-
“በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ”መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017 | ታኅሣሥ
-
-
15. ኢየሱስ “በኩራት” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?
15 መንፈሳዊ አካል ይዞ መጀመሪያ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ነው፤ የእሱ ትንሣኤ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ አያጠራጥርም። (ሥራ 26:23) ይሁን እንጂ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ የሄደው ኢየሱስ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ፣ ለታማኝ ሐዋርያቱ በሰማይ ከእሱ ጋር እንደሚገዙ ቃል ገብቶላቸዋል። (ሉቃስ 22:28-30) ይህን ሽልማት የሚያገኙት ግን ከሞቱ በኋላ ነው። ከዚያም ልክ እንደ ክርስቶስ መንፈሳዊ አካል ይዘው ከሞት ይነሳሉ። ጳውሎስ “ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል” ሲል ጽፏል። በተጨማሪም ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሌሎችም እንዳሉ ሲጠቁም እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፦ ክርስቶስ በኩራት ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት ሕያዋን ይሆናሉ።”—1 ቆሮ. 15:20, 23
16. ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ከሞት የሚነሱበትን ጊዜ ለማወቅ የሚረዳን ምንድን ነው?
16 ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ፣ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ከሞት ስለሚነሱበት ጊዜ የሚጠቁመን ነገር አለ። ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው ክርስቶስ “በሚገኝበት ጊዜ” ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ባደረጉት ምርምር፣ ኢየሱስ ‘የሚገኝበት ጊዜ’ የጀመረው በ1914 እንደሆነ ተገንዝበዋል። አሁንም የምንኖረው በዚህ ጊዜ ውስጥ ሲሆን የዚህ ክፉ ሥርዓት ማብቂያ ደግሞ በጣም ተቃርቧል።
17, 18. በክርስቶስ መገኘት ወቅት አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ይሆናሉ?
17 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማያዊው ትንሣኤ የሚከተለውን ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል፦ “በሞት አንቀላፍተው ስላሉት ሳታውቁ እንድትቀሩ አንፈልግም። ኢየሱስ እንደሞተና ከሞት እንደተነሳ የምናምን ከሆነ . . . በሞት ያንቀላፉትንም አምላክ ሕይወት ሰጥቶ ከእሱ ጋር እንዲሆኑ ያደርጋል። . . . ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ በሕይወት የምንኖር በሞት አንቀላፍተው ያሉትን በምንም መንገድ አንቀድምም፤ ምክንያቱም ጌታ ራሱ በትእዛዝ ድምፅ . . . ከሰማይ ይወርዳል፤ ከክርስቶስ ጋር አንድነት ኖሯቸው የሞቱትም ቀድመው ይነሳሉ። ከዚያም በሕይወት ቆይተን የምንተርፈው እኛ በአየር ላይ ከጌታ ጋር ለመገናኘት ከእነሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መንገድ ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።”—1 ተሰ. 4:13-17
18 ሰማያዊው ትንሣኤ የሚከናወነው፣ ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ ‘የሚገኝበት ጊዜ’ ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። በታላቁ መከራ ወቅት በምድር ላይ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘በደመና ይነጠቃሉ።’ ‘በደመና የሚነጠቁት’ ቅቡዓን፣ ሞተው ረጅም ጊዜ ስለማይቆዩ ‘በሞት አያንቀላፉም’ ሊባል ይችላል። እነዚህ ቅቡዓን “የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ወቅት ድንገት፣ በቅጽበተ ዓይን [ይለወጣሉ]።”—1 ቆሮ. 15:51, 52፤ ማቴ. 24:31
-
-
“በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ”መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017 | ታኅሣሥ
-
-
20. የወደፊቱ ትንሣኤ በተደራጀ መልኩ እንደሚከናወን መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
20 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰማያዊው ትንሣኤ ስለሚከናወንበት መንገድ ሲናገር “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል” ይላል። (1 ቆሮ. 15:23) በምድር ላይ ለመኖር ከሞት የሚነሱት ሰዎች ትንሣኤም በተደራጀ መልኩ እንደሚከናወን መተማመን እንችላለን። ይህ በጉጉት የምንጠብቀው ክንውን ነው። የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ከጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ በዘመናችን የሞቱ ሰዎች በቅድሚያ ከሞት ተነስተው ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ይገናኙ ይሆን? አመራር የመስጠት ችሎታ ያላቸው በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ አገልጋዮች፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የአምላክን ሕዝቦች በማደራጀቱ ሥራ እንዲካፈሉ ሲባል በቅድሚያ ከሞት ይነሱ ይሆን? ፈጽሞ ይሖዋን አገልግለው ስለማያውቁ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች የሚነሱት መቼ እና የት ነው? ከዚህ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች ይፈጠሩብን ይሆናል። ይሁን እንጂ ስለ እነዚህ ነገሮች አሁን መጨነቅ ያስፈልገናል? እዚያው ደርሰን የሚሆነውን እስክናይ መጠበቁ የተሻለ አይሆንም? ይሖዋ እነዚህን ነገሮች እንዴት እንደሚያከናውን ስንመለከት እንደምንደነቅ ጥርጥር የለውም።
-