የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ!
“ወዳጆቼ ሆይ፣ . . . በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ።”—ፊልጵስዩስ 2:12
1, 2. ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውን መቆጣጠር እንደማይችሉ ሆኖ እንዲሰማቸው የሚያደርጓቸው በሰፊው የሚነገሩ ሐሳቦች የትኞቹ ናቸው?
“ተፈጥሮህ ነውን?” ይህ ጥያቄ በቅርቡ በአንድ ታዋቂ መጽሔት ሽፋን ላይ ወጥቶ ነበር። ከርዕሱ ሥር የሚከተሉት ቃላት ይገኙ ነበር:- “ባሕርይ፣ ዐመልና ሌላው ቀርቶ በሕይወት ውስጥ የምናደርጋቸው ምርጫዎች። እነዚህ ነገሮች በአብዛኛው በዘር ውርስ የሚተላለፉ መሆናቸውን በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።” እንዲህ የመሳሰሉ አባባሎች አንዳንዶች የራሳቸውን ሕይወት መቆጣጠር የሚችሉት በጥቂቱ ብቻ እንደሆነ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል።
2 ሌሎች ደግሞ ወላጆቻቸው በጥሩ ሁኔታ ሳያሳድጓቸው መቅረታቸው ወይም አስተማሪዎቻቸው በደንብ ሳያስተምሯቸው መቅረታቸው ለአሳዛኝ ሕይወት እንደዳረጋቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። የወላጆቻቸውን ስህተቶች መድገማቸው፣ እጅግ መጥፎ የሆኑ ዝንባሌዎችን መከተላቸው፣ ይሖዋን መተዋቸው ወይም በአጭር አነጋገር መጥፎ ምርጫዎችን ማድረጋቸው የማይቀር ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ይህን ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚል ዓይነት መሠረተ ትምህርት ያስተምራል የሚሉ አንዳንድ ሃይማኖታውያን እንዳሉ የተረጋገጠ ነው። እንደዚህ መሠረተ ትምህርት አባባል ከሆነ አምላክ በሕይወታችሁ ውስጥ የሚያጋጥማችሁን እያንዳንዱን ነገር አስቀድሞ ወስኗል ማለት ነው።
3. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊት ሕይወታችን ኃላፊነት የመውሰድ ችሎታ እንዳለን የሚያሳይ ምን የሚያበረታታ መልእክት አለው?
3 እነዚህ የተለያዩ ሐሳቦች በሙሉ የሚያስተላልፉት መልእክት አንድ ነው። ይሄውም የወደፊት የሕይወት አቅጣጫህን መምረጥም ሆነ መቆጣጠር አትችልም የሚል ነው። ይህ ደግሞ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነው፤ አይደለም እንዴ? ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል። ምሳሌ 24:10 “በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው” ይላል። ይሁንና ‘የራሳችንን መዳን መፈጸም’ የምንችል መሆናችንን በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ማወቃችን ያጽናናናል። (ፊልጵስዩስ 2:12) በዚህ አዎንታዊ አመለካከት በተንጸባረቀበት ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ትምክህታችንን ልናጠናክር የምንችለው እንዴት ነው?
በራሳችን ላይ የምናከናውነው ‘የመገንባት’ ሥራ
4. በ1 ቆሮንቶስ 3:10–15 ላይ እሳትን ሊቋቋሙ በሚችሉ ነገሮች ስለ መገንባት ቢናገርም ይህ ምንን አያመለክትም?
