የወጣቶች ጥያቄ . .
ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር የሌለብህ ለምንድን ነው?
“ሁለት ዓይነት ኑሮ እኖር ነበር፤ ከክርስቲያን ጓደኞቼ ጋር ስሆን አንድ ዓይነት፣ አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች ጋር ስሆን ደግሞ ሌላ ዓይነት ኑሮ እኖር ነበር”
ከላይ የተጠቀሰችው ወጣት ያለችበት ሁኔታ እምብዛም ያልተለመደ ነገር አይደለም። ነገር ግን “ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር” ማለት ምን ማለት ነው? ቼንጂንግ ቦዲስ፣ ቼንጂንግ ላይቭስ የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ሩት ቤል ለድርጊቱ የሰጡት ፍቺ “ለወላጆቻችሁ የማትናገሩትን ማንኛውም ነገር ማድረግ ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር ነው” የሚል ነው።
እኚሁ ደራሲ ለብዙ ወጣቶች ቃለ ምልልስ አድርገው ቀጥሎ ያለውን ዘግበዋል:- “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ልጆች ለወላጆቻቸው ሳይናገሩ ተደብቀው የሚያደርጓቸው አንዳንድ ነገሮች መኖራቸውን ተናግረዋል። በአብዛኛው በምሥጢር የሚይዟቸው ድርጊቶች የፆታ ግንኙነት ማድረግን፣ አደንዛዠ ዕፆችን መውሰድንና የአልኮል መጠጦችን መጠጣት ሲሆኑ ወጣቶቹ በጊዜ አለመግባትን፣ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ወዳጅነት መፍጠርን፣ በትምህርት ቤት ከክፍል ጠፍቶ መውጣትን፣ መጣላትንና ወላጆቻቸው ከማይወዷቸው ልጆች ጋር መሆንን ጨምረው ጠቅሰዋል።”
ክርስቲያን ወላጆች ያሳደጓቸው ወጣቶች እንኳ ምን ዓይነት ልጆች መሆናቸውን ከወላጆቻቸውና ከሌሎች መደበቃቸው ያሳዝናል።a (ከመዝሙር 26:4 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ወጣቶች ከወላጆቻቸውና ከእምነት ጓደኞቻቸው ጋር ሲሆኑ ትክክለኛ ሥነ ምግባርና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው መስለው ይታያሉ። በቅርብ ከሚከታተላቸው ሰው ሲርቁ ግን ፈጽሞ የተለየ ጠባይ ያሳያሉ።
አንድን ወጣት ሁለት ዓይነት ኑሮ እንዲኖር የሚገፋፋው ምክንያት ምን ይሆን?
የራስን ኑሮ በራስ ለመምራት ያለው ምኞት የሚያመጣው ወጥመድ
ውሎ አድሮ “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:24) ስለዚህ ለማደግ፣ ራስህ ስለ ራስህ ማሰብና የራስህን ውሳኔ ለማድረግ መፈለግህ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ነገር አይደለም። ችግሩ ግን ሙሉ ሰው ወደ መሆን ገና ያልደረስህ ልትሆን መቻልህ ነው። ደግሞም የሕይወት ተሞክሮ ስለሚያንስህ አምላካዊ የሆኑ ወላጆች ድጋፍ የግድ ያስፈልግሃል።—ምሳሌ 1:8
ብዙ ወጣቶች ይህን ሐቅ መቀበል ያስቸግራቸዋል። ሃው ቱ ሰርቫይቭ ዩር ቻይልድስ ሪቤሊየስ ቲንስ የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ባቀረበው ዘገባ መሠረት ብዙ ወጣቶች “ያዳበሩትን አዲስ ጉልበትና ጡንቻ ለማሳየትና ራሳቸውን የቻሉ መሆናቸው በይፋ ለማሳወቅ” ይፈልጋሉ። አንዳንድ ወጣቶች ጥበብ የጎደለው ወይም የተሳሳተ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ወላጆቻቸው ሲከለክሏቸው ያምፃሉ። ወጣቶቹ በሚፈጽሙት እንዲህ ባለው በደል ትንሽ እንኳን ጸጸት አይሰማቸውም። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለች አንዲት ልጃገረድ “[ወላጆቼ] እንደማደርግ የማያውቁትን ነገር ሳደርግ ትልቅ እንደሆንሁ ስለሚሰማኝ ተገቢ ነገር ያደረግሁ ይመስለኛል። ከወላጆቼ የተለየ ሕይወት አለኝ። የማደርገውን ጨርሶ የሚያውቁ አይመስለኝም። . . . እያደረግሁት ካለው ግማሹን እንኳ ታደርጋለች ብለው አያምኑም” ብላለች።
