-
“የክርስቶስን አስተሳሰብ” ማወቅመጠበቂያ ግንብ—2000 | የካቲት 15
-
-
“የክርስቶስን አስተሳሰብ” ማወቅ
“እንዲያስተምረው የጌታን ልብ [“የይሖዋን አስተሳሰብ፣” NW ] ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ [“አስተሳሰብ፣” NW ] አለን።”—1 ቆሮንቶስ 2:16
1, 2. ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ኢየሱስን በተመለከተ ስለ ምን ነገር መግለጽን ይበልጥ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል?
ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው ነበር? የፀጉሩ፣ የቆዳው፣ የዓይኑ ቀለም ምን ዓይነት ነበር? ረዥም ነበር ወይስ አጭር? ክብደቱስ ምን ያክል ነበር? ባለፉት መቶ ዘመናት ኢየሱስን በተለያየ መንገድ በሥዕል ለመግለጽ ተሞክሯል። አንዳንዶቹ ሥዕሎች ከእውነታው ብዙም ያልራቁ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ምንም የማይገናኙ ናቸው። አንዳንዶች ፈርጠም ያለ ሰውነት ያለው ወንዳ ወንድ አድርገው ሲሥሉት ሌሎች ደግሞ ከሲታና ልፍስፍስ አድርገው ሥለውታል።
2 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ቁመና ላይ ትኩረት አያደርግም። ከዚያ ይልቅ ይሖዋ ይበልጥ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው ኢየሱስ ምን ዓይነት ባሕርይ ያለው ሰው እንደነበር መገለጹ ላይ ነበር። የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ የተናገረውንና ያደረገውን ነገር መዘገብ ብቻ ሳይሆን ከተናገራቸውና ካደረጋቸው ነገሮች በስተጀርባ የነበረውን ጥልቅ ስሜትና አስተሳሰብ ጭምር ገልጠውልናል። እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ አራት ዘገባዎች ሐዋርያው ጳውሎስ “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ብሎ የጠቀሰውን ነገር ቀረብ ብለን እንድንመረምር ያስችሉናል። (1 ቆሮንቶስ 2:16 NW ) ከኢየሱስ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ባሕርይ ጋር መተዋወቃችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው።
3. የክርስቶስን አስተሳሰብ በሚገባ ማወቃችን ምን ማስተዋል ያስገኝልናል?
3 አንደኛ፣ የክርስቶስ አስተሳሰብ የይሖዋ አምላክን አስተሳሰብ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ኢየሱስ ከአባቱ ጋር በጣም የጠበቀ ቅርርብ ስለነበረው እንዲህ ብሎ ለመናገር ችሏል:- “ወልድንም ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፣ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም።” (ሉቃስ 10:22) እዚህ ላይ ኢየሱስ ‘ይሖዋ ምን እንደሚመስል ለማወቅ ከፈለጋችሁ እኔን ተመልከቱ’ ብሎ የተናገረ ያህል ነበር። (ዮሐንስ 14:9) ስለዚህ ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ አስተሳሰብና ስሜት የሚናገሩትን ዘገባ በምናጠናበት ጊዜ እግረ መንገዳችንን የይሖዋን አስተሳሰብና ስሜት እየተማርን ነው ማለት ነው። እንዲህ ያለው እውቀት ወደ አምላካችን ይበልጥ እንድንቀርብ ያስችለናል።—ያዕቆብ 4:8
4. ልክ እንደ ኢየሱስ ለማድረግ በመጀመሪያ ምን ነገር መማር አለብን? ለምንስ?
4 ሁለተኛ፣ የኢየሱስን አስተሳሰብ ማወቃችን ‘ፈለጉን በቅርብ እንድንከተል’ ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስን መከተል ማለት እንዲያው የተናገራቸውን ቃላት ደግሞ መናገርና ድርጊቱን መቅዳት ማለት አይደለም። በንግግርና በድርጊት የሚንጸባረቀው አስተሳሰብና ስሜት ስለሆነ ክርስቶስን መከተል እርሱ የነበረው ዓይነት “አሳብ” ማዳበርን ይጠይቅብናል። (ፊልጵስዩስ 2:5) በሌላ አባባል የኢየሱስን ተግባር መኮረጅ የምንፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ ፍጽምና የሌለን ቢሆንም እንኳ አቅማችን በሚፈቅድልን መጠን የኢየሱስን ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት ማዳበርን መማር አለብን። ስለዚህ ከወንጌል ጸሐፊዎች በምናገኘው እርዳታ የክርስቶስን አስተሳሰብ ቀረብ ብለን ለመመርመር እንሞክር። ኢየሱስ ያን ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት እንዲኖረው ያደረጉትን ነገሮች በመጀመሪያ እንመለከታለን።
ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረው ሕይወት
5, 6. (ሀ) አብረናቸው የምንውላቸው ሰዎች በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ? (ለ) የአምላክ የበኩር ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከማን ጋር ይኖር ነበር? ይህስ በእርሱ ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል?
5 አብረን የምንውለው ሰው በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችንና በድርጊታችን ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።a (ምሳሌ 13:20) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ሰማይ እያለ ከማን ጋር እንደነበር አስብ። ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት “ቃል” ወይም የአምላክ ቃል አቀባይ ይባል እንደነበር የዮሐንስ ወንጌል ይገልጽልናል። ዮሐንስ እንዲህ ይላል:- “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር [“አምላክ፣” NW ] ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።” (ዮሐንስ 1:1, 2) ይሖዋ መጀመሪያ ስለሌለው ቃል ‘በመጀመሪያ’ ከአምላክ ጋር ነበር የሚለው አባባል የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች መጀመሪያ መሆኑን የሚያመለክት መሆን አለበት። (መዝሙር 90:2) ኢየሱስ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው።” ስለዚህ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታትና ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በሕይወት ይኖር ነበር ማለት ነው።—ቆላስይስ 1:15፤ ራእይ 3:14
6 አንዳንድ ሳይንሳዊ ግምቶች እንደሚሉት ከሆነ ግዑዙ ጠፈር 12 ቢልዮን ለሚያክል ዓመት ኖሯል። እነዚህ ግምቶች ትንሽ እንኳ ወደ ትክክለኛው የሚቀርቡ ከሆኑ የአምላክ የበኩር ልጅ ከአዳም መፈጠር በፊት ሕልቆ መሳፍርት ለሌለው ዘመን ከአባቱ ጋር ኖሯል ማለት ነው። (ከሚክያስ 5:2 ጋር አወዳደር።) ስለሆነም በሁለቱ መካከል የጠበቀና ጥልቀት ያለው ዝምድና ሊመሠረት ችሏል። ይህ የበኩር ልጅ ሰው ከመሆኑ በፊት በነበረው ሕይወት በጥበብ ተመስሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ዕለት ዕለት [ይሖዋን] ደስ አሰኘው ነበርሁ፤ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበር” ብሏል። (ምሳሌ 8:30) በእርግጥም የአምላክ ልጅ የፍቅር ምንጭ ከሆነው አካል ጋር ቁጥር ስፍር ለሌለው ጊዜ ተቀራርቦ መኖሩ ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ጥርጥር የለውም! (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ልጅ የአባቱን አስተሳሰብ፣ ስሜትና መንገድ ከሌላ ከማንም በበለጠ መንገድ ለማወቅና ለማንጸባረቅ ችሏል።—ማቴዎስ 11:27
ምድራዊ ሕይወቱና የገጠሙት ተጽዕኖዎች
7. የአምላክ የበኩር ልጅ የግድ ወደ ምድር እንዲመጣ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ምንድን ነው?
7 የይሖዋ ዓላማ ልጁ “በድካማችን ሊራራልን” የሚችል ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት ሆኖ እንዲያገለግል ማዘጋጀት ስለነበረ የአምላክ ልጅ ተጨማሪ ትምህርቶችን መቅሰም ነበረበት። (ዕብራውያን 4:15) ይህ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣበት አንዱ ምክንያት ለዚህ ቦታ የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ነው። ኢየሱስ እዚህ ምድር ላይ ሥጋና ደም ለብሶ ሲኖር ቀደም ሲል በሰማይ ይመለከታቸው ብቻ የነበሩትን ሁኔታዎችና ተጽዕኖዎች ተጋርቷል። አሁን ሰዎች የሚሰማቸው ስሜት በራሱ ላይ ሊደርስ ነው። በተለያዩ ጊዜያት በድካም ዝሏል፣ ተጠምቷል እንዲሁም ተርቧል። (ማቴዎስ 4:2፤ ዮሐንስ 4:6, 7) ከዚያም በላይ የደረሰበትን ችግርና ሥቃይ በሙሉ ተቋቁሟል። በዚህ መንገድ ‘መታዘዝን ተምሮ’ ሊቀ ካህናት ሆኖ ለሚያከናውነው ሥራ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኗል።—ዕብራውያን 5:8-10
8. ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው የልጅነት ሕይወት ምን የምናውቀው ነገር አለ?
8 ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው የልጅነት ሕይወትስ ምን ይመስል ነበር? ስለ ልጅነቱ የተዘገበው ታሪክ በጣም አናሳ ነው። እንዲያውም በተወለደበት ወቅት ስለደረሱት ክንውኖች የዘገቡት ማቴዎስና ሉቃስ ብቻ ናቸው። የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ይኖር እንደነበር ያውቃሉ። ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ አጥጋቢ በሆነ መንገድ ማብራሪያ ሊያስገኝ የሚችለው ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረው ሕይወት ነው። ያም ሆኖ ግን ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው ነበር። ፍጹም የነበረ ቢሆንም እንኳ ትምህርት እየቀሰመ ከሕፃንነት ወደ ልጅነት ከዚያም ከጉርምስና ወደ ሙሉ ሰው ማደግ ነበረበት። (ሉቃስ 2:51, 52) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ የልጅነት ሕይወት አንዳንድ ነገሮችን ይገልጻል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ተጽዕኖ እንዳሳደሩበት ምንም ጥርጥር የለውም።
9. (ሀ) ኢየሱስ የተወለደው በድሃ ቤተሰብ ውስጥ እንደሆነ የሚጠቁም ምን ማስረጃ አለ? (ለ) ኢየሱስ ያደገው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም?
