የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የይሖዋን በጎች እንዲጠብቁ የተሾሙ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’
    መጠበቂያ ግንብ—1999 | ሰኔ 1
    • “ማስተካከል” አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ

      8. ሁላችንም አልፎ አልፎ በምን በምን መንገዶች ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገናል?

      8 አንደኛ፣ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ የተሰጡት “ቅዱሳንን ለማስተካከል” እንደሆነ ጳውሎስ ተናግሯል። (ኤፌሶን 4:​12 NW) “ማስተካከል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው ስም አንድን ነገር “ወደ ተገቢው ቦታ መመለስን” ያመለክታል። ሁላችንም ፍጽምና የሌለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን አስተሳሰባችን፣ ዝንባሌያችን ወይም ጠባያችን ከአምላክ አስተሳሰብና ፈቃድ ጋር እንዲስማማ በየጊዜው መስተካከልና “ወደ ተገቢው ቦታ መመለስ” ይኖርብናል። ይሖዋ በፍቅሩ ተገፋፍቶ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንድናደርግ የሚረዱንን ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ሰጥቶናል። ይህን የሚያከናውኑት እንዴት ነው?

      9. አንድ ሽማግሌ አንድን ስህተት የፈጸመ በግ እንዲስተካከል ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?

      9 አንድ ሽማግሌ በደል የፈጸመን ምናልባትም ‘ሳያውቀው የተሳሳተ እርምጃ የወሰደን’ አንድ በግ እንዲረዳ ሊጠየቅ ይችላል። እርዳታውን ሊሰጥ የሚችለው እንዴት ነው? ገላትያ 6:​1 “እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት” ይላል። አንድ ሽማግሌ ምክር በሚሰጥበት ጊዜ ሻካራ ቃላት በመጠቀም ስህተት የፈጸመውን ግለሰብ አይቆጣውም። ምክሩ፣ ምክር ተቀባዩን የሚያበረታታ እንጂ ‘የሚያስፈራራ’ መሆን የለበትም። (2 ቆሮንቶስ 10:​9 የ1980 ትርጉም፤ ከኢዮብ 33:​7 ጋር አወዳድር።) ግለሰቡ ራሱ በሠራው ድርጊት አፍሮ ሊሆን ስለሚችል አንድ አፍቃሪ እረኛ የግለሰቡን መንፈስ ሊሰብሩ የሚችሉ ቃላትን ከመሰንዘር ይቆጠባል። ምክር፣ ሌላው ቀርቶ ጠንካራ ተግሳጽ እንኳ በፍቅር አነሳሽነት የተሰጠና በፍቅራዊ መንገድ የቀረበ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ከሆነ የተሳሳተውን ሰው አመለካከት ወይም አካሄድ ለማቃናት እንዲሁም ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ እንደሚረዳ እሙን ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​2

      10. ሌሎችን ማስተካከል ምንን ይጨምራል?

      10 ይሖዋ የሚያስተካክሉንን ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ የሰጠን ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የሚያነቃቁና ለሕዝቡ ምሳሌ ይሆናሉ በሚል ነው። (1 ቆሮንቶስ 16:​17, 18፤ ፊልጵስዩስ 3:​17) ሌሎችን ማስተካከል ማለት የተሳሳተ አካሄድ የሚከተሉትን ማረም ብቻ ሳይሆን ታማኝ የሆኑትም ከትክክለኛው ጎዳና እንዳይወጡ መርዳትንም የሚያካትት ነው።a የምንኖረው ተስፋ የሚያስቆርጡ በርካታ ችግሮች በሞሉበት ጊዜ እንደመሆኑ ብዙዎች ጸንተው እንዲቀጥሉ ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶች አስተሳሰባቸው ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር እንዲስማማ ጥንቃቄ የተሞላበት እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ታማኝ ክርስቲያኖች ጥልቅ ከሆነ የዋጋቢስነት ወይም የከንቱነት ስሜት ጋር ይታገላሉ። እነዚህ “የተጨነቁ ነፍሳት” ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይወዳቸውና ከልብ ተጨንቀው የሚያቀርቡትን አገልግሎት እንኳ እንደማይቀበል ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 5:​14 NW) ሆኖም ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አምላክ ለአገልጋዮቹ ካለው ስሜት ፈጽሞ የራቀ ነው።

      11. ሽማግሌዎች ከከንቱነት ስሜት ጋር የሚታገሉትን ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

      11 ሽማግሌዎች እንደነዚህ ያሉትን ለመርዳት ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ይሖዋ ለእያንዳንዱ አገልጋይ እንደሚያስብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን አንብቡላቸው። እንዲሁም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በእነርሱም ላይ እንደሚሠሩ አረጋግጡላቸው። (ሉቃስ 12:​6, 7, 24) ይሖዋ እንዲያገለግሉት ወደ እርሱ እንደሳባቸውና ይህ ደግሞ ጥሩ ባሕርይ እንዳየባቸው የሚያሳይ መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዷቸው። (ዮሐንስ 6:​44) እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም ተመሳሳይ የሆነ ስሜት እንደሚሰማቸው አረጋግጡላቸው። ነቢዩ ኤልያስ በአንድ ወቅት በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ከመደቆሱ የተነሳ ሞትን ተመኝቶ ነበር። (1 ነገሥት 19:​1-4) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የተቀቡ ክርስቲያኖች ልባቸው ‘ይፈርድባቸው’ ነበር። (1 ዮሐንስ 3:​20) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት ታማኞች ‘የእኛው ዓይነት ስሜት’ እንደነበራቸው ማወቁ የሚያጽናና ነው። (ያዕቆብ 5:​17 NW) ከዚህም በተጨማሪ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የወጡ የሚያበረታቱ ርዕሶችን ለእነዚህ ተስፋ ለቆረጡ ሰዎች ልትከልሱላቸው ትችላላችሁ። እነዚህ ሰዎች አጥተውት የነበረውን በራስ የመተማመን መንፈስ መልሰው እንዲያገኙ የምታደርጉትን ከፍቅር የመነጨ ጥረት ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ አድርጎ በሰጣችሁ አምላክ ዘንድ ፈጽሞ የሚረሳ አይደለም።​—⁠ዕብራውያን 6:​10

