት፣ የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናችሁን በማሳየት ሳይሆን ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁ።” (1 ጴጥ. 5:1-3) ክርስቲያን ሽማግሌዎች አምባገነን ወይም ፈላጭ ቆራጭ እንዲሁም ምክንያታዊነትና ደግነት የጎደላቸው መሆን የለባቸውም። ሽማግሌዎች የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል በአደራ ለተሰጧቸው በጎች ፍቅርና አሳቢነት ለማሳየት እንዲሁም በጎቹን በትሕትናና በደግነት ለመያዝ ጥረት ያደርጋሉ።
13 በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ወንድሞች ፍጽምና የጎደላቸው ናቸው፤ በመሆኑም አቅማቸው ውስን መሆኑን ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ሮም 3:23) እንግዲያው ስለ ኢየሱስ ለመማርና የእሱ ዓይነት ፍቅር ለማንጸባረቅ ከልብ ሊነሳሱ ይገባል። አምላክና ክርስቶስ ሰዎችን በሚይዙበት መንገድ ላይ ማሰላሰልና የእነሱን ምሳሌ ለመከተል መጣር ይኖርባቸዋል። ጴጥሮስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶናል፦ “እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሁላችሁም ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፤ ምክንያቱም አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”—1 ጴጥ. 5:5
14. ሽማግሌዎች እስከ ምን ድረስ ሌሎችን ማክበር ይኖርባቸዋል?
14 በጉባኤ ውስጥ የተሾሙ ወንዶች የአምላክን መንጋ በሚይዙበት ጊዜ ግሩም ባሕርያትን ማሳየት ይኖርባቸዋል። ሮም 12:10 እንዲህ ይላል፦ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ለሌሎች አክብሮት ያሳያሉ። እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ሁሉ እነዚህ ወንዶችም ‘ሌሎች ከእነሱ እንደሚበልጡ አድርገው በትሕትና ማሰብ እንጂ በምቀኝነት ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር ማድረግ’ የለባቸውም። (ፊልጵ. 2:3) ኃላፊነት ያላቸው ወንዶች ሌሎች ከእነሱ እንደሚበልጡ አድርገው ማሰብ ይኖርባቸዋል። እነዚህ የተሾሙ ወንዶች እንዲህ ሲያደርጉ የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር በተግባር ያውላሉ፦ “እኛ ብርቱዎች የሆንን ብርቱ ያልሆኑትን ሰዎች ድክመት ልንሸከም ይገባል እንጂ ራሳችንን የምናስደስት መሆን የለብንም። እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን የሚጠቅመውን ይኸውም ሊያንጸው የሚችለውን ነገር በማድረግ እናስደስተው። ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተም።”—ሮም 15:1-3
‘ለሚስቶች ክብር መስጠት’
15. ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት ሊይዟቸው ይገባል?
15 እስቲ አሁን ደግሞ ጴጥሮስ ላገቡ ወንዶች የሰጠውን ምክር እንመልከት። “ባሎች ሆይ፣ . . . ከእናንተ ይበልጥ ተሰባሪ ዕቃ ለሆኑት [ለሚስቶቻችሁ] ክብር በመስጠት ልክ እንደዚሁ ከእነሱ ጋር በእውቀት መኖራችሁን ቀጥሉ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥ. 3:7) አንድን ሰው ማክበር ሲባል ያንን ግለሰብ ከፍ አድርጎ መመልከት ማለት ነው። ስለዚህ የግለሰቡን አመለካከትና ፍላጎት እንዲሁም የሚያስፈልገውን ነገር ከግምት ታስገባለህ፤ እንዲሁም ሐሳቡን እንዳትቀበል የሚያደርግህ በቂ ምክንያት እስከሌለህ ድረስ ከእሱ ፈቃድ ጋር ትስማማለህ። አንድ ባልም ሚስቱን መያዝ ያለበት በዚህ መንገድ ነው።
16. የአምላክ ቃል ሚስቶቻቸውን ከማክበር ጋር በተያያዘ ለባሎች ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?