4 በ1 ቆሮንቶስ 3:10–15 ላይ የሚገኘውን የሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ ተመልከቱ። እዚህ ላይ ጳውሎስ ስለ ክርስቲያን የግንባታ ሥራ እየተናገረ ሲሆን የምሳሌው መሠረታዊ ሥርዓት በራሳችንም ሆነ በሌሎች ላይ በምናከናውነው የግንባታ አገልግሎት ላይ የሚሠራ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ አንድ ደቀ መዝሙር በመጨረሻ ላይ ይሖዋን ለማገልገል እንዲመርጥና በምርጫው እስከ መጨረሻ እንዲጸና የማድረጉ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የወደቀው በሚያስተምሩትና በሚያሰለጥኑት ሰዎች ላይ ነው ማለቱ ነውን? አይደለም። ጳውሎስ አስተማሪው የተቻለውን ያህል ጥራት ያለው የግንባታ ሥራ ለማከናወን ጥረት ማድረግ እንዳለበት ማሳሰቡ ነበር። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ተማሪው ወይም ደቀ መዝሙሩ ጉዳዩን በተመለከተ የመምረጥ ነፃነት የለውም ማለቱ አልነበረም። እርግጥ የጳውሎስ ምሳሌ ያተኮረው ራሳችንን ሳይሆን ሌሎችን በመገንባቱ ሥራ ላይ ነው። ጳውሎስ በግዴለሽነት የተሠራ የግንባታ ሥራ በሚጠፋበት ጊዜ ገንቢው ግን እንደሚተርፍ ከተናገረው ነገር ይህን ለመረዳት እንችላለን። ያም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ ምሳሌያዊ አነጋገር አንዳንድ ጊዜ በራሳችን ላይ ስለምናከናውነው ሥራ ለመግለጽም ይጠቀምበታል።
5. ክርስቲያኖች በራሳቸው ላይ ‘የግንባታ’ ሥራ ማካሄድ እንዳለባቸው የሚያሳዩት ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
5 ለምሳሌ ያህል ይሁዳ 20, 21ን ተመልከቱ:- “እናንተ ግን፣ ወዳጆች ሆይ፣ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።” እዚህ ላይ ይሁዳ ‘ማነጽ’ ለሚለው ቃል የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 3 ላይ ከተጠቀመበት ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ሆኖም ሊያስገነዝብ የፈለገው ነጥብ በእምነታችን መሠረት ላይ ራሳችንን የመገንባቱን አስፈላጊነት ይመስላል። ኢየሱስ ቤቱን በዓለት ላይ ስለ መሠረተው ሰው የተናገረውን ምሳሌ ሉቃስ በሚመዘግብበት ጊዜ “መሠረት” ለሚለው ቃል የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል ጳውሎስ ስለ ክርስቲያን ግንባታ በተናገረው ምሳሌ ላይ ከተጠቀመበት ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው። (ሉቃስ 6:48, 49) ከዚህም በላይ ጳውሎስ መሰል ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ባሳሰባቸው ጊዜ በአንድ “መሠረት” ላይ ስለ መመሥረት የሚናገር ምሳሌያዊ መግለጫ ተጠቅሟል። አዎን፣ የአምላክ ቃል በራሳችን ላይ ‘የግንባታ’ ሥራ እንደምናከናውን ያስተምረናል።—ኤፌሶን 3:15–17፤ ቆላስይስ 1:23፤ 2:7
6. (ሀ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ደቀ መዝሙር የጋራ የግንባታ ፕሮጀክት ውጤት መሆኑን በምሳሌ አስረዳ። (ለ) እያንዳንዱ ግለሰብ ደቀ መዝሙር ምን ኃላፊነት አለበት?
6 አንድን ክርስቲያን መገንባት የአንድ ሰው ሥራ ነውን? ቤት ለመገንባት አስበሃል እንበል። ንድፉን እንዲያወጣልህ ወደ አንድ አርኪቴክት ትሄዳለህ። አብዛኛውን ሥራ ራስህ ለመሥራት ብታስብም አብሮህ የሚሠራና የተሻሉ ዘዴዎችን ሊነግርህ የሚችል አንድ የሕንፃ ተቋራጭ ትቀጥራለህ። ጠንካራ መሠረት ከጣለ፣ ንድፉን እንድታስተውል የሚረዳህ ከሆነ፣ የተሻሉ የግንባታ ቁሳቁሶችን እንድትገዛ ሐሳብ ካቀረበልህና ሌላው ቀርቶ ስለ ግንባታ ሥራ ብዙ ነገር ካስተማረህ የእሱ መኖር እጅግ እንደጠቀመህ እንደምትስማማ አያጠራጥርም። ነገር ግን ምክሩን ችላ ብትል፣ ርካሽ ወይም ጥራታቸው ዝቅተኛ የሆነ ዕቃዎችን ብትገዛና አርኪቴክቱ ያወጣውን ንድፍ ባትከተልስ? ቤቱ ቢፈርስ ተቋራጩን ወይም አርኪቴክቱን ልትወቅስ እንደማትችል የተረጋገጠ ነው! በተመሳሳይም እያንዳንዱ ክርስቲያን ደቀ መዝሙር የጋራ የግንባታ ፕሮጀክት ውጤት ነው። ዋናው አርኪቴክት ይሖዋ ነው። ‘የአምላክ የሥራ ባልደረባ’ በመሆን አንድን ተማሪ የሚያስተምረውንና የሚያሰለጥነውን ታማኝ ክርስቲያን ይሖዋ ይደግፈዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:9) ሆኖም ራሱን ተማሪውንም የሚመለከት ጉዳይ አለ። መጨረሻ ላይ በሚደረገው ግምገማ ለራሱ ሕይወት በኃላፊነት የሚጠየቀው ራሱ ነው። (ሮሜ 14:12) ግሩም የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያት እንዲኖሩት የሚፈልግ ከሆነ እነዚህን ለማግኘትና በውስጡ ለመገንባት መጣር አለበት።—2 ጴጥሮስ 1:5–8
7. አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል? ምንስ ሊያጽናናቸው ይችላል?