  • የይሖዋን በጎች እንዲጠብቁ የተሾሙ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’
    መጠበቂያ ግንብ—1999 | ሰኔ 1
    • መንጋውን “መገንባት”

      12. “የክርስቶስን አካል እንዲገነቡ” የሚለው አባባል ምንን ያመለክታል? መንጋውን ለመገንባት የሚያስችለው ቁልፍ ምንድን ነው?

      12 ሁለተኛ፣ “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” የተሰጡት “የክርስቶስን አካል እንዲገነቡ” ነው። (ኤፌሶን 4:​12) እዚህ ላይ ጳውሎስ አንድ ምሳሌያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል። “መገንባት” የሕንፃ ሥራን የሚያመለክት ሲሆን “የክርስቶስ አካል” ደግሞ የቅቡዓን የክርስቲያን ጉባኤ አባላት የሆኑ ሰዎችን ያመለክታል። (1 ቆሮንቶስ 12:​27፤ ኤፌሶን 5:​23, 29, 30) ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸው በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንዲሆኑ መርዳት ይኖርባቸዋል። ግባቸው መንጋውን ‘ማፍረስ ሳይሆን ማነጽ ነው።’ (2 ቆሮንቶስ 10:​8) ‘ፍቅር የሚያንጽ’ በመሆኑ መንጋውን ለመገንባት የሚረዳው ዋነኛ ቁልፍ ፍቅር ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 8:​1

      13. ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ማለት ምን ማለት ነው? ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌሎች ቦታ ማስቀመጣቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      13 ሽማግሌዎች መንጋውን ለመገንባት የሚረዳቸው አንደኛው የፍቅር ገጽታ ራስን በሌሎች ቦታ የማስቀመጥ ባሕርይ ማዳበራቸው ነው። ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ማለት ለሌሎች ከልብ ማዘን ሲሆን ይህም ያለባቸውን የአቅም ገደብ ግምት ውስጥ በማስገባት አስተሳሰባቸውንና ስሜታቸውን ለይቶ ማወቅ ማለት ነው። (1 ጴጥሮስ 3:​8) ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌሎች ቦታ ማስቀመጣቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ዋናው ምክንያት ‘ወንዶችን ስጦታ’ አድርጎ የሰጠው ይሖዋ ስለ ሌሎች ከልቡ የሚያስብ በመሆኑ ነው። አገልጋዮቹ ሲሰቃዩ ሥቃያቸው ይሰማዋል። (ዘጸአት 3:​7፤ ኢሳይያስ 63:​9) የአቅማቸውን ውስንነት ግምት ውስጥ ያስገባል። (መዝሙር 103:​14) ታዲያ ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌላው ቦታ የሚያስቀምጡ መሆናቸውን ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?

      14. ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌሎች ቦታ የሚያስቀምጡ መሆናቸውን ሊያሳዩ የሚችሉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?

      14 አንድ ተስፋ የቆረጠ ሰው ሊያነጋግራቸው ሲመጣ በጥሞና በማዳመጥ ስሜቱን ለመረዳት ይሞክራሉ። የወንድሞቻቸውን አስተዳደግ፣ ባሕርይና ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳት ይጥራሉ። ከዚያም ሽማግሌዎች ገንቢ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ እርዳታ በሚሰጧቸው ጊዜ በጎቹ ችግሮቻቸውን ከሚረዱላቸውና ከሚያስቡላቸው እረኞች የመጣ በመሆኑ እርዳታቸውን ያለ ችግር ይቀበላሉ። (ምሳሌ 16:​23) በተጨማሪም ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌላው ቦታ ማስቀመጣቸው የሌሎችን የአቅም ገደቦችና በዚህም ሳቢያ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ስሜቶች ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ይገፋፋቸዋል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ትጉህ ክርስቲያኖች በእድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል ምክንያት ሊሆን ይችላል በአምላክ አገልግሎት የሚፈልጉትን ያክል ከፍተኛ ድርሻ ማበርከት ባለመቻላቸው የተነሳ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ አገልግሎታቸውን ለማሻሻል ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልጋቸው ይሆናል። (ዕብራውያን 5:​12፤ 6:​1) ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌላው ቦታ ማስቀመጣቸው ገንቢ የሆኑ ‘ያማሩ ቃላትን’ እንዲናገሩ ይገፋፋቸዋል። (መክብብ 12:​10) የይሖዋ በጎች የሚያንጻቸውና ከልባቸው የሚያነሳሳቸው ነገር ካገኙ እርሱን ለማገልገል የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ!

  • የይሖዋን በጎች እንዲጠብቁ የተሾሙ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’
    መጠበቂያ ግንብ—1999 | ሰኔ 1
    • a “ማስተካከል” ተብሎ የተተረጎመው ይኸው ቃል በግሪኩ የሴፕቱጀንት ትርጉም በመዝሙር 17[16]:​5 ላይ የተሠራበት ሲሆን እዚያ ላይም ታማኙ ዳዊት አረማመዱ ከይሖዋ ጎዳና ሳይወጣ ጸንቶ እንዲቆም ጸልዮአል።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