የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የፍቅር መንገድ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል
    መጠበቂያ ግንብ—1999 | የካቲት 15
    • 9. መጽሐፍ ቅዱስ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይጥሩ ስለነበሩ ግለሰቦች የሚገልጹ ምን የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ይዟል?

      9 ፍቅር “የራሱን ጥቅም ብቻ ፈላጊ አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 13:​5 የ1980 ትርጉም) አፍቃሪ የሆነ ሰው የራሱን ጥቅም ለማስፈጸም ሲል ሌሎችን በተንኮል ለማግባባት አይሞክርም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገሩ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን ይዟል። በምሳሌ ለማስረዳት:- የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ሌሎችን በተንኮል ለማግባባት ስለ ሞከሩ እንደ ደሊላ፣ ኤልዛቤልና ጎቶልያ ስላሉ ሴቶች እናነባለን። (መሳፍንት 16:​16፤ 1 ነገሥት 20:​25፤ 2 ዜና መዋዕል 22:​10-12) የንጉሥ ዳዊት ልጅ የሆነው አቤሴሎምም አለ። ወደ ኢየሩሳሌም ለፍርድ የሚመጡትን ሰዎች ቀርቦ በማነጋገር የንጉሡ ፍርድ ቤት ለችግሮቻቸው ተገቢውን ትኩረት እንደማይሰጥ በለሰለሰ አንደበት ይነግራቸው ነበር። ከዚያም ፍርድ ቤቱ እንደ እሱ ያለ ከልብ የሚያስብ ሰው እንደሚያስፈልገው ፊት ለፊት ይናገር ነበር! (2 ሳሙኤል 15:​2-4) አቤሴሎም በእርግጥ ለተገፉት ሰዎች አዝኖ ሳይሆን የራሱን ፍላጎት ለማሟላት ነበር። ራሱን በራሱ ንጉሥ አድርጎ በመሾም የብዙዎችን ልብ አሸፈተ። ሆኖም ከጊዜ በኋላ አቤሴሎም አሳዛኝ ሽንፈት ገጥሞታል። በሚሞትበት ጊዜ ተገቢ የሆነ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንኳ አልተከናወነለትም።​—⁠2 ሳሙኤል 18:​6-17

      10. የሌሎች ሰዎችን ፍላጎት ግምት ውስጥ እንደምናስገባ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      10 ይህ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ነው። ወንዶችም ሆንን ሴቶች ሌሎችን አግባብቶ የማሳመን ተፈጥሯዊ ችሎታ ሊኖረን ይችላል። በአንድ ውይይት ላይ የበላይነቱን በመያዝ ወይም የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በመጫን ነገሮች እኛ ወደፈለግነው አቅጣጫ እንዲያመሩ የማድረግ ችሎታ ሊኖረን ይችላል። ይሁን እንጂ በእርግጥ ፍቅር ካለን የሌሎች ሰዎችን ፍላጎትም ግምት ውስጥ እናስገባለን። (ፊልጵስዩስ 2:​2-4) ተሰሚነት ያላቸው እኛ የምንሰጣቸው አመለካከቶች ብቻ የሆኑ ይመስል በአምላክ ድርጅት ውስጥ ባካበትነው ተሞክሮ ወይም ባለን የኃላፊነት ቦታ አማካኝነት ሌሎችን መጠቀሚያ አናደርግም ወይም አጠያያቂ የሆኑ አስተሳሰቦችን አናስፋፋም። ከዚህ ይልቅ “ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እናስታውሳለን።​—⁠ምሳሌ 16:​18

  • የፍቅር መንገድ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል
    መጠበቂያ ግንብ—1999 | የካቲት 15
    • 11. (ሀ) በደግነት ላይ የተመሠረተና ተገቢ የሆነ ፍቅር ማሳየት የምንችለው በምን መንገዶች ነው? (ለ) ክፉ በሆነ ነገር እንደማንደሰት እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

      11 በተጨማሪም ጳውሎስ ፍቅር “ደግ” እንደሆነና “ሥርዓተ ቢስ” እንዳልሆነ ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:​4, 5 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ ፍቅር ስድ፣ ባለጌ ወይም ግብረገብነት የጎደለን እንድንሆን አይፈቅድልንም። ከዚህ ይልቅ ስለ ሌሎች ስሜት እናስባለን። ለምሳሌ ያህል አፍቃሪ የሆነ ሰው የሌሎችን ሕሊና የሚረብሹ ነገሮችን ከማድረግ ይቆጠባል። (ከ1 ቆሮንቶስ 8:​13 ጋር አወዳድር።) ፍቅር “ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም።” (1 ቆሮንቶስ 13:​6) የይሖዋን ሕግ የምንወድ ከሆነ የብልግና ድርጊቶችን በግዴለሽነት አንመለከትም ወይም አምላክ በሚጠላቸው ነገሮች አንዝናናም። (መዝሙር 119:​97) ፍቅር በሚያፈርሱ ሳይሆን በሚያንጹ ነገሮች እንድንደሰት ይረዳናል።​—⁠ሮሜ 15:​2፤ 1 ቆሮንቶስ 10:​23, 24፤ 14:​26