16 ጴጥሮስ፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲያከብሩ ምክር ሲሰጥ “ጸሎታችሁ እንዳይታገድ” የሚል ማስጠንቀቂያም ሰጥቶ ነበር። (1 ጴጥ. 3:7) ይህ አባባል አንድ ወንድ ሚስቱን የሚይዝበትን መንገድ ይሖዋ አክብዶ እንደሚመለከተው በግልጽ ያሳያል። ለሚስቱ አክብሮት የማያሳይ ከሆነ ጸሎቱ ሊታገድ ይችላል። ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ ሚስቶች ጥሩ ምላሽ የሚሰጡት ባሎቻቸው በአክብሮት ሲይዟቸው አይደለም?
17. አንድ ባል ሚስቱን እስከ ምን ድረስ ሊወዳት ይገባል?
17 ሚስትን መውደድን በተመለከተ የአምላክ ቃል እንዲህ የሚል ምክር ይሰጣል፦ “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። . . . ምክንያቱም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም ሰው የለም፤ ከዚህ ይልቅ ይመግበዋል እንዲሁም ይሳሳለታል፤ ክርስቶስም ለጉባኤው ያደረገው እንደዚሁ ነው፤ . . . ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ።” (ኤፌ. 5:28, 29, 33) ባሎች ሚስቶቻቸውን እስከ ምን ድረስ ሊወዷቸው ይገባል? ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ለእሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:25) በእርግጥም፣ ክርስቶስ ለሰዎች እንዳደረገው ሁሉ አንድ ባልም ሕይወቱን እንኳ ለሚስቱ ለመስጠት ፈቃደኛ ሊሆን ይገባል። አንድ ክርስቲያን ባል ለሚስቱ ፍቅርና አሳቢነት የሚያሳያት፣ ትኩረት የሚሰጣት እንዲሁም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ የሚይዛት ከሆነ ሚስቱ ለራስነት ሥልጣኑ መገዛት ቀላል ይሆንላታል።
18. ባሎች በትዳራቸው ውስጥ ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ምን እርዳታ ማግኘት ይችላሉ?
18 ባሎች ለሚስቶቻቸው የዚህን ያህል አክብሮት መስጠት ከአቅማቸው በላይ ነው? አይደለም፣ ይሖዋ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ በፍጹም አይጠይቃቸውም። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ አምላኪዎች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለውን ኃይል ማለትም የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ማግኘት ይችላሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!” (ሉቃስ 11:13) ባሎች በሚጸልዩበት ጊዜ ሚስቶቻቸውን ጨምሮ ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲረዳቸው መጠየቅ ይችላሉ።—የሐዋርያት ሥራ 5:32ን አንብብ።
19. በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
19 በእርግጥም ወንዶች፣ ለክርስቶስ እንዴት መገዛት እንዳለባቸውና የራስነት ሥልጣኑን የተጠቀመበትን መንገድ እንዴት መከተል እንደሚችሉ በመማር ረገድ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ይሁንና ስለ ሴቶች በተለይም ስለ ሚስቶች ምን ማለት ይቻላል? የሚቀጥለው ርዕስ ሴቶች፣ በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ ስላላቸው ቦታ ምን አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያብራራል።
-
-
እናንት ሴቶች፣ ለራስነት ሥልጣን መገዛት ያለባችሁ ለምንድን ነው?መጠበቂያ ግንብ—2010 | ግንቦት 15
-
-
እናንት ሴቶች፣ ለራስነት ሥልጣን መገዛት ያለባችሁ ለምንድን ነው?
“የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ [ነው]።”—1 ቆሮ. 11:3
1, 2. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋ የራስነት ሥልጣንንና ለዚህ ሥልጣን መገዛትን በተመለከተ ስላደረገው ዝግጅት ምን ብሏል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
ሐዋርያው ጳውሎስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ . . . የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ” በመናገር ይሖዋ ያቋቋመውን የሥልጣን ተዋረድ ገልጿል። (1 ቆሮ. 11:3) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ፣ ራሱ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ሥልጣን መገዛት ያስደስተው የነበረ ከመሆኑም ሌላ እንደ ክብር ይቆጥረው ነበር። ክርስቲያን ወንዶችም ራስ እንዳላቸውና እሱም ክርስቶስ እንደሆነ ተመልክተናል። ክርስቶስ ሰዎችን በደግነት፣ በገርነት፣ በርኅራኄ እንዲሁም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ይይዝ ነበር። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶችም ከሌሎች በተለይም ከሚስቶቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት እነዚህን ባሕርያት ማሳየት ይኖርባቸዋል።
2 ስለ ሴቶችስ ምን ማለት ይቻላል? ራሳቸው ማን ነው? ጳውሎስ “የሴት ሁሉ ራስ . . . ወንድ” እንደሆነ ጽፏል። ሴቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን ይህን ሐሳብ እንዴት ሊመለከቱት ይገባል? አንዲት ሚስት ባሏ የማያምን ቢሆንም ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ሊሠራ ይችላል? ሚስቶች ለወንድ የራስነት ሥልጣን መገዛት አለባቸው ሲባል በትዳር ውስጥ በሚደረጉት ውሳኔዎች ረገድ ምንም ድርሻ አይኖራቸውም ማለት ነው? አንዲት ሴት ለራሷ ምስጋና ማትረፍ የምትችለው እንዴት ነው?
“ረዳት አበጅለታለሁ”
3, 4. የራስነት ሥርዓት በትዳር ውስጥ ጠቃሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
3 የራስነትን ሥርዓት ያዘጋጀው አምላክ ነው። ይሖዋ አምላክ፣ አዳም ከተፈጠረ በኋላ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” ብሎ ነበር። ሔዋን በተፈጠረች ጊዜ አዳም ጓደኛና ረዳት በማግኘቱ እጅግ ስለተደሰተ “እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት” አለ። (ዘፍ. 2:18-24) አዳምና ሔዋን መላዋን ምድር ገነት በማድረግና ፍጹማን የሆኑ ልጆችን በመውለድ ለዘላለም ከልጆቻቸው ጋር በደስታ የመኖር ግሩም አጋጣሚ ነበራቸው።
4 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በኤደን ገነት በአምላክ ላይ ካመፁ ወዲህ የሰው ልጆች የራስነትን ሥርዓት ፍጹም በሆነ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም። (ሮም 5:12ን አንብብ።) ይሁንና በአምላክ ዘንድ አሁንም ቢሆን የሚስት ራስ ባል ነው። የራስነት ሥርዓት በተገቢው መንገድ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በትዳር ውስጥ ብዙ ጥቅም እና ደስታ ያስገኛል። ባልና ሚስቱ ይህን ሥርዓት በአግባቡ መከተላቸው ኢየሱስ፣ ራሱ ለሆነው ለይሖዋ በመገዛቱ የተሰማው ዓይነት ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት “ሁልጊዜ [በይሖዋ ፊት] ሐሤት” ያደርግ ነበር። (ምሳሌ 8:30) ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸው ስለሆኑ ወንዶች የራስነት ሥልጣናቸውን ፍጹም በሆነ መንገድ ሊጠቀሙበት አይችሉም፤ ሴቶችም ቢሆኑ ፍጹም ታዛዥነት ማሳየት አይችሉም። ይሁን እንጂ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች በዚህ ረገድ አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ ሁልጊዜ የሚጥሩ ከሆነ ይህ ዝግጅት በዛሬው ጊዜም ከትዳር ማግኘት የሚቻለውን የላቀ ደስታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
5. የትዳር ጓደኛሞች በሮም 12:10 ላይ የሚገኘውን ምክር በቁም ነገር ሊመለከቱት የሚገባው ለምንድን ነው?