7 ታዲያ ይህ ሲባል የዘር ውርስ፣ አካባቢና የአስተማሪዎቻችን የማስተማር ችሎታ ትርጉም የለሽ ናቸው ማለት ነው? በፍጹም። የአምላክ ቃል እነዚህ እያንዳንዳቸው አስፈላጊ እንደሆኑና ተጽእኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይናገራል። ብዙ ኃጢአተኛና መጥፎ ዝንባሌዎች አብረውን የሚወለዱ ሲሆኑ ለመዋጋትም በጣም አስቸጋሪ ናቸው። (መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12፤ 7:21–23) ወላጆች የሚሰጡት ስልጠናና በቤት አካባቢ ያለው ሁኔታ በጥሩ ጎኑም ይሁን በመጥፎ በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል። (ምሳሌ 22:6፤ ቆላስይስ 3:21) ኢየሱስ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የሚያስተምሩት ትምህርት በሌሎች ሰዎች ላይ መጥፎ ውጤት በማስከተሉ አውግዟቸዋል። (ማቴዎስ 23:13, 15) ዛሬ እንዲህ ያሉ ነገሮች በሁላችንም ላይ ተጽእኖ በማሳደር ላይ ናቸው። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦች በልጅነታቸው ወቅት አስቸጋሪ ሕይወት በማሳለፋቸው ምክንያት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። እንዲህ ያሉትን በደግነት ልንይዛቸውና ልናዝንላቸው ያስፈልጋል። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እንደሚያሳየው ወላጆቻቸው ስህተት መፈጸማቸው ወይም ታማኝነታቸውን ማጉደላቸው እነሱም የግድ ተመሳሳይ ነገር ይፈጽማሉ ማለት አለመሆኑን በመገንዘብ ሊጽናኑ ይችላሉ። በጥንቷ ይሁዳ የነበሩ አንዳንድ ነገሥታት ይህን በተመለከተ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት እንደሆነ ተመልከቱ።
የይሁዳ ነገሥታት—የራሳቸውን ምርጫ አድርገዋል
8. ኢዮአታም አባቱ ምን መጥፎ ምሳሌ ትቶለት አልፏል? ሆኖም ምን ለማድረግ መረጠ?
8 ዖዝያን የይሁዳ ንጉሥ የሆነው ገና የ16 ዓመት ለጋ ወጣት እያለ ሲሆን ለ52 ዓመታት ነግሦአል። በአብዛኛው የሕይወት ዘመኑ ‘አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አድርጓል።’ (2 ነገሥት 15:3) ተከታታይ የሆኑ አስደናቂ ወታደራዊ ድሎችን እንዲቀዳጅ በማድረግ ይሖዋ ባርኮታል። የሚያሳዝነው ግን ዖዝያን ያገኘው ስኬት እንዲታበይ አደረገው። በትዕቢት ተነሳስቶ ለካህናቱ በተወሰነው ሥራ ውስጥ በመግባት በቤተ መቅደሱ መሠዊያ ላይ ዕጣን በማጤስ በይሖዋ ላይ ዓመፀ። ዖዝያን ቢገሰጽም ምላሽ የሰጠው በቁጣ ነበር። ከዚያም በለምጽ ተመትቶ ተዋረደ፤ የተቀረውን የሕይወት ዘመኑንም ከሰው ተገልሎ እንዲያሳልፍ ተገደደ። (2 ዜና መዋዕል 26:16–23) ልጁ ኢዮአታምስ ያደረገው ነገር ምን ነበር? ይህ ወጣት የአባቱ ሁኔታ በቀላሉ ተጽእኖ ሊያደርግበትና የይሖዋን ማስተካከያ ችላ ሊል ይችል ነበር። ሕዝቡ በአጠቃላይ የተሳሳቱ ሃይማኖታዊ ልማዶችን ተከትለው ስለነበረ ጎጂ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችሉ ነበር። (2 ነገሥት 15:4) ይሁን እንጂ ኢዮአታም የራሱን ምርጫ አድርጓል። “በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።”—2 ዜና መዋዕል 27:2
9. በአካዝ ላይ በጎ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምን ነበሩ? ሆኖም ሕይወቱ እንዴት ያለ ሆነ?