      12, 13. (ሀ) አንድ ሰው በሚያስቀይመን ጊዜ ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ሊሆን ይገባል? (ለ) የተቆጣነው በበቂ ምክንያት ቢሆንም እንኳ ጥበብ የጎደለው እርምጃ እንድንወስድ ሊያደርገን እንደሚችል የሚያሳዩ ምሳሌዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቀስ።

      12 ጳውሎስ ፍቅር “አይበሳጭም” (“አትንኩኝ ባይ አይደለም፣” ፊሊፕስ) ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:​5) ፍጹማን ስላልሆንን አንድ ሰው ሲያስቀይመን መበሳጨታችን ወይም መቆጣታችን የሚጠበቅ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ለረዥም ጊዜ ቅሬታን አምቆ መያዝ ወይም ተቆጥቶ መቆየት ስህተት ነው። (መዝሙር 4:​4፤ ኤፌሶን 4:​26) የምንቆጣበት በቂ ምክንያት ቢኖርም እንኳ ይህን የመሰለውን ቁጣ ካልተቆጣጠርነው በይሖዋ ፊት ሊያስጠይቀን የሚችል ጥበብ የጎደለው እርምጃ እንድንወስድ ያደርገን ይሆናል።​—⁠ዘፍጥረት 34:​1-31፤ 49:​5-7፤ ዘኁልቁ 12:​3፤ 20:​10-12፤ መዝሙር 106:​32, 33

      13 አንዳንዶች የሌሎች አለፍጽምና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዳይገኙ ወይም በመስክ አገልግሎት እንዳይካፈሉ እንቅፋት እንዲሆንባቸው ፈቅደዋል። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰብ ተቃውሞን፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውን ማንጓጠጥና ሌሎች ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም ለእምነታቸው በብርቱ የተጋደሉ ሰዎች ነበሩ። እነዚህን እንቅፋቶች በጽናት የተቋቋሟቸው በንጹህ አቋማቸው ላይ እንደተቃጡ ፈተናዎች አድርገው ስለተመለከቷቸው ነበር፤ ደግሞም ናቸው። ሆኖም አንድ መሰል ክርስቲያን ፍቅር የጎደለው ነገር ቢናገር ወይም ቢያደርግስ? ይህስ ቢሆን በንጹህ አቋም ላይ የመጣ ፈተና ሊሆን አይችልምን? በእርግጥ ነው፤ ምክንያቱም እንደ ተቆጣን ከቆየን ‘ለዲያብሎስ ስፍራ ልንሰጥ’ እንችላለን።​—⁠ኤፌሶን 4:​27

      14, 15. (ሀ) ‘በደልን መቁጠር’ ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) ይቅር ባዮች በመሆን ረገድ ይሖዋን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?

      14 ጳውሎስ፣ ፍቅር “በደልን አይቈጥርም” ብሎ መናገሩ አለምክንያት አልነበረም። (1 ቆሮንቶስ 13:​5) እዚህ ላይ ጳውሎስ መቁጠር የሚል ከሒሳብ ጋር የተያያዘ ቃል መጠቀሙ የተሠራው በደል እንዳይረሳ በቋሚ የሒሳብ መዝገብ ላይ ማስፈርን ለማመልከት ነው። የተሠራውን በደል መጥቀስ የሚያስፈልግበት ጊዜ ይመጣ ይመስል ጎጂ የሆነን ቃል ወይም ድርጊት በአእምሮ መዝግቦ መያዙ ፍቅራዊ ነውን? ይሖዋ ይህን በመሰለ ምሕረት የለሽ መንገድ አንድ በአንድ ስለማይመረምረን ምንኛ አመስጋኞች መሆን እንችላለን! (መዝሙር 130:​3) አዎን፣ ንስሐ ከገባን የሠራነውን ስህተት ሁሉ ይደመስስልናል።​—⁠ሥራ 3:​19

      15 በዚህ ረገድ ይሖዋን ልንመስለው እንችላለን። አንድ ሰው ትንሽ ቅር የሚያሰኝ ነገር ያደረገብን በመሰለን ቁጥር እንዲያው ለምን ተነካሁ ባዮች መሆን የለብንም። በቀላሉ የምንቀየም ከሆነ ያስቀየመን ሰው ሊያደርስብን ከሚችለው ጉዳት የበለጠ ራሳችንን ልንጎዳ እንችላለን። (መክብብ 7:​9, 22) ከዚህ ይልቅ ፍቅር ‘ሁሉን እንደሚያምን’ ማስታወስ ያስፈልገናል። (1 ቆሮንቶስ 13:​7) ማናችንም ብንሆን የተነገረንን ሁሉ ማመን አለብን ማለት ባይሆንም የወንድሞቻችንን ሐሳብ ከልክ በላይ የምንጠራጠር መሆን ደግሞ አይገባንም። በተቻለ መጠን አንዳችን ስለ ሌላው አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ እንጣር።​—⁠ቆላስይስ 3:​13

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