5 የትዳር ጓደኛሞች ጋብቻቸው የተሳካ እንዲሆን ከፈለጉ ለሁሉም ክርስቲያኖች የተሰጠውን የሚከተለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በተግባር ማዋላቸው አስፈላጊ ነው፦ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:10) በተጨማሪም ባልም ሆነ ሚስት ‘አንዳቸው ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የሚራሩ ለመሆን እንዲሁም እርስ በርሳቸው በነፃ ይቅር ለመባባል’ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።—ኤፌ. 4:32
የትዳር ጓደኛ የማያምን በሚሆንበት ጊዜ
6, 7. አንዲት ክርስቲያን ሚስት ለማያምን ባሏ መገዛቷ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
6 የትዳር ጓደኛችሁ የይሖዋ አገልጋይ ባይሆንስ? አብዛኛውን ጊዜ ከትዳር ጓደኛሞች መካከል አማኝ የማይሆነው ባል ነው። በዚህ ጊዜ ሚስት ለባሏ ምን አመለካከት ሊኖራት ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን መልስ ይሰጣል፦ “እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ፤ ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት በዓይናቸው ሲመለከቱ ነው።”—1 ጴጥ. 3:1, 2
7 የአምላክ ቃል ሚስት ለማያምነው ባሏ እንድትገዛ ያዛል። ሚስት መልካም ምግባር ማሳየቷ ባሏ እንዲህ ዓይነት ጥሩ ጠባይ እንዲኖራት ያደረጋት ምን እንደሆነ ለማወቅ እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል። በዚህም ምክንያት ይህ ባል ክርስቲያን ሚስቱ የምትከተለውን እምነት ሊመረምርና ውሎ አድሮ እሱ ራሱ እውነትን ሊቀበል ይችላል።
8, 9. አንዲት ክርስቲያን ሚስት መልካም ምግባር ብታሳይም የማያምን ባሏ ለጥረቷ ጥሩ ምላሽ ባይሰጥ ምን ማድረግ ትችላለች?
8 ይሁንና አንድ የማያምን ባል ሚስቱ ለምታደርገው ጥረት ጥሩ ምላሽ ባይሰጥስ? አማኝ የሆነችው ሚስት ሁልጊዜ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማሳየት አስቸጋሪ ቢሆንባትም እንኳ ይህን ማድረጓን እንድትቀጥል ቅዱሳን መጻሕፍት ያበረታታሉ። ለምሳሌ ያህል 1 ቆሮንቶስ 13:4 “ፍቅር ታጋሽ” እንደሆነ ይናገራል። በመሆኑም ክርስቲያን የሆነችው ሚስት ሁኔታውን በፍቅር በመያዝ ‘ፍጹም ትሕትናና ገርነት እንዲሁም ትዕግሥት’ ለማሳየት ሁልጊዜ ጥረት ማድረጓ የተሻለ ነው። (ኤፌ. 4:2) አንዲት ሚስት አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥርም እንኳ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማንጸባረቅ ትችላለች።
9 ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵ. 4:13) የአምላክ መንፈስ ክርስቲያን የሆነችው የትዳር ጓደኛ፣ በራሷ ኃይል ቢሆን ኖሮ የማትችላቸውን በርካታ ነገሮች እንድታደርግ ያስችላታል። ለምሳሌ ያህል፣ የትዳር ጓደኛዋ መጥፎ ነገር ሲያደርግባት እሷም በዚያው መንገድ ምላሽ ለመስጠት ትፈተን ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ያሳስባል፦ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። . . . ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ’ ተብሎ [ተጽፏል]።” (ሮም 12:17-19) በተመሳሳይም በ1 ተሰሎንቄ 5:15 ላይ እንዲህ የሚል ምክር እናገኛለን፦ “ማንም ሰው በማንም ላይ በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁሉ ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ።” የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ የሚያደርግልን ድጋፍ በራሳችን አቅም ፈጽሞ የማንችለውን ነገር ለማድረግ ያስችለናል። እንግዲያው የሚጎድለንን ነገር ለማሟላት እንዲረዳን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት መጸለያችን ምንኛ ተገቢ ነው!
10. ኢየሱስ ሰዎች መጥፎ ነገር ሲናገሩት ወይም ሲያደርጉበት ጉዳዩን የያዘው በምን መንገድ ነው?
