‘ድካማችሁ ከንቱ አይደለም’
1 እንዴት የሚያበረታታ ሐሳብ ነው! በይሖዋ አገልግሎት የምታከናውኑት ተግባር ከንቱ አይደለም። (1 ቆሮ. 15:58) ከዚህ በተቃራኒ ግን ሰዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ወይም የኢኮኖሚ ሁኔታቸውን ለማሻሻል ሲሉ ምን ያህል እንደሚደክሙ አስቡ። ምናልባትም ለዓመታት ከፍተኛ ትምህርት ይከታተሉ ወይም ብዙ ቁሳዊ ንብረት ለማካበት ላባቸው ጠብ እስኪል ይሠሩ ይሆናል። ሆኖም ‘ጊዜና አጋጣሚ’ በሚያመጣው ነገር የፈለጉትን ክብር ላያገኙ ወይም ደግሞ ቁሳዊ ሃብት በማካበት ያሰቡትን ያህል ላይሳካላቸው ይችል ይሆናል። ልክ ‘ነፋስን የመከተል’ ያህል ድካማቸው ሁሉ ከንቱ ነው። (መክ. 1:14፤ 9:11 NW ) እንግዲያው ካለው ዘላቂ ጥቅም አንጻር ከንቱ ባልሆነው ብቸኛ የጌታ ሥራ መጠመዳችን እንዴት ወሳኝ ነው!
2 ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ሥራ፦ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች መስበክ በምድር ላይ ካለው ከማንኛውም ሥራ ይበልጥ ዋጋ ያለው ሥራ ነው። ሰዎች አዳመጡም አላዳመጡ መሠራት ያለበት ሥራ ነው። እኛም ልክ እንደ ጳውሎስ “እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ። የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፣ ምንም አላስቀረሁባችሁም” ብለን መናገር መቻል እንፈልጋለን።—ሥራ 20:26, 27
3 ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት አዳምጠው ምላሽ ሲሰጡ እንዴት ደስ ይላል! አንዲት ወጣት ሴት አክስቷን በሞት አጣች። አክስቴ ገነት ገብታ ይሆን ወይስ ሲኦል እያለች ታስብ ነበር። ከዚያም እህቷ እንዳስተማረቻት ይሖዋ የሚለውን ስም በመጠቀም አምላክ እንዲረዳት ጸለየች። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች። ስለ ሕይወት ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ አመለካከት በማግኘቷ ከወሮበሎች ቡድን ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠች። ሲጋራ ማጨሷን፣ አደገኛ ዕፆች መውሰዷን እንዲሁም መስረቋን አቆመች። እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “እንዲህ ያለውን መጥፎ የሕይወት መንገድ እንድተው ያደረገኝ ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ብቻ ነው። በታላቅ ምሕረቱ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሊሰጠኝ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።” ይህች ሴት ከአሁን በኋላ ከንቱ የሆኑ ግቦችን በመከታተል ሕይወቷን አታባክንም።
4 ሰዎች እኛን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቢቀሩ እንኳን አንድ ጠቃሚ ተግባር አከናውነናል። የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንደጎበኟቸው ያውቃሉ። ከዚህም በላይ የአቋም ጽናታችሁ፣ የታመናችሁ መሆናችሁና ፍቅራችሁ ይረጋገጣል። ታዲያ በጌታ ሥራ የምትደክሙት ድካም ከንቱ ነውን? በፍጹም!