የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የክርስትና እምነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ተዳረሰ
    መጠበቂያ ግንብ—2005 | ጥቅምት 15
    • የክርስትና እምነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ተዳረሰ

      በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌም ውስጥ አንድ ወሳኝ ስብሰባ ተካሄደ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ “እንደ አዕማድ የሚቈጠሩት” ዮሐንስ፣ ጴጥሮስና የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። በቦታው እንደነበሩ በስም የተጠቀሱት ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኛው በርናባስ ነበሩ። የስብሰባው አጀንዳ ሰፊው የአገልግሎት ክልል ለስብከቱ ሥራ በሚያመች መንገድ እንዴት ቢከፈል ይሻላል የሚል ነበር። ጳውሎስ “ለእኔና ለበርናባስ የትብብር ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ከዚያም እኛ ወደ አሕዛብ፣ እነርሱ ደግሞ ወደ አይሁድ እንድ[ን]ሄድ ተስማሙ” ሲል ገልጿል።—ገላትያ 2:1, 9a

      ይህ ስምምነት ምን ትርጉም ነበረው? ምሥራቹ የሚታወጅበት ክልል በአንድ በኩል አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተቀየሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አሕዛብ በሚል የተከፈለ ነበር? ወይስ ስምምነቱ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥን የተከተለ ነበር? መልሱን ለማግኘት ስለ ፈላሻዎች ማለትም ከጳለስጢና ምድር ውጪ ይኖሩ ስለነበሩ አይሁድ አንዳንድ ታሪካዊ መረጃ ማግኘት ይኖርብናል።

      በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የአይሁዳውያን ዓለም

      በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ ምን ያህል አይሁዳውያን ነበሩ? ብዙ ምሑራን የአይሁዳውያን ዓለም ካርታ (እንግሊዝኛ) የተባለው ጽሑፍ ካሰፈረው ሐሳብ ጋር የሚስማሙ ይመስላል:- “ትክክለኛውን አኃዝ ማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም ከ70 [ከክርስቶስ ልደት በኋላ] ቀደም ብሎ በነበሩት ጥቂት ዓመታት በይሁዳ ሁለት ሚሊዮን ተኩል አይሁዳውያን፣ በተቀረው የሮማ ግዛት ደግሞ ከአራት ሚሊዮን በላይ ይገኙ እንደነበር ይገመታል። . . . በሮም ግዛት ውስጥ ከአጠቃላዩ ሕዝብ አንድ አሥረኛ ያህሉ አይሁዳውያን ሳይሆኑ አይቀሩም። አይሁዳውያን በብዛት በሚኖሩባቸው በሮማ ግዛት በስተ ምሥራቅ ባሉ ከተሞች ደግሞ ከነዋሪዎቹ መካከል አንድ አራተኛ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት እነርሱ ነበሩ።”

      አይሁዳውያን በብዛት ይኖሩ የነበሩት በስተ ምሥራቅ በሚገኙት በሶርያ፣ በትንሿ እስያ፣ በባቢሎንና በግብፅ ሲሆን በአውሮፓ የነበሩት ቁጥራቸው አነስተኛ ነበር። ታዋቂ የሆኑ አንዳንድ የቀድሞ ዘመን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የኖሩት ከእስራኤል ውጪ ነበር። ከእነርሱም መካከል የቆጵሮሱ በርናባስ፣ የጳንጦስ ተወላጅ የሆኑትና ሮም ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ጵርስቅላና አቂላ፣ የእስክንድርያው አጵሎስ እንዲሁም የጠርሴሱ ጳውሎስ ይገኙበታል።—የሐዋርያት ሥራ 4:36፤ 18:2, 24፤ 22:3

      ከአገራቸው ፈልሰው የሄዱ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ከትውልድ አገራቸው ጋር የሚያገናኟቸው ብዙ ጉዳዮች ነበሩ። ከእነዚህም አንዱ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚልኩት ዓመታዊ ግብር ሲሆን ይህም በቤተ መቅደሱ እንቅስቃሴና በዚያ በሚከናወነው አምልኮ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ይህን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ጆን ባርክሌይ እንዲህ ብለዋል:- “የፈላሻ ማኅበረሰቦች ለዚህ ዓላማ የሚሰበሰበውን ገንዘብ (ሃብታም የሆኑ አይሁዳውያን የሚሰጡት ተጨማሪ መዋጮ ታክሎበት) በወቅቱ ይከፍሉ እንደነበር የሚያሳይ አጥጋቢ ማስረጃ አለ።”

      ከአገራቸው ጋር የሚያገናኛቸው ሌላው ነገር ታላላቆቹን በዓላት ለማክበር በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉት ጉዞ ነው። በሐዋርያት ሥራ 2:9-11 ላይ የሚገኘው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ስለተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል የሚተርከው ዘገባ ይህን ያሳያል። በበዓሉ ላይ የተገኙት አይሁዳውያን ከጳርቴና፣ ከሜድ፣ ከኢላም፣ ከመስጴጦምያ፣ ከቀጰዶቅያ፣ ከጳንጦስ፣ ከእስያ፣ ከፍርግያ፣ ከጵንፍልያ፣ ከግብፅ፣ ከሊቢያ፣ ከሮም፣ ከቀርጤስ እንዲሁም ከዐረብ አገር የመጡ ነበሩ።