10 ኢየሱስ ሰዎች መጥፎ ነገር ሲናገሩት ወይም ሲያደርጉበት ጉዳዩን የያዘበት መንገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። አንደኛ1 ጴጥሮስ 2:23 እንዲህ ይላል፦ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” እኛም የክርስቶስን ግሩም ምሳሌ እንድንከተል ምክር ተሰጥቶናል። ሌሎች መጥፎ ነገር ሲያደርጉብን አጸፋውን መመለስ አይኖርብንም። ሁሉም ክርስቲያኖች የሚከተለው ምክር ተሰጥቷቸዋል፦ “ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፣ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ይኑራችሁ፣ ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ።”—1 ጴጥ. 3:8, 9
ምንም ድርሻ አይኖራትም?
11. አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶች የትኛውን ታላቅ መብት ያገኛሉ?
11 ሴቶች ለባላቸው የራስነት ሥልጣን ይገዛሉ ሲባል በትዳራቸው ውስጥ ምንም ድርሻ የላቸውም ማለት ነው? ከቤተሰብም ሆነ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሐሳብ መስጠት አይችሉም ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች በርካታ መብቶችን ሰጥቷል። ክርስቶስ ምድርን በሚገዛበት ጊዜ በሰማይ ከእሱ ጋር ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑት 144,000 ሰዎች የተሰጣቸውን ታላቅ መብት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል ሴቶችም ይገኙበታል! (ገላ. 3:26-29) በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ በዝግጅቱ ውስጥ ለሴቶችም ድርሻ ሰጥቷቸዋል።
12, 13. ሴቶች ትንቢት እንደተናገሩ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
12 ለምሳሌ ያህል፣ በጥንት ዘመን ሴቶች ትንቢት ይናገሩ ነበር። ኢዩኤል 2:28, 29 እንዲህ ይላል፦ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ . . . በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ እንኳ፣ መንፈሴን አፈሳለሁ።”
13 በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን ኢየሩሳሌም በሚገኝ ሰገነት ላይ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ ከተሰበሰቡት 120 የሚያህሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል ሴቶችም ይገኙበት ነበር። የአምላክ መንፈስ የፈሰሰው በተሰበሰቡት ሁሉ ላይ ነበር። በመሆኑም ጴጥሮስ፣ ኢዩኤል የተናገረውን ትንቢት በመጥቀስ ትንቢቱ በወንዶችም በሴቶችም ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ መናገር ችሏል። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ይህ የሆነው ነቢዩ ኢዩኤል እንዲህ ሲል በተናገረው መሠረት ነው፦ አምላክ እንዲህ ይላል፦ ‘በመጨረሻው ቀን መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ . . . በዚያ ቀን በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር መንፈሴን አፈሳለሁ፤ እነሱም ትንቢት ይናገራሉ።’”—ሥራ 2:16-18
14. በጥንት ጊዜ ክርስትናን በማስፋፋት ረገድ ሴቶች ምን ሚና ተጫውተዋል?
14 በአንደኛው መቶ ዘመን ሴቶች ክርስትናን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ስለ አምላክ መንግሥት ለሰዎች የሰበኩ ከመሆኑም ሌላ ከስብከቱ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አከናውነዋል። (ሉቃስ 8:1-3) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ፌበን ‘በክንክራኦስ ጉባኤ እንደምታገለግል’ ተናግሯል። እንዲሁም ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሰላምታ በላከ ጊዜ በርካታ ታማኝ ሴቶችን የጠቀሰ ሲሆን ከእነሱ መካከል ‘በጌታ ሆነው በትጋት የሚሠሩት ጥራይፊና እና ጥራይፎሳ የተባሉት ሴቶች’ ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ “በጌታ ሥራ ብዙ የደከመችውን የምንወዳትን ጰርሲስን ሰላም በሉልኝ” ብሏል።—ሮም 16:1, 12
15. በዛሬው ጊዜ ክርስትናን በማስፋፋት ረገድ ሴቶች ምን ሚና ይጫወታሉ?