9 ኢየሱስ በአንድ ድሃ ቤተሰብ መካከል እንደተወለደ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ይህም ኢየሱስ ከተወለደ ከ40 ቀናት በኋላ ዮሴፍና ማርያም በቤተ መቅደስ ለመሥዋዕት ካቀረቡት ነገር መረዳት ይቻላል። ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ጠቦት፣ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ የእርግብ ጫጩት ወይም አንድ ዋኖስ ይዘው ከመሄድ ይልቅ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች” ይዘው ሄዱ። (ሉቃስ 2:24 የ1980 ትርጉም ) በሙሴ ሕግ መሠረት እንዲህ ያለውን መሥዋዕት የሚያቀርቡት ደግሞ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ናቸው። (ዘሌዋውያን 12:6-8) ከጊዜ በኋላ ይህ ዝቅተኛ ኑሮ ያለው ቤተሰብ በቁጥር እያደገ ሄደ። ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከተወለደ በኋላ ዮሴፍና ማርያም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ቢያንስ ስድስት ልጆችን ወልደዋል። (ማቴዎስ 13:55, 56) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ሰፊ በሆነ ምናልባትም መጠነኛ ገቢ ባለው ቤተሰብ ውስጥ አደገ።
10. ማርያም እና ዮሴፍ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች እንደነበሩ የሚያሳየው ምንድን ነው?
10 ኢየሱስን ተንከባክበው ያሳደጉት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ናቸው። እናቱ ማርያም በጣም ጥሩ ሴት ነበረች። መልአኩ ገብርኤል ሰላምታ ሲሰጥ “ደስ ይበልሽ፣ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” እንዳላት አስታውስ። (ሉቃስ 1:28) ዮሴፍም ቢሆን ለአምላክ ያደረ ሰው ነበር። የማለፍን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም በየዓመቱ 150 ኪሎ ሜትር በእግሩ ይጓዝ ነበር። በዚህ በዓል ላይ እንዲገኙ የሚጠበቅባቸው ወንዶች ብቻ ቢሆኑም ማርያምም አብራው ትሄድ ነበር። (ዘጸአት 23:17፤ ሉቃስ 2:41) እንዲህ ባለው አንድ አጋጣሚ ዮሴፍና ማርያም የጠፋባቸውን ኢየሱስን ለማግኘት ከፍተኛ ፍለጋ ካደረጉ በኋላ የ12 ዓመቱ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመምህራን መካከል ተቀምጦ አገኙት። ኢየሱስ በጣም ተጨንቀው ለነበሩት ወላጆቹ “በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። (ሉቃስ 2:49) “አባቴ” የሚለው ቃል ልጅ ለነበረው ለኢየሱስ ሞቅ ያለ የመውደድ ስሜት የሚያስተላልፍና አዎንታዊ አንድምታ የነበረው መሆን አለበት። አንደኛው ነገር፣ እውነተኛ አባቱ ይሖዋ መሆኑን ተነግሮት መሆን አለበት። ከዚህም በተጨማሪ ዮሴፍ ለእርሱ ጥሩ አሳዳጊ አባት ነበር። መቼም ይሖዋ ውድ ልጁን እንዲያሳድግለት ኃይለኛ ወይም ጨካኝ የሆነ ሰው እንደማይመርጥ የታወቀ ነው!
11. ኢየሱስ ምን ዓይነት የእጅ ሙያ ተምሮ ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በዚህ ሙያ መሥራት ምን ይጠይቅ ነበር?
11 ኢየሱስ ናዝሬት በኖረበት ዓመታት ከአሳዳጊው አባቱ ከዮሴፍ ሳይሆን አይቀርም የአናፂነትን ሙያ ተምሯል። ኢየሱስ ይህን የእጅ ሙያ ተክኖት ስለነበር እሱ ራሱ “ጸራቢው” ተብሎ ተጠርቷል። (ማርቆስ 6:3) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አናፂዎች ቤቶችን፣ (ጠረጴዛ፣ በርጩማና አግዳሚ ወንበሮችን ጨምሮ) የቤት ዕቃዎችንና የግብርና መሣሪያዎችን ይሠሩ ነበር። በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው ሰማዕቱ ጀስቲን ዲያሎግ ዊዝ ትራይፎ በተባለው መጽሐፉ ላይ ስለ ኢየሱስ ሲጽፍ “በአናፂነት ሙያው ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ ሞፈርና ቀንበሮችን የመሥራት ልማድ ነበረው” ብሏል። በዚያ ዘመን አንድ አናፂ ለሥራው የሚጠቀምባቸውን እንጨቶች በግዢ ማግኘት ስለማይችል እንዲህ ዓይነቱ ሥራ አድካሚ ነበር። ወደ ጫካ ሄዶ ዛፍ መርጦ ከቆረጠ በኋላ ተሸክሞ ወደ ቤት የሚያመጣው ራሱ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ መተዳደሪያ ማግኘት፣ ደንበኞችን ማግባባትና ቤተሰብን በገንዘብ መደጎም ያለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ሳይገነዘብ አይቀርም።
12. ዮሴፍ ከኢየሱስ ቀድሞ እንደ ሞተ የሚጠቁሙ አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ይህስ ኢየሱስ ምን እንዲያደርግ ይጠይቅበታል?
12 ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ እንደ መሆኑ መጠንና በተለይ ደግሞ ዮሴፍ የሞተው ከእርሱ ቀድሞ ሳይሆን ስለማይቀር ቤተሰቡን የማስተዳደሩ ኃላፊነት በእርሱ ጫንቃ ላይ ሳይወድቅ አልቀረም።b የጥር 1, 1900 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እንዲህ ብሎ ነበር:- “ዮሴፍ የሞተው ኢየሱስ ገና ወጣት በነበረበት ጊዜ እንደሆነና በዚህም የተነሳ ኢየሱስ የአናፂነቱን ሥራ ተረክቦ ቤተሰቡን ማስተዳደር እንደጀመረ በአፈ ታሪክ ይነገራል። ይህም ኢየሱስ አናፂ እንደሆነ ተደርጎ መጠራቱ እንዲሁም እናቱና ወንድሞቹ ሲጠቀሱ ዮሴፍ ግን አለመጠቀሱ ይህን አፈ ታሪክ ቅዱሳን ጽሑፎችም በጥቂቱ የሚደግፉት ይመስላል። (ማርቆስ 6:3) . . . ይህ ሁኔታ ከተከሰተበት [በሉቃስ 2:41-49 ተመዝግቦ የሚገኘው ማለት ነው] ጊዜ አንስቶ እስከ ተጠመቀበት ጊዜ ድረስ ያለውን ማለትም ጌታችን ረዥሙን አሥራ ስምንት ዓመት ያሳለፈው የዕለት ተዕለት የኑሮ ተግባሮችን በማከናወን ሳይሆን አይቀርም።” ኢየሱስን ጨምሮ ማርያምና ልጆቿ ተወዳጅ የሆነን ባልና አባት በሞት ማጣት ምን ያህል አሳዛኝ መሆኑን እንደሚያውቁ ግልጽ ነው።
13. ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር ሌላ ማንም ሰው ያልነበረው እውቀት፣ ማስተዋልና የአዛኝነት ስሜት ነበረው የምንለው ለምንድን ነው?
13 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ የተመቻቸ ኑሮ ባለው ቤተሰብ ውስጥ አልተወለደም። ከዚያ ይልቅ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ሕይወት ምን እንደሚመስል ቀምሷል። ከዚያም በ29 እዘአ ኢየሱስ የተሰጠውን መለኮታዊ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ ደረሰ። ልክ በዚያ ዓመት በውኃ ተጠመቀና የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ እንደገና ተወለደ። በዚህ ወቅት ‘ሰማይ መከፈቱ’ አሁን ቀደም ሲል የነበረውን አስተሳሰብና ስሜት ጨምሮ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ የነበረውን ሕይወት ማስታወስ የሚችል መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። (ሉቃስ 3:21, 22) ስለዚህ ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረው ሌላ ማንም ሰው የሌለውን እውቀት፣ ማስተዋልና ጥልቅ ስሜት ይዞ ነው። የወንጌል ጸሐፊዎች በአብዛኛው ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ባከናወናቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ያለ ምክንያት አልነበረም። እንደዚያም ሆኖ እንኳ በአገልግሎቱ ወቅት የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች በሙሉ መጻፍም አልቻሉም። (ዮሐንስ 21:25) ሆኖም እነዚህ የወንጌል ጸሐፊዎች በመንፈስ አነሳሽነት የመዘገቧቸው ነገሮች እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የነበረውን አስተሳሰብ በሚገባ እንድናውቅ ያስችሉናል።
ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው ነበር?
14. ወንጌሎች ኢየሱስ ጥልቅ የሆነ የመራራትና የአዛኝነት ስሜት እንደነበረው የገለጹት እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ጥልቅ የሆነ የመራራትና የአዛኝነት ስሜት እንደነበረው ከወንጌል ዘገባዎች ለመረዳት ይቻላል። ለአንድ ለምጻም የርኅራኄ ስሜት በማሳየት (ማርቆስ 1:40, 41)፣ ጥሩ ምላሽ ላልሰጡ ሰዎች ከልቡ በማዘን (ሉቃስ 19:41, 42)፣ ስግብግብ በሆኑ የገንዘብ ለዋጮች ላይ የጽድቅ ቁጣ በመቆጣት የተለያየ ዓይነት ስሜት አንጸባርቋል። (ዮሐንስ 2:13-17) ኢየሱስ የሌሎችን ችግር እንደራሱ አድርጎ ይመለከት ስለነበር የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በእንባው እንኳን ለመግለጽ ወደኋላ አይልም ነበር። በጣም አድርጎ ይወደው የነበረው አልአዛር በሞተ ጊዜ የአልአዛር እህት ማርያም ስቅስቅ ብላ ስታለቅስ ሲያያት ስሜቱ በጥልቅ ከመነካቱ የተነሳ በሰዎች ፊት እንባውን አፍስሷል።—ዮሐንስ 11:32-36
15. ኢየሱስ ሰዎችን የተመለከተበትና የያዘበት መንገድ ጥልቅ የሆነ የመራራት ስሜት እንደነበረው ያንጸባረቀው እንዴት ነበር?