9 ኢዮአታም ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ለ16 ዓመታት ገዝቷል። ስለዚህም ልጁ አካዝ የአባቱን መልካም ምሳሌ ሊከተል ይችላል። አካዝ መልካም ተጽእኖ ሊያሳድሩበት የሚችሉ ሌሎች ነገሮችም ነበሩ። እንደ ኢሳይያስ፣ ሆሴዕና ሚክያስ ያሉት ታማኝ ነቢያት በምድሪቱ ላይ ትንቢት በመናገር በንቃት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ላይ በመኖሩ ተባርኳል። ሆኖም መጥፎ ምርጫ አደረገ። “እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም።” የበዓል ምስሎችን በመሥራት አመለካቸው፤ ሌላው ቀርቶ ከልጆቹ መካከል አንዳንዶቹን ለአረማውያን አማልክት መሥዋዕት እንዲሆኑ በእሳት አቃጠለ። በዙሪያው በጎ ተጽእኖ የሚያሳድር ሁኔታ የነበረ ቢሆንም በንግሥናውና በይሖዋ አገልጋይነቱ የፈጸመው ነገር እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነበር።—2 ዜና መዋዕል 28:1–4
10. አካዝ እንዴት ያለ አባት ነበር? ይሁን እንጂ ልጁ ሕዝቅያስ ምን ለማድረግ መረጠ?
10 ከንጹሕ አምልኮ አንጻር ስንመለከተው ከአካዝ የከፋ አባት ይኖራል ብሎ ለመገመት ያዳግታል። ይሁን እንጂ ልጁ ሕዝቅያስ የአካዝን አባትነት ሊለውጥ የሚችልበት ምንም መንገድ አልነበረውም! አካዝ ለበዓል መሥዋዕት እንዲሆኑ ያረዳቸው ትንንሽ ልጆች የሕዝቅያስ ወንድሞች ሳይሆኑ አይቀሩም። ሕዝቅያስ ያደገበት መጥፎ ሁኔታ ለይሖዋ የታመነ እንዳይሆን አድርጎታልን? ከዚህ በተቃራኒ ሕዝቅያስ ታማኝ፣ ጠቢብና ተወዳጅ ሰው በመሆን ታላላቅ ከሚባሉት ጥቂት የይሁዳ ነገሥታት መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል። “እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።” (2 ነገሥት 18:3–7) እንዲያውም ሕዝቅያስ ገና ወጣት መስፍን እያለ 119ኛውን መዝሙር በመንፈስ ተነሣስቶ መጻፉን ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት አለን። ይህ ከሆነ ደግሞ “ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ አንቀላፋች [“እንቅልፍ አጣች፣” NW]” ብሎ የጻፈበትን ምክንያት ለመረዳት አስቸጋሪ አይሆንብንም። (መዝሙር 119:28) ከባድ ችግሮች ቢኖሩበትም ሕዝቅያስ የይሖዋ ቃል ሕይወቱን እንዲመራለት አድርጓል። መዝሙር 119:105 “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ይላል። አዎን፣ ሕዝቅያስ ምርጫው ትክክለኛ ነበር።
11. (ሀ) የአባቱ በጎ ተጽዕኖ ቢኖርም ምናሴ በይሖዋ ላይ በማመፅ ምን ያህል ርቆ ሄዶ ነበር? (ለ) ምናሴ በሕይወቱ ማብቂያ ላይ ምን ለማድረግ መረጠ? ከዚህስ ምን ለመማር እንችላለን?