‘ወላጆቼ በጣም ጥብቅ ናቸው’
አንዳንድ ወጣቶች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ጥሩ ክርስቲያናዊ ሥልጠና ያገኙ ቢሆንም እንኳ በድብቅ መጥፎ ተግባር የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ ይህን ጥያቄ ለአንድ የወጣቶች ቡድን ባቀረበ ጊዜ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ልጃገረድ “ወላጆቻቸው ያናድዷቸዋል። ወላጆቻቸው በእነርሱ ላይ የሚጥሉትን ገደብ ለመበቀል ይፈልጋሉ” በማለት መልስ ሰጥታ ነበር። የክርስትና ኑሮ ብዙ ነፃነት የሌለበት የሕይወት መንገድ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ “ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና” ብሏል። (ማቴዎስ 7:14) የአምላክን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ማግኘት ከፈለግህ አንዳንድ ወጣቶች ያስደስታሉ ብለው ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል ማድረግ የሌለብህ አንዳንድ ነገሮች ይኖራሉ። ለምሳሌ ልቅ ፓርቲዎች፣ ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጦችን መጠጣት፣ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ማድረግ፣ መዳራት፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ የተወገዙ ድርጊቶች ናቸው።—ገላትያ 5:19–21
በተጨማሪም አንዳንድ ወላጆች ከመጠን በላይ ጥብቅ መስለው የመታየታቸው ጉዳይ አለ። ኪም የተባለች ወጣት ልጃገረድ “ምንም ዓይነት ፊልም አናይም። ሙዚቃ የምሰማበትን ጊዜ በጣም ቀንሻለሁ፤ ሙዚቃ ሳዳምጥም ጥሩዎቹን ብቻ እየመረጥኩ ለማዳመጥ እሞክራለሁ። ሆኖም አባቴ ምንም ዓይነት ሙዚቃ እንዳንሰማ ይከለክለናል። መስማት የምንችለው ክላሲካልና የጃዝ ሙዚቃዎችን ብቻ ነው” በማለት ምሬቷን ገልጻለች። አንዳንድ ወጣቶች የተጣለባቸው ገደብ ምክንያታዊ ካልመሰላቸው እኩዮቻቸው ባላቸው ነፃነት መቅናት ይጀምራሉ።
ሌሎችን የመምሰል ፍላጎት
ታሚ የተባለች ወጣት ሴት እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “በትምህርት ቤት ውስጥ የብልግና አነጋገር መናገር ጀመርኩ። እንዲህ በማድረጌ ይበልጥ የተቀሩትን ልጆች እንደመሰልኩ ተሰማኝ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሲጋራ ማጨስ ጀመርኩ። በተጨማሪም ሞቅ እስኪለኝ ድረስ የአልኮል መጠጥ እጠጣ ነበር። ከዚያም በምሥጢር የወንድ ጓደኞች መያዝ ጀመርኩ። ምክንያቱም ወላጆቼ ጥብቅ ስለሆኑ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ለመጫወት እንድቀጣጠር አይፈቅዱልኝም።”
በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኘው ፒት የተባለው ወጣትም ተመሳሳይ ተሞክሮ አለው። “ያደግሁት የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ነው። ነገር ግን ሌሎች እንዳያሾፉብኝ በጣም ፈራሁ። ስለዚህ ከሌሎች ልዩ ሆኜ ላለመታየት ስል ሌሎች ልጆች የሚያደርጉትን ማድረግ ጀመርኩ። ተወዳጅነትን ለማግኘት ጣርኩ። በሃይማኖታዊ በዓሎች ጊዜ ምንም ዓይነት ስጦታ መቀበል ስለማልፈልግበት ምክንያት የውሸት ሰበብ እፈጥር ነበር።”b ፒት በትንሽ ነገር ታማኝነቱን ማጉደል ስለጀመረ ከበድ ባሉ የምግባረ ብልሹነት ተግባሮች ለመካፈል ጊዜ አልወሰደበትም።
“ክፉ ባልንጀርነት” — የት?