15 በዛሬው ጊዜ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ ከሚያውጁት ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አብዛኞቹ በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች ናቸው። (ማቴ. 24:14) ከእነዚህ ሴቶች መካከል ብዙዎቹ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች፣ ሚስዮናውያን እንዲሁም ቤቴላውያን ናቸው። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጠ፤ ብዙ ሴቶችም ዜናውን አሰራጩ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 68:11 የ1980 ትርጉም) እነዚህ ቃላት በእርግጥም እውነት መሆናቸው ተረጋግጧል! ይሖዋ ምሥራቹን በመስበክና ዓላማውን ከግብ በማድረስ ረገድ ሴቶች የሚጫወቱትን ሚና ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ ክርስቲያን ሴቶች ለራስነት ሥልጣን እንዲገዙ መመሪያ ሰጥቷል ሲባል ምንም ድርሻ አይኖራቸውም ማለት አይደለም።
ዝም አላሉም
16, 17. ሴቶች በትዳር ውስጥ ሐሳባቸውን መግለጽ እንደሚችሉ የሣራ ምሳሌ የሚያሳየው እንዴት ነው?
16 ይሖዋ ለሴቶች ብዙ መብቶችን ሰጥቷቸዋል፤ ታዲያ ባሎች ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ከማድረጋቸው በፊት ሚስቶቻቸውን ማማከር አይኖርባቸውም? እንዲህ ማድረጋቸው ጥበብ ነው። ሚስቶች፣ ባሎቻቸው ባያማክሯቸውም እንኳ ሐሳባቸውን እንደገለጹ ወይም እርምጃ እንደወሰዱ የሚናገሩ የተለያዩ ዘገባዎችን በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እናገኛለን። እስቲ ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እንመልከት።
17 የአብርሃም ሁለተኛ ሚስትና ልጇ አክብሮት የጎደለው ነገር በማድረጋቸው አብርሃም እንዲያባርራቸው ሣራ በተደጋጋሚ ትነግረው ነበር። “ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው።” ይሖዋ ግን የሣራን ሐሳብ ተቀብሎት ነበር። አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ አሳብ አይግባህ፤ . . . ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ።” (ዘፍ. 21:8-12) አብርሃም ይሖዋን በመታዘዝ የሣራን ሐሳብ የተቀበለ ሲሆን ያለችውንም አድርጓል።
18. አቢግያ በራሷ ተነሳስታ ምን እርምጃ ወስዳለች?
18 የናባል ሚስት የነበረችውን የአቢግያንም ሁኔታ እንመልከት። ዳዊት፣ ይቀናበት ከነበረው ከንጉሥ ሳኦል በሸሸ ጊዜ የሚኖረው የናባል መንጋ በሚሰማራበት አካባቢ ነበር። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ይህ ሀብታም ሰው ካሉት በርካታ ንብረቶች መካከል አንዱንም አልወሰዱም፤ ከዚህ ይልቅ ንብረቱን ጠብቀውለታል። ናባል ግን “ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው” ስለነበረ ዳዊት በላካቸው ሰዎች ላይ “የስድብ ናዳ አወረደባቸው።” ናባል ‘ጅልነት አብሮት የኖረ ባለጌ’ ሰው ነበር። ዳዊት የላካቸው ሰዎች ናባል ምግብ እንዲሰጣቸው በአክብሮት ሲጠይቁት ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም። አቢግያ የተፈጠረውን ነገር ስትሰማ ምን እርምጃ ወሰደች? ዘገባው እንደሚገልጸው “አቢግያም ጊዜ አላጠፋችም፤ ሁለት መቶ እንጀራ፣ ሁለት አቍማዳ የወይን ጠጅ፣ አምስት የተሰናዱ በጎች፣ አምስት መስፈሪያ የተጠበሰ እሸት፣ መቶ የወይን ዘለላና ዘቢብ፣ ሁለት መቶ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ ወስዳ” ለዳዊትና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ሰጠቻቸው፤ ለባሏ ለናባል ግን ይህን አልነገረችውም። አቢግያ ያደረገችው ነገር ትክክል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ” ይላል። በኋላ ላይ ደግሞ ዳዊት አቢግያን አግብቷታል።—1 ሳሙ. 25:3, 14-19, 23-25, 38-42
‘የተመሰገነች ሴት’
19, 20. አንዲትን ሴት ምስጋና እንድታተርፍ የሚያስችላት ምንድን ነው?