11 የሚያስገርመው ነገር በጣም መጥፎ ከሚባሉት የይሁዳ ነገሥታት መካከል አንዱ እጅግ ጥሩ ከነበረው የይሁዳ ንጉሥ መወለዱ ነው። የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ የጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ እምነትና ዓመፅ ይህ ነው በማይባል መጠን እንዲስፋፋ አድርጓል። ዘገባው ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም “ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው” ይላል። (2 ዜና መዋዕል 33:10) የአይሁድ ወግ እንደሚለው ከሆነ ምናሴ ምላሽ የሰጠው ኢሳይያስ በመጋዝ እንዲሰነጠቅ በማድረግ ነበር። (ከዕብራውያን 11:37 ጋር አወዳድር።) ይህ ነገር እውነትም ይሁን አይሁን ምናሴ ምንም ዓይነት መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም። እንዲያውም አያቱ አካዝ እንዳደረገው ከገዛ ልጆቹ መካከል አንዳንዶቹን በሕይወት እያሉ መሥዋዕት አድርጎ አቃጥሏቸዋል። ቢሆንም ይህ ክፉ ሰው በሕይወቱ የኋለኛ ዓመታት በከባድ መከራ ላይ እያለ ንስሐ ገባ፤ አካሄዱንም ቀየረ። (2 ዜና መዋዕል 33:1–6, 11–20) የእሱ ምሳሌ ምርጫው መጥፎ የነበረ ሰው ሁሉ የመመለስ ተስፋ የለውም ማለት እንዳልሆነ ያስተምረናል። ሊለወጥ ይችላል።
12. ይሖዋን ማገልገልን በተመለከተ አሞንና ልጁ ኢዮስያስ ምን ተቃራኒ ምርጫዎች አድርገዋል?
12 የምናሴ ልጅ አሞን ከአባቱ ንስሐ መግባት ብዙ ሊማር ይችል ነበር። ሆኖም የተሳሳተ ምርጫ አደረገ። በመጨረሻ እስከ ተገደለበት ጊዜ ድረስ አሞን “መተላለፉን እጅግ አበዛ።” ልጁ ኢዮስያስ ግን ፍጹም የተለየ ነበር። ኢዮስያስ አያቱ ከደረሰበት መጥፎ ነገር ለመማር እንደመረጠ አያጠራጥርም። መግዛት የጀመረው ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ነበር። ይሖዋን መፈለግ የጀመረው 16 ዓመት ሲሞላው ሲሆን ከዚያ በኋላ ምሳሌ የሚሆን ታማኝ ንጉሥ መሆኑን አስመስክሯል። (2 ዜና መዋዕል 33:20—34:5) ያደረገው ምርጫ ትክክለኛ ነበር።
13. (ሀ) ከተመለከትናቸው የይሁዳ ነገሥታት ምን እንማራለን? (ለ) ወላጆች የሚሰጡት ስልጠና ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
13 የሰባቱን የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ በአጭሩ መለስ ብለን መመርመራችን አንድ የሚያስተምረን ትልቅ ትምህርት አለ። አንዳንድ ጊዜ በጣም መጥፎ የሆኑ ነገሥታት እጅግ ጥሩ ልጆች ሲኖሯቸው በተቃራኒው ደግሞ እጅግ ጥሩ የሚባሉት ነገሥታት በጣም መጥፎ ልጆች ነበሯቸው። (ከመክብብ 2:18–21 ጋር አወዳድር።) ይህ ወላጆች የሚሰጡትን ስልጠና አስፈላጊነት አይቀንሰውም። ልጆቻቸውን በይሖዋ መንገድ የሚያሰለጥኑ ወላጆች ልጆቻቸው የኋላ ኋላ የታመኑ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ስልጠና እንዲያገኙ እንደሚያደርጉ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘዳግም 6:6, 7) ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ልጆች የታመኑ ወላጆቻቸው የተቻላቸውን ያህል ቢጥሩላቸውም መጥፎ አካሄድ ለመከተል ይመርጣሉ። ሌሎች ልጆች ደግሞ ከወላጆቻቸው በጣም መጥፎ የሆነ ተጽእኖ ቢደርስባቸውም ይሖዋን ለመውደድና ለማገልገል ይመርጣሉ። እነሱ በሚያደርጉት ጥረት ላይ የይሖዋ በረከት ሲታከልበት ሕይወታቸው የተሳካ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ‘እኔስ ምን እሆን ይሆን’ ብለህ አስበህ ታውቃለህን? እንደዚያ ከሆነ ትክክለኛውን ምርጫ ማድረግ እንደምትችል ይሖዋ በግል የሰጠውን ማረጋገጫ ቀጥሎ ተመልከት!
ይሖዋ ይተማመንባችኋል!