15 ኢየሱስ የነበረው ከአንጀት የመራራት ስሜት በተለይ ለሰዎች በነበረው አመለካከት እንዲሁም ለእነርሱ ባደረገው አያያዝ ግልጽ ሆኖ ታይቷል። ድሆችና የተጨቆኑ ሰዎች ‘ለነፍሳቸው ዕረፍት እንዲያገኙ’ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። (ማቴዎስ 11:4, 5, 28-30) አንዲት ደም የሚፈስሳት ሴት ልብሱን በነካች ጊዜም ይሁን አንድ ዓይነ ስውር በጩኸት ልመናውን ባበዛ ጊዜ ባደረገው ነገር እንደታየው መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማድረግ ሥራ እንደበዛበት ሆኖ አልተሰማውም። (ማቴዎስ 9:20-22፤ ማርቆስ 10:46-52) ኢየሱስ ሌሎች የሚያደርጉትን መልካም ነገር በመመልከት ያመሰግናቸው የነበረ ሲሆን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም ተግሣጽ ለመስጠት ወደኋላ አይልም ነበር። (ማቴዎስ 16:23፤ ዮሐንስ 1:47፤ 8:44) ሴቶች ብዙ መብታቸውን በተነፈጉበት በዚያ ዘመን ኢየሱስ ሚዛናዊ የሆነ አክብሮት ይሰጣቸው ነበር። (ዮሐንስ 4:9, 27) የተወሰኑ ሴቶች በራሳቸው ወጪ እርሱን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑት አለምክንያት አይደለም።—ሉቃስ 8:3
16. ኢየሱስ ለኑሮ ጉዳዮችና ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?
16 ኢየሱስ ለኑሮ ጉዳዮች ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። ቁሳዊ ነገሮችን በአንደኛ ቦታ አላስቀመጠም። ቁሳዊ ነገር እንዲያው ምንም አልነበረውም ለማለት ይቻላል። “ራሱን የሚያስጠጋበት” እንኳ እንደሌለው ተናግሯል። (ማቴዎስ 8:20) ሆኖም ኢየሱስ ሌሎች የሚደሰቱበትን ነገር አድርጓል። ሙዚቃ፣ ዘፈን፣ ሣቅና ጨዋታ በነበረበት በአንድ የሠርግ ድግስ ላይ የተገኘው ለመደሰት እንደሆነ ግልጽ ነው። እንዲያውም የመጀመሪያውን ተዓምር የፈጸመው በዚህ ወቅት ነበር። የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ ውኃውን “የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል” ወደተባለለት መጠጥ ማለትም ወደ ጥሩ ወይን ጠጅ ቀይሯል። (መዝሙር 104:15፤ ዮሐንስ 2:1-11) በዚህ መንገድ ዝግጅቱ ሳይቋረጥ ሊቀጥል ችሏል፤ ሙሽሮቹም ከኃፍረት ድነዋል። ኢየሱስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ብዙ ጊዜውን በአገልግሎቱ ያጠፋ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ መገለጹ ሚዛናዊነቱን የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው።—ዮሐንስ 4:34
17. ኢየሱስ የተዋጣለት አስተማሪ መሆኑ የማያስገርመን ለምንድን ነው? ትምህርቶቹስ ምን ነገር የሚያንጸባርቁ ነበሩ?
17 ኢየሱስ የተዋጣለት አስተማሪ ነበር። አብዛኞቹ ትምህርቶቹ ዕለት ተዕለት በሚያጋጥሙ እውነታዎች ላይ የተመሠረቱ ሲሆኑ እርሱም በሚገባ የሚያውቃቸው ነበሩ። (ማቴዎስ 13:33፤ ሉቃስ 15:8) በጣም ግልጽ፣ ቀላልና ተግባራዊ የሆነ የማስተማር ዘዴው አቻ የማይገኝለት ነበር። ከሁሉም ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ግን ያስተማረው ነገር ነው። የኢየሱስ ትምህርቶች አድማጮቹ ከይሖዋ አስተሳሰብ፣ ስሜትና መንገዶች ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ ያለውን ውስጣዊ ምኞት የሚያንጸባርቁ ነበሩ።—ዮሐንስ 17:6-8
18, 19. (ሀ) ኢየሱስ አባቱን የገለጸው በየትኞቹ ሕያው የሆኑ ቃላት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ምን ነገር ይብራራል?
18 ኢየሱስ ምሳሌዎችን ደጋግሞ በመጠቀም አባቱን ሊረሳ በማይችል መንገድ ሕያው አድርጎ ገልጾታል። ስለ አምላክ መሐሪነት በደፈናው መናገር አንድ ነገር ነው። ሆኖም ጠፍቶ የነበረው ልጁ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ገና ከሩቅ ሳለ ተመልክቶ ‘ሮጦ ሄዶ አንገቱ ላይ ጥምጥም ብሎ በሳመው’ ይቅር ባይ አባት ይሖዋን መመሰል ግን ሌላ ነገር ነው። (ሉቃስ 15:11-24) ኢየሱስ የሃይማኖታዊ መሪዎች ተራውን ሕዝብ በንቀት እንዲመለከቱ የሚያደርገውን አጉል ልማድ በማስወገድ አባቱ የሚሰማው በጉራ ለታይታ ጸሎት የሚያቀርበውን ፈሪሳዊ ሳይሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ ልመና የሚያቀርብን ቀረጥ ሰብሳቢ እንደሆነ በመግለጽ አባቱ በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ መሆኑን አብራርቷል። (ሉቃስ 18:9-14) ይሖዋ ትንሿ ድንቢጥ መሬት ብትወድቅ የሚያውቅ አሳቢ አምላክ መሆኑን ኢየሱስ ሕያው በሆነ መንገድ ገልጾታል። ኢየሱስ “አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 10:29, 31) ሰዎች በኢየሱስ ‘የማስተማር ዘዴ’ የተደነቁበትና የተሳቡበት ምክንያት ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 7:28, 29) እንዲያውም በአንድ ወቅት “ብዙ ሕዝብ” ምግብ በአፋቸው ሳይዞር ለሦስት ቀናት አብረውት ቆይተዋል!—ማርቆስ 8:1, 2
19 ይሖዋ በቃሉ ውስጥ የክርስቶስን አስተሳሰብ ስለገለጠልን አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን! ታዲያ እኛስ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበርና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህ በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መንፈሳዊ ፍጥረታት አብረዋቸው ባሉ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታት ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ራእይ 12:3, 4 ላይ ተመልክቷል። እዚህ ጥቅስ ላይ ሰይጣን ሌሎች “ከዋክብት”ን ወይም መንፈሳዊ ልጆችን የእርሱ የዓመፅ ድርጊት ተባባሪ እንዲሆኑ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል “ዘንዶ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል።—ከኢዮብ 38:7 ጋር አወዳድር።
b ዮሴፍ ለመጨረሻ ጊዜ በቀጥታ የተጠቀሰው የ12 ዓመት ልጅ የነበረው ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በተገኘበት ወቅት ነው። ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት በቃና ተደርጎ በነበረው የሠርግ ግብዣ ላይ ዮሴፍ እንደተገኘ የሚገልጽ ማስረጃ የለም። (ዮሐንስ 2:1-3) በ33 እዘአ ኢየሱስ ተሰቅሎ ሳለ ማርያምን አደራ የሰጠው ለተወደደው ለሐዋርያው ዮሐንስ ነበር። ዮሴፍ በሕይወት የነበረ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ እንዲህ አያደርግም ነበር።—ዮሐንስ 19:26, 27
-
-
‘ክርስቶስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ’ አላችሁን?መጠበቂያ ግንብ—2000 | የካቲት 15
-
-
‘ክርስቶስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ’ አላችሁን?
“ጽናትንና መጽናናትን የሚሰጠው አምላክ . . . ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ ይስጣችሁ።”—ሮሜ 15:5 NW
1. በብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና ሥዕሎች ላይ ኢየሱስ በምን መንገድ ተገልጿል? ይህስ ኢየሱስን በትክክል የማይገልጽ የሆነው ለምንድን ነው?
“አንድም ቀን ሲስቅ ታይቶ አያውቅም።” አንድ የጥንት የሮማ ባለ ሥልጣን ጽፎታል ተብሎ በሃሰት በሚነገርለት በአንድ ጽሑፍ ላይ ኢየሱስ የተገለጸው በዚህ መንገድ ነው። አሁን ባለበት ሁኔታ ከ11ኛው መቶ ዘመን አንስቶ ይታወቅ የነበረው ይህ የጽሑፍ ሰነድ በብዙ ሠዓሊያን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይነገርለታል።a በብዙ ሥዕሎች ላይ ኢየሱስ ፈገግታ የሚባል ነገር የማያውቅ በሐዘን የተደቆሰ እንደሆነ ተደርጎ ተስሏል። ወንጌሎች ሞቅ ያለ መንፈስና የጠለቀ የርኅራኄ ስሜት እንዳለው አድርገው የገለጹትን ኢየሱስን ይህን ዓይነት ገጽታ እንዲላበስ ማድረግ አግባብ አይሆንም።
2. “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረውን ዓይነት አስተሳሰብ” ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ ለምን ነገር ያስታጥቀናል?