19 ቅዱሳን መጻሕፍት ነገሮችን በይሖዋ መንገድ ስለሚያከናውኑ ሚስቶች በአድናቆት ይናገራሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ “ጠባየ መልካምን ሚስት” እንዲህ በማለት ያወድሳታል፦ “ከቀይ ዕንቍ እጅግ ትበልጣለች። ባሏ ሙሉ በሙሉ ይተማመንባታል፤ የሚጐድልበትም ነገር የለም። በሕይወት ዘመኗ ሁሉ፣ መልካም ታደርግለታለች እንጂ አትጐዳውም።” አክሎም እንዲህ ስላለችው ሚስት እንደሚከተለው ይላል፦ “በጥበብ ትናገራለች፤ በአንደበቷም ቀና ምክር አለ። የቤተ ሰዎቿን ጕዳይ በትጋት ትከታተላለች፤ የስንፍና እንጀራ አትበላም። ልጆቿ ተነሥተው፤ ቡርክት ይሏታል፤ ባሏም እንዲሁ።”—ምሳሌ 31:10-13, 26-29
20 አንዲትን ሴት ምስጋና እንድታተርፍ የሚያስችላት ምንድን ነው? ምሳሌ 31:30 “ቍንጅና አታላይ ነው፤ ውበትም ይረግፋል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን የተመሰገነች ናት” ይላል። ይሖዋን መፍራት እሱ ላቋቋመው የራስነት ሥርዓት በፈቃደኝነት መገዛትንም ይጨምራል። “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ” እንዲሁም “የክርስቶስ ራስ . . . አምላክ እንደሆነ” ሁሉ “የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ” ነው።—1 ቆሮ. 11:3
ለአምላክ ስጦታ አመስጋኞች ሁኑ
21, 22. (ሀ) በትዳር የተጣመሩ ክርስቲያኖች ከአምላክ ላገኙት የጋብቻ ስጦታ አመስጋኝ እንዲሆኑ የሚያነሳሷቸው ምን ምክንያቶች አሉ? (ለ) ይሖዋ ከሥልጣንና ከራስነት ሥርዓት ጋር በተያያዘ ላደረጋቸው ዝግጅቶች አክብሮት ማሳየት የሚኖርብን ለምንድን ነው? (በገጽ 17 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
21 በትዳር የተጣመሩ ክርስቲያኖች አምላክን እንዲያመሰግኑ የሚያነሳሷቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ! በትዳራቸው ደስተኛ ሆነው መኖር ይችላሉ። በተለይ ከአምላክ ያገኙት የጋብቻ ስጦታ አንድ ሆነው ከይሖዋ ጋር እንዲሄዱ ስለሚያስችላቸው ለዚህ ስጦታ አመስጋኞች ሊሆኑ ይችላሉ። (ሩት 1:9፤ ሚክ. 6:8) በትዳር ውስጥ ደስተኛ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ በትክክል የሚያውቀው የጋብቻ መሥራች የሆነው ይሖዋ ነው። ማንኛውንም ነገር ከእሱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ አድርጉ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜም እንኳ “የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ” ይሆናል።—ነህ. 8:10
22 ሚስቱን እንደራሱ የሚወድ ክርስቲያን ባል የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ፍቅርና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ፈሪሃ አምላክ ያላት ሚስቱ ደግሞ እሱን ስለምትደግፈውና በጥልቅ ስለምታከብረው ተወዳጅ ትሆናለች። ከምንም በላይ ደግሞ በትዳራቸው ምሳሌ ስለሚሆኑ ውዳሴ ለሚገባው አምላካችን ለይሖዋ ክብር ያመጣሉ።
-