እንዲህ ያሉት ተሞክሮዎች ክርስቲያኑ ሐዋሪያ ጳውሎስ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ሲል የተናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት ያጎላሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱትን የሕይወት መመሪያዎችና የሥነ ምግባር ደረጃዎች ከማያከብሩልህ ወጣቶች ጋር አብረህ ብትውል በቀላሉ ወደ እነርሱ የአኗኗር ዘይቤ ተስበህ ትገባለህ። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ከላይ ያለውን ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ከማያምኑ ጋር ባልንጀራ ስላለመሆን ለይቶ አልተናገረም። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቢሆኑም በክርስትና ትምህርት ከማይመላለሱ ሰዎች ጋር ጭምር ባልንጀርነት እንዳይፈጥሩ አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 15:12) ዛሬም በተመሳሳይ ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ቢሰበሰቡም ትክክለኛውን የክርስትና አኗኗር በታማኝነት የማይከተሉ አንዳንድ ወጣቶች ይኖሩ ይሆናል። እነዚህ ወጣቶች ስውር በሆነ መንገድ ሁለት ዓይነት ኑሮ እንድትኖር ግፊት ሊያሳድሩብህ ይችላሉ።
ወላጆቿ “በጣም አፍቃሪ” እንደሆኑ የምታምነውን የታሚን ሁኔታ እስቲ እንደገና እንመልከት። አባቷ “በጣም ቀናተኛና ሁልጊዜ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚያስብልን ሞቅ ባለ ስሜት የሚናገር ሰው” እንደሆነ ትናገራለች። አባቷ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። ታዲያ ልትሳሳት የቻለችው እንዴት ነው? “በጉባኤው ውስጥ ካሉት ጋር መጥፎ ጓደኝነት በመመሥረቴ ነው” ትላለች። “ሌሎች በተለያዩ ፓርቲዎች ላይ በመገኘታቸው ስላገኙት ደስታና ስለ ጠጡት የአልኮል መጠጥ ይነግሩኛል። ወይም ስለ ወንድ ጓደኞቻቸውና ከጉባኤ ስብሰባዎች በኋላ ስለሚሄዱባቸው የዳንስ ቤቶች ይነግሩኝ ነበር።”
ከክፉው ነገር መራቅ
ወጣቶች የሚፈጽሟቸውን እንዲህ ያሉ መጥፎ ድርጊቶች ‘የእድገት ክፍል ነው’ ወይም ‘ሁሉም ልጆች ከወላጆቻቸው ተደብቀው የሚሠሯቸው ብዙ ነገሮች አሉ’ በሚል ሰበብ አትለፋቸው። አምላክ በመክብብ 11:9, 10 ላይ ለወጣቶች የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ በል:- “አንተ ጎበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፣ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ፤ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ። ሕፃንነትና ጉብዝና ከንቱዎች ናቸውና ከልብህ ኀዘንን አርቅ፣ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ።”
ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር አስደሳች ሊመስል ይችላል። ውሎ አድሮ ግን ሞት የሚያመጣ ወጥመድ ነው። (ከመዝሙር 9:16 ጋር አወዳድር።) የእንቢተኝነት ድርጊቶች ይበልጥ ከባድ የሆኑ ስሕተቶችን ወደ መፈጸም ማምራታቸው የማይቀር ነው። ለምሳሌ ፒት የተባለው ወጣት በ17 ዓመቱ ቤቱን ትቶ በሄደበት ጊዜ በፆታ ብልግና ውስጥ ተዘፍቆ ነበር። ፒት በ18 ዓመቱ በመሣሪያ አስፈራርቶ ዘረፋ በመፈጸሙ ምክንያት ወደ ወኅኒ ወረደ።