2 እውነተኛውን ኢየሱስ በትክክል ለማወቅ ከፈለግን አእምሯችንንና ልባችንን ኢየሱስ ምድር በነበረበት ወቅት ምን ዓይነት ሰው እንደነበር በሚገልጸው ትክክለኛ እውቀት መሙላት አለብን። ስለዚህ ስሜቱን፣ ማስተዋሉን፣ አስተሳሰቡንና ምክንያታዊነቱን ስለሚገልጸው ስለ “ክርስቶስ አስተሳሰብ” የጠለቀ ማስተዋል ማግኘት እንችል ዘንድ አንዳንድ የወንጌል ዘገባዎች የሚሰጡትን መግለጫ እንመርምር። (1 ቆሮንቶስ 2:16 NW ) እግረ መንገዳችንንም “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ” ማዳበር የምንችልበትን መንገድ እንመልከት። (ሮሜ 15:5 NW ) እንዲህ ካደረግን በራሳችን ሕይወትም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ እሱ የተወልንን ምሳሌ ለመከተል በተሻለ ሁኔታ የታጠቅን ልንሆን እንችላለን።—ዮሐንስ 13:15
በቀላሉ የሚቀረብ
3, 4. (ሀ) በማርቆስ 10:13-16 ላይ የተመዘገበው ታሪክ መቼት ምን ይመስላል? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ ልጆች ወደ እርሱ እንዳይቀርቡ በከለከሉ ጊዜ ኢየሱስ ምን ብሎ ተናገረ?
3 ሰዎች ከኢየሱስ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። በተለያዩ ጊዜያት የተለያየ ዕድሜና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች ሳይሸማቀቁ ይቀርቡት ነበር። ማርቆስ 10:13-16 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ታሪክ ተመልከት። ታሪኩ የተፈጸመው አሰቃቂ ሞት ለመጋፈጥ ወደ ኢየሩሳሌም ለመጨረሻ ጊዜ እያመራ ባለበት በአገልግሎቱ መደምደሚያ አካባቢ ነበር።—ማርቆስ 10:32-34
4 ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ኢየሱስ እንዲባርክላቸው ሰዎች ልጆቻቸውን፣ ሕፃናትን ጭምር ወደ እሱ ማምጣት ጀመሩ።b ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ልጆቹ ወደ ኢየሱስ እንዳይቀርቡ ለመከልከል ሞከሩ። ምናልባት ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በዚህ ወሳኝ በሆነ ሳምንት በልጆች መቸገር እንደማይፈልግ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ተሳስተው ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እያደረጉ ያሉትን ነገር ሲያስተውል አልተደሰተም። ኢየሱስ “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው” በማለት ልጆቹን ወደ እሱ ጠራቸው። (ማርቆስ 10:14) ከዚያም ልባዊ ርኅራኄና ፍቅር የሚያንጸባርቅ ነገር አደረገ። ዘገባው “አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው” በማለት ይነግረናል። (ማርቆስ 10:16) ኢየሱስ ባቀፋቸው ጊዜ ልጆቹ ምንም እንዳልተሸማቀቁ ግልጽ ነው።
5. ማርቆስ 10:13-16 ላይ የሰፈረው ዘገባ ስለ ኢየሱስ ማንነት ምን የሚነግረን ነገር አለ?
5 ይህ አጭር ዘገባ ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው እንደነበር ብዙ ነገር ይነግረናል። ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረብ ሰው እንደነበር አስተውል። በሰማይ ከፍተኛ ቦታ የነበረው ቢሆንም ፍጹም ያልሆኑ ሰዎችን የሚያሸማቅቅ ወይም የሚያንኳስስ አልነበረም። (ዮሐንስ 17:5) ልጆች እንኳን እንደ ልባቸው የሚቀርቡት መሆኑ አንድ ነገር የሚጠቁም አይደለም? ኢየሱስ ፈጽሞ ፈገግ ብሎ ወይም ስቆ የማያውቅ ፊቱ የማይፈታ ሰው ቢሆን ኖሮ ልጆች ሊቀርቡት እንደማይችሉ የታወቀ ነው! በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ኢየሱስ ሞቅ ያለ መንፈስ ያለውና ለሰዎች የሚያስብ ሰው መሆኑን በማወቅና ፊት ይነሳናል የሚል ስጋት ሳያድርባቸው በቀላሉ ይቀርቡት ነበር።
6. ሽማግሌዎች ራሳቸውን ይበልጥ በቀላሉ የሚቀረቡ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
6 በዚህ ታሪክ ላይ በማሰላሰል ራሳችንን ‘የኢየሱስ ዓይነት አስተሳሰብ አለኝ? በቀላሉ የምቀረብ ሰው ነኝ?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። በዚህ አስጨናቂ ዘመን የአምላክ በጎች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ” ሆነው የሚያገለግሉ በቀላሉ የሚቀረቡ እረኞች ይፈልጋሉ። (ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) እናንት ሽማግሌዎች ለወንድሞቻችሁ ጥልቅ የሆነ የአሳቢነት ስሜት ካዳበራችሁና ራሳችሁን ለእነርሱ ለመስጠት ፈቃደኞች ከሆናችሁ የምትጨነቁላቸው መሆናችሁን በቀላሉ ይረዳሉ። ይህን ስሜታችሁን ከፊታችሁ ላይ ሊያነቡት፣ ከድምፃችሁ ቃና ሊረዱትና ከምታደርጉት የደግነት ድርጊት ሊያስተውሉት ይችላሉ። እንዲህ ያለው ልባዊ ስሜትና አሳቢነት የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን ስለሚያደርግ ልጆችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ወደ እናንተ ለመቅረብ አያዳግታቸውም። አንዲት ክርስቲያን ሴት ለአንድ ሽማግሌ የልቧን ግልጥልጥ አድርጋ የተናገረችው ለምን እንደሆነ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ያነጋገረኝ በደግነትና በርኅራኄ ነበር። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ አንዲትም ቃል አልተነፍስለትም ነበር። ምንም እንዳልሸማቀቅ አድርጎኛል።”
ለሌሎች አሳቢ ነበር
7.(ሀ) ኢየሱስ ለሌሎች አሳቢ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነበር? (ለ) ኢየሱስ አንድን ዓይነ ሥውር ቀስ በቀስ የፈወሰው ለምን ሊሆን ይችላል?
7 ኢየሱስ አሳቢና ለሌሎች ስሜት የሚጠነቀቅ ነበር። መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች በተመለከተ ጊዜ የተሰማው ጥልቅ ሃዘን ከሥቃያቸው እንዲገላግላቸው ገፋፍቶታል። (ማቴዎስ 14:14) የሌሎች ሰዎችን የአቅም ገደብና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር። (ዮሐንስ 16:12) በአንድ ወቅት ሰዎች አንድ ዓይነ ሥውር ወደ ኢየሱስ አመጡና እንዲፈውሰው ለመኑት። ኢየሱስ ሰውየውን ፈወሰው። ሆኖም የፈወሰው ቀስ በቀስ ነበር። በመጀመሪያ ሰውየው ሰዎችን የተመለከተው በድንግዝግዝታ ነበር። “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ” አለ። ከዚያም ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ እንዲያይ አደረገው። ሰውዬውን ቀስ በቀስ የፈወሰው ለምን ነበር? ብርሃን ሳያይ ለረዥም ጊዜ የኖረን አንድ ሰው ድንገት ለፀሐይ ብርሃንና በአካባቢው ላለው ሁኔታ በማጋለጥ ሊደርስበት የሚችለውን ድንጋጤ ለማስቀረት ብሎ መሆን አለበት።—ማርቆስ 8:22-26
8, 9. (ሀ) ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ዲካፖሊስ እንደደረሱ ምን ነገር ተከሰተ? (ለ) ኢየሱስ መስማት የተሳነውን አንድ ሰው እንዴት እንደፈወሰው ግለጽ።
8 በተጨማሪም በ32 እዘአ ከተከበረው የማለፍ በዓል በኋላ የተከሰተ አንድ ሁኔታ ተመልከት። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ዲካፖሊስ ወደተባለ አውራጃ ገና መድረሳቸው ነበር። እዚያም ብዙ ሕዝብ አገኟቸውና የታመሙና የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች እንዲፈውሳቸው ወደ ኢየሱስ አመጧቸው። (ማቴዎስ 15:29, 30) የሚገርመው ኢየሱስ ለየት ያለ ትኩረት የሚያሻውን አንድ ሰው ከሕዝቡ መካከል ለይቶ ለብቻው ወሰደው። ይህን ታሪክ የመዘገበው የወንጌል ጸሐፊ ማርቆስ በዚህ ወቅት የሆነውን ሁኔታ ዘግቧል።—ማርቆስ 7:31-35
9 ሰውዬው መስማት የተሳነውና መናገር የሚቸግረው ሰው ነበር። ኢየሱስ ይህ ሰው የተሰማውን የመረበሽ ወይም የእፍረት ስሜት ተገንዝቦ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ አንድ ያልተለመደ ነገር አደረገ። ሰውዬውን ከሕዝቡ ለይቶ ገለል ወዳለ ስፍራ ወሰደው። ከዚያም ኢየሱስ የሚያደርገውን ነገር ለማስረዳት ለሰውዬው ምልክት አሳየው። “ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ።” (ማርቆስ 7:33) ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመለከተና ቃተተ። እነዚህ ድርጊቶች ለሰውዬው ‘አሁን ለአንተ የማደርግልህ ከአምላክ ባገኘሁት ኃይል ነው’ የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። በመጨረሻም ኢየሱስ “ተከፈት” አለ። (ማርቆስ 7:34) በዚያን ጊዜ ሰውዬው መሥማትና አጥርቶ መናገር ቻለ።
10, 11. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ላሉ ሰዎች ስሜት አሳቢ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በቤተሰብ ውስጥስ?