14. ይሖዋ ያሉብንን የአቅም ገደቦች እንደሚገነዘብ እንዴት ልናውቅ እንችላለን?
14 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር ይመለከታል። ምሳሌ 15:3 “የእግዚአብሔር ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ” ይላል። ንጉሥ ዳዊት ስለ ይሖዋ ሲናገር “ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ” ብሏል። (መዝሙር 139:16) በመሆኑም ይሖዋ ከምን ዓይነት መጥፎ ዝንባሌዎች ጋር እየታገልን እንዳለን ያውቃል፤ እነዚህ ዝንባሌዎች ደግሞ የወረስናቸው ወይም ከእኛ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ተጽእኖዎች ምክንያት በውስጣችን የተተከሉ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች ምን ያህል ተጽእኖ እንደሚያሳድሩብህ በሚገባ ይረዳልሃል። ያሉብህን የአቅም ገደቦች ሌላው ቀርቶ ከአንተ ከራስህም እንኳ በተሻለ ሁኔታ ያውቃል። ደግሞም መሐሪ ነው። ከአቅማችን በላይ እንድናደርግ አይጠብቅብንም።—መዝሙር 103:13, 14
15. (ሀ) ሌሎች ሆን ብለው ጉዳት ላደረሱባቸው ሰዎች የሚሆን አንዱ የመጽናኛ ምንጭ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በእያንዳንዳችን ላይ ምን ኃላፊነቶች ጥሎብናል?
15 በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ሁኔታዎች የሚያሳድሩት ተጽእኖ ሁሉ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ አድርጎ አያስብም። ከአሁን ቀደም በሕይወታችን ውስጥ አንድ መጥፎ ሁኔታ ገጥሞን ከነበረ ይሖዋ ሆን ተብለው የሚፈጸሙብንን እንዲህ ዓይነት ጎጂ ድርጊቶች እንደሚጸየፍ እርግጠኞች መሆናችን ያጽናናን ይሆናል። (መዝሙር 11:5፤ ሮሜ 12:19) ይሁን እንጂ ከአካሄዳችን ዞር በማለት አውቀን መጥፎ ለማድረግ ብንመርጥ ድርጊታችን ከሚያስከትልብን መዘዝ ይከላከልልናልን? በፍጹም አይከላከልልንም። ቃሉ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም [ይሸከማል]” ይላል። (ገላትያ 6:5) ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታቱን በሙሉ ትክክለኛውን ነገር የማድረግና እሱን የማገልገል ኃላፊነት ጥሎባቸዋል። ሁኔታው ሙሴ ለእስራኤል ብሔር እንደተናገረው ነው:- “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ።” (ዘዳግም 30:19) ይሖዋ እኛም ትክክለኛ ምርጫ እንደምናደርግ ይተማመናል። ይህን እንዴት እናውቃለን?
16. ‘የራሳችንን መዳን በመፈጸም’ ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን ልብ በሉ:- “ስለዚህ፣ ወዳጆቼ ሆይ፣ . . . በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።” (ፊልጵስዩስ 2:12, 13) እዚህ ላይ ‘መፈጸም’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድን ነገር ዳር ማድረስን ያመለክታል። ስለዚህ ማናችንም ብንሆን እስከ መጨረሻው በጽናት እንዳንቀጥል አስቀድሞ አልተወሰነብንም። ይሖዋ አምላክ እንድንሠራው የሰጠንን ወደ መዳን የሚመራ ሥራ ማጠናቀቅ እንደምንችል እርግጠኛ ባይሆን ኖሮ እንዲህ ብሎ ባላስጻፈ ነበር። ሆኖም ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው? በራሳችን ጥንካሬ አይደለም። እኛ በራሳችን ጠንካሮች ብንሆን ኖሮ ‘መፍራትና መንቀጥቀጥ’ ባላስፈለገ ነበር። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ‘በውስጣችን ይሠራል፤’ ማለትም ቅዱስ መንፈሱ በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ በመሥራት ‘እንድንፈልግና እንድናደርግ’ ይረዳናል። እንዲህ ያለ ፍቅራዊ እርዳታ እያለን በሕይወታችን ውስጥ ትክክለኛ ነገር እንዳንመርጥና በእዚያ መሠረት ተመርተን እንዳንኖር የሚያግደን ምን ነገር ይኖራል? ምንም አይኖርም!—ሉቃስ 11:13
17. በራሳችን ላይ ምን ለውጦችን ልናደርግ እንችላለን? ይሖዋ እንዲህ እንድናደርግ የሚረዳንስ እንዴት ነው?