      በኢየሩሳሌም የሚገኘው የቤተ መቅደሱ አስተዳደር ከአገራቸው ውጪ ከሚኖሩት አይሁዳውያን ጋር በደብዳቤ ይገናኝ ነበር። በሐዋርያት ሥራ 5:34 ላይ የተጠቀሰው የሕግ አስተማሪ የነበረው ገማልያል ወደ ባቢሎንና ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ደብዳቤ ይልክ እንደነበር ማወቅ ተችሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ በ59 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ እስረኛ ሆኖ ሮም ሲደርስ ‘የአይሁድ መሪዎች’ “ስለ አንተ ከይሁዳ ምድር የተጻፈ አንድም ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከዚያ የመጡ ወንድሞችም ስለ አንተ ያቀረቡት ወይም የተናገሩት አንዳች መጥፎ ነገር የለም” በማለት ነግረውታል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ከእስራኤል ወደ ሮም በየጊዜው ደብዳቤዎችና ሪፖርቶች ይላኩ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 28:17, 21

      ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ አይሁዳውያን የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስ ሰብዓ ሊቃናት በመባል የሚታወቀው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ግሪክኛ ትርጉም ነበር። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ከእስራኤል ውጪ የሚኖሩ አይሁዳውያን ሰብዓ ሊቃናትን የእነርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ‘ቅዱስ ጽሑፍ’ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩትና ያነብቡት ነበር ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።” የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለማስተማር ሥራቸው በዚሁ መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ይጠቀሙ ነበር።

      በኢየሩሳሌም የሚገኙት የክርስትና እምነት የበላይ አካል አባላት እነዚህን ጉዳዮች በሚገባ ያውቁ ነበር። ምሥራቹ በሶርያና ከዚያም አልፎ እንደ ደማስቆና አንጾኪያ ባሉ ቦታዎች በሚገኙ አይሁዳውያን ዘንድ ቀደም ሲል ተዳርሶ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 9:19, 20፤ 11:19፤ 15:23, 41፤ ገላትያ 1:21) ስለዚህ በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተደረገው ስብሰባ ላይ የተወያዩት ወደፊት ሥራው እንዴት መከናወን እንዳለበት ነው። የክርስትና እምነት በአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት በመጡ ሰዎች ዘንድ እንዴት እንደተስፋፋ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እንመልከት።

      የጳውሎስ ጉዞና ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ አይሁዳውያን

      ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያ የተሰጠው ሥራ ‘በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት [የኢየሱስ ክርስቶስን] ስም መሸከም’ ነበር።b (የሐዋርያት ሥራ 9:15) በኢየሩሳሌም ከተካሄደው ስብሰባ በኋላ ጳውሎስ በሄደበት ሁሉ ከአገራቸው ውጪ ለሚኖሩ አይሁድ ምሥራቹን ማድረሱን ቀጠለ። (በገጽ 14 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው የአገልግሎት ክልሉን የተከፋፈሉት ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስና በርናባስ የሚስዮናዊነት ሥራቸውን በስተ ምዕራብ በኩል ያስፋፉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በአገራቸው ለሚኖሩ አይሁድና በምሥራቁ ዓለም ለሚገኙት ሰፋፊ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ምሥራቹን ሰብከዋል።

  • የክርስትና እምነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ተዳረሰ
    መጠበቂያ ግንብ—2005 | ጥቅምት 15
    • ጳርቴናን፣ ሜድንና ኢላምን ጨምሮ ባቢሎን አይሁዶች በብዛት የሚገኙባት ሌላዋ አገር ነበረች። አንድ የታሪክ ምሑር “ከአርሜንያ አንስቶ እስከ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ድረስ፣ ጤግሮስና ኤፍራጥስ አካባቢ ያለው ግዛትም ሆነ በስተ ሰሜን ምሥራቅ እስከ ካስፒያን ባሕር ድረስ፣ በስተ ምሥራቅ ደግሞ እስከ ሜድ ድረስ ያለውን ቦታ አይሁዳውያን ይገኙበት ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ ብዛታቸው 800,000 ወይም ከዚያ በላይ እንደሚገመት ጠቅሷል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ዓመታዊዎቹን በዓላት ለማክበር በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የባቢሎን አይሁዶች ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ እንደነበር ተናግሯል።

      ከባቢሎን ከመጡት አይሁዶች መካከል አንዳንዶቹ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ተጠምቀው ይሆን? ይህን ማወቅ አንችልም፤ ሆኖም በዚያን ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ያቀረበውን ንግግር ካዳመጡት መካከል ከመስጴጦምያ የመጡ አይሁዶች ይገኙበት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:9) ሐዋርያው ጴጥሮስ ከ62 እስከ 64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ በባቢሎን እንደነበረ ይታወቃል። የመጀመሪያ ደብዳቤውን ምናልባትም ሁለተኛውንም የጻፈው እዚያ እያለ ነበር። (1 ጴጥሮስ 5:13) በ49 በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያን የሚገኙባት ባቢሎን ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስና ለያዕቆብ ተመድባ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

  • የክርስትና እምነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ተዳረሰ
    መጠበቂያ ግንብ—2005 | ጥቅምት 15
    • a ይህ ስብሰባ የተደረገው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የበላይ አካሉ በግርዘት ጉዳይ ላይ ለመወያየት በተሰበሰበበት ወቅት ወይም ከዚያ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል።—የሐዋርያት ሥራ 15:6-29

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