10 ኢየሱስ ለሰዎች ያሳየው እንዴት ያለ አሳቢነት ነው! ለስሜታቸው ይጠነቀቅ ነበር፤ እንዲህ ያለው የአዛኝነት ባሕርይ ደግሞ የሌሎችን ስሜት የሚጎዳ ነገር እንዳያደርግ ይገፋፋዋል። እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በዚህ ረገድ የኢየሱስ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበርና ማንጸባረቅ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል:- “በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፣ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፣ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8) ይህም የሌሎችን ስሜት ግምት ውስጥ እንዳስገባን በሚያሳይ መንገድ እንድንናገርና እንድናደርግ ይጠይቅብናል።
11 ለእኛ እንዲደረግልን የምንፈልገውን ነገር ለሌሎች በማድረግ ሰብአዊ ክብራቸውን ከጠበቅን ለሌሎች ስሜት አሳቢ መሆናችንን በጉባኤ ውስጥ ማሳየት እንችላለን። (ማቴዎስ 7:12) ይህም ስለምንናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን እንዴት ብለን እንደምንናገር ጠንቃቆች መሆንንም ይጨምራል። (ቆላስይስ 4:6) ‘ሳይታሰብ የሚሰነዘሩ ቃላት እንደ ሰይፍ ሊያቆስሉ እንደሚችሉ’ አስታውስ። (ምሳሌ 12:18) በቤተሰብ መካከልስ? እርስ በርሳቸው ከልብ የሚዋደዱ ባልና ሚስቶች አንዱ ለሌላው ስሜት ያስባሉ። (ኤፌሶን 5:33) ሻካራ ቃላትን ከመናገር፣ የነቀፋ ውርጅብኝ ከማውረድና የሚከነክን የሽሙጥ ቃል ከመናገር ይቆጠባሉ። እነዚህ ሁሉ በቀላሉ የማይሽር የስሜት ቁስል ሊያስከትሉ ይችላሉ። ልጆችም ቢሆኑ ስሜት አላቸው፤ አፍቃሪ ወላጆች ይህን ግምት ውስጥ ያስገባሉ። እርማት መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ እንደነዚህ ያሉት ወላጆች የልጆቻቸውን ክብር በሚጠብቅ መንገድ እርማት በመስጠት ልጆቻቸውን ከማበሳጨት ይቆጠባሉ።c (ቆላስይስ 3:21) በዚህ መንገድ ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት ስናሳይ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዳለን እናንጸባርቃለን።
በሌሎች ላይ እምነት እንደሚጥል አሳይቷል
12. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በተመለከተ የነበረው ሚዛናዊና ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት ምን ነበር?
12 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በተመለከተ ሚዛናዊና ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት ነበረው። ፍጹማን አለመሆናቸውን በሚገባ ያውቃል። ከዚህም በላይ የሰዎችን ልብ ማንበብ ይችላል። (ዮሐንስ 2:24, 25) ሆኖም የሚመለከተው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ከመሆናቸው አንጻር ሳይሆን ካላቸው ጥሩ ባሕርይ አንጻር ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ የሳባቸው እነዚህ ሰዎች ያላቸውን ችሎታ ተመልክቷል። (ዮሐንስ 6:44) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የነበረው ግንኙነትና እነርሱን የያዘበት መንገድ ለእነርሱ አዎንታዊ አመለካከት እንደነበረው የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል እምነት እንደሚጥልባቸው አሳይቷል።
13. ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ እምነት ይጥል እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ እምነት እንደሚጥል ያሳየው እንዴት ነበር? ምድርን ለቅቆ በሄደበት ጊዜ ለተቀቡት ደቀ መዛሙርቱ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። በምድር ዙሪያ ያለውን የመንግሥቱን ፍላጎቶች የማካሄዱን ኃላፊነት የተወው ለእነርሱ ነበር። (ማቴዎስ 25:14, 15፤ ሉቃስ 12:42-44) በአገልግሎቱ ወቅት ትናንሽ በሆኑ ጉዳዮችና ቀጥተኛ ባልሆኑ መንገዶች እንኳ እምነት እንደሚጥልባቸው አሳይቷል። ተሰብስበው የነበሩትን ሰዎች ለመመገብ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ምግቡ እንዲበዛ ባደረገ ጊዜ ምግቡን የማከፋፈሉን ሥራ የሰጠው ለደቀ መዛሙርቱ ነበር።—ማቴዎስ 14:15-21፤ 15:32-37
14. በማርቆስ 4:35-41 ላይ የሚገኘውን ታሪክ ጠቅለል ባለ ሁኔታ እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
14 በማርቆስ 4:35-41 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ታሪክ ተመልከት። በዚህ ወቅት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በአንዲት ጀልባ ተሳፍረው ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ አቀኑ። መቅዘፍ ከጀመሩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በጀልባዋ በኋለኛው በኩል ተኛና ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደው። ይሁን እንጂ ወዲያው “ብርቱ ዐውሎ ነፋስ” ተነሳ። እንዲህ ያለው አውሎ ነፋስ ለገሊላ ባሕር እንግዳ አይደለም። ረባዳማ ቦታ (ወደ 200 ሜትር ከባሕር ወለል በታች) በመሆኑ በዚህ አካባቢ የሚኖረው አየር አካባቢው ካለው አየር ይበልጥ ሞቃታማ ነው። ይህም አየሩ እንዲለዋወጥ ያደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ በስተ ደቡብ ከሚገኘው ከሄርሞን ተራራ ኃይለኛ ነፋስ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ይነፍሳል። ጸጥ ያለው አየር ከመቅጽበት ተለውጦ ከፍተኛ አውሎ ነፋስ ሊፈጥር ይችላል። ይህን ደግሞ አስብ:- ኢየሱስ ያደገው በገሊላ ስለሆነ በዚያ አካባቢ አውሎ ነፋስ ሲነሳ በተደጋጋሚ እንደተመለከተ የተረጋገጠ ነው። ሆኖም አንዳንዶቹ ዓሣ አጥማጅ የሆኑት ደቀ መዛሙርቱ ባላቸው ችሎታ ላይ እምነት በመጣል ያለ ስጋት ተኛ።—ማቴዎስ 4:18, 19
15. ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የነበረውን እምነት የመጣል መንፈስ እንዴት መኮረጅ እንችላለን?
15 እኛም ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ያሳየው ዓይነት እምነት የመጣል መንፈስ ልናሳይ እንችላለን? አንዳንዶች ኃላፊነቶችን ለሌሎች መስጠት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ሁሉንም ነገር ራሳቸው መሥራት ይፈልጋሉ። ‘አንድ ነገር በትክክል እንዲሠራ ከፈለግሁ ራሴ መሥራት አለብኝ!’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር ራሴ ካልሠራሁት የምንል ከሆነ ራሳችንን ልናደክምና ምናልባትም ለቤተሰቦቻችን ልንሰጣቸው የሚገባውን ጊዜ ሳያስፈልግ ልንነፍጋቸው እንችላለን። በተጨማሪም ተገቢ የሆኑ ሥራዎችንና ኃላፊነቶችን ለሌሎች የማንሰጥ ከሆነ ሊያገኙ የሚገባቸውን ተሞክሮና ሥልጠና እንዳያገኙ ልንነፍጋቸው እንችላለን። አንዳንድ ኃላፊነቶችን በማካፈል በሌሎች ላይ እምነት መጣልን መማር ጥበብ ይሆናል። ራሳችንን እንዲህ ብለን በሃቀኝነት መጠየቃችን ጥሩ ነው:- ‘በዚህ ረገድ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ አለኝ? አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል እንደሚሠሩ በማመን አንዳንድ ሥራዎችን ለሌሎች ለማካፈል ፈቃደኛ ነኝን?’
ደቀ መዛሙርቱን እንደሚተማመንባቸው አሳይቷል
16, 17. (ሀ) ኢየሱስ እንደሚተዉት ቢያውቅም በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ለሐዋርያቱ ምን ማረጋገጫ ሰጣቸው?
16 ኢየሱስ በሌላ አንድ አስፈላጊ በሆነ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ አዎንታዊ አመለካከት እንዳለው አሳይቷል። እንደሚተማመንባቸው እንዲያውቁ ያደርግ ነበር። ምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ለሐዋርያቱ ከተናገራቸው የማረጋገጫ ቃላት ይህን በግልጽ ለማየት ይቻላል። የሆነውን ነገር ተመልከት።
17 ኢየሱስ የቀረው ጊዜ አንድ ሙሉ ሌሊት ብቻ ነበር። እግራቸውን በማጠብ ለሐዋርያቱ ትሕትናን በሚመለከት አንድ አስፈላጊ የሆነ ትምህርት አስተማረ። ቀጥሎም ለሞቱ መታሰቢያ የሚሆን የእራት ዝግጅት አደረገ። ከዚያም ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሚሆን የጦፈ ክርክር ያዙ። ኢየሱስ በጣም ታጋሽ በመሆን እነርሱን በቁጣ ከመገሰጽ ይልቅ ምክንያት እያቀረበ አስረዳቸው። ከፊታቸው ምን ነገር እንደሚጠብቃቸው ነገራቸው:- “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና።” (ማቴዎስ 26:31፤ ዘካርያስ 13:7) እርዳታ በሚያስፈልገው ወቅት የቅርብ ወዳጆቹ እንደሚተዉት ያውቅ ነበር። እንዲህም ሆኖ አላወገዛቸውም። ከዚያ ፈጽሞ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የሚከተለውን አላቸው:- “ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው።” (ማቴዎስ 26:32) አዎን፣ እነርሱ ቢተዉትም እርሱ እንደማይተዋቸው አረጋገጠላቸው። ይህ ከባድ የመከራ ጊዜ ካለፈ በኋላ እንደገና ያገኛቸዋል።
18. ኢየሱስ በገሊላ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ከበድ ያለ ተልእኮ ሰጣቸው? ሐዋርያትስ የተሰጣቸውን ተልእኮ ወደ ፍጻሜ ያደረሱት እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ቃሉን አላጠፈም። ከዚያም ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ፣ ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ከሌሎች በርካታ ሰዎች ጋር ለነበሩት ለአሥራ አንዱ ሐዋርያት ተገለጠላቸው። (ማቴዎስ 28:16, 17፤ 1 ቆሮንቶስ 15:6) እዚያም ኢየሱስ አንድ ከበድ ያለ ተልእኮ ሰጣቸው:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ሐዋርያት የተሰጣቸውን ይህን ተልእኮ ወደ ፍጻሜ እንዳደረሱት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በግልጽ ያሳያል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው በታማኝነት አከናውነዋል።—ሥራ 2:41, 42፤ 4:33፤ 5:27-32
19. ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ያደረገው ነገር ስለ ክርስቶስ አስተሳሰብ ምን ነገር ያስተምረናል?