17 ልናሸንፋቸው የሚገቡ እንቅፋቶች፣ ምናልባትም አብረውን የኖሩና አስተሳሰባችንን ሊያዛቡ የሚችሉ መጥፎ ልማዶችና ጎጂ ተጽእኖዎች ይኖሩን ይሆናል። ሆኖም እነዚህን በይሖዋ መንፈስ እርዳታ ልናሸንፋቸው እንችላለን! ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች እንደጻፈው የአምላክ ቃል “ምሽግን” እንኳን ለመስበር የሚያስችል ከፍተኛ ኃይል አለው። (2 ቆሮንቶስ 10:4) እንዲያውም ይሖዋ በራሳችን ላይ ሥር ነቀል ለውጥ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ቃሉ ‘አሮጌውን ሰው እንድናስወግድና’ ‘ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድንለብስ’ አጥብቆ ያሳስበናል። (ኤፌሶን 4:22–24) የይሖዋ መንፈስ እንዲህ ያለውን ለውጥ እንድናደርግ በእርግጥ ሊረዳን ይችላል? ምንም ጥርጥር የለውም! የአምላክ መንፈስ ሁላችንም እንዲኖሩን የምንፈልጋቸውን ውብና ውድ ባሕርያት በውስጣችን እንድናፈራ ያደርገናል። ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው ፍቅር ነው።—ገላትያ 5:22, 23
18. ማንኛውም የማመዛዘን ችሎታ ያለው ሰው ምን ምርጫ ማድረግ ይችላል? ይህስ ምን ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዳን ይገባል?
18 እዚህ ላይ ነፃ የሚያወጣ አንድ ታላቅ እውነት ይገኛል። ይሖዋ አምላክ ያለው የማፍቀር ችሎታ ውሱን አይደለም፤ እኛ ደግሞ በእሱ አምሳል የተፈጠርን ነን። (ዘፍጥረት 1:26፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ስለዚህ እኛም ይሖዋን ለመውደድ ልንመርጥ እንችላለን። የወደፊቱ ሕይወታችን የተመካው በዚህ ፍቅር ላይ እንጂ ክርስቲያን ከመሆናችን በፊት እንከተለው በነበረው የሕይወት መንገድ፣ ባዳበርናቸው የተሳሳቱ ልማዶች ወይም በወረስናቸው መጥፎ ነገር የመሥራት ዝንባሌዎች አይደለም። አዳምና ሔዋን በኤደን ውስጥ በታማኝነት ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ነገር ይሖዋ አምላክን መውደድ ነበር። እያንዳንዳችን አርማጌዶንን በሕይወት ለማለፍና በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ ከሚኖረው የመጨረሻ ፈተና ለማለፍ የሚያስፈልገን እንዲህ ያለው ፍቅር ነው። (ራእይ 7:14፤ 20:5, 7–10) እያንዳንዳችን ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እንዲህ ያለውን ፍቅር ልንኮተኩት እንችላለን። (ማቴዎስ 22:37፤ 1 ቆሮንቶስ 13:13) ለዘላለም ዓለም ይሖዋን ለመውደድና በዚህ ፍቅር ላይ ለመገንባት ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።
[ምን ይመስልሃል?]
◻ ግለሰቦች ያለባቸውን ኃላፊነት በተመለከተ አዎንታዊ ከሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚቃረኑ በሰፊው የሚታወቁ ሐሳቦች የትኞቹ ናቸው?
◻ እያንዳንዱ ክርስቲያን በራሱ ላይ ምን የግንባታ ሥራ ማካሄድ ይኖርበታል?
◻ የይሁዳ ነገሥታት ምሳሌ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ምርጫ ማድረግ እንደሚችል የሚያሳየው እንዴት ነው?
◻ በዙሪያችን አፍራሽ ተጽእኖዎች ቢኖሩም በሕይወታችን ላይ ትክክለኛ ነገር መምረጥ እንደምንችል ይሖዋ ማረጋገጫ የሚሰጠን እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የወደፊት ሕይወትህ በዘር ውርስ አስቀድሞ የተወሰነ ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አባቱ መጥፎ ምሳሌ ትቶለት ቢያልፍም ንጉሥ ኢዮስያስ አምላክን ለማገልገል መርጧል