ብዙውን ጊዜ ብዙ ወጣቶች በሚሠሩት የጥፋት ድርጊት ምክንያት ምንም ዓይነት ጉዳት የማይደርስባቸው መስሎ ይታያል። ቆይቶ ስሕተቱን እንዳመነው እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ እንደ አሳፍ ዓይነት አስተሳሰብ በቀላሉ ሊያድርብህ ይችላል። “በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና። ለሞታቸው መጣጣር የለውምና፤ ኃይላቸውም ጠንካራ ነውና። እንደ ሰው በድካም አልሆኑም።” ሆኖም አስተማማኝ ይመስል የነበረው የክፉዎች ሰላም ክፉ ቅዠት ሆኖ ተግኝቷል። አሳፍ “በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፣ ወደ ጥፋትም ጣልካቸው” በማለት ደምድሟል። (መዝሙር 73:3–5, 18) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ “ልብህ በኃጢያተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር” በማለት ያስጠነቀቀው በጥሩ ምክንያት ነው።—ምሳሌ 23:17
ለወላጆች አለመታዘዝ የአንድን ወጣት እድገት ያፋጥናል፣ ራሱንም እንዲችል ይረዳዋል ስለሚባለው አስተሳሰብስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆችህን መስማት እንዳለብህ ከሚሰጠው ምክር ጋር ይቃረናል። (ምሳሌ 23:22) በእርግጥም የሞኝነት ወይም የግድየለሽነት ባሕርይ ስሜታዊና መንፈሳዊ እድገትህን ከማደናቅፍ በቀር የሚጠቅምህ ነገር አይኖረውም። ከዚህ ይልቅ “ሙሉ ሰው” የምትሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ በማዋል “የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ” ስትደርስ ነው።—ኤፌሶን 4:13
እውነት ነው፣ አንዳንድ ወላጆች ከሚገባው በላይ ጥብቅ መስለው ይታዩ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ የሚያደርጉት ለአንተ ጥልቅ ፍቅር ስላላቸውና ጉዳት እንዳያገኝህ ስለሚመኙ አይደለምን? ስለዚህ ወላጆችህ በአንተ ላይ የጣሉትን ገደብ ትንሽ ላላ ማድረግ እንዳለባቸው ከተሰማህ በምሥጢር ዓመፅ ከማካሄድ ይልቅ ስለ ጉዳዩ ለምን አትነግራቸውም?c በወላጆች ላይ ማመፅ ወላጆችህንም ሆነ ራስህን ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ አምላክን ያሳዝናል።—ምሳሌ 10:1፤ 27:11
ከዚህ ቀደም ሁለት ዓይነት ኖሮ መኖር ጀምረህ ከሆነስ? ከዚህ ዓይነቱ አኗኗር የምትላቀቅበት መንገድ ይኖራልን? ወደፊት የሚወጡት ርዕሶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመጠበቂያ ግንብ 15–109 ላይ “ወጣቶች ሆይ፣ ሁለት ዓይነት ኑሮ ከመኖር ተጠበቁ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ በዓላትን አስመልክቶ ስላላቸው አቋም የተሰጠውን ማብራሪያ በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ትምህርት ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።
c ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብና የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የታተመውን የወጣቶች ጥያቄና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ምዕራፍ 3ን ተመልከት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምትኖረው ሁለት ዓይነት ኑሮ ነውን?