19 ይህ ግልጽ ዘገባ ስለ ክርስቶስ አስተሳሰብ ምን ነገር ያስተምረናል? ኢየሱስ የሐዋርያቱን ደካማ ጎን አብጠርጥሮ ያውቅ የነበረ ቢሆንም ‘እስከ መጨረሻ ወድዷቸዋል።’ (ዮሐንስ 13:1) ጉድለት ቢኖርባቸውም የሚተማመንባቸው መሆኑን እንዲያውቁ አድርጓል። ኢየሱስ በእነርሱ ላይ እምነት መጣሉ ስህተት እንዳልነበር ልብ በል። በእነርሱ ላይ እምነትና ትምክህት እንዳለው ማሳየቱ ያዘዛቸውን ሥራ ዳር ለማድረስ ከልባቸው ቆርጠው እንዲነሱ እንዳበረታቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
20, 21. የእምነት ባልደረቦቻችንን በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
20 በዚህ ረገድ የክርስቶስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? የእምነት ባልደረቦችህን በተመለከተ አፍራሽ አስተሳሰብ አትያዝ። ስለ ድክመታቸው የምታስብ ከሆነ በምትናገረው ቃላትና በምታደርገው ድርጊት መገለጡ የማይቀር ነው። (ሉቃስ 6:45) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ሁሉን ያምናል” በማለት ይነግረናል። (1 ቆሮንቶስ 13:7) ፍቅር አዎንታዊ እንጂ አሉታዊ አይደለም። ይገነባል እንጂ አያፈርስም። ሰዎች ጥሩ ምላሽ የሚሰጡት ለሚያሸማቅቃቸው ሳይሆን ፍቅር ለሚያሳያቸው ሰው ነው። እንደምንተማመንባቸው በመግለጽ ሌሎችን ልንገነባና ልናበረታታ እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:11) እንደ ክርስቶስ ለወንድሞቻችን አዎንታዊ አመለካከት ካለን በሚገነባቸውና ያላቸውን መልካም ነገር መጠቀም በሚቻልበት መንገድ እንይዛቸዋለን።
21 የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበርና ማንጸባረቅ ኢየሱስ ያደረጋቸውን አንዳንድ ነገሮች ከመኮረጅ አልፎ የሚሄድ ነገር ነው። ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው ኢየሱስ እንዳደረገው ማድረግ የምንፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ ነገሮችን እርሱ በተመለከተበት መንገድ መመልከትን መማር ይገባናል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደሚብራራው ወንጌሎች ኢየሱስ የነበረውን ባሕርይ፣ አስተሳሰብና ለተሰጠው ሥራ የነበረውን ስሜት ከሌላ አቅጣጫ እንድንመለከት ይረዱናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህን የሐሰት ሰነድ ያዘጋጀው ሰው የፀጉሩን፣ የፂሙንና የዓይኑን ቀለም ጨምሮ የኢየሱስን ጠቅላላ ቁመና በራሱ ግምት ገልጿል። ኤድገር ጄ ጎድስፒድ የተባሉ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ሲገልጹ ይህ የፈጠራ ሐሳብ “የኢየሱስን ቁመና በሚመለከት ለሠዓሊያን ፍንጭ ለመስጠት ታልሞ የተዘጋጀ ነው” ብለዋል።
b ልጆቹ የተለያየ ዕድሜ ያላቸው እንደሚሆኑ የታወቀ ነው። እዚህ ላይ ‘ልጆች’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል የ12 ዓመቷን የኢያኢሮስ ልጅ ለማመልከትም ይሠራል። (ማርቆስ 5:39, 42 NW ፤ 10:13 NW ) ይሁን እንጂ ሉቃስ ይህንኑ ታሪክ በመዘገበበት ቦታ ላይ ሕፃናትን በሚያመለክት ቃል ተጠቅሟል።—ሉቃስ 1:41 NW ፤ 2:12፤ 18:15
c “ክብራቸውን ትጠብቅላቸዋለህን?” የሚለውን በሚያዝያ 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት።
-
-
እንደ ኢየሱስ ለማድረግ ትገፋፋለህን?መጠበቂያ ግንብ—2000 | የካቲት 15
-
-
እንደ ኢየሱስ ለማድረግ ትገፋፋለህን?
“ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፣ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።”—ማርቆስ 6:34
1. ሰዎች የሚደነቁ ባሕርያትን ማንጸባረቅ መቻላቸው ብዙም ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው?
በታሪክ ዘመናት ሁሉ በርካታ ሰዎች ድንቅ ባሕርያትን አንጸባርቀዋል። ይህ የሆነው ለምን እንደሆነ ሊገባህ ይችላል። ይሖዋ አምላክ እንደ ፍቅር፣ ደግነት፣ ለጋስነትና ሌሎች ከፍተኛ ግምት የምንሰጣቸው ባሕርያት ያሉት ሲሆን እነዚህንም ባሕርያት አሳይቷል። ሰዎች የተፈጠሩት በአምላክ አምሳል ነው። ስለዚህ ብዙ ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ፍቅርን፣ ደግነትን፣ ርኅራኄንና ሌሎች መለኮታዊ ባሕርያትን ለምን እንደሚያሳዩ በቀላሉ ሊገባን ይችላል። እንዲያውም ብዙዎች በሕሊናቸው በመመራት ብቻ እነዚህን ባሕርያት ያሳያሉ። (ዘፍጥረት 1:26፤ ሮሜ 2:14, 15) ሆኖም አንዳንዶች እነዚህን ባሕርያት ከሌሎች በተሻለ መንገድ እንደሚያንጸባርቁ ተገንዝበህ ሊሆን ይችላል።
2. ሰዎች የክርስቶስን አርዓያ እየኮረጁ እንዳሉ በማሰብ የሚያከናውኗቸው አንዳንድ በጎ ተግባራት ምንድን ናቸው?
2 የታመሙ ሰዎችን የሚጠይቁ ወይም የሚያስታምሙ፣ ለአካል ጉዳተኞች የበጎ አድራጎት ተግባር የሚያከናውኑ ወይም ድሆችን የሚረዱ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል። በተጨማሪም ውስጣዊ የርኅራኄ ስሜት ገፋፍቷቸው መላ ሕይወታቸውን ለሥጋ ደዌ በሽተኞች ወይም ለሙት ልጆች እንክብካቤ በሚደረግበት ቦታ ያሳለፉ በሐኪም ቤት ወይም በሌሎች የሕክምና ተቋማት በፈቃደኝነት የሚሠሩ ወይም መኖሪያ ቤት የሌላቸውን ወይም ስደተኞችን ለመርዳት ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎችንም አስብ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ለክርስቲያኖች ምሳሌ የተወውን ኢየሱስን እየኮረጁ እንዳሉ ይሰማቸው ይሆናል። ክርስቶስ የታመሙትን እንደፈወሰና የተራቡትን እንደመገበ በወንጌሎች ውስጥ እናነባለን። (ማርቆስ 1:34፤ 8:1-9፤ ሉቃስ 4:40) ኢየሱስ ያሳየው የፍቅር፣ የርኅራኄና የአዘኔታ ስሜት “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ነጸብራቅ ሲሆን እርሱም የሰማዩ አባቱን ምሳሌ በመኮረጅ ያገኛቸው ባሕርያት ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 2:16 NW
3. ኢየሱስ ስላከናወናቸው መልካም ሥራዎች ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ለመያዝ ምን ነገር መመርመር ይኖርብናል?
3 በኢየሱስ ፍቅርና ርኅራኄ ልባቸው የተነካ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች የክርስቶስን አስተሳሰብ ዋነኛ ገጽታ የዘነጉ መሆናቸውን አስተውለሃል? ማርቆስ ምዕራፍ 6ን በጥንቃቄ መመርመራችን ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጥልቅ ማስተዋል እንድናገኝ ይረዳናል። እዚህም ላይ ኢየሱስ እንዲፈውስላቸው ሕዝቡ የታመሙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ እንዳመጡ እናነባለን። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ከርሱ ጋር የነበሩት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በተራቡ ጊዜ በተአምር እንደመገባቸው በጥቅሱ ዙሪያ ካሉት ሐሳቦች መገንዘብ እንችላለን። (ማርቆስ 6:35-44, 54-56) የታመሙትን መፈወስና የተራቡትን መመገብ አስደናቂ የፍቅራዊ ርኅራኄ መግለጫ ቢሆንም ኢየሱስ ሌሎችን የረዳበት ዋነኛ መንገድ ይህ ነውን? ኢየሱስ ይሖዋን እንደመሰለ ሁሉ እኛም የኢየሱስን ፍጹም የሆነ የፍቅር፣ የደግነትና የርኅራኄ ባሕርይ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
የጎደላቸውን መንፈሳዊ ምግብ ለማሟላት መገፋፋት
4. በማርቆስ 6:30-34 ላይ የሚገኘው ዘገባ መቼት ምን ይመስል ነበር?
4 ኢየሱስ አብረውት ለነበሩት ሰዎች በአንደኛ ደረጃ ያዘነው ለጎደላቸው መንፈሳዊ ምግብ ነበር። እነዚህ ምግቦች ከአካላዊ ምግብ እንኳ ሳይቀር የበለጡ የግድ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። በማርቆስ 6:30-34 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት። ሁኔታው የተፈጸመው በገሊላ ባሕር ዳርቻ ሲሆን በ32 እዘአ የሚከበረው የማለፍ በዓል ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ነበር። ሐዋርያቱ ደስ ብሏቸው የነበረ ሲሆን ለዚህም በቂ ምክንያት ነበራቸው። ረጅም ጉዞ ካደረጉ በኋላ ወደ ኢየሱስ ገና መመለሳቸው ነበር። ያገኟቸውን ተሞክሮዎች ሁሉ ሊነግሩት ጓጉተው እንደነበር ጥርጥር የለውም። ሆኖም ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። የተሰበሰበው ሕዝብ በጣም ብዙ ስለነበረ ኢየሱስና ሐዋርያቱ መብላትም ሆነ ማረፍ አልቻሉም። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው።” (ማርቆስ 6:31) ቦታው ቅፍርናሆም ሳይሆን አይቀርም በአንድ ጀልባ ተሳፈሩና የገሊላን ባሕር አቋርጠው ጸጥ ወዳለ ቦታ መጓዝ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ሕዝቡ የባሕሩን ዳርቻ ተከትለው ሮጠው ከጀልባው በፊት ቀድመው ደረሱ። ኢየሱስ ምን ተሰማው? ማረፍ ባለመቻሉ ተበሳጭቶ ይሆን? በፍጹም!
5. ኢየሱስ ወደ እሱ ስለ ተሰበሰበው ሕዝብ ምን ተሰማው? ከዚህስ የተነሳ ምን አደረገ?
5 ኢየሱስ የታመሙትን ጨምሮ በጉጉት ይጠባበቁት የነበሩትን በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በተመለከተ ጊዜ ልቡ በጣም ተነካ። (ማቴዎስ 14:14፤ ማርቆስ 6:44) ከልቡ እንዲያዝን ያደረገው ነገር ምን እንደሆነና ምን እርምጃ እንደወሰደ ማርቆስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፣ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።” (ማርቆስ 6:34) ኢየሱስ ያየው እንዲሁ ዝም ብሎ የተከማቸ ሕዝብ አልነበረም። መንፈሳዊ ነገር የሚያስፈልጋቸውን ግለሰቦች ተመልክቷል። ኢየሱስ ሕዝቡን የተመለከታቸው የለመለመ መስክ ወዳለበት ቦታ የሚያሰማራቸው ወይም ከአደጋ የሚጠብቃቸው እረኛ አጥተው እንደባዘኑ በጎች ነበር። በጎቹን በእንክብካቤ መጠበቅ ይገባቸው የነበሩት ጨካኞቹ የሃይማኖት መሪዎች ተራውን ሕዝብ እንደሚንቁና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን ችላ እንዳሉ ኢየሱስ ተገንዝቧል። (ሕዝቅኤል 34:2-4፤ ዮሐንስ 7:47-49) ኢየሱስ አቅሙ የፈቀደለትን ያህል ጥሩ ነገር በማድረግ ሕዝቡን በተለየ መንገድ ለመያዝ አስቧል። ስለ አምላክ መንግሥት ያስተምራቸው ጀመር።
6, 7. (ሀ) በወንጌሎች ዘገባ መሠረት ኢየሱስ ቅድሚያ ሰጥቶ ለሕዝቡ ምን ነገር አደረገ? (ለ) ኢየሱስ እንዲሰብክና እንዲያስተምር ያነሳሳው ውስጣዊ ግፊት ምንድን ነው?
6 በሌላ ተመሳሳይ ዘገባ ውስጥ ያለውን የታሪኩን ቅደም ተከተል እንዲሁም ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ነገር ምን መሆኑን ልብ በል። ይህን ታሪክ የጻፈው ሐኪምና የሌሎች አካላዊ ጤንነት ያሳስበው የነበረው ሉቃስ ነው። “ሕዝቡም . . . [ኢየሱስን] ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፣ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው።” (ሉቃስ 9:11፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ ቆላስይስ 4:14) ተዓምር ስለመፈጸሙ የሚናገሩት ዘገባዎች በሙሉ ይህን የመሰለ አቀማመጥ አላቸው ማለት ባይሆንም ሉቃስ በመንፈስ አነሳሽነት ባሰፈረው በዚህኛው ዘገባ ላይ ቅድሚያ የተሰጠው ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ ሕዝቡን ማስተማሩን ነው።
7 ይህም ማርቆስ 6:34 ላይ ተመዝግቦ በምናገኘው ታሪክ ላይ ጠበቅ ተደርጎ ከተገለጸው ታሪክ ጋር በትክክል የሚስማማ ነው። እዚያ ላይ ኢየሱስን ከልብ እንዲያዝን ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን በማስተዋል ሕዝቡን አስተምሯል። ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል” ብሎ ተናግሯል። (ሉቃስ 4:43) ሆኖም ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት ያወጀው የስብከቱን ሥራ እንደ ግዴታ አድርጎ በመቁጠር እንዲያው በዘልማድ ነው ብለን አስበን ከሆነ ተሳስተናል። ምሥራቹን ለሕዝቡ እንዲያካፍል የገፋፋው ቁልፍ ነገር ለሕዝቡ የነበረው ፍቅራዊ ርኅራኄው ነው። ኢየሱስ ለታመሙ፣ በአጋንንት ለተያዙ፣ ለድሆች ወይም ለተራቡ ሰዎች ሳይቀር ሊያደርግ የሚችለው ከሁሉ የላቀ ጥሩ ነገር ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን እውነት እንዲያውቁ፣ እንዲቀበሉና እንዲወዱ መርዳት ነበር። የይሖዋ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠውና ለሰው ልጆች ዘላቂ የሆኑ በረከቶች የሚመጡት በዚህ መንግሥት አማካኝነት በመሆኑ ስለዚህ መንግሥት የሚናገረው እውነት በጣም አስፈላጊ ነው።
8. ኢየሱስ ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ የነበረው ስሜት ምን ነበር?
8 ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ምክንያት መንግሥቱን በቅንዓት መስበክ ነው። ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ሊያጠናቅቅ በተቃረበበት ወቅት ለጲላጦስ እንዲህ አለው:- “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው።” (ዮሐንስ 18:37) ኢየሱስ ከአንጀት የመራራት ስሜት የነበረው ማለትም ለሰዎች የሚያስብ፣ በቀላሉ የሚቀረብ፣ በሌሎች ላይ እምነት የሚጥልና ከሁሉም በላይ ደግሞ አፍቃሪ እንደነበር ቀደም ባሉት ሁለት ርዕሶች ተመልክተናል። የክርስቶስን አስተሳሰብ በትክክል ለመረዳት ከፈለግን እነዚህን የባሕርያቱን ገጽታዎች በሚገባ ማወቅም ይኖርብናል። የክርስቶስ አስተሳሰብ ኢየሱስ በሰበከበትና ባስተማረበት ወቅት ለምን ነገር ቅድሚያ እንደሰጠ ማወቅንም የሚያካትት ነው።
ሌሎችም እንዲመሰክሩ አበረታቷል
9.የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ እነማንም ጭምር ማስቀደም ነበረባቸው?
9 የፍቅርና የርኅራኄ ስሜት መግለጫ ለሆኑት ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ኢየሱስ ብቻ አይደለም። ተከታዮቹ የእርሱን ዓይነት ውስጣዊ ግፊት እንዲኖራቸው፣ እርሱ ያስቀደማቸውን ነገሮች እንዲያስቀድሙና ተግባሩን እንዲኮርጁ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት የመረጠው ምን እንዲያደርጉ ነበር? ማርቆስ 3:14, 15 እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፣ ለማስተማርም [“ለመስበክ፣” NW ] እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ ‘ሐዋርያት’ ብሎ ሰየማቸው። አጋንንትን እንዲያወጡም ሥልጣን ሰጣቸው።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን) ሐዋርያቱ ለየትኛው ሥራ ቅድሚያ መስጠት እንደነበረባቸው አስተዋልክ?
10, 11. (ሀ) ኢየሱስ ሐዋርያቱን በላከ ጊዜ ምን እንዲያደርጉ ነገራቸው? (ለ) ሐዋርያቱ የተላኩበት ዋነኛ ዓላማ ምን ነበር?
10 ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ለአሥራ ሁለቱ የመፈወስና አጋንንትን የማውጣት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 10:1፤ ሉቃስ 9:1) ከዚያም “የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች” እንዲሄዱ ላካቸው። ምን እንዲያደርጉ? ኢየሱስ የሚከተለውን መመሪያ ሰጣቸው:- “ሄዳችሁም:- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ። ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ።” (ማቴዎስ 10:5-8፤ ሉቃስ 9:2) በእርግጥ ያደረጉት ምን ነበር? “ወጥተውም [1] ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፣ [2] ብዙ አጋንንትንም አወጡ፣ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።”—ማርቆስ 6:12, 13
11 ማስተማር በሁሉም ጥቅሶች ላይ በአንደኛ ደረጃ አለመጠቀሱ እሙን ነው። ታዲያ ቅድሚያ የተሰጠውን ወይም ሥራው የተከናወነበትን ውስጣዊ ግፊት ለማስረዳት ከላይ የተገለጸውን ቅደም ተከተል እንደ ማስረጃ አድርጎ መጥቀስ አጉል መመራመር አይሆንምን? (ሉቃስ 10:1-8) እንደዚያ ብለህ ታስብ ይሆናል። ነገር ግን ማስተማር ከፈውስ ቀድሞ የተጠቀሰባቸው ቦታዎች ተደጋጋሚ መሆናቸው ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ነው። በዚህ ረገድ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ተመልከት። ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ከመላኩ በፊት በሕዝቡ ሁኔታ ልቡ በጣም ተነክቶ ነበር። እንዲህ እናነባለን:- “ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፣ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፣ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን:- መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።”—ማቴዎስ 9:35-38
12. ኢየሱስና ሐዋርያቱ የፈጸሙት ተአምር ምን ተጨማሪ ዓላማ አከናውኗል?
12 ሐዋርያቱ ከኢየሱስ ጋር ስለነበሩ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የኢየሱስን አስተሳሰብ ቀስመው ሊሆን ይችላል። ለሰዎች እውነተኛ ፍቅርና ርኅራኄ እንዳላቸው የሚያሳዩበት አንደኛው መንገድ ስለ መንግሥቱ መስበክንና ማስተማርን የሚጨምር መሆኑን መገንዘብ ይችላሉ። ይህም ከሚያከናውኗቸው መልካም ሥራዎች መካከል ዋነኛው ነው። ከዚህ ጋር በመስማማት በሽተኞችን መፈወስን የመሰሉት ለሰብዓዊ ደህንነት የሚጠቅሙ መልካም ተግባራት ተጨማሪ ዓላማዎችን አከናውነዋል። አንዳንድ ሰዎች የመጡት በተመለከቱት ፈውስና በተአምር በቀረበው ምግብ ተስበው እንደሆነ ልትገምት ትችላለህ። (ማቴዎስ 4:24, 25፤ 8:16፤ 9:32, 33፤ 14:35, 36፤ ዮሐንስ 6:26) ሆኖም እነዚያ ሥራዎች አካላዊ ጥቅም ከማስገኘትም ባሻገር ሁኔታውን ያስተዋሉ ሰዎች ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነና ሙሴ አስቀድሞ የተናገረለት “ነቢይ” መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።—ዮሐንስ 6:14፤ ዘዳግም 18:15
13. በዘዳግም 18:18 ላይ የሚገኘው ትንቢት “ነቢዩ” ምን ሚና እንደሚጫወት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል?
13 ኢየሱስ “ነቢይ” መሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው? በትንቢት የተነገረው የዚህ “ነቢይ” ቁልፍ ሚና ምንድን ነው? ተአምራዊ ፈውስ በመፈጸም ወይም ለተራቡ ሰዎች በማዘንና በተአምር በመመገብ ዝነኛ መሆን ነውን? ዘዳግም 18:18 እንዲህ በማለት ተንብዮአል:- “ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ አንተ [ሙሴ] ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፣ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል።” ሐዋርያቱ ከአንጀት የመራራት ስሜት ማዳበርንና ማንጸባረቅን ቢማሩም የክርስቶስ አስተሳሰብ የሚንጸባረቀው በስብከትና በማስተማር ሥራቸው ጭምር መሆኑን ሊገነዘቡ ይችላሉ። ለሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ከሁሉ የላቀ ነገር ደግሞ ይህ ነው። በዚህ መንገድ ሕመምተኞችም ሆኑ ድሆች በሕይወት በቆዩባቸው አጭር ዕድሜ ወይም ጥቂት ምግብ በመመገብ ላገኙት ጊዜያዊ ጥቅም ሳይሆን ከዚያ የሚበልጥ ዘላቂ ጥቅሞችን ሊያገኙ ይችላሉ።—ዮሐንስ 6:26-30
ዛሬም የክርስቶስን አስተሳሰብ አዳብሩ
14. የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበርና የስብከቱ ሥራ የተያያዙ ነገሮች የሆኑት እንዴት ነው?
14 የክርስቶስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ ለነበሩት ለኢየሱስና ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛ ግን የክርስቶስ ልብ [“አስተሳሰብ፣” NW ] አለን” ብሎ ለጻፈላቸው ለመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ብቻ የተተወ ነገር አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 2:16) ምሥራቹን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግዴታ እንዳለብን ያለ አንዳች ማቅማማት እንቀበላለን። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ሆኖም ይህን ሥራ ለማከናወን ያነሳሳኝ ውስጣዊ ግፊት ምንድን ነው? እያልን ራሳችንን መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ግዴታ እንደሆነ ተሰምቶን ብቻ የምናከናውነው ነገር መሆን የለበትም። በአገልግሎቱ እንድንካፈል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። ደግሞም በትክክል ኢየሱስን መምሰል በርኅራኄ ተነሳስቶ መስበክንና ማስተማርን ይጨምራል።—ማቴዎስ 22:37-39
15. ርኅራኄ የሕዝባዊ አገልግሎታችን ክፍል መሆኑ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
15 እምነታችንን ለማይጋሩን በተለይ ደግሞ ግዴለሽ ለሆኑ፣ ፍላጎት ለሌላቸው ወይም ለተቃዋሚዎች የርኅራኄ ስሜት ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል እንዳይደለ የታወቀ ነው። ሆኖም ለሰዎች ያለን ፍቅርና የርኅራኄ ስሜት ከውስጣችን ከጠፋ በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንድንካፈል የሚያነሳሳንን ውስጣዊ ግፊት ልናጣ እንችላለን። ታዲያ የርኅራኄን ስሜት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው ዓይነት አመለካከት እኛም እንዲኖረን ጥረት ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም” ተመልክቷቸዋል። (ማቴዎስ 9:36) በዛሬው ጊዜ ያሉ የብዙ ሰዎች ሁኔታ እንደዚህ አይደለምን? በሐሰት ሃይማኖታዊ እረኞች ተጥለውና በመንፈሳዊ ታውረው ይገኛሉ። በዚህም የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛ መመሪያም ሆነ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በምድር ላይ የሚያመጣውን ገነታዊ ሁኔታ አያውቁም። የመንግሥቱን ተስፋ ስለማያውቁ በዕለታዊ ሕይወታቸው የሚገጥሟቸውን እንደ ድህነት፣ የቤተሰብ ብጥብጥ፣ ሕመምና ሞት ያሉትን ችግሮች የሚጋፈጡት ብቻቸውን ነው። እኛ ግን እነዚህ ሰዎች የግድ ሊያውቁት የሚገባ በሰማይ ተቋቁሞ ስለሚገኘው ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው ሕይወት አድን ምሥራች አለን!
16. ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች ለማካፈል መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?
16 በአካባቢህ የሚገኙ ሰዎች ስለሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ነገር ስታሰላስል ስለ አምላክ ፍቅራዊ ዓላማ ለእነርሱ ለመንገር የቻልከውን ሁሉ እንድታደርግ ልብህ አያነሳሳህም? አዎን፣ ሥራችን የርኅራኄ ስሜት ማንጸባረቅን የሚጠይቅ ነው። ኢየሱስ ለሰዎች ያሳየው ዓይነት የሐዘኔታ ስሜት ካለን በፊታችን ላይ ይነበባል፣ በድምፃችን ቃናና በምናስተምርበት ሁኔታ ግልጽ ሆኖ ይታያል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች መልእክታችን ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ’ ላላቸው ሰዎች ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን ያደርጋሉ።—ሥራ 13:48 NW
17. (ሀ) ለሌሎች ሰዎች ያለንን ፍቅርና ርኅራኄ ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? (ለ) ጉዳዩ መልካም ሥራዎችን ከመሥራትና በሕዝብ በሚደረገው አገልግሎት ከመካፈል አንዱን የመምረጥ ጉዳይ ያልሆነው ለምንድን ነው?
17 እርግጥ ነው፣ ፍቅራችንና ርኅራኄያችን በመላ አኗኗራችን መንጸባረቅ ይኖርበታል። ይህም አቅማችን የፈቀደውን ያህል የተቸገሩትን፣ የታመሙትንና ድሆችን በመርዳት ደግነት ማሳየትን ይጨምራል። የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎችን በቃላችንም ሆነ በድርጊታችን ማጽናናትንም ያካትታል። (ሉቃስ 7:11-15፤ ዮሐንስ 11:33-35) ሆኖም እነዚህ የፍቅር፣ የደግነትና የርኅራኄ መግለጫዎች እንደ አንዳንድ በጎ አድራጊዎች የመልካም ሥራችን ዋነኛ ግቦች መሆን የለባቸውም። ሆኖም ይበልጥ ዘላቂ ጠቀሜታ ያለው በእነዚሁ መለኮታዊ ባሕርያት ተገፋፍተን በክርስቲያናዊ የስብከትና የማስተማር ሥራ የምናደርገው እንቅስቃሴ ነው። ኢየሱስ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን በማስመልከት “ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፣ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ” በማለት የተናገረውን አስታውስ። (ማቴዎስ 23:23) ኢየሱስ አካላዊ ጉዳት የነበረባቸውን ሰዎች ፈውሷል እንዲሁም ሕይወት አድን የሆነውን መንፈሳዊ ጉዳይ አስተምሯል። ኢየሱስ ሁለቱንም አድርጓል። ሆኖም ቅድሚያ የሰጠው ለማስተማሩ ሥራ ነበር። ምክንያቱም ዘላቂ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችለው በማስተማሩ ሥራ አማካኝነት የሚያከናውነው መልካም ተግባር ነው።—ዮሐንስ 20:16
18. የክርስቶስን አስተሳሰብ መመርመራችን ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?
18 ይሖዋ የክርስቶስን አስተሳሰብ ማወቅ የምንችልበትን አጋጣሚ ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በወንጌሎች አማካኝነት እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የነበረውን አስተሳሰብ፣ ስሜት፣ ባሕርይ እንዲሁም ያከናወናቸውን ተግባራትና ቅድሚያ ይሰጣቸው የነበሩትን ነገሮች በተሻለ መንገድ ለማወቅ እንችላለን። ስለ ኢየሱስ የሚገልጹትን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ዘገባዎች ማንበብ፣ በእነርሱ ላይ ማሰላሰልና ተግባራዊ ማድረግ የእኛ ፈንታ ነው። ኢየሱስን መምሰል የምንፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ ፍጹማን ባለመሆናችን አቅማችን የፈቀደልንን ያህል እንደ እርሱ ማሰብን፣ የእሱ ዓይነት ስሜት ማንጸባረቅንና እርሱ ነገሮችን ይመዝን በነበረበት መንገድ መመዘንን መማር እንዳለብን አስታውስ። ስለዚህ የክርስቶስን አስተሳሰብ ለማዳበርና ለማንጸባረቅ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ከዚህ ጋር የሚተካከል አንድም የሕይወት መንገድ የለም። ለሰዎች ጥሩ አያያዝ ለማሳየትና እኛም ሆንን ሌሎች ኢየሱስ ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀውን ሩኅሩኅ አምላክ ይሖዋን ለመቅረብ የሚያስችል ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም።—2 ቆሮንቶስ 1:3፤ ዕብራውያን 1:3
-
-
እንደ ኢየሱስ ለማድረግ ትገፋፋለህን?መጠበቂያ ግንብ—2000 | የካቲት 15
-
-
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]
-